May 29, 2021
35 mins read

የሃገራችን ወቅታዊ ሁኔታና ዲፕሎማሲ ከውስጥም እንመልከት! – መላኩ ከአትላንታ

ኢትዮጲያ በአለም አቀፋዊ ጫና እንደዚህ ተወጣጥራ ባለችበት ሁኔታ ለሃገራችን ችግር መፍትሄ እኛው ኢትዮጲያውያንና ትውልደ ኢትዮጲያውያን ስለሆንን ፣ ሁላችንም ኢትዮጲያንና ኢትዮጲያን ብቻ በማስቀደም እንደ አድዋው ዘመን በአንድነት መቆም ይኖርብናል። የሚነገረው ሁሉ በትግራይ ስላሉ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ችግርና ሰብዓዊ ቀውስ መሆኑ ልባችንን የሚሰብር ቢሆንም ፣ ፈርዖን ከግርግሩ ለማፈስ ሀገራችንን እንደ ጦስ ዶሮ እየዞረ ፣ ከጎረቤቶቻችንጋ ስምምነቶች ከመፈራረም ባለፈ የጦር ልምምዶችንም እያደረገ መሆኑን ስንመለከት በጉዳዩ የፈርዖን እጅ ፈፅሞ የለበትም ብሎ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻልበት ሁኔታ ላይ አይደለንም። በዚህ ሁኔታ ለኢትዮጲያውያን በአንድ ላይ መቆም ዋናው የሀገር ፍቅር ቢሆንም ተጨማሪውን  ትልቁን ስንቅ የሚያቀብለው በዶር አብይ አህመድ የሚመራው አስተዳደር የሚያራምዳቸው ፖሊሲዎችና አተገባበሮችም ናቸው።

በቅርብ መንግስት ሽብርተኝነትን አስመልክቶ ካወጣውም መግለጫ እንደምንረዳው ፣ የሀገሪቱ ዋነኛ የውስጥ ችግሮች የሚመነጩት ትህነግ (ወያኔ) እና ኦነግ (ሸኔ) የሚባሉ ድርጅቶች ከሚያቀነቅኑት የጠባብ ብሄርተኝነት አስተሳሰብ መሆኑን እንመለከታለን ። በሀገራችን ውስጥ በርካታ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች በሱማሌ ፣ በኦሮምያ ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝና በደቡብ ክልሎች ተፈፅመዋል ። በህገ መንግስትነት የሰፈሩት የወያኔና የኦነግ የፖለቲካ ፕሮግራሞች በሀገራችን ላለው አለመረጋጋት መሰረት ናቸው። ይህ አመለካከት ተነቅፎ ከህገ መንግስቱም እስካልተሰረዙ ደረስ ፣ የዘር ፍጅትና ማፈናቀል ዛሬም ይሁን ነገ ስላለመፈፀሙ ማንም የማስረጃ ፋክቱር ማቅረብ አይችልም።

በሀገራችን ይህ ሁሉ እልቂት ሲፈፀም ፣ አንድ ሁለት ተብለው የሚጠቀሱ ከተሞች ሲነዱ በአይናችን በዘመናችን እያየን ፣ የዶር አብይ መንግስት እንደ አፄ ምኒሊክ “የበደልኩህ አይመስለኝም አንተም እስካሁን አላስቀየምከኝም”  … ወይም ችግርህን በጉያህ … የሚል አዋጅ ሊያስነግር እንደማይችል ባውቅም ፣ ይህን ሀሳብ በዋነኛነት የማቀርበው የትግራይን ህዝብ ከሌላው ኢትዮጲያዊ ወገኑ ለመለየት ፣ ወያኔ ካጠመደበት የሴራ ጉንጉን በማላቀቅ ፍፁም በኢትዮጲያዊ ማንነቱ ላይ እንዲቆም በማድረግ የኢትዮጲያ አንድነትን ለማጠናከር ይረዳል ከሚል ነው። የኢትዮጲያ አንድ አካል የሆነው የትግራይ ህዝብ አካባቢ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ ሲስተካከል ፣ ጣልቃ ገብ የተባለውም የምዕራባውያን አቋም ዘይት ያጣል።ያደፈጠው ፈርዖንም የውሃ ብርጭቋችንን ለመገልበጥ ካሴረው ተንኮል ይታቀባል።

