December 10, 2021
39 mins read

ክተቱን ክተትበት!  በውጭ አገር የምትኖረው ኢትዮጵያዊ ሆይ እቤትህ ድረስ የመጣውን ዕድል ተጠቀምበት!

261984146 921551718797525 8148190223670528541 nታህሳስ 1 ቀን 2014ዓም(10-12-2021)

የኢትዮጵያው ጠ/ሚኒስቴር፣የኦህዴዱ መሪ አብይ አህመድ  ዲያስፖራ  አንድ ሚሊዮን ሆነህ ለታህሳስ 29 ቀን 2014 (07-01 2022) አገርህ ግባ ያለውን የክተት ጥሪ እንደ መልካም ዕድል ቆጥረህ የድጋፍ ክተቱን ጥሪ ሕዝባዊ ትግልህን ክተትበት  የሚለው ምክሬ የዛሬው ጽሁፌ መንደርደሪያ ነው።

በቅድሚያ ግን እኔ ዲያስፖራ ብዬ አልጠራህም፤እኔም አንዱ ስለሆንኩኝ ስያሜው አይጥመኝም፤አልቀበለውምም።ምክንያቱን ከታሪካዊ ትርጉሙ በመነሳት ላቀርብ እወዳለሁ።ዲያስፖራ(Diaspora) የሚለው ቃል ከግሪክ የተወረሰ ሲሆን ትርጉሙ የተበተነ፣አገረቢስ ሕዝብ ማለት ነው። አመጣጡም በስድስተኛው ክፍለዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት (ዓመተዓለም) የዬሩሳሌምን መውደም ተከትሎ ነዋሪው በያቅጣጫው  ሲበተን፣እግሩ እንዳደረሰው በከባቢ አገራት ሲሰደድ፣ለፈረኦናውያን ባርያ ሆኖ  ምንም የአገር ባለቤት ሳይሆን ለኖረው ሕዝብ የተሰጠ ስያሜ መሆኑን ታሪክ ያረጋግጣል።የዚህ ተጓዳኝ የሆነው  ደስፖራዶ(Desporado) የሚለው የላቲን ቃል ደግሞ ተስፋ ቢስ፣ግራ የተጋባ፣ወንበዴ፣ሽፍታ፣ገዳይና ቀማኛ፣ሃብት ፈላጊ በማለት ሲገልጸው አድራጎቱንም ከአሜሪካኖች  ከ1607-1920 የነበረውን የወረራና የወርቅ ፍለጋ ታሪክ  ዌስት ዋይልድ ዌስት(West wild West) የሚለው የፊልም ተውኔት ተቀርጾበታል።ይህን የመሰለው ታሪክ በተመሳሳይ ዘመን በተግባር በአገራችን ኢትዮጵያ በኦሮሞ ጎሳ እንደተካሄደ በታሪክ ሊቆች በሆኑት በአለቃ ታዬና በአቶ ይልማ ድሬሳ እንዲሁም በሌሎቹ ምሁራን በሰፊው ተገልጿል። በቅርቡም ከኦነግና የወያኔ የመስፋፋት እቅድ ወረራ ጋር ይመሳሰላል፤ስለሆነም ደስፖራዶ የሚለው ስያሜ ለነዚህ ወራሪዎች ተገቢና ተስማሚ ነው እላለሁ።

ያም ሆነ ይህ ግን ዲያስፖራ(Diaspora) የሚለው ስያሜ የአገር ባለቤት ለሆነው ኢትዮጵያዊ የሚስማማ  አይደለም።እኛ ኢትዮጵያውያን አገር አለን፤ያጣነው በአገራችን በነጻነትና በእኩልነት የመኖር መብትን የሚያረጋግጥና የሚያስከብር መንግሥትና ሥርዓት ነው። ከዘጠና  በመቶ(90%) ያላነሰው  አገሩን ጠልቶና ክዶ የሚኖር አይደለም።ጥቂቶች ሊኖሩ ይችላሉ።እነሱም በውስጥና በውጭ ኢትዮጵያዊ አይደለንም ብለው በባዕዳን እዬታገዙ አገር ለማፍረስ የሚቅበዘበዙት ከሃዲዎች ብቻ ናቸው።አብዛኛው ስደተኛ ቢሆንም በትዳር፣በትምህርትና በሥራ ምክንያት ከአገሩ ወጥቶ የሚኖረውና የአገሩን ፓስፖርት የያዘው ጥቂት አይደለም።ስደተኛውም ቢሆን በመኖር ምክንያት የሚኖርበት አገር ዜግነት ያለው ነው።ስለሆነም አገረ ቢስ ዲያስፖራ ተብሎ ሊጠራ አይገባም፤አይደለምም።ይህንን ስያሜ ሹመትና ሽልማት መስሎት የሚኩራራ ካለ ተሳስቷል።የሚያኮራው በትውልድ አገር፣በዘር ግንዱ መታወቁ ነው።በያለህበት አገር የምትታወቀው በመጣህበት አገር ስለሆነ ዲያስፖራ(Diaspora) የሚለውን ስያሜ አትቀበለው።የኢትዮጵያን ታሪክና ህልውና ብሎም ያንተን ትስስር ለመበጠስና ለማደብዘዝ ታስቦ የተሰራ ሴራ መሆኑን ተረዳ።ይህንን ጉዳይ ለታሪክ ባለሙያዎች በመተው ለጽሁፌ መነሻ ወደሆነው ዋናው ቁም ነገር አመራለሁ።

