ሰኔ 24 ቀን 2013
ብዛት ያለው የትግራይ ተወላጅ፣ አምባገነኑን ወያኔን ማስወገድን ጨምሮ፣ “ኢትዮጵያ ትመርጣለች!” እና “ኢትዮጵያን እናልብስ!” በመሰሉ እጅግ ግዙፍ የኢትዮጵያ ፕሮጀክቶች ሳይሳተፍና አስተዋጽዖ ሳያደርግ ቀረ! ያሳዝናል! ይህ የሆነው በወያኔ ተሸውዶ ነው፤ አሁን ይህ አንዴ ተፈጽሞ፤ ታሪክ ሆኗል፤ ወደ ኋላ ተመልሰን እንዳይሆን ማገድና መለወጥ አንችልም! እኛ አቅምና ሥልጣን ያለን በዛሬና በነገ ላይ ነው! ዛሬም፣ ኢትዮጵያ እጅግ ግዙፍ የሆኑ ሌሎች ሕይወት ለዋጭ የዕድገት፣ የሰላምና የለውጥ ፕሮጀክቶችን ወጥና በመፈጸም ላይ ትገኛለች፡፡ ኢትዮጵያውያን በፈተናም ውስጥ ሆነን እንኳን ታሪክ በመሥራት ላይ ነን! አሁን የሚታየው የሐይል አሰላለፍ ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ፣ የወያኔ ደጋፊ የሆኑ ብዙ የትግራይ ተወላጆች፣ የታላቁን የአባይ ግድብ ግንባታ አጠናቆ ሥራ በማስጀመርና በመሰል የታሪክ ሥራዎች ተሳታፊና ተቋዳሽ ላይሆኑ ነው፡፡ እንዳለፉት 3 ዓመታት ይህም ተሳትፎ ካልተሳካ፣ ቢያንስ በድጋሚ አሳዛኝ የታሪክ ጠባሳ ልንተው ነው፡፡ የትግራይ ተወላጆች፣ በቀሪዎቹ የኢትዮጵያ የዕድገት፣ የሰላምና የለውጥ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ውስጥ ቀልባቸውን ሰብስበው ይካፈሉና አስተዋጽዖ ያደርጉ ዘንድ የጥሞና ጊዜ በእርግጥ ያስፈልጋቸዋል!
የወያኔ ደጋፊ ቁጥሩ ብዙ ነው!
ከእንግዲህ ወያኔ ድንገተኛ አደጋ ጣይ ሽፍታ እንጂ፣ አስፈሪ ወራሪ ኃይል የሚሆንበት ቁመና የለውም፡፡ የትናንቱ የመሪ ስብስብ የለ! ሠራዊት የለ! ባንክ የለ! ታንክ የለ! ሞራል የለ! ጤና የለ! መዋቅር የለ! …
ከወያኔ ጋር በተያያዘ ዛሬ አሳሳቢ የሚሆነው፣ ቁጥሩ የበዛ የትግራይ ተወላጅ አሁንም እንደተሸወደ መሆኑ ነው፡፡ ለ47 ዓመታት በትህነግ መዋቅር ውስጥ የታቀፈው ቁጥር እጅግ ብዙ ነው፤
– የወያኔ አባላት ብቻ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው!
