January 2, 2022
16 mins read

የጦቢያ ዘመን አቆጣጠር ከፈረንጅ ዘመን አቆጣጠር አንጻር – መስፍን አረጋ

ይህ ጦማር የሚያተኩረው አገራችን ጦቢያን ጦቢያ ካሰኟት ዐበይት ትውፊቶች ውስጥ አንዱ በሆነው በዘመን አቆጣጠራችን ላይ ነው፡፡  አስቀድመን ግን ዘመን መቁጠርያ የሚለው ሐረግ የተንዛዛ ስለሆነ ዮማዝ በሚለው አጭር ቃል እንተካዋልን፡፡   ዮማዝ (calendar) ማለት ሳይቸግረን ጤፍ ተበድረን፣ እንግሊዘኛውን እንዳለ ወስደን ካሌንደር የምንለው ሲሆን፣ ቃሉ የተገኘው ደግሞ ዮም (ዛሬ) እና አሃዝ (ቁጥር) ከሚሉት ቃሎች ነው፡፡  ስለዚህም የአገራችን የዘመን አቆጣጠር የኢትዮጵያ ዮማዝ (Ethiopian Calendar) ወይም ባጭሩ ኢዮ (EC) ሲሆን፣ የፈረንጆች የዘመን አቆጣጠር ደግሞ ጎርጎሮሳዊ ዮማዝ (Gregorian Calendar) ወይም ባጭሩ ጎዮ (GC) ይሆናል፡፡   አማረኛችን ደግሞ ግሱን እንደ ባለቤቱ በመለዋወጥ እንዳበጁት ስለሚበጅ፣ ዮማዝ የሚለውን ቃል ግስ በማድረግ ዮመዘ፣ ዩምዝ፣ ዮማዥ፣ ዩመዛ፣ ዮማዛዊ እያልን ልናስኬደው እንችላለን፡፡  ዮመዘ ማለት ዮማዝ አዘጋጀ፣ ዮማዛዊ አደረገ ማለት ሲሆን፣ የእንግለዚኛ አቻ የለውም፡፡

አገራችን ጦቢያ ከሰለጠነው ዓለም ጋር አብራ ትራመድ ዘንድ የራሷን ዮማዝ ንቃ ጥላ የፈረንጆችን መከተል አለባት የሚሉ ምሁር ነን ባዮቸ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡  የነዚህ ‹‹ምሁሮች›› ምክኒያቶች የተለያዩ ቢሆኑም፣ ዋናወቹ ግን የሚከተሉተ ሁለቱ ናቸው፡፡  የመጀመርያው ምክኒያት የስልጣኔን ምንነት በትክክል ባለመረዳት ፈረንጅን በሁሉም ረገዶች ስልጡን፣ የፈረንጅን እሴቶች ደግሞ ምጡቅ አድርጎ የማየት የተሳሳተ አመለካከት ነው፡፡  ለዚህ አመለካከት ዋነው ተጠያቂ ደግሞ በነጮች (በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያ ጠሎቹ በመሠሪወቹ በእንግሊዞች) ከፍተኛ ተሳትፎ የተሠረተው ዘመናዊ ሳይሆን ዘመናዊ ነው የሚባለው የትምህርት ሥሪታችን ነው፡፡

ሁለተኛውና ይበልጥ አደገኛ የሆነው ምክኒያት ደግሞ የሐበሻ (ይበልጡንም ደግሞ የአማራ) ናቸው ተብለው የሚታሰቡን የኢትዮጵያን አሻራወች ተራ በተራ በማጥፋት ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት የተሸረበው በምዕራባውያን የሚደገፈውና የሚደጎመው የኦነጋውያን ሤራ ነው፡፡  በክርስትና የማያምኑት ዋቄፈተኞቹ ኦነጋውያን የጵንጠጣ ሊቃቡኖች (ፓትርያርኮች) የሆኑት ተዋሕዶን ለመግደል ሲሉ ብቻ እንደሆነ ሁሉ፣ የኦሮሞ ናቸው የሚሏቸውን እነ ገዳን ምጡቅ እያሉ የሐበሻ ናቸው የሚሏቸውን እሴቶች ኋላቀር የሚሏቸው ደግሞ በዘመናዊነት ሰበብ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለመግደል ሲሉ ብቻ ነው፡፡