ሰሞኑን የኦህዴድ/ብልጽግና መሪ አብይ አህመድ አንድ ሚሊዮን “ዲያስፖራ” በታህሳስ 29 ቀን 2014(07-01 2022)አገሩ እንዲገባ ጥሪ አድርጓል።(አሁንም የሱን ቃል ለመጠቀም  እንጂ እኔ ዲያስፖራ የሚለውን ስያሜ ተቀብዬ ለማስተጋባት እንዳልሆነ ይታወቅልኝ።)ይህንን ጥሪም በመስማት ብዙ ሰው ለመሄድ ሽርጉድ እያለ መሆኑ ይስተዋላል።በእርግጥ ስንቱ ጥሪውን አክብሮ በቦታው ላይ እንደሚገኝ ባይታወቅም የሚሄድ አይጠፋም።

የመንግሥት በተለይም የአብይ አህመድ ጥሪ በዋናነት ለእርሱ መንግሥት ድጋፍና እውቅና ብሎም ለገጠመው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ማካካሻ ይሆናል ከሚል ግምት እንደሆነ ለማወቅ ነብይ መሆን አይጠይቅም።ለመሳቢያ እንዲሆን የአዬር ትኬትና የሆቴሎች ክፍያ ቅናሽ እንደሚደረግም ይፋ ሆኗል።እዚህ ላይ ለአገር ጥቅም ቢሆን የመደበኛ ክፍያውም እጥፍ ቢከፈል አይቆጭም ነበር፤ግን ነገሩ ወዲህ ነው።አዬር መንገዱ በጥቂት መንገደኞች ብቻ በባዶ በመብረሩ ለሚያስከትለው ኪሳራ በግማሽ ዋጋም ቢሆን  ሌላው ቢቀር የነዳጅ ወጭውን ሊቀንስለት ይችላል።ሆቴሎቹም ቢሆኑ በቱሪስት እጥረት ገቢያቸው ቀንሶ ብዙ ሠራተኞቻቸውን ለማባረር ስለተገደዱ በግማሽም ክፍያ ቢሆን ለቀሩት ሠራተኞች ገቢ መፈለጉ አማራጭ የሌለው ምርጫ ነው።

ብንታደልማ ኖሮ ፣የዱሮው የኢትዮጵያ አዬር መንገድ ቢሆንማ ኖሮ፣ለአገር ጥቅምም ቢሆን ኖሮ እጥፍም ከፍለን ብንጓጓዝበት ቅር አይለንም ነበር።ከሰላሳ ዓመት ወዲህ ግን አዬር መንገዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወይም መንግሥት ንብረት ነው የሚለው እይታ እዬኮሰሰ በመሄዱ አንዳንዶቹም ለምልክት የቀረው ጅራቱ ላይ የሚታዬው አረንጓዴ ቢጫና ቀይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ምልክት ብቻ ነው እስከማለት ደርሰዋል።ያንንም እንደሚከተለው ያብራሩታል።

