ላለፉት 3 አመታት በኦሮሞ ክልል የነበረውንና አሁንም ያለውን አሳዛኝ ሁኔታ ሁላችንም የምናውቀው ነው። እንደዚያም ሆኖ ግን በርካታ ወገኖች የዶር አብይ አህመድ የብልጽግና መንግስት ላይ ተስፋ እንዳላቸው ሳይ በጣም ይገርመኝ ነበር። “ግድ የለም ከምርጫው በኋላ መንግስት ሲመሰረት ለውጦች ይመጣሉ” እያሉ።
በኦሮሞ ክልል ምክር ቤት ጨፌ ከ500 በላይ የክልሉ ምክር ቤት ተወካዮች አሉ። ለነዚህ ተወካዮች ምክር ቤት ተደረገ በተባለው ምርጫ በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በሚመራው ምርጫ ቦርድ ፣ ኦህዴድ በኋላ ኦዴፓ የነበረው የኦሮሞ ብልጽግና ወይንም በዳዲና ፣ መቶ በመቶ አሸናፊ እንደሆነ ተገልጽዋል። ከ99% በላይ ወረዳዎች በዳዲና/ብልጽግና ብቻውን ነው የተወዳደረው። በተቀሩት 10% ደግሞ ሌሎች፣ ለመወዳደር እጩ ያቀረቡ ቢኖሩም፣ የመቀስቀስ ሆነ ለምርጫ የሚያስፈልጉ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ለማድረግ አልቻሉም።
በአጭሩ እነጋገር ከተባለ፣ የኦሮሞ ክልል ማህበረሰብ ምርጫ አንዲቀርብለት አልተደረገም። “እኛ ነን የምንመርጥልህ ” ተብሎ አንድ አማራጭ ብቻ እንዲሰጠው ነው የተደረገው። ከፖለቲካ አላማቸው ጋር ባንስማም ቀላል የማይባሉ ዜጎች የሚደግፏቸው በአቶ ዳዎድ ኢብሳም ሆነም በአራርሶ ቢቀላም የሚመሩት ኦነጎች ፣ በዶር መራራ ጉዲና የሚመራው ኦፌኮ በምርጫው አልተሳተፉም ወይም እንዳይሳተፉ ተደርጓል። እንደ ኢዜማ ያሉ እጩዎቻቸው ተገድለዉባቸዋል። በኦሮሞ ብልጽግናዎች አፈና ለደህንነታቸው ከመስጋታቸው የተነሳ ከ125 በላይ ወረዳዎች እጪዎች ማቅረብ አልቻሉም።፡ ባቀረቧቸውም ወደ 50 የሚሆኑ ወረዳዎች መቀስቀስ አልቻሉም።
እንደዚያም ሆኖ፣ ብዙዎች ብልጽግና አጭበርብሮና አፍኖ ስልጣን ቢይዝም ፣ ላለፉት 3 አመታት በኦሮሞ ክልል የነበረውንና አሁንም ያለውን አሳዛኝ ሁኔታ ይሻሻል ዘንድ፣ ብዙዎች መንግስት ሲመሰርት መሰረታዊ ለውጦች ያመጣል የሚል ተስፋ ነበራቸው።
ሆኖም ግን የኦሮሞ ክልል ጨፌ ትላንት የነበሩትን መልሶ ሾሟል። አቶ ሺመልስ አብዲሳ የኦሮሞ ክልል ርእስ መስተዳደር ሆነው እንዲቀጥሉ ተወስኗል። ላለፉት በርካታ አመታት ለተፈጠረው ጂኖሳይድ፣ የዘር ማጥራት፣ ግፍና ሰቆቃ ተጠያቂነት ሳይኖር፣ ባለው እንዲቀጥል ተደርጓል። በኦሮሞ ክልል የሚለወጥ ነገር እንደማይኖር፣ አፓርታይዳዊውና ዘረኛው የኦሮሞ ክልል እንደሚቀጥል፣ በዚያ የሚኖሩ ኦሮሞ ያልሆኑ ከአስር አምስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች ሁለተኛ ዜጎች ሆነው እንደሚቀጥሉ አመላካች ነው። የዘር ልዩነቶች፣ አፈናዎች፣ ጂኖሳይዶች፣ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች መቀጠላቸው እንደሚቀጥሉ ነው። ከኦሮሞ ውጭ ያሉ ማህበረሰባት በብዛት የሚኖሩባቸው ከተሞች፣ ወረዳዎች ፣ ዞኖች፣ ራሳቸውን በራሳቸው እንዳያስተዳድሩ አይደረግም። ለምሳሌ አማርኛ ተናጋሪዎች በብዛት በሚኖሩባቸው እንደ ፈንታሌ፣ ግራር ጃርሶ፣ ደራ፣ ቦሰት፣ ሎሜ… ባሉ ወረዳዎች ፣ እንደ አዳማ፣ ቢሾፍቱ፣ አሰላ ፣ ሁሩታ ባሉ ከተሞች፣ በአማርኛ አገልግሎት እንዳያገኙ በማድረግ፣ የነበረው የከፍተኛ አፓርታይዳዊ የመብት ገፈፋ ይቀጥላል።
በነገራችን ላይ ዶር አብይ አህመድ ፣ “ብቻችንን መንግስት የመመስረት ድምጽ ቢኖረንም ስልጣን እናጋራለን” የሚል አስተያየት ሰጥተው ነበር። በዚያ መሰረት ነው መሰለኝ የሺመልስ አብዲሳ መስተዳደር ሌሎች ተቃዋሚዎች ያላቸውን የኦነግ አመራሮችን የክልሉ ካቢኔ አባል አድርጓል። ለምሳሌ የኦነግ ሊቀመንበር አቶ አራርሶ ቢቂላ የኦሮሞ ክልል የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሃላፊ ሆነው ተሾመዋል። ከኢዜማ ሆነ ከሌሎች የኦሮሞ ድርጅት ካልሆኑ ድርጅቶች የተካተተ ስለመኖሩ የተለጸ ነገር የለም። በሌላ አባባል የኦሮሞ ክልል ሙሉ በሙሉ በኦሮሞዎች ብቻ የተሞላ ነው የሚሆነው ማለት ነው። በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ስርዓት ሙሉ ለሙሉ ነጮች ተቆጣጥረዉት እንደነበረው። ታዲያ ከበዚህ የዜጎች መብት በማክበር ዙሪያ ምን የተለወጠ ነገር አለ ????
እንግዲህ የዶር አብይ አህመድ የብልጽግና መንግስት ከምርጫው በኋላ ለውጥ ያመጣል ብለው ሲጠብቁና ተስፋ ሲያደርጉ ለነበሩ ወገኖች ፣ የነ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተመልሶ በስልጣን መቀጠል፣ በአገር ደረጃ ላይ ላዩን የማስመሰል ካልሆነ፣ የሚለወጥ ነገር ላይኖር እንደማይችል፣ የኦሮሞ ብልጽግና/በዳዲና በበላይነት የሚመራው የብልጽግና ፓርቲም ሕወሃት ይመራው ከነበረው ኢሕአዴግ፣ የዘር ፖለቲካን በተመለከተ፣ እንደውም የባሰ እንጂ የተሻለ እንደማይሆን አመላካች ነው።