ኑ! እንወቃቀስ-1 እንድ ጊዜ ጥንቃቄ! – ቴዎድሮስ ጌታቸው

251192834 1485747978490920 5359248086967530946 nየተከበራችሁ አንባቢያን በዚህ ‹‹ዐብይ ርዕስ›› ምንም ግር እንዳይላችሁ! ይህን ፅሁፍ ባስቸኳይ ለማቅረብ የተገደድኩት፤ አሁን በምንገኝበት ሀገራዊ የህልውና ዘመቻ ውስጥ፤ መበሳጨት መጀመራችንን ታሳቢ በማድረግ እና ምንም ሳንደባበቅ በግልፅ መነጋገር ስለሚገባን ነው፡፡ በመሆኑም ፀሐፊው በግሉ እያስተዋለ ያለውን በግልፅ ለማስቀመጥ ኃላፊነቱን ወስዷል፡፡ እነሆ፤

መወቃቀስ!

የመረረ መወቃቀስ ከተጀመረ! ክቡር፣ እርሶ እና እርሳቸው የሚሉ የአንቱታ ቃላትን አንጠቀምም! ምንአልባትም ‹‹ኢሄ!›› እያልን ልንጠቀም እንችላለን፡፡ በዚህ ወቀሳ ውስጥ ክፋት የሌለባቸው የሀገር ተቆርቋሪ ዜጎች፤ የህልውና ዘመቻው በሚገጥመው /እየገጠመው ካለው/ ጊዜያዊ ችግር የተነሳ! እከሌን ከነካሁ ችግር ይገጥመኛል፣ ሰው ይተናሎለኛል፣ እባብ ይነድፈኛል ሳይሉ! ብስጭት የወለደውን ወቀሳቸውን ሊያዥጎደጉዱት ይችላሉ!! በሌላ በኩል! የሀገር ተቆርቋሪ የሆኑ፤ የፖለቲካ ተመልካቾች፣ ተንታኞችና ፀሀፊዎች፤ ለችግሩ መፍትሄ የሚያመጡ እየመሰላቸው! ምሬት የታከለበት የወቀሳ ሚሳኤላቸውን፤ በማሕበራዊ ሚዲያና በአመቺ የመገናኛ መንገድ፤ ሊተኩሱት ይችላሉ!! ወይም የወቀሳ ሚሳኤሉን እየተኮሱት ይገኛሉ፡፡

እንዲህ ያለው መወቃቀስ ከተጀመረ! የሕዝብ፣ የፖለቲካ፣ የተቋምና የጦር አመራር በሆነ አንድ ግለሰብ ላይ! ወቀሳው ተጀምሮ የሚጠናቀቅ አይደለም፡፡ ወደእርስ-በርስ መወቃቀስ አምርቶ! ማንም ከወቀሳው የማያመልጥበትን ‹‹ትብታብ›› ወይም ‹‹ድር›› እየዘረጋ የሚሄድ! የህልውና ዘመቻውን አዘናግቶና መጠላለፍን አስከትሎ! ለጠላት /ለወራሪው/ ኃይል ቀጣይ የወረራ እቅድ ምቹ እድል ይፈጥራል፡፡ ባጭሩ ‹‹ችኩሉ›› እና ‹‹ብስጩው›› መወቃቀስ! ሽንፈትን የምንከናነብበት መንደርደሪያችን ይሆናል፡፡ ስለዚህ ይህ መንገድ ላያዛልቀን ባንሄድበት ይመረጣል!!

ቅድመ መወቃቀስ!

‹‹ቅድመ መወቃቀስ›› ለወቀሳ ወደሌላው አካል ከማምራታችን በፊት፤ ያለንን መረዳት፣ ያለንን አበርክቶና ፅናታችንን ቀድመን የምንፈትሽበት ማንሸራሸሪያ ነው፡፡ በመሆኑም ‹‹ሀገራዊ የህልውና ዘመቻ›› ውስጥ፤ አሁን ለሚታየው ችግር ተገቢውን መፍትሄ ለማመላከት! የኛ የወቃሾች ‹‹ቅድመ መወቃቀስ›› በአማራጭነት ይቀርባል፡፡ በዚህም መሠረት ‹‹የመረዳት ጥግ››፣ ‹‹የመቶ ሜትር ድል›› እና ‹‹የተገባን ቃል በትዕግስት መጠባበቅ›› የተሰኙትን ወሳኝ ነጥቦች በጥቂቱ እንመለከታለን፡፡

የመረዳት ጥግ!

