የኦሕዴድ መንታ መንገድ – አገሬ አዲስ

ነሓሴ 14 ቀን 2013 ዓም (19-08-2021)

1024x538 439109
1024×538 439109

በዚህ ዕርእስ ለመጻፍ ያነሳሳኝ ወያኔ ከገባበት መቀመቅና  የሞት ጠርዝ  አንሰራርቶ የትግራይን ወሰን አልፎ የሌላውን አጎራባች ሕዝብ  መሬት ወሮ በኑዋሪው ሕዝብ ላይ በተለይም በአማራው ላይ የሚፈጽመውን ዓለም ያወቀውን  ግፍ ዘረፋና ወንጀል በግልጽና በእጅ አዙር ተባባሪነት ሚና የተጫወቱትን አካሎች ለማሳዬት ነው።አሜሪካኖች  በአፍጋኒስታን ሕዝብ ላይ የሽብር ድርጊት ሲፈጽም የቆዬውን ታሊባንን ከገባበት የቶራቦራ ገደል አውጥተው ለካቡል ቤተመንግሥት ያበቁትን ያህል፣ ቀደም ሲል ወያኔ በተከፈለ የሕዝብ መስዋእትነት ከሥልጣን መንበሩ ተባሮ ከገባበት የተንቤን ሸለቆና በርሃ እጁን ይዞ አምጥቶ ስንቁንም ትጥቁንም ተረክቦ  ለመቀሌ ቤተመንግሥት መብቃቱን ስናይ የኦነግ መራሹን ኦሕዴድን የተንኮል ሴራና አንድነት በብዙ መልኩ ተመሳስሎ እናገኘዋለን።ይህንን  አለማዬትና አለመረዳት በጥቅም ተጋርዶ  ወይም በውሸት ፕሮፓጋንዳ  ተጠልፎ እውነቱን መካድ ይሆናል።  በቸልታና በመዘናጋት የችግሩን ምንጭ ሳያድበሰብሱ ወደፊት ሊከሰት የሚችለውን  አስከፊ የውጭ ሃይሎችን ያካተተ የወያኔ-የኦሕዴድ/ኦነግን ጣምራ ሴራ ለማሳዬት መሞከር ለመፍትሔው ይረዳል ብዬ አምናለሁ።

ብዙሃኑ በሚባል ደረጃ በሥልጣን ላይ ባለው ኦሕዴድ መራሹ ቡድንና በኦነግ መካከል ልዩነት እንዳለ አድርጎ የመሳልና አንዱን ጸረ ኢትዮጵያና ለአንድነት ያልቆመ፣ሌላውን ደግሞ ለኢትዮጵያ አንድነት የቆመ አድርጎ የማዬት  የተሳሳተና ፍጹም እውነትነት የሌለው ግንዛቤ ሲንጸባረቅ ይታያል።ይህንን ውዥንብር ለመግፈፍ የበኩሌን ግንዛቤና እይታ ለማካፈል እወዳለሁ።

