የኢትዮ ቴሌኮም ለውጪ ሀገር ድርጅት ይሸጥ ወይስ አይሸጥ ? (መላኩ ከአትላንታ)

ሁሌም የሀገራችንን ፖለቲካ የሚዘውረው ህገ መንግስት ላይ በማተኮራችን ፣ የኢኮኖሚ ነክ ጉዳዮችን አናሳና ጥቃቅን ብለን ትኩረት አንሰጣቸውም። ወደ ኢኮኖሚው መስክ ፊትን በማዞር ፣ የኢትዮጲያ ቴሌኮሚኒኬሽንን በመሸጥ ኢትዮጲያ ተጠቃሚ ትሆናለች አትሆንም ለሚለው ጥያቄ ፣ እንደ አንድ የኢኮኖሚ መስክን ከግል ንግዱ ዘርፍ አንፃር እንደሚረዳ ባለሙያ ጉዳዩን ስመለከት፣  ስለድርጅቱ የማውቃቸው በርካታ የውስጥ ጉዳዮች በህሊናዬ ይመላለሳሉ።

በደርጉ ዘመን የኢትዮጲያ ቴሌኮሙኒኬሽን ትርፍ ሙልጭ እየተደረገ ለሲቪል ሰርቪሱና ለወታድሩ ደመወዝ መክፈያ ይውል የነበረ ቢሆንም በባለሙያዎች ይተዳደር ነበር ። ሁኔታው እድገቱን በብዙው ጎድቶታል። በወያኔ ዘመን ደግሞ ይባሱኑ በርካታ ልምድ ያላቸው የድርጅቱ ከፍተኛ ባለሙያዎች በብሄረሰብ ማንነት ካርድ እየተመነጠሩ ፣ የባለጊዜዎች መጠቃቀሚያና የንቅዘት ማዕከል ነበር። ዛሬም ከዚህ የተለያ ሁኔታ ስለመኖሩ ማስረጃ የለም።  የድርጅቱ ትርፍና ኪሳራ በትክክል ታውቆ ትርፉም ሆነ የሚገኝ ብድር ፣ በድርጅቱ በተጠኑ የምርምርና ዕድገት ( R &D ) አቅጣጫዎች ላይ እንዲውል ባለመደረጉ ትርፋማው ድርጅት ፣ በበቂ ሁኔታ ሊያድግ በአለም አቀፉም መድረክ ተፎካካሪ ሊሆን አልቻለም።

ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጲያ መደወል ፣ ወደ ኬኒያ ናይጄሪያ ወይም ህንድ ከመደወል ዋጋው ምናልባትም ከኪዩባ (Cuba) ቀጥሎ እጅግ ውድ የሆነበትን ሁኔታ ስናይ ፣ የኢትዮጲያ ቴሌኮሙኒኬሽን ከተመሰረተ ጀምሮ  ከገበያ ህግጋትና ውድድር ውጪ በሆነ መንገድ መተዳድሩ የችግሩ አብይ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል እንገነዘባለን። በሀገር ውስጥም ቢሆን በዋጋ ፣ በግልጋሎት ጥራት ፣ በተደራሽነት ወዘተ ያሉት ችግሮች ዋና ምክንያታቸው  ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ተፎካካሪ የሌለው የመንግስት ቢሮክራሲ አካል መሆኑ እንደሆነ ግልፅ ነው። ይህ ሁሉ ችግር እያለው ወደ ግል ይዞታ እንዲተላለፍ የውጭ ሀገራት አይናቸውን የጣሉበት ትርፋማ ድርጅት ስለሆነ ነው።

እነዚህን የኢትዮ ቴሌኮም ጠቅላላ ችግሮች በአንድ በኩል ፣ በኢትዮጲያ መንግስት ላይ ያለውን ጫና እና  የዓለም አቀፍ ድንበር ዘለል ኩባንያዎች የአለምን ኢኮኖሚ የመቆጣጠር ጠንካራ ፍላጎት በሌላ በኩል በመያዝ ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ለውጭ ኩባንያ ቢሸጥ የሚኖሩትን ጥቅምና ጉዳቶች ማገናዘብ ይኖርብናል። የአለም ባንክ (World Bank) ፣ የአለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (International Monetary Fund) እና የበለፀጉት ሀገራት ፣ በአፍሪካ ፣ በምስራቅ አውሮፓ ወይም በሌሎች ሀገራት ያሉ መንግስታዊ ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታ ቀይሩ ፣ ለውጭ ፉክክርም ክፍት አድርጉ ፣ የሚሉበት ዋነኛ ምክንያት ለነሱ ድንበር ዘለል ድርጅቶች ገበያ ፍለጋ ወይም ገበያ ማስፋት እንጂ ለኢትዮጲያውያን ጥቅም እንዳልሆነ ግልፅ ሊሆንልን ይገባል። ይህን መሰረታዊ ሀቅ ይዘን የኢትዮ ቴሌኮምን መሸጥ ያለውን ጥቅምና ጉዳት እንመልከት።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሁለቱም ጓዛቸውን ጠቅልለው ኢትዮጵያ ውስጥ ከትመዋል! - ግርማ በላይ

