ብዙዎች የማናውቀው ወይንም ልብ የማንለው አንድ ነገር አለ። አሁን ባለው ሕገ መንግስት፣ አሰራርና ፖለቲካዊ ሲስተም ኢትዮጵያ የለችም። ኢትዮጵያዊነት በሕገ መንግስቱ ቦታ የለውም። ኢትዮጵያዉያን እንደ ዜጋ እንደ ኢትዮጵያዊ እውቅና የላቸውም። የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ብሎ ነገር የለም።ቴክኒካሊ ኢትዮጵያ የለችም።
ያለው አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ ጉራጌ የሚሏቸው ብሄር ብሄረሰቦች ናቸው። የአማራ መሬት፣ የኦሮሞ መሬት፣ የትግሬ መሬት የሚል ነው ያለው። ለአንድ ጎሳ/ዘር አንድ አካባቢ ተሸንሽኖ ተሰጥቶታል። ተከልሎ። ታጥሮ። የዚህ ጎሳ አባላት ለነርሱ በተመደበው ክልል ወይም ዞን ውስጥ ባለአገር ናቸው። ከዚያ ውጭ ደግሞ በሌሎች በጎ ፍቃድ ነው የሚኖሩት።
ባይገርማችሁ ውህድ ኢትዮጵያዊነት ብሎ ነገር የለም። አንድ ዜጋ የግድ አንዱ ጎሳ መምረጥ አለበት። አንድ ኢትዮጵያዊ በአንዳንድ የኢትዮጵያ ግዛቶች ውስጥ ካለው መብት ይልቅ በውጭ አገር ያለው መብት ይበልጣል። አንዳንድ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሄዶ ኢንቨስት ከማድረግ ታምራት ነገራ እንዳለው ኬኒያ ሄዶ ኢንቨስት ማድረግ ይቀላል።
እንግዲህ አሁን ያለው ስርዓት ሲስተም ይህ እንደመሆኑ፣ ኢትዮጵያን ማግኘት ከፈለግን ኢትዮጵያን ያጣፈውን ሕግ መንግስትና የጎሳ አወቃቀር መቀየር አስፈላጊ ነው።
ሕግ መንግስቱ የሚሻሻል፣ የጎሳን አወቃቀሩ የሚቀየር ከሆነ ያኔ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ይሆናል። ከኦሮሞ ልዩ ኃይል፣ ከፋኖ፣ ከአማራ ልዩ ኃይል፣ ከአፋር፣ ሶማሌ .…ልዩ ኃይሎች ጠንከር ጠንከር ያሉት፣ ብቃት ያላቸው ተወስደው፣ ወደ መከላከያ እንዲገቡ ተደርጎ ፣ ጠንካራ የአገር መከላከያ ሰራዊት መገንባት ይቻላል። ፋኖም፣ ልዩ ኃይሎችም ሆነ ሌሎች የታጠቁ ሚሊሺያዎች እንዲከስሙ ይደረጋል። የአብይ መንግስት ይሄን ካደረግ፣ ቀደም ሲል ለሰራቸው ስህተቶችና ጥፋቶች ይቅርታ አድርግለታለሁ።
ሕግ መንግስቱ ካልተሻሻ፣ የጎሳ አወቃቀሩን ካልተቀየረ ግን፣ እመኑኝ ኢትዮጵያ አትኖርም። ኢትዮጵያን እርሷት።
የመከላከያ ሰራዊትም አለ ቢባልም በውስጡ ያሉ ወታደሮች ከዘር ተጽኖ ሊላቀቁ አይችሉም። ጦረነቱ የአማራ ነው አንዋጋም ብለው ስንቱ የመከላከያ ሰራዊት አባል ሲሸሽ አልነበረም እንዴ ???? መከላከያ በብቃት ዜጎች ሊጠብቅ አይችልም። አልቻለምም።
የአማራ ማህበረሰብ ለኢትዮጵያ ብሎ ብዙ ዋጋ ከፍሏል። ተለይቶ ጭፍጨፋ ጄኖሳይድ ተፈጽሞበታል። አሁን ግን በአማራው ላይ የደረሰው የግፍና የሰቆቃ ጽዋ ሞልቶ ስለፈሰሰ አማራው ተደራጅቶ የሕልውና ትግል እያደረገ ነው። ፋኖ በጎጃም፣ በጎንደር፣ በሸዋ በወሎ እየተደራጀ ነው። እየሰለጠነ ነው። እየታጠቀ ነው። ሌሎች እንደፈለጉ ፣ ከዚህ በፊት እንደሚያደርጉት አማራዉን ሲገድሉ፣ ሲጨፈጭፉ የሚታገስ ማሀበረስብ ከዚህ በኋላ አይኖርም።