ለእኔ ወያኔም ሆነ ኦሕዴድ/ ኦነግ ከሚሠሩት ደባና የሚስጥር ግንኙነት እንዲሁም  የዓላማ አንድነት አንጻር ሁለቱም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጾች ሆነው ይታዩኛል።ሁለቱም በአንድ የጎሳ ፖለቲካ፣በአንድ የፖለቲካ ህሳቤና ሕገመንግሥት፣አገራዊ የክልል አወቃቀር የሚያምኑ ናቸው።ልዩነታቸው በሥልጣን ክፍፍሉ ምክንያት የተፈጠረው ሽኩቻ ብቻ ነው።ወያኔ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ አቅዶ ሕገመንግሥትና መመሪያ ነድፎ ኦነግን/ኦሕዴድን፣ብአዴንንና መሰሎቹን  አሰልፎ ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በኢትዮጵያ የሥልጣን መንበሩን ተቆጣጥሮ  እመሠረታታለሁ ያለውን አገረ ትግራይን ከኤኮኖሚው መስክ በበለጠ ደረጃ ትኩረት ሰጥቶ የጦር ሃይሉን ሲገነባ፣ኦነግ ያፈጠጠ ያገጠጠ ምኞቱን ኢትዮጵያን አፈራርሼ ኦሮሚያ የተባለች አገር እመሠርታለሁ፣አዲስ አበባም የተባለችውን የሁሉንም ኢትዮጵያዊ የጋራ  ከተማ ነጥቄ ፊንፊኔ ብዬ ሰይሜ እይዛለሁ፣ ኦሮሞ ያልሆነውን ሕዝብ ወደ መጣበት እመልሳለሁ ብሎ ሳያቅማማ  በድፍረት ከመግለጽ አልፎም ጫካ ገብቶ ንጹሃንን ሲገድልና ሲዘርፍ መኖሩ አይካድም።ይህንኑ ንድፈ ሃሳብ የቀድሞው ኦነግ መሥራችና መሪ የነበረው የአሁኑ የዓብይ አህመድ ዋና አማካሪና የቤተመንግሥቱ ባለሟል ዲማ ነገዎ ከዛሬ ሰላሳ ዓመት በፊት በጀርመን ሞንሃይም በተባለ ከተማ በተደረገ ስብሰባ ላይ የተናገረውን ማስታወሱ ይበጃል።አራት  ድርጅቶች ማለትም ኢሕአፓ በወይዘሮ ገነት ግርማ፣ደርግ በአምባሳደሩ፣ሕወሃት በካሱ ኢላላና አሁን ለጊዜው ስሙን የዘነጋሁት ፣ኦነግ በዲማ ነገዎ ተወካይነት  በተደረገ ስብሰባ ላይ ይኸው ጉደኛ በአንድ ጀርመናዊ ለመሆኑ ፊንፊኔ የምትሉትን የአዲስ አበባ ከተማ ብትቆጣጠሩ ኑዋሪውን ኦሮሞ ያልሆነውን ብዙ ሕዝብ ምን ታደርጉታላችሁ ላለው ጥያቄ ሲመልስ “ ኦሮሞ ያልሆነው ሌላው የፊንፊኔ ኑዋሪ ለኦሮሚያ መንግሥት  የሚጠቅመው መኖሪያ ፈቃድ እያሳደሰ ሲኖር የማይጠቅመው ደግሞ የማርያም መንገድ (ሴፍ ኮሪደር) ተከፍቶለት ወደ የመጣበት ይመለሳል”ብሎ ነበር። ይህንን ዓላማና ግብ ተሸክሞ ነው ዛሬ አራት ኪሎ ቤተመንግሥት ውስጥ ገብቶ ብልጽግና የሚል ካባ ደርቦ የሚንጎባለለው።

ኦሕዴድ የተባለው የኦነግ  የበኩር ልጁ ደግሞ የወያኔ አጃቢ ሆኖ ለሃያሰባት ዓመታት በታማኝነት ሲያገለግል ቆይቶ በሕዝቡ ትግል ወያኔ ከአራት ኪሎ ቤተመንግሥት ሲባረር ክፍተቱን ተጠቅሞ አልጋ ወራሽ ሆኖ በዙፋኑ ላይ ጉብ አለ።ሥልጣኑን በተቆጣጠረ ማግስት በጫካና በውጭ አገር  ሲርመሰመስ የቆዬውን  የመንፈስ አባቱን ኦነግን ከነትጥቁ አዲስ አበባ ሰተት ብሎ እንዲገባ አደረገ።እስከአሁንም ድረስ መሪዎቹ በከተማ የተንደላቀቀ ኑሮ እዬኖሩ በጫካ ና በከተማ ጦራቸውን አሰማርተው በንጹሃን ዜጎች በተለይም በአማራው ተወላጅ ላይ የግፍ እርምጃ በመውሰድ በመግደልና በማፈናቀል ንብረቱንም በመዝረፍና በማውደም ላይ ተሰማርተው አያሌ ወንጀል ፈጽመዋል፤በመፈጸምም ላይ ናቸው። የግብር አጋራቸው የሆነው ኦሕዴድ  የሕዝቡን ትግል በመጠምዘዝና በመጥለፍ ላለፉት ሦስት ዓመታት የአገሪቱ ብቸኛ ባለቤት በመሆን በሆድ አደር አጃቢዎቹ ተሳትፎ ለጋራ ዘላቂ ዓላማ መዳረሻ ሁለገብ ዝግጅት በማድረግ ላይ ነው።በሁሉም አቅጣጫ ግልጽነት የለም። ከያገራቱ የሚገኘው ብድርና እርዳታ እንዲሁም ስምምነት ምን እንደሆነ ሕዝብ አያውቅም።ሌላው ቀርቶ ለአባይ ግንባታ ከሕዝብ የተሰበሰበው መጠን ወጣ ከተባለው መጠን 10% (13 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር)  መሆኑ ሲገለጥ፣ቀሪው 90% (110 ቢሊዮን)ግን ከዬት እንደመጣ አይታወቅም።ግድቡ ተሽጧል የሚለውም ሃሜታ ሳይሆን እውነት እንደሆነ ያመላክታል። አሁን ባለው አቅጣጫ አገራችን ከተጓዘች የግድቡ ባለቤት የመሆኑም ነገር አጠራጣሪ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  “ይቺ ሌላ ያቺ ሌላ” አሉ አሉ አለቃ ገ/ሃና - አምባቸው ዓለሙ (ከወልዲያ)

