አማራም ሆነ ትግሬ ሆኖ መወለድ ወንጀል አይደለም! – ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

ሀገራችን ልትወለድ ምጥ ላይ ናት፡፡ በምጥ ጊዜ ብዙ የሚጠበቁና የማይጠበቁ ችሮች መከሰታቸው ያለ ነው፡፡ ከበርካታ ዓመታት አስጨናቂ እርግዝና በኋላ የምትገላገለው ሀገራችን ደግሞ በችግሮች ብዛትና በከበቧት አዋላጆች የጤንነት ሁኔታ አጠራጣሪነት በጣም የምትታወቅ መሆኗ ግልጽ ነው፡፡ በችግሮቻችን ዙሪያ የሚሰማኝ ባገኝ ጥቂት እውነቶችን ልናገር፡፡

አማራ ወይ ትግሬ ልሁን ብሎ አማርኛ ወይ ትግርኛ ከሚናገሩ ቤተሰቦች ለመወለድ ፈጣሪን የጠየቀ አንድም ዜጋ የለም፡፡ ከመወለድ በፊት ምርጫ የሚሰጥ ቢኖር ኖሮ የገዛ የትውልድ ቀየውን ጨምሮ በመላዋ ኦሮምያ የምትባል አዲስ ወያኔወለድ ግዛት ውስጥ ደረቱን በጥይትና አንገቱን በቆንጨራ ለመቀላት ፍላጎት ኖሮት በኢትዮጵያ ለመፈጠር የሚፈቅድ አንድም አማራ ባልኖረ ነበር፡፡ በበኩሌ በዚህች አሁን ተመሰቃቅላ በማያት ኢትዮጵያ ከምፈጠር ካናዳ ወይም ኖርዌይ ውስጥ መፈጠርን እመርጥ ነበር፡፡ ስለዚህም እየተገደልን ያለነው ወደንና ፈቅደን ባልተወለድንበት ብሔርና የግዛት ክልል መሆኑን ሁሉም ሊገነዘብ ይገባል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታም ሃዲያም ሆነ ኦሮሞ ወይም ሶማሊያም ሆነ አፋር መርጦ የተወለደበት ጎሣና ነገድ የለም፡፡ ጥቂት የአጋንንት ሥሪት የሆኑ ሰዎች ግን ለጥቅማቸውና ለሥልጣናቸው ሲሉ ያልሆነ ካርድ መዝዘው ዕድሜ ልካችንን ርስ በርስ ያባሉናል፤ ያቆራቁሱናል፡፡ ለነሱ ሲባል ሕዝቡ ምድራዊ ሲዖል ውስጥ ገብቶ እውነተኛውን ሲዖል በሚያስንቅ ስቃይ ውስጥ አሣሩን ያያል፡፡

