እኔ በደርግም : በኢህአደግም ሆነ በብልፅግና አስተዳደር ስር ያልኖርኩና የማልኖር: ከዲያስፖራ ሆኜ ከአገርና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ፍቅር የተነሳ የታዘብኩትንና የምትታዘበውን በእስተያየት መልክ ማቅረቤ ተገንዛቢ ይሁን:: ያለውን መንግስትና መሪውን ሳሞግሰው በጭፍንነት ሳይሆን : በሶስት አመት ውስጥ ያሳየው አጥጋቢ ስራዎች ላይ ተንተርኩዤና ከበፊቶቹ መሪዎች ጋር በማወዳደር ነው:: ሕይወት ፍፁም ሳትሆን ውጣ ውረድ የሞላባት የጉዞ ሂደት መሆኗን ከተገነዘብን አንዱ ከሌላ መሻሉን ወይም መክፋቱን የምናውቀው በአንፃራዊ ሚዛን ነው:: ትዝብታችን: ድጋፋችን : ቅዋሜያችን ስሜታዊ ሳይሆን ነግሮችን ምክንያታዊ አድርገን ስናቀርብ መግባባትንና መስማማትን እናዳብራለን:: በጭፍንነት ጥላቻ መነዳት ለአገርም : ለሕዝብም ከሚያመጣው ጥቅም ጉዳቱ ይበልጣል:: ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ ምንድነው የሚጠቅመው : ምንድነው የሚጎዳው የሚሉትን ጥያቄዎች ሰከን ብለን ራሳችንን መጠየቅ ያስፈልጋል:: ጎሳና ነገድ ዝቅተኛ የሰው ልጆች መግለጫዎች ናቸው:: መጀመሪያ ሁላችንም ሰዎች መሆናችንን ልብ እናድርግ::
በተጨባጭነት የሚታይ የለውጥና የብልፅግና ጉዞ ኢትዮጵያ መራመድ የጀመረችበትን ያለፉትን ሶስት አመታት ትተን ከዚያ በፊት ያሳለፈችውን 45 አመታት ስንመለከት : የተወሰነ ልማትና እድገት ቢታይባትም : ሕዝብ በነፃ ሃሳቡን የማይገልፅበት : ተወዳዳሪ የፖለቲካ ድርጅቶች መዋቀር ያልቻሉበት : ጋዜጠኞች ትዝብታቸውን የማይፅፉበት : የፖለቲካ ተንታኞች ከገዢው መንግስት ድጋፍ ውጭ ሂስ የማያቀርቡበት: ጭቆናና ድህነት በዝቶበት ትንሹም ትልቁም አገር ለቆ ነፃነትንና ብልፅግና ፍለጋ በበረሓ በባህር የተሰደደበትና በዚያ ሂደት ሽዎች እህቶቻችንና ወንድሞቻችን በየሜዳው ወድቀው : በባህር ተውጠው ያለቁበት ዘመን ነበር:: እነዚህን የጥቂቶች ባለስልጣኖችና ባለጊዜዎች ምቾት ማራመጃ : የአብዛኛው ኢትዮጵያውያን የመከራና የእስረኝነት 45 አመታት : ካለፉት ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተስፋ ጮራ ካበሩት 3 አመታት ጋር ስናወዳድር ልዩነታቸው የጨለማና የብርሃን ነው::
ያለፉት ሶስት አመታት ያሳዩን ጥሩም ሆነ መጥፎ ድርጊቶች የሚፈፀሙት በሰዎችና በፍላጎታቸው እንደሆነ ነው:: ሰዎች ልባቸውን በሰው ፍቅር ከሞሉት : ድርጊታቸውም በፍቅርና በእርህራሄ የተሞላ በመሆን ለመላው የአገር ሕዝብ ጠቃሚ ውጤት ያመጣል:: እያንዳንዱ የማህበረሰብ አባል ለእራሱ የሚመኘውን በንፁህ ልቦና ለሌላው ከተመኘ አካባቢውም ሆነ አገር የሰላምና የእንድነት ምሳሌ መሆን ትችላለች:: እንደ እኔ ቢሆን በአለም ውስጥ ድንበርና አገሮች ባልኖሩ ነበር:: እግዚአብሔር ይህችን ምድር