ሀገራችንን ለማዳን ምን ማድረግ ይኖርብናል? – ዶ/ር በቀለ ገሠሠ

ዶ/ር በቀለ ገሠሠ (drbekeleg@gmail.com)

1ኛ/        መግቢያ፤

በዉስጥ ወድቀናል። ህዝባችን በእልፍ አእላፍ ታድኖ እየተገደለና ተፈናቅሎ እጅግ በጣም ሲቃይና መከራ በማየት ላይ ይገኛል። በጎረቤቶቻችን ጭምር በዉጪ ተንቀናል። ሱዳን እንኳን ድንበራችንን ከደፈረች ቆየች። የግብፅ ማስፈራሪያ እንደቀጠለ ነዉ። ምዕራቦች አስከፊ ማዕቀብ ለመጣል እየተዘጋጁ ይገኛሉ።

ስለዚህ ከመንግሥትም ሆነ ከህዝባችን የሚጠበቁ እጅግ አስቸኳይ እርምጃዎች ይኖራሉ። እነዚህን በሚከተለዉ መልክ ባጭሩ አቀርባለሁ። ሁላችንም ኃላፊነታችንን ተወጥተን የዉድ ሀገራችንን ሉዓላዊነትና የህዝባችንን ደህንነት ማስጠበቅ ይኖርብናል። ቸሩ ፈጣሪያችንም ይጨመርበት።

 

2ኛ/        አንድነታችን ሲጠነክር እንከበራለን፤ ሲላላ ሰለባ እንሆናለን

እድሜ ለአባቶቻችንና አያቶቻችን ጀግንነት፤ አርበኝነትና መስዋዕትነት፤ ኢትዮጵያ ነፃነቷን አስጠብቃ ለዘመናት ኖራለች። ከራሷም አልፋ በቅኝ ግዛት እጅ የወደቁትን የአፍሪቃ ሀገሮች የተቻላትን ያህል ስትረዳና ስታሰለጥን ኖራለች። እንደነደቡብ አፍሪቃ ኒልሰን ማንዴላ፤ የኬኒያ ጆሞ ኬኒያታና የታንዛኒያዉ ጁሊዬስ ኔየረረ በግልፅ የሚጠቀሱ ምሣሌዎች ናቸዉ። በሰሜንና ደቡብ ሱዳን መካከል ለረጅም ዓመታት የዘለቀዉን የርስ በርስ ፍጅት በሽምግልና አስቀርተዉ ሰላም አዉርደዋል። በአድዋም ሆነ በማይጨዉ አስከፊ ጦርነቶች ላይ ያስገኘችዉ ድል ለዓለም  ጭቁን ህዝቦች ተምሳሊት ሆኖ ነፃነታቸዉን እንዲጎናጸፉና ቀና ብለዉ እንዲሄዱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከፍለዋል። በዚህም ምክንያት ለዉጪ ጠላቶች ከባድ የጉሮሮ አጥንት ሆና እንደኖረች የታወቀ ሃቅ ነዉ። በመሆኑም፤ በኢትዮጵያ ጠንካራና ህዝባዊ የሆነ መንግሥት እንዲመሠረት አይፈልጉም።  ጨፍጫፊዉ የደርግ አምባገነን መንግሥት በሶቪዬት ህብረት የተደገፈዉ ለኢትኦጵያ ህዝብ ጠቀሜታ ሳይሆን በኢትዮጵያ ምድር ዲሞክራሲ እንዳይመሰረት ነበር። ሀገር ወዳድ ወጣቶች፤ ምሁራንና መላዉ ተራማጅ ትዉልድ ክፉኛ ተጨፈጨፈ።

