አልረሳውም! እኔም የኢትዮጵያ ሰራዊት ነኝ!!
ክፍል 1
ለአፍታ ወደሊባኖስ!
ወታደራዊ ክንፉን በራሱ ዕዝ-ሥር ይዞ በሊባኖስ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ሄዝቦላህ!! ‹‹አሸባሪ ቡድን ነው›› እየተባለ በውግዘት ለሚሰጠው ሥያሜና ፍረጃ ማስተባበያ እየሰጠ፤ ለራሱ ትክክል ነው ብሎ የሚያምንበትን፤ በሚያምንበት እቅድና ስልት፤ ጠላቶቼ በሚላቸው ላይ የተለያዩ ጥቃቶች እየፈፀመ፤ በምላሹም ተጠቃን (ተሸበርን) ከሚሉ ወገኖች፤ በሚሰነዘረው አፀፋዊ የጦር ድብደባ በሊባኖስ ሕዝብና መሠረተ-ልማት ላይ ጉዳት ሲደርስ እያወገዘ! ለሌላ የማጥቃት ተግባር ዘወትር ራሱን ሲያዘጋጅና ሲያደራጅ የሚኖር! ረፍት የለሽ የሊባኖስ ታጣቂ ቡድን ነው፡፡
‹‹ሄዝቦላህ ከሽምቅ ውጊያ በተጨማሪ፤ በሌባኖስ ፖለቲካም መሳተፍ አለበት›› የሚሉ አመራሮች በድርጅቱ ተደማጭነት ማግኘታቸውን ተከትሎ፤ ‹‹ሄዝቦላህ በሽምቅ ውጊያው ብቻ መቀጠል አለበት›› የሚል አቋም የነበራቸውን፤ የመጀመሪያው የሄዝቦላህ ዋና ፀሐፊ የነበሩትን ሱብሂ አል-ቱፋይሊን፤ ድርጅቱ ከዋና ፀሐፊነታቸው እንዲነሱ አድርጎ፤ 1984 አባስ አል-ሙሳዊን በዋና ፀሐፊነት ተካቸው፡፡
የሄዝቦላህ ዋና ፀሐፊው አባስ አልሙሳዊ እና ምክትላቸው እንዲሆኑ የመረጧቸው ሀሰን ነስራላህ! ‹‹ሄዝቦላህ ከሽምቅ ውጊያ በተጨማሪ፤ በሊባኖስ ፖለቲካም በቂ ተሳትፎ ማድረግ አለበት›› በሚለው ሀሳብ የጋራ አቋም ነበራቸው፡፡
የሄዝቦላው ዋና ፀሐፊ አባስ አል-ሙሳዊ! በ1992 እስራኤል በወሰደችው የአፀፋ ጥቃት እርምጃ! በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ውስጥ በመገደላቸው! ምክትል ፀሐፊያቸው የነበሩት ሐሰን ነስራላህ በዋና ፀሐፊነት ሄዝቦላን የመምራት ኃላፊነት ተረከቡ፡፡ ሀሰን ነስራላህ ጊዜ አላጠፉም! ቀደም ሲል ከአባስ አል-ሙሳዊ ጋር ይጋሩት የነበረውን! በሊባኖስ ፖለቲካ ውስጥ የመሳተፍ ሀሳብ፤ ተግባራዊ ለማድረግ ተንቀሳቀሱ!! ሀሰን ነስራላህ ሀሳባቸውንም ወደተግባር ለውጠው! 128 የሕዝብ ውክልና መቀመጫዎች ባሉት በሊባኖስ ፓርላማ ውስጥ! ሄዝቦላህ 12 የውክልና ወንበር አጊኝቶ እንዲቀመጥ አደረጉ፡፡
ሄዝቦላህ! በሊባኖስ ፖለቲካ ውስጥ ተፅእኖውን ማሳደር የጀመረው! በሊባኖስ ፓርላማ ያገኘውን 12 መቀመጫና ወታደራዊ ክንፉን ተገን በማድረግ፤ ሊባኖስ ስለሚኖራት የውጭ ግንኙነት ‹‹እኔ ነኝ መወሰን ያለብኝ›› በማለት፤ የሊባኖስ መንግስትን በመገዳደር ነበር፡፡ መገዳደር ብቻ ሳይሆን! ሶሪያንና ኢራንን በተመለከተ ሊባኖስ ስለሚኖራት ግንኙነት፤ ሄዝቦላህ ብቸኛ ፖሊሲ ነዳፊ እና ፖሊሲውንም አስፈፃሚ በመሆን ጉልበተኛነቱን በተግባር አሳየ!!
