ለኢሳትና መሰል ሚዲያዎች ማስጠንቀቂያ – – ሰርፀ ደስታ

ኢሳት የተባለው ሚዲያ በተደጋጋሚ የመንግስት ባለሥልጣናትን በተለይም ደግሞ ከፍተኛ የሆኑ የጦር አመራሮችን ቃለመጠይቅ በሚል በአደባባይ ሲያውል ታዝበናል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ባለሥልጣናቶቹም ቢሆኑ ያሉበትን የኃላፊነት ከግንዛቤ በመውሰድ በልዩ ሁኔታ አስፈላጊ ብቻ ሆኖ ሲገኝ በራሳቸው ተዘጋጅተው ለሁሉም ሚዲያዎች በይፋ መሥጠት ከሚገባቸው መግለጫ ወይም አስፈላጊ ንግግር በቀር ማንም ከእነሱ ጋር በአንድም ይሁን በሌላ ትውውቅ ያለው ሁሉ በተናጥል ለቃለ መጠይቅ ሲጋብዛቸው ፍቃደኛ መሆናቸው በራሱ ስህተት ብቻም ሳይሆን አደገኛም ነው፡፡ በተለይ ደግሞ የአገር መከላከያ ባለስልጣናት ቦታው ከሚጠይቀው የደህንነት ፕሮቶኮል አንጻር በመንግስት ወይም በተቋሙ ከሚያዝላቸው መድረክ ውጭ በየትኛውም መልኩ ቃለመጠይቅ ባያደርጉ እላለሁ፡፡ በተለይ ደግሞ ዛሬ አገራችን በዚህ ከፍተኛ የሆነ የደህንነት ችግር በገጠማት ጊዜ ማንም ስልክ ደውሎ ሊያገኛቸው የሚችል የመከላከያው በየትኛውም ደረጃ የሆኑ መሪዎች ሊኖሩ አይገባም፡፡

ኢሳት በተደጋጋሚ እንደሚያድረገው ዛሬም ሊያውም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሕግ ከተፈቀደለት አካል ውጭ መረጃ በተከለከለበት ወቅት የመከላከያውን የታማጆር ሹሙን በስልክ ቃለመጠይቅ ሲያደርግ አይተናል፡፡ ያ ብቻም ሳይሆን ኢሳት ጀነራሉን ሲጠይቃቸው የነበረው ጥያቄም በእርግጥም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተፈቀደለት አካል ውጭ መረጃ መስጠት የተከለከለባቸውን ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ጠላት እንዲህ ያለውን ቃለመጠይቅ እንዴት እንደሚጠቀምበት እናውቃለን፡፡ ጉዳዩ ለተራው ሰው ጆሮ እንደሚሰማው ሳይሆን ከደህንነት አንጻር ሊመነዘሩና ጠላት ሊጠቀምባቸው የሚችሉ ብዙ እድሎችን ይሰጣል፡፡ ምንም አይነት መረጃ ግን የማይወጣ ከሆነ ጠላት ይጨነቃል፡፡ ኢሳት በተለይም ደግሞ መሳይ መኮንን የተባለው ጋዘጠኛ በተደጋጋሚ ከባለስልጣን ጋር የሚያደርገው ግንኙነት አደገኛ እንደሆነ አስተውሉ፡፡ ማንኛውም ባለስልጣን በራሱ ተዘጋጅቶ በመግለጫ መልክ ወይመ በሌላ ከመንግስት ወይም የራሱ ተቋም ውሳኔ ከሚያስተላልፋቸው መልዕክቶች ውጭ በየትኛውም በግብዣ ከሚቀርብለት ቃለመጠይቅ መታቀብ ግድ የሚልበት ወቅት ላይ ነን፡፡ ይህ ሚዲያ በዚሁ መሳይ በተባለው ጋዜጠኛ በቅርቡ በቤተክህነት በታሪካዊ ቅርስነት የተመዘገበን 1800 ጥይት በተሳሳተ መልኩ የአዲስ አበባን ከንቲባ አዳነች አቤቤን በማነጋገር ከንቲባዋ በስሜተኝነት ከሆነም ተሳስተው ብዙ ውዝግብ እንዳስነሳ እናስታውሳለን፡፡ እንዲህ ያሉ ቃለመጠይቆች ዝግጅትም ስለሚያንሳቸው ተጠያቂዎች በስሜትም ይሁን በሌላ ሊሳሳቱባቸውም ይችላሉና፡፡ ሆኖም የእነሱ መሳሳት ሳያንስ ለጠላትም ወሳኝ የሆነ መረጃን ያስተላልፋሉና፡፡ ኢሳት በተለይም ደግሞ መሳይ መኮንን በየትኛውም ሁኔታ ታማኝ ሆኖ በዚህ ወቅት ባለስልጣናትን ሊያናግር የሚችልበት አንዳችም አሰራር ሊኖር ባልተገባው ነበር፡፡ ሆኖም በተደጋጋሚ እናያለንና ሀይ ሊባል ግድ ነው፡፡ የሀገር ሚስጢር የዩቲዩበት ሸቀጥ ሊሆን አይገባም፡፡ ባለስልጣናቱም የተቀመጡበትን ቦታ አስበው ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ብአዴናዊነት (ከበሃይሉ ምኒልክ)