– በአባላቱ ላይ ቤተሰቦቻቸው፣ ጎረቤቶቻቸውና ወዳጆቻቸው ይጨመራሉ፤
– በነዚህ ላይ ደግሞ ወያኔ ያደራጃቸውና የሚቆጣጠራቸው የ1ለ5 ዓባላት፣ የሕዝብ ክንፍ አባላት (የሴት፣ የወጣት ሊግ፣ ዕድር ወዘተ)፣ የሲቪክ ማኅበራት (የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጭምር)፣ የሜዲያ አባላትና ልሂቃን ወዘተ ይጨመራሉ፤
– በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች እየኖሩ፣ በብሔራቸው ምክንያት በአድልዎ ልዩ ተጠቃሚ የነበሩ ብዙ (ሁሉም አይደሉም!) የትግራይ ተወላጆችም እዚህ ውስጥ ይገባሉ፤
– እነዚህ መላውን የትግራይ ሕዝብ ባይወክሉም፣ ወደድንም ጠላንም ሰፊ የሕዝብ ቁጥር ይወክላሉ፡፡
በወያኔ ተሸውደው የኢትዮጵያ የለውጥ ፕሮጀክቶች አካል ያልነበሩትን እነዚህን ሁሉ የትግራይ ተወላጆች “የራሳቸው ጉዳይ” ብለን ጥለን ልናልፋቸው አንችልም! ልዋጋም ብትል ከነዚህ ሁሉ ጋር ተዋግተህ አትችልም፤ ከገዛ ዜጎችህ ጋር መዋጋትም ትክክል አይሆንም (Civil war)፡፡ ከጦርነት ውጭ ያሉ ልዩ ልዩ አማራጭ የመፍትሔ ሐሳቦችን ማጤን ግድ ነው፡፡ ለትግራይ ሕዝብ የጥሞና ጊዜ እንስጠው መባሉ ትክክል የሚሆነው ለዚህም ጭምር ነው፡፡
የጥሞና ጊዜ የሚያስፈልግበት ምክንያት
ሰው ፍጹም አይደለም፣ በሕይወት ዘመኑ፣ በኑሮ፣ በሥራና በግንኙነት ሂደት ጎዳና ላይ መሳሳቱና ማጥፋቱ፣ ራሱን ወይም ሌላ አካልን መጉዳቱ የማይቀር ነገር ነው፡፡ መሳሳት ብርቅ ነው እንዴ?! እርግጥ አንዳንድ ስህተትና ጥፋት ከመክፋቱ የተነሣ ለማረም፣ ለመታረም፣ አገግሞ ለመመለስና የበደሉትን ክሶ ሕይወትን ለማስቀጠል ዳግመኛ ዕድል አይሰጥ ይሆናል! ይህ አለመታደል ነው!
ነገር ግን፣ አብዛኛውን ጊዜ የሚሆነውና ገዢው ነገር፣ ከስህተት ተምሮ ሕይወትን ለመቀጠል ፈጣሪም ሕይወትም ዕድል የሚሰጡ መሆናቸው ነው፡፡ ብልህ ከምክር ይማርና ራሱን ከስህተትና ከውድቀት ይጠብቃል፤ በምክር አልባንን ያለ ደግሞ ምናልባት በሌሎች ላይ የደረሰ መከራን አይቶም ሊማር ይችላል፤ ከምክርም ሆነ በሌሎች ከደረሰ መከራም ለመማር ዝግጁ ያልሆነ ሠነፍ ደግሞ የተፈራው፣ የተነገረውና በሌሎች ላይ ደርሶ ያየው መከራ በራሱ ሲደርስበት፣ ማለትም በአሳር ብቻ ይሆናል የሚማረው፤ ይኸውም ካልረፈደበት ነው! ከስህተት፣ ከጥፋት፣ ከመከራና ከአሳር በኋላ የማረምና የመታረም ዕድል ባለ ጊዜ ትልቁ ቁምነገር ተመሣሣይ ስህተትን ማቆም፣ አለመደጋገም፣ ከስህተት መማርና ወደ ተሻለ አፈጻጸም ለመጓዝ ከልብ መሻትና መጣር ነው!