ተረኝነት ያሰከራቸው ወገኖች ሰሞኑን እያደረጉት የሚገኙት ዘግናኝ ታሪክ የሀገራችንን ምጥ አበርትቶባታል፡፡ ዜጎችን በስምና መታወቂያ ላይ በሚገኝ የብሔር ፍረጃ መሠረት እየለዩ ፍዳቸውን በማሳየት ላይ ናቸው፡፡ ወያኔን ያኔ ገና በጧት በ1980ዎቹ እኩሌታ “ተው፣ ይሄ መታወቂያ ላይ ብሔር መጻፍ ያጨራርሰናልና ይቅር” ብንል በጥጋባቸው ማየል የተነሣ አልሰሙንም፡፡ እነሱ በህግ ያስቀመጡት ዘረኝነት እነሱን ከሀብትና ከሥልጣን ማማ አስፈንጥሮ ከጣለም በኋላ ጦሱ ለተራው ዜጋ ተርፎ ይሄውና አሁን በሰላም የሚኖረው ሐጎስ በስሙ ምክንያት ብቻ ከባለቤቱ ወ/ሮ ሸዋነሰሽ ጋር እየተሳቀቀ እንዲኖር ተገዷል፡፡ አጥፊው ፍትዊ እያለ፣ አጥፊዋ አብረኸት እያለች … በነሱ መዘዝ ከምኑም ከምኑም የሌሉበትና ኢትዮጵያዊነታቸውን ብቻ ይዘው የሚኖሩትን ተስፋጋብርንና አምለሰትን እያሳደዱ ስማቸው ትግሬነትን በማጣቀሱ ብቻ እነሱን ማሰርና ለከፍተኛ እንግልት መዳረግ ኢትዮጵያዊነትን የማስካድና ወያኔነትን በግድ እንዲቀበሉ የማድረግ ታላቅ ሤራ ነውና በቶሎ መቆም አለበት፡፡ ኢትዮያዊነትን ደግሞ ሰጭም ሆነ ነሺ የለም፡፡ ኢትዮጵያዊነት የቡና ቁርስ ወይም የጓሮ እሸት አይደለምና ማንም እየተነሣ ለማንም የሚቸረው ወይም የሚነፍገው የስጦታ ዕቃ አይደለም፡፡ ሲልቪያ ፓንክረስትን የመሰሉ እንግሊዛውያንና በርካታዎቹ ጃማይካውያን በመወለድ ሳይሆን በምርጫቸው ከሀገራቸው አስበልጠው ያከበሩትን፣ የወደዱትንና የሆኑትን ኢትዮጵያዊነት የጠሉት ጠልተው ይካዱት እንጂ የተወለዱበትንና እትብታቸው የተቀበረበትን ምድር ሊያስክድ የሚነሳ አካልም ሆነ ግለሰብ ሊኖር አይገባምና ከዚህ ብልግና መቆጠብ ያለባቸው ሰዎች በአስቸኳይ ልብ ይግዙ ለነገሩ ጀምበራቸው እያቆለቆለች በመሆኗ የነዚህ ወገኖች ጉዳይ በቅርብ መልስ ያገኛል፡፡ የሆኖ ሆኖ ግን አሁን በብዙ ቦታ እያየነው ያለው እውነታ ከዚህ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ በሀሰት ሰውን ወደ እሥር ማጋዙ ሁለትም ሦስትም መልክ አለው፡፡ አንደኛው ባለፉ ሥርዓቶች እንዳስተዋልነው ባልን አስሮ ሚስትን ለማባለግ እና/ወይም ጉቦ ለመቀበል፣ ሁለትም በተሳሳተ ጥቆማና በቂም በቀል ሰውን ይዞ ለማሰቃየት፣ ሦስትም በፍተሻ መሣሪያ ማግኘት ሳይችሉ ሲቀሩ ባለጌ ፖሊሶች ሊያስሩት በሚፈልጉት ሰው ኪስ ውስጥ በሥውር ሀሽሽ አስቀምጠው እንደሚያስሩት ሁሉ በተመሳሳይ ሁኔታ በንጹሓን ትግሬዎች ቤት ሽጉጥ ወይ ሌላ መሣሪያ እንደተገኘ በማስመሰል ራሳቸው ባስቀመጡት መሣሪያ ሰዎቹን አስገድደው በመውሰድ አስረው ለማሰቃየት …. ነው፡፡ ሁሉም ቂልነት ነው፡፡ ወር ተራውን ጠብቆ ለሁሉም ይደርሳ

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከኦሮሙማው የፋሽስት መንግሥት ጋር ድርድር አይሞከር፤ ለፋሽስቶች ድርድር ጠላቶቻቸውን አዘናግቶ ማጥፊያ መሳሪያ ነውና!!

፡፡ የትናንት አሳሪና ገራፊ ዛሬ ምን እየደረሰበትና በምን ደረጃ ላይ እንዳለ እያየን ነው፡፡ አማራው ከትግሬው፣ ትግሬው ከአማራው፣ ኦሮሞው ከትግሬው፣ ጉራጌው ከኦሮሞው …. ከትናንቱ ገና ያልጠገገ ቁስላችን ካልተማረ “አንዱ በአንዱ ሲስቅ ጀምበር ጥልቅ” እንዲሉ ነውና ተረግመናል ከማለት ውጪ ሌላ ቃል የለንም፡፡ አእምሮ የተፈጠረው ለማገናዘብ ነው፡፡ እሳቱ ራሳችንን እስኪለበልበን የእሳትን አቃጣይነት ብዙዎቻችን አሁን አሁን ምናልባት ሁላችንም አንረዳም፤ የድንቁርናዎች ሁሉ ቁንጮ በሀገራችን እየታዬ በጥቂቱም ቢሆን እናስተውላለን የምንል ወገኖች በጅልነታችን ተሳቅቀን ልንሞት ነው፡፡

