በዳማት (አበሻ) ምድር ላይ ርስት እና ብረት ምን ማለት እንደሆነ የዚህን ህዝብ ባህል እና ማንነት መግለፅ ለቀባሪ ማርዳት ከመሆኑ በላይ ፤ መድከም ነዉ፡፡
በኢጣሊያ ዳግም ወረራ ራስ/ ደጃአዝማች በላይ ዘለቀ ……ሶማ በረሃ ሲገቡ አንድ ለአንድ ጠበንጃ ይዘዉ እንደሚሆን አያጠያይቅም ፡፡
ነገር ግን በዘመኑ ጠላትም ሆነ መንግስት ያልተረዳዉ ፅኑ ዓለማ እና ሙሉ ልብ እንደነበራቸዉ ነዉ ፡፡ በላይ ዘለቀ ከ40,000 በላይ ጦር ሲመለምሉ፣ሲያዘጋጁ፣ ሲመሩ እና ሲያዋጉ ዘንግ እና ከዘራ ይዘዉ አልነበረም፡፡
ዓምላክ ልበ ሙሉ አድርጎ ሲፈጥራቸዉ የጣሊያን ወራሪ ኃይል እና አሽከሮች በገቡበት እያሳደዱ መጀመሪያ ክንዳቸዉን ቀጥሎ የተሸከሙትን ዘመናዊ ጦር በማራገፍ እና ተከታዮቻቸዉን በማስታጠቅ እንደነበር የሚጠቀስ ነዉ ፡፡
በጎጃም (ዓባይ ፣ ሶማ ፣ ሸበል…..) ፣ ሸዋ እና ወሎ ወራሪ ፤መሰሪ ጠላትን ከዉስጥ ምንደኛ ባንዳ ጭምር መዉጫ መግቢያ በማሳጣት ትንፋሽ እስኪያጣ አይቀጡት ቅጣት በመቅጣት ከጎጃም እና ዙሪያ የደመሰሱት በዓለማ ቁርጠኝነት እና የድል ባለቤትነት እንደነበር ወዳጅ ቀርቶ ጠላት የተመለከተዉ እና የሚመሰክረዉ ፤የመሰከረዉ ነዉ ፡፡
በላይ ዘለቀ የንጉሱ ጦር አላሰለጠናቸዉም ፣ልረዳቸዉም ፤ አላስታተቃቸዉም እንዲያዉም ከኢጣሊያ ወረራ አስቀድሞ በረሀ የወጡ እና ከነበረዉ ስርዓትም የሚግባቡ አልነበሩም በዚህም ከነጻነት ማግስት ከጠላት ( እንግሊዝ) ዳኝነት ብቀላ ተፈጽሞባቸዋል፡፡
በአሁኑ ዘመን ቢያንስ ደጃች በላይ ዘለቀን የሚስተካከል ልበ ብርሃን እና ልበ ሙሉ ባይኖር እንኳን የራሳቸዉን ፈለግ የሚከተል ከ 500 ማያንስ ጀግና ከአቢሲንያ ፣ ከፈለገ ግዮን( ከአባግዮን መንደር) እንደማይጠፋ መጠራጠር ሠዉ አለመሆን ስለሚሆን የክልሉ መንግስት ብረት እና ርስት(ብር) ለዘረፈህ ታሪካዊ ጠላት ብረት እና ርስትህን መልስ ፤አስጠበቅ ማለቱ ተገቢ ጥሪ ነዉ ፡፡
ከሰሞኑ የዓማራ (ዳማት) ግዛት የመንግስት አስተዳደር“ አጥፍቶ ጠፊዎች ” እያደረጉ ላሉት የአገር ክህደት እና የህዝብ ጥፋት ሊገታ እና ሊመታ የሚችለዉ በህዝባዊ ተሳትፎ መሆኑን በመቀበል የክልሉ መንግስት ህዝባዊ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ይህም በክልሉ ህዝብ በተለይም በወጣቱ በተለያ ጊዜ እና ዓመታት እነዘጋጅ ጥያቄ ለዓመታት የቀረበ ቢሆንም ይህ የህዝብ የቀደመ ስጋት ዕዉነተኛ ለመሆኑ የዚህችን አገር ጥልቅ ታሪክ እና ጥንታዊነት ለሚያዉቅ ተጠባቂ እና ተገማች ነበር ፡፡