የሰዎችና የሌላ ፍጡሮች መኖሪያ አድርጎ እንደፈጠራት: ሰዎችም እንደልባችን ያለመታወቂያና ያለፓስፖርት ከቦታ ቦታ እየተዘዋወርን በነፃነትና በሰላም እንደፈለግነው በኖርን ነበር:: ይህ የእኔ ምኞት ተምኔታዊ አመለካከት ነው:: አይሆንም:: ምክንያቱም ሰዎች ፍፁምነት ስላልተካንን የተንኮልና የሻጥር ምንጮች በመሆናችን ተማምነንና ተሳስበን የመኖር ችሎታችንን ከማዳበር ይልቅ ራስወዳድነትንና መተኖካከስን ስላጎለበትን ነው::
የምንኖርበት አለም በድንበር የተከለሉ አገሮች የተደራጁባት ነች:: እያንዳንዱ አገር የእራሱ አስተዳደር ስላለው ከድንበር ውጭ ያለው ጎረቤት ወይም ከሩቅ አገር የመጣ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት መብት የለውም:: ከገባም የሚደርስበትን ጥቃት ሳንገነዘብ አልቀረንም:: ከአገሪቱ ተወላጆች መሃል የሚወጡት መሪዎች ለዚያች አገር የወደፊት እድገት : ልማት : ብልፅግና : ሰላም : አንድነትና ሉአላዊነት ኃላፊነት አለባቸው:: አገርን አገር የሚያሰኘው የሕዝብ መኖር ነው:: አገርን የሚያነሳውም የሚጥለውም የሕዝብ ተባብሮ በሰላምና በአንድነት መኖርና ተግቶ በጋራ መስራት ነው:: ሕዝብ በሰላም ሲኖርና እንድነቱን ሲያጠናክር : አገር ሰላምና አንድነት አላት ይባላል:: ሕዝብ በሰላምና በአንድነት ኑሮ አገር እንድትበለፅግ ከተፈለገ መልካም አመለካከትና ቅንነት ያላቸው ግለሰቦች አስተዳዳሪና መሪ መሆን ይገባቸዋል:: ጥሩ መሪ የመጀመሪያ ግንዛቤ ማድረግ ያለበት : የሕዝብ ተወካይና ጉዳይ አስፈፃሚ እንጂ አዛዥና ገዢ እንዳልሆነ ነው:: የኢትዮጵያ ሕዝብ የለመደውና ሲስተዳደር የኖረው በግብዝ አምባገነን መሪዎች ስለነበረ : ዛሬ ያለውን መሪ ለመረዳት ችግር ላይ ወድቋል:: ይህንን ስል መላው የኢትዮጵያ ሕዝብን ሳይሆን : በጣም ጥቂቶች የሆኑትን ኢትዮጵያን በጎሳ በመከፋፈል ለመበታተንና ለዘመናት በአንድነትና በፍቅር ተከባብሮና ተሳስቦ የኖረውን ሕዝብ በማጋጨት ሰላም የሚያሳጡትን የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞችንና የፌስቡክና የዩቱብ ሳንቲም ለቃሚዎችን ነው:: ለሕዝብና ለሰው ልጅ መልካም ትምህርትና ጠቃሚ ሃሳቦችን ለሚያካፍሉ በፌስቡክ በዩቱብ በኢንስታግራምም ሆነ በቲክቶክ ሳንቲም ለቃሚዎች እሰየሁ በርቱበት እላለሁ::
ጠ/ሚ ዶ/ር አቢይ አህመድን ብዙሃኑ ይረዳዋል:: የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር የሚያመጣውን ጥቅምና ጉዳት አገር ቤት ውስጥ ያለው የአገሪቱ ተወላጆች በግልፅ ያዩታል:: የሚያስደስታቸውንና የሚያስከፋቸውን ፊትለፊት ይጋፈጣሉ:: ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምኞታቸውና አሳቢነታቸው ቀና መሆኑን በግልፅ ይረዳል:: ለውጡ ሁሉንም የሚፈለግበትን