ደርጉ ደግሞ ለወያኔ፤ ለሸአቢያና ለኦነግ አስረክቦ እንዲፈረጥጥ የምዕራብ ኃይሎች ከፍተኛ ድጋፍ አደረጉ። የወያኔ/ኢህአዴግ መንግሥት ለኢትዮጵያ ስለሚጠቅም ሳይሆን ፍላጎታቸዉ ሀገሪቷን ከፋፍሎ እንዲያዳክም ነበር። ለዚህም ተረቅቆ እስካሁን በሥራ ላይ የሚገኘዉ ከፋፋይ ሕገ መንግሥት ተብዬዉ እንዲረቀቅና ህዝባችን በጎሣ ተከፋፍሉ እንዲጨራረስ የተደረገዉ። የተከፋፈለችና የተዳከመች ሀገር የሚፈልጉት ለማሽከርከር እንዲመቻቸዉና ከፍተኛ ጥቅማቸዉን ለማስጠበቅ ነዉ። በዚህም ላይ የተያዘብን የረጅም ጊዜ ቂም አለ። በቀድሞ ዘመናት ኢትዮጵያ የጠየቀቻቸዉ ቴክኖሎጂን እንጂ የምግብ ዕርዳታ አልነበረም። ለም መሬታችንን በማረስ ራሳቸዉን መመገብ ይችሉ ነበርና። በተለይ ባለፉት 50 ዓመታት ገደማ ግን ራሳችንን መመገብ አቅቶን በዉጪ እርዳታ ሥር ወደቅን። የወጣቶች ፍልሰትና ስደት እንደጉድ ነዉ። ዛሬ በአሜሪካ፤ በአዉሮፓ፤ በመካከለኛዉ ምሥራቅ፤ በአዉስትራሊያ፤ ወዘተ ተበትኖ የሚኖረዉን ወገን ቁጥርና ሁኔታ ማየት በቂ ነዉ፤ በየቀኑ መርዶ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የትግራይ ነጻ አውጪዎች ኢትዮጵያን ማጥፋት ይችላሉን - ከሳሙኤል አሊ

 

3ኛ/        ከመንግሥት የሚጠበቁ ኃላፊነቶች

ዛሬ እንደዚህ የተናቅነዉና የተዋረድነዉ እንድነታችን በመላላቱ፤ ጭቆና በመብዛቱና ህዝብን የሚታደግ ኃይል በመጥፋቱ ነዉ። ህዝብ እንዳይጨፈጨፍ የሚከላከል ኃይል የለም። መንግሥት በግልፅ ወጥቶ ይቅርታ ጠይቆ ዋስትና ሲሰጥ አይታይም። ግዲያና መፈናቀል እንደቀጠለ ነዉ። የተፈናቀሉት ወደየቀዬአቸዉ ሲመለሱ አይታዩም፤ በቂ ድጋፍም አያገኙም። የተላከልን የእርዳታ እህል ተሰረቀብን የሚሉም ብዙ ናቸዉ።

በዚህ እጅግ አስጨናቂ ወቅት ከመንግሥት የምንጠብቀዉ፤

  • የህዝብ ግድያ ማስቆም፤
  • ህዝባችን እንዳይፈናቀል መከላከል፤
  • የተፈናቀሉትን ወደየሰፈራቸዉ መመለስ፤ በቂ ድጋፍ መስጠት፤
  • ወንጀለኞችን ለፍርድ ማቅረብ፤
  • ሰላም ያላት ኢትዮጵያ ለጎረቤትም ሆነ ለመላዉ ዓለም ሰላም እጅግ አስፈላጊ መሆኗን ለዓልም ህብረተሰብ ለመግለጽ መቻል፤
  • እስካሁን ድረስ ራሷን ከመጠበቅና ከመከላከል በስተቀር የማንንም ሀገር ፍላጎት ነክታ እንደማታዉቅ ደጋግሞ ማስታወስና መግለፅ፤
  • ህዝባችንን ለመከራና ሲቃይ የሚጋብዙ ሕገ መንግሥት የመሳሰሉ ጉዳዮች እንዲቀየሩ ማመቻቸት፤
  • የሽግግር መንግሥት ማጠናከርና ወደዲሞክራሲ የሚያመሩ ተቋማትን መገንባት።

 