የዘመናት ህዝብ የማንነት ፣የነጻነት፣ አትንኩኝ ባይነት እና ዝግጅት ጥያቄ ትተን የቅርቡን ምን አልባትም ከአምስት ወራት በፊት በዓማራ ክልል የሚገኝ ህዝብ በተለይም ወጣቱ ከሊቅ አስከ ደቂቅ በነቂስ በሁሉም የሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚኖር ዜጋ ራሳችንን፣ አገራችንን እና አካባቢያችንን ከጥቃት ለመታደግ አገሩን እና ወገኑን የሚወድ መንግስታዊ ሆነ ያልሆነ ሁሉ እንድንደራጅ ይርዳን፣ይረዳን እና ይደግፈን ብለዋል ፡፡
ለጊዜዉ ጆሮ ዳባ ልበስ መባሉን እና ሌላ ስም ለመስጠት የቋመጠ ሁሉ የኢትዮጵያን እና ህዝቧን በሠላም ፣በዕድገት እና በብልፅግና መኖር ለማይፈልግ የዉስጥ እና የዉጭ ጠላት እንደ መልካም አጋጣሚ ያዩት መኖራቸዉን በተግባር የታየበት ሁነት ነበር ፡፡
ከዚህ በተቃራኒ ጠላት ያፈረበትም ጉዳይ መኖሩን ስንጠቅስ በተለይ የዓማራ ወጣት ትግላችን ሆነ ጥያቄያችን አገርን እና ህዝብን ከሚመጣ እና እየሆነ ካለ ብሄራዊ አደጋ ለመከላከል እንጅ የየትኛዉም ወገን ጥቅም እና ስልጣን ለማስጠበቅ ወይም ለማስነጠቅ አይደለም በሚል ቅጠል ሳይበጠስ ፤ ምንጭ ሳይደፈርስ መልዕክታቸዉን/ መልዕክቱን ለዓለም ማሰማት የተቻለበት ልዩ እና ታሪካዊ ትዕይንተ ህዝብ እንደነበር ተጠቃሽ ነዉ፡፡
የክልሉ መንግስትም ሆነ ማዕከላዊ መንግስት ያን ዕዉነተኛ እና ትንቢት የሚመስል ህዝባዊ አርቆ አስተዋይነት እና ነብይነት ለአገር እና ለህዝብ ጥቅም ሲባል በለሆሰሳ እና በጥሞና በመቀበል ዕዉቅና በመስጠት ተግባራዊ ምላሽ ሰጥቶ ቢሆን ዳግም ዛሬ አገሪቷ እና ህዝብ ተደጋግሞ ለተፈራዉ መቋጫ ላጣ መከራ እና ስቃይ ባልተዳረጉ ነበር ፡፡
ኢትዮጵያ አገራችን ህዝብን እና አገርን እንደመዥገር ተጣብቀዉ ደም ከሚጠጡት ዉጭ የህዝብን ድምፅ እና ጩኸት የሚሰማ ባለመኖሩ ይህ ልማድ ሆኖ ቀጥሏል፡፡
ይህ ህዝብ እና መንግስት የመደማመጥ ባህል ግን የሚቀየርበትን ሁኔታ በክህደት ለሚታበይ ጠላት በመጣ መጠን ያለፈ ግፍ እና ወረራ የዓማራ ክልል የህዝቡን ብሄራዊ የነጻነት ትግል ተሳትፎ ዕዉቅና በመስጠት ላደረገዉ ጥሪ ቢረፍድም በሚኖረዉ አወንታዊ ሚና ክብር እና ቅቡልነቱን ማስመር ያስፈልጋል፡፡
ህዝብ ለዓመታት እንደራጅ ሲል ባጅቱ ከሰሞኑ ትጥቅ እና ስንቅ የአንተ እና የአገርህ ህልዉና ነዉ እና ያለህን ይዘህ በራስህ ወዝ እና ደም ከህዝብ ኪስ በተዘረፈ ሀብት እና ንብረት ጠላት የታጠቀዉን የጦር መሳሪያ በመማረክ ራስህን እና አገርን ከጥፋት ታደግ የሚለዉ የመንግስት(ክልል) ከፍተኛ ህዝባዊ መነቃቃት የሚፈጥር እና ድሉንም በመጠነኛ ጥረት እና በአነስተኛ ጊዜ እንደሚያቀርበዉ ዕሙን ነዉ፡፡
