መቼም አያድርስ ነው።ወላጅ እናትን ያህል በመውለድ ምጥና ጭንቅ ላይ እያለች፣ጎረቤትና ዘመድ አዝማድ ተሰብስቦ የአማላጅቷን ስም እዬጠራ ማርያም! ማርያም! እያለ ሲማጠን፣አዋላጅ ላብ አስምጧት ደፋ ቀና ስትል፣ ሁኔታው ሰርግና ምላሽ የሆነለት ሌባ ልጅ ከእናቱ መቀነት ፈትቶ ሰረቀ ሲባል ጉድና አያድርስ ነው።ጉድና አያድርስ ከማለትም ባሻገር አይቀጡ ቅጣት ይቀጣ የሚለው ብዙ እንደሚሆን አይጠረጠርም።
ማዘንና መጨነቁ እንኳን ቢቀርበት በዚያ ክፉና የጭንቅ ሰዓት አመሉን ገታ አድርጎ ቢያልፈው መልካም ነበር።ግን ሱስ ነውና የለመደው ልማድ የእናቱን ፍቅርና ደግነት አስረስቶት፣ ጭንቅና መከራዋን ዘንግቶት ሌባ ላመሉ ዳቦ ይልሳል ሆነበትና ከድሃ እናቱ መቀነት ያለችውን ልቅምቃሚ ፍራንክ ለመስረቅ መወሰኑ ህሊና ቢስነቱን ፍንትው አድርጎ ያሳያል።
በተመሳሳይ ደረጃ እናት ኢትዮጵያ በውጭ ወራሪዎችና በውስጥ ተባባሪ ባንዳዎች ተከባ፣በመኖርና ባለመኖር የሞት የሽረት ትግል እያደረገች፣አገር ወዳዱ ሕዝብም ያለ የሌለውን መሣሪያ አንግቦ፣እምቢ ለአገሬ ብሎ በዬአቅጣጫው ሲፋለም፣ኑሮዬ ትዳሬ፣ጨርቄን ማቄን ሳይል አንድ ህይወቱን ለመገበር ሲረባረብ፣የጠላትን ዱካ እዬተከተሉና ሁኔታውን በመጠቀም በአገራቸውና በሚታገለው ሕዝብ ጉዳት ላይ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የሚቅበዘበዙት በንግድ ስም የሚዘርፉ ከሃዲና እራስ ወዳዶች በምጥ ቀኗ ከናቱ መቀነት ከፈታው ባለጌ ልጅ ቢበልጡ እንጂ የሚተናነሱ አይደሉም።ለእናቱ ያልበጀ፣ለእናቱ ያላዘነ ጭንቅና መከራዋ ያልተሰማው ልጅ፣ለአገሩ ሕልውናና ለወገኑ የማያስብ ሆዳም ለማን ያዝናል ተብሎ ይታሰባል? በተለምዶ እንዲህ ያለውን ካሳደገ የገደለው ይጸድቃል ይባላል።እውነትም የገደለው ይጸድቃል።
አገር ወዳዶቹ ሃብታሙም ሆነ ደሃው ከአገር በላይ ሃብትና ኩራት፣ክብርና ጸጋ የለም ብለው ሁሉንም እርግፍ አድርገው ጦር ሜዳ ሲሰለፉ፣ለዚያ ጀግንነት ያልታደለው ለቃቃሚ ሌባ ነጋዴ ነኝ ባይ ግን የሚሠራው ሁሉ የተገላቢጦሽ ሆኗል።ባይዘምት እንኳን ለዘማቹ ስንቅና ትጥቅ ማቀበል ሲገባው ከመኖሪያ ቦታው የተፈናቀለ፣ሴት አሮጊት ሽማግሌና ህጻን፣በሽተኛና ደካማ ዜጋ ህይወቱን ለማትረፍ ሲንቀሳቀስ በጥቂት ክፍያ የሚገለገሉበትን የማመላለሻ አገልግሎት ከእጥፍ ድርብ በላይ በማሳደግ እንዲከፍሉ ማስገደድ ከወራሪው ሃይል የተለዬ በደል አይደለም።