በዚህ ንዑስ ርዕስ ትኩረት የምናደርገው፤ በውስን ሚዲያዎችና የፖለቲካ ተንታኞች ‹‹ያልተገባ የመረጃ ስርጭት›› አማካኝነት፤ ሕዝብ እየጨበጠ ያለውን ግንዛቤና ያለውን የመረዳት ጥግ ነው፡፡ በዚህ ጥቅምት ወር ብቻ! በፖለቲካ ተንታኞች እና በውስን ሚዲያዎች /የመንግስትንም ይጨምራል/፤ ለሕዝብ ከተሰራጩ ‹‹የተሳሳቱ መረጃዎች›› ውስጥ የሚከተለው ነጥብ ይገኝበታል፡-

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መንግስት /መከላከያ ሠራዊት/ የሚያደርገው ወታደራዊ ዝግጅት፤ አሸባሪውንና ወራሪውን የህ.ወ.ሓ.ት. ቡድን ለመግታት ብቻ የሚደረግ ዝግጅት አድርጎ፤ ለሕዝብ የማሳየት ስህተት፡፡

ለሕዝብ ግንዛቤ የማስጨበጥ ጥረታችን ውስጥ፤ የፈፀምነው ይህ ስህተት! ለወረራው ምላሽ መስጠት የሚገባው ‹‹የመጀመሪያ ተጠባቂውን››፤ ማለትም! በተወረረው አካባቢ የሚገኘውን ክልላዊ ልዩ ኃይሉንና ሚሊሻውን /ሀገር ወዳድ ታጣቂውን/፤ ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ ወረራውን እንዳይከላከል የሚያደርግ፤ እንዲሁም የአካባቢውን ማሕበረሰብ በጠባቂነት የሚያዘናጋ ሆኖ ይታያል፡፡ የዚህ ግብረ-መልስም በተወረረ አካባቢ የሚገኘውን ማሕበረሰብ፤ ‹‹መከላከያ ሠራዊቱ ስጠቃ አልደረሰልኝም›› የሚል የተዛባ መረዳት ላይ የሚያደርስ ይሆናል፡፡ ይህ ‹‹የተዛባ መረዳት›› ቀጥሎም! ‹‹በተዛባ መረዳት ላይ የተቃኘ›› ያልተጠበቀ ሕዝባዊ ቁጣን ሊወልድ ይችላል፡፡

የስህተታችን ግብረ-መልስ በዚህ ብቻ የሚያበቃ አይደለም! የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መከላከያ ሠራዊት እቅዱን፣ ስትራቴጂውን እና ስልቱን ተጠቅሞ፤ አሸባሪውን የህ.ወ.ሓ.ት. ቡድን ለማክሰም ያስቀመጠውን አቅጣጫ! ሊያዛባው ይችላል፡፡ ስለዚህ ግንዛቤ በማስጨበጥ ጥረታችን ውስጥ፤ የፈፀምነውን ስህተታችንን ማረም ብቻ ሳይሆን፤ ሕዝብ ቀደም ሲል በመከላከያ ሠራዊታችን ላይ የጣለውን እምነት ‹‹ሳያጓድል እንዲቀጥል›› የማድረግ፤ ሀገራዊ፣ ሙያዊ እና ህሊናዊ ኃላፊነት አለብን፡፡

የመቶ ሜትር ድል!

