የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ:- ጥና! (በላይነህ አባተ)

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! የአድዋውና የአምስቱ ዘመን የቅኝ ገዥዎች ወረራ እንደገና መጥቶብሃል፡፡ የአሁኑን ወረራ ተበፊቶቹ የቅኝ ገዥዎች ወረራ የሚለየው የእጅ አዙር ወረራ መሆኑ ብቻ ነው፡፡ በበፊቶቹ ወረራዎች ባንዶች የቅኝ ወራሪዎች መንገድ መሪዎች፣ ጀሌዎችና እንቁላል ቀቃይዎች ነበሩ፡፡ ዛሬ ቅኝ ገዥዎች ሳይችሏት የኖረችውን ጥንታዊት አገር በቋንቋ ካራ አርደውና ትናንሽ አገር ፈጥረው ምስራቅ አፍሪካን እንደ ፈለጋቸው በአሽከርነት እስከ ዳግም ምጣት ሲያሽከረክሩ ለመኖር ባንዳዎችን በገንዘብ፣ በመሳሪያና በፕሮፓጋዳ በመርዳትና በማደራጀት እንደ አበደ ተናካሽ ውሻ ለቀውብሃል፡፡ ይህ ወቅት እንደ አምስቱ ዘመን ወረራ ጥናትን ይጠይቃልና ጥና!

በየትኛውም የወረራ ዘመን የዓለም ሕዝብ ተቅኝ ገዥዎችና ተባንዳዎች እንጅ ተኢትዮጵያ አርበኞችና ፋኖዎች ጋር የቆመበት ዘመን አልነበረም፡፡ እንደምናውቀውም የዓለም ሕዝብ ተጀርባችን አልቆመም ብለው ቅደመ አያቶቻችን ክንዳቸውም ሆነ ተስፋቸው አልዛለም፡፡ እንዲያውም በተቃራኒው የዓለም ሕዝብ ፍረደ፟ ገምድል አድሏዊነት የበለጠ ቅየው እንደተደፈረ አንበሳ አስቆጥጧቸው ራሳቸውን በጎዝ አለቃ በማደራጀት መንግስት ባልነበረበት ዘመንም የወራዎችን የጀርባ አጥንት ሰበረው እንዳባረሩ ታሪክ፣ድርሳናትና የዓይን ምስክሮች ይመሰክራሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! የእጅ አዙር ቅኝ ገዥዎች የሚመኙት በቋንቋ ክልል ታጥረህና ትናንሽ የመንደር አገር መስርተህ ሲጠሩህ አቤት ሲያዝዙህ ወዴት የምትል የዘላለም አገልጋይ እንድትሆን ነው፡፡ ቅድም አያቶች “አንተ ማነህ እኔን ማነኝ” አሻፈረኝ እያሉ ሲታገሉ የኖሩት ባርነትን፣ ሎሌነትና ክብር የለኝነት በመፀየፍ ነው፡፡ ባርነትና ክብር የለለሽነት የሚመነጩት ተማነስ፣ ተመበታተን፣ በክልል ተመታጠርና ትናንሽ የመንደር አገር ተመመስረትና አደራን ታለመወጣት ነው፡፡

የ”ዓለም መንግስታት ድርጅት” ነኝ የሚባለው የጉልበተኞች “ሕጋዊ” መሳሪያ ጨምሮ ሌላው ዓለም አቀፍ የስብአዊ ድርጀት ነኝ የሚለው አስመሳይ ድርጅት ሁሉ ፀረ ኢትዮጵያ አቋም የያዘው ለሰው ነፍስና ክብር አዝኖ እንዳልሆነ ተራሻችንም ሆነ ተዓለም ታሪክ እናውቀዋለን፡፡ ደጋግመው ራሳቸው እንደሚናገሩት ምዕራባውያን የሚረዱት ጥቅማቸውን የሚያስጠብቅላቸውን የሌላ አገር ባንዳ ብቻ ነው፡፡ ለጥቅማቸው ሳይሆን ለሰው ነፍስ ወይም ለሰብአዊ ክብር አዝነው ቢሆንማ በሰላሳ ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠመውን የዘር ፍጅትም አጣርተው ወንጀለኞችን ለፍርድ ያቀርቡ ነበር፡፡ ለሰው ነፍስ አዝነው ቢሆንማ ኖሮ የዘር ፍጅት የፈጠሙትን ድርጅት መሪዎች በየመስሪያቤቶቻቸው እየቀጠሩ አገልጋይ አያደርጉም ነበር፡፡ ለሰው ነፍስ አዝነው ቢሆንማ ኖሮ ሽብርተኞችን ለማደራጀት በአንቀልባ አዝለው እሽሩሩ አይሉም ነበር፡፡ ለሰው ልጅ መብት ተጨንቀውማ ቢሆን በሰላሳ ዓመታት ውስጥ ሕዝብ እየተጨፈጨፈ እሬሳው መሬት ላይ ሲጎተት፣ ወህኒ ገብቶ ቆዳው እንደ በግ ሲገፈፍና ብልቱ እንደ ሰንጋ ሲስለብ፣ እግሩ እንደ ግንድ ሲቆረጥና ዓይኑ እንደ ድንች እየተፈነቀለ ሲውጣ ጪጭ አይሉም ነበር፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኸረ በህግ አምላክ!!! - ከተማ ዋቅጅራ