ለሃያ ሰባት ዓመት ወያኔ በራሱ አመራርና ቁጥጥር ሥር አድርጎት ገቢውን ሲመጠምጠው ኖረ።ከሦስት ዓመት ወዲህም ኦህዴድ ነጥቆ የራሱ የገቢ ምንጭ አደረገው።በፈረቃ የተቀባበሉትን የአዬር መንገዱን አመራር አባላት መተካካትና በጎሳ ተዋረድ የቅጥር ስርዓቱን መመልከት በቂ ነው።የደፋሩና ሃቀኛው የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ  የፍትህ መጽሔት  በተከታታይ ያቀረበውና በኢትዮ 360 ስርጭት በጋዜጠኛ ብሩክ ይባስ የተነበበው ዘገባ የሻጥሩን ውስጠ ምስጢር ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።የወያኔው አንዱ መሪ  ሰዬ አብርሃ ተነስቶ የኦህዴዱ አባዱላ ገመዳ የአዬር መንገዱ የቦርድ ሰብሳቢ የመሆኑ ቅብብሎሽ ምስጢሩንና አሻጥሩን ፍንትው አድርጎ ያሳያል።በዚያ ላይ ደግሞ “አባ ዱላ አባ ብላ” በሚለው ጽሁፉ የስካይ ላይን ሆቴልን  ጭምር አሻጥር ስትሰማ ዓይነጥላህ ይገፈፍና እውነቱን ትረዳዋለህ።የእሰዬም ሆነ የአባዱላ መተካካት ለምን ይመስልሃል? ለአዬር መንገዱ ታስቦ በአዬር መንገድ ተቋምና አሠራር ልምድና ዕውቀት ያላቸው በመሆናቸው ከመሰለህ ተሸውደሃል።ሁለቱም እንኳንስ ስለአዬር መንገድ ተቋም ይቅርና ስለሚያመላልሰውም ጭነትና ሻንጣ እውቀት የላቸውም።ለዚያ ቦታ ያበቃቸው ለድርጅታቸው ያላቸው ታማኝነትና ላበረከቱት አገልግሎት ውለታ ብሎም ደፋር ሌቦች ስለሆኑ ብቻ ነው።ታዲያ አዝማሚያውን ሲያዩት በኢትዮጵያ አዬር መንገድ መጓዙን ለአገር እድገትና ጥቅም የሚውል እርዳታ አድርጎ ከማዬት በሥልጣን ላይ ያሉ ቡድኖች የሚመዘብሩት ብሎም ሁኔታው ከቀጠለ በባለቤትነት የሚወርሱት ወይም ሸጠው የሚከፋፈሉት ድርጅት ሊሆን እንደሚችል ማሰቡ ብልህነት ነው።አይሆንምን ትተሽ ይሆናልን አስቢ፣ወይም ያልጠረጠረ ተመነጠረ ነው።ይህ ያቀዱት ዓላማ እንዳይሳካና አገርም እንዳትፈርስ ሁሉም አገር ወዳድ ተባብሮ ሕዝባዊ ትግሉን መቀላቀል አለበት። ለዚያም ይህ የክተት ጥሪ እውጭ ለሚኖረው አገር ወዳድ መልካም አጋጣሚ ነው።

በጥሪው መሠረት አገር ቤት መግባቱና ከዘመድ አዝማድ እንዲሁም ከወገን ጋር መገናኘቱ፣ብሎም በዚህ ክፉ ወቅት አገርና ሕዝብ በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ በአካል ማዬቱ የሚደገፍ እርምጃ ነው። በዋናነት መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ በውጭ አገር የሚኖረው ኢትዮጵያዊ በሚኖርበት አገር ለዓመታት ብርዱን፣ሃሩሩንና የቦታ እርቀቱን ተቋቁሞ በየከተማው አደባባይ ተሰልፎ ስለአገሩ ክብርና አንድነት፣ ስለወገኑም ስቃይና መከራ ድምጹን ሲያሰማ፣ሲታገል፣ገንዘቡን፣እውቀቱንና ጊዜውን ሲያፈስ መኖሩ የሚካድ አይደለም።የታገለው ለአገሩ አንድነት፣ለዴሞክራሲ ሥርዓት መስፈንና ለሰብአዊ መብት መከበር ነው።ያንንም እስከዛሬዋ እለት እያከናወነው ይገኛል።ይህንን ትግሉን በቀረበለት ጥሪ መሰረት እሩቅ ሆኖ ከማካሄድ በአገሩ መሬትና በወገኑ መሃል ሆኖ ሊያካሂደው ዕድል ሰጥቶታል።የመንግሥት ባለሥልጣኖች ወይም አብይ አህመድ እንደሚያስበው ለነሱ የሥልጣንና  በትረ መንግሥት ዕድሜ የሚያራዝም የድጋፍ ድምጽ እንዳይሆን ማድረግ ይጠበቅበታል።

