በዚህ የህልዉና ጦርነት ተሳትፎ የማይኖረዉ አንድም አማራ መኖር የለበትም!! – ቹቹ አለባቸው

ሰሞኑን የታወጁት አገራዊና ክልላዊ አዋጆች ማዕከላዊ ጭብጣቸዉ፣ ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር የሚል ነዉ። ሁሉም ነገር ወደጦር ግንባር/ክተት ሲባል ከማን ምን ይጠበቃል? ምንስ ማለት ነው? የሚሉትን ጉዳዮች በዉል መገንዘብ ያስፈልጋል።

ከመቸዉም ጊዜ በላይ ግልፅ እንደሆነዉ፣ የትግራይ ወራሪ ኃይል መንጋውን ከህፃን እስከ አዛውንት አሰማርቶ ወርሮናል። ይሄን አዉዳሚ ወረራ ተከትሎ፣ እንደ አማራ ይህን ወራሪ ኃይል ለመመከት ሁላችንም በመክሊታችንና በሚናችን አስተዋፆ ማድረግ እንዳለብን ወስነን መንቀሳቀስ ከጀመርን ሰነባብተናል። የዚህ ስምምነታችን ማሰርያ ሁሉም አማራ የጦርነቱ አካል ሆኖ ከሱ የሚጠበቀዉን አስተዋፆውን በማበርከት ጠላትን በአጠረ ጊዜ ወደመቃብር ማውረድ ይኖርብናል የሚል ነዉ።

እናም ፦

  1. ከምሁራን ምን ይጠበቃል?

የገጠመን ውስብስብ ችግር ነው። ጠላት የውጭ ጠላቶችን ከኋላው አሰልፎ በተላላኪነት እየሰራ ይገኛል። ለጠላት ቴክኖሎጅና እውቀት፣ የሚዲያ ሽፋንንና የፕሮፖጋንዳ እገዛ እያደረጉ እያስወጉን ነው። በዚህ ወቅት የገጠመንን ችግር ለመፍታት እውቀት ያስፈልጋል። ምን እናድርግ? ሲባል መፍትሄ የሚያመጣ አካል ያስፈልጋል። በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሉ ምሁራን በቀጥታ ጦር ግንባር ላይዘምቱ ይችላሉ። እውቀታቸው ግን ጦርነቱን ለማሸነፍ ያግዛል። ለሕዝብ ግንዛቤ በመስጠት፣ የጠላትን ሁኔታና ሴራ በመተንተን ትልቅ እገዛ ያደርጋሉ። በዲፕሎማሲው፣ የጠላትን ሀሰት በማጋለጥ፣ ከጠላት ጋር አውቀውም ይሁን ሳያውቁ የተደረቡትን በማስገንዘብ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። ስለሆነም ምሁራኑ ዳር ሆነው ከመመልከት ተቆጥበው እውቀታቸው ጦርነትን ማሸነፍ የሚያስችል ሀብት መሆኑን አውቀው የበኩላቸውን ሚና መወጣት ይኖርባቸዋል።

  1. ከወጣቱ ምን ይጠበቃል?

ወጣቱ ትልቅ አደራ አለበት። ጠላት የወረረን በዚህ ትውልድ ነው። አባቶቹ በዘመናቸው ዘመናዊ መሳርያ የታጠቀን የውጭ ኃይል ከእሱ ያነሰ መሳርያ ይዘው አሸንፈው፣ አሳፍረው መልሰዋል። አሁን የገጠመን ጠላት በብዙ ሁኔታ ከእኛ ያነሰ እንጅ የሚበልጥ አቅም ኖሮት አይደለም። ወጣቱ አልባሌ ቦታ ከመዋል ተቆጥቦ፣ ጠላትን ተከላክሎ ሕዝብና አገሩን የመጠበቅ ግዴታ የዚህ ትውልድ መሆኑን ማመን ይገባል።

ስለሆነም በወጣቱ ዘመን ጠላት የአማራ ሕዝብን አንገት አስደፍቶ፣ አገርን በትኖ የታሪክ ባለዕዳ እንዳያደርገው ግዴታውን መወጣት አለበት። በጠላት የሐሰት ወሬ ሳይወናበድ፣ የፀጥታ ኃይሉን በመቀላቀል፣ ደጀን በመሆን፣ አካባቢውን ከሰርጎ ገብ በመጠበቅና በመዝመት ታሪካዊ ግዴታውን መወጣት አለበት።

  1. አርሶ አደሩ ምን ያድርግ?