4ኛ/        ከሰፊዉ ህዝብ የሚጠበቁ ኃላፊነቶች

ከሀገር ወዳድ ህዝባችንም ብዙ ነገሮች ይጠበቃሉ። ከነዚህም ዉስጥ፤

  • መንግሥት እላይ የተጠቀሱትን ኃላፊነቶች እንዲወጣ መቆስቆስና መጠየቅ፤
  • ምንም ያላጠፋ ወጣትና መጪዉ ትዉልድ ሀገር አልባ ሆኖ እንዳይቀር የሀገርን ኅልዉና ማስጠበቅ፤
  • የንፁህ ዜጋን ህይወት ማጥፋት ከባድ አረመኔነት መገንዘብ፤
  • ራስን ከዉሸት ትርክቶች መጠበቅና ወገንን ማፍቀር፤ መንከባከብና መደጋገፍ፤
  • ለተፈናቀሉት ወገኖቻችን የሚቻለዉን ድጋፍ ማድረግ፤
  • በርካሽ ራስ ወዳድነት የተነሣ የዉጪና የዉስጥ ጠላቶች አገልጋዮች ከመሆን መቆጠብ፤
  • ሰላም ያላት ኢትዮጵያ ለጎረቤትም ሆነ ለመላዉ ዓለም ሰላም እጅግ አስፈላጊ መሆኗን በተቻለ መንገድ ለዓልም ህብረተሰብ ለመግለጽ መሞከር፤
  • ህብረታችን ሲጠነክር የዉጪ ኃይሎች ሊደፍሩን እንደማይችሉ መገንዘብ፤
  • በዚህ ረገድ በተለይ የሺማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች ሚና ከፍተኛነት መገንዘብና መፈጸም፤
ተጨማሪ ያንብቡ:  ታሪክን የኋሊት፤ የአቶ መለስ ድንጋጤ! (አቤ ቶኪቻው)