ላለፉት አርባ ምናምን አመታት ከህወሃት የሃሳብ ልዩነት ያለው የትግራይ ህዝብ ፣ በትህነግ (ወያኔ ) ኢህአፓ ነህ  ፣ ኢዲዩ ነህ ፣ ኢትዮጲያ ትላላህ ወዘተ እየተባለ እንዲጠፋ የተደረገና የወያኔን መርዘኛ ርዕዮት ብቻ እንዲጋት የተደረገ ነው። ነገር ግን ከኤርትራ ወታደሮች በኢትዮጲያ መግባት ጉዳይ ውጪ ፣ ዛሬም ቢሆን የወያኔን ሃሳብ የማይጋሩ በርካታ የትግራይ ልጆች እንዳሉ የሚታወቅ ነው። ወያኔ በኢትዮጲያ ሰሜን ዕዝ ላይ ቅፅበታዊ ብሎ በፈፀመው የአርባ አምስት ደቂቃ ጥቃት ተከትሎ በተጫረው ጦርነት ምክንያት ፣ የኤርትራም ወታደሮች በኢትዮጲያ ተከስተዋል። ይህን ተከትሎ በትግራይ ተወላጆችና በሌሎች የዜግነት ትርጉም በገባቸው ኢትዮጲያውያን ያደረውን ስሜት ለመረዳት ስሞክር ፣ በመጀመርያ የትግራይ ተወላጆችን በሚከተሉት ጎራዎች ከፋፍዬ መመልከት እንዳለብኝ እገነዘባለሁ።

  1. የወያኔ ከፍተኛ አመራርና የቅርብ ተጠቃሚ የሆኑ ቤተሰቦቹ
  2. የወያኔ የአፈና መዋቅር አካላት

3 የወያኔ የፖለቲካ ካድሬ

4 የወያኔ ተራ የፓርቲ  አባላት

5 የትግራይ የፖሊስ እና የልዩ ሃይል አባላት

6 ወያኔ የዘረፈው ሁሉ የኔ ነው ብሎ በስግብግብነት ወይም ካለማወቅ በስሜት የሚናጥ

7 ወያኔ የትግራይን ህዝብ ከሌላው የአትዮጲያ ህዝብ አጋጭቶ ትግራይን ለመገንጠል የሄደበትን መርዘኛ መንገድና ወያኔ በሌላው የኢትዮጲያ ህዝብ በተለይ በአማራው ብሎም በወልቃይት ፀገዴና መሰል ህዝብ ላይ ከአርባ ዓመታት በላይ የሰራውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ጭምር ተረድተው ፣ ለኢትዮጲያ ልዕልና የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ለማድረግ አመቺ ሁኔታን እንዲመጣ የሚጠባበቁ

8 ምንም አይነት የፖለቲካ ጉዳይ ውስጥ የመግባት ፍላጎት የሌለው ባብዛኛው መሬት ጭሮ ቀኝ አውለኝ ብሎ የሚኖር ህዝብ

እንደ አድዋው ዘመን አንድ እንሁን ስል በአድዋ ዘመቻ አልፎ አልፎ ለጠላት ያደሩ ባንዳዎች እነደነበሩ ሳልገነዘብ አይደለም።በአጠቃላይ ዕይታ ግን አፄ ምኒሊክ ከሰሜን እስከ ደቡብ ፣ ከምስራቅ አስከ ምዕራብ ያለውን ኢትዮጲያዊ ሁሉ አሰባስበው በአንድ የዕዝ ሰንሰለት ማሰለፍ ችለው ነበር። ዛሬ ኢትዮጲያውያንን ለማመስ ብሎም ሀገር ለማፍረስ የሚያቀንቅነው ፣ ዘረኛ የወያኔ ስርዓት በቀጠለበት፣ ሀገሪቱ እንድትበታተን የሚፈቅድ ህገ መንግስት ባለበትና ፅንፈኛ ብሄርተኝነት የምናየው ደረጃ በደረሰበት ፣ ሁኔታችን ኢትዮጲያውያን የጣልያን ጦርን አድዋ ላይ ከገጠሙበት ተመሳሳይ ነው ማለት አይቻልም።ኢትዮጲያ ካላት ወቅታዊና ሀገራዊ ጉዳዮች አንፃር በሀገር ውስጥ ያለውን ሁኔታ ለመቀየር መንግስት ብዙ መስራት ይጠበቅባታል። እዚህ ላይ ዳግም ሊሰመርበት የሚገባው የትግራይ ህዝብ የተለያየ አመለካከት ቢኖረውም በኤርትራ ወታደሮች ኢትዮጲያ ውስጥ መኖር ዙሪያ ባለው አመለካከት ልዩነት አይታይበትም።

