ይድረስ ለጥምር ጎሳ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን! – አገሬ አዲስ

/

ታህሳስ 22 ቀን 2014 ዓም (31-12-2021)

ማንኛውም የሰው ልጅ የሚወለድበትን ቤተሰብ፣ቦታና ጊዜ መርጦ አልተፈጠረም። በሁኔታ አጋጣሚ በሁለት ጾታዎች መፈቃቀድና ፍቅር፣ ወይም የኑሮ ግዴታ በሚፈጠረው ግንኙነት ባላሰበበትና ባልመረጠው ቦታና ጊዜ ይወለዳል።ከአንድ ጎሳ ብቻ ሳይሆን በአንድ አገር ውስጥ ከሚኖሩ የተለያዩ ጎሳዎች የመወለዱ ዕድል ከፍተኛ እንደሆነ በአገራችን በኢትዮጵያ የተወለዱት የጥምር ጎሳ ተወላጆች ከፍተኛ ቁጥር ማስረጃ ነው።ይህ ከእገሌ ጎሳ ልወለድ ብሎ ባልመረጠው ሁኔታ  የተወለደ ልጅ ከሁለት አብራክ፣ደምና ስጋ የተፈጠረ በመሆኑ በውስጡ የሁለቱም የእናትና የአባቱ እኩል ድርሻ የሆነ ማንነት አለው።የተወለደው ህጻን የተለያዩ ቋንቋዎችን ከሚናገሩ ጎሳዎች ከሆነም የነዚያ ጎሳዎች የቋንቋ ባለቤት ሆኖ ያድጋል።ይህም አንድ ጸጋ ነው። ከቶም ቢሆን የአንዱን ጥሎ የሌላውን አንጠልጥሎ፣አንዱን ወዶ ሌላውን ጠልቶ ሊኖር አይቻለውም።ለሁለቱም እኩል ፍቅርና ክብር አለው።

በዚህ የጋራ ማንነት የተወለደ ዜጋ ለጎሳ ማንነቱ ሳይሆን በሰው ልጅነቱ ለሁሉም የሰው ልጅ የማያዳላ ፍቅር ይዞ ያድጋል።ለአገር የአንድነትም የሚቆም ጠንካራ ደጀን  ይሆናል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ከሰማንያ የሚበልጡ የጎሳ ማህበረሰቦች ይኖራሉ፤እነዚህ ማህበረሰቦች በሚኖሩበት አገር የሚቀራረቡበት መንገድ የኤኮኖሚ፣የባህል፣የቋንቋና የታሪክ ዘርፎች ብቻ ሳይሆኑ በመውለድና በመዋለድ የቤተሰብ ሐረግ በመፍጠርም ጭምር ይሆናል፤ሆኗልም።ይህንን የቤተሰብ ሐረግ ለመፍጠር ያስቻላቸው ትልቁ ምክንያት ኢትዮጵያ የምትባለዋን አገር በጋራ በመመስረታቸውና በአገር ባለቤትነት ኩራት የአንዱ ጎሳ ተወላጅ እንደልቡ በፈለገበት ቦታ ሄዶ ከሌላው ጎሳ ተወላጅ ጋር ተቀራርቦ ለመኖር የሚያስችል ነጻነት በመጎናጸፉ ነው።  ያም መቀራረብ በጎረቤትነት ብቻ ሳይወሰን በቤተሰብነት ደረጃ ከፍ እንዲል እረድቶታል።ወልዶ ተዋልዶ አንዱ በሌላው ውስጥ የሚኖርበትን ልጅ የተባለ ሰንሰለት፣ በሥጋና ደም የተገነባ ህያው መታሰቢያ ለመፍጠር በቅቷል።

በዚህ አገራዊና የኢትዮጵያዊነት የዜግነት ስሜት በፈጠረው ዕድል የተገናኙ የተለያዬ ጎሳ ተወላጆች በመሰረቱት የትዳርና የፍቅር ጎጆ በብዙ ሚሊዬን ብሎም ከአንዳንዶቹ የክልል ነዋሪ ሕዝብ የበለጠ ቁጥር ያላቸው የሁለት ጎሳ ስብጥር ፍሬዎች የሆኑ ኢትዮጵያውያን ተወልደዋል።ብዙዎቹም ላገራቸው አንድነትና እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተው አልፈዋል፤አሁንም በማበርከት ላይ ይገኛሉ።የሁለት ጥምር ጎሳ ልጆች በመሆናቸው የአንድ ነጠላ ጎሰኝነት አጥሩን አፍርሰውታል።የአንዱ ጎሳ ወዳጅ የሌላው ጎሳ ጠላት ሳይሆኑ ሁሉንም ጎሳ በሚያስተሳስረው፣ለመፈጠራቸው ምክንያት የሆነውን ኢትዮጵያዊነትን ለመጠበቅ ግንባር ቀደም ሰልፈኞች መሆናቸውን በታሪክ አስመስክረዋል።

