አልበርት አነስታይን እንደተናገራቸው የሚጠቀሱና ለአሁኒቷ ኢትዮጵያ ዜጎች ትክክለኛ መግለጫ የሆኑ ሁለት ግሩም አባባሎች አሉ፡፡
“Two things are infinite: the universe and human stupidity; and I’m not sure about the universe.”
“ሁለት ድንበር የለሽ ነገሮች አሉ፡- ዩኒቨርስና የሰው ልጅ ድድብና፡፡ ስለዩኒቨርስ ድንበር የለሽነት ግን እርግጠኛ መሆን አልችልም (ስለሰው ልጅ ድድብና እንጂ!)”
“Insanity Is Doing the Same Thing Over and Over Again and Expecting Different Results.”
“ዕብደት ማለት አንድን ነገር በተደጋጋሚ በማከናወን የተለዬ ውጤት (እንደ)መጠበቅ (ያለ ሞኝነት) ነው፡፡”
አጫጭር ምሣሌያዊና የበሳል ምሁራን አነጋገሮች ከመጻሕፍትም በላይ ናቸው፡፡ በጥቂት ቃላት ብዙ ይናገራሉ፡፡ መዘብዘብ አያስፈልጋቸውም፡፡ ዕጥር ምጥን ብለው አይረሴነት ያለው መልእክት ያስተላልፋሉ፡፡ ከፍ ሲል የተቀመጡት የአነስታይን ንግግሮችም እንደዚሁ ናቸው፡፡
በዓለማችን በተለይም በሀገራችን እየሆነ ያለው ሁሉ በአጭሩ በነዚህ ጥቅሶች ይገለጣል፡፡ ለሰው ልጅ ድድብና ወይም ድንቁርና ለከት እስከሚበጅለት ድረስ የዓለማችን ቅርጽ አሁን ባለበት ሁኔታ መጓዙ የሚጠበቅ ነው፡፡ ድድብና ሲባልም ከመማርና ካለመማር ጋር የሚገናኝ ሳይሆን በሆነ ግላዊ ዓላማና ፍላጎት ተውጦ ከእውነቱ በማፈንገጥ በቅዠት ዓለም ውስጥ መኖር ማለት ነው፡፡ እንዲያውም ብዙ ከተማሩ ሰዎች ምንም ያልተማሩ ሰዎች ተሽለውና በልጠው ቀናዎችና ለሰው ልጅ መልካም አሳቢዎች የሚሆኑበት አጋጣሚ በጣም ብዙ ነው፡፡ ተማረ የተባለው ግን ትምህርቱን በድንቁርና ስብ እያሸ ጠብደል ማይም ይሆንና አስተሳሰቡ ከአፍ እስካፍንጫው እንኳን መዝለቅ እያቃተው የመጨረሻው ሆድ አምላኩ አጋሰስ የሚሆንበትና ከእንስሳትም በእጅጉ የሚያንስበት ሁኔታ በተለይ በዘመናችን በስፋት ይስተዋላል፡፡ ይሄ ሆድ የሚሉት የሰው ልጅ ዋነኛ ጠላት ደግሞ ብዙ ሰዎችን በቁም እየገደለ ሲያበለሻሻቸው ማየት ከብርቅነት ያለፈ የክፍለ ዘመናችን ዓይነተኛ መገለጫ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ ጋዜጠኝነትንና አክቲቪስትነትን ጨምሮ የት ይደርሳሉ የተባሉ የሀገርና የወገን አለኝታዎች በትንንሽ የሥልጣንና የጥቅማ ጥቅም ወጥመዶች ውስጥ እየገቡ ለትልልቅ ባለሥልጣናት የትውከት ባልዲ አቅራቢና የቆሻሻ ማስተላለፊያ ቱቦ ሆነዋ፡፡ ከነዚህ በቁም ከጠፉብን ሰዎች አንዳንዶቹ በዕድሜ ጫናና የጠበቁት እንደጠበቁት ሳይሆን ቀርቶ በተስፋ መቁረጥ ምክንያት ወደዚህ የማይገባቸው ሥፍራ እንደሄዱ በበኩሌ ባምንም ትንሽ መታገስ ግን ነበረባቸው እላለሁ፡፡ “የማይወጣ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል” ይባላልና ሥልጣን ከያዘበት ማግሥት አንስቶ እስካሁን ድረስ ሀገራችንን የደም ጎርፍ ያደረገውንና ባልተለወጠ የዘር ፖለቲካ ቅኝት አንዱን ነገድ አባርሮ ሌላ ነገድ በመተካት በኬኛ ፖለቲካ አገር ምድሩን የሚንጠውን ሰውዬ ተከትለው መንጎዳቸው ለነሱም ሆነ ለልጅ ልጆቻቸው ደግ ታሪክ እያስቀመጡ እንዳሆነ መረዳት