ያሟላል? አያሟላም:: ከበፊቱ ይሻላል? አዎን ይሻላል:: ሕዝብ በመራቡና በመቸገሩ : ልጆቹን ለአረብ አገረ ግርድና እየላከና : ለተሻለ ሕይወት በማለት በችግር ምክንያት ልጆቹ በመሰደድ የበረሃና የባህር ቀለብ ያደረገውን ሕዝብ ትተን : በሙስናና በዝምድና የአገርን ገንዘብ በመስረቅ ሀብት አዳብረው ዛሬ ያ ስርቆት የቀረባቸው ስስታሞች ላይመቻቸው ይችላል:: ለዚህም ነው በተሰረቀው የሕዝብ ገንዘብ የሚንደላቀቁ የወደቀው ስስታም ወያኔ ጁንታ እርዝራዥዎችና አተላዎች ለውጡን የሚቃወሙት:: በምቾት በዲስ : በቦስተን : በዳላስ: በአትላንታ : በሲአትል : በሳንፍራንሲኮ : በቢርትን : በጀርመን : በሲውድን : በኖርወይና በመላው አለም ተቀምጠው የመጣውን ለውጥ ቀልብሰው የተለመደውን ጭቆናና ብዝበዛ ለማካሄድ የሃሰት ፕሮፓጋንዳ እየነሰነሱ ያሉት:: ሱሚ ይሁንባቸው:: የተጀመረው የእድገትና የእንድነት ለውጥ እንደፀደይ አበባ እያበበ ይሄዳል እንጂ ኢትዮጵያን ደም የመጠጡ ቅማሎች ተመልሰው ራሷ ላይ አይወጡም::
በሰላም የመጣው ለውጥ የክርስትና ስም ብሰጠው : ደርግ “ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም: ” ያለውን አነጋገር ለደርግ ሳይሆን : ዶ/ር አቢይ አህመድን ለዚህ ኃላፊነት ላበቃቸው የዛሬ ሶስት አመት ለመጣው ለውጥ ተስማሚ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ:: ያለምንም ደም ራስ ወዳዱን የወያኔ ጁንታን በሰላማዊ መንገድ አስወግዶ የኢትዮጵያን የፖለቲካና የኢኮኖሚ አቅጣጫ ጥሩ መንገድ በማስያዝ ኢትዮጵያን ማስቀደም ታላቅ የስራ ውጤት ተደርጎ መውሰድ የማንም መልካም አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን አመለካከት መሆን ይገባል:: ይህችን አነጋገር ቀንጠብ አድርገው እንዴት ኢትዮጵያ ውስጥ ደም አልፈሰሰም ትያለሽ በማለት ትግራይ ክልል ውስጥ ያለውን አረመረጋጋት : በአማራና በቤንሻንጉል : በሱማሌና በአፋር መሃል ያለውን ግጭት : በኦሮምያ ክልል ውስጥ አልፎ አልፎ የሚታየውን በጠባብ ጎሰኝነትና በነገድ ላይ የተመሰረተ ሰው ግድያ የሚያነሱ አሉ:: እነዚህ አስከፊ ኢሰባአዊ ድርጊቶች ሊካዱ አይችልም:: እየተፈፀሙ ናቸው:: ሆኖም እነዚህ እርስበርስ ግጭቶች ከጀመሩ ቆይተዋል:: መፍትሔው የሁላችንም አስተዋፅኦ ይፈልጋል:: በጭፍን ይህ የዛሬ ሶስት አመት የመጣው ለውጥ ውጤት ነው ማለት ተገቢ አይደለም:: ለውጡ ምቾታቸውን የቀነሰባቸው የወደቀው ጁንታ እርዝራዦችና ተላላኪዎች: ችግሩን አንዳባባሱት አይካድም:: ያንን ለማስተካከልና ለማረም የሚጥረውን መንግስትና መሪ በመውቀስ የሚመጣ መፍትሔ የለም::