ህገ መንግስቱ ኢትዮጲያ የሀገሮች ስብስብ ነች ፣ አባል ሀገራቱም ከፈለጉ በብልፅግና ‘ህብረ-ሄራዊነት’ ተብሎ ከሚጠራው ህብረት አንቀፅ 39ን ተጠቅመው ከኢትዮጲያ መገንጠል ይችላሉ ይላል። ወያኔዎቹም እየነገሩን ያሉት ይህንኑ ተጠቅመው የዘረፉትን ይዘው የትግራይን ነፃ ሀገርነት እንደሚያውጁ ነው። በኦሮምያና በቤንሻንጉልም እጅግ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጥቁ ሃይሎች ይንቀሳቀሳሉ ፣ ንፁሃንን ያርዳሉ ፣ ከዚያም አልፈው ያወደሟቸውን ከተማዎች ጭምር ፣ ሻሸመኔ አንድ አጣዬ ሁለት በማለት እያስቆጠሩን ነው ። ይህ የሚሆነው ከመንግስት አካላት ፍቃድ ውጪ ነው ካልን ታጣቂዎቹ ከመከላከያው አቅም በላይ ናቸው ማለት ነው። በፍጅቱ የመንግስት እጅ አለበት ወይም ከመንግስት አቅም በላይ ሆነዋል ከሚሉት ከሁለቱ አንዱን መምረጥ ግድ ነው።

ይህ ሁሉ ውጥንቅጥ ባይኖር ከትግራይ ውጪ በሆነው የሀገራችን ክፍል ያለውን ህዝብ ፣ ገዢው የብልፅግና ፓርቲና ሀገር ውስጥ ያሉ ተፎካካሪ ድርጅቶች በመረባረብ ኢትዮጲያ አሁን ካጋጠማት አደጋ እንድትሻገር ኢትዮጲያዊያንን በጋራ ቆመው በሁሉም መስክ በአንድነት እንዲታገሉ ለማድረግ ይቀላቸው ነበር። ትግራይን በተመለከት ወያኔ ሀገረ ኢትዮጲያን ከሚጎዳ መንገድ እንዲታቀብ ማግባባት ማለት ሳትናኤልን ለማቀሰስ ከመሞከር ተለይቶ የሚታይ አይመስለኝም። ነገር ግን በተራ ቁጥር አንድ እና ሁለት ከተቀመጡት ማለትም ከወያኔ ከፍተኛ አመራርና የቅርብ ተጠቃሚ የሆኑ ቤተሰቦቹና የአፈና መዋቅሩ አካላት ውጪ ያሉትን የትግራይ ባለድርሻዎች ወደ ሰላማዊና መሀከለኛ ሀሳብ ማምጣት ይቻላል። ይህም ኢትዮጲያዊነት ላይ ብቻ የቆመ ጥበብን ይጠይቃል።

የኢትዮጲያ ህገ መንግስትና የዶር አብይ አስተዳደር የሚያቀነቅነው ያንኑ የወያኔ ከፋፋይ የጎጥ ፖለቲካ መሆኑ ትግራይ ውስጥ ተንሰራፍቶ ያለውን ከፋፋይ ወያኔያዊ አመለካከትና ፍልስፍና ከትግራይ ህዝብ ለመነጠል ትልቁ እንቅፋት መሆኑ ከግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል። ይህ ትልቁ ችግር እንደተጠበቀ ሆኖ ፣ የዶር አብይ አስተዳደር የትግራይ ህዝብን በቀጥታ በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ የሚከተሉትን የማረሚያ እርምጃዎች ቢወስድ ፣ በወቅታዊው የሀገራችን ችግር ብቻ ሳይሆን ለዘለቄታው ኢትዮጲያን እያንዣበበባት ካለው ውጪያዊ አደጋ በጋራ ለመቋቋም ብሎም ለማሸነፍ ለልጆቿ በአንድ አላማ መሰባሰብ አሌ የማይባል አዎንታዊ አስተዋፅፆ ይኖረዋል።እነዚህ የመንግስትን ስራ የሚጠይቁ ጉዳዮችም የሚከተሉት ናቸው።

