ከቅኝ አገዛዝ እስከ ኒዮሊብራሊዝም ፣ – ከደረጀ ተፈራ፣

1. መግቢያ፣

15 ኛው እስከ 18 ኛው ክ/ዘ በአውሮፓ የባህል ህዳሴና የአዕምሮ መነቃቃት ዘመን (Renaissance & Enlightenment) እና የኢንዱስትሪ አብዮት የተከናወነበት ነው። በተለይ ክርስቶፎል ኮሎምቦስ የተባለ የባህር አሳሽ በ1492 ከስፔን የባህር ወደብ ተነስቶ የቅመማ ቅመም እና የሃር የንግድ መስመር ለማግኘየት ወደ ህንድ እና ቻይና በባህር ላይ በሚጓዝበት ጊዜ ከአሜሪካ ድንበር በቅርብ ርቀት የሚገኙትን የባሃማና የካሬቢያን ደሴቶች አካል የሆኑትን ሄይቲ፣ ዶሚኒካን ሪፐብሊክ፣ ኩባ፣ ቬንዙላ እና የመሳሰሉትን ደሴቶች ባገኘ ጊዜ ምዕራባዊ የህንድ ግዛት (West Indies) የደረሰ ስለመሰለው እነዚህ አካባቢዎች ቀድሞ የማይታወቁ አዲስ የዓለማችን ክፍሎች መሆናቸውን አልተገነዘበም ነበር። ይሁን እንጂ ከሱ በመቀጠል አሜሪጎ ቪስፑቺ (Amerigo Vespucci) የተባለ የጣሊያን የባህር አሳሸ ወደዚሁ አካባቢ በመምጣት የተገኙት ደሴቶቹ አዲስ የዓለማችን ክፍል መሆናቸውን አስታወቀ። በእሱም ስም አካባቢው አሜሪካ ተብሎ መጠራት ተጀመረ። በቀጣይም ስፔኖች ከአካባቢው ነባር ህዝቦች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ባደረጉት አሰሳ ከፍተኛ የሆነ የወርቅና አልማዝ ክምችት አገኙ። ከስፔን አሳሾች ጎን ለጎን የፖርቹጋል የባህር አሳሾችም ወደዚሁ አካባቢ ወርቅና ሌሎች ሃብቶችን ፍለጋ በተለይም ወደ ብራዚል ይጎርፉ ነበር። በመቀጠልም በሃገራቸው መንግሳት ከሚደገፉ ከስፔን እና ከፖርቹጋል አሳሾች በተጨማሪ የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ፣ የደች መንግስታት እና ሌሎች አውሮፓውያን በግልና በቡድን በመሆን ወደ አካባቢው በብዛት መፍለስ ጀመሩ። በወቅቱ በአውሮፓ ገበያ የስኳር እና የትንባሆ ምርት ከፍተኛ ተፈላጊነት ስለነበረ አውሮፓውያን በሰሜን እና ደቡብ አሜሪካ እንዲሁም በአካባቢው በሚገኙ የካሪቢያን ደሴቶች አፍሪካውያንን እግርና አንገታቸውን በሰንሰለት እያሰሩ ወደ አካባቢው በባርነት በማጋዝ በጥቁር ህዝብ ጉልበት ለስኳር ማምረቻ የሚሆን የሸንኮራ አገዳ፣ ቱባኮ (ሲጋራ)፣ ጥጥ እና በመሳሰሉት ገንዘብ አመንጪ (cash crop) የሆኑ እርሻን በማስፋፋት አምርተው በአውሮፓ ገበያ በመሸጥ ከፍተኛ ገቢ (ሃብት) አገኙ።

2. የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች፣

በመካከለኛው ዘመን አውሮፓውያን አዲስ የዓለማችንን ክፍሎች ፍለጋ (Exploration) ላይ ትኩረት ያደረጉበት ወቅት እንደነበር ይታወቃል። በወቅቱ የባህር ላይ ጉዞ በማድረግ አዲስ ዓለማት ፍለጋ ላይ የተሰማሩበት ዋናው ምክንያት ሃብት ፍለጋ ሲሆን ከዚህ ሲቀጥል ደግሞ ግዛት በማስፋፋት የፖለቲካና የወታደራዊ የበላይነት ለማግኘት፣ እምነትን ለማስፋፋትና ንጉሶቻቸው በነበራቸው የግል ዝና (Glory) ፍለጋ ጭምር ነበር። በመሆኑም ለምዕራባውያን አፍሪካ የጥሬ እቃና ነጻ የሰው ሃይል ምንጫቸው በማድረግ የአፍሪካን ህዝብ በባርነት ወደ አሜሪካና በቅርብ ወደሚገኙ የካሬቢያን ደሴቶች በመርከብ እንደ ሰው ሳይሆን እንደ ከብት አጉረው በማጋዝ በነፃ ጉልበት ቱባኮ፣ የስኳርና የጥጥ ምርቶች እንዲሁም እንደ ወርቅና አልማዝ የመሳሰሉ የከበሩ መዐድናትን አስቆፍረው በማውጣት በአውሮፓ ገበያ በመሸጥ ከፍተኛ ሃብት (Capital) ሰበሰቡ። ይህ አፍሪካን አሜሪካን እና አውሮፓን ያስተሳሰረ የሶስትዮሽ የባሪያ፣ የጥሬ ዕቃና የሸቀጥ ንግድ Triangular slave trade በመባል ይታወቃል። በዚህ ሁኔታ በተገኘ ሃብት በእንግሊዝ እና በበርካታ የአውሮፓ ሃገራት ኢንዱስትሪዎችን ገነቡ፣ ከተሞችን አስፋፉ። ስራቸውንም ለማቀላጠፍ የሚያግዙ ባንኮችን አቋቋሙ። በመቀጠልም በካሪቢያን (west Indies) ይኖሩ የነበሩ የአውሮፓ ከበርቴዎች ግማሾቹ እዛው ሰሜን አሜሪካ ሲጠናከሩ በጃማይካና በአካባቢው በሚገኙ ደሴቶች የነበሩት ደግሞ በባርነት ያስተዳድሯቸው የነበሩ አፍሪካውያንን አስከትለው ወደ እንግሊዝ (አውሮፓ) በመመለስ ትላልቅ የቤተሰብ እርሻዎችን እና የኢንዱስትሪ ከተሞችን አስፋፉ።

