በዚሁ ዘ–ሐበሻ ድረ ገፅ ‹‹ከዱቄት እስከ ሰብዓዊ አንበጣነት›› በሚል ርዕስ፤ መነሻውን ትግራይ ያደረገው ወራሪ ኃይል፤ ከዚህ ቀደም በተበተነው! በአሸባሪው ህ.ወ.ሓ.ት. ‹‹የዱቄት ብናኝ›› የሚመራ ኃይል መሆኑን! በግልፅ አሰቀምጫለሁ፡፡ መፍትሄውም ይህን ‹‹የዱቄት ብናኝ›› ለማክሰም ‹‹ለይቶ የመምታት ስልት›› መከተል እንደሚገባ፤ በዱቄት ብናኙ ለሚመራው ኃይል ማለትም ለሰብዓዊ አንበጣው ‹‹ተገቢ ቅጣት›› ለመስጠትም! ‹‹ሰብዓዊ ድሮን›› የመሆን አማራጭነትን ጠቅሻለሁ፡፡
ሰሞኑን ደግሞ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መንግስት ‹‹እውነት ነው›› ወይም ‹‹አይደለም ብሎ›› አቋሙን ባልገለፀበት ሁኔታ፤ ‹‹ድርድር›› በሚል ሥም! እንደኩታ በርካታ ቦታ የሚተጣጠፉ መረጃዎችና ሀሳቦች እየወጡ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ መረጃዎች በቀጥታ በሚመለከታቸው አካላት፤ ቁርጥ ውሳኔ ላይ የተደረሰባቸው ቢሆኑም ባይሆኑም፤ ‹‹ድርድርማ አይታሰብም!›› ብሎ ማሰብን ከማቋረጥና ከማስቆም ይልቅ! ምን የሚሉት ድርድር? የሚል ጥያቄ፤ በሀሳብ ደረጃ እያነሱ መጣል የተሻለ ይሆናል፡፡ ምን ማለት ነው?
መስመር!
የኢትዮጵያን ሕዝብ መከራውን ካሳየው አንዱ! ‹‹መስመር›› የሚባለው ሕገ–ወጥ የፖለቲካ አኗኗር ዘይቤ ነው፡፡ ይህ ‹‹ሕገ–ወጥ የፖለቲካ አኗኗር ዘይቤ›› በአጭሩ ሲገለፅ ‹‹የአዋቂዎች ድንቁርና›› ይባላል፡፡ ይህን እውነት ለመረዳት ብዙ ርቀን መሄድ አያስፈልገንም! አሸባሪው የህ.ወ.ሓ.ት. ቡድን ለ27 ዓመታት የኢትዮጵያን ሕዝብ በግድያ፣ በአፈና፣ በዝርፊያና በጭቆና! ፍዳ እና መከራውን ያሳየው! በዚሁ ‹‹መስመር›› በሚባል ድንቁርና ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍዳና መከራ አንገሽግሾት! በመጋቢት 24/2010 ማዕበል አሸባሪውን ቡድን ጠራርጎ ትግራይ ክልል ቢያላትመውም፤ የሽብር ቡድኑ ተላትሞ ራሱን በሳተበት ክልል ሆኖ ‹‹የጥፋት መስመር›› ማስመሩን አልተወም፡፡ ለዚህ ነው አሸባሪ ቡድኑ ጥቅምት 24/2013 ሠሜን እዝ በሚገኘው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መከላከያ ሰራዊት ላይ! የተቀናጀ የሽብር ጥቃት የፈፀመው!!
