ሮፍናን በዚህ ፈታኝ ወቅት – መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

ሮፍናን በዚህ ፈታኝ ወቅት ፣ በሰውነት ተፋቅረን ዳግማዊ አደዋን እንድንሰራ ወቅታዊ ጥሪ ያሥተላለፈልን ጀግናችን ነው ።

ለሁሉም ጌዜ አለው

የእኛን ሰው ፣ አዋከቡት
ዘር ጭነውበት
ሰውነቱንም አሥረሱት
በቋንቋ ከፋፍለውት ።
ሰው የተሰኘውን የወል ስሙን
የደም፣ የሥጋና አጥንት አንድነቱን
የቆዳውን ፣ የጭቅላቱን ና የፊት ቅርፁን ።
የቁመናውን ተመሳሳይነት
ሰረዙት ሰውነቱን ፣ የቋንቋ ሥም በመሥጠት ።
የሰው ፍጥረቱ ሲመረመር
ሰው በሳይንሥ ሆነ በኃይማኖት
ከሰው በሥተቀር ሌላ ሥም ሳይወጣለት
በእኛ አገር ግን ለሙከራ
ሰው ተፈረደበት በቋንቋው እንዲጠራ ።
ይባስ ተብሎ የእገሌ ቋንቋ እየተባለ ፣አገር ተከለለ
ዜግነት ረክሶ የፖለቲከኞቹ ቋንቋ
ሰማይ አከለ።
በህዝብ መካከልም የባቢሎን
ግንበኞች ታሪክ ተደገመ
አንዱ የዳቦ ያለህ ብሎ ሲጮኽ ፤
ሌላው አፈር አሥቃመ ።
ለሠላሣ ዓመት ግተው አሠከሩት
እንዲሆን ድንብርብር
እንዲወላገድ መያዣ መጨበጫ በሌለው ፣ በአበደ የፖለቲካ ዛር ።
ዛሬ ግን ያ ሰውነቱን የረሳው ፣ ተርታው ሰው
ሰውነቱን በኢትዮጵያ ጠላቶች ሴራ ተረዳው ።
የዘር ፖለቲካ ሴራ ምን እንደሆነ አወቀ
በውሥጥ እና በውጪ ጅቦች ሴራም ተደነቀ ።

ግንቦት 11/2013 ዓ/ም
የግጥሙ ባለቤት መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

ይህንን ግጥም እንድፅፍ ያነሳሳኝ የሮፍ ናን ( የኑሪ ሙዘይን )” ሠከላ “የተሰኘ አዲስ ዘፈን ነው ። የዘፈኑ ግጥም ፣ ኮርኳሪ ና አንቂ ነው ። ከታሪክ አንፃርም በታሪካችን እንድንኮራ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ጥቂት ጀግኖቻችንን በማውሳት ፣ የእነዚህ ሥመ ጥር ጀግና የአፍሪካ ኩራት የሆኑ ጀግኖች ልጆች መሆናችንን በማሥታወሥ ፤ ሰው መሆናችንን ተገንዝበን ፣ ለፍቅርና ለይቅርታ ልባችንን እንድንከፍት የሚመክር ፣ ወቅታዊ መልክት ያለው ጥበባዊ ስራ ነው ፡፡

ሮፍ ናንን በግሌ በጣም አደንቀዋለሁ ። በእርግጥ ማንም ልቡ ለኪነት የቀረበ ይወደዋል ። በበኩሌ ግን የራሱ የሆነ ፣ ልዩ የሆነ የሙዚቃ ፈጠራና የአገጣጠም ሥልት ያለው ፣ የዘመናችን ሊቀ ኪነት ያሬድ ብዬዋለሁ ።