 

አንደኛ የኤርትራ ወደ ኢትዮጲያ መግባት

የኤርትራ ጦር ወደ ኢትዮጲያ ውስጥ እንዲገባ ምክንያት የሆነው ወያኔ በሰሜን ዕዙ ላይ በወሰደው ጥቃት መሆኑ ጤነኛና ሚዛናዊ አመለካከት ያለው ሁሉ በቀላሉ የሚረዳው ነው። አፄ ምኒሊክ ከአፄ ዮሃንስ ተፋጠው በነበረበት ሁኔታ ፣ ማዕከላዊ መንግስት ከነበሩት ከአጼ ዮሀንስጋ ጦርነት ውስጥ መግባት ስልጣናቸውን ብቻ ሳይሆን ፣ የስልጣን መሰረታቸው የነበረው የሸዋ አማራ ፣ የሸዋ ኦሮሞ ጉራጌና ሌሎች ማህበረሰቦች ላይ ሊደርስ ይችል የነበረውን ጥፋት አጎንብሰው በማሳለፍ ፣ ያላቸውን የፖለቲካ ጥበብ አሳይተዋል። በአንፃሩ ወያኔ ታላቋ ትግራይን እፈጥራለሁ በሚል ወንዝ ተሻግሮ የወልቃይትና የራያ ህዝብ ላይ የሰራውን ወንጀልና ያ የሚያመጣውን መዘዝ ሳያገናዝብ ፣ በሰሜን ከኤርትራጋ አብሮ ዘርፎ ብቻዬን ልብላ በማለቱ ከፕሬዛዳንት ኢሳያስ አፈወርቂጋ የፈጠረውን ቁርሾና መዘዙን ሳያገናዝብ ፣ ለስልጣን የበቃው በሶቪየት ህብረት መፍረስ መሆኑን ሊረዳ ባለመቻሉ ፣ በዕብሪት ከማዕከላዊ መንግስትጋ በቀሰቀሰው ጦርነት ነዷል፣አስመራም በሚሳዬል ተመትታለች ፣ የኤርትራ ጦር አንዲገባ ሆኗል ፣ በጦርነቱም የትግራይ ህዝብ ብዙ ችግር እያሳለፈ ነው።

በኢትዮጲያና በኤርትራ መሃከል እስካሁን በአግባቡ ያልተፈታ የወደብ ጉዳይ ቢኖርም ፣ የኤርትራ ህዝብ በብዙ ምክንያት መልካም የምንመኝለት ከጎረቤትም በላይ የሆነ ህዝብ ነው። የክልል ልዩ ሃይል በሚል ከመቶ ሺህ በላይ በውትድርና የሰለጠነ ሰራዊት በየክልሉ ባለበት ፣ ትግራይ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ለመቆጣጠር የኤርትራ ወታደሮች ዛሬም ኢትዮጲያ ውስጥ መኖር በብዙ ምክንያት ትርጉም የለሽ ብቻ ሳይሆን አብሻቂ ነው። ትልቁ ችግር በቅርቡ ባድመን አስመልክቶ በነበረውም ጦርነት ምክንያት በነበሩ ቁርሾዎች ፣ የትግራይ ተዋላጆች ብሎም ዜግነትን የምናቀነቅን ኢትዮጲያውያን የኤርትራን ወታደሮች በኢትዮጲያ መንቀሳቀስ በበጎ ልንመለከተው አንችልም። የዜግነት ትርጉምን ያፋልሳል። ለምን ገቡ ለሚለው ተጠያቂው ሙሉ በሙሉ ወያኔ እራሱ ነው። ሀገሪቱን ከኤርትራ ጦር ለመከላከል ድንበር ላይ የነበረውን የሰሜን ዕዝ መገናኛውን ቆርጠው ፣ ከፍተኛና ዘግናኝ ጥቃትና ወንጀል ከፈፀሙ በኋላ ተመልሶ የኤርትራ ጦር ለምን ገባ ማለት አላዋቂነት ወይም ተራ ማጭበርበር ነው።