“ስህተቶች ወደ አዳዲስ ግኝቶችና ስኬቶች መግቢያ በሮች ናቸው” (Mistakes are portals of discovery) ይባላል:: ስህተቶችን በቅንነትና ቆፍጠን ብሎ ለመረመራቸው፣ ውጤታቸው ዓይን ገላጭ ብቻ ሣይሆን ጨዋታን / ሕይወትን ቀያሪም ነው፡፡
በአንድ በኩል ጠንካራ ሥራና ስኬትን አጠናክሮ ለመቀጠል፣ በወዲህም ከስህተት፣ ከውድቀትና ከጥፋት ተምሮ ለመታረም ከሚያስችሉ የታወቁና ተሞክረው ከሠሩ ዘዴዎች መካከል አንዱ ጥሞና ነው፡፡
የጥሞና ተግባር ምንነት፣ መርሆዎች፣ መገለጫዎችና አካሄዶች
– የጥሞና ጊዜ (Time of Reflection)፣ መነሻና መድረሻው በተወሰነና በታወቀ የጊዜ መሥመር ላይ በዓይነ ህሊናና ልቡና በመጓዝ ራስን በታማኝነት ማየትና መፈተሽ ማለት ነው፤
– የጥሞና ጊዜ ማለት ከንስሐ ዝቅ ያለ ደረጃ ያለው፣ የነፍስ/ሕሊና እና የሥጋ/ስሜት መጠያየቂያና ዕውነትን መርምሮ፣ ፈትሾና ፈልጎ የማግኛና የመተማመኛ ጊዜ ማለት ነው፤
– ሰው በጥሞና ጊዜው፣ በአንኳር ጉዳዮች ዙሪያ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ይጠይቃል፤ ምን? መቼ? ለምን? ምን ያህል? እንዴት? በምን? ከማን ጋር? እንደሠራ ወይም እንዳልሠራ፣ ማንን እንደጠቀመና እንደጎዳ ወዘተ በሐቀኝነት፣ በቅን መንፈስ፣ በንጹህ ልቡና ራሱን የሚጠይቅበትና መልስ የሚያገኝበት ከራስ ጋር የመነጋገሪያ ጊዜ ነው፤
– በጥሞና ጊዜ (የንስሐ ታናሽ) ራስን ማታለልና መሸዋወድ አክሳሪዎች ናቸው፤ የምንሰራውን የራስ በራስ ግምገማችንን ሁሉ ሕሊናችን ይመለከታል፤ ሕሊና የፈጣሪ ተወካይ ማለት ነው፤ በግምገማ ጊዜ ለስሜታችንና ለጥቅማችን ተሸንፈን፣ ህሊናችንን ሳንፈራ ራሳችንን ልናታልልና ፍርድ ልናዛባ ብንሞክር ፈጣሪም ያያል! ብሎም ይፈርዳል!
– ሰው በጥሞና ወደ ኋላ ተመልሶ የሠራውንና ያልሠራውን፤ መሆን ሲገባው ያልሆነውን፣ መሆን ሳይገባው የሆነውን፤ ምን እንዳለማ፣ ምን እንዳጠፋ ሁሉ አንድ በአንድ መመርመር አለበት፤
– የጥሞና ጊዜ፣ ጥፋቶችን፣ ስህተቶችንና ያልተሳኩ ነገሮችን ከተፈጸሙበት መንገድና ዘዴ ይልቅ በሌላ በምን ዘዴ ቢሰሩ ኖሮ ከስህተት ይዳን ወይም የተሻለ ውጤት ይገኝ እንደነበር በሐቀኝነት መመርመርንም ያጠቃልላል፤
– የጥሞና ጊዜ መውሰድ፣ ለግለሰብም፣ ለትንሽና ለትልቅ ቡድንም ወይም ለሰፊ ማኅበረሰብም ይጠቅማል፤
– የጥሞና ጊዜ ዋና ግቡ፣ በተለይ ከስህተት፣ ከጥፋትና ከውድቀት ተምሮ፣ ከሌሎችም ጋር ታርቆና ተናቦ የወደፊቱን ጊዜ፣ ሥራና ሕይወት ማሻሻልና የተሳካ ማድረግ ነው፡፡
ፈጣሪ ይርዳን!!!