እነዚህ በአፍሪካውያን ጉልበት ከፍተኛ የገንዘብ (የካፒታል) አቅም የገነቡ የኢንዱስትሪ ባለቤቶችና ዓለም አቀፍ ነጋዴዎች በአውሮፓ ሃገራት የመንግስት ስልጣንን በመቆጣጠር የሃገራቸውን ፖለቲካ ይዘውሩ ጀመር። በመቀጠልም ለኢንስትሪያቸው ጥሬ ዕቃ በነጻ ለማግኘት እና ምርታቸውን አፍሪካ ላይ ለማራገፍ ያስችላቸው ዘንድ የአውሮፓ መንግስታት በጀርመኑ ቻንስለር በኦቶቫን ቢስማርክ ጋባዥነት በ1884 በርሊን ከተማ ላይ አፍሪካን ሙሉ ለሙሉ በቅኝ ግዛት ለመቀራመት ተስማሙ። በወቅቱ ስምንት የሚሆኑ የአውሮፓ መንግስታት አፍሪካን በቅኝ ግዛት ለመቀራመት ጉባኤ ተቀምጠው በነበረ ጊዜ የአፍሪካን ካርታ ጠረጴዛ ላይ ዘርግተው ይህ ለኔ ያ ደግሞ ላንተ እያሉ እንደ ቅርጫ ስጋ ሃገሩን እና ህዝቡን በማናህሎኝነት ተከፋፈሉት። ዓላማቸውም ሃብት (capital) በመሰብሰብ በቁስ ለመበልጸግ ነው። የአውሮፓ ስልጣኔ በገንዘብ፣ በሃብትና በቁስ የሚለካ እንጂ ሰብአዊነ የሌለው ለመሆኑ በአፍሪካ ህዝብ ላይ ያደረሰው ግፍ፣ መከራ፣ ስቃይና ውድመት ምስክር ነው።

በመሆኑም አውሮፓውያን የአፍሪካን ህዝብ በባርነት በማጋዝና በነፃ ጉልበቱን ከመበዝበዝ በተጨማሪ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ላይ ኢሰብአዊ ድርጊት እና ወንጀል ፈጽመዋል፣ ጥንታዊ አፍሪካዊ መንግስታትን፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ እሴቶችን አፈራርሰዋል። ህዝቡን በከፋፍለህ ግዛ ፓሊሲያቸው እርስ በርሱ አባልተዋል። አንድ ቋንቋ ተናጋሪ ማህበረሰብና ቤተሰብን ከአንድ በላይ በሆኑ ሃገራት እንዲከፋፈሉ በዘፈቀደ ድንበር አስምረዋል፣ ቀድሞ በአፍሪካ የማይታወቁ የአውሮፓ በሽታዎች (ደዌዎች) አውቀውም ሆነ በንዝህላልነት አስፋፍተዋል። (ለምሳሌ ጣሊያን በግብርና ላይ የተመሰረተውን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሽመድመድ ከአድዋ ጦርነት በፊት የከብቶች በሽታ ከህንድ ሃገር በማምጣት በኢትዮጵያ አዛምቷል)። አፍሪካውያንን በባርነት ወደ አሜሪካ በሚያጓጉዝበት ወቅት በርካታ ልጃገረዶች በነጮች እየተደፈሩ የጌቶቻችውን ልጆች በሆዳቸው ይዘው ነው ከመርከብ የወረዱት። በቤት ውስጥ በሚያገለግሉ ሴት አፍሪካ እህቶቻችን ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ በየጓዳው አስገድዶ መድፈር ተፈጽሞባቸዋል። ቅኝ ገዢዎች በግፍ የወረሩትን የአፍሪካ ህዝብ ከሰውነት በታች በማድረግ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳት በማድረስ አንገቱን ደፍቶ ዘለዓለም የእነሱ ተገዥ ሆኖ እንዲኖር የቻሉትን ሁሉ አድርገዋል። የተፈጥሮ የቆዳ ጥቁረትን ከእርግማንና ከሃጢያት ጋር በማያያዝ በአፍሪካ ህዝብ ስነ ልቦና ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል። ሲያሻቸው ደግሞ በዘረኛ ሳይንቲስቶቻቸው የአፍሪካ ህዝብ የአዝጋሚ ለውጥ ሂደትን ያላጠናቀቀ በሰውና በእንስሳት መሃል የሚገኝ ነው በማለት አፍሪካውያንን ከሌሎች እንሣት ጎን በማቆም በሙዚየም (Human Zoo) እንዲጎበኝ እስከማድረግ ደርሰዋል። ለምሳሌ በቤልጂየም እና በሰሜን አሜሪካ የነበሩ The Human zoo of Tervuren, Belgium (1897/1958) እና The Human zoo of St. Louis Missouri USA (1904) መጥቀስ ይቻላል። የኢትዮጵያ ነገስታት ግን በኢትዮጵያና በህዝቧ ላይ ይህ ሁሉ እንዳይሆን በየዘመኑ በአረቦች፣ በግብጾች፣ በቱርኮች እና በአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች የሚቃጣውን ተደጋጋሚ ወረራ ህዝባቸውን እያስተባበሩ፣ እነሱም በግንባር በየጦሩነቱ ላይ እየተሰለፉ የህይወትና የአካል መስዋዕትነት በመክፈል የህዝባቸውን እና የሃገራቸውን ነጻነት፣ ባህል፣ ቋንቋ እና ኢትዮጵያዊ ብዝሃነትን አስጠብቀው መዝለቅ ችለዋል። ነጻነታችንን እና ማንነታችንን በከፈሉት የደም ዋጋ ጠብቀው ላቆዩልን አባቶቻችን ክብርና ምስጋና ይሁን!