የኤርትራ ወታደሮች በኢትዮጲያ አሉ የሉም የሚለው ብዙ ውዝግብ የተደረገብትና በዲፕሎማሲው ረገድ የኢትዮጲያን ተሰሚነት እጅግ የጎዳ ጉዳይ ነው።እያሰብን ያለነው አሜሪካኖቹ ያነጣጠሩት አትዮጲያ ላይ ብቻ እንደሆነ ብቻ ይመስላል። የኤርትራ ጦር ከኢትዮጲያ አለመውጣት ምክንያት ሆኖ ፣ አሜሪካ የኢሳያስን መንግስት ለማፈራረስ ፣ ከእስታር ባክስ ድሮኖቿን አና ሚሳኤሎችን በማስወንጨፍ በኤርትራ የመንግስት ለውጥ ብታደርግ ፣ የወያኔ እንደገና ነፍስ መዝራት ወይም ስለ ፈርኦን በዙሪያችን መሽከርከር ስለምንለው ነገር የሚፈጥረውን ሁኔታ ከግምት ያስገባን አይመስልም። የኤርትራ ወታደሮችን በማስወጣት የኢትዮጲያውያንን አንድነት ማረጋጋት፣ የሚኖረውን የዲፕሎማቲክ ጫናም ማቀዝቀዝ በራሱ ጥበብ ነው። ከሁሉም በላይ የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ መውጣት ፣ ለትግራይ ተወላጆች ብቻ ሳይሆን የዜግነት ትርጉሙ ለገባን ፣ የሰንደቃችንን ትርጉም ለምናውቅ ፣ ስለ ኢትዮጲያ አንድነት ትልቅ ትርጉም አለው።

 

ሁለተኛ ወልቃይት ፀገዴ ራያና ወያኔ የዘረፈው ሁሉ የኔ ነው

ኢትዮጲያ በሀገራት ህብረት የተፈጠረችና በአባላቱ ፍላጎት ልትፈርስ የምትችል ነች የሚለውን የብሄር ፖለቲካና ዘረኝነት ፈፅሞ እጠየፋለሁ። ኢትዮጲያውያን በብሄረሰብ ወይም በዘር መከፋፈል የለብንም ፣ ፖለቲካችን ከዚህ ቆሻሻ አስተሳሰብ ሊፅዳ ይገባል የሚል ፅኑ  እምነት አለኝ። በዚህም መሰረት ወልቃይት ፀገዴ በጎንደር ይካለል በትግራይ ፣ በአማራ ክልል ይካለል ወይም በትግራይ ክልል የሚል ወገንተኝነት የለኝም። ትግሬም ሆነ አማራ ሁለቱም ኢትዮጲያዊ ወገኖቻችን ናቸው። ያም ሆኖ ግን ዛሬ ሀገራችን ባለው የፖለቲካ መነፅር ስንመለከት ፣ አክሱም ፣ አድዋ ፣ ሽሬ ፣ ኢሮብ ወዘተ ነን የሚሉ የትግራይ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ ፣ ወልቃይቴ ነን የሚሉ ኢትዮጲያውያንም እንዳሉ መታወቅ አለበት።

ፍትህን ለምንሻ ፣ ትልቁ ቁም ነገር ወልቃይት የትግራይ ክልል አካል ነው ወይስ የአማራ ክልል አላ፤ የሚለው ሳይሆን ፣ ወልቃይቴ ነን የሚሉት ሰዎች ምንድን ነን ብለው እራሳቸውን ይሰይማሉ የሚለው ነው። ስለዚህ ነፃ ህሊና ያለው ኢትዮጲያዊ በሙሉ የወልቃይት ፀገዴና መሰል ህዝብ ድምፅ ይከበር በሚለው ልንግባባ ያሻል። ስልጢ ጉራጌ ነው አይደለም ለሚለው ስብሃት ነጋ ስልጢዎች ብቻ እንዲወስኑ አድርጓል። በቅርቡም ስለ ሲዳማ ድምፅ የሰጡት ሲዳማዎች ናቸው። ስለዚህ መንግስት ባስቸኳይ ወልቃይቴዎች ራያዎችና ሌሎች  ማህበረሰቦች ፣አማራ ነን ይላሉ፣ ትግሬ ነን ይላሉ ወይስ ከሁለቱም አይደለንም ይላሉ የሚለው ላይ በድምፅ ብልጫ በማስወሰን ፣ ይች ችግር ተለባብሶ ፣ በአለም አቀፉ መድረክ አማራ ይውጣ ፣ እንትና ይግባ ከሚል የውዝግብ አጀንዳነት ሊያፀዳው ይገባል። አይ ከተባለ ህገ መንግስቱን ቀይሮ የክልል ሳይሆን የአስተዳደር አመቺነትን አገናዝቦ በመላው ኢትዮጲያ አዲስ ካርታ መስራት።