ማንነታችን ኢትዮጵያዊነት ነው የምንል አለን። ዉህድ ኢትዮጵያዉያን የሆንን። ባይገርማችሁ እኛን የኦሮሞም ሆነ የትግራይ ብሄርተኞች “አማራዎች” ነው የሚሉን። ለምን ለነርሱ የኢትዮጵያ ብሄረተኝነት ብሎ ነገር ስለሌለ። ሁሉንም ነገር በዘር መነጽር ብቻ ስለሚያዩ። ስለዚህ የፋኖ መደራጀትና መጠናከር ለኛም ለዉህድ ኢትዮጵያዉያን የሚተርፍ ነው። ፋኖችን የምንደግፈውም ለዚህ ነው። በአሁኑ ጊዜ ፋኖችን አለመደገፍ፣ አለማጠናከር ማለት በአማራው ማህበረሰብ ላይ መፍረድ፣ የአማራ እልቂት፣ ጄኖሳይድ ይቀጥል ማለት ነው።
አማራውና ዉህድ ኢትዮጵያዊ በብዛት በሚኖርባቸው አካባቢዎች ጎጠኞች እንደፈለጉ ማድረግ የለባቸውም። የአዲስ አበባ ፣ የናዝሬት፣ የደብረ ዘይት፣ የደራ፣ የፈንታሌ፣ በአጠቃላይ የሸዋ፣ የምስራቅና ሆሮጉድሩ ወለጋ የመሳሰሉት..…ጉዳይ በሰላም በፍቅር፣ በመከባበር እልባት ካለገኘ፣ አገርህ አይደለም እየተባለ፣ እየተገደለ፣ እየተገፋ፣ አሁን ባለው የጎሳ አወቃቀር መሰረት አብዛኛው ሸዋ ለምሳሌ የኦሮሞ መሬት ነው በመባሉ፣ አማራው መጤ፣ ነፍጠኛ እየተባለ፣ ሊቀጥል አይችልም። ስለዚህ የመብት፣ የሕልውና ጉዳይ ስለሆነ የአማራ ነው፣ የኦሮሞ ነው በሚል ውጊያና ጦርነት መከሰቱ አይቀርም። የትግሬ ነው የአማራ ነው በሚል እነ ወልቃይት እንዳወዛገቡት፣ የሶማሌ ነው የኦሮሞ ነው በሚል እነ ሞያሌ ድሬዳዋ፣ ባቢሌ … እንደሚያወዛግቡት በአማራና በኦሮሞ መካከል ውዝግብ መነሳቱ አይቀርም።
እስቲ አስቡት አሁን ናዝሬት ላይ 75% ኦሮምኛ የማይናገር አማርኛ ተናጋሪው ማህበረሰብ ባለበት ከተማ፣ የከተማዋ መስተዳደር፣ ፖሊስ ቀበሌዎች ወዘተ አገልግሎት የሚሰጡት በላቲናቸው ናቸው። ይሄ አይነት ዘረኛና አፓርታይዳዊ አስራር እንዴት ሊቀጥል ይችላል ? በነገራችን ላይ የአብይ መንግስት ይሄንን እንኳን ማስተካከል አልቻለም፣ ላለፊት 4 አመታት።
አንዱ እየገደለ፣ ሌላው እየተገደለ፣ አንዱ እየገፋ ሌላው እየተገፋ ፣ አንዱ እያፈናቀለ፣ ሌላው እየተፈናቀለ ልንኖር አንችልም። አሁን ያለው ሕገ መንግስትና የጎሳ አወቃቀር ይሄንን ነው እያበረታታ ያለው።
በመሆኑም አሁንም መፍትሄው ተከባብረን፣ የዘር ፖለቲካ ተወግዶ፣ ማናችንም በፈለግነው የአገሪቷ ግዛት እንደ ባለ አገር በነጻነት መኖር የምንችልበት ስርዓትና ሲስትም ስንዘረጋ ነው። የትግሬ መሬት፣ የአማራ መሬት፣ የኦሮሞ መሬት የሚለው ነገር መቆም አለበት።
አንዳንድ የአማራ ፖለቲከኞች በኦሮሞ ፖለቲከኞች ማስፈራሪያ በፍርሃት የተሸበቡ አሉ።፡ማስፈራራቱንም የኦሮሞ ፖለቲከኞች መሳሪያቸው ነው። “አዲስ አበባ ክልል ከሆነች ደም ይፈሳል፣ ኦሮሚያ ግዛት ካነሰች ፣ ሸዋ የሚል መስተዳደር ከተመሰረተ ደም መፋሰስ ነው የሚሆነው ፣ .… ወዘተ” እያሉ ማስፈራራት ልማዳቸው ነው። ታዲያ እስከመቼስ እየተፈራ ይኖራል ??? እስከመቼስ የኦሮሞ ፖለቲከኞን የመለመንና የመለማመጥ አባዜ ይቀጥላል ??? እስካሁን አንዴ ኦሮሞራ እያሉ አንዴ ሌላ እየተባለ እኮ ብዙ ተሞከረ። የአማራ ፖለቲከኞች የኦሮሞ ፖለቲከኞችን አምነው እኮ አራት ኪሎ ሁሉ ተሸክመው አስገብተዋቸዋል። ኦህዴድን ማገዙ፣ መለማመጡ ለአማራ ምን ተረፈለት ? የተረፈለት ጄኒሳይድና እልቂት አይደለምን ?
አሁንም እላለሁ ከዘር ፖለቲካ እንወጣ ዘንድ ግፊት፣ ግፉት፣ ግፊት እናድርግ። ጎጠኛ ፖለቲከኞች አምቢ ብለው ከዘር ፖለቲካ መውጣት ካልተቻለ፣ ጨዋታው የዘር ነው ነውና አማራው ከመቼውም ጊዜ በላይ የበለጠ መደራጀት፣ መጠናከር መታጠቅ አለበት። ዉህድ ኢትዮጵያዊዉን ከአማራ ጎን መሰለፉ ነው የሚበጀው። ለምን ወደደም ጠላ አማራ ተብሎ ስለሚመደብ።