የትግራይ ወራሪ ኃይል የአርሶ አደራችን ጠላት መሆኑን በግልፅ አሳይቷል። ወራሪው ኃይል የአማራ ልሂቅ ዋና መፍለቂያ ባህሩ አርሶ አደሩ ነው የሚል ግምት በመውሰድ፣ የሕዝባችን አብዛኛውን ክፍል የሆነውን ማሕበረሰብ መትቶ አንገት ለማስደፋት ጥረት አድርጓል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሰባተኛው ንጉሥ ጉድ አፈላ! - ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

አርሶ አደሩን ከመጨፍጨፍ ጀምሮ ሀብትና ንብረቱን በመዝረፍና በማውደም ለድህነት ለመዳረግ ሰርቷል። አርሶ አደሩ የወረራው ቀዳሚ ገፈት ቀማሽ ሆኗል። ይህ ጠላት እስካልተመታ ድረስ በቀጣይም በአርሶ አደሩ ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል።

ስለሆንም አርሶ አደሩ ልጆቹ ጠላትን ለመደምሰስ በሚደረግ ትግል ተሳታፊ እንዲሆኑ መርቆ በመሸኘት፣ በየአካባቢው የጠላትን ሁኔታ በመከታተልና ለሚመለከተው አካል በመጠቆም፣ ስንቅ በማቅረብ ትልቅ ሚና የመጫወት ታሪካዊ ኃላፊነት አለበት።

  1. ከታላላቅ የሀገር ሽማግሌዎችና አባቶች

የአገር ሽማግሌዎች በሕዝብ ዘንድ ትልቅ ማህበራዊ ተቀባይነት አላቸው። ጦርነት ማሸነፍ የምንችለው መጀመርያ በመካከላችን ያሉ ልዩነትን ወደጎን ብለን አንድነታችን ስናጠናክር ነው። ጠላት በውስጣችን ልዩነት በማጉላት ወደእሱ እንዳናይ ጥረት ያደረጋል። የአገር ሽማግሌዎች በሕዝቡ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት ተጠቅመው ውስጣዊ አንድነታችን ማጠናከር ይገባቸዋል።

በተጨማሪም የወረረን ኃይል የሕዝባችን ደመኛ ጠላት መሆኑን ለሕዝብ በማስገንዘብ፣ አገርና ሕዝብ በመስዋዕትነት እንደሚቆሙ ካላቸው ልምድ ጀግንነት በማስተማር፣ አቅም ያለውን መርቀው ወደ ጦር ግንባር መሸኘት ይጠበቅባቸዋል።

  1. ከባለሀብቱ ምን ይጠበቃል?

የወረረን ጠላት ከሰብዓዊ ጥፋቱ ጎን ለጎን ሌላኛው ፍላጎቱ ዘረፋና ማውደም ነው። በዚህ ረገድ ቀዳሚ ተጠቂ ባለሀብቱ ነው። ይህ ጠላት ወደመቃብር ካልወረደ በስተቀር ለባለሀብቱ አደጋ መሆኑ ታውቆ ያደረ ነው።

አሁን ከሚፈፅመው ዘረፋና ውድመት በተጨማሪ ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት በደባ ባለሃብቶቻችን ላይ ሲፈፅመው የኖረው አይዘነጋም። በጦርነቱ ወቅትም ባለሀብቱ ላይ ጣቱን መጠቆም በጠላትነት ፈርጆታል።