በምሣሌ ልንገርህ አንድ አካባቢ ሰዎች ሲጫወቱ ጆሮየን ጣል አድርጌ የሰማሁት ነው፡፡ ይህን ታሪክ የምታነቡ የሥርዓቱ ሰዎች ደግሞ ለተጨማሪ የበቀል ስህተት እንዳትነሳሱና ሰዎችን እንዳትጎዱ በምታምኑት እማጠናችኋለሁ፡፡ ስህተትን ማረም እንጂ በስህተት መንገድ መመላስን መምረጥ ተገቢም አስተማሪም አይደለም፡፡ ለማንኛውም ፖሊሶች በጥቆማ ይሁን በጥርጣሬ ወደ አንድ ትግሬ አረጋዊ ቤት ለፍተሻ ይሄዳሉ፡፡ ሰውዬው “ከዳዊት በስተቀር ምንም ነገር አታገኙም፤ ግን እንደፈለጋችሁ ፈትሹ፤ ግዴለም” ብለው እንዲፈትሹ ወደቤት ያስገቧቸዋል፡፡ ፖሊሶቹ ሁሉንም የቤቱን ግቢ ፈተሹ፤ ምንም አላገኙም፡፡ ግን ሁለት ሽጉጥ አንዳገኙ በመናገር ሰውዬውን “ይቀጥሉ!” ይሏቸዋል፡፡ ሰውዬውም ራሳቸውን ያውቁ ነበርና ይጮሃሉ፡፡ ጎረቤት ይሰበሰባል፡፡ አረጋዊው ብሶታቸውን ባደባባይ ይናገራሉ፡፡ ከፖሊሶቹ የአንደኛው የሽጉጥ ማኅደር ባዶውን ሆኖ የታየው አንዱ ጎረቤት “እንዴ! ሽጉጥህ የት አለ?” ቢለው ቢሮ እንደተወው ይነግረዋል፡፡ የሌላኛው ፖሊስም የሽጉጡ ሰገባ ባዶ ነበር፡፡ ሽጉጦቹን ያስቀመጡት ፖሊሶቹ ነበሩ፡፡ ሕዝቡ ተጯጩኾ ሰውዬውን አስቀረ፡፡ በዚህ መልክ የሚሳደዱ ንጹሓን ትግሬዎችን ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡

አንድ አካባቢ ሊፈትሹ የሄዱ ሁለት ፖሊሶች ደግሞ ልክ እንደዚሁ ሽጉጥ አገኘን ይሉና ትግሬውን ይወስዱታል፡፡ ዋናው የፖሊስ አዛዥ ሲጠይቀው እርሱ አንድ ህጋዊ ሽጉጥ እንዳለውና ያንንም ሽጉጥ ቢሮው ውስጥ ማስቀመጡን ለፈታሾቹ እንደነገራቸው ጠቅሶ ያን አገኘነው ያሉትን ሽጉጥ “እንዴትና የት እንዳገኙት ላሳይህ እችላለሁ” ብሎ ዋናውን አለቃ ወደ ቤቱ ይዞት ይሄዳል፡፡ ሰውዬው ቤቱን በካሜራ ጠምዶት ስለነበር የፖሊሶቹ ጉድ ታወቀና አጭበርባሪዎቹ ፖሊሶች ታስረው ለህግ እንዲቀርቡ ተደረገ፡፡ ይህ ጥሩ ነው፡፡ ይህን የመሰለ የቴክኖሎጂ እገዛ የማያገኙ ምስኪን ዜጎች ግን ይጎዳሉ፤ እየተጎዱም ነው፡፡

በተጨማሪም አንድ ሰው ለትዳር አጋርነት የሚመርጠው ቀልቡ የወደደውንና ያፈቀረውን እንጂ ዘርና ብሔር ተመርኩዞ ወይንም መንግሥት መርጦለት አይደለም፡፡ በዚህ መሠረት ባል ትግሬ ሚስት አማራ ወይ ኦሮሞ፣ ሚስት ኦሮሞ ባል ትግሬ ወይ አማራ የሚሆኑበት አጋጣሚ እጅግ ብዙ ነው፤ ላለፉት 30 ዓመታት ብዙ የዘረኝነት መርዝ ቢረጭብንም እስካሁን በጋብቻም ሆነ በአምቻና በመሳሰሉት ማኅበራዊ ትስስሮች እንደተጋመድን አለን፤ ለዚህም ነው ኢትዮጵያ ጠላቶቿ የጠበቁትን ያህል ልትፈርስላቸው ያልቻለችው ናላቸው ይፍረስና፡፡ ይህን ሁኔታ ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ከከፍተኛ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ጀምረን መታዘብ እንችላለን፡፡ ይህ የዘር ፖለቲካ የማይሠራው እንግዲህ ሁሉም በአንዱ፣ አንዱም በሁሉም ስለሚገኝ አፍንጫ ሲነካ ዐይን ማልቀሱ የማይቀር በመሆኑ ነው፡፡ “እንትን እንካ ጭን አትንካ” እንደማይባል መቼም ለአቅመ አዳም ወሔዋን የደረሰ ሁሉ ያውቀዋል፡፡ ስለዚህም ነው ይህ ክርፋታም የዘር ፖለቲካ ኢትዮጵያን ለመሰለች አሁን ድረስ እርስ በርስ ለሚጋባና ለሚዛመድ ማኅበረሰብ አይበጅም የምንለው፡፡ ስለዚህም ነው ኢትዮጵያ ተኛች እንጂ አልሞተችም ብለን ትንሣኤዋን በጉጉት የምንጠብቀው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የፖለቲካዉን መስቅልቅል ተረድተህ ጽንፈኛ : ቁርጠኛ ብሎም ጦረኛ እስክትሆን ሀገር እና ህዝብም ከቶም አይኖርህም

