በዙሪያችን የምናያቸው ሁኔታዎች ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ብሎ ስለሚያስተጋባ፥ ስጋታችን ለባለ አዕምሮ ሰው ትክክል ሊመስል ይችላል። ይሁን እንጂ በዓይነ ሥጋ ከሚታየውና ከሚሆነው ትዕይንት ጀርባ ያለውን እውነት ለሚያስተውል ሰው፥ የኢትዮጵያ ትንቢት ፍፃሜ ዋዜማ ላይ እንደሆንን ፍንትው ብሎ ይገለጥለታል።
ለመሆኑ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች ሲባል ምን ጠብቀን ነበር?
ኢትዮጵያ እጆቿን የምትዘረጋበት አውድ ሁለት ምዕራፍ አለው። አንደኛው ምዕራፍ በመጀመሪያ የሚሆን ሲሆን፥ ሁለተኛው ምዕራፍ ራሱ የመጀመሪያው ምዕራፍ የሚወልደው ነው። ወደ እግዚአብሔር የመጀመሪያው እጅ መዘርጋት ምዕራፍ ለፈጣሪ መሸነፍንና በእርሱ መታመንን ያመለክታል። ሰው ተንበርክኮ እጁን ወደ ፈጣሪ ሲዘረጋ፥ መማረኩንና ረድኤትን ከላይ መጠበቁን ያሳያል። እጅ መዘርጋቱ፥ “ተስፋችን አንተ ነህ” ብሎ እርዳታ ከላይ እንደሚመጣለት ማወቁን ያመላክታል ። የዚህ የመጀመሪያው የእጅ መዘርጋት ምዕራፍ፥ ገሀዱ ዕይታ የሚያመለክተው ምስኪንነትን ነው። ፈተናችን ከአቅማችን በላይ ሆኖ ሲያንገዳግደን፥ እንዳንሻገር የሚከለክሉ ተግዳሮቶች በግራና ቀኝ ሲያይሉብን፥ የሚመለከተን ሁሉ በመፍረስ አፋፍ ላይ እንዳለን አድርጎ ሊቆጥረን ይችላል። በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ እጆቻችንን ወደ ፈጣሪ ዘርግተን በእምነት እንደምንሻገር ስንናገር አንዳንዶች የማይገባቸው ለዚህ ነው። በዚህ ጊዜ መደገፊያችን እና ትምክዕታችን ፈጣሪን አድረገን አንገታችንን ቀና ስናደርግ፥ ከትእቢት ይልቅ ትህትና እንደሚያሸንፍ የምናውቀውና፥ በዚህ የመጀመሪያው የትንቢት ፍፃሜ ምዕራፍ ውስጥ የሚያለመልመን በፈጣሪ ላይ ያለን እምነት ሲሆን፥ ያም እምነት ጉልበት የሚሆነን በእውነት መነፅር ኢትዮጵያን ማየት ስንችል ብቻ ነው።
ይህን የጨለማ ጊዜ በመጀመሪያው እጃችንን የመዘርጋት ምዕራፍ በፈጣሪ ከተሻገርን በሁዋላ፥ ሁለተኛው እጅ የመዘርጋት ምዕራፍ ይወለዳል። ያም እጆቻችንን ዘርግተን በረከቱን የምንቀበልበት የመታደስ ዘመን ነው። በዚህ በሁለተኛው የእጅ መዘርጋት ምዕራፍ፥ ፈጣሪ ኢትዮጵያን እንደ ምልክት አድርጎ እንድታበራ የሚያደርግበት የጉብኝት ወቅት ነው። ፈተናችን ሊያጠራን እና ወደ ከፍታችን ሊያወጣን እንጂ ሊያጠፋን የማይችለው ምክንያት፥ ፈጣሪ ስላለና ስለሚረዳን ብቻ ነው። በዚህም ምክንያት ከመሬት ተነስተን፥ ማማ ላይ ስንታይ፥ ክብርን ለፈጣሪ እናመጣለን።
እናት ምጥ ላይ ስትሆን በጭንቋ ተስፋ አትቆርጥም፥ ይልቁንም የሚወለደውን ሕፃን ለመታቀፍ ትናፍቃለች። እኛም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ኩራት እና ለዓለም ተስፋ ሆና ከወደቀችበት ቀና ብላ ቆማ እጆቿን ዘርግታ ልትሞሸር ያለችበት ወቅት በደጅ እንደሆነ የሚያረጋግጥልን፥ የዛሬው በስብራታችን እና በጨለማችን እጆቻችንን ወደ ኢትዮጵያ አምላክ መዘርጋታችን ነው።