እነዚህ  ከአሥር ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የኢትዮጵያዊነት የፍቅር ውጤት፣የጥምር ጎሳ ፍሬ የሆኑ ዜጎች ባላቸው ብዙ ቁጥር ላይ በኢትዮጵያዊነታቸው የሚያምኑት የነጠላ ጎሳ ተወላጆች ሲጨመሩበት የአገሪቱን ሕዝብ ከፍተኛ ቁጥር እንደሚሸፍኑ አያጠራጥርም።ይህንን ወሳኝ ቁጥር ግን እንደሌለ ቶቆጥሮ ድምጸ አልባ ሆኖ የጥቂት አክራሪዎች ተጎታች ካሮሳ እንዲሆን ለማድረግ በሽብርና በተሳሳተ ትርክት ሙከራ ሲደረግ ቆይቷል፤አሁንም እየተሞከረ ነው።

ለድፍረቱ ዕድል የሰጠው ኢሕአዴግ በተባለ መሰሪ የጎሰኞች ስብስብ የሰፈነው የጎሳ ስርዓት ከመሆኑም በላይ ያንን የሚቃወመው ሃይል የጥምር ጎሳ ተወላጅ የሆኑትን ባለማቀፉና በአንድ መዋቅር ስር አለመደራጀቱ ነው።አደረጃጀቱ ኢትዮጵያዊነትን በሚያጎላና የጥምር ጎሳ ተወላጁን ለማፍራት ያበቃው ወላጆቹን ለመገናኘትና ለእሱም መወለድ ምክንያት በሆነው ቀድሞ በነበረው የክፍላተ ሃገር አወቃቀርን በሚያራምድ የፖለቲካ ድርጅት

እንቅስቃሴ ስር ቢሆን የተሻለ ከመሆኑም በላይ አሁን በየአቅጣጫው እንደ መብትና ፋሽን የሚዥጎደጎደውን ጎሰኝነትንም ያጠፋል።ስጋት ላይ ያለውንም አገር የመበታተን አደጋ ያሶግዳል።

ምስጋና ይግባቸውና ይህንን በተረዱት የየክፍላተ ሃገሩ ተወላጆች ኢትዮጵያን ለማዳን አንገታቸውን ቀና ቀና እያደረጉ ነው።ያንን መነሳሳት ለማኮላሸት ግን በሥልጣን ላይ ያለው የጎሰኞች ቡድንና ስርዓት የማይገለብጠው ድንጋይ፣የማያሴረው ሴራ የለም።ግማሹን በጥቅም ሌላውን በጎሰኝነት ለማጥመድ መረቡን ከዘረጋ ውሎ አድሯል።ለዚያ ትልቁ ኢላማ የሆነው የጥምር ጎሳ ተወላጁ ነው።ዓላማቸውን ካሳኩ በዃላ ግን ቀድሞ የሚመታው ይኸው የጥምር ጎሳ ተወላጁ ኢትዮጵያዊ  መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።በነሱ አባባል ይህ ትውልድ ዲቃላ ነው።ዲቃላ ደግሞ በጠላትነት የሚፈርጁት እንጂ የእኛ ነው ብለው የሚያቅፉት አይሆንም፤ተጠቅመውበት ይፈጁታል።

 

ከጥምር ጎሳ የተወለዱት ኢትዮጵያውያን የናታቸውን ወይም የአባታቸውን ነጠላ የጎሳ ማንነት እንዲሸከሙና የሌላውን አካላቸውን ክፍል የሆነውን ጎሳ እንዲረሱ ብሎም እንዲጠሉ የሚደረገው ቅስቀሳ ከቀን ወደ ቀን እያደገ በመምጣት ላይ ነው።ከመጥላትም አልፎ ከማጥቃት ደረጃ ላይ ደርሷል።ይህ አዝማሚያ በፍጥነት ካልተቀጨና ከጎሳ አደረጃጀት ነጻ በሆነ አገራዊ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ካልተተካ በቤተሰብነት ክፉና ደጉን

ተካፍለው የኖሩትን ባልና ሚስቶች፣ ልጆችና የልጅልጆችን የሚያጠፋ ብቻ ሳይሆን በፍቅርና በደስታ በሰላም የኖሩባትን ፣ለግንኙነታቸው ምክንያት የሆነችውን አገራቸውን አትዮጵያንና በዓለም መታወቂ የሆናቸውን ኢትዮጵያዊነታቸውን የሚያጠፋ ይሆናል።

ከሁለት ጎሳ ቤተሰብ የተወለዳችሁ ኢትዮጵያዊያን ሆይ!