ስለሆነም ባለሀብቱ የጀመረዉን አበረታች ተግባር አጠናክሮ በመቀጠል፣ ለጦርነቱ ሀብት በማሰባሰብ/በማዋጣት፣ ገበያውን በማረጋጋት፣ ተቀባይነት በሚያገኝበት አካባቢ ሕዝብን በማደራጀትና በማስተባበር ከመቸውም ጊዜ በላይ የበኩሉን ሚና መወጣት ይጠበቅበታል። ከሁሉም በላይ በተለይም የአማራ ባለሀብት በዚህ ጊዜ የሚቆጥበዉ ሀብት ሊኖር አይገባም፤ምክንያቱም ይህ አደገኛ ጠላት እስካለ ድረስ የዛሬ ንብረቱ ነገ የሱ እንዳልሆነ ነጋሪ አያስፈልገዉምና።

  1. ከሴቶችና እናቶች፦

በጠላት ወረራ ገፈታ ቀማሽ ከሆኑት መካከል ሴቶች ይገኙበታል። ተፈናቅለው ለችግር ተዳርገዋል። ተደፍረዋል። ልጆቻቸው ተገድለውባቸዋል። ሴቶች በጅምላ ከተጨፈጨፉት መካከል ናቸው። በአንድም ሆነ በሌላ ጠላት ለሴቶች ከፍተኛ ችግር ይዞ መጥቷል። ጦርነቱን በድል መወጣት የሴቶችንና የእናቶችን ስቃይ መቀነስ ነው። ለዚህም ሲባል ሴቶች( በተለይም ወጣት ሴቶች ግንባር በመሰለፍ)፣ በየአካባቢያቸው ያሉ መረጃዎችን ለፀጥታ ኃይል በማድረስ፣ እንዲሁም ባለፉት ዘመቻዎች ውጤታማ የሆኑበትን የስንቅ ማዘጋጀት ተግባር አጠናክረው መቀጠል አለባቸው።

  1. ማህበረሰብ አንቂዎች/አክቲቪስቱ፦

ጠላት በመሳርያ ከሚያደርሰው ጥቃት በከፋ በሐሰት መረጃ ጦርነቱን ለማሸነፍ እየሰራ ይገኛል። በራሱ ብቻ ሳይሆን የእኛ ወገን በሚመስሉ፣ እንዲሁም አውቀውም ይሁን ሳያውቁት አብረውት በተሰለፉ ባንዳዎች በኩል እየወጋን ይገኛል። አክቲቪስቱ ይህን የፕሮፖጋንዳ ጦርነት በመመከት፣ ጠላትን በማጋለጥ የማይናቅ ሚና አለው። የወገንን ጦር ምስጥር ሲያገኝ ባለመዘርገፍ፣ የጠላትን ሁኔታ በማጋለጥ፣ የወገንን ጦር ሞራል በመገንባት፤ ሕዝብን በማረጋጋትና ግንዛቤ በመፍጠር የጦርነቱ አካልና የድል ባለቤት በመሆን ትውልዳዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።

  1. ከፖለቲከኛው ምን ይጠበቃል፣
ተጨማሪ ያንብቡ:  ኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ወይስ አማራ ጨፍጫፊ መንጋ (አጨመ)

የገጠመን ችግር ከፓርቲ-ፖለቲካ በላይ መረባረብን ይጠይቃል። በዚህ ዙሪያ ጥሩ መረዳቶችና ንቅናቄ የታየ ቢሆንም በጦርነቱ ፍፃሜ ምዕራፍ ላይ እንደመገኘታችን መጠን የአማራም ሆነ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ኃይሎች ታሪካዊ ኃላፊነት አለባቸው። በዚህ ወሳኝ ምዕራፍ በዕውቀትና መረጃን መሠረት ያደረጉ ትንንታኔዎችን በመስጠት ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ፣ ሕዝብን በማስተባበር ሀገረ-መንግሥቱን ከፍርሰት መታደግና ማፅናት ይጠበቅባቸዋል። ስለሆነም በዚህ በኩል የአማራ ሙህራን ሊተጉ ይገባል።

  1. የኪነ-ጥበብ ባለሙያው፦

አጠቃላይ ማኀበራዊ ኃይሎችን በማንቀሳቀስ ዙሪያ ኪነ-ጥበብ ትልቅ አቅም አለው። ይህም ከዐድዋ ድል እስከ አምስት ዓመቱ የአርበኝነት ተጋድሎ፣ ከካራማራው ድል እስከ ጥቅምት 24ቱ የምከታና የህልውና ዘመቻ ድረስ ኪነ-ጥበብና ባለሙያው የማይተካ ሚና ነበራቸው። ይህን ታሪካዊ ውርስ አሁን በደረስንበት የጦርነቱ የፍፃሜ ምዕራፍ ላይ አጉልቶ ማውጣት ግድ ይላል።