ሲሆን በነጻ አለያም በነባሩ ክፍያ ማስተናገዱ በተገባ ነበር። ሌላው የሚያሳዝነው ደግሞ ፣ለነጋዴውም ጭምር ነጻነትና ለአገሩ አንድነት ሕይወቱን ለመገበር የሚንቀሳቀሰውን የአማራ ፋኖ፣ሚሊሽያና ሕዝባዊ ጦር በመደገፍ ደጀን መሆን ሲገባው ለቅርብ እርቀት ጉዞ፣በደህናው ቀን ከአንድና ሁለት ሽህ ብር ለማይበልጠው የቀን የመኪና ኪራይ ከአርባ አምስት ሽህ ብር በላይ መጠዬቁ ይቅር የማይባል ወንጀል ብቻ ሳይሆን ሃጢያት ነው።
የያዙት የመጓጓዣ ንብረት በኖሩበት ሕዝብ ትከሻ ላይ ያገኙት ሃብት መሆኑን ቢያስቡት ኖሮ በዚህ ጭንቅ ወቅት ተጠቃሚውን ሕዝብ በመከራ ላይ መከራ እንዲያይ ባላደረጉት ነበር።በሌላውም የንግድ ዘርፍ የተሰማራው ሌባና አጭበርባሪ በተፈላጊ ቁሳቁሶች ላይ ከመጠን ያለፈ ዋጋ በመጨመር በሕዝቡ ቁስል ላይ እንጨት እዬከተተበት መሆኑ በግልጽ ታይቷል።
በተመሳሳዩም ሃብት ንብረት ያፈራበትን ቦታ የዃሊት ትቶ ቤተሰቡን ጭኖ የሚፈረጥጠውማ ነገር አይነሳ።አንዳንዱም በፍርሃትና በድንጋጤ በሚያሽከረክረው መኪና ገደል እዬገባ ምንም የማያውቁ ልጆቹን የአደጋው ሰለባ ያደረጋቸው መኖሩ ሲሰማ የሞት ምርጫ የለው፣ምነው በኖረበት ቦታ አብሮት ከኖረው ሕዝብ ጋር የመጣውን ቢቀበል ያሰኛል።ያካበተውን ሳይበላው መሞት እንዳለ ይህ አንዱ ማሳያ ነው።እንዲህ አይነቱ እራስ ወዳድ ደህና ቀን ሲመለስ መጥቼ እንደ ልማዴ ዘርፌ ሃብት አግበሰብሳለሁ የሚል ምኞት ካለው ተቀብሎ የሚያስተናግደው እንደማይኖር አውቆ እርሙን ያውጣ! እንደወጣ ቢቀር ይሻለዋል፤መመለሱም ያጠራጥራል፤ ምክንያቱም በሄደበትም ቦታ እሳት አለና ነው።
ክፉ ቀን ክፉ ስም ይሰጣል ነውና በዚህ ክፉና አስቸጋሪ ወቅት ለሰው ልጅ መመዘኛው የሚያደርገው አድራጎት ነው።ባንዳ ባንዳ ሲባል የሚኖረው በጠላት ወረራ ጊዜ ባሳዬው ተግባሩ ነው፤የአሁኑም ባንዳና አድርባይ በሚያሳዬው ተግባር የዘመናት መታወቂያ ሰሌዳ ተሸክሞ ይኖራል፤አድራጎቱም ለተተኪው ትውልድ የታሪክ መማሪያ ይሆናል።ከሱም የተዛመደ ሲያፍርበትና ሲሸማቀቅበት ይኖራል።ከዚያ ለመዳን አገርና ሕዝብን ከማይጎዳ ሥራ እርቆ መገኘት ነው።ከሕዝብ ጋር ሆኖ የመጣውን መቀበል ነው።የመጣውን መቀበል ማለት ደግሞ ጊዜ ያነሳውን ጉልበተኛና ወንጀለኛ መንግሥትም ሆነ ሥርዓት መቀበል ማለት አይደለም።ለመልካም ስርዓት፣ለሰብአዊ መብት መከበርና ለአገር ልዑላዊነት ከሚታገሉት ጋር አብሮ መታገል ማለት ነው።ትግላቸውን መቀበልና መቀላቀል ማለት ነው።በዚያ ሙያ ላይ የዋለው የታደለው ዜጋ ሲኖርም ሲሞትም የተመሰገነና የተከበረ ይሆናል።