ጥሪውን ተከትሎ የሥርዓቱ ደጋፊዎችም ሊገቡ ይችላሉ።ለእነሱ ጥሪው አስረሽ ምችው ፌስታና ደስታ ነው።እንኳንስ በአገር ቤት ካሉት መሰሎቻቸው ጋር ተገናኝተው፣በመንግሥት ድጋፍ አደባባይ ወጥተው ይቅርና የዴሞክራሲን ትርጉም በሚያዩበትና በሚያውቁት ብሎም በሚጠቀሙበት አገርም ውስጥ ሆነው ባገራቸው ያለውን ኢዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከመደገፍ አልቦዘኑም።የዴሞክራሲንና የሰብአዊ መብትን ጥያቄ ብሎም የአገር አንድነትንና ልዑላዊነትን ጉዳይ ለቁራሽ መሬት፣ቤትና ጥቅም አሳልፈው ሸጠዋል።ጥያቄው ግን እውነት እንደሚያስቡት የንብረቱ ባለቤት ሆነው ይዘልቃሉ? የሚለው ነው።መልሱ በጭራሽ ነው። እንኳንስ የተሸለሙት ቀርቶ በአንጡራ ገንዘባቸው የገዙትም ቤትና ንብረት ላለመነጠቃቸው፣ወይም ላለመውደሙ ዋስትና የለም።የጊዜ ጉዳይ ነው፤ ጎሰኛው ቡድን ከተጠቀመባቸው በዃላ እንደ አገዳ መጦ ይጥላቸዋል።እነዚሁ አሽቃባጮች ለሚያደርጉት ድጋፍ ይሉኝታ የላቸውም።አብይ አህመድ ከሰው የተለዬ መለኮታዊ ፍጡር ነው ከማለት ላይ ደርሰዋል፤ያም ብቻ አይደለም  ነብያት ነን የሚሉት የፕሮስቴስታንት  አውደልዳይ ጉዶች በአድዋ ጦርነት ጊዜ በጦር ሜዳው ነጭ ፈረስ ላይ ተቀምጦ የታዬው የአብይ መንፈስ ነው፣አሁን በአካል ቢገለጽም ቀድሞ በመንፈስ ተገልጿል ከማለት አልተመለሱም። የሙስሊሙም እምነት መሪ የሆኑት ሃጂ ሙፍታህ በሽህ ዓመት አንድ ጊዜ ብቅ የሚል መሪ ሲሉ ከነብዩ ሞሃመድ ጋር ጠጋ ጠጋ አድርገውታል። የኦርቶዶክስ መሪዎችም የአብይ ስም በመጥፎ ሲነሳ የሚያንቀጠቅጣቸውና ለውግዘት የሚሽቀዳደሙት ጥቂቶች አይደሉም። አብይ አህመድም ይችን ከፍ ከፍ ስለሚወዳት አበጃችሁ ጨማምሩባት  ይላል እንጂ ለምን ያልሆንኩትን ታደርጉኛላችሁ፣አደብ ግዙ አይላቸውም።በጣም የሚያሳዝነው ግን አብይ አህመድ በሚመራው ድርጅት በኦሕዴድ ግዛት የክርስቲያንና የሙስሊም እምነት ተቋማት ሲወድሙና ምዕመናኑ በግፍ ሲታረዱ በሽህ የሚቆጠረው የክልሉ ጦር ንጹሃንን ለማዳን ትዕዛዝ አለማግኘቱ ብቻ ሳይሆን የወንጀሉ ተባባሪ መሆኑ ነው።ይህ ከምን ሂሳብ እንደሆነ  በሂደት ይታያል።

ሌላው በጣም የሚያሳዝነውና የሚያበሳጨው ድርጊት የሥርዓቱ ሰለባ በሆነው በአማራው ማህበረሰብ ስም ለክብሩና ለማንነቱ መስዋዕት የሆኑትን፣ለኢትዮጵያ ነጻነትና አንድነት የደከሙትን፣የጎሳ በሽታ ካልነካካቸው መሪዎች ከቴዎድሮስ፣ከምኒልክና ከጣይቱ ፎቶ ግራፎች በላይ በጎሳ ፖለቲካ አገር ለመበታተን የተዘጋጀውን ሕገ ጥፋት አንግቦ ለአማራው ስቃይ፣መገደል፣መፈናቀል፣ለአገሪቱም መበታተን አደጋ የሆነውን  ስርዓት መሪ የአብይን ፎቶ ግራፍ በእጥፍ ዋጋ በጨረታ መሸጡና መግዛቱ  አንዱ ሲሆን ሌላው ደግሞ በቆረቆረችው ከተማዋ ሃውልቷ አይቆምም ብላ የወሰነችውን የኦሮሙማ ከንቲባ አዳነች አበቤን በዬሰልፉ ቦታ  ጣይቱ ብጡል እያለ በሙገሳ አፉን የሚከፍተውን ስትሰማ የአድር ባይነቱ ጥግ የት ላይ እንደደረሰ ታውቃለህ።