 

ኢትዮ ቴሌኮምን መሸጥ ያሉት ጥቅሞች

  1. የኢቲዮ ቴሌኮምን በጨረታው አሸንፎ የሚገዛው የውጪ ድርጅት የሚከፍለው ክፍያ ፣ ለአንድ ጊዜ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ መንግስት ካዝና ያስገባል።

 

  1. ድርጅቱን ለማዘመን የሚያስፈልገውን የቴክኖሎጂ ግብዓት ለማደራጀት የሚሆን ብድር ፣ ገዢው የውጪ ድርጅት ከውጭ ሀገር አበዳሪዎች በውጭ ምንዛሪ በመውሰድ ፣ ቁሳቁሶችና ባለሙያዎች ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባል።

 

  1. በሙያው ሰፊ ልምድ ያላቸው የውጭ ባለሙያዎች ኢትዮጲያ መጥተው በመስራት፣ ልምዳቸውን ለኢትዮጲያውያን ያካፍላሉ።

 

  1. የድርጅቱ የእድገት ፣ የዝመና እና ሌሎች ፍላጎቶች ሳይገናዘቡ የሚገኘው ትርፍ የመንግስት ወጪ መሸፈኛ መሆኑ ስለሚያቆም ፣ ድርጅቱ ከጊዜውጋ በቀጣይነት በመዘመን ግልጋሎቱ ትልቅ መሻሻልን ያሳያል።

 

  1. አሁንም ቢሆን ለሳተላይትና መሰል ጉዳዮች በውጭ ምንዛሪ የሚከፈል ክፍያ እንደሚኖር የሚጠበቅ ቢሆንም ፣ ምናልባት ገዢው የውጪ ድርጅት የራሱ ሳተላይትና መሰል መሰረታዊ አቋም (Infrastructure) ካሉት ፣ ለዚህ በየወሩ የሚወጡ ወጪዎች ከኢትዮጲያ እንዳይከፈል ወይም ቢከፈልም ባነሰ ዋጋ እንዲከፈል የሚያደርግበት ሁኔታ አለ። ነገር ግን በሂሳብ አያያዝ ህግ የትርፍ ማዕከል (Profit center) እንዲሁም የዋጋ መሸጋገር (International Transfer Pricing) ህጎች ይህን ክስተት እንዳይፈፀም እንቅፋት ይሆናሉ።

 

  1. የምዕራቡ ዓለም ኢኮኖሚ የተወሳሰቡ ቁልፎች ኢትዮጲያ ወደ ውጭ ሀገር ገበያ ለምታቀርባቸው ዕቃዎች በሮች ካሁኑ በተሻለ ደረጃ ክፍት ይሆናሉ። ይህም ወደፊት ለትርፍ ክፍያ ከሀገር በውጭ ምንዛሪ ለሚወጣው ገንዘብ ኢትዮጲያ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ አቅም እንዲኖራት የበኩሉ አስተዋፅዖ ይኖረዋል።እንደ ኬኒያ ካሉ ሀገሮች በውጭ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን የምዕራባውያኑ አንዱ መስፈርት ይህ ነው።ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ግልፅ የማይሆኑልንን የተዘጉ የንግድ በሮች ይከፋፍቷቸዋል።

 

 

  1. ገዢው የውጭ ድርጅት እንዲሁም ዓለም አቀፍ አጋሮቹ አሁንም ሆነ ወደፊት የኢትዮጲያ ሰላምና አንድነት ግድ ስለሚላቸው ፣ አሁን በሀገራችን ያለው የዘርና የጎሳ መከፋፈል ላይ የራሳቸው አሻራ ይኖራቸዋል።

 

  1. በዓለም ባንክና መሰል አለም አቀፋዊ ድርጅቶች ኢትዮጲያ ላይ ያለውን ጫና የመቀነስና የመልካም ገፅታ ግንባታ ላይ አዎንታዊ አስተዋፅዖ ይኖረዋል። ድርጅቱ በመሸጡ ኢትዮጲያ የተሻለ ትሆናለች ማለት ሳይሆን ጥቅም ስለሚያገኙባት ጥሩ ነች የሚል የገፅታ ስራ ይሰራሉ።
ተጨማሪ ያንብቡ:  ዛሬም እዚያው ነሽ ወይ - (ሸንቁጤ ከአዲስ አበባ)