ከኦነግ አካሄድ የተለዬ መስሎ በተራዘመ ስልት ለወደፊቷ ኦሮሚያ ግብአት ና ጉልበት የሚሆን የመከላከያ፣የኤኮኖሚ፣የመሬት …ወዘተ አቅሞችን ገንብቶ ፣ሌላውን በተለይም በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደረውን የአማራውንና ሌላውን ማህበረሰብ  አዳከሞና አመናምኖ እርስ በርሱም  እዬተጋጨ የሚኖርበትን ሁኔታ ፈጥሮ መገንጠሉ ይሻላል በሚል ስልት በመንቀሳቀስ ላይ ነው።በትግል ዓለም ለሚፈልጉት ዓላማ እንቅፋት የሚሆነውን ጠንካራ ሃይል ወይም ምሰሶ ፣ወይም በወታደራዊ አጠራር የስበት ማዕከል(center of Gravity)የሆነውን መምታት ለዘላቂው ድል ዋስትና ስለሆነ ሁሉም ጸረ ኢትዮጵያ ቡድን በአማራው ላይ ጦሩን መዞ ተሰልፏል።ሌላው ደግሞ በቅርቡ ኢትዮጵያ ለዘመናት የገነባችውን የዲፕሎማሲ ግንኙነትና  አቅም በመስበር ከሌላው አገር ጋር የነበራትን ክብርና መቀራረብ በአንድ ጀንበር በአንድ ሰው ውሳኔ እንክትክቱ ማውጣቱ ነው። የተሰጠው ምክንያት ወጭ ለመቀነስ ሲሆን ሥራውን በዬአገሩ የሚኖሩ የሥርዓቱ ደጋፊዎች የሆኑ በዲፕሎማሲ ሥራ ቀርቶ በቀን ሥራ ላይ እንኳን ልምድ የሌላቸውን ዋልጌና የጥቅም ተገዢዎች በቦታው በመመደብ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ሜዳ ተሸንፋና ተዋርዳ ለጠላቶቿ አመቺ ታርጌት እንድትሆን ያደረገ ውሳኔ ነው።ይህም ለወደፊቱ ሴራ ለኢትዮጵያ የሚቆም ወዳጅ አገር እንዳይኖር ለማድረግ የታቀደ ሴራ ነው።የዲፕሎማሴ ሚሽን ከሚያሶጣው ወጭ  ይልቅ የሚሰጠው ጥቅም ይበልጣል።የዬአገራቱ ከበርቴዎች በቱሪዝምና በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንዲሳተፉ የመቀስቀስና የማግባባት ጉልበት አለው።ስለሕዝቡ ታሪክና ባሕል የማሳወቂያ መድረክም ሆኖ ያገለግላል።የዚያ ጉልበት ደሃ መሆን እንኳንስ በእድገትና ሰላም በኩል ቀርቶ የአገርም ስም እንዳይታወቅ ያደርጋል።ኢትዮጵያም ለወደፊቱ ከዓለም ሕዝብ ትውስታ ለማራቅ ይህ እርምጃ  ተወስዷል።   የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሚዛኑ ባጋደለበት ወቅት ጭራሽ መጠናከር የሚገባው የዲፕሎማሲ ሚሽን በዚህ መልኩ መንከታከቱ ከተገለጸው ሴራ ተለይቶ አይታይም።በተለይም የአፍሪካ ወዳጅ አገሮችን ግንኙነት ማመንመኑ ኢትዮጵያን የቅርብ አጋረ ቢስ ያደርጋታል።ታዛቢ በሌለበት አገር እንደ ግብጽ ያሉ ታሪካዊ ጠላቶቿ እንደልባቸው እንዲቦርቁበት ያደርጋል።እንኳንስ ዘንቦብሽ ዱሮውንም ጤዛ ነሽ እንዲሉ ይህ የአንድ ሰው ውሳኔ ለጠላት ዱላ የማቀበል ያህል ነው። የሚያስከፍለው ዋጋ በቀላሉ አይገመትም።