ኢትዮጵያን አለመጠን ከመጥላታቸው የተነሳ ዋና መፈክራቸው ‹‹ኢትዮጵያ ከኦሮምያ ትውጣ ›› (Ethiopia out of Oromia) የሆነው ኦነጋውያን፣ የኢትዮጵያን ዮማዝ ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ቆርጠው ቢነሱ ደግሞ አይፈረድባቸውም፣ በኢትዮጵያ ዬማዝ የማትጠቀም ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ ልትባል አትችልምና፡፡  ያስራ ሦስት ወሮች አገር የመባልን ብርቃይነት (uniqueness) ማንም አያገኘውም፡፡  ምዕራባውያን የራሳቸው ጠጠር እያዋደዱ ያፍሪቃውያንን ወርቅ የሚያራክሱት ያፍሪቃውያንን በራስ መተመማን እንደ ጦር ስለሚፈሩት እንደሆነ ልንገነዘብ ይገባል፡፡  ካብዛኛው ዓለም ተለይቶ በግራ በመንዳቱ (driving on the left) ወይም ደግሞ ለሰገል (science) እንዲሁም ለኪንሲን (technology) አመቺ ያልሆነ የቁነና ስርዓት (measurement system) በመጠቀሙ ራሱን ብርቃይ (unique) አደርጎ ለመኩራራት የሚሞክር እንግሊዛዊ መደዴ፣ በአፍሪቃዊ እሴቶች ለመሳለቅ ሲሞክር ከት ብለን ልንስቅበት ይገባል፡፡

የኢትዮጵያ ዮማዝ የተቀመረው በዘፈቀደ ሳይሆን ካገራችን አየር ንብረት፣ ባሕልና ሐይማኖት ጋር በጥብቅ ተቆራኝቶ መሆኑን ከወሮቹ ስያሜወች መረዳት ይቻላል፡፡  እነዚህ የወሮች ስሞች ደግሞ በታላቁ ሊቅ በአለቃ ደስታ ተክለወልድ ‹‹ዐዲስ ያማረኛ መዝገበ ቃላት›› ውስጥ ተዘርዝረዋል፡፡

መስከረም (መዝከረ፣ ዓም) ማለት ያመቱ መዘከርያ (ማስታወሻ) ማለት ነው፡፡

ጥቅምት ማለት ከመሬት ብዙ ጥቅም የሚገኝበት፣ እህሉ፣ ተክሉ ፍሬ የሚሰጥበት ማለት ነው፡፡

ኅዳር ማለት ገበሬ ሰብሉን እየጠበቀ ከቤቱ ውጭ (ማሳ ላይ) የሚያድርበት ማለት ነው፡፡

ታኀሣሥ ማለት ሰብዓ ሰገል ወልደሔርን (ማለትም እየሱስን) ለመፈለግ (ለማሠሥ) ወደ ቤተልሄም የሄዱበት ጊዜ ማለት ነው፡፡  የገና በዓል የሚውለውም በዚሁ ወር ነው፡፡

ጥር ማለት የጠረረ፣ ሙቀቱ ብርቱ የሆነ ማለት ነው፣ ጠራራ ፀሐይ እንዲሉ፡፡

የካቲት (ከተተ) ማለት የመከር (ማለትም ያዝመራ) መክተቻ ማለት ነው፡፡

መጋቢት ማለት ወልደሔር (ኢየሱስ) በጸሎተ ሐሙስ (ከፋሲካ በፊት ባለው ሐሙስ) ሥጋውንና ደሙም የመገበበት (ማቴወስ 26፣ 26፣ ማርቆስ 14፣ 24) ማለት ነው፡፡  ለምሳሌ ያህል መጋቢ ዓለም ማለት በዝናብ አብቅሎ፣ በፀሐይ አብስሎ የሚመግብ ማለት ሲሆን፣ የመድሐኔ ዓለም ሌላኛው ስሙ ነው፡፡

ማዚያ (ሚያዚያ) ማለት የሙሽራና የሚዜ ወር ማለት ነው፡፡

ግንቦት (ገነባ) ማለት ለክረምት የሚገነባበት (የሚዘጋጁበት) ጊዜ ማለት ነው፡፡  በግንቦት ወር አትጋቡ የሚባለው ደግሞ የግንቦት አየር ለጤና ተስማሚ ስላልሆና የግንቦት መናዝል (zodia) መንታይ (Gemini) ስለሆነ ነው፡፡  ‹‹እንኳን ያንች ፍቅር ተጨምሮበት፣ እንደውም ሞቃት ነው ሰኔና ግንቦት›› እንዲሉ፡፡