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሽምግልና የህወሃት የጥቃት ደመና -  ከሳዲቅ አህመድ

3. ድህረ ቅኝ አገዛዝ እና ኒዮሊብራሊዝም (Post-colonization and Neo-liberalism)

ምዕራባውያን በዓለም ላይ ዘርግተውት የነበረው ቅኝ አገዛዝ ከተወገደ በኋላ እንደ Commonwealth ዓይነት ህብረቶችን እና የመሳሰሉትን በማቋቋም ከቀድሞ ቅኝ ግዛቶቻቸው ያገኙ የነበረውን ጥሬ ዕቃ፣ ማዕድናት፣ ነዳጅ፣ የሰው ሃይል እና የመሳሰሉት እንዳይቋረጥባቸው፣ ምርታቸውንም አፍሪካ ወስደው ለመሸጥ የሚያስችላቸውን ዘዴ በመንደፍ ግንኙነታቸውን ቀጠሉ። አሁን ባለንበት ዘመን ደግሞ ይበልጥ በረቀቀ መንገድ ግሎባላይዜሽን፣ ነጻ ገበያና ፕራይቬታይዜሽን በሚል ስልት የዓለምን ኢኮኖሚና ፖለቲካ ለመቆጣጠር የሚያስችላቸውን ኒዮሊብራሊዝም (Neo-liberalism) የሚባል ርዕዮት በማራመድ ላይ ይገኛሉ። በኢኮኖሚው ዘርፍ ስርዓቱን ለማሳለጥ የዓለማችን ግዙፍ የገንዘብ ተቋማት የሆኑትን IMF, World Bank, European Central Bank (ECB)USAIDUN (የተባበሩት መንግስታትን)እና የመሳሰሉትን ህብረቶችን እና ስብስቦችን፣ የሰብዓዊና የእርዳታ ሰጪ ተቋማትን የሚጠቀሙ ሲሆን፣ በፖለቲካውና በወታደራዊው ዘርፍ ደግሞ እንደ NATO ዓይነት ህብረቶችን በመጠቀም የአሜሪካ እና የእንግሊዝ መንግስታት ሌሎች የምዕራቡን ሃገራትን በማስተባበር ነው። በተለይም በ1980 ዎቹ የአሜሪካን ፕሬዝዳንት በነበሩት በሮናልድ ሬገን እና በእንግሊዟ ማርጋሪ ታቸር ወቅት የኒዮሊብራሊዝም ርዕዮት ፖሊሲና ስትራቴጂ ተቀርጾለት የታዳጊ ሃገሮችን የተማረ የሰው ሃይል፣ የተፈጥሮ ሃብት፣ ትላልቅ ተቋማትን በ privatization ስም በመቆጣጠር፣ የሃገር በቀል አፍሪካዊ ባለሃብቶችን እና የመንግስት ተቋማትን አቀጭጮ በማጥፋት የሃገራቱን ኢኮኖሚ የምዕራቡ ባለሃብቶች እንዲቆጣጠሩት ለማድረግ ሲሆን ኒዮሊብራሊዝም (Neoliberalism) ከቅኝ ግዛት ማብቃት በኋላ መልክና ቅርፁን ቀይሮ የመጣ የምዕራባውያን አዲስ የብዝበዛ ስልት ነው። በመሆኑም ምዕራባውያን የዓለምን ኢኮኖሚ ከተቆጣጠሩ በኋላ ልኡዋላዊ መንግስታትን በማፍረስ ፈላጭ ቆራች (Totalitarian) የሆነ መንግስት በመመስረት የማህበረሰቡን መልካም እሴቶች በማጥፋት በተለይ በእኛ ኢትዮጵያውያን ባህል እና እምነት ተቀባይነት የሌላቸውን የረከሱ ነገሮችን ለማስፋፉ እንዳቀዱ ይነገራል።