 

ኢትዮ ቴሌኮምን መሸጥ ያሉት ጉዳቶች

 

  1. በየዓመቱ በቋሚነት የሚገኘው ከገቢ ወጪ ትርፍ በውጭ ሀገር ላሉ የአክስዮን ባለድርሻዎች የትርፍ ክፍያ (Profit Repatriation) ፣ በውጭ ምንዛሪ ከሀገር ይወጣል።

 

  1. ኢትዮጲያውያን የስራ ዕድል ፣ የአቅርቦትና የግብር እንጂ የትርፉ ተጠቃሚ አይሆኑም።

 

  1. በድርጅቱ በከፍተኛ አመራር ወይም ወሳኝ ቦታዎች ላይ የሚሰሩ የኢትዮጲያውያን የስራ እድል በውጭ ሀገር ዜጎች ይወሰዳል።

 

  1. በየትኛውም ሀገር እንደሚታየው ድርጅቱ ትርፍ ላይ ስለሚያተኩር ፣ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሰራተኛ ቁጥር ይቀንሳል። በርካታ የኢትዮጲያ ቴሌኮሙኒኬሽን ሰራተኞች ከስራ ይፈናቀላሉ።

 

  1. . የኢትዮጲያ መንግስት የቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ በመረጃና ደህንነት ጉዳዮች አካባቢ ባለው ትስስር ዙሪያ ባሉ ጉዳዮች ያለው ቁጥጥር ይቀንሳል። የውጭ ሀገራትም እጅ በዚህ ምክንያት ይረዝማል። ሞስኮ በካስፐርስኪ ላብ (Kaspersky Lab) በሚሰራው የካስፐርስኪ የኮምፒዩተር ቫይረስ ምክንያት አሜሪካ የብሄራዊ ደህንነቴ አደጋ ላይ ወድቀ ባለችበት የዓለም ሁኔታ ፣ ኢትዮ ቴሌኮምን ለውጭ ሀገር መሸጥ ለኢትዮጲያ ብሄራዊ ደህንነት ችግር አያመጣም ማለት አይቻልም።

 

  1. አንድ በኢትዮጲያውያን ለኢትዮጲያውያን የሆነ የአፍሪካም ኩራት ሊሆን የሚችል ትልቅና በአፄ ምኒሊክ የተጠነሰሰ ታሪካዊ ተቋም ቀለሙን ያጣል ወይም በአንድ የቦርድ ሲብሰባ በሚወሰን ሌላ አለም አቀፋዊ ሽያጭ ወይም ውህደት (Business Combination) በሌላ የዓለም አቀፍ ቴሌኮም ተቋም ተውጦ ዱካው ፣ ታሪኩ ይጠፋል።

 

እነዚህ የጥቅምና ጉዳት ንፅፅሮች እንደ የፖለቲካና የዓለም አቀፍ ሁኔታ ግንዛቤያችን ሊለያዩ የሚችሉ ቢሆንም ፣ በኔ አመለካከት ፣ የኢትዮጲያ አየር መንገድን (Ethiopian Air Lines) በዚህ ደረጃ በዓለም አቀፉ መድረክ ታዋቂና ተወዳዳሪ ያደረገ ታታሪ ህዝብ ያለበት ሀገር ፣ የኢትዮጲያ ቴሌኮሙኒኬሽንን በዘመናዊ መልኩ ማስተዳደር ያቅተዋል ብዬ አላምንም። የኢትዮጲያ ቴሌኮሙኒኬሽን ትልቁ ችግር ገቢው ፣ ሁሌም በንቅዘት የሚታወቀው የእትዮጲያ መንግስት የበጀት አካል መሆኑና ፣ በትክክለኛ የንግድ ህግ ሊታዳደር ባለመቻሉ ፣ መዘመን ፣ ማደግና ገበያውን በማስፋት በአለም አቀፉ መድረክ ተወዳዳሪ ኩባንያ አለመሆኑ ነው።ችግሩ አሁንም በመንግስት ይዞታ ስር መሆኑ እንጂ ባለቤትነቱ ለውጭ ኩባንያ አለመሸጡ አይደለም።

 

ስለዚህ የውጭ ድርጅቶችን ማሳተፍ ግድ ከሆነ ፣ በመሸጥና እንዳሁኑ በመንግስት ይዞታ ማቆየት ከሚሉት ሁለት መንገዶች መሃከል ያለው አማራጭ ለሀገራችን የተሻለ ጠቀሜታ ሊኖረው ይችላል። ይህም ከፊሉን ለውጭ ኩባንያ በመሸጥ በዚህ የሚመጡ ጥቅሞችን ማግኘት ሲሆን ፣ከፊሉንም በኢትዮጲያውያን ባለቤትነት እንዲቆይ በማድረግ ፣ ከመሸጥ የሚመጡ ጉዳቶችን መቀነስ ነው። ይህ የሚያካትተው :-

