ህዳር 15 ቀን 2014 ዓም (23-11-2021)
በጣልያን ወረራ ጊዜ በተደረገው አገር አድን የነጻነት ዘመቻ ብዙ አርበኞችና አገር ወዳዶች ከንጉሳቸው ጎን በመሰለፍ መስዋዕትነት በመክፈል ለድል እንደበቁና ለተተኪው ትውልድ ነጻ አገር ለማስረከብ የሚያኮራ ጀብዱ እንደፈጸሙ ታሪክ ይመሰክራል።በዚህ እልህ አስጨራሽ ዘመቻ ወቅት ለጣልያን ያደሩ ባንዳዎችም ከጠላት ጎን በመሰለፍ በራሳቸው አገርና በወገናቸው ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው በደል ፈጽመዋል።
የግፉሃን አምላክ ከኢትዮጵያውያን ጋር ሆኖ በብዙ ዘመናዊ መሣሪያ የታጠቀን ጦር ድባቅ እንዲመታ እረድቶታል። የቀድሞዎቹን ትተን በንጉሥ ቴዎድሮስ፣በንጉስ ዩሃንስ፣በንጉስ ምንሊክ ከዚያም በንጉሥ ሃይለሥላሴ መሪነት የተካሄደው አገር አድን ዘመቻ ለአሁኒቷ ኢትዮጵያ ነጻነትና አንድነት መሰረት መሆኑን ጠላቶችም ያልካዱት ሃቅ ነው።በዚያን ጊዜ የነበሩት መሪዎች ጠላት ከመናገሻ ከተማቸው ደጃፍ እስኪመጣ ድረስ የጠበቁ ሳይሆን ገና ከጅምሩ ቀይ ባሕርን ሲያልፍ ጀምሮ የሚችሉትን ትግል አድርገዋል። በመቅደላ፣ በመተማ፣በአድዋም ሆነ በማይጨው ጦር ሜዳ ላይ ያደረጉት የጀግንነት ውጊያ ጠላትን ከመረብ ባሻገር ብሎም ከቀይባሕር ድንበር ለማሶገድ እንጂ መናገሻ ከተማቸውንና ዙፋናቸውን ለማዳን ያደረጉት ትግል አልነበረም።ጠላት ካለበት ቦታ ዘልቀው ተዋጉ እንጂ በቤተመንግሥታቸው ዙሪያ የሰፈረን የጠላት ከበባ ለመስበር፣ሥልጣናቸውን ለማዳን በመሸ ሰዓት ላይ አልተንቀሳቀሱም።
በዚያ እልህ አስጨራሽና የሞት የሽረት ትግል ውስጥ ጠላታቸውን ለይተው ያወቁና ባላቸው አቅም የታገሉ ኢትዮጵያውያን እንደነበሩ ሁሉ ለጠላት እንቁላል ከመገበር ባሻገር በፊርማቶሪነት ወይም በሰላይነት ግፋ ሲልም በወታደርነት ያገለገለው ባንዳ ቁጥሩ ቀላል አልነበረም።ይህ የባንዳ መንጋ ኢትዮጵያውያን ለድል መቃረባቸውን ሲያውቅና ሲያረጋገጥ ተገልብጦ የጀግና አርበኞችን ቦታ ለመያዝ ተሽቀዳድሞ የድል አጥቢያ አርበኛ ሆኖ ብቅ አለ።ያልፈጸመውን ጀብዱ እንደፈጸመ በፉከራና ሽለላ ሜዳውን አጥለቀለቀው።
ታሪክ እራሱን ይደግማል እንደሚባለው አሁንም የሚታዬው የባንዳዎች አለሁ ባይነት ከዚያ የተለዬ አይደለም።ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የጎሳ ፖለቲካና ያንን የሚንከባከብ ሕገመንግሥት ተሸክሞ ሥልጣን ላይ የተቀመጠ ቡድን አጅቦ ዘመቻ እያሉ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት ከቀድሞዎቹ የባንዳዎች የድል አጥቢያ አርበኝነት የተለዬ አይደለም።በተለይም የጎሰኞች ሰለባ የሆነው የአማራ ማህበረሰብ ባለው የማያወላውል ኢትዮጵያዊነቱ ምክንያት ግፍና በደል ሲፈጸምበት ድምጽን አጥፍቶ ኖሮ አሁን አንገቱን ቀና ሲያደርግ ዘመቻ ወረድን እያሉ ማስተጋባቱ እውነት ለኢትዮጵያና ለሕዝቡ በማሰብ ሳይሆን የቆሙለት ኢትዮጵያን የማፍረስ ዓላማ ፣በተለይም የአማራው መነሳሳት እንቅፋት ሆኖ ስላገኙት በዘመቻ ስም አንገቱን ለመስበር የተደረገ የሴራ ዘመቻ መሆኑን መገንዘብ ያሻል።