ከ3 ወር በፊት ወያኔ ጋሸናን ይዛ ወደ ጋየንት መስመር አቀናች። በሰሜን ወሎ ጎንደር ድንበር አካባቢ ያለችዋን የደብረ ዘቢጥ ከተማን ተቆጣጠረች። እጅግ በጣም ጠመዝማዛ፣ ተራራማና ስትራቴጂ ከተማ። ጎንደር እንደተገባ ደግሞ ጨጨሆ ላይ የወገን ለመመከት ተዘጋጀ። አቶ ደመቀ መኮንን በጨጨሆን ግንባር ተገኝቶ ጉብኝነት አድርጎ ነበር። ያኔ የአማራ ክልል ክተት ባወጀ ገና ወሩ ነበር።
ብዙም አልቆየም የወገን ጦር ከጨጨሆ ደብረ ዘቢጥ ላይ ጥቃት ከፈተ። ደብረ ዘቢጥ ከተማን ተቆጣጠረ። አልፎም ኮኪት ደረሰ። የተረፉት የወያኔ ታጣቂዎች ወደ ፍላቂት ሸሹ። መከላከያ ቆርጦ በመግባት ጋሸናን ተቆጣጠረ። በጣም ከፍተኛ የወያኔ ጦር በጋሸናና በኮኪት መካካል ተከበበ። ያኔ ከትግራይ ከ25 ሺህ ተጨማሪ ኃይል ተላቀ። መልሰው ጋሸናን ያዙ። ያ ብቻ አይደለም፣ ፍላቂት ካለው ጋር ተቀላቅለው እንደገና ፊታቸውን ወደ ጎንደር አዞሩ። ኮኪት አልፈው ደብረ ዘቢጥን ያዙ። ለመጀመሪያ ጊዜ ደቡብ ጎንደር ዞን ገቡ። ጨጨሆ፣ ንፋስ መውጫ፣ ጋየንት፣ ክምር ድንጋይ እያሉ ደብረ ታቦር ደጃፍ ደረሱ። የጉና ተራራን ያዙ።
የደብረ ታቦር ህዝብ፣ ፋኖ፣ ሚሊሺያ፣ የአማራ ልዩ ኃይል ከመከላከያ ጋር በመሆን ከ15 ቀን በላይ ከፍተኛ ዉጊያ በየወረዳዉ ተደረገ። በ15 ቀናት ውስጥ የወገን ጦር ከደቡብ ጎንደር ሙሉ ለሙሉ ወያኔን አጸዳ። በዚያ ብቻ አልተወሰነም፣ ከፍተኛ ዉጊያ አድርጎ የወያኔ ዋና ምሽግ የነበረችውን ደብረ ዘቢጥን መልሶ ያዘ። ወያኔዎች መሸሽ ጀመሩ። ወደ ፊት የወገን ጦር መገስገስ ጀመረ። ኮኪት፣ ፍላቂት፣ ገረገራ እያለ አርቢት ደረሰ። ከጋሸና 12 ኪሎሜትር ረቀት ላይ። ያኔ የወገን ጦር ግስጋሴህን አቁም ተባለ።
የአዲስ መንግስት ምስረታ፣ በዓላ ሲመት ወዘተ ሲባል ትኩረቱ ወደሌላ ቦታ ሆነ። ለወያኔዎች ጊዜ ተሰጣቸው። በጎንደር በኩል እንደማይሳካላቸው ስላወቁ፣ ፊታቸውን ወደ ወሎ አዞሩ። እኛ በዓላት ስናከብር እነርሱ መዘጋጀት ጀመሩ። በጋሸና 14 ኪሎሚተር ምሽጎች ሰሩ። ፈንጂዎች መቅበር ጀመሩ። ተጨማሪ ከመቶ ሺህ በላይ ወታደር ከትግራይ አምጥተው መስከረም 27 ወደ ደሴ በአምባሳል በኩል በነጓዝ አዲስ ጥቃት ክፈቱ። ወገልጤና፣ ማርዬ፣ ውጫሌ፣ ኩታበር እያሉ ደሴ ደጃፍ ደረሱ። እዚያ አላቆሙም ደብረ ሲና ፣ ሸዋ ደረሱ።
አሁን የወገን ጦር እንደገና ተንቀሳቅሶ ከፍተኛ መስዋትነት ተከፍሎ፣ ብዙ ውድመት ከተፈጸመ በኋላ ወያኔና ኦነግ የወረሩትን ብዙ ቦታዎች እያስለቀቀ ነው። ወደፊት እየገፋ ነው።፡