ሰኔ (ሠነየ) ማለት ሠናይ (ውብ፣ መልካም) ማለት ሲሆን፣ የእርሻ ማሳ ተተልሞ (ተገምሶ)፣ ታይሞ (ተቀብቅቦ)፣ እንዲለሰልስ መደረጉንና ዘር መዘራትን ያመለክታል፡፡  ‹‹ቀልደኛ ገበሬ በሰኔ ይሞታል›› እንዲሉ፡፡  ባገራችን በጦቢያ ተሸከርካሪን በግራ መንዳት ቀርቶ በቀኝ መንዳት የተጀመረው በኢትዮጵያ ዮማዝ (ኢዮ) ሰኞ፣ ሰኔ 1 ቀን፣ 1957 ዓ.ም ነበር፡፡

ሐምሌ ማለት የልምላሜ (የሐመልማል፣ የቅጠል) ወር ማለት ነው፡፡

ነሐሴ (ናሴ)፡፡  የዚህን ወር ትርጉም በትክክል ላውቀው አልቻልኩም፡፡  የቃሉ መሠረት ግን ነሐሰ (ነሐስን፣ መዳብን፣ ግንብን፣ መደብን) ሠራ የሚለው የግእዝ ግስ ስለሆነ፣ ነሐሴ ማለት ያመቱ መጨረሻ፣ ያመቱ ገደብ ማለት ሊሆን ይችላል፡፡

ጳጉሜ ማለት ደግሞ ተረፈ ዓመት፣ ጭማሪ፣ ተውሳክ ማለት ነው፡፡  ራሱ ፊደል ጰ ከፊደል ጸ የተገኘ ትርፍ ወይም ዲቃላ ፊደል ነው፡፡

 

የኢትዮጵያን ዮማዝ ከጥቅም ውጭ ለማድረግ የሚጣጣሩት ምሁር ነን ከሚያቀርቧቸው የማታለያ ምክኒያቶች አንዱ ዮማዙ ዘመንን በትክክል ስለማይቆጥር የወቅቶች መዛባትን ያስከተላል የሚለው ነው፡፡  ይህ ችግር ግን የኢትዮጵያ ዮማዝ ብቻ ሳይሆን፣ የሁሉም ዮማዞቸ ችግር ነው፡፡  እቅጭነትን (ማለትም እቅጩን መሆንን፣ precision) በተመለከተ ደግሞ ከሁሉም ዮማዞች የበለጠ እቅጭ (precise) የሆነው የፈረንጆቹ ጎርጎሮሳዊ ዮማዝ ሳይሆን፣ የፐርሺያኖች ዮማዝ ነው፡፡  እንደ ሁሉም ዮማዞች፣ የጦቢያ ዮማዝ ያለበትን የእቅጭነት (precision) ችግር ደግሞ በሚከተለው መንገድ በቀላሉ ማስተካከል ይቻላል፡፡

አንድ ዕለት (day) ማለት 24 ሰዓት ማለት ሲሆን፣ ምድር በዛቢያዋ ላይ አንድ ጊዜ ለመሾር (spin) የሚፈጅባት ጊዜ ነው::  አንድ ዓመት (year) ማለት ደግሞ ምድር በምሕዋሯ ላይ ፀሐይን አንድ ጊዜ ለመሖር (orbit) የሚፈጅባት ጊዜ ማለት ነው፡፡  የአንድ ዓመት እሴት እቅጩን (precisely) 365.24219 ዕለት ነው፡፡  በጦቢያ ዮማዝ መሠረት ደግሞ አንድ ዓመት 365.25 ዕለት ነው፡፡  ስለዚህም፣ የጦቢያ ዮማዝ በያንዳንዱ ዓመት

 

365.25 ዕለት – 365.24219 ዕለት = 0.00781 ዕለት = 11.2464 ደቂቃ

 

ይስታል ማለት ነው፡፡  በሌላ አባባል፣ የጦቢያ ዮማዝ በያንዳንዱ ዓመት ላይ በስሕተት 0.00781 ዕለት ወይም 11.2464 ደቂቃ ይጨምራል ማለት ነው፡፡ አሁንም በሌላ አባባል፣ የጦቢያ ዮማዝ በያንዳንዱ ዓመት ላይ በስሕተት 11 ደቂቃ ገደማ ወደኋላ ይቀራል ማለት ነው፡፡   ይህ ማለት ደግሞ የጦቢያ ዮማዝ በ 128 ዓመታት ውስጥ አንድ ዕለት (ማለትም 24 ሰዓት) ገደማ ወደኋላ ይቀራል ማለት ነው፡፡