በተመሳሳይ በቅርቡ ራሱን የአባይ ንጉስ እያለ የሚጠራው የኡስታዝ ጀማል ዩቲዩብ የኢትዮጵያ መከላከያን የአየር ኃይል ቤዝ በይፋና በግልጽ በፊልም በመቅረጽ በዩቲዩብ ለቆት ተመልክቻለሁ፡፡ ቪዲዮው ለጥቂት ደቂቃዎች ዩቲዩብ ላይ ከዋለ በኋላ ተነስቷል፡፡ በጣም አሳዛኝና አሳፋሪ የሆነ ድርጊት ነው፡፡ ሲጀምር የአየር ኃይልን የሚያህል ቦታ እንኳንስ ማንም ተራ ዩቲውበር ቀርቶ የትኛውም ባለስልጣን እንኳን የሥራ ባሕሪያቸው ከሚፈቅድላቸው በቀር ሊጎበኝ ሊፈቀድለት ባልተገባ ነበር፡፡ አሳዛኙ ነገር በዚህ ጉብኝት ወቅት ከአስጎብኚዎቹ አንዱም ዋናው የአየር ኃይሉ አዛዥ መሆናቸው ነው፡፡ እንግዲህ ለጎብኚዎቹ በዩቲዩብ ከለቀቁትና በጨረፍታም ቢሆን ከአየንው ቪዲዮ በተጨማሪ ምን ሚስጢር እንዲያዩ እደተደረጉ አናውቅም፡፡ ዛሬ በተለይም አየር ኃይሉ ምን ዓይነት አውሮፕላኖችና መሣሪያዎች እንዳሉት ለማወቅ ብዙዎች ከፍተኛ ዋጋ ሊከፍሉ በሚችልበት በዚህ ወቅት ይህን ሳይ ከፍተኛ የሆነ ሀዘን ነው የተሰማኝ፡፡ በጎብኚ ሥም እንዲህ ያለውን ቦታ ለማየት እድል የተሰጣቸው ምን አልባትም በሚሊየን ዶላር የሚያስቆጥር ዋጋ ያለውን መረጃ የማውጣትና ለጠላት የመሸጥ ከፍተኛ የሆነ እድል አላቸው፡፡ ዛሬ እንደ ግብጽ ያሉ ጠላቶቻችን ከሚፈልጉት መረጃ ዋነኛው የኢትዮጵያ አየር ኃይል የታጠቃቸውን አውሮፕላኖችና መሳሪያዎች እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ይሄ ቢዲዮ በተለቀቀ በሁለተኛው ቀን ስለ ኢትዮጵያ አየር ኃይል ዝርዝር የሚናገር ጽሁፍም ማንበብ ችያለሁ፡፡ እንግዲህ እንዲህ ባለ የደህንነት ንዝላልነት ወይም ሆን ተብሎ የሚሰራ ሴራ የአገር ደህንነት አደጋ ላይ እየወደቀ ጠላት እድል የማያገኘው እንዴት ነው? ለማንኛውም ሁሉም ያስብበት፡፡ ሁላችንም የአገራችንን ደህንነት አደጋ ላይ እየጣሉ ያሉ ድርጊቶችን ማውገዝ ይገባናል፡፡ ባለስልጣናቱም ከእንዲህ ያል ፕሮቶኮል ካልጠበቀ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ እላለሁ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በለው! ቄንጠኛ ዳንስ በዕንባ ሲደንስ