ወደኢትዮጵያ ስንመለስ!
የኢትዮጵያው ሄዝቦላ ልክ እንደሊባኖሱ ሄዝቦላህ ሽምቅ ውጊያዎችን አካሂዷል፣ ልክ እንደሊባኖሱ ሄዝቦላህ በኢትዮጵያ ፓርላማ ውስጥ አነስተኛ መቀመጫዎች ነበሩት፤ የኢትዮጵያው ሄዝቦላህ ከግንቦት 1983 አንስቶ የመጋቢት 2010 ማዕበል አንከባሎ ትግራይ ክልል እስኪያደርሰው ድረስ፤ ሀገር-አቀፍ ተግባሮችንና ዓለም-አቀፍ ስምምነቶችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካለው 347 መቀመጫ ውስጥ፤ ምንም እንኳን ከ35 ያልበለጠ ወንበር ቢኖረውም፤ ልክ እንደሊባኖሱ ሄዝቦላ የወታደራዊና ፖለቲካዊ ጉልበትቱን ተጠቅሞ፤ ያልተገባ የቡድን ሥልጣኑንና ጥቅሞቹን ማስጠበቂያ የሆኑ ፖሊሲዎቹን፤ በፓርላማው እያፀደቀ ያስፈፅምም ነበር፡፡
የኢትዮጵያው ሄዝቦላ! ለ27 ዓመታት በኢትዮጵያ ፓርላማ አነስተኛ ቁጥር ይዞ፣ ወታደራዊና ፖለቲካዊ የበላይነቱን በመጠቀም፤ ከሕገ-መንግስት
ከሕገ-መንግስት ባፈነገጠ መንገድ ፖሊሲ ተኮር የብሄር ክፍፍል፣ ‹‹እርስ-በርስ›› የማጠራጠር፣ ‹‹እርስ-በርስ›› የማገዳደል፣ ‹‹ፖሊሲያዊ ዝርፊያዎች››፣ ጅምላ ጭፍጨፋ እና የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ሲፈፅም! የሌባኖሱን ሄዝቦላህ ባህሪና አካሄድ መላበሱን ማንም ልብ አላለውም ነበር!!
ነገር ግን ‹‹እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል›› እንደሚባለው፤ ከሚገባው በላይ ተቆናጥጦበት ከነበረው የፌዴራል ሥልጣን፤ በሕዝብ ማዕበል ተባሮ ትግራይ ክልል ከመሸገ በዃላ! ሲሸፋፍነው የነበረውን የሄዝቦላ ባህሪውን በግልፅ አወጣው!!
ይህን እውነታ በሚገባ ግልፅ ለማድረግ፤ የሊባኖሱ ሄዝቦላህ የሄደበትን መንገድ፤ የኢትዮጵያው ሄዝቦላ እንዴት ሲከተል እንደነበር በንፅፅር ማሳየት ተገቢ ነው፡፡
- የኢትዮጵያው ሄዝቦላ በመቀሌ ከተማ ከመሸገ በዃላ! ልክ እንደሊባኖሱ ሄዝቦላህ የብሮድካስት ሚዲያ በመገንባትና ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም! ራሱ በተሳተፈበት ምርጫ የተቋቋመውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መንግስት፤ ጠላት አድርጎ በማየት የስድብ፣ የንቀት፣ የእርግማንና የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎችን አካሄደ!!