በክፉ ቀን፣በወገን ስቃይ ለመጠቀም የሚሹ እራስ ወዳዶች በማንኛውም ጊዜ ከቅጣት አያመልጡም።የደርግን አምባ ገነን አገዛዝ ዘመን እንደምሳሌ ብንወስድ ምንም እንኳን በፍርድ ቤት ውሳኔና ሕግን የተከተለ እርምጃ ባይሆንም የነበረውን የዕቃ አቅርቦት እጥረት በመጠቀም ትርፍ ለማግበስበስ ያሰቡ ነጋዴዎችን በሞት ቅጣት መቅጣቱ ብዙዎቹን ከአድራጎቱ እንዲታቀቡ አድርጓቸዋል።በሌሎቹም አገሮች ተመሳሳይ እርምጃ ተወስዷል።በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ በተመሳሳይ ተግባር ላይ በዋሉት ላይ የዬአገሩ አርበኞቹ የጦር ሜዳ ፍርድ በይነውባቸዋል።ከዚህ አይነቱ ቅጽበታዊና ሕዝባዊ ቅጣት ለመዳን እራስን ከጥፋት ማራቅና ከሕዝቡ ጎን መቆም ነው።ዛሬ ሃብት ንብረቴ አይበልጥብኝም ብሎ ከአገር አድኑ ዘመቻ ውስጥ የገባው ባለሃብት ነገ ከድል በዃላ ያጣውን እጥፍ፣ድርብ ድርብርብ ሃብት ለማግኘት የሚያግደው አይኖርም።ከሃብቱ በላይ ግን የሚያገኘው ከበሬታና ሕዝባዊ ምስጋና ይበልጣል። ልጅና የልጅ ልጆቹም ይኮሩበታል።
በተለይም ለተፈናቀለውና ከቤቱ ለወጣው፣ከሞት ተርፎ ፣ቆስሎ በዬቦታው ተበትኖ ለሚገኘው ሕዝብ የተላከ እርዳታ እዬመዘበረ ለግል ጥቅሙ የሚያውልና የሚቸበችብ፣በተለይም ባለሥልጣን መኖሩ ሲሰማ ህብረተሰባችን የአውሬዎች ዋሻ መሆኑን ያሳያል፤ያ የአውሬዎች ዋሻ ካልተደረመሰ አውሬው አውሬውን እዬወለደ ሌብነት የሚያሳፍር ወራዳ ምግባር ሳይሆን የሚኮሩበት ሙያ ሆኖ ይቀራል።
አድርባይነትን፣ ሌብነትንና ማጭበርበርን ከአገር አጥፊው ጎሰኝነት እኩል እንታገለው!
ማሳሰቢያ ለአገር ወዳዱ በተለይም ለአማራው ማህበረሰብ
ሁለገቡ ትግላችን በተቀናጀ፣በተደራጀና፣በአንድ ወጥ አመራር ሊካሄድ ይገባዋል።ከዛሬው አገር አድን ትግል ጋር የነገው ተመሳሳይ የጠላቶቻችን ዝግጅትና ጥቃት መኖሩን አውቀን የግድ ሃይላችንን መገንባት ይኖርብናል።በአሁኑ ትግል ሃይላችን መንምኖ በዝግጅት ላይ ያሉት የኢትዮጵያ ጠላቶች እንዲያንሰራሩ ወይም በመተካካት እንዳያጠቁንና ሃሳባቸውን ከግቡ እንዳያደርሱ ነቅተን መጠበቅ አለብን።ገንዘብ ያለው በገንዘቡ ፣እውቀት ያለው በእውቀቱ፣ጉልበት ያለው በጉልበቱ የሚረባረብበት ወቅት አሁን ነው።ጎጠኝነትንና አላስፈላጊ ልዩነትን አሶግደን አገር በማዳኑ ብሎም ለኢትዮጵያዊነት ህልውና የምንቆምበት ጊዜው አሁን ነው።አገር ሳይኖር ለእራስም ሆነ ሃብትና ንብረት እንዲሁም የፖለቲካ እምነትና መስመር ቦታ የለውም።መጀመሪያ የመቀመጫዬን እንዳለችው በሰላምና በእኩልነት የምንኖርበት አገር ሊኖረን ይገባል።
አገሬ አዲስ