የአሮጌው ወይም የክላሲካል ሊብራል አስተሳሰብ መርሆዎች የነበሩትን ነጻነት፣ እኩልነት፣ ዲሞክራሲ (Liberty/ Freedom, Equality, Democracy) እና የመሳሰሉ ቃላቶችን የኒዮሊብራሊዝም (NeoLibralism) አራማጆች ለእነሱ በሚያመቻቸው አንጻር እያወላገዱ ይጠቀሙበታል። ለምሳሌ liberty and free market በኒዮሊብራሊዝም መዝገበ ቃላት ስለ ሰው ልጅ ነጻነት ሳይሆን መንግስት በካፒታሊስቶች ላይ የገበያ ቁጥጥር (Regulation) አያድርግ፣ ባለሃብቱ እንደፈለገ በነጻነት ስም ይለቀቅ ወይም ቁጥጥር አይደረግበት ለማለት ነው። አንድን ሰው በሌሎች ሰዎችና በሃገር ላይ እንደፈለገ እንዲሆን መልቀቅ ጥቂት ባለሃብቶችን ማንገስ ብቻ ሳይሆን ስለሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ስነልቦና አለመረዳትም ጭምር ነው። ብዙ ውስብስብ ግብአቶች ባሉባት ዓለም “Demand and Supply የሚባሉ ሁለት የምጣኔ ሃብት ቃላቶችን መዘህ አውጥተህ የዓለምን ህዝብ ጠቅልለህ በሞኖፖል ለጥቂት ሃብታሞች እንዳሻችሁ በገበያው መሰረት አድርጉ ብልህ የምትሰጥ ከሆነ የአንተን ድንቁርና እንጂ የእነሱን ድክመት አያሳይም። በመሆኑም ካፒታሊስቱ ልጓም እንደሌለው ፈረስ ያለተቆጣጣሪ እንዳሻው እንዲጋልብ ሲለቀቅ፣ ሃብት ለማካበት በሚያደርገው ፉክክር ሁሉም እንኳን ባይሆኑ ጥቂቶች የሌላውን መብት ከመጋፋታቸውም በተጨማሪ ለሰባዊ ፍጡር አደገኛ የሆነ ነገር ሊሰሩ ይችላሉ። የሰው ልጅ እንደከብት ታርዶ ኩላሊቱ በሚሸጥበት እና ቫይረስ ይፈበረካል በሚባልበት በዚህ ክፉ ዘመን፣ ጥንቃቄ እንጂ የዋህነት አያዋጣም። መጽሃፉ እንደሚለው “ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ምንጭ ነው”።

4. የምዕራባውያን ግብዝነት እና ዝግ ህሊና (Western Hypocrisy and Close mindedness)