- የሊባኖሱ ሄዝቦላህ የሊባኖሱን ህጋዊ መንግስት የአንድ ጠቅላይ ሚኒስትር መንግስት በማስመሰል! ‹‹የሀሪሪ መንግስት›› በሚል ሲጠራው! የኢትዮጵያውም ሄዝቦላ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ.ን መንግስት ‹‹የዐቢይ አህመድ መንስት›› ብሎ በመጥራት! የሊባኖሱን ሄዝቦላህ አሳሳች የፕሮፓጋንዳ መንገድና አካሄድን ተከተለ!!
- የሊባኖሱ ሄዝቦላህ ‹‹የሀሪሪ መንግስት›› እያለ የሌባኖስን ሕጋዊ መንግስት አኮስሶ ከመጥራት አልፎ! የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩትን Rafic Haririን በፖለቲካ-ተኮር ግድያ/Assassination/ አስወገዳቸው!!
የኢትዮጵያው ሄዝቦላ ደግሞ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ.ን መንግስት ‹‹የአብይ አህመድ መንግስት›› እያለ ከመጥራት አልፎ! የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስት ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ላይ፤ ሰኔ 16/2010 ‹‹ፖለቲካ ተኮር ግድያ›› /Assassination/ ሞከረ! ፖለቲካ ተኮር ግድያው ግን ከሸፈበት!! ሙከራው ባይሳካለትም ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰነዘረው ጥቃት፤ ድጋፍ ለመስጠት የተሰበሰቡ የንፁሀን ዜጎችን ሕይወት ቀጥፏል፤ አካላዊ ቁስለትም አድርሷል!!
- የሌባኖሱ ሄዝቦላህ በ2017 በሊባኖስ ውስጥ ባሰፈነው ሽብር-ተኮር ተፅዕኖ! ቀደም ሲል የሽብር ሰለባ ባደረጋቸው ጠቅላይ ሚኒስትር የተተኩት! አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር Saad Hariri የሄዝቦላን ጥቃት በመፍራት፤ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሹልክ ብለው እንዲወጡ አስገደደ!! ይህ የሄዝቦላህ ሽብር-ተኮር ተፅዕኖ! ጠቅላይ ሚኒስትር ሀሪሪን ‹‹ሄዝቦላህና ኢራን በገዛ ሀገሬ ሥራ ሊያሰሩኝ አልቻሉም፤ ሊገድሉኝ ያሴሩብኛል፤ ይህ ጉዳይ እስኪፈታም ወደ ሊባኖስ ተመልሼ ሕዝቤን አልመራም›› የሚል መግለጫ እስከማውጣት አደረሳቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀሪሪ በዚህ መልኩ የፈጠሩት ክፍተት፤ 2018 በሊባኖስ በተካሄደው ሀገር-አቀፍ ምርጫ፤ ሄዝቦላህ ጥምር መንግስት እንዲመሠርት አስቻለው፡፡