ፍፁም ሰዎች በሌሉበት አለም : አንድን መሪ ፍፁም ሁን ማለት የሌለውንና ታይቶ የማይታወቅ የሰው ልጅ ባህሪ መፈለግ ይሆናል:: አንዳችንም ፍፁም እንዳልሆንን ከጎናችን ያለው የሰው ልጅ ፍፁም እንዳልሆነ እያወቅን ያልወለድነውን ፍፁም ልጅ እንደመፈለግ ነው:: በእግዚአብሔር ለሚያምኑት የሰው ልጆች : ፍፁም ፈጣሪ ብቻ ነው:: ሰው ከትላንት ዛሬ የተሻለ መሆን ይችላል? ይችላል:: ጥሩ ሰው መሆን እፈልጋለሁ ብሎ ሰው ከተነሳ በእርግጥ ይችላል:: ቀና ቀናውን ላድርግ ካለ ይችላል:: አሁን ያለው መሪ ከበፊቶቹ መሪዎች የተሻለ በመሆን የሕዝቡን ስቃይና ሰቆቃ በመረዳት አጠገቡ ካሉት የስራ ባልደረቦቹ የተሻለ በመሆን እነሱንም እንዲሻሻሉ ስብእናቸው በሰባዊነትና በእርህራሄ የተሞላ እንዲሆን መግፋት ይችላል:: ይህንን የሚያደርግ መሪ ከዚህ በፊት በአገራችን አልታየም:: አሁን ግን ሳናገኝ አልቀረንም:: ማበራታት ተገቢ ይመስለኛል::
አዎን! አንዳንዶች በማንኛውም ጊዜ መቃወምን እንጂ መደገፍ የሚባል እይታ የተሳናቸው : የዛሬ ሶስት አመት የመጣውን ለውጥ : የጉልቻ መቀያየር እንጂ ለውጥ አላየሁም በማለት የሚምሉ ምጽአት ጠባቂዎች አሉ:: እነዚህ ብርሃንን ጨለማ : ጨለማን ብርሃን አድርገው ማየትን እንጂ የማስተዋል ብርሃን ብልጭታ አእምሮአቸውን ያልጎበኛቸውን በምንም አይነት ቀና ነገር እዩ ማለት ይከብዳል::ለዚህ ነው አውቆ የተኛን ሰው ቢቀሰቅሱት አይሰማም የሚባለው:: የአገርን ማንነት ጥያቄ ውስጥ ለመክተትና የሕዝብን አንድነት ከሚያውኩት የጎሰኝነትና የወገናዊነት ፖለቲካ በተጨማሪ : ኢትዮጵያውያን ነን: ለኢትዮጵያ ሉአላዊነትና አንድነት እንቆማለን እያሉ : ግን የመጣውን መንግስትና አስተዳደር በስራውና በድርጊቱ ድጋፍ ወይም ቅዋሜ ከማሳየት : በጭፍን ጥላቻ በመመራት: መሪው የመጣበትን ጎሳና ክልል በመመልከት ብቻ ሲረግሙትና ሲያንቋሽሹ ይገኛሉ:: ለእነዚህ ትልቁ ኢትዮጵያዊነትን የሚያሳዩበት መንገድ : ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ካለው አመራርና እስተዳደር ያገኙት ጥቅም ከሚጎዳው ድርጊት ይበልጣል ወይስ ያንሳል የሚል ጥያቄ በማቅረብ በመጠናዊ ሚዛን ማየት ሳይሆን : መሪውን አንወደውምና ምንም ያድርግ አንደግፈውም የሚል የተዛባ አመለካከት ከመጀመሪያውኑ በጠበበችው ጭንቅላታቸው በማሳደራቸው ነው:: በምኖርበት የዲያስፖራ አሜሪካ ከተማ በሶሻል ሚዲያዎች በሚደረገው ውይይት የታዘብኩት : ጭፍን ድጋፍ ወይም ጭፍን ቅዋሜ ነው:: ድጋፍና ቅዋሜ የዜሮ ድምር ጨዋታ መሆን የለበትም:: አንድ ሰው ድጋፍና ቅዋሜን ማራመድ ይችላል:: ምክንያቱም የሚፈልገው ውጤት ጠቃሚ እንዲሆን ከድጋፉ ጋር ገንቢ ቅዋሜ ማሰማት የሚቻል ስለሆነ:: ያለፉት ሁለቱ ስርዓቶች : የሰሩት 100 በ100 ጥፋት ነው የሚል ካለ ሚዝናዊነት ምን እንደሆነ መርምሮ የመገንዘብና የመዳኘትን ተሰጥኦ ማዳበር ይኖርበታል:: በተመሳሳይ 100 በ100 ጥሩ ሰርተዋል የሚል ካለም ባልተናነሰ መንገድ የግንዛቤንና የዳኝነትን ትርጉም ማጥናት ይኖርበታል:: ምክንያቱም 100 በ100 የፍፁሙነት ምልክት ስለሆነ የሰው ልጆች የሚያሳኩት አይደለም:: ፍፁም ያልሆንን ሰዎች በምንኖርበት አለም ውስጥ: ፍፁም የሆነ መሪና አመራር ይውጣ ማለት : ላም አለኝ በሰማይ ወተቷንም አላይ : የሚለውን ምሳላዊ አነጋገር ያስታውሰኛል::