በአገር ውስጥ በኦሮሙማ መርሆ የሚንቀሳቀሱት እነዚህ ሁለት የሚመስሉ የአንድ ዓላማ ቤተሰቦች ቢሆንላቸው ሥልጣኑንም፣ሃብቱንም፣መሬቱንም ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥረው አሁን እንደሚታዬው  ኢትዮጵያ የሚለውን ስም ብቻ አንግበው ቢቀጥሉ አንዱ ምርጫቸው ይሆናል፣ነውም።ምክንያቱም  ከትንሽና ከጠባብ አገር ይልቅ ሰፋ ያለና ትልቅ አገር ለዘረፋውም ለግብአቱም ስለሚሻል ሳይመርጡት አይቀሩም። ከወያኔም ተመክሮ ቀስመዋል።የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው ነውና በዚያም ሆነ በዚህ የኦሮሞን የበላይነት፣የኦነግንም ፈላጭ ቆራጭነት የሚያስከብርና የሚያረጋግጥ ከሆነ ዓይናቸውን አያሹም።የወያኔውስ ጌታቸው ረዳ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እንገባለን ብሎን የለምን?ታዲያ ለኦነግ /ኦሕዴድ ከጫካው ይልቅ አራት ኪሎ ቤተመንግሥት ገብቶ የሚሹትን ማድረጉ አይሻላቸውም?  ለዚያም ነው እንደ ወያኔ ሲኦልም ከመግባት ይልቅ ባይዋጥላቸውም ከአንገት በላይ ኢትዮጵያ!  ኢትዮጵያ!  እያሉ ሕዝቡን ማማለል የመረጡት።ይህ ሙከራቸው ግን ፋይዳ ቢስ ሲሆንባቸው ወደ ዋናውና ተሸክመው ከኖሩት እቅዳቸው የማይገቡበት ምክንያት አይኖርም። ሁለት ባላ ትከል ፣አንዱ ቢሰበር በሌላው ተንጠልጠል እንዲሉ!

ለዘላቂው ግባቸው

 • የኤኮኖሚ ምንጮችን መቆጣጠር፣የኦሮሚያ ባንኮችን እያጠናከሩና የብሔራዊ ባንኩን እያሽመደመዱ ባዶ ማስቀረት።ለዚህ ተግባር ይሆናሉ የሚሏቸውን ታማኞቻቸውን መመደብና ማሰማራት፣
 • የሌላውን ማህበረሰብ መሬት እዬወረሩ  ኦሮሞ ያልሆነውን ነዋሪ ሕዝብ  እያፈናቀሉና ንብረቱን እዬዘረፉ ወሰናቸውን ማስፋት፣በምትኩ የራሳቸውን ጎሳ ተወላጅ ማስፈር፣
 • የአገሪቱን ካዝና በመመዝበር ከሌላው አካባቢ በተለዬ ፍጥነትና መጠን  ክልላችን ነው በሚሉት አካባቢ መሠረተ ልማቶችን ማስፋፋት፤የሌሎቹን ማዳከም ወይም ማፍረስ፣
 • በአገሪቱ ሃብትና ጥሪት የራሳቸውን የመከላከያ ሃይል እዬገነቡ የሌላውን ማፍረስ ወይም እንዳይገነባ ማድረግ፣
 • ከወያኔ ጋር በተደረገው  የሥልጣን ግብግብ ሳቢያ የተከሰተውን  ጦርነት ሽፋን በማድረግ የሌላውንም ተቀናቃኝ ጎራ ለማፍረስ እንደ ስልት መጠቀም።ለኢትዮጵያ  አንድነት ዋልታና መከታ ሆኖ የኖረውን በተለይም የአማራውን ማህበረሰብ ለመምታትና ቅስሙን ለመስበር ከወያኔ ጋር የጥምረት ዘመቻ ማካሄድ፣ቦታዎችን መውረርና ማሶረር፣ንብረቶቹን መዝረፍና ማዘረፍ።የጦርነቱን አውድ አማራ በሚኖርበት  መሬት ላይ ማድረግ።በዚህም ሕዝቡን  ሰላም በመንሳት ለስደትና ለችግር ማጋለጥ፤እርሻ ና ሌላው እንቅስቃሴ ታግዶ ለርሃብ እንዲጋለጥ ማድረግ።
 • ኢትዮጵያ እንደ አገር እንዳትኖር ፣ታሪካዊ ቅርሷና መግለጫዎቿ መውደም እንዳለባቸው በማመን በእጅ አዙርና በቀጥታ ከወያኔ ጋር በማበር ማፈራረስ፣የታሪክ አሻራ እንዳይኖር ሌት ተቀን መሥራት።ወያኔ በላሊበላ ቅድስት ታሪካዊ ቦታ ላይ ሲዘምት ኦሕዴድ /ኦነግ በአዲስ አበባና አካባቢዋ ያሉትን ታሪካዊ ተቋማት ማፈራሱ የዚያ እኩይ ተግባር ማሳያዎች ናቸው።የኢትዮጵያ መታወቂያና ንብረት የሆኑትን ተቋማት በጠራራ ጸሃይ በሃራጅ መቸብቸብም አንዱ ተልእኮ ነው።
ተጨማሪ ያንብቡ:  አማራው ላይ እየደረሰ ያለው ግፍና በደል… | በቪዲዮ የቀረበ