ትልቁ ፍርሃት አለኝ።
– ለጋሸና 12 ኪሎሚትር ቀርቶ የወገን ጦር ግስጋሴህን አቁም እንደተባለው፣ አሁንም “ቆቦን በወሎ መስመር፣ አደርቃይን በጎንደር መስመር እንዳታልፍ፣ ግስጋሴህን አቁም” የሚል ት እዛዝ የፖለቲካ አመራሩይሰጣል የሚል።
– ያኔ ትኩረቱ ከጦረነቱ ወደ በዓለ ሲመቱ እንደሆነው፣ አሁን ትኩረቱ ወያኔን ሙሉ ለሙሉ ከመደምሰስ ወደ 1 ሚሊዮን ዳያስፖራ ዝግጅት ላይ ይሆናል የሚል።
– የብልጽግና መንግስት ይሄን ሁሉ ጥፋት እንዲፈጸም ካደረጉ የሕወሃት መሪዎች ጋር ለድርድር በመቀመጥ፣ ህወሃት በትግራይ እንድትቀጥል ያደርጋል የሚል።
በድርድር የማምን ሰው ነኝ። ብዙ ሰው እየተቃወመኝም፣ ከአራት ወራት በፊት ህወሃት ብዙ ገፍታ ከመሄዷ በፊት ወራ ከያዘችው የአማራና የአፋር ቀበሌዎች ለቃ እንድትወጣና ያሉ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት እንደትዘጋጅ ግፊት ሳደርግና ባሉኝ የሜዲያ መድረኮች ሁሉ ሳስተጋባ ነበር። ነገር ግን አሁን ህወሃት ቀይ መስመር አልፋለች። የፈጸመችው ውድመት ጭፍጨፋ ከአይምሮ በላይ ነው። በመሆኑም
1ኛ ይህ የአሸባሪና ወንጀለኛ ቡድን ለፈጸመው መጠየቅ አለበት።
2ኛ ይህ ቡድን እንዲቀጥል ተደረገ ማለት ጦርነቱን ማራዘም እንጂ ጦርነቱን ማቆም ተደርጎ አይታየም። ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ይህ ቡድን ሙሉ ለሙሉ መደመሰስ አለበት።
3ኛ ይህ ቡድን እንዲቀጥል ከተደረገ በአማራውና በአፋር ማህበረሰብ ላይ የሚፈጸም ክህደት ነው።
4ኛ የህ ቡድን ከቀጠለ የትግራይ ህዝብ ሰቆቃ ይቀጥላል።
ስለዚህ ሁላችንም የመንግስት መሪዎች የሚሉንን በጭፍን እየሰማን፣ እነርሱን አምነን ፣ እያጨበጨብንላቸው መቀመጥ የለብንም። “ወያኔ ስጋት አትሆንም፣ ወያኔንን እንደ ዱቄት በትነናታል ወዘተ” ሲሉን፣ ሲዋሹን እንደነበረ አንርሳ። ሰዎቹ ያው ናቸው። አሁንም ሊዋሹን ይችላሉ። ለኛ አንድ ነገር ብለው፣ ለፈረንጆች ሌላ ነገር እየተናገሩ እንደሆነ የምናወቀው ነገር የለም።
ሰዎቹ ካለፉት ስህተቶቻቸው ሃቀኛ ሆነው ከቀጠሉ ጥሩ ነው። እሰየው ነው። ግን ባይሆኑስ ብለን መጠየቅ፣ የሚያደርጉት ሁሉ መመርመር ያስፈለጋል። በሚናገሩት ሳይሆን በሚሰሩት ስራ እንመዝናቸው።
አሁን ያለንበት ቀውስ ውስጥ መጀመሪያውኑ እንድንገባ ያደረጉንን አምነን፣ እንደገና ለመበላት ከተዘጋጀን ጥፋቱ የነርሱ ሳይሆን የኛ ነው የሚሆነው።
አበቃሁ!