የሰውነት ንቅሳቶችን በተመለከተም ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ ለምሣሌ የኔ የትውልድ አካባቢ እንደትግሬዎቹ ዐይንን ማነው ቅንድብን መበጣት የተለመደ ነው፡፡ የዐይን ህመምን ለመከላከል ተብሎ ነው የምንበጣው እንጂ ትግሬ መሆን አምሮን አይደለም መሆን ቢያምረንም መሆን እንችላለን መብታችንም ነው፡፡ በመሆኑም ቅንድቡን የተበጣ ሁሉ ወያኔትግሬ ስለሆነ ይታሰር ቢባል ስህተት ነው፡፡ ከዚህ ከዚህ ዓይነቱ ኋላ ቀርነት እንውጣ እባካችሁን፡፡ እስኪ ሰው ሰው እንሽተትና ሌላው ዓለም ይግረመው!!

የማይካድ ነገር አለ፡፡ እጅግ ብዙ ትግሬ በጥንቱ አነጋገር የእናት ጡት ነካሽ ሆኖና በወያኔ የዘመናት ስብከት ተጠልፎ እናት ሀገሩንና የገዛ ኢትዮጵያዊ ወገኑን እየጎዳ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በየቦታው ሲፈተሸ እንደሚገኘው የመሣሪያና የሸር ብዛት ቢሆን ኖሮ እኮ አዲስ አበቤዎች አንድም ቀን ባላደርን፡፡ በአንድ ወገን ወያኔዎች በሌላ ወገን ደግሞ ኦነግ ሸኔዎችና የነሱ ጌቶች የሆኑት አቢይና ሽመልስ አብዲሣ ሰቅዝው እንደመያዛቸው ፈጣሪ ባይታደገን ኖሮ ዕድሜያችን ከአንድ ሐሙስ ባልዘለለ፡፡ ግን ፈጣሪ ይመስገን እስካሁን አለን አለን ማለት ከቻልን፡፡ ለአዲስ አበባ ጸልዩ!! ብዙ ክፉ ዐይኖች አርፈውባታልና ለዚች ከተማ እንጸልይ፡፡ ወደፍርስራሽነት ሳይለውጡን ፈጣሪ እነሱን እርስ በርስ አፋጅቶ ዐመድ እንዲያደርግልን እንጸልይ፡፡ እርሱ ይችላል፡፡