በርግጥ! የህ.ወ.ሓ.ት. ቡድን ሰሜን እዝ ላይ ለፈፀመው የሽብር ጥቃት፤ በኢትዮጵያ ሕዝብና ተቋማት ፈጣን የአፀፋ ምላሽ ተሰጥቶት፤ በዕብደት ሲጭረው የነበረውን ‹‹አብዮታዊ የጥፋት መስመር›› ዳግመኛ እና ጨርሶ እንዳይመራበት ተደርጓል፡፡ ነገር ግን ይህም የአፀፋ ምላሽ! ልክ እንደመጋቢት 24ቱ ማዕበል! የሽብር ቡድኑን ሌላ ‹‹የጥፋት መስመር›› ከማስመር አላስቆመውም፡፡ ለዚህ ነው! በፖለቲካ ውስጥ የሚገኘው መስመር! ‹‹ሕገ–ወጥ የአኗኗር ዘይቤ›› እና ‹‹ሕዝብን ለመከራ የሚዳርግ›› ነው የሚባለው፡፡ መፍትሄውም በፖለቲካ ውስጥ የተሰመረን! የትኛውንም ‹‹የጥፋት መስመር›› ማስቆም ነው!!
የጥፋት መስመርን ማስቆም!
የመዲናችን አዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ፤ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በዚህ ሣምንት (ሰኞ) የህወሓትን የሽብር ቡድን አስመልክተው ሲናገሩ፤ ‹‹መጋቢት 2010 ህ.ወ.ሓ.ት. በሕዝባዊ ቁጣ ከፌዴራል ሥልጣኑ ተባርሮ፤ ብልፅግና ፓርቲ ሲመሠረት፤ ህ.ወ.ሐ.ት.ን እንደፓርቲ አትኑር ያለው አካል የለም›› የሚል ሀሳብ ሰንዝረዋል፡፡
ወ/ሮ አዳነች በዚህ ንግግራቸው ‹‹ህ.ወ.ሓ.ት የትግራይን መንግስት የማቋቋም ፍላጎት ቢኖረው እንኳ፤ በሕገ–መንግስት የተቀመጠ አሠራር እያለ፤ የሕዝብ እልቂትና ሀገራዊ ውድመት በሚያስከትል መንገድ፤ ፍላጎቱን ለማስፈፀም መሞከሩ ስህተት ነው›› የሚል ሀሳብ አክለውበታል፡፡
ይህ የክብርት ከንቲባዋ ንግግር! ከአሸባሪው የህ.ወ.ሓ.ት. ቡድን ጋር ስለሚደረገው ‹‹ድርድር›› ፍንጭ የሚሰጥ መስሎ ሊታይ ይችላል፤ ነገር ግን መዘንጋት የሌለበት! አሸባሪው የህ.ወ.ሓ.ት. ቡድን ከውስን ምዕራባውያንና የአረብ ሀገራት ጋር ተማምሎ፤ እንደአዲስ ያሰመረውን ‹‹የጥፋት መስመር›› የሚያስተናግድ ድርድር! በኢትዮጵያ መርህ ውስጥ የለም፡፡ ምን ማለት ነው?
ትጥቅ የማስፈታት ድርድር!
የመጋቢት 24/2010 ለውጡን ተከትሎ በኢትዮጵያ የሚገኘው ተጨባጭ እውነታ፤ ‹‹የጦር ታጣቂ የሆኑ›› የፖለቲካ ድርጅቶችን መኖር የሚፈቅድ አይደለም፡፡ በተጨማሪም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መንግስት ይህን በሚመለከት! ‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች የጦር ታጣቂነት›› ስህትት /ወንጀል/ መሆኑን የሚገልፅ አዋጅ በቅርቡ እንደሚያወጣ፤ አዋጁንም በመላው ኢትዮጵያ ተፈፀሚ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡ ሀገርን የመታደግ /የህልውና ዘመቻው/ አንዱ አካል አድርጎም! ያካትተዋል ተብሎ ይታመናል፡፡
የኢፌዴሪ መንግስት ይህን አዋጅ ተፈፃሚ ለማድረግ መንቀሳቀሱ! የድርድር አይቀሬነት ከመጣ! ‹‹እንደፓርቲ›› እና ‹‹ታጣቂ›› ከሚንቀሳቀሰው አሸባሪው የህ.ወ.ሓ.ት. ቡድን ጋር፤ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መንግስት የሚያደርገው ድርድር! ‹‹ተኩስ የማቆም እና ፓርቲውን ትጥቅ የማስፈታት ድርድር›› ላይ እንዲወሰን ያደርገዋል፡፡ ምክንያቱም! ‹‹አዋጁ›› የፓርቲ ‹‹መስመር›› ሳይሆን! የኢ.ፌ.ዴሪ. ‹‹መንግስት›› እና ‹‹ሕዝብ›› ሕግ በመሆኑ ነው፡፡
‹‹ተኩስ በማቆም እና ፓርቲውን ትጥቅ በማስፈታት›› ላይ ተመርኩዞ የሚካሄደው ድርድር፤ የህ.ወ.ሓ.ት.ን የሽብር እንቅስቃሴ ከማስቆም ባለፈ፤ በትግራይ ክልል ሕዝብ በሕግ አግባብ የተመረጠ ፓርቲ እስከሚኖር ድረስ! ‹‹ክልላዊ የሽግግር አስተዳደር እንዲቋቋም›› እና በክልሉም ‹‹ሠላም እንዲሰፍን›› ምቹ መደላድል የሚፈጥር ይሆናል፡፡
ቀጭን መጠቅለያ!