ልብ እንበል! “የተባበሩት የዓለም መንግስታት ድርጅት ነን፣ የዓለም ሰብአዊ ድርጅት ነን፣ ዓለም አቀፈ የዜና አውታር ነን” ባይዎቹም ሆነ ሌሎች ለአስርተ ዓመታት ግፍ እንደ ዶፍ ሲወርድ ሲሸፋፍኑ ኖረው ዛሬ አፋቸውን እንደ ዓባይ በርሃ ቦርግደው የሚጮኹት በእርጉም ባንዳዎች በኩል የእጅ አዙር ቅኝ ገዥዎችን ተንኮል ለማስፈጠምና ጥቅማቸውን እስከ ዘላለም ለማስጠበቅ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! ይህ በቅኝ ገዥዎች የተሸረበ ተንኮልና ሼር ለኢትዮጵያውያን አዲስ ወይም እንግዳ ነገር አንዳልሆነ ታውቃለህ፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ዓይን ያዋጣ የቅኝ ገዥዎች ሸር መበጣጠስም ለኢትዮጵያውያን አርበኞች አዲስ ነገር እንዳልሆነ ትረዳለህ፡፡ ይኸንን ሸር አርበኛ ቅድም አያቶች በአንድነትና በጥናት በመቆም እንደበጣጠሱት ታውቃለህ፡፡ ይህ ትውልድ የዛሬውን ሸር በጥናት እንዲያከሽፍም ታሪክ፣ ያለፈው ትውልድና መጪው ትውልድ አደራ እንደጣሉብህ ትገነዘባለህ፡፡ ይኸንን መሰሪ የቅኝ ገዥዎች ተንኮል ያለከሸፈ የዛሬ ትውልድ አገሪቱን በአጥንቱ ካስማነትና በደሙ ምርግነት ገንብቶ ባለፈው ትውልድና ይህንን አኩሪ የኢትዮጵያ ታሪክ ለመረከብ በሚቋምጠው መጪው ትውልድ ሲወቀስ እንደሚኖርም ታውቃለህ፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! ጥና! ጥና! ጥና! ጉልበት ያለህ በጉልበትህ፣ ገንዘብ ያለህ በገንዘብህ፣ እውቀት ያለህ በእውቀትህ፣ ሁሉም ያለህ በሁሉም ሁሉም የሌለህ በእስተንፋስህና በፀሎትህ እርዳ፡፡ በውስጥም ሆነ በውጪ ያለህ ኢትዮጵያዊ “በልቶ መሞት” ተሚል የአሳማ ፍልፍና ራስህ አጽዳ! እንደ አድዋውና እንደ አምስቱ ዘመን እንኳን ሕዝቡ እንሰሳት ስንቅ በመጫን፣ ወንዞች የቅኝ ገዥዎችን ተላላኪ ባንዳ በማስመጥ፣ ስርጡ በማዳለጥ፣ ተራሮች በማንሸራተት፣ ጫካውና ዱሩ አርበኛና ፋኖ ምሽግ በመሆን ይሳተፉ፡፡ የዱር አራዊት የባንዳን መቀመጫ ይግመጡ፤ ይቦትርፉ፡፡ ካህናትም እንደ አቡነ ጴጥሮስ ምድሪቱ ለቅኝ ገዥና ለባንዳ እንዳትገዛ እንደገና ይገዝቱ፤ ታቦት ይዘውም ይዝመቱ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:   ዛሬም ዜሮ ሊያደርጉን የሚፈልጉ አሉና እንንቃ!( የኢትዮጵያ ችግር በዘመናዊ ፉከራ እንደ በጋ ጉም በን ብሎ አይጠፋምና !!)

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! ይህም በትግልህ ያልፋልና እንደ አድዋውና እንደ አምስቱ ዘመን አባቶችህ ጥና! ጥና! ጥና!

አመሰግናለሁ፡፡

ጥቅምት ሁለት ሺህ አስራ አራት ዓ..

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share