ትንሽም ብትሆን ኅሊና ያለቻችሁ የመንግሥት የፀጥታ አካላት እባካችሁ ከዚህ በላይ የጠቀስኩትን ችግር ተነጋገሩበትና መፍትሔ ፈልጉለት፡፡ ጊዜ አትስጡት፡፡ ይህን ሰበብ ተጠቅመው ሌት ተቀን በሚቃዡበት ሀብት ለመክበርና በበቀል ስሜት የሚጠሏቸውን ለመጉዳት የሚጥሩ የሞራል ዕሤትና ሃይማኖት የሌላቸው የአእምሮ ጉንዲሾች ሞልተዋልና ምስኪኖችን ከነዚህ የቀን ጅቦች ታደጓቸው፡፡ አንዳንድ መጥፎ አጋጣሚዎች ለባለጌዎችና ሀዘን አምላኪዎች ሠርግና ምላሽ ናቸው፡፡ አንድን ሰው በማሰር በሚቀበሉት ገንዘብ በአንዴ የሚከብሩ እንዳሉ ይነገራል፡፡ ጉቦና ሙስና ባህል ሆኗል፡፡ በገንዘብ መክበራቸው መልካም ሆኖ በሰው ደምና አጥንት መክበራቸው ግን የምድሩን ብቻ ሳይሆን የሰማዩንም ቤታቸውን የሚያዘጋ በመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረግ፡፡ ሰው አለሥራው አይታሰር፡፡ በሥራው አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በህጉ መሠረት ይሙት በቃ ይፈረድበት፡፡ ነገር ግን ገና ለገና ትግሬ ወይም አማራ ወይም ኦሮሞ ስለሆነ ብቻ ወይም ይህ ነገድ ወይ ያ ነገድ ይጠራበታል ተብሎ በሚታሰብ ስም ስለተጠራ ብቻ እየያዙ ማሰቃየት ወንጀልም ኃጢኣትም ነው፡፡ በስም ሰውን መፈረጅ እጅግ የወረደ አሠራር መሆኑን እንረዳ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በሳንሆዜ ከተማ ለወራት የታቀደው የወያኔ የማጭበርበር ሴራ በሚያሳፍር መልኩ ተጠናቀቀ

በዚያ ላይ አንድን ሰው በስሙ ብቻ ብሔሩን መገመት ይቻል እንደሆነ እንጂ በእርግጠኝነት ማወቅ በፍጹም አንችልም፡፡ ተሾመ አበበ የሚባ

ትግሬ ጓደኛ አለኝ፡፡ ሐጎስ ገመቹና አብርሃም ገመቹ የሚባሉ ሰዎች አውቃለሁ፡፡ ተስፋማርያምና ጆንሰን የሚባሉ ስሞች ለአኙዋኮችና ለኑዌሮች ብርቅ አይደሉም፡፡ አገሩ አበረ የሚባል ጉሙዝ መኖሩን ካላወቅን በርግጥም ስም አምላኪዎች ነን፡፡ ስም መጠሪያ እንጂ ከተጠሪው ሰውዬ ጋር የሚያገናኘው ምንም ዓይነት ባሕርያዊ ዝምድና የለውም፡፡ “ገመቹ” የሚል ስም ሲጠራ ልቡ በደስታ የሚዘልና በተቃራኒው “ፍስሐ” ወይንም “ሐጎስ” ሲባል በንዴት የሚንጨረጨር ሰው ካለ በሽታው ብሶበት ሀገር ምድሩን ሳያቃጥል በጊዜ ወደ ሐኪም ቤት ይወሰድ፡፡ ባጠቃላይ ቋንቋም ሆነ በተለይ ስም የሰው ልጅ መገልገያ እንጂ እንደጣዖት የምናመልከው አይደለምና ዐዋቂ ነን የምትሉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እባካችሁን ጠበንጃን ከነዚህ ዓይነት ደናቁርት እጅ አውጥታችሁ በተማሩና በሚያስቡ ወገኖች እጅ አስገቡ፡፡ ሲባል የሰሙትን ስም ለልጃቸው የሚሰጡ ብዙ ወገኖች አሉ፤ ዱሮም አሁንም፡፡ ያለንበት ውልየለሽ ዘመን ይመጣል ብላ ያልገመተችና ያልጠረጠረች ንጽሕት ኢትዮጵያዊት በጓደኛዋ ስም ልጇን “ጫልቱ” ብላ የምትጠራ አማራ ነበረች፤ ምንድን ነው ችግሩ? የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ስም እስከሰባተኛና 14ኛ ትውልድ ብንዳስስ ስንትና ስንት ጎሣና ነገድ ተሰባጥሮበት እናገኝ የለም እንዴ? ጋዲሣ የሚባል የአማራ ነገድ ተወላጅ ሀኪም ጓደኛ እንዳለኝ አሁን ትዝ አለኝ፡፡ ስለዚህ እባካችሁ በዚህ ተራ በሆነ የስም አሰጣጥ ሂደት ተነስተን ወንድምና እህቶቻችንን አናሰቃይ፡፡ የሰው መሣቂያም አንሁን፡፡ ስም ለውጦ ወንጀል የሚሠራ ሰው እንዳም እንወቅ በስስ ብልትህ ገብቶ ጉድ ይሠራሃልና ተጠንቀቅ!! ይህ የሚሆነው “ጉርሜሣን”ና “ጉተማ”ን ለቀህ “ግደይና”ና “አምባቸው”ን ስታሰቃይ የሚያይህ” ታዛቢ ነገ በልዩ መታወቂያ “ሁንዴሣ” ሆኖ ይመጣና ሰደቃህን በቁምህ ሊያበላህ ይችላል፡፡ እምልህ ገብቶህ ከሆነ በሥራ እንጂ በስም አትመን እያልኩህ ነው፡፡ በስምና በቋንቋ የሚያምን “ሰው” ከሰውነት ተራ የወረደ፣ ሃይማኖት የሌለውና አስተዳደግ የበደለው የመጨረሻው ደንቆሮ ማይም ነው፡፡ በአዲስ አበባ ውስጥና በአካባቢዋ የሚታየው ስምን መሠረት ያደረገ ተወርቶ የማያልቅ የነውር ሥራ አያቀባብርም፤ ይህ ጊዜ ማለፉ አይቀርም፡፡ ሲያልፍ ግን የማይሽር ጠባሳ ትቶ እንዳያልፍ ፊደል የቆጠራችሁ በተለይ ከአሁኑ አስቡበት፡፡ ነገ ማቄን ጨርቄን አይሠራም ይህ ዓይነቱ ሸውራራ አካሄድ ለወያኔም አልጠቀመም፡፡ እናም ይህን እንረዳ የሰዎች ችግር ስማቸው አይደለም ተግባራቸው እንጂ፡፡ አንድ ሰው ጥፋት ካለበትና ጥፋቱ በማስረጃና በመረጃ ከተደገፈ ማንም ዜጋ ከህግ በላይ ሊሆን አይችልምና በአግባቡ ወደ ህግ ቀርቦ በሥነ ሥርዓትም ተይዞ ሳይገረፍና ሰብኣዊ መብቱ ሳይጣስ ይዳኝ፡፡ እስኪ ሰው ለመሆን እንሞክር፡፡ ስሙ ማንም ይሁን ማን፣ ዘሩ ምንም ይሁን ምን …. ማንም ዜጋ መዳኘት ያለበት በህግ እንጂ በስሜትና በዘመን አመጣሽ የጎሣ ፖለቲካ አይሁን፡፡ ነገ ድራሹ የሚጠፋ ይህ ዘረኝነት አሁን ሊያሳብደን/ኝ ነው ወንድሞቼ ….