በመጨረሻም ወያኔ በየቦታው ግብዓተ መሬቱ እየተፈጸመ ቢሆንም አሁንም ቢሆን መዘናጋት እንዳይኖር ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ በተለይም ደግሞ በሰሜን ሸዋና ምንአልባትም በሌላ አቅጣጫም ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡ እነ አሜሪካ በየቀኑ ዜጎቻቸውን ውጡ እያሉ የሚለፈልፉበትን ሁኔታ እንደተራ ነገር መቁጠር ትክክል አደለም፡፡ አሜሪካ በግልጽ የወያኔ የጦር አማካሪና ንድፍ ሰጭ እንደሆነች አያየን ነው፡፡ ከወዳጆቻቸው ከኢትዮጵያ ጠላቶች የሚያገኙት መረጃም ሊኖራቸው ይችላል፡፡ የሳተላየት ወይም ሌላ መረጃም ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ለዚህ መድሀኒቱ ወያኔን የገባበት እየገቡ ቢያንስ ከሰሜን ሸዋና አካባቢው ማጽዳት ነው፡፡ የወያኔና አጋሮቿ እቅድ እንደምንም ብሎ የቦሌ አውሮፕላን ጣቢያ በረራን ማስቆም ነው፡፡ ይሄም በቅርብ እርቀት ከባድ መሣሪያ መበጥመድ አውሮፕላን እንዳይነሳና እዳያርፍ ማድረግ ነው፡፡ ይሄን ከግንዛቤ ወስዶ ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡ ብዙ ሰራዊት ሳይሆን ከባድ መሳሪያና የተወሰኑ ሰዎችን ሰርጎ በማስገባት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ እንታዘባለን፡፡ እየተሸነፈና እየሸሸ ያለውን ወያኔ ብቻ ሳይሆን ቁጥሩን ሳይንቁ በተለይ በሸዋ ምድር በየትኛውም አቅጣጫ ያለውን የደህንነት ሁኔታ አስተማማኝ ማድረግ ግድ ነው፡፡ እየተሸነፈ እየሸሸ ነው በሚል በሌሎች ግንባርም ዝንጋኤ እዳይኖር ስጋት አለኝ፡፡ ወያኔ ከምትጠቀምባቸው ስልቶች አንዱ ነውና፡፡ ሌላ ቀርቶ ብዙ ምርኮ በመስጠትም ማዘናጋት የቻሉባቸውን ብዙ አጋጣሚዎች ታዝበናልና፡፡ ሁሉንም ነገሮች በጥንቃቄ ማየት ያስፍልጋል፡፡ ወያኔ የትኛውንም ተንኮል ለማድረግ የሚያግዳት የለም፡፡ አረመኔያዊነቷ ያለቀውም ቢያለቅ አጥፍቶ መጥፋት የመጨረሻ እቅዷ ነው፡፡ መዘናጋት እንዳይኖር ስለተሰማኝ ነው፡፡ ከእኔ በላይ ሁኔታውን የሚረዱ የሉም ብዬ አደለም፡፡ እኔም በአቅሜ የተሰማኝን ስጋት ማጋራት ስላለብኝ እንጂ፡፡