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሕዳሴ አብዮት ለፖለቲካው ( አስራት አብርሃም)

ከቶ ከወላጆቻችሁ መካከል የትኛውን ወዳችሁ የትኛውን ልትጠሉ ትችላላችሁ? የአባቶቻችሁን ጎሳ መርጣችሁ ዘጠኝ ወር ተሸክማ ወልዳ፣ጡት አጥብታና ተንከባክባ ያሳደገችን እናት ጎሳ መጥላት ማለት የእራሳችሁን ግማሽ አካል መጥላት ብሎም የጠቡበትን ጡት ነካሽነትና ከሃዲነት ይሆናል።የእናትንስ ጎሳ መርጦ የአባትን ጎሳ መጥላት ደፋ ቀና ብሎ ያሳደገን አባት እጅ ቆርጦ መጣል ብሎም የራስን ግማሽ አካል መካድና መጥላት አይሆንምን?ብዙሃኑ የዚህ አይነት ጎደሎ ሰይጣናዊ አስተሳሰብ የምትቃወሙ እንጂ የምትደግፉ እንዳልሆናችሁ ይታወቃል።ለእናንተ ለጥምር ጎሳ ተወላጆች መፈጠር የእናትና ያባቶቻችሁ ግንኙነት ወሳኝ መሆኑ አይካድም።ለዚያ ደግሞ የመገናኛው ምክንያት የሁሉም ጎሳ ተወላጅ ተከባብሮ በሰላም የኖረባት ኢትዮጵያ መኖሯ ነው።

 

በጎሳ ተዋረድ የሚደረግ የጠባብ ጎሰኝነትና ጸረ ኢትዮጵያ ቅስቀሳ የኢትዮጵያዊነት ፍሬ የሆናችሁትንም መብት ለመግፈፍና ለማጥፋት የታቀደ ሴራ መሆኑን አትዘነጉትም።ስለሆነም ኢትዮጵያን ማዳን ማለት የጎሰኞችን ተንኮል ማክሸፍና ፣የትልቅ አገር ባለቤትም መሆን ማለት  ነው። ኢትዮጵያን ማዳን  እራሳችሁን፣ወላጆቻችሁንና በቤተሰብ ሐረግ የተሳሰረውን ዘመድ አዝማድ ማዳን ማለት ነው።ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትንም ማዳን ማለት እናንተም እንደ እናትና አባቶቻችሁ፣እንደ አያትና ቅድመአያቶቻችሁ የጎሳ ማንነት ሳያግዳችሁ ከፈለጋችሁት ጋር አብሮ የመኖርና ወልዶ የመሳም ፣በፈለጋችሁበት ቦታ በመኖር የመሥራትና ንብረት የማፍራት መብታችሁን ማስከበር ማለት ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጠላት መሳሪያ የሆኑ ጥቂት መሰሪዎች በሚያራምዱት ጸረ አንድነት የጥላቻ ዘመቻ ጎሳ ለይቶ መፋጠጡ፣ማፈናቀሉ፣መግደሉና ማሳደዱ፣መሬት መንጠቁ እያደገ በመምጣት ላይ ነው፣እርምጃው አገራችንንና ሁላችንንም ከመበታተን ስጋት ላይ ጥሏል።በጊዜው ካልተገታ ሁሉም ተያይዞ መቀመቅ መግባቱ አይቀሬ ነው።ያ ከመሆኑ በፊት የአንድነት ተምሳሌት የሆናችሁት የጥንድ ጎሳ ተወላጆች ድምጻችሁን ማሰማት ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ እርምጃ ልትውስዱ ይገባችዃል።የጎሰኝነትን አስተሳሰብና የተገነባውን የክልል ግምብ አፈራርሶ አገራዊ አንድነትን በጠንካራ መሰረት ላይ ለመገንባት ከሚታገሉት ጋር በመሆን ብሔራዊ ግዳጃችሁን ለመወጣት ተነሱ።

 

በሰላም ተከብራችሁ ለመኖር የሚያስችላችሁን ኢትዮጵያዊነትን ለማዳን በአንድነት ተሰለፉ።ኢትዮጵያን ማዳን ማለት እራስን ማዳን ነውና!

የጥቅም ተገዥ የሆኑ አነስተኛ የጥንድ ጎሳ ተወላጆች ወይም ከሌላው ጎሳ ጋር ተጋብተው የኖሩና የሚኖሩ ብሎም የወለዱ በአንዱ የጎሳ ሰልፍ ውስጥ ገብተው የአባታቸውን ወይም የእናታቸውን ጎሳ መርጠው፣የኑሮ ጓደኛና የልጆቻቸውን ግማሽ አካል የሆነውን ሌላውን ጎሳ ሲያጠቁና ሲያስጠቁ እንደኖሩና አሁንም በማስጠቃትና በማጥቃት ላይ እንዳሉ የሚታወቅ ነው። በአሁኑም ጊዜ በጋብቻ ተሳስረው ፣ልጆች ወልደው በፍቅር የኖሩ የተለያዩ ጎሳዎች ትውልድ የሆኑ ባለትዳሮች በተበተነው የጎሳ ማንነት ቫይረስ ተበክለው ለቤት መፍረስና ለልጆች መበተን ምክንያት ሆነዋል። እነሱ ያለፉበትን የፍቅር ህይወት ልጆቻቸው እንዳያልፉበት ደንቃራ ሆነዋል።የጥላቻና የበቀል ኢሰብአዊነት ምግባር ተከታዮች አድርገዋቸዋል። ልጆቻቸው የአንድ ወገን ተከታይ ሆነው እርስ በርሳቸው በጠላትነት እንዲቆሙ አድርገዋቸዋል።ይህ ኢሰብአዊና ከፋፋይ አድራጎት ሊቆም ብሎም ሊወገድ ይገባል።ልጆችን በማያውቁት ጣጣ ውስጥ መንከር አስነዋሪ ብቻ ሳይሆን ምድራዊ ሃጢያት ነው።