ትልቁና መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ  ከወያኔ ጋር የይምሰል ግብግብ የገቡበት ምክንያት በትግራይ ውስጥ ምርጫ አካሂዶ የራሱን መንግሥት አቋቁሜያለሁ ማለቱን ተከትሎ ሲሆን በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ግን ጊዜያዊ መንግሥት  ለሦስት ዓመታት አቋቁመናል ብለው ያወጁትን አጋሮቹን የኦሮሞ ፌዴራሊስትና ኦነግን በዝምታ ማለፉ  የወደፊቱን የጋራ አቅጫጫቸውን ያመለክታል። “አንተም በዚህ እኔም በዚያ- ወዲያ ማዶ እንገናኝ” የተባባሉትን አዳኞች ታሪክ ልብ ሊሉ ይገባል። በዬት አገር ነው በመንግሥት ላይ መንግሥት(a state within a state) አውጃለሁ ሲባል በዝምታ የሚታለፈው?የኦህዴድ መራሹ መንግሥት ይህንን ትልቅ ድፍረት በዝምታ ማለፉ  ለአንድነታቸው ሌላው ማሳያ ነው።የአማራው ክልል የራሱን የህንነት ሃይል ለማቋቋም ያደረገውን ሙከራ ሲያጨናግፉ ግን ቅር አላላቸውም።የሽግግር መንግሥትማ አቋቋምኩ ቢላቸው አጸፋው ምን ሊሆን እንደሚችል ለመገመት አያዳግትም።

የኦነግና የኦሮሞ ፌዴራሊስት መሪዎች ከአገር ወጥተው በውጭ አገር በአሜሪካና በአውሮፓ እዬተዘዋወሩ ነገ እንመሠርታታለን ለሚሏት ኦሮሚያ ድጋፍ እንዲሰበስቡ መፍቀዱም ሌላው አማላካች ነው።በተሰማሩበት ሁሉ እርዳታና ድጋፍ እዬሰበሰቡ ለመሆናቸው ብዙ ፍንጮች ብቅ ብለዋል። ለሽርሽር ወይም ለህክምና አለመውጣታቸውን እንኳንስ የፖለቲካ ሰው ጢብ ጢብ የሚጫወትም ልጅ ቢሆን ይረዳዋል።

ምዕራብያውያኑ በተለይም አሜሪካ የሽግግር መንግሥት ይቋቋም የሚሉትም እነዚህንና መሰሎቻቸውን ሃይሎች ከወያኔ ጋር አጣምረው እንደሆነ መገመት አያቅትም።ይህ ሃሳባቸው ግን ከልባቸው ሳይሆን ነገ ቢገነጠሉ እንጋልባቸዋለን ለሚሉት ሃይሎች የተዘዋዋሪ እውቅና የመስጠት ጅማሮ ነው።ለጥቅማቸው ሲሉ ጠላት ነው ከሚሉትም ጋርም ቢሆን ይተባበራሉ፤የአፍጋኒስታንና የታሊባን የቀናት ታሪክ ይህንኑ ያመለክታል።የምዕራባውያን  ወዳጅነት አብሮ አያመሽም።ኢትዮጵያንም  በተደጋጋሚ ከድተዋታል።