እናም ነጻነት ውርሱ ከሆነው ሕዝባችን ታሪክ ጋር የተሰናሰሉ ወኔ ቀስቃሽ ኪናዊ ሥራዎችን ወደመድረክ ማውጣት፣ በግንባር ተገንቶ የወገን ጦርን ማነቃነቅ ይጠበቅባቸዋል።

  1. አሽከርካሪው፦

ሁሉም ህሊናዊና አካላዊ ትኩረቶች በህልውና ጦርነቱ ላይ ማተኮርን፣ አቅምና የሰው ኃይልን አሟጦ መጠቀም የግድ የሚል በመሆኑ አሸከርካሪዎች የዘመቻው ቁልፍ ተዋናይ ናቸው። አሽከርካሪዎች ግንባር ድረስ ዘማቹን በማድረስ፣ ስንቅና ሎጀስቲክስ በማሰራጨት፣…ወዘተ አገልግሎቶችን በመስጠት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል።

  1. የመንግስት ሰራተኛዉ፣

ሁሉም የመንግስት ሰራተኛ በመክሊቱ ዙሪያ ይሄን ጦርነት መቀላቀልና የበኩሉን ታሪካዊ ሀላፊነት ሊወጣ ይገባል።

በዚህ በኩል በተለይም የጤና ባለሙያው ከፍተኛ ሀላፊነት ይጠብቀዋል። ጦርነት ውስጥ ግድያ መጣል ያለውን ያህል ጉዳት መድረሱ የሚጠበቅ ነው። በተለይም በውጊያ ወቅት ቁስለኞች አፋጣኝና ተገቢነት ያለው ህክምና ማግኘት የሚችሉት የጤና ባለሙያዎች ሲኖሩ ነው። የጤና ባለሙያዎቻችን ከመደበኛ የስራ ቦታዎቻቸው በተጨማሪ እንደየሁኔታር በግንባር ስምሪት ይጠበቅባቸዋል። ይህን ሙያዊና ሀገራዊ ተልዕኮ በስኬት እንደሚወጡት ይጠበቃል።

  1. ዲያስፖራው፦

ዲያስፖራው ትልቅ አቅምና ፀጋ የታደለ በመሆኑ በዚህ የህልውና ጦርነት የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ሳይገድበው ላሳደገው ሕዝብና ለእናት ሀገሩ ዘብ ሊቆም ይገባል።

የእውነት፣ የፍትሕና የሞራል የበላይነት አቅሞቻችንን በመጠቀም በዓለማቀፍ ሚዲያውና በዲፕሎማሲው ጦርነት ወታደር ሁነው በሀሳብ ሊዋጉና የድሉ ባለድርሻ እንዲሆኑ ታሪክ አጭቷቸዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  እናስራችኋለን? ለካንስ የነአጅሬ ጀግንነት ከድንበርም ተሻግሯልና!

በመጨረሻም አሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ኃይል ከከፈተብን ጥቃት ሊቆም የሚችለው ተዋጊ ኃይል ሲያጣ ብቻ ነው። በእኛ በኩል ህሊናዊና አካላዊ አቅሞቻችን በሙሉ በህልውና ጦርነቱ ላይ በማድረግ በአጠረ ጊዜ የጠላትን የሰው ኃይል ወደባዶነት መቀየር የግድ ይለናል። ማሸነፍ ብቸኛው የጦርነቱ መፍትሔ የሚሆነው ከዚህ አንፃር ነው። የትምና በምንም ሁኔታ ያለ ኢትዮጵያዊ፣ ከሀገሩ ጎን በመሰለፍ የዚህ ጦርነት አካል መሆን ይጠበቅበታል።