ነበረባቸው፡፡ ሆድ እንደሆነ እንዳደረጉት ነው፤ እኛም እየኖርን ነው፡፡ ዐይናቸውን የጋረደባቸውን የጣዖታቸውን አንደርባዊ ምትሃት እንደምንም ገፍፈው ከአሁኑም በከፋ ብዙ ሳይጨልም በቶሎ እንዲመለሱ የወንድምነቴን እመክራቸዋለሁ፡፡ በነሱ መጎዳት ማንም አያተርፍምና፡፡ ለማንኛውም ይህ የሚያልፍ ጊዜ ብዙ የማያልፍ የታሪክ ጠባሳ እያሳየን ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን እየሆነ ያለውን ነገር አለማየት ይሻላ፡፡ ይህን ጊዜ ያላዩ የታደሉ ናቸው፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ ተወልደን አሁን ይህን የእፉኝቶች ዘመን ለማየት የተገደድን ዜጎች ዕድላችን በእጅጉ ጠማማ ነው፡፡ የሞቱት ከሚኖሩት ተሻሉ፡፡ ሞት የሚናፈቅበት ዘመን፣ ወንድም በወንድሙ ላይ ሠይፉን የሚመዝበት ወቅት ላይ መገኘታችን በዘመን ፍጻሜ ላይ እንደምንገኝ አመላካች ነው፡፡
ኢትዮጵያን እየመራ ያለው ሰው በአጋንንቱ ጎራ የተመረጠ እንጂ በፈጣሪ የተሾመ እንዳ ሆነ ያለፉትን አራት ዓመታት በመቃኘት መረዳት አያቅትም፡፡ ሰውዬው የተበተበባቸው አፍዝ አደንግዝ ወይም ያቀመሳቸው ብኤልዘቡላዊ ሥጋ ወደሙ እየጠመዘዘ በርሱ ጋጣ ውስጥ የሚያንደባልላቸው እጅግ በርካታ ምሁራንና የሃይማኖት ሊቃውንት በውነቱ በጣም ያሳዝናሉ፡፡ እነሱም እኮ ወደው ላይሆን ይችላል፡፡
የሰው ልጅ ድድብናው ካላስገደደው በስተቀር “ትግሬንና አማራን አፋጅቼ፣ የትግሬንና የአማራን ሀብትና ንብረት አውድሜ የኢትዮጵያ (7ኛው) ንጉሠ ነገሥት እሆናለሁ” ብሎ ማሰብ ከጅምሩ ዕብደት ነው፡፡ በዚህ የዕብደት መንገድ አራት ዓመታትን መጓዝ አነስታይን እንዳለውና ብዙ ሥነ ቃላት እንደሚያጠናክሩት ከእባብ ዕንቁላል ዕርግብ እንደመጠበቅ ነው፡፡ በክፋት መንገድ ምንም ዓይነት ዓላማ ሊሠምር አይችልም – ለጊዜው ካልሆነ በስተቀር፡፡ ክፋትም ሆነ ደግነት ደግሞ ለራስ ናቸው፡፡ ማንም ከማንም በላይ ብልጥ ነኝ ብሎ ቢያስብ የመጨረሻው ጅል ነው፡፡ ብልጥነትም ሆነ ጅልነት የጊዜ እንጂ የአእምሮ መበላለጥ ጉዳይ ብቻም አይደለም፡፡ ነገን ታያላችሁ!! በኦሮሙማ ጽንሰ ሃሳብ ታውሮ አገር ምድሩን በኦሮሞ ማጥለቅለቅና መከላከያን፣ ፖሊስን፣ ደኅንነትን፣ አየር መንገድን፣ ባንክን፣ ኢንሹራንስን፣ ክልሎችን፣ … ሁሉንም በአክራሪና አማራ ጠል ኦሮሞ ማጨናነቅ ከድድብናና ከዕብደትም ባለፈ አዲስ ቃል የሚያስፈልገው የዘመናችን ታላቅ ክስተት ነው፡፡ የነዚህ ጅልነት ከነዚያኞቹ ብልጠት ባሰና አስደመመን፡፡ አምናና ታች አምና ዘረኞቹ ወያኔዎች በሠሩት አሳፋሪና አስነዋሪ ሥራ ዘንድሮ ምን እንደደረሰባቸው ያልተረዳ ደንቆሮ ጽንፈኛ አራት ኪሎን ስለተቆጣጠረ ብቻ የሚፏ ልበትን ኦሮሙማ እውን አድረጋለሁ ብሎ ካሰበ “ኢትዮጵያ የማይተኛ ጠባቂ አምላክ አላትና ለደደቦችና ለደናቁርት የሚሆን ጊዜ ከእንግዲህ የለም” በሉት፡፡