ተጓዡ አገር ወዳድ ሆይ! ይህንን ብሔራዊ ዘመቻ የመንግሥት ደጋፊዎች እንደሚያስቡትና እንደሚያደርጉት የአስረሽ ምችው፣የሆያ ሆዬና እሸሸ ገዳሜ እንዳታደርገው የታሪክ አደራ አለብህ።በወያኔ ዘመነ መንግሥት በኢትዮጵያ ዘመን (ሚሌኒዬም)መለወጫ ጊዜ አገር ወዳዱ የተስፋ ስንቅ ሰንቆ አገር መግባቱን ወያኔ እንደተጠቀመበት አይዘነጋም፤አሁንም የኦህዴድ መራሹ የወያኔ ስልጡን ስብስብ እንዳይጠቀምብህ ካለፈው ተማር።ሲሆን ከአርባ አምስት ዓመት በፊት በእድገት በሕብረት ዘመቻ ወቅት የተደረገውን የአንጋፋውን ትውልድ የተማሪዎች ትግል እንደ ምሳሌ ወስደህ ጊዜው የሚጠይቀውን ትግል አካሂድ። በዚያን ጊዜ ተማሪው በገጠር ተሰማርቶ የደሃ ገበሬውን ኑሮ እዬኖረ የሚያምንበትን ትግል አካሂዷል፤ከሕዝቡም ጋር አጋርነቱን አሳይቷል፣ሕዝቡንም አንቅቷል።ስለሆነም  የመንግሥት ደጋፊና አድር ባይ አደባባይ ወጥቶ የድጋፍ ጫጫታ ለማሰማት የሚያደርገውን ዝግጅት አትቀላቀል።በዋልጌዎች ቦታ አትገኝ።የራስህን ሕዝባዊ የትግል ድርሻ ለመግለጽ ወስነህ ተዘጋጅ።

ጊዜውን  እንደ ጥቂቶቹ አድርባዮች የዳንኪራና የአስረሽ ምችው ፣የከንቱ ውዳሴ እጅ መንሻ  አታድርገው።ለኢትዮጵያ ሕዝብ ስታደርግ የነበረውን ትግል በገሃድ ለማሳዬትና አጋርነትህን ለመግለጽ ተጠቀምበት እንጂ!በኢትዮጵያ ላይ በአድማ የተነሱት ምዕራባውያን ተወካዮች በሚገኙበት ኤምባሲ ደጃፍ ሁሉ ኖ ሞር! (No More!)በሚለው መልእክት ላይ እኔም ኔቨር አጌን(Nevere Again)የሚለውን ልጨምርልህና ተቀብለህ አስተጋባ።አጋርና ወዳጅ ናቸው የሚለውን የአቀባባዮችና  አባባል አትስማ። ምዕራባውያን  ጊዜ እያዩና እዬጠበቁ የሚክዱህ አሁንም አገር ለማፍረስ ከተሰለፉት ጋር ያበሩ ባላጋራዎች እንጂ አጋሮችህ አይደሉም።እነሱም ቢሆኑ ቋሚ ወዳጅና ቋሚ ጠላት የለንም፤ለጥቅማችን የቆመ ወዳጃችን፣ለአገሩ ጥቅም የቆመ ደግሞ ጠላታችን ነው ሲሉ በይፋ ተናግረዋል፤በተግባርም ገልጸውታል።በኢራን፣በቬኑዝዌላ በሌሎቹም አገሮች ላይ የጣሉት እቀባና ተጽእኖ ጥቅማችን ተነካ ብለው እንጂ ለአገሩ ሕዝብ አስበው አይደለም።በሚመሩበት የኔዎሊበራል ፍልስፍና ስር ልዩ ልዩ ስም እያወጡ አዲስ የኤኮኖሚ ሕግ፣ግሎባላይዜሽን፣ስትራክቸራል አድጅስትመንት—ወዘተ በሚሉ ፈሊጦች አገራትን ለዘመናዊ ብዝበዛ ያመቻቻሉ።በዚህ ፍልስፍናቸው የአገር ሃብት በጥቂቶች እጅ እዬተሰበሰበ ብዙሃኑ ለሥራ አጥነት፣ለቤት አልባነት ለድህነትና ፣ለወንጀል ይጋለጣል።የዚያ መንፈስ ተቀባይ የሆኑ የዬአገራቱ ምሁራንም ያንን ተቀብለው ያስተጋባሉ።የአገር ቋሚ ንብረቶችን ይቸበችባሉ፤በግለሰብ ነጻነት ስም የሕዝብና ያገር ንብረት ለገበያ ሸቀጥ ሆኖ ይቀርባል።ብልጽግና የተባለውም የአብይ አህመድ ትርክት የዚያ  ፍልስፍና ተከታይ ነው።ለድህነትና ለሕዝብ መበሳቆል ምክንያት ነው በማለት ሕዝባዊ ስርዓት የሆነውን  ሶሻሊዝምን ይኮንናሉ። የሶሻሊዝም ውጤት ግን በቻይናና በሌሎቹም አገሮች እዬታዬ ነው።ትልቅም ስጋት የሆነባቸው የነዚያ አገሮች እድገትና ተፈላጊነት እዬጨመረ መምጣቱ ነው።ስለሆነም በራስህ ብቻ ተማመን።ያገርህ ባለቤት አንተ እንጂ እነሱ እንዳልሆኑ፣ሊያሽከረክሩህና ሊወስኑልህ እንደማይችሉ ንገራቸው።ያንንም በአደባባይ አሳያቸው።ሌላው የአፍሪካ ተወላጅ በያገሩ ኢትዮጵያን ደግፎ ሲወጣ አንተ ባገርህ ልዑላዊነት ላይ  አትሽኮርመም።