ከዚህ ጉዳይጋ ተያይዞ የሚነሳው  ድምፅ መስጠት ያለበት ማን ይሁን የሚለው ነው። ማንነትን በሚያቀነቅን ስርዓት ከአድዋ ፣ ከአክሱም ፣ ከጎንደር ወይም ከጎጃም የመጡ ሰዎች ስለ ወልቃይት ፀገዴ ራያ ወይም ሌሎች ማንነት ድምፅ መስጠት የለባቸውም። ከወለጋና ከጋምቤላ የመጣ ህዝብ ስለ ወልቃይቴ ማንነት ድምፅ መስጠት የለብትም። የወልቃይት ፀገዴ፣ የራያ የአዲስ አበባና መሰል ጉዳዮች ወያኔ በዐማራና በትግራይ ፣ በዐማራና በኦሮሞ ህዝብ መሃከል ቋሚ ቁርሾ ለመፍጠር በማሰብም የተከላቸው ናቸው። ጥንትም ትግሬው ዐማራው ሰፈር ሄዶ ይኖራል፣ ዐማራው ትግሬው ሰፈር ሄዶ ይኖራል ፣ ህዝቡ ይጋባል ፣ ይዋለዳል ፣ ይጋጫል ፣ ይታረቃል ፣ በቋንቋ ፣በባህል ፣ በአመለካከት በጣም ተቀራራቢ ህዝብ ነው። ስለዚህ ወልቃይት ማን ነው የሚለው ባስቸኳይ ምላሽ ተሰጥቶት በሁለቱ ህዝቦች መሃል በዚህ ምክንያት የሚርገበገብ የልዩነት አጀንዳ እንዳይኖር ሊደረግ ይገባል።

በወልቃይት በራያና ሌሎች ቦታዎች ወያኔ ሆን ብሎ ያጠመዳቸውን መረቦች ማምከን እጅግ አሰፈላጊ ነው። ወያኔ የዘረፈው ሁሉ የኛ ነው በሚሉ ስግብግቦች ወይም አላዋቂዎች ምክንያት ፣ ወያኔ የትግራይ ህዝብ ብቸኛ ልዩ ጥቅም አስከባሪ ተደርጎ እየታየ ነው።የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ሆነ በትግራይ ያለው አዲሱና ወጣቱ ትውልድ ፣ ወያኔ በወልቃይትና መሰል አካባቢዎች ላይ የፈፀመውን የዘር ማጥፋት ወንጀሎች የሚያውቅም አይመስልም።ይህ አርባ ዓመታትን ያስቆጠረ ወንጀል በሀገሪቱ ፓርላማ ቀርቦ ውይይት ሊደረግበት ፣ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም እንዲያውቀው ሊደረግ ይገባል።ከዛ ውጪ ከየትኛውም የኢትዮጲያ ክፍል የሚመጡ ኢትዮጲያውያን በወልቃይት ፀገዴ ራያና ሌሎች ቦታዎች የመኖር ፣ ሀብት የማፍራት በፖለቲካው የመምረጥ የመመረጥ ወዘተ መብታቸው መከበር አለበት።

የህዝብን አመለካከት ማረም ፣ የኤርትራ ወታደሮችን ማስወጣት ፣ ተሰሩ የሚባሉ ወንጀሎችን በገለልተኛ ወገን ማጣራትና የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ቁርጠኛ ጥረት ማድረግ፣ ወያኔ በቀላሉ  ጠመንጃ ተሸካሚ እንዳይኖረው ያደርጋል። በዚህም በሚኖረው ሰላም  ችግር ውስጥ ላሉ ወገኖቻችን የአስቸኳይ እርዳታ እንዲደርስ በማድረግ ፣ ህዝባችንን ከርሃብ በመታደግ፣ ሀገራችን እንደገና በርሃብ ስሟ እንዳይጠራ ለማድረግ አሰተዋዕዖ አለው።የትግራይ ህዝብ ሀገሩ መላው ኢትዮጲያ እንጂ ትግራይ አይደለችም። በየትኛውም የኢትዮጲያ ክፍል ሄዶ የመኖር ፣ የመስራት ፣ በእኩል የመዳኘት ፣ የመምረጥና የመመረጥ መብቱ ሊረጋገጥለት ይገባል ። የአማራውም መብት እንደዚሁ።