ተመልከቱልኝ፡፡ አንድን ሰው ማጥቃት ለጊዜው ቀላል ነው – የዞረ ድምሩ በታሳቢነት ተቀምጦ፡፡ ግን ግን 46 ሚሊዮን ሕዝብ ከነሀብት ንብረቱ አጥፍቼ ልንገሥ እንዴት ይባላል? የሚገርም ዕብደት አይደለም ይሄ? ከዚህ የበለጠ ሰይጣናዊነት ከየት ይመጣ ? ኧረ ሰይጣንም ይህን ያህል መረን የለቀቀ ድፍረትና የክፋት ሥራ የለውም!! አንዳንዴ ሊመሰገን የማይገባውም ቢሆን ማመስገን ጥሩ ነው – የሚያስመሰግነው ነገር ሲገኝ፡፡ ኦሮሙማዎች የደብረ ብርሃን ፋብሪካና ኢንዱስትሪዎች ቢቃጠሉ ምን ይጠቀማሉ? ኦሮሙማዎች የኮምቦልቻና የባህር ዳር ፋብሪካዎች ቢወድሙ ምን ያገኛሉ? ኦሮሞን አንቀጥርም አሉ? ምርቱን ወደ ፊንፊኔ ማነው ወደ አዲስ አበባ አንልክም አሉ? ምን ዓይነት ቂልነት ነው? የኦሮሞ ባለሀብት በነዚህ አካባቢዎች የለም? የትግሬ ባለሀብት በነዚህ አካባዎች የለም? የአንዱ ሀብት ለሌላው መኩሪያ መሆኑ ቀረ? ዕብደታችንክ ቢኖረው ምናለበት? ይህን ፖለቲካ የሚያራምድ ሰው ቤተ መንግሥታችንን መቆጣጠሩ በርግጥም ዕንቆቅልሽ ነው፡፡ ብሎ ብሎ በዜጎች መሀል ግርድና አመሳሶ የሚለይ መሪ ይግጠመን? በመለስ አልበቃ ብሎ በእጅጉ የተሣለ ጎራዴ ሌላ መለስ ሆኖ ይምጣብን? ወይ መረገም!! ያቺ ባሏን የጎዳች መስሏት ሰውነቷን በጋሬጣ የወጋችው ሴት ምን አተረፈች? ልክ እንደርሷ እኮ እየሆን ነው፡፡ ሃይማኖተኛ ነኝ ባዩ ሳይቀር በዘርና በእምነት ተቋማት ተከፋፍሎ ከፈጣሪ የእውነት መንገድ ሲወጣ ምን ይባላል? ሰሞኑን የኦሮሙማ ጴንጤዎች በዶክተር ደረጀ ከበደ ላይ የሚያደርጉትን የማጥላላት ዘመቻ አያችሁ አይደል? የሚገርም የታሪክ አንጓ ላይ ነን በውነቱ፡፡ አንዳንዶቻችን ማፈሪያ የሰውነት ክፍላችንን ሳንነጠቅ አንቀርም፡፡ ዶክተሩ መግደል ይቅር ብሎ የክርስቶስን ቃል በመስበኩ የሚወርድበትን ዱላ ተመልከቱልኝማ፡፡ ዛሬ የሚፈለገው “አማራን ቀጥቅጠው! ኢትዮጵያን በታትናት!” የሚል ቅኝት ያለው ዜማ ብቻ ነው፡፡ ቤታችሁን ዘግታችሁ የምትታዘቡ እባካችሁን ይህን ሁሉ ጉድ እየመዘገባችሁ ለታሪክ አኑሩ፡፡
በመጨረሻ ግን ይህ ዕብደት እንደማይቀጥል መረዳት እንደሚገባን ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ትንሣኤዋ ቅርብ ነው፡፡ ምንም እንኳን እጅግ ብዙ ነገሮች ተስፋ አስቆራጭ ቢመስሉም ክፉን ካላዩት ደግ አይገኝምና የሀገራችን ነፃነት የማይቀርና በደጅ ቆሞ እያንኳኳ የሚገኝ በጉጉትም የምንጠብቀው የመገፋታችን በረከት ነው፡፡ ይብላኝ በሰው ደም እየታጠቡ ላሉ፡፡ ይብላኝ ለዚህች የማትረባ ምድራዊ ሥልጣንና ሀብት ብለው ወገናቸውን እያረዱና እያሳረዱ ላሉ የጨለማው መንግሥት አባላት፡፡ ይብላኝ በወለጋና በሸዋ፣ በወሎና በትግራይ ንጹሓን ወገኖቻችንን እርስ በርስ እያባሉና በሤራ ፖለቲካ በሀገርና በሕዝብ ላይ እሳት እያዘነቡ ለሚገኙ የእፉኝት ልጆች፡፡ ይብላኝ ለዚህ ሁሉ ጥፋትና ውድመት ዋና መሃንዲስ ሆነው ላለፉት 50 ገደማ ዓመታት ከጠላቶቿ ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ለሞከሩ ሰሜነኛ ወንድሞቼና እህቶቼ፡፡ ይብላኝ የአሜሪካ መንግሥትን ለመሰሉ የጨለማው መንግሥት ዋና ምድራዊ አምባሳደሮችና ወኪሎቻቸው፡፡ ኢትዮጵያስ ትነሳለች፡፡ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን በምሕረት እጆቹ ይዳብሳታል፡፡ “ዶፉን ያቅልልን፤ ለተወናበዱና ለካዱን ልቦናቸውን ይመልስልን፡፡” ብለን ይልቁንስ እንጸልይ፤ ሙስሊሙም ዱኣውን ያድርግ፡፡ …ግን ግን ይህንንም ጨምሮ ሁሉም ያልፋል፡፡