በቅኝ ግዛት ባህልና ፖለቲካ ተኮትኩቶ ያደገው የዘር መድሎና እራስን ከሁሉ በላይ የማድረግ የነጭ የበላይነት አስተሳሰብ (White Supremacy) እስካለንበት ዘመን ድረስ ከዓለማችን ፈጽሞ ሊወገድ ባለመቻሉ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ሰንኮፉ እንዳልፈረጠ እባጭ እዚህም እዛም ሲከሰት ይታያል። በመሆኑም ከዘረኝነት በሽታ እራሳቸውን ማላቀቅ ያልቻሉ አንዳንድ ምዕራባውያን በሚያስተዳድሩት ሃገር የሚፈጸም የራሳቸውን ጉድ አስቀምጠው በግብዝነት (hypocrisy) በሌሎች ልኡዋላዊ ሃገራት የውስጥ ጉዳይ ያውም “አፍራሽ በሆነ መልኩ” እጃቸውን በማስገባት ለመፈትፈት ይሞክራሉ። ለምሳሌ በተባበሩት የአሜሪካ መንግስታት (USA) የግዛት ክልል ውስጥ በርካታ የዘር መድሎና ኢሰባዊ ድርጊቶች ሲፈጸሙ ማየት የአደባባይ ሚስጥር ነው። እንግሊዞች በደቡብ አፍሪካ ተክለውት በሄዱት ዘረኝነት እና አፓርታይድን ጨምሮ በምዕራቡ ዓለም በሚኖሩ በጥቁር ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ላይ የሚፈጸሙ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች እና የዘር መድሎዎችን በተመለከተ የጥቁሮች መኖሪያ መንደሮችን (ጌቶ)፣ በአሜሪካና በአውሮፓ ወደሚገኙ እስር ቤቶች፤ ፍርድ ቤት፣ በስራ አካባቢ፣ በሆስፒታል እና በመሳሰሉት በጥቁር ህዝብ ላይ የሚፈጸም ስልታዊ የሆነ ዘረኝነት (Systematic Racism) ይታያል። በጠራራ ጸሃይ በየመንገዱ የሚፈጸም የፖሊስ ጭካኔ (Police brutality)፣ በት/ት ቤቶች እና በኳስ ሜዳ የሚታዩ በተለይም በአውሮፓ በሚጫወቱ ጥቁር ፕሮፌሽናል ኳስ ተጫዋቿች ላይ የሚደርስ አዋራጅ (derogatory) ስድቦች፣ በስራ አካባቢ የሚታዩ አድሎና እንደ ችሎታ ተገቢውን ቦታ አለመስጠት (Neglect and occupational inequality) ሌላው የዘረኝነት ማሳያ ነው። በአሜሪካ “Black lives Matter” የሚለው መሪ ቃል በፖሊስ የሚፈጸም ጭካኔን የሚቃወም፣ ለጥቁር ህዝብ ፍትህ የሚጠይቅ እንቅስቃሴ ነው። በ2020 በአሜሪካ ሚኒያ ፖሊስ በጆርጅ ፍሎይድ ላይ በአደባባይ በፖሊስ የተፈፀመ ዘግናኝ አረመናዊ ግድያ የችግሩን ግዝፈት በግልፅ የሚያሳይ ነው። ይሁን እንጂ የምዕራቡ ዓለም መንግስታት በታብዮ የራሳቸውን የቤት ጣጣ አስቀምጠው ከሞራልም ሆነ ከዓለማቀፋዊ ህግ ውጪ ያልፈለጉትን ሃገር መንግስት ለመቀየር የኢኮኖሚና የዲፕሎማሲ ጫና ያደርጋሉ። የምዕራቡ ስልጣኔ በገንዘብ፣ በሃብትና በቁስ የሚለካ እንጂ የመንፈስ ልዕልና የሌለው በመሆኑ ምዕራባውያኑ ሰባዊነት፣ ዲሞክራሲ፣ ፍትህን ከጥቅማቸው በኋላ የሚያዩት በሁለተኛ ደርጃ ነው። ከዚህም አልፎ ሰባዊ እርዳታን ለፖለቲካ ፍጆታ ወይም የደሃ ሃገራትን እጅ ለመጠምዘዝ ሲጠቀሙበት ይታያል። ለምሳሌ አሜሪካ ታላቅ ሃገር ሆና ሳለ የግብጽ ጉዳይ አስፈጻሚ በመሆን ፕሪዝዳንት ትራምፕ በንቀት ተሞልተው ለግብጾች በቦምብ ግድቡን አውድሙት ሲሉ፣ አሁን ደግሞ የባይደን አስተዳደር ያለ ደረጃው እታች ወርዶ እየተርመጠመጠ ከአሸባሪው ወያኔ ጋር ሽርክና መፍጠሩ እጅግ አሳፋሪ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ እና ዶክተሩ መሪዋ (ድንቄም ዶክተር) - ከፋንታ ስለሽ

ባጠቃላይ የምዕራባውያን መንግስታት በባሪያ ንግድ እና በቅኝ ግዛት ከዛም በኋላ በድህረ ቅኝ ግዛት በአፍሪካ ህዝብ ላይ ከጥንት እስከ ዛሬ በርካታ ግፍና በደል ፈፅመዋል። በህዝቡ ላይ የስነ ልቦና፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ አስከትለዋል። ከነጻነት በኋላ አፍሪካውያን በሰላም እንዳይኖሩ አንዱን ጎሳ ከሌላው ጎሳ እርስ በርስ የሚያጋጭ የጊዜ ቦንብ እየቀበሩ፣ እንደ ወያኔ ዓይነት ያሉ የእነሱ ታማኝ ባንዳዎችን (Colonial Loyalist) አደራጅተውና በማይጨው ጦርነት ላይ እንዳደረጉት አስታጥቀው ስለሚወጡ አፍሪካ ሰላም ስለሌላት በከርሰ ምድሯ ውስጥ ወርቅ፣ አልማዝ፣ ነዳጅ እና የመሳሰሉ የተፈጥሮ ሃብት ይዛ እድገት ግን ማምጣት አልቻለችም። ለምሳሌ ከኮንጎ በዘረፉት የአልማዝ መአድን አውሮፓውያን ሲከብሩ እስካሁን ድረስ የኮንጎ ህዝብ ባዶ እግሩን የሚሄድ በድህነት የሚማቅቅ ጦርነት ያልተለየው ህዝብ ነው። ምዕራባውያን በአፍሪካ ህዝብ ላይ በፈጸሙት የበደል፣ የግፍና ኢሰባዊ ስራቸው ተጸጽተው እስካሁን በይፋ ይቅርታ አልጠየቁም። ከትናንት እስከ ዛሬ በጥቁር ህዝብ ብዙ መከራና እልቂት እንዳልፈጸሙ እና የአፍሪካን ነባር ስልጣኔን እንዳላፈራረሱ ሁሉ፣ ዛሬ እንደ ጲላጦስ እጃቸውን ታጥበው የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪና ተሟጋች መስለው ይቀርባሉ። እንደሚታወቀው ዘረኝነት እንደቀድሞ ጊዜ በምዕራባውያን መንግስታት ባይደገፍምና በህገ መንግስታቸው የተወገዘ ቢሆንም አሁንም ከነጭ የበላይነት ክፉ መንፈስ (አስተሳሰብ) የልተላቀቁ “ግለሰቦች” አይጠፉም። እነዚህ ለጥቁር ህዝብ መልካም አመለካከት የሌላቸው አዕምሮዋቸው በዘረኝነትና በጥቅም የተጋረደ፣ እንደ ጋሪ ፈርስ በአንድ አቅጣጫ የሚጋልቡ close minded/ arrogant ግለሰቦች በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በሃገራቸው ወሳኝ የመንግስት ስልጣን በእጃቸው ከገባ ደሃ ሃገራት በተለይም አፍሪካውያን በራሳቸው ጥቅምም ሆነ የውስጥ ጉዳይ ላይ የመወሰን ልኡዋላዊ መብት የሌላቸው እስኪመስል ድረስ ሰባዊ እርዳታን እንደ ፖለቲካ መሳሪያነት በመጠቀም፣ በረጅም እጃቸው ከአለማቀፋዊ ባንኮች እርዳታና ብድር እንዳያገኙ በማስደረግ፣ ሽብርተኛ ቡድኖችን አስታጥቀው ለእነሱ አንገዛም ያሏቸውን መንግስታትን እስከመቀየር ይደርሳሉ።