ከጠላት የሚቀማዉ ወይም የሚማርከዉ የጦር መሳሪያ የግል ባለንብረትነት መሆኑ ከመረጋገጡም በላይ በጦር አዉድ የክልሉ ህዝብ ለሚያደርገዉ ራሱን ፣አካባቢዉን እና አገሩን ከጠላት ወረራ ለመታደግ በሚኖረዉ ትንቅንቅ የድል ባለቤትነት እና ሽልማት በመሆን ለጀግኖች ቁርጥ ቀን ልጆች ዕዉቅና እንደመስጠት በመሆኑ ወቅታዊ እና ትክክለኛ የድል አድራጊነት ስልት ነዉ ፡፡
እንግዲህ ልብ እና ልባዊ ብሄራዊ ፍቅር እና ክብር እንጅ ትጥቅ አለመኖር የነጻነት ትግሉን ጥረት እና ጊዜ ለማሳጠር እንደ ዋና ችግር ላይሆን ይችላል፡፡
ይህ ብረት(የጦር መሳሪያ) እና ርስት/ብር ለአቢሲንያ፣ዳማት ወይም በአሁኑ ዓማራ እና ድፍን ኢትዮጵያ የሞት ሽረት (ህልዉና) ጉዳይ ስለመሆኑ ማብራራት ….ድካም ይሆንብኛል፡፡
ምንጊዜም በሠላም ሆነ በጦርነት ጊዜ ለቀጣይ እና አስተማማኝ ለዉጥ እና ዕድገት የስራ ፈጠራ እና ዕዉቀት ወሳኝ ስለሚሆኑ እና እነኝህም በባህሪያቸዉ ግላዊ (የግል ) መሆናቸዉ ስለማያጠያይቅ የጥረት፣ የስራ ፣የድል ፣ የጀግንነት …..ዉጤት ባለቤትነት ሲረጋገጥ ከፍተኛ ለዉጥ እና ዕድገት በየትኛዉም መስክ መመዝገቡ አይቀርም እና የጠላት ትጥቅ የአንተ እና ለአንተ እና ለአገር ማጥፊያ ነዉና ነብረትህን ንብረት አድርግ ራስህን ፣ ህዝብህን እና አገርህን ከአጥፍቶ ጠፊዎች ታደግ አቻ የለሽ ወራደራዊ ስልት በመሆን አዋጭ እና ተመራጭ ወቅታዊ ፤ህዝባዊ ቅስቀሳ ነዉ ፡፡
እዚህ ላይ ትልቁ ነገር ራስን እና አገርን ከጥፋት ለመታደግ በሚደረገዉ ጥንቅንቅ እና ተጋድሎ የጠላትን ትጥቅ ለራስ የማድረግ የንብረት ባለቤትነት ከመሆን የላቀ ጠላትን ድል በማድረግ የሚኖረዉ የድል ባለቤትነት ዕዉቅና እና ባለቤትነት ለትዉልድ የሚያስተላልፈዉ ታሪካዊ ዘላለማዊ ክብር እና ስም ነዉ ፡፡
ሠዉ በራሱ ምድር ፤ሠዉ በራሱ መንደር ከሆነ ባይተዋር፣
ጠላት ሲመኝልን ዉድቀት እና ዉርደት እየሞቱ መኖር፣
አስኪ እኛ እናሳየዉ እንዴት እንደሆነ እየኖሩ መሞት ለራስ ፤ለአገር ክብር፡፡
ተባብሮ በአንድነት ድሮ ከጥዋቱ እሾክ አሜኬላ ነቅሎ መጣል ጠፍቶን፣
ዕድሜ ልክ መከራ በሬ ካራጅ ሆነን ፣
እነርሱ አዉሬ ሆነዉ እኛ በበግነት እንዴት ይዘለቃል“ ጠፊ እና አጥፊ” ሆነን ፡፡
የማይሆን ነዉና ዕድሜ ልክ መኖር አጋም እና ቁልቋል ሲላቀሱ መኖር፣
የዞትር ዕሮሮ ፤የዞትር መከራ ከሞት ለማያድን ለሚያሳጣ ክብር፣
ወገኔ ተነሳ ከንቱ አትዘናጋ ይህን ዕኩይ አረም የዘመን ነቀርሳ የማይበጅ ለሀገር ፣
ተባብረን እናርም እሾኩ ፤ ይቃጠል አረሙ ፤ይቀበር ቅሪቱ ይሁን እንዳልነበር ፡፡
“አንድነት ኃይል ነዉ ”
ማላጂ