አሁን የምንገኝበትን የውስጥ ጦርነት /የሀገር ውስጥ ‹‹ሽብር-ተኮር›› ወረራ/ ለመቀልበስ፤ በምናደርገው ጥረት ድል ማድጋችን ጥያቄ የማይነሳበት ነው፡፡ ነገር ግን የምንጎናፀፈው ድል በአጭር ቀናት ጦርነት ወይም በተራዘመ ጦርነት መሆኑን የሚወስነው፤ የወገን ኃይል የሚከተለው የጦር ስልት ብቻ ሳይሆን፤ የጠላት ኃይልም እየተከተለ ያለው የወረራ ስልት ጭምር ነው፡፡ ያም ማለት የጦርነት ባህሪው ይወስነዋል፡፡

እርጥ ነው! ቀደም ሲል በአሸባሪው ህ.ወ.ሓ.ት. ላይ የህልውና ዘመቻ አካሂደን፤ በሦስት ሣምንታት ውስጥ አንፀባራቂ ድል ተጎናፅፈናል፡፡ ይህ ድል ግን በወቅቱ ለነበረው የጦርነት ባህሪ! የተከተልነው ‹‹ስልት››፣ ‹‹አሰላለፍ›› እና ‹‹ተጋድሎ›› ያስገኘልን መሆኑ ሊታወስ ይገባል፡፡ ስለዚህ አሁን ያለውን የጦርነት ባህሪ በባለፈው ስልተ-ምት ‹‹መቃኘት›› እና ‹‹ማስቃኘት››፤ ሕዝብን ‹‹የመቶ ሜትር ድል ጠባቂ›› አድርጎ! እኛንም ስህተት ውስጥ ይጥለናል፡፡

በመሆኑም አሁን በአሸባሪው ቡድን አመራር ሰጪነት እየተካሄደ ያለውን ‹‹ሽብር ተኮር ሕዝባዊ ወረራ››፤ ለመቀልበስና በድል ለማጠናቀቅ የሚደረገውን ጥረት ‹‹አጭር ወይም ረጅም›› በማለት ጊዜውን ከመወሰን ይልቅ፤ ሕዝባዊውን እና ተከላካዩን የወገን ኃይል ‹‹የሽብር ወረራውን የመቀልበስ ርብርብ›› ላይ ብቻ ማፅናት! ተመራጭ ይሆናል፡፡

የተገባን ቃል በትዕግስት መጠባበቅ!

ቃል የእምነት ዕዳ ነው! ከዚህ የተለምዶ አባባል ወጣ ብለን ስንቃኘ፤ ‹‹ቃል መግባት›› አንድ አካል የተጣለበትን ሕዝባዊ ኃላፊነቱን ወይም በጎ ፈቃደኛነቱን፤ የማድረግ አቅሙን እና ዝግጅቱን መሠረት በማድረግ፤ በአሠራር አስገዳጅነት ወይም በራስ ተነሳሽነት፤ በቃል የሚፈፅመው የድርጊት መርሀ-ግብር ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹ቃል የእምነት ዕዳ›› የሚሆነው! ‹‹ቃል›› የገባው አካል ዕዳነቱን ተረድቶ፤ በተግባር ለማሳየት በሚያደርገው ጥረት ነው፡፡

ይህን መንደርደሪያ ይዘን፤ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር ከአንዴም ሁለቴ ወደገቡት ‹‹ቃል›› እናምራ! ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ2013 መጨረሻዎቹ ወራት እንደመንግስት ባወጡት መግለጫቸው፤ ለአሸባሪው የህ.ወ.ሓ.ት. ቡድን የሚሰጡትን የአፀፋ ምላሽ አመላክተዋል፡፡ አፀፋውንም ‹‹እጅን በአፍ የሚያስጭን›› ሲሉ ገልፀውታል፡፡

እንደአንድ የፖለቲካ ተመልካች የምመክረው! በህልውና ዘመቻ ውስጥ የሚገኙትን አካላት ከመውቀሳችን በፊት፤ ሁላችንም ‹‹ቅድመ መወቃቀስ›› ውስጥ ሆነን፤ በአሸባሪው የህ.ወ.ሓ.ት. ቡድን አመራር ሰጪነት የተቃጣውን፤ ሽብር-ተኮር ወረራ በፅናት እየተከላከልን! ‹‹እጅን በአፍ የሚያስጭን›› የተሰኘውን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ‹‹ቃል›› በትዕግስት እንድንጠባበቀው ነው፡፡ ‹‹እውነት እና ትዕግስት›› ከብርቱ ጥረት ጋር ያሸንፋሉ!!

ሠላም ለኢትዮጵያ ሠላም ለአፍሪካ

ቴዎድሮስ ጌታቸው

/ደራሲና የፖለቲካ ተመልካች/

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.