በፋኖና የአማራው ሚሊሽያ ወይም ሕዝባዊ ጦር ላይ የሚደርሰው የጀርባ ጥቃት ለዚያ ምስክር ነው።እርግጥ ነው ጥቂት አገር ወዳዶች ለዘመቻ መነሳሳታቸው የሚካድ አይደለም፤ከማን ጋር እንደቆሙም ሰልፋቸውን አሳይተዋል።በባንዳነትና በድል አጥቢያ አርበኝነት የሚታሙት በአብይ ዙፋን ጀርባ ተሰልፈው ያዙን ልቀቁን የሚሉት ናቸው።የመመላለሻ የአዬር ትኬትና የሸራተን ሆቴል መስተንግዶ ይቀርብናል ብለው የሚያስቡ ከንቱዎችን ነው።እነዚህ ከንቱዎች ከመጣው ጋር ለመለጠፍ ችግር የለባቸውም።መገለባበጥ ችሎታና እውቀት ይመስላቸዋል።ለወደፊቱ ግን ይህንን አይነት አድርባይነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊሸከም የሚችልበት ትከሻ እንደሌለ ሊያውቁት ይገባል።
እውነት ለአንድነትና ለአገር ህልውና ብሎም ለሰብአዊ መብት መከበር የሚደረግ ዘመቻ ቢሆን ኖሮ ወያኔ ሸዋ መሬት ደርሶ ከመናገሻ ከተማ በቅርብ እርቀት ላይ እስኪሰፍርና ጥቃት እስኪያደርስ ድረስ ባልተጠበቀ ነበር።ዋናው ምክንያት ግን በተረኝነት የያዙት የሥልጣን ወንበር ሲነቃነቅ ያንን ለማዳን የሚደረግ እርብርቦሽ ነው።ለሰብአዊ መብትና ለሕዝቡ ደህንነት ብሎም ለአገር አንድነት ቢታሰብማ ኖሮ ወያኔ እንዲያንሰራራና አሁን በሚገኝበት ደረጃ ላይ እንዳይደርስ የትጥቅና የስንቅ ብሎም የስትራተጂ ቦታዎችን እንዲቆጣጠር ዕድሉን እንዲያገኝ አይተባበሩም ነበር።ሌላው ቀርቶ አብይ አህመድ በሚመራው ኦህዴድ በሚያስተዳድረው ክልል ውስጥ የሚጨፈጨፈውን አማራና ሌላውን ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለማዳን ገና ከጅምሩ በተዘመተ ነበር።ለሱና ለተከታዮቹ ግን የአማራው ደህንነት የሚያስጨንቀው ጉዳይ አይደለም።እሱን አጅበው የቁራ ጩኸት የሚያሰሙት ጋዜጠኞች፣የፖለቲካ ድርጅቶች፣ግለሰቦችም በአብይ ጀርባ ለሚያገኙት ጥቅምና ወደፊት እናገኛለን ብለው ለሚያልሙት ከወያኔ የተነጠቀ ንብረትና የንግድ ተቋም ፣ለሚያገኙት እንክብካቤና መስተንግዶ ተከላካይ ለመሆን እንጂ ብሔራዊ ስሜት ይዟቸው የሚዘምቱ አገር ወዳዶች አይደሉም። የእነሱ አገራቸው ሆዳቸው ነው፤እውነትም ሆድ ካገር ይሰፋል!የእነሱ ተግባር ሞሶሊኒን ተቃውሞ ግራዚያኒን የመደገፍ ያህል ነው።ሞሶሎኒና ግራዚያኒ አንድ መሆናቸው ሲታወቅ! ህወሃት/ኢሕአዴግና ኦህዴድ/ብልጽግናም አንድ አካል አንድ አምሳል ግን በጥቅምና በሥልጣን የሚሻኮቱ መሆናቸው እዬታወቀ አንዱን አገር አፍራሽ ሌላውን አገር አድን አድርጎ ማዬት ስህተት ብቻ ሳይሆን በአገር ላይ የተሰነዘረ ክህደትና ወንጀል ነው።የዚህ ስርዓት ደጋፊ ፣ህገመንግሥቱን ተሸክሞ የሥልጣን ተካፋይ የሆነ ሁሉ ከወያኔ ተነጥሎ አይታይም።
ውድ ኢትዮጵያዊ ሆይ !ከሳት ወደ እረመጥ እንዳይሆንብህ እሳቱን አመድ አድርገው!በከንቱ ዲስኩርና ጩኸት አትታለል፤ለአስመሳይ አጭበርባሪዎች ጆሮህንም አትስጥ!