አሁን ያለው የዶ/ር አቢይ አመራር ፍፁም ትክክል ነው ለማለት ይከብዳል:: አይደለምም:: ካለፉት አስተዳደሮች የተሻለ ነው? በእርግጥ ይሻላል:: መችስ ፍርጃ ሆኖበት የመንግስት ቁንጮ ላይ ስለተቀመጠ : ሌሎች የመንግስት ተወካዮች በሚያጠፉትና ሕዝብን በሚያጎሳቁሉበት ምክንያት ይወቀሳል:: መወቀስም ይገባዋል:: ምክንያቱም እንግሊዘኛ ተናጋሪዎች እንደሚሉት : “The buck stops with him.” እንደመሪ ከስሩ ላሉት ጥፋት እሱ ተጠያቂ ለመሆን የተቀመጠበት ወንበር ያስገድደዋል:: ወዶ መሪ ስለሆነ ይህንንም ወቀሳ በፀጋ የሚቀበል መሪ መሆኑን አሰመስክሯል:: በሶስት አመታት ያከናወናቸው የስራ እቅዶች ለአገሪቷና ለሕዝቧ ብልፅግናና እድገት እንደሚደክም ማረጋገጫ ነው:: በውጭ ጠላቶችና የጠቡትን የእናት ኢትዮጵያን ጡት ለመቁረጥ ከግብፅና ሱዳን ጋር አድማ የሚመቱትን ባንዳዎች ጋር እየተፋለመ የአባይን ግድብ ለማስጨረስ የሚያደርገው ጥረትን በኢትዮጵያዊ ዜግነታችን ከመደገፍ ይልቅ : ያልሆነ አገር አጥፊ : የሕዝብ አንድነትን የሚከናከን ፍሬፈሪሲኪ ቅዋሜዎች ማሰማት አቢይንና አስተዳደሩን አይጎዳም:: የሚጎዳው አገርንና ሕዝብን መሆኑ ለሁላችንም ግልፅ ይሁን::
በጣም የሚገርመው የሚቀርቡት ቅዋሜዎች በፖሊሲዎች ላይ ሳይሆን ጎሳና ነገድን የተመረኮዘ መሆኑ ነው:: ዶ/ር አቢይ አህመድ ለኦሮሞዎች ያደላል:: ለኦሮሞዎች ነው ስልጣን የሚሰጠው:: አማራዎችን ይጠላል:: ትግሬዎችን ያስጨፈጭፋል የሚሉት መሰሩተ ቢስ ክሶች ለአገር የሚያመጡት እርስ በርስ መጠላላትን ለማራመድ ካልሆነ እውነትን የተንተራሳ ክስ አይደለም:: ከተሳሳትኩ መታረም እችላለሁና : የዶ/ር እቢይ አህመድ ባለቤት ቀዳማዊት ዝናሽ አማራ ኢትዮጵያዊ አይደለች? እንዴት ብሎ ነው አማራ ኢትዮጵያውያንን የሚጠላው? አንድ ሰው ኦሮሞ ወይም አማራ ወይም ትግሬ ወይም ክርስትና ወይም እስልምና ሃይማኖት ተከታይ ስለሆነ የኢትዮጵያ መሪ መሆን የለበትም የሚል አስተሳሰብ : የኢትዮጵያን ብዙሃነጎሳነቷን አለመቀበልና ወገናዊ መሆን ነው:: ባይሆን ሹመት በጎሳ ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በእውቀትና በችሎታ የተለካ መሆን አለበት ብሎ መከራከር አግባብ ነው:: አለመታደል ሆኖ የኢትዮጵያን ፖለቲካ የምንተነትነው በተነደፉት እቅዶች : በፖሊሲዎችና በአስተዳደር ዘይቤዎች ሳይሆን ጎሳ ላይ በማትኮር ነው:: ይህ እካሄድ የዛሬ ሰላሳ አመት ስልጣን ላይ የወጣው የወሮበላው አረመኔ ጁንታ ስራ ውጤት ነው:: ከዚህ አዙሪኝ ልክፈት ውስጥ መሽከረር