 

ይህንን ወራዳ አመለካከትና አድራጎት የቅኝ ገዥዎች መሣሪያ የሆነው፣አገራችንን በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ መዳፍ ሥር የጣለው ኢሕአዴግ የተባለው ቡድን ያሰፈነው ስርዓት ለሃያ ሰባት ዓመት ተጠቅሞበታል።በአሁኑ ጊዜ በቦታው የተተካውም የዚያው የኢሕአዴግ አካል የነበረው ኦሕዴድ መራሹ የብልጽግና ስብስብ ያንኑ ያረጀ ያፈጀ አገር አፍራሽ፣ሕዝብ አጫራሽ የሆነ የጎሳ ፖለቲካ በማራመድ አገራችንን ከባሰ ውድቀት ላይ አድርሷታል።ለውጥ ተብዬው ትያትር የግለሰቦች የሥልጣን ቦታ መቀያዬር እንጂ የሥርዓት ለውጥ እንዳላመጣ ባለፉት ሦስት ዓመታት አይተነዋል።ከአሁን በዃላም በብልጽግናና በአጃቡዎቹ ለውጥ ይመጣል ብሎ መጠበቅ፣የጅልነት ጅልነት ከመሆኑም በላይ አንገትን ለካራ አመቻችቶ መቀመጥ ማለት ነው።ይህንን በማወቅና ባለማወቅ እያጨበጨቡ ከበው የሚያወናብዱ የጥቅምና የሥልጣን ተቋዳሾች ሕዝቡን በማደንዘዝ ላይ ተሰልፈዋል። ቦታው በጎሰኞቹና ለነሱ መሳሪያ በሆኑ ቡድኖችና ግለሰቦች  መፈንጫ እንዳይሆን ነቅቶ መጠበቅና መከላከል የሁሉም ድርሻ ነው።

 

የፖለቲካ ሥራ በእውቀት ላይ የተመሰረተ አገርና ሕዝብ የተጋለጡበትን አደጋ ለማሶገድ፣ የወደፊቱንም ትውልድ ዕድልና ኑሮ የተሻለ እንዲሆን የሚቀይሱበት ሁለእንተናዊ ሳይንሳዊ ችሎታ እንጂ በጭፍን ጥላቻና ፍላጎት ላይ የሚመሰረት የመንጋ ወይም የጭፍራ ድግስና ዳንኪራ የሚመቱበት የሆያ ሆዬ መድረክ አይደለም።

የጎሳ ማንነት የፖለቲካ መዘውር ከሆነ አገር ያፈርሳል፣ሕዝብ ያጫርሳል።ይህንን ከሌሎች የቅርብና የሩቅ አገሮች ላይ በደረሰው ልንገነዘበው እንችላለን።በአገራችንም የሚከናወኑት ጎሳ ተኮር ጥፋት፣ጥቃት፣ማፈናቀልና የጥላቻ እርምጃዎች የዚያ መንደርደሪያዎች ናቸው።ይህ ጎሳ ተኮር አሰላለፍ የአስራ ስድስተኛውና አስራሰባተኛው የዘመነ የመሳፍንት ስርዓት ነጸብራቅ እኩይና ዃላ ቀር ድርጊት ነው።በሰለጠነው የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ተቀባይነትና ቦታ የለውም።ጎሰኝነት ከከረረ ፋሽዝምን ይወልዳል። የሁሉም ፋሽስቶች መነሻ ጎሰኝነት ነው።የጎሰኝነት ትርፉ የአንድ አገር  ሕዝብ ደቆና ደህይቶ አገረቢስ ሆኖ በመሰደድ ፤መሳቂያና መሳለቂያ ከመሆን በተረፈ እራሱን ለሚጨርስበት፣ለእርስ በርስ ጦርነት ለሚውል  ለመሳሪያ ቸብቻቢ አገራትና  ማፊያ  የጥቅም በርና ዕድል መፍጠር ነው።በራስ ኪሳራ ሌላውን ማበልጸግ ማለት ነው።ላለፈው አንድ ዓመት ሲካሄድ የቆየው የሥልጣን ግብግብ ያስነሳው ጦርነት ብዙ ሕዝብ በተለይም የአማራውን ማህበረሰብ የጎዳ፣ከመኖሪያ ቦታው ያፈናቀለ፣ ንብረቱን ያወደመ ትርጉመ ቢስ ጦርነት ነው።ይህንን ጦርነት ማሸነፍ የሚቻለው የጦርነቱ ባለቤቶች የሆኑትን ህዋሃቶችንና  የአስተሳሰባቸው ተሸካሚ የሆኑትን ኦነግ መራሹ ኦህዴድ/ብልጽግና  የጎሰኞች ስብስብ  በሙሉ በማሶገድና ጭራሽ እንዳያንሰራሩ ማድረግ ሲቻል ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በትህነግ የጦርነት ክተት አዋጂ  “ወራሪ እና ተስፋፊ ” ማን ነበር ? - ማላጅ