ስለዚህም፣ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ2014 ዓመታት ውስጥ የጦቢያ ዮማዝ 16 ዕለታት ገደማ በስሕተት ወደኋላ ቀርቷል ማለት ነው፡፡  ስለዚህም፣ 2014 ዓ.ም ላይ ሰኔ 18 መሆን የሚገባው ሰኔ 2 ይሆናል ማለት ነው፡፡  ይህ ስሕተት ደግሞ ወቅቶችን በማዛባት በተለይም በእርሻ ሥራ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ስለሚያሳድር በሚከተለው መንገድ በቀላሉ ሊታረም ይቻላል፡፡

2014 ዓ.ም ላይ ሰኔ 2 የሚባለውን ዕለት ሰኔ 18 ነው ብሎ በነጋሪት ማወጅ፡፡  በሌላ አባባል፣ ሰኔ 1 ካልን በኋላ ሰኔ 2 ማለት ትተን ሰኔ 18 ማለት፡፡  ይህን በማድረግ፣ ከክርስቶስ ልደት ጀምሮ የተከሰቱትን የዘመን አቆጣጠር ግድፈቶች ከሞላ ጎደል ሙሉ በሙሉ እናስተካክላለን፡፡

ከ 2014 በኋላ ደግሞ በየ 128 ዓመት፣ ከቋጉሜ ወር ላይ አንድ ዕለት በመቀነስ አምስት ከሆነች አራት፣ አራት ከሆነች ደግሞ ሦስት እንድትሆን በነጋሪት ማወጅ፡፡  በሌላ አባባል የእጅ ሰዓት አቆጣጠሩን እንዳይስት በየጊዜው እንደሚሞላ ሁሉ፣ ዮማዛችንም አቆጣጠሩን እንዳይስት በየ 128 ዓመት መሞላት አለበት፡፡

 

እነዚህን ቀላል ርምጃወች በመውሰድ ብቻ ኩራታችን የሆነውን የዘመን አቆጣጠራችንን አዘምነን ከፈረንጆች የዘመን አቆጣጠር የበለጠ ትክክልኛ እናደርገዋለን፡፡  ለትንሽ ለትልቁ መፍትሔ ለመሻት ወደ ምዕራባውያን ማማተር አፍሪቃን ለድቀትና ለንቀት ዳረጋት እንጅ ምንም አልጠቀማትም፡፡   ራሳችንን በራሳችን ካዋረድን ደግሞ ቢንቁን መከፋት የለብንም፡፡  ወደሽ ከተደፋሽ ቢገፉሽ አይክፋሽ እንዲሉ፡፡

 

የራሱን ንጹህ ጥብቆ፣ ራሱ ጥሎ አውልቆ

የሰው ቆሻሻ አጥልቆ፣ ተበክሎ ተጨመላልቆ፣

ሰው ተጸይፎት ርቆ፣ ሲሳለቅበት በሽቆ፣

ዙሮ እንባ ፈንጥቆ፣ እያለቀሰ ተነፋርቆ

ተናቅኩኝ ይላል ተንሰቀስቆ፣ ራሱን በራሱ አስንቆ፡፡

 

ምዕራባውያን አፍሪቃውያንን የሚንቁት ደግሞ ካፍሪቃውያን በሰረቁት መሆኑን ጊወርጊስ ያቆብ (George James) ‹‹የተሰረቀ ቅርስ፡ የግሪክ ፍልስፍና የተሰረቀ የኑባውያን ፍልስፍና ነው›› (Stolen Legacy: Greek Philolsophy is Stolen Egyptian Philosophy) በሚል ርዕስ በጻፈው ደንቅ መጽሐፉ ሊስተባበሉ በማይችሉ ማስረጃወች እያስደገፈ በሰፊው አብራርቶታል፡፡

 

ትናንት ጉግማንጉግ የነበረው አሕዛቡ ፈረንጅ

ዛሬ ስልጡን ነኝ ብሎ በሁሉም ዓይነት ፈርጅ

ቢንቅ ቢጸየፋችሁ አሳንሶ ከውሻ ልጅ፣

አዲስ በመፍጠር አይደለም አክብሮ በማንሳት እንጅ

ተንቆ የተጣለውን በናንተው ከናንተው ደጅ፡፡

 

መስፍን አረጋ

[email protected]

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

Go toTop