ተጨማሪ ያንብቡ:  በወለጋ በተከታታይ ለሚካሄደው የአማራ ሕዝብ እልቂት ተጠያቂዎች የኢትዮጵያ ፌደራል መንንግሥት ባለሥልጣናት ናቸው  - አክሎግ ቢራራ (ዶር)

 

  1. ኢትዮ ቴሌኮም ትልቅ ከመሆኑ አንፃር የአሜሪካው ቤል ሳውዝ (Bell South) የተከተለውን የመከፋፈል (Break up) መንገድ ወይም ሌላ ሞዴል ተከትሎ ድርጅቱን ከፋፍሎ ማሳነስ የሚቻልበትን መንገድ ማየትና የሚቻል ከሆነ መተግበር።

 

  1. ኢትዮ ቴሌኮምን ከመንግስት ይዞታ ወደ ግል ይዞታ በአክስዮን / በድርሻ / Share መቀየር።

 

  1. የአክስዮኑን / የድርሻውን 51 በመቶ ይዞታ ለኢትዮጲያውያን ፣ ለትውልደ ኢትዮጲያውያን እና ለኢትዮጲያ መንግስት በገበያ ዋጋ ለሽያጭ ማቅረብ።

 

  1. ቀሪውን 49 በመቶ ይዞታ ለውጭ ኩባንያ መሸጥ።

 

ይህን በማድረግ በመሸጥ የሚገኙት ጥቅሞችን በከፊል ማግኘት የሚቻል ሲሆን ፣ ከመሸጥ የሚመጡ ጉዳቶችንም እንደዚሁ በማሳነስ በውጤቱ ድርጅቱን የተሻለ ዘመናዊ ፣ ትርፋማና በዓለሙ መድረክ ተፎካካሪ ማድረግ ይቻላል።ከዚህም የሚገኙ መልካም ውጤቶች : –

 

  1. የኢትዮ ቴሌኮም ሙሉ በሙሉ በንግድ ህግ እንዲተዳደር ማድረግ ይቻላል።

 

  1. ኢትዮ ቴሌኮም በውጭ ድርጅቶች የገንዘብ የቴክኖሎጂና የልምድ አቅም ተጠቃሚ ይሆናል።

 

  1. በውጭ ድርጅቶች ተሳትፎ አለም አቅፋዊ የሀገር ገፅታና የውጭ ገበያ አቅም ከፍ ይላል።

 

  1. ወደፊት በትርፍ ሪፓሬሽን ወደ ወጭ የሚወጣውን ምንዛሪ በግማሽ መቀነስ ይቻላል።

 

  1. ትርፍ ዜግነት የሌለው ቢሆንም በድርጅቱ ዋና ዋና እንቅስቃሴ የኢትዮጲያውያን ተሳትፎ አብላጫ ድምፅ ይዞ ይቆያል። ድርጅቱም ኢትዮጲያዊ ሆኖ ይቀጥላል።።49 በመቶ ድምፅ ያለው የውጭ ድርጅት ለአንድ ውሳኔ 51 በመቶ ድምፅ ለማግኘት የሚያስፈልገው አንድ ሁለት በመቶ ድምፅ የያዘን ግለሰብ በተለያየ ጥቅማ ጥቅም መደለል ብቻ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም።

 

 

ትልቁ ቁም ነገር ፣ግማሹን የኢትዮ ቴሌኮም የባለቤትነት ይዞታ ብቻ መሸጥ ፣ ድርጅቱ ሀገራዊ ዜግነቱን ሳይቀይር በዓለም ካሉ የቴሌኮሙኒኬሽን ተቋሞች በሁሉም ረገድ ተወዳዳሪ እንዲሁም ምናልባት በሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ግልጋሎቱን በማስፋት ፣ከእትዮጲያ አየር መንገድም በተሻለ ፣ ለኢትዮጲያ የውጭ ምንዛሪ አስገኚ ሊሆን ይችላል። ድርጅቱ ለውጭ ድርጅት እንዲሸጥ የሚያስገድድ ትልቅ ዓለም አቀፋዊ ጫና ከሌለ ፣ የሚሻለው ቢያንስ የድርጅቱን 51 በመቶ የባለቤትነት ይዞታ ወደ ግል ይዞታ በመቀየር ፣ መቶ በመቶ ኢትዮጲያዊ የመንግስት ሳይሆን የንግድ ተቋም አድርጎ ውጤቱን መመልከት ነው።

 

መላኩ ከአትላንታ

1 Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share