ጊዜው አሮጌውንና ዃላቀሩን የጎሳ ፖለቲካ አስተሳሰብ አውልቀን ዘመናዊና አገራዊ የፖለቲካ አመለካከት የምንላበስበት እንዲሆን ተግተን መስራት ይኖርብናል።የጥምር ጎሳ ተወላጆች ለዚህ አገራዊ ትግልና ተጋድሎ ትልቅ ሚና ሊጫወቱ ይገባቸዋል።ከነጠላ የጎሳ አስተሳሰብ ወጥተው በኢትዮጵያዊነት ጎራ ሊሰለፉ ግድ ይላል።አክራሪ ጎሰኞች የእናት ወይም የአባታቸውን የጎሳ ማንነት ለጥፋት እዬተጠቀሙበት መሆኑን በመረዳት መቃወም ይኖርባቸዋል።

ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነውን ሰሞኑን ከአንድ ጓደኛዬ ያገኘሁትን መካሪና አስተማሪ የሆነ ታሪክ ለማቅረብ እውዳለሁ።ጽሁፉም አንድ  ከገባበት የስህተት ጎዳና የወጣ ወንድማችን ያቀረበው የግል ታሪክ ነው።ጽሁፉን ከአውሬነት ወደ ሰውነት ደርሶ መልስ ብዬዋለሁ። በስያሜው የታሪኩ ባለቤት እንደማይቀዬመኝ እተማመናለሁ።ቁም ነገሩ ይዘቱ አለመነካቱ እንጂ ስያሜው አይደለም። ሌላውም እንዲማርበት ያቀረበው ጽሁፍ ነው።በጠዬቀው መሰረት ለሌሎቹ የጥምር ጎሳ ተወላጆች መልካም ምሳሌ ስለሚሆን እኔም በጽሁፌ ውስጥ እንደሚከተለው አካትቼ አቅርቤዋለሁ።

 

 

ከአውሬነት ወደ ሰውነት ደርሶ መልስ

 

ለመምህር ፋንታሁን ዋቄ

ከ ጳጳ ኩምሳ(የአባቴን ስም ቀይሬ ነው)

ይህንን ጽሁፍ እንድልክለዎትና በገጽዎ ላይ እንዲለጥፉልኝ የመከረኝ እርሰዎ የማያውቁት ግን እርሰዎ በግቢ ጉባኤ ያስተማሩት ጓደኛዬ ነው።እኔ በራሴ ምክንያት ፌስቡክ አልጠቀምም።ፈቃደኛ ከሆኑ ያስተናግዱልኝ።

በቁሜ መሞቴን ያሳዬኝ ጓደኛ አገኘሁ።እናንተ ደግሞ ተነስቼ ቆሜ ለሌሎች የምተርፍበትን መንገድ ምከሩኝ።ታሪኬ እንዲህ ነው።

እናትና አባቴ በቤተክርስቲያን ሥርዓት በቅዱስ ቁርባን ተጋብተው እኔን ወለዱኝ።ዕድሜዬ ሶስት ዓመት እንደሞላኝ የብሔር ፖለቲካ እራሱን አሳምሮ ፣ሃይማኖት መስሎና አክሎ ወደ ቤታችን ገባ።አባቴ እናቴን ፈትቷት የራሱን ብሔረሰብ ከእናቴ ብሔረሰብ ነጻ እናወጣለን ወደሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ተቀላቀለ።በኬንያ በኩል በስደት አሜሪካን አገር ገባ።ከዚያም ሚኖሶታ ከሚኖሩ ጓደኞቹ ጋር ተገናኝቶ በብሔረሰብ ነገረ-ሰብ እና ማሕበረሰብ ሳይንስ የዶክትሬት ዲግሪውን አግኝቶ 2 መጽሕፍትን አሳተመ።አሁን ጀርመንና ቤልጅዬም እዬተመላለሰ ነገረ-ዘረኝነትን ያስተምራል።በዘረኝነት ትምህርት ፕሮፌሰር ሆኗል።እኔንም ከሥጋ ወላጅ እናቴ እንድለይ ሰብኮ አሳመነኝ።የእርሷንም እምነት የጠላቶቻችን ነው በማለት ከእምነት አሶጣኝ።አሁን 26 ዓመቴ ነው።እኔም እንዳባቴ ስደት ጀምሬ ሶማሊያ ገባሁ።ከዚያም ኤርትራ በርሃ ውትድርና ሰልጥኜ ስመረቅ በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ ተደርጎ በአጋጣሚው ወደ አገር ቤት ተመለስኩ።በልጅነቴ የማውቃቸውን የአባቴ ዘመዶችን ለመጠዬቅ ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ ተጓዝኩ።ዘመዶቼ በመቱ የታወቁ ኦርቶዶክሳውያን ናቸው።