‹‹ትጥቅ የማስፈታት ድርድርን›› ሕጋዊ መሠረት አላብሶ መጓዝ! በአሜሪካን ፕሮጀክት ነዳፊነት እና ስኬት ባላገኙ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች የሚራመደውን፤ ‹‹በኢትዮጵያ ጊዜያዊ የሽግግር መንግስት ማቋቋም›› የተሰኘውን እንቅስቃሴ ‹‹በነበር›› እንዲቀር ያደርገዋል! ከዚህ አንፃር ‹‹ተመራጭ ስልት›› ሆኖ ይታያል፡፡
የፓርቲነት፣ የታጣቂነት እና የአሸባሪነት ቁመናውን በአንድነት አዋህዶ! በኢትዮጵያ ከሚንቀሳቀሰው የህ.ወ.ሓ.ት. ቡድን ጋር የሚደረግ ድርድር ካለ! ‹‹ትጥቅ የማስፈታት መርህ›› ላይ ብቻ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል! የሚባልበት ዋነኛው ምክንያት!! ይህ የሽብር ቡድን ከዚህ ቀደም ‹‹ሥልጣን የያዝኩት በ60 ሺ የትግራይ ወጣቶች መስዋዕትነት ነው›› በሚል ሰበብ፤ ኢትዮጵያና ሕዝቧ ላይ 27 ዓመታት ሙሉ ያደረሰውን በደል፤ ጨርሶ የማንዘነጋው በመሆኑ ነው፡፡
ያለመዘንጋት ብቻ ሳይሆን! አሁን በሽብር ተግባር እያለ አስገድዶ በማገዳቸውና ባስፈጃቸው የትግራይ ክልል ሟቾች ሥም! አሸባሪው ህ.ወ.ሓ.ት. በኢትዮጵያ ሊያስከትል የሚችለው ጥፋት! ከዚህ ቀደሙ የከፋ እንደሚሆን በርካታ ማረጋገጫዎች በመገኘታቸው ነው፡፡ ለዚህ ነው ‹‹ድርድር›› ካለ! ‹‹አሸባሪውን ህ.ወ.ሓ.ት. ትጥቅ የማስፈታት ድርድር›› ብቻ እንዲሆን የሚመከረው!!
ሠላም ለኢትዮጵያ ሠላም ለአፍሪካ
ቴዎድሮስ ጌታቸው
/ደራሲና የፖለቲካ ተመልካች/
ድሬዳዋ
ማስታወሻ፡ በአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ ላይ የሚያተኩረውን መጽሐፍ በቅርቡ ለሕዝብ ይፋ እንደማደርግ ቃል ገብቼ ነበር፤ ነገር ግን በድሬዳዋ አስተዳደር መጥፎነት እና አቅም በማጣት፤ መጽሐፉን ማሳተም ያልተቻለኝ መሆኑን፤ ይቅርታ ከታከለበት አክብሮት ጋር አሳውቃለሁ፡፡