1 በጣልያን ወረራ ጊዜ ከወራሪው ጋር በመቆም ወረራውን አጽድቀው ነበር፤ግን የሂትለር ዱላ ወደ እነሱ ሲዘረጋ ፊታቸውን ወደ ኢትዮጵያ አዞሩ።በእግሩ ተተክተው በቅኝ አገዛዝ መዳፋቸው ስር ለመያዝ ያደረጉት ሙከራ በቆራጦቹ አትዮጵያውያን  ንቃትና ዘዴ ሊከሽፍ ችሏል።

2 ከአርባ ዓመት በፊት የሶማሌው ሰዒድ ባሬ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ ወረራ ሲፈጽም፣ ከፍላ የገዛችውን  የጦር መሣሪያ በማገድ  ለወራሪው የጦርና የሎጅስቲክስ እንዲሁም የምክር ድጋፍ በማድረግ ኢትዮጵያን አሶግተዋል፣ ወግተዋልም።

3 ወያኔ፣ኦነግና ሻእብያን ለሥልጣን አብቅተው ኤርትራን አስገንጥለው ወደብ አልባ አድርገውናል፤ከዚያም በፊት የጅቡቲ ነገር እንዲሁ ኢትዮጵያ እንድታጣ ያደረጉት በተባበረ ሴራቸው ነበር።

4  አሁን ደግሞ ወያኔ፣ ኦነግ፣ሱዳንና ኢጅብት ከሌሎች ደቃቃ የውስጥ ባንዳ ቡድኖች ጋር ተመሳጥረው በያቅጣጫው ጦር ሲከፍቱባት ወገንተኝነታቸውን ለወንጀለኛው አካል በይፋ አሳይተዋል።ኢትዮጵያ በአንጡራ ሃብቷ ከፈረንሳይ የገዛችውንም መሳሪያ እንደ ልማዳቸው እንዳይደርሳት አግደዋል።ምንም እንኳን ቢመጣም በኦሕዴድና በኦነግ እጅ ላይ መውደቁ ባይቀርም።

ያለፈውን ታሪክ መለስ ብለን ብናይ

የዛሬ ሰላሳ ዓመት በፈረንጆቹ 1991 ዓም በነበረው አገራዊ ቀውስ ደርግና የኦነግ፣ህወሃትና ሻእብያ አማጽያን በለንደን ከተማ የሰላም ድርድር ያድርጉ ተብሎ በስከጀርባ አማጽያኑ ሃይላቸውን አንቀሳቅሰው አገሪቱን እንዲቆጣጠሩና አዲስ አበባም እንዲገቡ የተደረገው ሴራ ሰሞኑን የአፍጋኒስታን መንግሥትና የታሊባን አማጽያን በካታር የሰላም ድርድር ያድርጉ ተብሎ ስብሰባው ሳይቋጭ የታሊባን ጦር አገሪቷን መቆጣጠሩ በእኛ አገር ላይ የተፈጸመውን ደባ ይመስላል።አሁንም ህወሃት፣ኦነግና ሌሎቹ ጸረ ኢትዮጵያ ሃይሎች በያቅጫጫው ድንበር ጥሰው ከገቡት የውጭ ጠላቶች ጋር በማበር ቦታዎችን እዬተቆጣጠሩ በሽብር ሕዝቡን  ሰላም በሚነሱበት ሁኔታ ድርድር ይካሄድ የሚሉት ለተመሳሳይ ሴራ ሊሆን እንደሚችል ነቅቶ መጠበቅ ይገባል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ይድረስ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጉልበት ላላችሁ ሁሉ | ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም

ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ ነውና ለዚህ ሁሉ መከራና ውርደት የዳረገን ሥልጣን ላይ ተቀምጦ የሴራው ተባባሪ የሆነው የኦሮሙማ ህሳቤ ተሸካሚ የሆነው አጭበርባሪው ኦነግ መራሹ የኦህዴድ  ቡድን የሚመራው መንግሥት ነው። ኦሕዴድ በሚያደርገው ጅዋጅዌ ጥርጣሬ ያደረባቸው ምዕራባውያን ለሚፈልጉት ተግባር አስተማማኝ ሆኖ ስላላገኙትና ከትዕዛዛቸው ውጭ ባላንጣ ናቸው ከሚሏቸው አገራት ከኤርትራ፣ከቱርክ፣ከኢራን፣ከቻይና፣ከሩስያ  ጋር  መሪው አብይ አህመድ ሽር ጉድ በማለቱ ይህች ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም በሚል ህሳቤ እሱን አሶግደው በሌላ ታማኝ ፈረስ ለመተካት የማይገለብጡት ድንጋይ የለም።ቀደም ሲልማ ይሆነናል ብለው ተሽቀዳድመው የኖቤል ሽልማት ሸልመውት ነበር።እሱ እራሱ የሥልጣኑን  ድካ ሳያውቅ ፣አጨብጫቢዎቹ ከሰውነት አውጥተው ወደ አማልእክትነት  ለውጠውና በሚያሰሙት ግፋ በለው  ጫጫታ ታውሮ አገራችንን ወዳጅ አልባ አደረጋት።እራሱንም ቀልቡን ነስተው ለአደጋ አጋለጡት።አሁንም አልመሸም !እራሱንም አገሩንም ከአደጋ ለማዳን፣ካለው አገር አጥፊ  የጎሳ ፖለቲካ የሚገላግሉንን አገር ወዳድ ሃይሎች የተካተቱበት የሽግግር መንግሥት በአስቸኳይ እንዲቋቋም በሩን ቢከፍት በታሪክ የተመሰገነ ይሆናል።

