ህወሓት የበግ ለምድ ያጠለቀ ተኩላ ባህሪያትን የተላበሰ ተቸካይ ስብስብ ስለሆነ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል!!!

ህወሃት አዲስ ሃሳብ የሌለው፤ በድሮ በሬ የሚያርስ፤ ተቸካይ ስብስብ ሆኗል። የበግ ለምድ ያጠለቀ ተኩላ ባህሪያትን የተላበሰ ስለሆነም የሚፈልገውን እስኪያገኝ ድረስ ህዝባዊ መስሎ ቀርቦ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን እውነተኛ ማንነቱን የሚገልፅ ቡድን ነው።  ብዙዎቻችን እንደምናውቀው ህወሓት በትጥቅ ትግሉ ወቅትና ስልጣን ይዞም በጣም ለአጭር ጊዜ “ጠላቶቸ ደርግና ገዥ መደቡ እንጅ ህዝቡ አይደለም” በማለት በየመድረኩ ሰብኳል። ስብከቱ እውነት መሆኑን ለማስመሰልም ህዝባዊ መልክ ያላቸው ስራዎችን ይሰራ እንደነበርም ይታወቃል። በዚህ ረገድ እስረኞችን መፍታቱ፣ አዳዲስ የሚዲያ ተቋማት እንደአሸን እንዲፈሉ መፍቀዱና የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲፈጠሩ ማድረጉ ተጠቃሾች ናቸው። በወቅቱ የተለያዩ አካባቢዎችን ይቆጣጠሩ የነበሩ ተዋጊዎቹም ህዝባዊ መስለው እንዲታዩ ጥረት አድርጎ ተሳክቶለታል። እንዲያውም እኔ የማውቃቸው ተዋጊዎችስ አይደለም ህዝብ ቀና ብለው ሊናገሩ እንጀራ እንዲጋገርላቸው ሲፈልጉ እንኳ በስነ ስርዓት ጠይቀው እንደነበረ አስታውሳለሁ። በነገሬ ላይ በተሳሳተ መንገድ ለትግል እንድወስን ያደረገኝም (እነዚህን ተዋጊዎች አይቸ) ድርጅቱ ህዝባዊ ነው የሚል እምነት ማሳደሬ ነው።

እንዳለመታደል ሆኖ ግን ህወሃት የሃገሪቱ ስልጣን ሙሉ በሙሉ በእጁ እንደገባ ካረጋገጠ በኋላ እውነተኛው ማንነቱ (Its true colour) ተገለጠና በኢትዮጵያ በተለይም በአማራ ህዝብ ላይ ሰይፉን መምዘዝ ጀመረ። በተለይ ትምክህተኛ፣ ቢሮክራት፣ የገዥ መደብና የደርግ ርዝራዥ እያለ ምንም የማይመለከታቸውን ንፁሃን ዜጎች ማሳደድና ማሰቃየት ስራየ ብሎ ተያያዘው። በዚህ ረገድ ወታደራዊ የመረጃና የክትትል ቡድን በየአከባቢው አቋቁሞ አማራን ለማዳከምና አንገት ለማስደፋት የፈፀመው እጅግ አሰቃቂ በደል ተጠቃሽ ነው። ንፁሃን ለፍተው፣ ጥረውና ግረው ያፈሩትን ሃብት ከመውረስና ከመዝረፍ በተጨማሪ ጠባብ ክፍል ውስጥ እያስገባ ያደርስባቸው የነበሩ አካላዊና ስነልቦናዊ ሰቆቃዎች ታሪክ ሲያስታውሳቸው ይኖራል።

ለምሳሌ የቀበሌ የህብረት ሱቅ ገንዘብ ያዦች፣  የደርግ ታጣቂዎች፣ ተራ የኢሰፓ አባላት፣  የቀበሌ አመራሮችና ስጋት ይሆኑኛል ብሎ ያሰባቸውን ሌሎችንም ንፅኋን ቢሮክራቶችና የደርግ ርዝራዦች እያለ እጃቸውን የፊጥኝ አስሮ በጣታቸው ደም እስኪንጠባጠብ ድረስ ያሰቃያቸው እንደነበር የሚካድ አይደለም።  ሌሎቹን ደግሞ የሽጉጥ አፈሙዝ አፋቸው ውስጥ በማስገባትና ራስ ራሳቸውን በመቀጥቀጥ ሌላ ጊዜ አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዳይኖሩ ለማድረግ የሄደበት ርቀት ቀላል አልነበረም።  እነዚህን ለምሳሌ አነሳሁ እንጅ ህወሓት የፈፀማቸው ግፎችና ሰቆቃዎች በዚህ ብቻ የሚያበቁ አይደሉም።

አሁንም ህወሓት እየሄደበት ያለው መንገድ ተመሳሳይ ነው። እንደምታዘበው የኢትዮጵያን በተለይም የአማራን ህዝብ የማታለል ጥረት ጀምሯል። ለምሳሌ በሚዲያዎቹና በተቆጣጠራቸው የአማራና የአፋር አከባቢዎች “የምፈልገው የአማራ ልሂቃንን፣ መከላከያ/ህዝባዊ ሰራዊቱን፣ ብልፅግናንና አብይን እንጅ ህዝቡን አይደለም የሚል አስመሳይ ስብከት እያሰማ እንደሆነ እያደመጥን ነው። ልክ ከ1984 ዓ.ም በፊት ያደርገው እንደነበረው ሁሉ ህዝባዊ የሚመስሉ ባህሪያት ሊያሳይ እንደሚችል እገምታለሁ። ይህ ቡድን  ተሳክቶለት እንደገና ሃገሪቱን የመቆጣጠር እድል ቢያገኝ ግን ባባለፉት ሃያ ሰባት አመታት የፈፀማቸውን ግፎችና ሰቆቃዎች ምናልባትም በከፋ መንገድ ሊደግማቸው እንደሚፈልግ ከተፈጥሮው በመነሳት ለመረዳት የሚከብድ አይደለም። ስለዚህ የህወሓትን እኩይና አስመሳይ ባህሪያት በሚገባ በመገንዘብ ህዝቡ እንዳይደናገር የሚያደርግ ስራ መስራት አስፈላጊ ነው ብየ አምናለሁ።

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.