1 Comment

  1. አንድ ሰው ሲናገር ፓለቲካ ማለት ሽቀላ ማለት ነው ብሎ ነበር። ልክ ነው የወያላዎች አስተሳሰብ ነው። እኔ ደግሞ ፓለቲካ የእብዶች ስብስብ ነው ብዬ አምናለሁ። ላስረዳ። በቅርቡ እስራኤልና ተክፋይ አስተሣሰብ ያነገበው አክራሪ የፓለስቲያን ቡድን ተፋለሙ። ንብረት ወደመ፤ ህዝብ ሞተ ግን እብዶቹ ፓለቲከኞች ጦርነቱ በተገታ ማግስት ድል አደረግን በማለት ጨፈሩ፤ ደነፉ። ያልታያቸው ግን ይህ ሁኔታ የዛሬ ሰባት ዓመት ገደማም ተጋጭተው እንደዚሁ በማለት ነው የዘጉት። ያ ለሁለቱም እብዶች ተዘንግቷቸዋል። ሌላ ልጨምር ኢራንና ኢራቅ በድንበር ሂሳብ ሲላተሙ እልፍ ሰውና ንበረት ከወደመ በህዋላ አንድም ኢንች መሬት ሁለቱም አልሰጡም ወይም አላገኙም። ወደ ሃበሻው የዘመን ሰቆቃ ስንመጣ ደግሞ ትሻልን ትቼ ትብስን አይነት ነው። ወያኔ ሃርነት ትግራይ ገና ከጅምሩ የትግራይን ህዝብ ነጻ አወጣለሁ ብሎ እልፎችን ጉድጓድ የከተተ፤ የሃገር መሪም ከሆነ በህዋላ በልዪ ልዪ ሴራ የኢኮኖሚውን፤ የወታደራዊ አመራሩን ጠፍንጎ በመያዝ፤ ባጠቃላይ ምድሪቱን ለራሱ ጥቅም ቀፍዶ ይዞ ይህ ነው የማይባል ግፍ ሲፈጽም የነበረ የአንድ አካባቢ ልጆች የማፊያ ስብስብ ነው። ጊዜአቸው አክትሞ በትግራይ ከመሸጉ ወዲህ ደግሞ የሚናገሩት ሁሉ ጋንጃ ያለ ልክ ያጨሰ ሰው የሚናገረው አይነት እንጂ ጭንቅላቱ በልኩ ከሚሰራ ሰው ህሊና የሚወጣ አይነት አይደለም። አሁን በየካቡና በየጥሻው ፎቶ እየተነሱ እየታገልን ነው የሚሉን ሁሉ ውሸት ነው። በከተማ ከሰው ቤት ተጠልለው ሌላውን እያስጨረሱ ለፕሮፓጋንዳ ብልሃታቸው ያለተሰዋውን ተሰዋ፤ ሜዳ የሌለውን ሜዳ ገባ፤ ይህን ያህል የኤርትራና የሃገር ጦር ደመሰስን ሲሉ በሃገርና በውጭ ያሉ የወያኔ አለቅላቂዎች ታምቡር ሲመቱ ማየት የመደንቆራችን ጥልቀት ያሳያል። ለትግራይ ህዝብ የቆመ፤ የእርዳታ እህል የሚቀበል ረሃብተኛን የትግራይ ልጆችን አይገድልም፤ ለትግራይ ህዝብ የቆመ የእርዳታ እህልና መድሃኒት የጫኑ መኪናዎችን አይዘርፍም፤ ሾፌሮችን አይገድልም። ግን ግባቸው አንድ ነው። ህዝቡ እንዲመረር፤ እንዲራብ፤ የዓለም እይታ ልክ የዛሬ 40 ዓመት እንዳደረጉት የፓለቲካ ሻጥር አሁንም የአለምን ቀልብ በትግራይ ህዝብ ረሃብተኞች መሳብ ነው። ለትግራይና ለህዝቦቿ ገዷቸው አያውቅም።
    የአሜሪካና የአውሮፓ በዚህ ጉዳይ ላይ ሽውራራ እይታም አገልጋዪቻቸው ከሥፍራው ስለተነሱባቸው እንጂ ለነጩ ህዝብ ለጥቁር ህዝብ ገዶት አያውቅም። ዛሬ ለሚሆነውና ለተፈጠረው ማንኛውም ግጭት ሁሉ የእነርሱ የቀደመ እና የአሁን እጅ አለበት። መሪ ቃላቸው “የራሳቸውን የሃገር ጥቅም ማስጠበቅ ነው” እንደ ስዬ አብርሃ ያሉት ወደ አሜሪካ ሃገር መተው የተደላደለ ኑሮና ከዚያም በላይቤሪያ ለተመድ ሰራተኛ እንዲሆን ያረገው ዓለምን የሚቆጣጠረው የአሜሪካ የስለላ ድርጅት ባመቻቸለት መንገድ ነው። ለቁጥር የሚበዙ የወያኔ ከፍተኛ አመራሮች የዚህ የስለላ መረብ ተከፋዪች ናቸው። አሜሪካ ለትግራይ ህዝብ ገዶአት የሚመስላቸው ሌቦች ዛሬ በኮሎምቢያ፤ በቬንዝዌላ፤ በብራዚል በሰላማዊው ሰው ላይ የሚደርሰውን ግፍ አይቶ መፍረድ ይችላል። ሲጀመር ወያኔ ምዕራባዊያንን የአማራ ጥላቻ አግተዋቸዋል። ለዛ ነው የአማራ ጦር ከትግራይ መሬት ይውጣ እስከማለት የደረሱት። የእብድ ገላጋይ ድንጋይ ያቀብላል እንዲሉ አይነት ነው። በዘመናት መካከል ያደረጉትም እንደዛ ነው እኛ እርስ በእርሳችን ስንላተም እነርሱ አስታራቂና ለመከራ ቀን ደራሽ ሆኖ ለዓለም መታየት።
