ወገኖች ስለ ጦርነቱ ትንሽ ልበላችሁና ለዛሬ ላብቃ፡፡
ግርማ ካሳ
የወሎ ክፍለ ሃገር ይባል በነበረው በሁሉም ቦታ ማለት ትችላላችሁ ጦርነት አለ፡፡ ወያኔዎች ደሴን ለመያዝ ሞከረው ውጫሌ ከሽፎባችዋል፡፡ ሆኖም እንደገና በሌላ መነገድ መሞከራቸው አይቀርም፡፡ የቀድሞ ወሎ ታላላቅ ከተሞችን ሰቆጣ፣ አላማጣ፣ ኮረም፣ ቆቦ፣ ላሊበላ፣ ወገልጤና፣ ጋሸና፣ ሃራገበያ የመሳሰሉትን ወያኔዎች ይዘዋል፡፡
የወሎ ሕዝብ የአብይ አህመድ መንግስት ፊቱን አዙሮበታል፡፡ በፌዴራል መንግስቱ ተክዷል፡፡ ሕዝቡ አቅም ባይኖረውም፣ ባለው ሁሉ ወያኔን ለመመከት ተነስቷል፡፡ ወያኔዎች በመከላከያ ውስጥ ካለው ሳቦታጅ፣ ካላቸው የከባድ መሳሪያ የበላይነትና ከፍተኛ የታጣቂዎች ቁጥር የተነሳ በአንዳንድ አካባቢዎች በለስ ሊቀናቸው ይችላል፡፡
ከአንድ አመት በፊት መከላከያ መቀሌን ይዞ ነበር፡፡ ግን አሸንፎ እንዳልነበረ አሁን ሁላችንም የተረዳን መሰለኝ፡፡ አሁንም እንደዚሁ ነው፡፡ ሕዝብን ማሸነፍ አይቻልም፡፡ በወልዲያ፣ በቆቦ ተቆጣጠርን ባሉበት ቦታ ብዙ ወታደሮቻቸው በሽምቅ ውጊያ እያለቁ መሆናቸውን እነርሱም ያውቁታል፡፡ወያኔዎች ሕዝቡ እንዲደግፋቸው ካላደረጉ በቀር መቆየት አይችሉም፡፡ ህዝቡ ደግሞ ስለ ወያኔ ምን እንደሚያስብ የሚታወቅ ነው፡፡
ምን አልባት የወሎ ሕዝብ በአብይ አህመድ ብልጽግና ትልቅ ክህደት ስለተፈጸመበት፣ ወያኔዎች ደግሞ “እኛ ችግራችን አብይ አሀመድ ጋር ነው” የምትል ጨዋታ ስላላቸው የተወሰኑ ስዎች ማታለል ይችሉ ይሆናል፡፡ ግን እርሱም ቢሆን ያንን ያህል በሰፋ መልኩ የሚያስኬድ አይደለም፡፡
ደግሜ እላለሁ ወያኔ በዶር አብይ አህመድ የተሳሳተ፣ ደካማ አመራር እየተመራ ያለውን የመከላከያ ሰራዊት ሊያሸንፉ ይችላሉ፡፡ ልክ ያኔ የደርግ ስራዊት እንዳሸነፉ፡፡ ነገር ግን ያኔ ሕዝብ አልተዋጋቸውም፡፡ ዘመቻ ዋለልኝ ብለው በወሎ በኩል ዘመቻ ቴዎድርስ ብለው በጎንደርና ጎጃም በኩል አዲስ አበባ የገቡት እየሮጡ ነው፡፡ በብዙ ቦታ በሰላም አሳልፉቸዋል፡፡ አሁን ግን የተለየ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ሕዝብ እየተዋጋቸው ነው፡፡ ሕዝብን ደግሞ ማሸነፍ አይችሉም፡፡ ስለዚህ አንዳንድ ውጊያዎችን ቢያሸንፉም ጦርነቱን አያሸንፉም፡፡ ጀነራል ደጎል፣ በናዚ ጦርነት ወቅት፣ ” La France a perdue une battaille ! Mais la France na pas perdu la guerre” (ፈርንሳይ አንድ ዉጊያ ተሸንፋለች፣ ጦርነቱን ግን አልተሸነፈችም” እንዳለው፣ አሁን አንዳንድ ቦታ ውጊያ ወያኔ ብታሸንፍም፣ ጦርነቱን ማሸነፍ አትችልም፡፡