የኢትዮጵያው ሄዝቦላ በበኩሉ የሌባኖሱ ሄዝቦላህ የሄደበትን መንገድ በመከተል! በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ላይ ከፖለቲካ ያፈነገጠ ‹‹ሽብር ተኮር ተፅእኖ›› ለማሳደር በተደጋጋሚ ቢሞክርም፤ ጠቅላይ ሚኒስት ዐቢይ አህመድ ሀሪሪ በሊባኖስ የተከተሉትን ከሀገር ሸሽቶ የመውጣትና የውጭ አገራትን ‹‹የዋስትና ስጡኝ ተማፅኖ›› መንገድ ባለመከተል፤ የኢትዮጵያውን ሄዝቦላ ‹‹ሽብር ተኮር ተፅዕኖ›› በግንባር መጋፈጥን መረጡ፡፡ በዋሽንግተን ዲሲ በአሜሪካን ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ፊት ቆመው! ይህን መልዕክት አስተላለፉ፤ ‹‹ልንገደል እንችላለን ነገር ግን እርግጠኛ ሆነን የምንነግራችሁ! ጫት ቤትና አረቄ ቤት ሞተን አንገኝም››፡፡
በሊባኖስ የሚገኘው ሄዝቦላህ ሲጠቀምባቸው የነበሩትን እነዚህን የፕሮፓጋንዳና የሽብር ስልቶች! የኢትዮጵያው ሄዝቦላህ እግር በግር እየተከተለ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ ቢያደርጋቸውም! ጠቅላይ ሚኒስትሩና ግንባር ቀደም የለውጥ አመራሮች፤ ለለውጥ ያነሳሱትን የኢትዮጵያ ሕዝብ ‹‹ለከፋ ሽብር ትተው እና በትነው›› የትም እንደማይሄዱ! ሄዝቦላው ተረዳ፡፡ የተጠቀመባቸው የሽብር ስልቶችም ውጤት እንዳላስገኙለት ተገነዘበ!!
ይህ ማለት ግን! ‹‹ውጤታማ ያደርጉኛል›› የሚላቸውን፤ የሊባኖሱ ሄዝቦላህ የተጠቀማቸውን ሌሎች የሽብር ስልቶችን ያፈላልጋል ማለት እንጂ፤ የኢትዮጵያው ሄዝቦላ! ያሸባሪነት ተግባሩን ያቆማል ማለት አይደለም!!
የብርቱ ጥፋት ድግስ!!
የኢትዮጵያው ሄዝቦላ! የዓለም-አቀፉ ኩነት አመቺ ባለመሆኑ፤ ያሰበውን ‹‹የአልባንያ ሶሻሊዝም›› ማራመድ ሳይቻለው ቀርቷል፤ እንዲሁ የትግራይ ክልል ሕዝብ ለዚህ የሽብር ቡድን ምቹ ባለመሆኑ፤ ክልሉን ማስገንጠል ተስኖት ቆይታል፡፡ ስለዚህ ብቸኛ ምርጫው ያደረገው! የሌባኖሱን ሄዝቦላህ አደረጃጀትና የሽብር መንገድ፤ እግር-በግር እየተከተለ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል! ሕገ-ወጥ ወታደራዊ ክንፍ በሚገባ በማደራጀት! የሊባኖሱን ሄዝቦላህ ሙሉ ቁመና የሚላበስበትን እድል መሞከር ነበር!! መሞከር ብቻ ግን አልነበረም! መቀሌ ከመሸገ በዃላ ልክ እንደሌባኖሱ ሄዝቦላህ የጦር ክንፉን በሚገባ አደራጀ፡፡
ይህን የመሰለው የሽብር ቡድኑ በጦር መደራጀት! የተለመደው አይነት የክልል ልዩ ኃይል ተቋማዊ አደረጃጀት ሳይሆን! ‹‹በብርቱ ጥፋት ድግስ የታጀበ›› የወታደራዊ ክንፍ አደረጃጀት ነበር፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያው ሄዝቦላ! ይህ ወታደራዊ ክንፍ ወደዋናው ግቡ እንደሚያደርሰው እርግጠኛ አልነበረም! ስለዚህ ‹‹የብርቱ ጥፋት ድግሱን›› በደንብ የሚያደምቅለት! ሌላ ተጨማሪ ክንፍ እና ‹‹የሽብር ስልት አስፈፃሚ›› የማደራጀቱን አስፈላጊነት አሰበበት!!