አገር ወዳድ ሆይ! ትግልህን ለማኮላሸት አንተን መስለው ሰርገው ሊገቡ ያሰፈሰፉትን የኦሕዴድ/ኦነግን መሪዎች፣ደጋፊዎችና ተባባሪዎች፣ ድርጅቶች፣አድርባይ ጋዜጠኞችና ግለሰቦችን ከጫንቃህ ላይ እንዳይፈናጠጡ ከርቀት አስቀራቸው።አሁን አካኪ ዘራፍ የሚሉት የራሳቸው ጥቅምና ስልጣን አሳስቧቸው እንጂ ለአንተና ለአገርህ ለኢትዮጵያ ብለው አይደለም።ለኢትዮጵያ ቢያስቡማ ኖሮ ጸረ ኢትዮጵያ የሆነ ሕገመንግሥት ተሸክመው ለዚህ ስቃይና መከራ ባልዳረጉህ ነበር። ለራስህ፣በራስህ የራስህ የሆኑትን መሪዎች ፈጥረህ ለአገርህና ለመብትህ የምታደርገውን ትግል በጥራትና በስልት ምራው።በአድዋ፣በማይጨው ያደረከውን ተጋድሎ ዛሬም ድገመው!። መሣሪያ የለኝም ብለህ አትፍራ፤ መሣሪያውን ከጠላትህ በመማረክ ታገኘዋለህ።አንተ በምታውቀው መሬትና ከባቢ እንግዳ የሆነ ጨካኝ ወራሪ መጥቶ ሲያጠቃህ ከመሸሽ ይልቅ መሽገህ ድባቅ ምታው፤ከጠላትህ ይልቅ ለአንተ የተመቸ ዕድል አለህ።በወሬ ፊትአውራሪዎች ተወናብደህ ቀየህን አታስረክብ።በምታውቀውና በኖርክበት ሜዳ፣ ዳገትና ጫካ መሽጎ የመጣውን መከላከል ብቻ ሳይሆን አመድ ለማድረግ ከፍተኛ ዕድሉ ያንተ ነው።
በዓመት ሦስት ጊዜ የምታመርትበት የአዬር ንብረት ፣ ደጋ፣ ወይና ደጋና ቆላ፣ለመስኖ የሚሆኑ ብዙ ወንዝና ጅረቶች፣ለም መሬትና ብዙ የሰው ሃብት ኖሮህ እጅህን ለልመና አትዘርጋ።ስደትና ልመናን ተጠዬፍ።ያለህን የተፈጥሮ ሃብት በመጠቀም ከድህነትና ከዃላ ቀርነት ለመውጣት እንደምትችል በራስህ ተማመን።
ውድ የመከራ ገፈት ቀማሹ አማራ ሆይ! በዬቦታው የተበተኑትን ልጆችህን ሰብስብ፣ባሉበትና በሚኖሩበት የኢትዮጵያ መሬት ላይ መብታቸው እንዲከበርላቸው አድርግ።ባለቤት ያቀለለውን አሞሌ ባለዕዳ አይቀበለውም ነውና እራስህን አክብረህ አስከብር!
የተማርከው የአማራ ልጅ፤ኢትዮጵያዊ ሆይ!የምትፈተንበት ወቅት አሁን ነው። የነጮች ተላላኪ በመሆን የቅንጦት ኑሮ አያጓጓህ፣የነጮቹን ደባ በአጋርነት ጥያቄ እያዬህ ደንዝዘህ አታደንዝዝ።ነጮች አጋር የሚያደርጉት የአገሩን ክብርና ነጻነት ሸጦ ለብዝበዛ የሚተባበራቸውን አገር በቀል ባንዳ ነው።ከራሳቸው ጥቅም በላይ የሌላውን አገር ጥቅም አያዩም።በነሱ ግብስብስ ምርት ከመጠቀም ይልቅ በራስህ ምርት በመጠቀም ያገርህን ሃብት አዳብር። ክብርና ጸጋ አገር ሲኖርህ ነው።ሳይማር ላስተማረህ ሕዝብ አለኝታ ሁን።የጨቃኞችና የአገር አጥፊ ጎሰኞች ጠበቃ ሆነህ ወገንህን አትጉዳ፤አገርህንም አታፍርስ።ትልቁ እውቀት ጎሰኝነትንና የእጅ አዙር አገዛዝን መቃወምና መታገል ነው።የአገር ፍቅር ባለቤት መሆን ነው።
አስቀድሞ መምታት የውስጥ ባንዳውን ነው።
አስመሳይ አድርባይ ሆዳም ሆዳሙን ነው።
የድል አጥቢያ አርበኛን፣አስመሳይ መንጋን ነው።
አገሬ አዲስ