ዛሬን ተሰብረን ባዶ እጃችንን ሆነን እጆቻችንን ዘርግተን እርዳን ብለን ስንጮህ፥ ፈጣሪ ወርዶና ፈርዶ የተዘረጉትን ባዶ እጆች በበረከቱ ነገ እንደሚሞላ ሁሉም ይወቀው።
ሦስት ሽህ ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ትንቢት ዛሬ በዓይናችን ፊት እየተፈፀመ እያየን፥ በድንዛዜ ሆነን ለምን እንጨነቃለን? አይሁድ የክርስቶስን መምጣት ለዓመታት ሲጠብቁ ቆይተው፥ ጌታ ሲመጣ የገባቸውና የሰማይ ደስታን የተቋደሱት ጥቂት እረኞችና መንገደኞች ነበሩ። ዛሬም ለዝንተ ዓለም ስንጠባበቀው የነበረው “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” የሚለው ትንቢት ለመጀመሪያ ጊዜ በገሀድ መፈፀም እየጀመረ መሆኑን እያየን ስለሆነ፥ ኢትዮጵያ ልትፈርስ ነው ብለን በመጨነቅ ፈንታ፥ አዲሲቷ ኢትዮጵያ ልትወለድ ነው በሚል እምነት እንፅና።
ፈጣሪ ከመሬት ያነሳቸው የዘመናችን ታላላቅ ሀገሮች፥ ጀርባቸውን ለፈጣሪ በሰጡበት በአሁኑ ወቅት፥ የኢትዮጵያ ሕዝብ አማራ ትግራይ ኦሮሞ ጉራጌ ሶማሌ አፋር ወዘተ ሳይል ሁሉም፥ ግኡዙን ምድር ጨምሮ፥ የፈጣሪን ረድኤት በየዕለቱ በአደባባይ ሲማጠኑ ማየት ትልቅ ምስጢር ነው። የነገው ትልቅነት ዛሬን በፈጣሪ ተደግፎ ለቆመ ደካማ የተመደበ ሲሆን፥ የነገው ውርደት ደግሞ ዛሬን በትዕቢት ተነፍቶ ለቆመ ሃያል የተመደበ ነው። ይህን እውነት ለሚያስተውል፥ ወደ ብሩህ ተስፋችን እየተገፋን እንደሆነ ይታየዋል።
ዋናው ቁምነገር ትንቢቱ የመፈፀሚያው ጊዜ ደርሶ፥ ፈጣሪን በአደባባይና በየቤታችን፥ በየቤተ እምነታችንና በየባለስልጣናት ሰፈር፥ ሃይማኖት ሳይለይ፥ ትልቅ ትንሹ ፈጣሪን እየተጣራ መሆኑ ነው። እኛ ከተሸነፍንለት፥ አምላክ እንደሚያሸንፍልን ለዘመናት የፀና እውነት ነው። እጆቻችንን መዘርጋት ላይ ስለደረስን፥ በዚህ ብቻ ደስ ይበለን። አምላክ የሚታመኑትን አሳፍሮ አያውቅም። ከሁኔታዎቻችን ላይ ዓይናችንን አንስተን፥ ሰዓቱ ሞልቶ እጆቻችንን የመዘርጋት ምዕራፍ መጀመራችንን እያየን፥ የፈጣሪን ክብር ለማየት በመጠባበቅ በደስታ ወደ የሥራችን እንሰማራ።
ፍርሃቴ የመጎብኘት ዘመን አይመጣ ይሆናል የሚል ጥርጥር ሳይሆን፥ መጎብኘታችን የማይቀር የሚፈፀም የፈጣሪ ተስፋ እንደሆነ በማወቅ፥ እርግጠኝነት ላይ በመድረስ፥ ያኔ ስንጎበኝ እኛም በጊዜያችን ፈጣሪን እንዳንረሳ ነው። ለዚህም ይሆናል ምኞት አይከለከልምና የፈጣሪን ውለታ ማስታወሻ እኛ ደግሞ በሰንደቅ ዓላማችን ላይ የተዘረጉ እጆች እንዲያርፉበት እናደርጋለን ብዬ የምፀልየው። ኢትዮጵያ ታላቅ ስትሆን፥ ከመፍረስ ታድጎ ለታላቅነት ያበቃትን አምላክ ያኔ በክብር ታከብረዋለች። አምላክ ምልክት አድርጎ ለአርአርያነት ሲያበቃት፥ ያኔ እኛም በፈጣሪ ስር እንዳለ አንድ ቤተሰብ ሆነን እንገለጣለን። በእውነት መነፅር ኢትዮጵያን ስንመለከት፥ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ብሎ ለመስጋት እንዴት ይሆንልናል? እውነት፥ ለውርደት የምትፈርስ ኢትዮጵያን ሳይሆን ለክብር የምትወለድ ኢትዮጵያን ያሳያልና!