5. ማጠቃለያ፣

ሃገራችን ኢትዮጵያ አመሠራረቷ እና ያለፈችባቸው የተፈጥሮና የታሪክ ጉዞዎች ከሌሎች ሃገራት የተለየ፣ የራሷ የሆነ አሻራና ማንነት ያላት ጥንታዊትና ቀዳሚት ሃገር ናት። ጎሣና ብሔር ከመፈጠራቸው፣ ባህልና ቋንቋ ከመስፋፋታቸው፣ አሁን በዓለማችን የሚገኙት የተለያዩ የሃይማኖት ድርጅቶች ከመከሰታቸው በፊት የሰው ልጅ በዚህች ምድር አስቀድሞ በኢትዮጵያ ምድር ይኖር ነበር። በዘመናችን ሃያላን የሚባሉት እነ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን እና የመሳሰሉት መንግስታት ከመፈጠራቸው በፊት ኢትዮጵያ ከህዝቧ ጋር ነበረች። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በ1928 /ም በስዊዘርላንድ በጄኔቭ ከተማ በሚገኘው በሊግ ኦፍ ኔሽን (በተባበሩት መንግሥታት ማህበር) ጉባኤ ላይ ተገኝተው ወራሪው የፋሽስት ጣሊያን መንግስት የተባበሩት መንግስታት አባል የሆነችወን ኢትዮጵያ ሃገራቸውን መውረሩን እና ህዝቧንም በመርዝ ቦንብ እየገደለ መሆኑን በመግለጽ የመንግስታቱ ጉባኤው ወራሪውን የጣሊያንን መንግስት እንዲያወግዝና ከተገፋው ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን እንዲቆም ያደረጉት ንግግር ይታወሳል። በወቅቱ በኢትዮጵያ ላይ የተደረገን ወረራ ሳያወግዝ እና በህዝቧም ላይ የተፈጸመን የጅምላ ጭፍጨፋ በተመለከተ አድበስብሶ ማለፉ ዛሬም አሸባሪው ወያኔ በአማራና በአፋር ሰላማዊ ህዝብ ላይ የሚፈጽመው የጅምላ ጭፍጭፋ፣ ማፈናቀል፣ በህዝብና በመንግስት ተቋማት ላይ የሚደርሰው ውድመት ምዕራባውያን እንዳላዩና እንዳልሰሙ ሆነው ከአሸባሪው ትህነግ ጎን መቆማቸው በብዙ መልኩ ከ1928 /ም የጄኔቭ የሊግ ኦፍ ኔሽን ከወራሪው ፋሽስት ጣሊያን ጎን ከመቆም ጋር የሚመሳሰል ነው። እንደሚታወሰው ንጉሱ መልዕክታቸውን በንባብ በሚያሰሙበት ጊዜ የፋሽስት ጣሊያን ተወካዮችና ደጋፊዎቿ በጉባኤው ላይ ያሰሙት የነበረው ፉጨትና ረብሻ ስርዓት አልበኝነታቸውን ብቻ ሳይሆን ለጥቁር ህዝብ የነበራቸውን ንቀትና ዘረኝነት የሚያሳይ ጭምር ነው። ቀ//ስላሴ በጉባኤው ላይ “ዛሬ እኛ ነን ነገ ደግሞ እናንተ ናችሁ” (“It is us today, it will be you tomorrow”) ያሉት ትንቢት ሆኖ ብዙ ሳይቆይ በርካቶቹ የናዚ መሪ አዶልፍ ሂትለር በለኮሰው እሣት ተለበለቡ። የምዕራባውያኑ ጡንቻ እያረፈብን ያለነው ዛሬ እኛ ኢትዮጵያውያን ነን ነገ ደግሞ ሌሎች አፍሪካ ወንድሞቻችን ናቸውና ለወገኖቻችን ችግሩን በየሃገሩ ባሉ ኢምባሲዎችና ልኡካን ቡድን በመላክ የኢትዮጵያ መንግስት የማሳወቅ ሞራላዊ ግዴታ አለበት። ከዛም አልፎ በሰሜን አሜሪካ ለሚገኙ የጥቁር ህዝብ መብትና ነጻነት ተሟጋች የሰባዊ መብት ተቋማት እና ታዋቂ ግለሰቦች ችግሩ የቅኝ ግዛት ተቀጥላ መሆኑን ከስር መሰረቱ ማሳወቅ ያስፈልጋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ስምንት ጠቃሚ ነጥቦች ከእስራኤላውያን -ክፍል 3 (ዮፍታሔ)