ሩቅ አደለም ወያኔ ታሪክ ትሆናለች፡፡ የማዝነው ትግራይ ከዚህ ጦርነት በኋላ ጥቂት ብቻ እድለኛ የሆኑ ወጣቶች የሚተረፉባት ምድር ትሆናለች፡፡ ብዙ ወጣት አልቋል፡ወያኔ ጦርነት ባደረገባቸው ቦታዎቹ ሁሉ መሳሪያ ያልታጠቁ ወጣቶችን ግማሾቹም እድሜያቸው ለጦርነት ያልደረሰ ጭምር ለጥይት ማብረጃነት ውለዋል፡፡ የትግራይ ሕዝብ እንደሕዝብ ከጅምሩ ጀምሮ የወያኔ የሴራ ግብር እንደሆነ ዛሬም ድረስ ቀጥሏል፡፡ ገና ከደደቢት እንደወጣ አንድ ሚሊየን የትግራይ ሕዝብ በረሀብ ሲያልቅ በእርዳታ ያገኘውን ገንዘብ ለጦር መሳሪያና የወያኔ ሥራ ማስኬጃ አድርጓል፡፡ሐውዜንን በሴራ አስደብድቧል፡፡ 27 ዓመት ሙሉ ሕዝቡን በሴፍቲኔት አኑሮ አሁን ደግሞ ለሚያለቅበት ጦርነት ዳርጎታል፡፡ በብዙ አመታተም ብዙውን የትግራይ ተወላጅ በአስተሳሰብ የባርነት መረብ ውስጥ ስለከተተው ዛሬ ላይ እየሆነበት ያለውን እንኳን ማስተዋል አልቻለም፡፡ ይሄው በምናየው መልኩ በወያኔ ዓላማ ታምኖም ይሁን ተገዶ በሚያሳዝን ሁኔታ እያለቀ እናያለን፡፡ ያሳዝናል፡፡ ይሄ ሁሉ ግን ለምንና እንዴት ሊሆን ቻለ?

ተጨማሪ ያንብቡ:  የህሊና ቢሶች መጫወቻ መሆን የማያሳፍረውና የማይቆጨው ትውልድ - ጠገናው ጎሹ

ሰሞኑን አንድ የአማራ የልዩ ኃይል ባለስልጣን ነው የተባለ ከወያኔ ጋር መረጃ ሲለዋወጥ እጅ ከፈንጅ ተያዘ በሚል አንድ መረጃ ያየሁ መሰለኝ፡፡ ወሬውን ግን ሌሎች ሲያሰራጩት አላየሁም፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮችም ጥንቃቄ ሊደረግባቸው ይገባል፡፡ ወያኔ በጣም ያስቸገራትን ሰው በተቃራኒው ወዳጇ በማስመሰል ማስመታት ሌላው የተካነችበት ሴራዋ ነው፡፡ ከድሮ ጀምሮ፡፡ በዙ ጠንከካራ የነበሩ የደርግ ሰራዊት አባላትን በዚህ መልኩ አስመትታለች፡፤ ወሬው ከየትም ይምጣ ከየት እንዲህ ያለ ሴራም ስላለ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡

ቅዱስ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ፤ ሠላምን በቶሎ ያምጣልን!

አሜን!

2 Comments

  1. ሰርጸ ልክ ነህ ኢሳት ካፈጣጠሩ ጀምሮ እሳት እንደሆነብን ነው ያለው አስተዳዳሪዎች መሰሪዎች የሰውን ደም መተዳደሪያቸው ያደረጉ ጨካኞች ጥቅመኞች ክፉዎች ናቸው በቅርብ ጊዜ ግን መሳይ መኮንን የተባለ ልጅ ትንታንግ ሁኖ ወጥቷል ድርጅቱ በነ ብርሀኑ ነጋ በነ አንዳርጋቸው የሚመራ ስለሆነ ወገን አይኑን ከነሱ እንዳያነሳ። መታሰር እንጅ ትግሬዎችን አዲስ አበባ አስገብቶ መልክ መልክ አስይዞ የወጣው አንዳርጋቸው ጽጌ መሆኑን መርሳት አይገባም። ስለ አረጋዊ በርሄ ጊዜው ሲደርስ ይሰነዴል።