    አሁን የኤርትራ ጦር ገለ መሌ ከትግራይ ይውጣ የሚባለው ጉዳይም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው። የአስመራው መንግስት ልብ አግኝቶ ጦር መጫሩን ረስቶ ጎረቤቱን መርዳቱ እና ራሱን መከላከሉ ምዕራቡ ዓለምና አረቦች በተለይም ግብጽ አልወደደችውም። ደስ የሚላቸው ሻቢያ ወደ አዲስ አበባ ቢገሰግስ ነበር። ግን ወያኔ ለምን አስመራንና የአማራ ክልልን በተለይም ጎንደርንና ባህርዳርን በሮኬት ደበደበ? ወያኔ በአማራ ህዝብ ላይ ያለው ጥላቻ ሰማይ ጠቀስ ነው። አሁንም ሲናገሩ “ከአማራ ህዝብ ጋር የምናወራርደው ሂሳብ አለን” ይላሉ። የሻቢያ ጥላቻቸው ከባድሜ ጦርነት በህዋላ “የአይናቸው ቀለም አላማረንም” ተብለው ተለይተው የተጋዙት ኤርትራዊያን ሃበሳ ይመስክር። አሁን ማን ይሙት የሃበሻው አይን ቀለም ትግሬ፤ ኤርትራ፤ ኦሮሞ፤ ወዘተ ብሎ ያመላክታል። ግን የተውሶ አባባል እንዲያ ነው ያለቦታው ሲሆን። እብዶች የሚያላግጡበት ፓለቲካ ሁሌ ገዳዳ አስተሳሰብ ይዞ ሲንሻፈፍ ነው የሚኖረው!
    የ30 ዓመታቸውን ነጻነትና ባርነት ሻቢያዎች ሲያከብሩ የእድሜ ልክ መሪው እንዲህ አሉ። “መሬታችን አስመልሰናል” ጸጉር የሌላቸው ሁለት መላጣዎች የሚናጠቋት ያቺ የባድሜ ምድር የወያኔ ሆነች የሻቢያ ፍሬፈርሲኪ ነው። ዋናው ነገር ህዝባችን ተዋዶ፤ ተፋቅሮ አብሮ መኖር ይችላል ወይ ነው። መልሱ አይችልም።
    ወደ ዶ/ር በቀለ ገሰሰ ሃሳብ ስመለስ ሃገር ማዳን የሚባል ነገር የለም። ስንራኮት፤ ስንጠላለፍ፤ ስንጋደል፤ ስንሰርቅ፤ ስናሳርቅ፤ ነጻነት በሌለበት ምድር ላይ ነጻ ነን እያልን ስንዘል የኖርንና የምንኖር ህዝቦች ነን። በተለይ ደግሞ ወያኔና ሻቢያ የሃገር አለቆች ከሆኑ ወዲህ የተዘረጋው የክፋት ሰንሰለት ባህር ተሻግሮ ከሃገር ውጭ የሚኖረውን የሃበሻ ህዝብ ጭምር ስላቆሰለው ህብረት፤ አንድነት፤ ሰላም የሚሉት ነገሮች ሁሉ ህልም እንጂ እውነትነት የላቸውም። ከ 30 ዓመት የእርስ በእርስ ግድያ በህዋላ ነጻነቷን ያወጀችው አዲሲቱ ኤርትራ ከ 30 ዓመት የነጻነት ዘመን በህዋላ ያለ ምንም ለውጥ እድሜን እየቆጠሩ በየአመቱ በውጭና በውስጥ ከበሮና ክራር ይዞ መጨፈሩ በምድሪቱ ያለውን መከራ አይሸፍነውም። የሰውን ገልቱነት እንጂ! ዛሬም ባርነት ትላንትም ባርነት። ለጊዜው በዶ/ር አብይ የሚመራው መንግስት ደግሞ በሃገር ውስጥም ሆነ ከሃገር ውጭ በመነጩ የመከራ ዝናቦች የበሰበሰ በመሆኑ የቆሙበት መሬት መናድ አይቀሬ ነው። አልፎ ተርፎም አሁን ከሻቢያ ጋር ያለው የፍቅረኝነት ጎዳናም ከመገራገጭ አልፎ እስከ መፋለም ሊደርስ ይችላል። ስለሆነም እንደ ሃገራችን ጎርፍ የሃበሻው ፓለቲካም የማይሸከመው ዝባዝንኬ ነገር የለም። እንዲህ ይሁን ያን እናርግ ማለቱ መልካም ሃሳብ ሆኖ ሳለ ለእኔ ግን የሚገባኝ የሃበሻው ፓለቲካ ታክሞ የማይድን፤ በጉራና በያዘው ጥለፈው የተገመደ፤ የማን ነህ ባለሳምንት አይነት የተረኛ ፓለቲካ በመሆኑ ለሃገርም ለወገንም አይጠቅምም። ሃገሪቱ እንድትድን ከተፈለገ ዝም ማለት የሚሻል ይመስለኛል። ዛሬም መለፍለፍ፤ ትላንትም መለፍለፍ የዲስኩረኞች ሃገር በአፍ ቆሎ የሚቆላበት። ተጨብጦ የማይቃም ነገር። እግዜር ይይላችሁ። በቃኝ።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share