እራሳቸውን የአለም ሰላም አስጠባቂ የዲሞክራሲ ፖሊስ ነን የሚሉት አሜሪካ መራሹ ምዕራባውያን መንግስታት እውነትን እያወቁ ለምን ከአሸባሪው ወያኔ ጎን በመቆም ኢትዮጵያን ከተባበሩት መንግስታት እስከ ዱቄት እና ዘይት አከፋፋይ የእርዳታ ሰራተኞች ድረስ ማጥቃት ፈለጉ ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማገኘት ምዕራባውያን የተገነቡበትን እሴት መረዳት ይጠይቃል። ከጥቅማቸው ውጪ ጆሮዋቸው አይሰማም። እራሳቸውን ከፍ የሚያደርግ እና ሌላውን የሚያሳንስ ግብዝ እና ዝግ ህሊና ነው ያላቸው። በቤተ መንግስትም ሆነ በቤተ መቅደስ ያሉት ቅድምያ የሚሰጡት ለጥቅማቸው ነው። በአንድ ወቅት የእንግሊዝ ጠ/ሚ “ቋሚ ጥቅም እንጂ ቋሚ ወዳጅ የለም” (“There are no permanent friends or permanent enemies, only permanent interests”) ብለዋል። በሃገራችን ደግሞ “ሆዳም ሰው ዘመድ የለውም” ይባላል። ለጥቅማቸው ያደሩ ናቸውና በተደጋጋሚ ተፈትነው ወድቀዋል። የትናንት ወዳጃቸውን በተመቻቸው ጊዜ የመክዳት፣ ውል የማፍረስና የማጭበርበር አስቀያሚ ታሪክ እንዳላቸው እንግሊዞችን በሂዎት ውል፣ ጣሊያኖችን በውጫሌ፣ አሜሪካኖች ደግሞ ኢትዮጵያ በዘይድ ባሬ በሚመራው በሶማሌ ተስፋፊ ሃይል በተወረረች ጊዜ ከንጉሱ ከቀ//ስላሴ ጋር የነበራቸውን ወዳጅነት በአፍጢሙ ደፍተው የወዳጃቸውን ሃገር ለማፈራረስ፣ ህዝቡን ለመጨፍጨፍ ለተነሳው ጠብ ጫሪ ለሆነው ለዘይድ ባሬ መንግስት የሎጂስቲክ እና የፖለቲካ ድጋፍ መስጠታቸው ይታወቃል። ይኸው ከቫይኪንግ የወረሱት የቀማኛ፣ የስግብግብ ባህሪያቸው ከቅኝ ግዛት እስካሁን ተከትሏቸው ዓለምን እያመሳት ይገኛል። ያለ እፍረት ቃል በቃል የሚሉት “national interestብሔራዊ ጥቅማችንን ለማስጠበቅ ነው እገሌ የሚባልን ሃገር የወረርነው ነው የሚሉት። ዘራፊውን እና ዘር አጥፊውን ህወሃት ጎን የቆሙት የግብፅን ጉዳይ ለማስፈጸም ወይም ከኢትዮጵያ በዝርፊያ ወደ ምዕራባውያን ባንኮች በህገወጥ መንገድ የተሻገረ በርካታ ቢሊዮን ዶላር ጋር በተገናኘ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተወሰኑ ባለስልታናት ስለተነካኩ ወይም ወያኔ ለጌይ፣ ሌዝቢያን እና ለሴጣን አምላኪ ኢሊሚናቲ ተባባሪ በመሆኑ እሱን ወደ ስልጣን በመመለስ በኢትዮጵያ ክፉ ልማድና ባህላቸውን ለማስፋፋት ስለሚያስችላቸው ብቻ ሳይሆን አሜሪካ መራሹ የምዕራቡ ጎራ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ምልክት የሆነችውን እና የአፍሪካ አንድነት (AU) መቀመጫዋን ኢትዮጵያን በማፈራረስ የአፍሪካን ህዝብ ቅስም ለመስበር ነው። ምዕራባውያን ይህንን ማድረጋቸው ደግሞ ትናንት ጥቁር ህዝብ የአዝጋሚ ለውጥ እድገቱን ያላጠናቀቀ ከነጭ በታች (inferior) ነው እያሉ ሲሳለቁበት የነበረውን እና በባርነት አግዘው ጉልበቱን በነጻ በዝብዘው ሃብት ያፈሩበትንና ከተሞችን ያስገነቡትን ህዝብ ዛሬ ደግሞ NeoLibralism በሚል አዲስ የማደናገሪያ ስም አፍሪካን ዳግም በመቀራመት የኢኮኖሚ/ የሃብት ሰቀቀናቸውን ሊወጡብን እየተረባረቡ ይገኛሉ።