  2. ይህ አይታህ ለእኔም ተመችቶኛል። ልክ ነህ። በየጊዜው አልቆላቸዋል፤ ተበትነዋል፤ ቀጥቅጠናቸዋል፡፤ በንፋስ ላይ የተበተኑ ድቄቶች ናቸው የተባለልን ወያኔ ድቄት መሆኑ ቀርቶ የመንደር ሊጥ ሰራቂ ሆኗል። ይታያችሁ ወያኔ ለዘመና አስቀድሞ በየሥፍራው በደበቃቸው መሳሪያዎች እየተደገፈ ሰሜን ሽዋ ሲደርስ እንዴት ለምን በማለት የሴራቸውን ጥምረትና ፍጥነት አጥንቶ ያጋለጠ የለም። ግን ከላይ እንደተባለው የሚዲያ ናፍቆትና ውል የለሽ የሚዲያ ላይ ሃተታ ሃገርንም ራስንም ለችግር ያጋልጣል። ትግል ላይ ያለ ሰው ትግሉ ሳያልቅ የሚጠቁማቸው መንገዶች ሁሉ ለጠላት ድጋፍ ሰጪ ናቸው። ይህን ይዘናል ያን ነገ እንይዛለን ማለትም ከወታደራዊ ዲሲፒሊን ውጭ ነው። በአንድ የውጊያ መስክ ላይ ጠበብቶች እንደሚሉት ዋናው ነገር “The element of surprise” ነው። ወያኔ የሰሜን እዝን ሲያጠቃ አጨዳ አስውሎ፤ አድክሞ፤ መሳሪያቸውን ግምጃ ቤት እንዲያገቡ አድርጎ፤ መሪዎቻቸውን ራት በመጥራት አብልቶና እጃቸው ላይ ካቴና አድርጎ የቀሩትን በተኙበት የፈጃቸው። አንድ የውጭ ሃገር የስላላ መረጃ እንደሚያሳየው በዚያ ጥቃት ከ6ሺ እስከ 10ሺ ወታደሮች ሲገደሉ፤ ሲኖ ትራክ የተነዳባቸው፤ አንተ አማራ ትመስላለህ ተብለው ከሚነድት መካከል ተለይተው የተረሸኑትን፤ ጡታችው የተቆረጠውን የሴት ወታደሮችና የወታደር ቤተሰቦች ይህ አሃዝ አይጨምርም። ታዲያ ያኔ በመቀሌ ዙሪያ ተቀብሮ ተገኘ ተብሎ ያየነውን ያን የሚያክል የነዳጅ ክምችት ያገኘ ሰራዊት እንዴት ሌላ ነገር በከተማና በገጠር፤ በእምነት ቤቶች ውስጥ ተቀብሯል ብሎ አይጠረጥርምና ፍተሻ አያካሂድም? ወያኔ መሳሪያ የቀበረው በትግራይ መሬት ላይ ብቻ አይደለም፡፤ በሁሉም የሃገሪቱ ምድር እንጂ። ይህን ጉዳይ ለመመርመርና ለማወቅ የእነርሱ ተላላኪ የሆኑ ቀንደኛ መሪዎቻቸውን በምርመራ ማናዘዝ ይጠይቃል። በአዲስ አበባ ብቻ የተከፋፈለውና የተቀበረው መሳሪያ ለዘመናት ያዋጋቸዋል። መፈልፈል አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ወደ አስመራና ወደ አማራ ክልል ወያኔ ስለወነጨፋቸው ሚሳይሎች ክትትልና ምርመራ አድርጎ የሚሳዪሎችን አይነት፤ የወፍ በረር ርቀታቸው፤ የት ላይ እንዳረፉ፤ ምን ጉዳት እንዳደረሱ፤ ስንት እንደተተኮሱ ሲተኮሱ የት ላይ ተጠምደው እንደሆነና ሌላ ነገርን ያስነበበን ጋዜጠኛ አለ? እኔ አላነበብኩም። ይህ ዘገባ ካለ አመላክቱኝና ልየው። ከተማ ተቀምጦ ሰበር ዜና ማለት ሃሳበ ጎደሎነትና የነጭ ልቅላቂ ሃሳብን መከተል ነው።