ከስደት ስመለስ በእምነታቸው በርትተው፣የተወሰኑት ካህናትና ዲያቆናት ሆነው ጠበቁኝ።ልጠይቃቸው ሄጄ 15 ቀናት ያህል አብሬያቸው ስቀመጥ አንድም ቀን ፣በምንም ጉዳይ በሃሳብ ልንግባባ አልቻልንም።አባቴ ባስተማረኝ መሠረት ስመዝናቸው ልክ እንደ እናቴ ዘመዶች ሆነው ስለሚታዩኝ አስጠሉኝ።

እነዚህ የመቱ ዘመዶቼ ሃይማኖታቸውም ልክ እንደ እናቴ ሆኖ አገኘሁት።በጥላቻ ተሞልቼ ወደ ፊንፊኔ ተመለስኩ።የገዛ ዘመዶቼን የምጠላበት አመክንዮ እረፍት ነሳኝ።ብሔር ብቻ ከሆነ ለምን ያስጠሉኛል?ምንድን ነው የምፈልገው?ውስጤ ውስጥ ሆኖ የሚቆምርብኝ ሌላ አካል አለ ወይስ እኔ በነጻነት የማስብ ልዑላዊ ሰው ነኝ? ሰው ነኝ በድን?የማያቋርጥ ጥያቄ እረፍት ነሳኝ።ይህ የጥያቄ ናዳ እንደወረደብኝ በልጅነቴ እጅግ ከምወደው ከሌላ ወዳጄ ጋር ተገናኘሁ።ዘመዶቼን ከዚያ ከጠላቶቼ እምነት እንዴት ማስወጣት እንደምችል ምክር ልጠይቀው  በስልክ ቀጠሮ ስጠይቀው ሳምንት አዲስ ዓለም ማርያም እንገናኝ አለኝ።በሁለት ነገር ተቸሁትና ቀጠሮውን ተቀበልኩ።አንደኛ አጅሬን “ አዲስ ዓለም “ብሎ በመጥራቱ፣ ሁለተኛ “ማርያም ቤተክርስቲያን እንገናኝ” ማለቱ ቅር እንዳሰኘኝ ነግሬው ስልክ ስዘጋ መልሶ ደውሎ “ይቅርታ፣ አንተ በፈቀድከው ቦታ እገኛለሁ፣ቦታዎችንም አንተ በምትነግረኝ ስም እጠራቸዋለሁ” አለኝና ዘጋው።

ውስጤን አንዳች ሃፍረትና ከንቱነት ተሰማኝ።የጓደኛዬ ትህትናና ፍቅር በጣም ገርሞኝ የእኔን ቦጅቧጃነት እያገናዘብኩ የቀጠሮውን ቀን በጉጉት ጠበቅሁ።ጓደኛዬ አምቦ-ወንጪ አካባቢ የተወለደ ወደ ኦሮሞነት የመለወጥ ሂደት ላይ ከሚገኙ የጨቦ ቤተሰቦች እንደተገኘ ዱሮ ነግሮኝ ነበር።ብሔርህ ምንድን ነው ሲሉት መልሱ “መጀመሪያ ሰው፣ቀጥሎ ኢትዮጵያዊ፣ከዚያም ጨቦ፣አሁን ግን ኦሮሞ የመሆን ሂደት ላይ ነኝ፤ከሁሉ የሚበልጥብኝ ማንነቴ የሥላሴ ልጅነቴ ነው።ምክንያቱም ከሰውነት በስተቀር በሌሎች ንዑሳን ማንነት እንዳልመካም፣እንዳልሸማቀቅም ነጻ አውጥቶኛልና፣ክርስቶስ በቸርነቱ የሰጠኝ ልጅነት ስላለኝ የማልደራደርበት ማንነቴ ብሔሬ እርሱ ነው”ይልና ይስቃል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአበበ ገላውና የዲያቆን ዮሴፍ  ኢንተርቪው