በዚህ እሳቤም በመመራት! በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መከላከያ ሠራዊት ሰሜን እዝና በሌሎች እዞች የሚገኙትን! የሰራዊት አባላት እና አዛዦችን! ሀገር-አቀፋዊ፣ ሕዝባዊ እና ኢትዮጵያዊ የሆነውን መሠረታዊ መርዃቸውን እንዲክዱ ለማድረግ! በብሄር፣ በቋንቋና በትውልድ መንደር አመለካከት ተብትቦ!! ትግራይ ክልል የራሳቸው ቋንቋ፣ ባህልና ማንነት ያላቸው የስብስብ ክልል መሆኑን እንዲዘነጉ በማድረግ! ትግራይ ሪፐብሊብክ በሚል ቅዠት ውስጥ ከትቶ! የሽብር ዓላማው ተባባሪነትና አስስፈፃሚነት አጫቸው!!
ቀድሞም ቢሆን በዘር ቆጠራ ውስጥ ጥቅም ከማመግበስበስና የኢትዮጵያን ወታደራዊ አቋም ከመሰለል ውጪ! ሀገር ለመከላከል፣ የሕዝብ አደራ ለመጠበቅና ለታላቁ ዓላማ ለመሰዋት የሚያስችል! ሞራል እና ችሎታ የሌላቸውን! ከሀዲና ‹‹ዘር ቆጣሪ›› የመከላከያ ሠራዊት አባላትን!! ካደራጀው ወታደራዊ ክንፍ ጋር አቀናጃቸው፡፡ የኢትዮጵያው ሄዝቦላ! ‹‹የብርቱ ጥፋት ድግሱን›› በዚህ መንገድ ምልአት ሰጥቶ! ለሽብር ተግባር ተዘጋጀ!!
ባቀናበረው ‹‹የብርቱ ጥፋት ድግስ›› የልብ-ልብ የተሰማው የኢትዮጵያው ሄዝቦላ! ወደዋናው ግቡ ተንቀሳቀሰ!! በዚህ ሽብር-ተኮር እንቅስቃሴው የተከተለው መንገድና የተጠቀመበት ስልት ግን! ከሌባኖሱ ሄዝቦላህ እጅግ የከፋና በዓለም ታሪክ ተፈፅሟል ተብሎ እስካሁንም ንፅፅር ያልተገኘለት ነው!!
የኢትዮጵያው ሄዝቦላ የሳለውን ካራ የመተረው! ጥይት ያጎረሰውን የክላሹን ምላጭ የሳበው! የመትረየስ እግሮችን ተክሎ እሣት ያዘነበው!! ሀገር በወረረ ኃይል ላይ አይደለም! ጠላት በሆነ ኃይል ላይ አይደለም! በሚፋለመው ቡድን ላይም አይደለም!!
አንድም!
የኢትዮጵያው ሄዝቦላህ አቅዶና ተዘጋጅቶ የሳለውን ካራ የመተረው! ጥይት ያጎረሰውን የክላሹን ምላጭ የሳበው! የመትረየስ እግሮችን ተክሎ እሣት ያዘነበው!! አምኖ ባቀረበው! አቅርቦ በወደደው! ወዶትም ሕይወቱን፣ ጉልበቱን፣ ገንዘቡንና እንጀራውን ባካፈለው! የአካሉም ክፋይ በሆነው! በወገኑ! በወንድሙ ላይ ነው!!
አንድም!
የኢትዮጵያው ሄዝቦላህ አቅዶና ተዘጋጅቶ የሳለውን ካራ የመተረው! ጥይት ያጎረሰውን የክላሹን ምላጭ የሳበው! የመትረየስ እግሮችን ተክሎ እሣት ያዘነበው!! ሀገርን ከማንኛውም የውጭ ኃይል ጥቃት እንዲጠብቅ ታስቦ! በሕግ በተቋቋመው፣ በሕግ በሚመራው፤ ሕጋዊ ሰውነት ባለው! በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መከላከያ ሠራዊት ላይ ነው!!
አንድም!