እስካላቆምን ድረስ : የሚከተለውንም ትውልድ በክለን አገሪቱን የባሰ እረመጥ ውስጥ በመክተት ሕዝባችንን የችግርና የስቃይ መደነሻ እናረጋዋለን:: ከባህር ማዶ ተቀምጠው በመንግስታት ድጎማ የሚኖሩ የፌስቡክና የዩቱብ እንዲሁም የሌሎች የሶሻል ሚዲያዎች ኪልክ ሳንቲሞች የሚለቅሙት ትህትናና ሰባዊነት የተሳናቸው ትምህርት የጣላቸውን እሳት ጫሪዎችን አንቅረን መትፋት ለአገር ሰላምና : ለሕዝብ አንድነት ይጠቅማል::
ሁላችንም ፍፁም አይደለንም:: ሁላችንም ውጣ ውረድ እናሳልፋለን:: በግል ኑሮአችን የሚገጥመን ችግርና መከራ ለእናንተ አንባቢዎች መነገር አይገባውም:: እንኳን አገር ማስተዳደር ይቅርና አንድ ቤተሰብ ማስተዳደር እየከበደ አይደል: ተማምለው በቁርባን የተጋቡት ሰዎች የሚለያዩት? እንዴት 110 ሚሊዮን ሕዝብ ያለበትን አንድ አገር ማስተዳደር እንደቀላል ታይቶ በመሪው ላይ የሚፈረጀው? ስንቱ ነው አራት አባላት ያለው ቤተሰብ ለማስተዳደር ችግር እየገጠመው እንባ የሚረጨው? ይህ መሪ እንደበፊቶቹ ተቃወማችሁኝ ብሎ አላሰረ: አልገደለ:: ማንኛውም ሰው የመኖር መብት በፈጣሪው ቢሰጠውም : ሲኖር የሌላውንም ሰውነትና ሰባዊነት ተረድቶ ማክበር አለበት:: የእገርን ህልውናና የሕዝብን አንድነት የሚያናጋ ከሆነ በሕጉ መሰረት ይጠየቃል:: ይቀጣል:: የመንግስት የመጀመሪያና ዋናው ግዴታና ስራ የአገርን ማንነትና የሕዝብን አንድነትና ደህንነት መጠበቅ ነው:: በዚህ ሂደት ውስጥ ሰዎች ሊጎዱ ይችላሉ:: በዚህም የዋስትና ጉዳት ይከሰታል:: ይህ የኢትዮጵያ ክስተት ብቻ ሳይሆን በማንኛውም የአለም እገር ይፈፀማል:: ምክንያቱም ሰዎች የተለያየ የቆዳ ቀለም : ቋንቋ: ሃይማኖት : ባህል ወይም ልምድ ቢኖረንም መሰረታዊ አመለካከታችን ስለሚመሳሰል : ችግራችንም ተመሳሳይ ነው:: እኛ ዛሬ በጎሳ በነገድና በወጋናዊነት አስተሳሰብ የምንመራበትን የጥላቻ ፖለቲካ የሰለጠኑ አገሮች ቀድመው አልፈው ትኩረታቸው ልማትና እድገት ላይ ነው::
ደርግና ወያኔን እናመዛዝን ብንል የሚያመሳስላቸው አረመኔነታቸው ነው:: ሁለቱም ለስልጣናቸው ሲሉ ያካሄዱት የሰው ጭፍጨፋ ካከናወኑት ጥሩ ነገሮች ጋር ሲነጥጠር የሰሩትንና ያመጡትን እድገት እንዳናስትውስ ያደርጋል:: የደርግ ቀይ ሽብር “አቢዮት ልጆቿን ትበላለች በሚል ፈሊጥ የጨረሰው ወጣትና ምሁር አገሪቱን 50 አመታት ወደሗላ ጎትቷቷል:: ከደርግ ሊብስ አይችልም በተባለበት ጊዜ ወደ ስልጣን የመጣው በወያኔ የሚመራው ኢሐደግ ኢትዮጵያን ሕዝብ ከመግደል በተጨማሪ በተለይ በእማራ ክልል ውስጥ የፈፀማቸው ሴቶችን እንዳይወልዱ የፈፀመው የሕክምና ማምከን ኢሰብአእዊ ድርጊት ሊረሳ አይችልም:: ከዚያም አልፎ ኢትዮጵያን በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ክልል በመፍጠሩ ሕዝባችንን ለጎሳና ለነገድ ፖለቲካ በማጋለጡ ዛሬ ልዩነቶች እየሰፉ በመሄዳቸው