እዚህ ላይ ግልጽ መሆን ያለብን ምዕራባውያን ለአገራችን ያስባሉ ብሎ መጠበቅ ስህተት መሆኑን ነው።ሁል ጊዜም ቢሆን ከራሳቸው ጥቅም በላይ የሌላውን አገር ጥቅም አያዩም፤ለነሱ ያልሆነ አገር መቀመቅ ቢገባ ደንታ የላቸውም።ይህንን በሌሎች አገሮች አይተነዋል፣በእኛም አገር እያዬነው ነው።ሰልፋቸውን ከግብጽ፣ከሱዳን፣ ከወንጀለኛው ከህወሃትና ከኦነግ  ጋር ሲያደርጉ ማንነታቸውን አሳይተውናል።

እዚህ ላይ  አገራችን ከሌሎች አገሮች ጋር ምንም አይነት ግንኙነት አታድርግ ማለት አይደለም።ከአገራት ጋር ሊኖር የሚገባው ግንኙነት በእኩልነትና በመከባበር መርሆ ላይ ያረፈ እንጂ በጌታና በባሪያ መካከል የሚኖር ግንኙነት መሆን አይገባውም። ለዚህ አይነቱ ግንኙነት ግን አገሩን የሚወድ፣ሕዝቡን የሚያከብርና የሚያስከብር መንግሥት ሲኖር ነው።አለበለዚያ ባለቤት ያቀለለውን ባለዕዳ አይቀበለውም ይሆናል።

ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግን አብይ ተነሳ አልተነሳ ለውጥ የለውም።በውጭ ሃይሎች የሚሽከረከር ቡድን በዚህም በዚያም ብሎ ስልጣን ላይ ቢወጣ ያው በገሌ ነው። ለውጡ የአገርን አንድነት የሚያረጋግጥ፣ለባእዳን ያልተንበረከከች አገር እውን የሚያደርግ  መዋቅራዊ መሆን ይገባዋል።

ይህንን ተረድቶ አገር ወዳዱ ሃይሉን አሰባስቦ ብሔራዊ ክብሩንና አገሩን ለማዳን  በአንድ ግንባር ካልተሰለፈ፣ በተያዘው መንገድ ነገሮች ከቀጠሉ የጊዜ ጉዳይ ነው የዛሬው ባላገር የሆነው ሕዝብ ነገ አገረ ቢስ የመሆኑ ዕጣ ይገጥመዋል።ከእልቂት የተረፈ ቢኖር እሱም ለስደት ይዳረጋል።ይህ በጨለምተኝነት የሚሰነዘር ፍርሃት ሳይሆን የሌሎቹን  አገሮች ታሪክና እስከ አሁን ድረስ በአገራችን የተከሰተውን ሁኔታ መሰረት በማድረግ ነው።

ከአደጋው ለመውጣት አገር አድን ሕዝባዊ ንቅናቄ መፍጠር አስፈላጊ ነው።የመጨረሻ ዓላማውም አንድነቷ የተጠበቀች፣ከጎሳና ከእምነት ግጭትና ንትርክ የተላቀቀች፣ለዜጎቿ ሁሉ የተመቸች፣ ዴሞክራቲክ ኢትዮጵያን መፍጠር ነው።በቅድሚያ ግን