ሰላም ለኢትዮጵያ፡፡

https://amharic.zehabesha.com/a-short-get-bent-to-alex-de-waal/

 

3 Comments

  1. አንጀት አርስ ፅሁፍ፣ ፀሀፊዉንም መድረኩነም የኢትዮጰያ አምላክ ይጠብቅልን፣

  2. ውድ ዳግማዊ ጉዱ ካሣ፣
    ማርያም ወርዳ መሆን አለበት፤
    ይህን የመሰለ ቊምነገር ጽፈህ አንብቤ አላውቅም።
    በርታልን፤ ያለቺን አንዲት አገር ብቻ ናት፤
    አገራችን የሐጎስ ገመቹ አገር ነች!
    “በሥራ እንጂ በስም አትመን እያልኩህ ነው” ያልካት አንጀት አርስ አባባል ነች

  3. ደሴን ያየ ብዙ መማር አለበት ማንም የጁንታ ደጋፊ መኖር እንጂ በአዲስ አበባም ሆነ ሌሎች ክልሎች መሳሪያ መታጠቅ የለበትም:: ጀግኒት አዳነች አቤቤም ከተማዋን እያፀዳች ነው የኢትዮጵያ ህዝብ ታጋሽና ፍትሀዊ ነው እንደእነሱ አረመኔነት ቢሆን ብዙ እልቂት ይፈጠር ነበ: በእዲስ አበባ እንደ ጁንታው ርዝራዦች የተሞላቀቀ ህብረትሰብ የለም ለእነዚህ የሚያለቃቅሱ የጥቅም ተጋሪዎች ያሳዝኑኛል : ደሴ የነበረውን ክህደት ምንም ዋጋ የማይሰጡ ጥሩምባ ነፊዎች ናቸው:: አዳነች አቤቤ የአማራ ክልል መሪ ብትሆን ኖሮ ደሴ ክህደት አይፈፀምባትም ነበር: ወያኔ ከመቀሌ አይመጣልህም አዲስ አበባ ያለውን ርዝራዥ ካላፀዳህ ሀገር አይኖርህም:: ማፅዳቱ ይቀጥል !

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share