በየክልሉ ሰውን ከአገሩ ከተወለደበት አካባቢና ቦታ ማፈናቀልና መግደል ልምድ ሆኖ ተወስዷል:: የወደቀውና በስብሶ የሟሸሸው ወያኔ ጁንታ እርዝራዦችና ፍርፋሬ ለቃሚዎች : ያለፈው ሕዝብን ማጋጨትና አገርን ለክፍፍል ማጋለጥ አንሷቸው : ዛሬ ከተቀበሩበት ጉድጏድና ዋሻ ብቅ እያሉ ኢትዮጵያ የምትባል አገር አትኖርም:: ትግራይን እንገነጥላለን:: አማራና ኦሮሞን እድሜ ልክ እንዲጋጩና እንዲዋጉ እናደርጋለን:: በአፋርና በሱማሌ ክልሎች መሃከል የማይበርድ የጥላቻ እሳት እናነዳለን በማለት እየፎከሩ ይገኛሉ:: ለዚህም ነው ወያኔ የሰራው ልማት ቢኖርም ከፈፀመው ወንጀልና : ዛሬ እርዝራዦቹ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሚያራምዱት ፖለቲካ አኳያ ሲታይ : ሰርቷል ብሎ መናገር አሳፋሪ ነው:: ስለዚህ ወያኔ ከደርግ ጋር ሲወዳደር : የአገር ጠላት : አገር አጠፋ እንጂ አገር መርቷል ተብሎ መቆጠር የለበትም:: የሚያሳዝነው የ2010 (EC 2018) አቢይን ስልጣን ያስጨበጠውን ለውጥ እንደለውጥ የማያዩት በምን መነፅራቸው ይሆን? በተለይ አማራና ኦሮሞ ኢትዮጵያውያን መገንዘብ ያለባቸው : በወያኔ ወጥመድ ውስጥ ገብተው : አማራ ኦሮሞን እንዲጠላ : ኦሮሞ አማራን እንዲጠላ ለማድረግ የሚመታውን ከበሮ አለመስማት አስፈላጊ ነው:: ከሆነም ይህንን ቅኝት የሌለውን ከበሮ በጋራ ማጥፋት እጅግ አስፈላጊ ነው:: አማራና ኦሮሞ ኢትዮጵያውያን የወያኔ መጋለቢያ ድንክ ፈረስ ከመሆን መጠንቀቅ ይገባቸዋል:: በአማራና ኦሮሞ ኢትዮጵያውያን ደም የወያኔ እርዝራዥዎችና አተላዎች አይነግዱም:: ትግራይ ኢትዮጵያውያንም በ27 አመት የወያኔ አስተዳደር ያገኘው መከራ ብቻ ስለሆነ የወያኔ ጁንታ እርዝራዦችና ፍርፋሬ ለቃሚዎች የረብሻ መሳሪያ መሆን አይገባቸውም:: ዶ/ር አቢይ አህመድን ማጠላላት የወያኔ ጁንታ እርዝራዦችና ጠባብ ጎሰኝነትን የሚያራምዱ ፀረኢትዮጵያውያን ቀዳሚ ተግባር ነው:: ለዝህም የአገር መሪ ለአንድ ጎሳ ወይም ነገድ አግዞ ሌላውን ጎሳ ተወላጅ ያስገድላል ማለት ፍርደ ገምድልነት ነው የምለው:: በየክልሉ የሚደረጉት የጎሳና የነገድ ግድያዎች የሚቆሙበትን መንገዶች መፈለግ የማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ግዴታ ነው::
ለአገርና ለመላው ሕዝብ የምናስብ ከሆነ ማድረግ ያለብን : ያለው የዶ/ር አቢይ አህመድ አስተዳደር የሚሰራውን ጥሩ ነገሮች እያሞገስንና እያመሰገንን በርታ እንበለው:: ስህተት የምናላቸውን ድርጊቶች ወይም ፖሊሲዎች ምን እንደጎደላቸው ከማሻሻያ ጋር መጦቀም ገንቢ እርማት ይሆናል:: እያንዳንዳችን ፍፁም ሳንሆን : ሌላው ላይ ሁን ብሎ ጣት መቀሰር አግባብ አይደለም:: ለዚህም ነው ፍፁም ሰዎች በሌሉበት ምድር : መሪን ፍፁም ሁን ማለት ተገቢ አይደለም የምለው::
ኢትዮጵያ ለዘለአለም ትኖራለች::