በሳምንቱ ስንገናኝ  መቱ የሚኖሩ የአባቴን ዘመዶች በምን መላ ከጠላት ሃይማኖት እንደምገላግላቸው ምክር ስጠኝ ብዬ በቀጥታ አፈነዳሁት።ለተወሰነ ደቂቃ አንገቱን አቀርቅሮ ቀና ብሎ ዓይኔ ውስጥ ሃዘኔታ በሚመስል ፊቴን ትኩር ብሎ ተመለከተኝ፤ዓይኑን አይቼ ወደ መሬት አቀርቅሬ ቀና ስል እርሱም ብድግ ብሎ እጁን ቀኝና ግራ ዘርግቶ አቀፈኝ።መንሰቅሰቅ ጀመረ።እኔም በማላውቀው ምክንያት አብሬው አነባሁ።ከመቅጽበት ለቅሶ አቁሞ፣ጠንክርና ትዕዛዝ በሚመስል ድምጽ ምክር የምሰጥህ በምነግርህ መርሆዎች ከተስማማህ ብቻ ነው።ከዚያ ውጭ ስለማልጠቅምህ ከዛሬ ጀምሮ አንገናኝም አለኝ።ደንግጬ እሺ ንገረኝ አልኩት።ወዲያው ልክ በጽሑፍ እንደተዘጋጀ ሰው የሚከተሉትን ነጥቦች ጻፍ ብሎ አጻፈኝ።

1 ከቡድን -እሳቤ ነጻ በመሆን በሰውነት መቆም እንድሞክር፣

2 ጭፍን እምነት ፣አመክንዮ አልባነት ስሜታዊነትን፣ለጊዜውም ቢሆን ገታ በማድረግ በአዲስ ማሰብ እንድጀምር፣

3 ፍትሕ፣ እውነትና ፍቅርን የማልደራደርበት የስብዕና መስፈርት አድርጌ እንደመርህ እንድቀበል፣

4 አሁን በእውነት ለመኖር  አድራጊና ተደራጊ በሌሉበት ያለፈን ታሪክ ለፖለቲካ ግብ ሲሉ በዝንባሌያቸው በክለው ከሚቀርቡ ሰዎች እንደወረደ ላለመቀበልና አሁን በህይወት ከሚገኝ አሉታዊ ነገር ተደረጉ በምላቸው ወገኖች ልጆች መካከል በማይመለከታቸው ጠላትነት በልቤ እንዳልይዝ ቃል እገባለሁ።

ጽፌ ሳበቃ ይህ ሁሉ ግን ለምን አስፈለገ?አልኩት።በመቆዬት ታውቀዋለህ!ስለተስማማህ ትጠቀማለህ እንጂ ምንም የምታጣው ነገር የለም።በመጨረሻ ሃሳብህን የመቀዬር ሙሉ መብት አለህ።ብቻ አደራህን የመጨረሻውን ነጥብ ዋና አድርገህ ያዝልኝ።ብዙዎች በራሳቸው አዕምሮ ሳይሆን በቡድን እያሰቡ እውነት የማግኘት መንገዳቸውን ዘግተው በነፍስም በሥጋም ተጎድተዋል፥አለኝ።በከፊል ተስማምቼ ምሳ እዬበላን አወጋንና ለሌላ ቀጠሮ ተስማምተን እኔም ወደ አስቼኳይ ጉዳይ በረርኩ።

በሌሎች ተከታታይ ቀጠሮዎች፣ በአብሮ ውሎ ማደር ሂደት ብዙ ጉዳይ ላይ ተነጋገርን።ከሁሉ ጎልቶ የሚጨቀጭቀኝን ጥያቄ ብልቱን ሁሉ ፈትቶና ገጣጥሞ በማስረዳት አሳረፈኝ።ከዚያ ቀጥሎማ  ነገረ-ሃይማኖትን አነሳን፣ለምን ከኦርቶዶክስ ወጥቼ ኢአማኒ በመሆን ያልሆንኩት ሌሎች እምነቶች በተለይ ፕሮቴስታንት ፣ውሃቢያ አክራሪ ኢስላም፣ከባሕል እጅግ እርቆ በፖለቲከኞች የተፈበረከ የዋቂፈታ አይነት እንደመደገፍ ኦርቶዶክስ ጠል መሆን እንደቻልኩ፣

ሀ/ አመክንዮታዊ ተጠየቅን፣ ለ/ነገረ-መለኮታዊ አስተምህሮን፣ሐ/የክርስትና ሃይማኖት ታሪክን፣መ/የኢትዮጵያን ጥንታዊ አፈጣጠርና በዘመናት ጉዞ የተፈጠሩ ግጭቶችና ውድመቶችን፣ሠ/ የማንነት ፖለቲካ የምዕራባውያን አስተምህሮን፣አምስቱን እንደምሰሶ ተጠቅመን መማርና መከራከር ላይ ተስማማን።