  1. የኔ ማሳሰብያዎች:-
  2. አሁን ያለዉ ህዝባዊ ንቅናቄ ጥሩ ነዉ። ነገር ግን ጥሪዉን ተቀብሎ ከመዝመት ይልቅ ወለም ዘለም የሚል አካል ካለ ብሄራዊ ግዳጅ ተግባራዊ መሆን አለባት። ለጋራ አገር/ክልል ሁሉም እኩል ሀላፊነት ሊሸከም ግድ ይላል። ይች አገር/ክልል ደፋሮች የሚሞቱላት ፈሪዎች የሚኖሩባት እንድትሆን መፍቀድ የለብንም።
  3. በርካታ የታጠቀ ሀይል በጠላት ላይ ማሰማራታችን ብቻዉን ለድል ሊያበቃን አይችልም። ስለዚህ ይሄን ግዙፍ ሀይል በተጀመረዉ አግባብ በሚገባ ማደራጀትና ለመስዋትነት እንደገና ደግሞ- ደጋግሞ እንዲወሰን መግባባት ያስፈልጋል። በተለይም ጠላትን አሁን ባለበት ቦታ ድረስ ሂዶ መተናነቅ ካልተቻለ ነገ ከቤታችን ድረስ መጥቶ እያንዳንዳችንን ለቅሞ እንደሚገለን ሁሉም መረዳት አለበት።
  4. በጦርነቱ ሂደት በሚፈጠሩ መሰናክሎች መረበሽና ወደሁዋላ መመለስን 100% ማስወገድ። የገባንበት ጦርነት የህልዉና ጦርነት ነዉ። በዚህም ሞት፣መቁሰልና መራብ የዚህ ጦርነት አይቀሬ “ፀጋዎች” መሆናቸዉን ሁሉም ወደጦርነቱ የሚገባ ሀይል አምኖና ተቀብሎ መግባት አለበት። ይሄም ማለት ጦርነት ከተገጠመ በሁዋላ እነዚህ “ፀጋዎች” አሰደንግጠዉት ወደሁዋላ መሸሽ ሊፈቀድ አይገባም ማለት ነዉ። እነዚህን “ፀጋዎች”ባለመቀበል ችግር የሚፈጥር ካለ አሰራሩን ተግባራዊ ማድረግ ነዉ።
  5. በተለይም የህልዉና ትግል ዉስጥ የገባ ህዝብ እራበኝ፣ጥይት አለቀብኝ፣መሪ አጣሁ፣ሴራ አለ ወዘተ… የሚሉ ለትግሉ የማይመጥኑ ሰበቦችን እየደረደሩ ከጦር ሜዳ ለመሸሽ መሞከር ፍፁም ተቀባይነት ሊኖራቸዉ አይገባም። ለአማራ ክብር ሲል ሂወቱን ሊሰጥ ወስኖ የዘመተ አንድ አሜራ እነዚህን ምክንያቶች ሰበብ አድርጎ ከጦር ግንባር ሊሸሽ አይገባም። ጠላት ያዉም አማራን ለማዋረድና ለመጨፍጨፍ እነዚህን መሰናክሎች ከመጤፍ አልቆጠራቸዉም። ታድያ እኛ ክብራችንን ለማስጠበቅ ስንል በምናካሂደዉ ጦርነት እንዴት እነዚህ ችግሮች ሰበብ ሊሆኑን ይችላሉ?
  6. በመጨረሻም የአማራ ህዝብ ለፈሪ ፊት መንሳት አለበት።የአማራ ህዝብ በዚህ ጦርነት እንደመክሊቱ አስተዋፅኦ ከማድረግ የተቆጠበን እንዲሁም ወደጦር ግንባር ከዘመተ በሁዋላ ያለበቂና አሳማኝ ምክንያት ከጦር ግንባር የሚመለስ ካለ ሊቆጣዉ/ሊመክረዉ ይገባል። እንደዚህ አይነት ወገኖች እንደ ጀግናና ጥሩ እንደሰራ ሰዉ ደረታቸዉን ነፍተዉ በማህበረሰቡ ዉስጥ እንዲኖሩ ሊፈቀድላቸዉ አይገባም።

 

1 Comment

  1. እናንተ እንደዚህ ዓይነት ሃሳብ የምታቀርቡ ። ቅድምያ እናንተ እንደ ተራ ወታደር መሰለፍ አላባችሁ።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share