የኢትዮጵያው ሄዝቦላህ አቅዶና ተዘጋጅቶ የሳለውን ካራ የመተረው! ጥይት የሞላበትን የክላሹን ምላጭ የሳበው! የመትረየስ እግሮችን ተክሎ እሣት ያዘነበው!! ሀገር ጠብቅ! ‹‹ሕገ-መንግስት ጠብቅ›› ብሎ አደራ በሰጠው! ‹‹ክፉ-አይንካህ›› ብሎ መርቆ በሸኘው ሕዝብና መንግስት ላይ ነው!!
ለዚህ ነው የኢትዮጵያው ሄዝቦላ ‹‹የሽብር-ግብር››፤ አገዳደልን አሰቃቂ ያደረገ እና ከሊባኖሱም ሄዝቦላህ የከፋ ‹‹ብርቱ ጥፋት›› የሚባለው!! የኢትዮጵያው ሄዝቦላ ማለት! እንዲህ ያለ የሽብር ቡድን ነው!!
ለአፍታ ወደሊባኖስ ስንጓዝ እ.ኤ.አ. በ2005 ሄዝቦላህ! የእሥራኤል ወታደሮችን በማገትና በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደል፤ የብርቱ ጥፋት እሣት ለኩሶ ነበር፡፡ በዚህ የሄዝቦላህ ጥፋት ምክንያት! እሥራኤል በወሰደችው የአፀፋ እርምጃ፤ የደረሰውን ጉዳት ብቻ ብንመለከት፤ በሊባኖስ ላይ የ1200 ንፁሀን ዜጎች ሞት፤ የ2000 ዜጎች መቁሰል፤ የ12000 ቤቶችና የ20 መሠረተ-ልማቶች ውድመትን አስከትሏል!! የቁሳዊው ውድመት መጠንም ወደገንዘብ ሲመነዘር 7 (ሰባት) ቢሊዮን ዶላር ተገምቷል፡፡
የኢትዮጵያውም ሄዝቦላ! ልክ እንደሊባኖሱ ሄዝቦላህ! አድብቶ ስለሚፈፅመው ሽብር መከረበት እንጂ! አገዳደልን እንዴት አሰቃቂ እንደሚያደርግ አሰበበት እንጂ! የሽብር ተግባሩ ስለሚያስከትለው ውጤት፤ አስቀድሞ እንዲያስብበትና እንዲመክርበት! የተጠናወተው ደም ጠማሽነት አላበረታታውም!! ስለዚህ የኢትዮጵያው ሄዝቦላ! ጥቅምት 24/2013 ለሊት! የብርቱ ጥፋት እሳቱን በአሰቃቂ አገዳደል ለኮሰው!!
የትኛውም አካል ሊረዳው የሚገባው ጉዳይ! ‹‹ብርቱ ጥፋት›› ማለት! ባልተገባ ጥጋብ፣ በእብሪት፣ በድንቁርናና በሽብር መንፈስ ተገፋፍቶ! የማይወጡትን የጦርነት እሣት መለኮስ ነው!! አንዴ ብርቱ ጥፋትን ከለኮሱ በዃላ! መግቢያም መውጫም ማፈላለግ ትርጉም የለውም!! ምክንያቱም ‹‹ብርቱ ጥፋት›› ከተለኮሰ በዃላ መግቢያም መውጫም የለም!! ስለዚህ ያለው ብቸኛ ምርጫ ‹‹የፍርድ ቀን›› ዘመቻውን መጠባበቅ ብቻ ነው!!
የመጨረሻው ክፍል ይቀጥላል..
ማስታወሻ፡ ደራሲው በቅርቡ ከሚያሳትመው አነስተኛ የመጽሐፍ ክፍል የተወሰደ ነው፡፡
ሠላም ለኢትዮጵያ ሠላም ለአፍሪካ
ቴዎድሮስ ጌታቸው
/ደራሲና የፖለቲካ ተመልካች
——————–