    ከዚህ ባሻገር የክልል መሪዎች፤ የተፎካካሪ መሪዎች፤ በሃገሪቱ ላይ በልዪ ልዪ የሲቪልና የወታደራዊ ሙያ የተሰማሩ ወገኖች ሁሉ ባልሰከነ መንገድ በግፍልተኝነትም ሆነ በተደረገ ነገር ላይም ቢሆን ያለጊዜውና ያለወቅቱ ወሬውን ማጦዝ ቢቀር መልካም ነው። አሁን በቅርቡ ጄ/ብርሃኑ ጁላ ለኢሳት የሰጡት አስተያየት ጉዳት ባይኖርበትም ጊዜአቸውን መሻማቱ አስፈላጊ መስሎ አይታየኝም። ጊዜው ፊልሚያ ነው። ሰአቱ የሞት ሽረት ጦርነት የሚደረግበት ወቅት ነው። ደሴን የመሰለ ከተማ ለጠላት አስረክቦ እንቅልፍ ሊኖር አይገባም። ስለሆነም በቅርብ ቀን የኢትዮጵያ መንግስት የዜና ስርጭትና ክፍፍልን በተመለከተ የወሰደው እርምጃ መተግበር አለበት። አንድ አማካኝ በሆነ የመንግስት ቃል አቀባይ ወይም አቀባዪች በኩል በተጠና መልኩ የሚለቀቅ መሆን አለበት። አይ እኔ ያን አልፈልግም ያለ የግልም ሆነ የኩባኒያ ወሬ አናፋሽ ጦር ሜዳው ድረስ ሂዶ መዘገብ ይችላል። ወያኔ ያደረሰውን ግፍና መከራም እኮ በፊልምም ሆነ በፎቶ ዶኮሜንት ማድረግ ለትውልድ አስተማሪ ነው። በቀረው እባካችሁ ፉከራውን፤ ቀረርቶውን፤ ገደልን ቀማን የሚለውን ሁሉ ለአሁኑ ረገብ አርጉት። ገና ብዙ ይቀራል። ወያኔ መሰሪ ድርጅት ነው። እጄን ሰጥቻለሁ ብሎ ዞሮ የሚፋለም፤ በዘሩና በቋንቋው የሰከረ፤ ያለ ትግራይ ሌላ ህዝብም ሃገርም አለ ብሎ የማያምን እብደትን የተላበሰ የአውሬዎች ስብስብ ነው። ይህ ነገር ሃሰት ነው የሚሉ ሁሉ ከጎናቸው የተሰለፉ ወይም በቅርብና በሩቅ ድጋፍ የሚያደርጉ የወያኔ ተባባሪዎች ብቻ ናቸው። እባካችሁ፤ ጥንቃቄና ወታደራዊ ሳንሱር ስያልፍ ዝም ብላችሁ የፈጠራም ወሬ ይሁን በምድር ላይ ያለ አታናፍሱ። ሰው ያሰለቻል። የወገንና የሃገርን ሰላም ይነጥቃል። የተሰበረ ወሬ ስታወሩ፤ እናንተም ሰባራ ትሆናላችሁ። ጀግና ማለት “Investigative Journalism” ተጠቅሞ ከመንግስትም፤ ከህዝብም ዓይንና ጀሮ የተደበቁ ነገሮችን በመረጃ ማቅረብ ነው። ሌላው ሁሉ የማይበቅል ዘር እንደመዝራት ነው። አይረባም። በቃኝ!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share