ከ5 ወራት በዃላ ስህተቴን አወቅሁ።የአባቴንና የእናቴን አንድነት ያፈረሰውን የማንነት ፖለቲካ አታላይነትን በኦርቶዲክሳዊ ዓይን ለማዬት ስችል ሞቼ እንደነበር ተረዳሁ።ለመሞቴም የአባቴ ስብከት ምክንያት መሆኑንና በፍጥነት እንዳልነሳ የመንጋ ጫጫታ ፣የቡድን ጭብጨባ፣እንደ መቃብር መክደኛ ድንጋይ አፍነው ይዘውኝ እንደቆዩ ብልጭ አለልኝ።ስብእናዬን ተቀምቼ በሌሎች ማህደርነት አዕምሮዬ ሲሠራ ንደኖረ ገባኝ።መቱ ተመልሼ የአባቴን ዘመዶች ይቅርታ ጠይቄ አመስግኘና አብሬ ቆይቼ  በደስታ ተመለስኩ።የሕሊና ወቀሳ ፣ጥላቻ ጫና፣ማስመሰልና ጫጫታን ጠላዃቸው።በአሁኑ ጊዜ የአባቴን 3 መጽሓፎች ገምግሜ በ5 ገጽ ወረቀት ፉርሽና ገለባ መሆኑን ሞግቼ ላክሁለት።እሱም በአንድ መስመር ኢሜል፥ አንተ ባንዳ የጎበና ዲቃላ ልጄ አይደለህም ድሮም ከነዚያ ተወልደህ መች ሰው ትሆናለህ?የሚል መልስ ላከልኝ።ጓደኛዬ ባስተማረኝ 4ቱ መርሆዎችና 5ቱ የመክንዮ ምሰሶዎች ስለጸናሁ በአባቴ ስድብና ማስፈራራት አልተሸበርኩም።አመሰግናለሁ የሚል ቃል ብቻ መልሼ ዝም አልኩ።

አሁን አዲስ ሰው ለመሆን እዬሞከርኩ ነው።ፕሮፌሰርነቱ መቅሰፍት እንደሆነ ከአባቴ አወቅሁ።የእርሱ ቢጤ ብዙ የተቀሰፉ አዕምሮዎች መኖራቸውን በኤርትራ በርሃ በነበርኩ ጊዜ እዬመጡ የሚሰብኩኝን አዋቂዎች ተብዬዎች እያስታወስኩ አዘንኩላቸው።አሁን በአገራችን የሚካሄደው ስደት፣ሞትና ጦርነት ፣ከሁሉም በላይ በለጋ ወጣቶች ልቦና የተዘራው መርዝ በተግባር የመገለጥ ዕድል ሲያገኝ ምን እንደሚፈጥር የእራሴን የቀደመ የውስጥ ፈንጂ እያስታወስኩ ፈራሁ።አሁን ለወገኖቼ የምለው፣

1/እኔስ መሞቴን አውቄያለሁ፣ተነስቼ በመቆም ለሌሎች መድሃኒት እንድሆን ልምዱ ያላችሁ ምከሩኝ።

2/ እንደአባቴ ያሉትን እስከሽበት ድረስ ዕድሜ አግኝተው መሞታቸውን ለመረዳት ያልቻሉና የእኔን ትውልድ በመግደል የቀጠሉትን በምን መንገድ መመለስ ይቻላል?

3/ሙታን ነቅተው እንዳይነሱ ጫና የሚያደርገውን መዋቅራዊና ሥርዓታዊ የዘረኝነት ፖለቲካ መታገል የሚቻለው እንዴት ነው?

እስኪ ለእኔም ምከሩኝ፤እናንተም ባላችሁበት ተመካከሩ።ለዚህ የትንሳኤ ጉዞ ምክንያት ለሆነኝ ለአምቦው ጓደኛዬና አምርረው ተጣልተውኝም ቢሆን በአርአያነት የመጀመሪያውን ከቡድን እሳቤ እስረኝነት ለመውጣት ጥያቄ ለመጠዬቅ የረዱኝን  የመቱ ዘመዶቼን ያለባቸውን ፖለቲካው ጫና ተቋቁመው ባሉበት እንዲጸኑ በጸሎት አግዙኝ።

የእኔ ስመ-ክርስትናዬ ተክለ-ሓዋርያት ነው።አስቡኝ!

 

ይህ ከዚህ በላይ የሰፈረው መልእክት በላከልን ወንድማችን በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ የሚገኙት የጥምር ጎሳ ተወላጅ የሆኑት ኢትዮጵያውያን ከታሪኩ ተምረው ካሉበት ወይም ሊገቡበት ከሚችለው አዘቅት ለመዳን ይረዳቸዋል ብዬ አምናለሁ፤ብርታትና ብልህነቱን እንዲሰጣቸው የእኔም ምኞቴ ነው።

 

ኢትዮጵያንና እራሳችንን ከጎሰኞች ጥቃትና ጥፋት እንከላከል!!

ኢትዮጵያ በልጆቿ የተባበረ ትግል በአንድነትና በነጻነት ለዘላለም ትኑር!!!

 

አገሬ አዲስ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share