 

ሶስት ልዩ ሃይሎችና መከላከያ

ኢትዮጲያ ከተማዎቿ በሽፍቶች ነደዱ እየተባለ ፣ ከደርግ ጦር በብዛት ብዙም ያላነሰ የሰለጠነና የታጠቀ የልዩ ሃይል የሚመሩ የክልል ፕሬዜዳንቶች እኛ ገበሬ ነን እያሉ የሚሳለቁባት ሀገር መሆኗ ማቆም አለበት። በፖለቲካው ምክንያት ህዝብ ከሀገሩ ክልሉን መርጦ በየክልሉ ልዩ ሃይል መታቀፍን ቅድሚያ በሚሰጥበት፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባልነት የሚመዘገብ ጠፋ የሚል ቀልድ መቆም አለበት። የሱዳን ጦር የኢትዮጲያን ጦር ጥሶ ገባ ሲባል የአማራ ሀገር ብቻ እንደተደፈረ የሚያስቡና የሚፅፉ በርካታ ኢትዮጲያውያንን ያየንበት ወቅት ላይ ነን። ነገ የግብፅ ጦር ገባ ሲባል በየትኛው ክልል መጣ ፣ ያገባናል አያገባንም ብለው የሚፈላሰፉ እንደሚኖሩም ግልፅ ነው። ሰለዚህ በየክልሉ ያሉ ልዩ ሃይሎች በሀገሪቱ የመከላከያ ሰራዊት ተጠቃልለው ፣ የሀገራችን የመከላከያ ሰራዊት በፍፁም ተጠናክሮ ህዝብንና ሀገርን ከውስጥና ከውጪ ጥቃት የመከላከል ከፍተኛ ብቃት እንዲኖረው ብቻ ሳይሆን ፣ በአካባቢው የተፈራ፣ የተከበረ ሃይልና የሀገር ኩራት እንዲሆን በዙ መሰራት አለበት። ያ አርቆ የማያይ ፊታውራሪያቸውም አልነበር ጥርሳቸውን አውልቀናል ምንትሴ እያለ የተዘባነነው።

 

ከወያኔጋ ተነጋገሩ

አሜሪካ ማወቅ የነበረባት ለኢትዮጲያ ሰላምና አንድነት ሲባል ከወያኔጋ ተነጋገሩ ስትል ፣ ከእባብ እንቁላል እርግብ የመጠበቅ ያህል መሆኑን ነበር። መንግስት የሚያራምደው ሃሳብ ከወያኔ የተለየ ባለመሆኑ ይህን ፀሀይ የሞቀው አውነታ ለአሜሪካኖቹ በትክክል ማስረዳት አልቻለም።የአንድነት ሃይሉም ይህን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ ከመጣር ደካማ መሆኑ ሳያንሰው ባንዲራ ስለማቃጠል ሲተርት ተደመጠ። ወያኔ ሁሌም ፍላጎቱ ለታላቋ ትግራይ መደላድልን ማዘጋጀት ፣ የሌላውን የኢትዮጲይ ክፍል በከፋፍለህ ግዛው መርህ በበላይነት ሆኖ መዝረፍና ያ ያልሆነ ዕለት የዘረፈውን ይዞ የትግራይን ነፃ ሀገርነት ማወጅ ነው። የዶር አብይ አስተዳደር ከዚህ ሃይልጋ ቢነጋገር ለኢትዮጲያ ህዝብ ጠብ የሚል አንዳች ነገር አይኖርም። ተነጋግረው የተስማሙ ዕለት ያው ዘርና ጎጥን መሰረት ያደረገ ሸምቀቆ ይጠብቃል።