በየምትኖርበት ውጭ አገር አደባባይ ስታውለበልብ  የኖረውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ሌጣ አረንጓዴ፣ቢጫና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ በባለቤቱ በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት በማውለብለብ  ለወጣቱ ትውልድ ምሳሌና አርአያ የመሆን ግዴታህን ተወጣ።በከበር ቻቻና ፣አስረሽ ምችው ከንቱ ውሎ ውስጥ ተዘፍቀህ ለትውልዱ መጥፎ ምሳሌ  አትሁን።ከትዝብትና ከታሪክ ተጠያቂነት እራስህን አድን፤ስለሆነም ጉዞህ የአርበኛ እንጂ የቱሪስት ወይም የጭፍን ደጋፊዎች  እንዳይሆን አቅደህ ተንቀሳቀስ። በውጭ አገር ትግልህ የምታስተጋባውን ጥያቄና መፈክር በወገንህ ፊት አስተጋባ።አገር አፍራሹ፣ሕዝብ አጫራሹ፣ሕገመንግሥት፣የጎሳ ፖለቲካና የከፋፍለህ ግዛ የክልል ስርዓት ይወገድ ብለህ ጩህ!ውቅያኖስ አቋርጠህ የምትሄድበት ተልዕኮ ትርጉም ያለው፣በታሪክ የሚያኮራ ሥራ ሠርተህ የምትመለስበት ይሁን። ጉዞህን ከቤተሰብህ ባሻገር የተፈናቀለውን ወገንህን የምታቋቁምበት፣የወደሙ ተቋማትን የምትገነባበት፣አገርህን ከቀጣዩ የመበታተን አደጋ ለመታደግ የሚረባረቡትን አገር ወዳድ ጀግኖችን የምታጠናክርበት የለውጥ ሃዋርያ ጉዞ አድርገው።

በከተማዎች ያለው የሆቴል አቅም ከሚገባው እንግዳ ቁጥር ጋር ስለማይመጣጠን ግፋ ቢል ከአስር ሽህ በላይ እንግዳ ለማስተናገድ ስለማይቻል ቆይታህን ከሕዝቡ ጋርና እንደ ሕዝቡ አድርገው።ሳትጠዬፍና ሳትንቅ አብረኸው ከርመህ ጉዳትና ችግሩን ተካፈል።ያለህን አካፍለው።ኪራይ ሰብሳቢዎች የዱባይን ቪላ  በቪድዮ እዬቀረጹ የሚልኩልህ መሳቢያ እውነት መስሎህ  ለዋጋው የማይመጥን ላልተሟላ ቤት ቀብድ አትክፈል።ጉዱን የምታዬው በሩን ከፍተህ ስትገባ ነው።እንኳንስ የዋና ቦታ ቀርቶ የሻወር ውሃና መስመር የሌለው “ ቪላ”ተብዬ ቤት እንደሚጠብቅህ እወቅ።ላለመሟላቱ ብዙ አሳዛኝ ትርክቶች ሊነግሩህ እንደሚችሉ ከወዲሁ አስብ። ሌብነት ሙያ ነው ተብሎ በሚታመንበት ስርዓት ውስጥ  በከተማዋ የተሰማራው ሌባና ቀማኛ ያበባ ጉንጉን ይዞ እንደማይጠብቅህ ተረዳ፣መንግሥት ይጠብቀኛል ብለህ ተስፋ አታድርግ፣ሥርዓቱ በራሱ የባለሥልጣን ቀማኛ አዘጋጅቶ ይጠብቀሃል።እንኳን ላንተ ዶላር ጭኖ ይመጣል ለምትባለው  ቀርቶ ላስቲክ ቤትም ውስጥ ለሚኖረው ደሃ ወገኑ የማይራራ ጨካኝ አረመኔ ወንበዴ እንዳለ ተረዳ።ሌባና ፖሊስ አንድ አይነት ላባ ያላቸው በአንድነት የሚዘሙ ጩልሌዎች(ወፎች) መሆናቸውን እወቅ።