U /  ሁሉም እንቅስቃሴዎች  በአንድ ቁጥጥርና  ማዕከላዊ እዝ(command post) እንዲመራ ማድረግ፣እዚያና እዚህ ተበታትኖ የሚደረግ ትግል ለአደጋ ስለሚያጋልጥ በተናበበና አንድ ወጥ በሆነ መልኩ በሚሰጥ መመሪያ መንቀሳቀስ።ንቅናቄው በሰርጎ ገቦች እንዳይበከል መጠንቀቅ፤ከመንግሥት አካላት ጋር በተለይም ከብአዴን መዳፍ ውስጥ እንዳይገባ ነቅቶ መጠበቅ።

ለ/ እያንዳንዱ በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምን ዜጋ እራሱን ማዘጋጀትና ለእናት አገር ጥሪው ተገቢውን መልስ ለመስጠት ፤ለአስፈላጊው ዝግጅትና ሎጅስቲክስ  መሟላት የገንዘብና ቁሳቁስ መዋጮ ማድረግ፣ ነገ ዛሬ ሳይባል ሁሉም እንደዬ ችሎታው ና አቅሙ በሚፈቅደው መጠን ለማበርከት መረባረብ፤

ሐ/ አንድ ጠንካራ የመረጃና የግንኙነት ተቋም(Media center) መፍጠር(በዬቦታው የተበታተኑትን አንድ ላይ ማሰባሰብ ወይም ማዕከላዊው አካል በሚሰጣቸው መመሪያ እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ።

እነዚህን ተግባራት ለመፈጸም በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ነገ ዛሬ ሳይሉ በሚመቻቸው መንገድ ተገናኝተው የሥራ ክፍፍል ሊያደርጉ ይገባል።

 

አገሬ አዲስ

5 Comments

 1. ንግግርህ እንደ ስምህ አዲስ አይደለም። አብን ነህ፤ የህወሓትን ሥራ አስፈጻሚ ነህ! ሰው በጣም ሠልጥኗል፤ ከ20 ዓመት በፊት ቢሆን እንኳ ትንሽ ታታልል ነበር። አሁን ኋላ ቀርተህ አላወቅህም።

 2. አሁን የሀገር ማፍረስ ጦርነት ውስጥ ወገን ውድ ህይወቱን እየሰጠ ወያኔያዊ ማዘናጊያ አጀንዳ እየቀረፁ ህዝብን የሚያደናግሩ ሰዎች ስለህሊናቸው አዝንላቸዋለሁ:: ቆራጡ ዘብ ቆሟል ኦሮሞው ከአማራ ጋር ከሲዳማና አፋር ጋር እጅ ተያይዞ ጠላት የሆነውን የወያኔ ጭፍራ እየመከተ ነው:: ሌላው በገንዘብና ጉልበት እየረዳ ነው:: ያንተን እንቶፈንቶ የሚከተል ጊዜ ያለው ወገን የለም

 3. ደክተር ጽሐፌ ትክክል ነህን ?አንድ ቤተሰብ መምራትም ከባድ ነው አደለም በፓለቴካ ስንጣቄ የተወረረን ህዝብ አንድ ለማድረግ ከባድ ይመስለኛል፡ሴቀጥል እይታህ ሁለት ነው እግዜአቭሔር ም ሰይጣንም ፈጠሩኝ እንደማለት ነው

 4. ውድ አገሬ፣
  ሥራ ፈት ትመስላለህ። ፎቶውን ተመለከትኩ። የኦሮምያ ክልል ሹማምንት ናቸው። የአማራ ክልል ወይም የትግራይ ክልል ሹማምንትም በመላ አማራ እና ትግሬ ናቸው! ምንም አዲስ ነገር የለበትም። ዘመን ጥሎህ እንደ ሄደ አላወቅህ እንደ ሆነ ላርዳህ! አብን ኮሮጆህን ካልጣልክ ሰው አትሆንም! የምታናፋው የህወሓትን ሥራ የሚሠራለት እንጂ አገሬ የምትላትን አይጠቅማትም!

  • አብን አመራር ከኦሮሞና አማራ ልዩ ሀይል ጋር ወያኔ እየተፋለሙ ነው:: ወንድም አትሳሳት ወያኔም አማርኛ መፃፍና መናገር ይችላል:: ዛሬ ፖለቲካ ቆማሪና አዘናጊ ይወያኔ ተከፋይ ብቻ ነው:: አማራው እንዲወረር ያመቻቹ ባንዳዎች ናቸው:: ልክ እንደ ኦሮሞ ሸኔ የአማራ ሸኔዎችም አይጠፉም:: ቅጥረኞች አላማ ሳይሆን ገንዘብ የሚገዛቸው እቃዎች

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.