አስመሳይና የተነቃበት አይን አውጣ ብልጣብልጥ የሆኑት ምዕራባውያን ለእነሱ ዲሞክራሲ፣ ሰብአዊነት፣ ፍትህ፣ እውነት ወዘተ ከጥቅማቸው በኋላ የሚመጣ መሆኑን ከተረዳን የራሳችንን የቤት ስራ ነው መስራት ያለብን። በአሁኑ ሰዓት በቅድሚያ ከኛ የሚጠበቀው ሃገራችንን ከጅቦች ማስጣል ነው። ሃገራችን ዙሪያዋን በችግር በተከበበችበት በዚህ ክፉ ጊዜ የእነሱን እኩይ ሃሳብ ለመፈጸም ለሃጫቸውን ሲያዝረከርኩ የሚውሉ እንደ ኦነግ አይነት opportunists ብዙ ናቸው። ወያኔ ሞራል የሌለው ከሃዲ የወንጀለኞች ስብስብ በመሆኑ ከተጸነሰበት ቀን ጀምሮ የንፁሃንን ደም ሲያፈስ፣ የኢትዮጵያን ሃብትና ንብረት ሲዘርፍ የኖረ ስጋ የለበሰ ሴጣን ነው። የወያኔ የጥፋት አጋር የሆነው ኦነግ በርካታ ኦሮሞ ወገኖቻችንን በክፉ ጥላቻ የመረዘ፣ ሃገራችንን በሃሰት ትርክት የበከለ የክፉዎች ስብስብ ነው። ተጨቆንኩ ብሎ ጭቆናን የሚፈጽም በቀለኛ እንጂ የፍትህና የነጻነት ታጋይ አይደለም። ኦነግ ከ1982 /ም በአሶሳ በንጹሃን ላይ ከፈጸመው ጭፍጨፋ ጀምሮ ይኸው እስከዛሬ ድረስ ጭካኔውን በመቀጠል እጁ በንጹሃን ደም እንደተጨማለቀ ይገኛል። አሁንም በህይወት ያሉት የኦነግና የወያኔ መስራቾች እኛ የታገልነው መብታችንን ለማስከበር እንጂ ሌላውን ህዝብ ለመግደል፣ ለማሰቃየትና ለመጨቆን አይደለም ሲሉ አለመሠማታቸው መጀመሪያም ወደ ትግል የገቡት በበቀልና በእልህ ተነሳስተው እንጂ ለፍትህ፣ ለዲሞክራሲና መብታቸውን ለማስከበር አለመሆኑን ያሳያል። መብት ለማስከበርማ ሂሳብ ማወራረድ ምን አመጣው፣ ችግር ካለም ማስተካከል ሲቻል 115 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላትን ሃገር ሲኦልም ቢሆን ገብተን ኢትዮጵያን እናፈራርሳለን ባልተባለ ነበር።

በመሆኑም ሃገራችንን እንወዳለን፣ ኢትዮጵያዊ ወገናችን የሶሪያና የየመን እጣ እንዳይደርሰው የምንፈልግ ሁሉ ወገባችንን ታጥቀን ዋጋ እንደከፈሉልን አባቶቻችን እኛም በተራችን ነጻነታችንን በትግላችን ከማረጋገጥ ውጪ አማራጭ የለንም። በሃገራችን እና በወገናችን ላይ ከውስጥም ከውጭም የተከፈተውን ጦርነትና ሃገር የማፍረስ፣ ህዝብን የመበተን የጥፋት ዘመቻ ሁላችንም ባለን ሙያና አቅም የምንችለውን ሁሉ በማድረግ ኢትዮጵያን ከመፍረስ፣ ወገናችንን ከስደትና ከስቃይ መታደግ የግድ ይለናል። ከልማት ህልውና ይቀድማል፣ ሃገራችን ነጻ ከወጣች በኋላ ወደ ልማቷ እንመለሳለን።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

ደረጀ ተፈራ

ምንጭ፣

  1. “The Story of the World” (W.B. Bartlett, 2014)
  2. “A Short History of Europe” (Simon Jenkins, 2018/ 2019)
  3. “Civilization – The West and the Rest” (Niall Ferguson, 2011)
  4. Encyclopedia Britannica”
  5. ወቅታዊ ታማኝ ዜናዎችና የተለያዩ የመረጃ ምንጮች ፣

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.