ቆይታህ በአዲስ አበባ ብቻ አይሁን። በዬቦታው በመሄድም የደረሰውን ስብራት በዓይንህ እዬው። ቤት ካጣህ የምታርፍበትን ድንኳንና ስስ ፍራሽ ወይም የፒክኒክ ትጥቅህን፣የሌት ልብስህን ይዘህ ሂድ።ለሕጻናትና ለተጎዱት ወገኖችህ መጸዳጃ፣መድሃኒት፣ ደረቅ (ዱቄት) ወተት፣ኢንሹ፣አንዳንድ ደረቅ ምግብ፣ብስኩትና ቫይታሚን፣ የአንደኛ ደረጃ የሕክምና እርዳታ ቁሳቁስ፣ስሪንጅና የመሳሰሉትን፣ቅባት—ወዘተ ብትይዝ ትልቅ እርዳታ ነው።በአገር ውስጥ ስለማይገኝ ቢገኝም ውድና የተወሰነ ስለሚሆን ያለውን ችግር በመጠኑም ቢሆን ትቀርፋለህ።ያንን ማድረግ ትልቅ እርዳታ ነው።

ለመጓጓዣ፣ለመስተንግዶ፣ለእርዳታ፣ለዘመድ አዝማድ፣ለጓደኛ፣የምታወጣው ወጭ ቀላል አይደለም።ይህንን ሁሉ ግን ተቋቁመህ የምታደርገው ጉዞ ለላንቲካና ለዋል ፈሰስ፣ ለባለሥልጣኖቹ ደስታ ወይም እጅ መንሻ አታድርገው።የምትለግሰው ገንዘብ በተገቢው ቦታ መዋሉን ለመከታተል ዕድሉ ስላለህ በቀጥታ ለምታምንበት ጉዳይ አውለው። ገንዘብህን ባለሥልጣናቱ ወይም መንግሥት ለሚቆጣጠረው ካስረከብክ እሳት ውስጥ የወደቀ ቅቤ ሆኖ እንደሚቀር ተረዳ።ከላይ እንደተጠቆመው ጉዞህ ለጎሰኞች ስርዓት ዕድሜ ማራዘሚያ፣የድጋፍ ሰልፍ የምታሳይበት እንዳይሆን የሕዝብ አደራ አለብህ።በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖችህ፣ሴት ሕጻን፣አሮጊት፣ሽማግሌ፣ደሃና አካለጎደሎ በስቃይና መከራ በሚኖሩበት አገርህ ገብተህ ከመዝናናት፣ከአስረሽ ምችው፣ከቅብጠትና ልታይ ልታይ ተግባር ተቆጠብ።የደግነትና፣የጀግንነት ተምሳሌት ሆነህ ወደ ምትኖርበት አገር ተመለስ።ለትውልዱ ምሳሌ ሁን።

በልዩ ልዩ ምክንያት ለመሄድ ያልቻልከው አገር ወዳድ ሆይ! አልሄድም ብለህ ዝም አትበል።ባለህበት ሆነህ ትግልህን ቀጥል።ለወገኖችህ መቋቋሚያና ለሚያስፈልገው ሁሉ ለመጓጓዣ፣ለመሰንበቻ ልታወጣ የሚኖርብህን ወጭ ደምረህ በምታምነው መንገድ አበርክት።