ወያኔ እንደዚህ ተዳክሞ ባለበት ጉልበት የሆኑት ፣ አስቀድሞ በወልቃይት ፀገዴ ፣ በራያ ፣ በአዲስ አበባ ወዘተ በሕገ መንግስትና በንዑስ ወያኔነት ርዕዮቱን ያጠመቃቸው በየክልሉ ያሉ ባለሟሎቹ ናቸው። ዲፕሎማሲ ሁሌም በተቻለ መጠን ከፍታ ያለው መርህ ላይ መቆምን ስለሚጠይቅ ፣ የዶር አብይ አስተዳደር በብልህነት ፣ ልክ ነው፣ ከወያኔጋ መነጋገር ችግር የለብንም ብሎ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ፊት በመቆም የችግሩ ምንጭና በአርግጥ በመነጋገር ፣በአብላጫ ድምፅ የማያምን ህወሃት መሆኑን ማሳየት አንዳይችል ፣ በወያኔ እና በብልፅግና መሃከል ማ ስልጣን ያዘ ማንስ ከስልጣን ተገፋ ከሚል ያለፈ መሰረታዊ የፖለቲካ ርዕዮት ልዩነት አለመኖሩ ትልቅ እንቅፋት ነው። ወያኔም ሆነ ብልፅግና ሁለቱም የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጎጥ ፖለቲካ አራማጆች ናቸው።

በዚህ ሁኔታ ቢያንስ ሕገ መንግስቱ ከወያኔም ሞት በኋላ በቀላሉ መሻሻል እንዳይችል፣ የአባላጫ ኢትዮጲያውያንን ድምፅ ለማፈን ፣ ወያኔ በጠመንጃ አፈሙዝ የተከላቸውን አንቀፆች አንቀፅ 39ን ጨምሮ በአስቸኳይ በመቀየር ፣ በሀገራችን የሰሜን ዕዝ መከላከያ ሰራዊት ላይ ለተፈፀመው ወንጀል በቀጥታ ተጠያቂ የሆኑ የወያኔ አመራር አባላትን ለይቶ በመዘርዘር ፣ ከወንጀል ነፃ የሆነ የህወሃት አባል ወይም አመራርጋ እነጋገራለሁ ቢል ኳሱ በወያኔ እጅ ገባ ማለት ነው። ከጠመንጃው መለስ ያሉትን የወያኔ ጥርሶች ማለትም ወልቃይት ፀገዴ ፣ ራያ ፣ አዲስ አበባ ፣ ሕገ መንግስት ፣ ልዩ ሃይል ወዘተ ማምከን ፣ የወያኔ ማንነት ራቁቱን እንዲቀር ፣ የትግራይ ህዝብ ዘለቄታዊ ጥቅም አስከባሪም አለመሆኑን ግልፅ እንዲሆን ያደርጋል። ተነጋገሩ አልተነጋገሩ ያው ዕጣ ፈንታችን አማራጭ የለሽ የብሄር ብሄረሰቦች የጎጥ ፖለቲካ በሆነበት በሚመጣ የዓለም አቀፍ ጫና ምክንያት የሱዳኖችና የፈርኦን መቀለጃ እንዳንሆን መንግስት በውስጣዊው ሁኔታ ብዙ መንቀሳቀስ አለበት።

ከላይ አንድ ሁለት ሶስት ተብለው የተዘረዘሩትን ባስቸኳይ መተግበር ፣ ትግራይን በተመለከተ ስላለው የፓለቲካ ፣ የሰላም ፣ የደህንነትና የመረጋጋት ብሎም የአለም አቀፋዊ ዲፕሎማሲ ዙሪያ ከፍተኛ አዎንታዊ አስተዋፅዖ ይኖረዋል። የሀገር አንድነትን ያበረታል። ዲፕሎማሲ የሀገርን ጥቅም ማስከበር ነው። ዲፕሎማሲ የሚጀመረው ውስጣችንን በማፅዳትና ሀገራዊ ጥቅማችንን በመረዳት ነው። የሀገርን ጥቅም በትክክል ለማወቅ ውስጣችንን ከከፋፋይ፣ ዘረኛ፣ ጎጠኛና ሁሉን ነገር ከሀገር ሳይሆን ከክልል ጥቅም አንፃር ከሚመለከት ጠባብ የትህነግ (ወያኔ) እና የኦነግ ( ሸኔ ) ፓለቲካ ማፅዳት ይኖርብናል። አለበለዚያ ስለ ነቀዘ ስንዴ እያወራን ነቅዘን አለን።

የሃገራችን ወቅታዊ ሁኔታና ዲፕሎማሲያችን የተሳሰሩ ናቸውና ከውስጥም እንመልከት!

 

መላኩ ከአትላንታ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop