ትህነግ ሀገር የማፍረስ ዓላማውን ለማስፈፀም ሲል ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ በመላው ኢትዮጵያ ፖለቲካውንም ሆነ ኢኮኖሚውን በበላይነት ተቆጣጥሮት ህዝብና ሀገርን ሲመዘብር ቆይቷል፡፡ ለዓመታት የዘረፈውና የገደለው አልበቃ ብሎት በህዝብ ተገፍቶ ከስልጣኑ ከወረደ በኋላ ሀገሪቱን ወደለየለት ትርምስ ውስጥ ለመክተት በርካታ ኢ–ሰብዓዊ ተግባራትን ፈጽሟል፡፡
በተለይም በህዝብና በመንግሥት የተደረገለትን የይቅርታ ጥሪ ገፍቶ በመጣል የለውጡን ሃይል የሚያንኳስሱና የሚያጠለሹ ተግባራትን በማን አለብኝነት አጽሟል፡፡ በግልጽ ለህዝብ ያለውን ንቀት ያሳየበት ድርጊትም ፈጽሟል፡፡
አገራችን በለውጥ ምህዋር ከገባች በኋላ እንደአገር የተመዘገቡ የለውጥ ሂደቶችን ጥላሸት በመቀባት፤ በአንድ በኩል ትህነግ በህዝብ ከጸደቀው ህገመንግስት በተቃራኒ ህገወጥ አሰራሮችን በራሱ በመተግበር መልሶ ደግሞ መንግስትን በመውቀስ እረስ በእርሱ የሚጣረስ ተግባር ሲፈጽም ቆይቷል፡፡
በአገራችን ያለው ስርዓት አካታች እና ሁሉን አቃፊ በሆነ መልኩ መሆን እንደሚገባው ግልጽ አቋም በመያዝ ሲተገብር የነበረውን የፌዴራል መንግስት በመንቀፍ ትህነግ ስልጣን ይዞ በቆየባቸው ዓመታት በራሱ ሲተገቡ የነበረውን እኩይ ተግባር ሁሉ ለለውጥ ሃይሉ በመለጠፍ የፌዴራል ስርዓቱ ወደ አህዳዊ ስርዓት ተቀይሯል የሚል የተውረገረገ አስተያየት በመስጠት ሲያወናብድ እንደነበረ የሚታወስ ነው፡፡
የአሸባሪው ህወሃት ማብቂያ የሌላቸው የውሸት ትርክቶች የቱንም ያህል አደባባዮችን የሞሉ ቢመስሉም በስተመጨረሻው የቡድኑ ርካሽ ባህሪ መገለጫ ከመሆን ባለፈ በራሳቸው ቆመው ለመሄድም ሆነ ረጅም መንገድ ለመጓዝ አቅም እንደሌላቸው በተጨባጭ እየታየ መጥቷል፡፡
ትህነግ ዛሬም እንደኮሶ ከተጣባው አመሉ አልተላቀቀም፡፡ በእርግጥ ይላቀቃል ብሎ ማሰብም የዋህነት ነው፡፡ ይህ የሽብር ቡድን ዛሬም ዋነኛ ስልቱ ሐሰተኛ መረጃ በመፈብረክና በማሰራጨት ሐገርና ህዝብ እንዲታመስ ማድረግ ነው፡፡ ዛሬም የበሬ ወለደ መረጃ ማሰራጨት የህወሃት የሽብር ቡድን ህዝብ ለመነጣጠል ዋና ስልት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በተለይ በጦር ሜዳ ውሎ ተስፋ እየቆረጠ ሲመጣ፣ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻውን ዋና ሥራ አርጎ ቀጥሎበታል፡፡
በወገን ሃይል ድባቅ እየተመታ የሚይዘው የሚጨብጠው ያጣው የጠላት ሃይል ራሱን ከአሸናፊተን ማማ ላይ ሰቅሎ የፌደራል መንግስቱን ትዕዛዝ በሚመስል መልኩ ወደ ድርድር የማይገባ ከሆነ የያዝነውን ጦርነት እንደሚቀጥልበት አፈቀላጤዎቹ ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡
ይህ የሚያሳየው የሽብር ቡድኑ አቅሙ እየተዳከመና እየተመናመነ መምጣቱን ነው፡፡ ቀኝ እጄ ናቸው ብሎ የተማመነባቸው ሃይሎችም ከዚህ ውጭ ምንም ማምጣት እንደማይችሉ ተረድቶታል፡፡ በጦርነቱ ውስጥ አያሌ ንጹሃን ዜጎችን በጅምላ ይረሽናል፣ ይዘርፋል፣ ያሰቃያል፣ ህጻናትና ሴቶችን ይደፍራል፤ በህዝብ ሃብት የተሰሩ መሰረተ ልማቶችን ያወድማል፤ የሽብር ቡድኑ ፍላጎት ይህ ነው እንጂ ዳግም ተመልሶ የአራት ኪሎን ወንበር እንደማያገኘው እሱም ያውቀዋል፡፡
የትህነግ የሽብር ቡድን ስራዬ ብሎ በያዘው የፕሮፖጋንዳ ስራ ህዝብን በማደናገር አገር እንዳይረጋጋ ለማድረግ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡ ይህን ህዝብን የማደናገር የፕሮፖጋንዳ ስራ እስከመጨረሻው ማስቆም የሚቻለው ደግሞ የጠላት ሃይል የሆኑትን ቀንደኛ መሪዎቹ ካሉበት አድኖ ላይመለሱ እስከወዲያኛው መሸኘት ሲቻል አልያም አማራጭ በማጣት እጃቸውን ሲሰጡ ብቻ መሆኑን ተረድተን ይህ እስኪሆን ድረስ ይህ ሐሰተኛ መረጃቸው የማይቀር ስለመሆኑ የመጡበት የተሳሳተ የታሪክ መንገድ ያሳየናል፡፡
የትህነግ የሽብር ቡድን ሳይወዱ በግዳቸው የተከተሏቸውን ወጣቶች አጉል ተስፋ እየጋቷቸው ተገቢ ያልሆነ መስዋዕትነት እያስከፈሏቸው ይገኛሉ፡፡ በትግራይ ክልል አገር ተረካቢ ትውልድ እንዳይኖር ወጣት፣ ሴት፣ ወንድ ሳይሉ ወደ ጦርነት እየማገዷቸው ይገኛሉ፡፡
ለአንዳንዶቹ ጦርነቱን በድል ካጠናቀቅንና ስልጣን ከያዝን በኋላ የፈለጋችሁትን እናሟላላችኋለን እያሉ በመዋሸት፣ ሌሎችንም የስራና ስልጣን መነሻ ከእኛ ነውና የፈለጋችሁትን ስልጣን ይዛችሁ ያሻችሁን ታደርጋላችሁ እያሉ በባዶ ተስፋ ይሞሏቸዋል፡፡ እምቢ፣ አያሻኝም ያለ ወጣት ካለ ግን በቤተሰቦቹ ፊት ላይመለስ እንዲረሸን ይደረጋል፡፡
ኢትዮጵያውያን አሁን አንድ ሆነው ተነስተዋል፡፡ ትህነግ አንድ እንዳይሆን ሴራ ሲሸርብበት የነበረው ህዝብ ዛሬ አንድ ሆኖ ጠላትን ድባቅ እየመታ ነው፡፡ የፈራው አንድነት በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ጎልቶ መታየት ጀምሯል፡፡ ከጥንት ጀምሮ በሀገራቸው ጉዳይ የማይደራደሩት ኢትዮጵያውያን አገር ሊያፈርሱ የመጡ ጠላቶቻቸው ወኔና ብርታት ሆኗቸው ስለአገራቸው አንድ ላይ ቆመዋል፡፡
ዛሬ ላይ ከዳር እስከ ዳር እየተነቃነቀ ያለውን ኢትዮጵያዊነት ለተመለከተ የአሸባሪው ትህነግ ዕድሜ እያጠረ መምጣቱን ያሳያል፤ የጠላት ሃይል የንጹሃን ደም አስክሮት መቀበሪያ ጉድጓዱን እያፋጠን ነው፡፡