በተጨማሪም መዘንጋት የሌለብህ አሁንም ትግሉ አላበቃም፤ወያኔና ተባባሪዎቹ ፣ብሎም አስተሳሰቡ ከሰፈነው የጎሳ ስርዓት ጋር ካልጠፉ ሰላምና አንድነት አይኖርም ለሁለተኛ ዙር ጦርነት የሚዘጋጁ ሃይሎች መኖራቸውን አስብ።ለምን ወታደራዊ ግንባታ እንደሚያደርጉ እራስህ ጠይቅ። ጦርነቱ አልቋል የሚሉትን አዘናጊና አሳሳቾች ወግዱ በላቸው፤አትስማ። ለእነሱ ጦርነቱ አለቀ ማለት ወያኔም አገር ገንጥሎ፣እነሱም አገር ገንጥለው፣ኢትዮጵያ ተበታትና እንድትቀር ያላቸውን ዓላማ በማሰብ ለወደፊቱ  የመደራደር ሥራቸውና ከምዕራባውያን ጋር ለመመሳጠር አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር  ያቀዱት ዘዴ እንደሆነ ተገንዘብ።አሁንም ሰው በተለይም አማራው በወለጋ፣በቤንሻንጉል፣በምዕራብና በሰሜን እዬተጨፈጨፈ ነው።የሕዝብና የአገር ንብረት እዬወደመ ነው። በአዲስ አበባና አካባቢዋ የመሬት ቅርምቱና ዘረፋው ዬት እየለሌ ሆኗል።

በገንዘብህ የሚገነባው ተቋምና የሕዝብ ቤት ዳግም ላለመውደሙ ዋስትና የሚኖረው ያለው የጎሳ ስርዓትና የአገር አፍራሾች ሴራ እስከነአካቴው ሲወገድ ብቻ ስለሆነ ያንን የሚያረጋግጥ የሥርዓት ለውጥ እንዲመጣ ከሕዝቡ ጋር ምከር፣እንዲደራጅም አበረታታው።ያ ካልሆነ ግን የሕዝብ ጭፍጨፋው፣የንብረት ዘረፋና ውድመቱ ይቀጥላል። ያ ከሆነ ደግሞ የጸጸትና የህሊና ቁስል ባለቤት ትሆናለህ።ስለሆነም ጉዞህን ውልና ትርጉም ያለው ጉዞ አድርገው።በመጨረሻም ወደምትኖርበት አገር ከመመለስህ በፊት አቅመ ደካማ፣ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን አዛውንቶች፣ከድሃ ቤተሰብ የተወለዱትን ሕጻናት ለማገዝ ፣ የርቀት ሞግዚት(Sponsor) ለመሆን ቃል ግባ።በወር 20-25 ዶላር ማለትም በቀን ሰማንያ ሳንቲም፣ በምትኖርበት አገር አንድ ስኒ ቡና የማትገዛበት  ለመላክ ወስነህ የመጀመሪያውን በአሁኑ እግርህ የዓመቱን ከ$250 ያልበለጠ በባንክ ብታስቀምጥላቸው ለተረጅዎቹ ትልቅ ስጦታ ነው።አንተም የመንፈስ ደስታ ታገኛለህ።

ስትመለስ ምግብ ነክ ኮተት አግበስብሰህ ገባያውን አታራቁተው።በምትኖርበት አገር ምግብ ተትረፍርፎ፣ሰው ጠግቦ የሚያድርበት አገር ነው።ሆኖም ግን የአገር አልባሳትን ፣በባለሙያ ልብስ ሰፊ በልክህ የተሰፋ ልብስና ጌጣጌጥ፣ በአገር ውስጥ የተመረተ ጫማ(ዳርማር፣አንበሳ፣አስኮ—) ብትገዛ ከዋጋ አንጻርም ሆነ  ከጥራት አንጻር ውጭ አገር ከምትገዛው ይሻላል።ይህ በራስ የመተማመን እርምጃ፣ከባለሙያው ተጠቃሚ ምስጋና የበለጠ በገንዘብ የማይለካ እርካታ ይሰጥሃል።አገርና ወገንን በተጨባጩ መርዳት ማለት ይህ ነው።ጊዜ ከሰጠው ባለሥልጣን ወይም መንግሥት ጋር ማሽቃበጥ አይደለም።

የአገራችን ሁኔታ በቀን ሳይሆን በዬሰዓቱ ተለዋዋጭ ስለሆነ እስከምትሔድበት ጊዜ ድረስ የሚሆነው አይታወቅም።ሁኔታው ፈቅዶልህ ከሄድክ ግን ከዚህ በላይ የተሰጡትን ምክሮች በተግባር ለመግለጽ ድፍረቱን ይስጥህ።

ጉዞህ የትግልና የድል  ይሁንልህ! በሰላምና በጤና ለቤትህ ያብቃህ!!

አገሬ አዲስ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

Go toTop