ሮፍ ናን ሙዚቃ የመፍጠር ና የማቀናበር ችሎታው ምጡቅ ነው ። ሮፍ ናን ለእኔ ከሙዚቃ አንፃር ፣ ምጡቅ ና ሰማያዊ የሆነ ምናብ ያለው የጥበብ ሰው ነው ። እንደ ኢትዮጵያዊው የዜማ ሊቅ ያሬድ እሱም አዲስ ሙዚቄ ፣ አዲስ ኢትዮጵያዊ ሥልትን ፈጣሪ በመሆኑም ዓለም ያደንቀዋል ። ነፍሱ የሰውን ተላላነት ጠልቃ የምትገነዘብ በመሆኗም ግጥሞቹ ጠንካራ መልዕክት ያላቸው ናቸውና ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው ልጅ የጥበብ መልክት ከእንቅልፋቸው ነቅተዋል ፡ ። ትላንትም እንደዛሬው ፣ ሰው ተላላነቱን ተገንዝቦ ሲያበቃ “እውነትም ይህ እውነት ፣ ጠፍቶን ነበር ! ” በማለት ፣ ሰው ማንነቱን አውቆ ፣ እንዲባንን የሚያደርጉ ግጥሞቹ ናቸው ከእንቅልፉ ያስነሱትና ፣ ሰው መሆኑን በቅጡ እነዲገነዘብ ያደረጉት ።

ሮፍ ናን ፣ በውብ ዜማ ና በተለየ የኤሌክትሮኒክሥ ሙዚቃ ቅንብር ፣ህሊናንን ኮርኩሮ በማንቃት ፣ ወደ ህይወት ውብ መንገድ ፣ ዝንጉ ሰዎችን አባኖ ንቁ የሚደርግ ምስጉን ሊቀ ጥበብ ነው ። ከ 2 ዓመት በፊት እንሆ ያለንን ነፀብራቅን መለሥ ብላችሁ ሥታዳምጡ ይህ እውነት እንደሆነ ለመመሥከር ትገደዳላችሁ ።

ሥለአገር ፣ ሥለፍቅር ፣ ሥለባህላችን ፣ ሥለማህበራዊ ኑሮ ትሥሥር እንዴትነት የሚገልፁ ፤ የሚያነቁና ወደማሥተዋል መንገድ የሚመሩ ዜማዎችን ትላንት በማዜም ኢትዮጵያዊያንን አንቅቷል። ” እውር አሞራን ማነው ያበለው…እውነት፣ እውነት ? ” ብሎ በመጠየቅ እንድናስብ አስገድዶናል ።

የረሳችሁትን ላሥታውሳችሁ ና የሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ” እሳት ወይ አበባ ” ግጥምንም በዘፈኑ ውሥጥ አካቶ በመጫወት ከፍቅርና ከእውነት ፈርሃት እንድንወጣም አስገድዶናል ። ፀገሽ ፍርሃትን ለማሸነፍ ፣ ሁሌም ተጋፋጭ ጠንካራ መንፈሥ ያለው ፣ ለእውነት ፣ ሥለ እውነት የኖረ በለቅኔ ና ከተውኔት አንፃርም ከሼክስፒር እኩል የሚታይ የትያትር ፀሐፊ ነው ። ከባለቅኔነት አንፃርም ራሱን እንደ ፑሽኪን ነበር ፀጋዬ የሚቆጥረው (በነገራችን ላይ ፣ በሀሁ ፐፑ ትያትር ውዝግብ ወቅት ፣ ሥለ ትያትሩ ግምገማ ላይ መቅረብ አውሥቶ ፀግሽ በቁጭት” ፑሽኪንን ማነው የገመገመው ? ” በማለት በአንድ መፅሔት ላይ መልሥ ሲሰጥ እንዳነበብኩ አሥታውሣለሁ ። እናም ሮፍ ናንን ከፀግሽ ግጥም ቀንጭቦ በተሸለመበት አንድ መድረክ ላይ ከሁለት ዓመት በፊት ተጫውቶት ነበር ። )

ዛሬም ሮፍ ናን ፣ ” የአገር ልጅ ሥምሽን አገኘሽ ወይ ? ሲል በመጠየቅ ፣ ሰው ነህ ፣ ሰው ነኝ ፣ ሰው ነን ፣… የሰው ልጅ ከፍጥረቱ ጀምሮ ከሰማይ የተሰጠው ሥም ” ሰው” ነው ። በማለት ፣ ማንም ለማንም የተለያየ የጎሳ ሥም በመሥጠት ሰውን ከሰውነቱ ሊያወጣው ና ሊፍቀው ከቶም አይችልም ። በማለት መልዕክቱን አሥተላልፏል ።

ሮፍናን ፣ ሰውነትን እና እኛ ኢትዮጵያዊያን የተለየ ባህላዊ ና ተፈጥሯዊ ቅርሰ እና ማንነት እንዳለን ” ሰከላ ” በተሰኘ የዘፈን ግጥሙ በማንጎራጎር ፣ በማንነታችን እንድንኮራ ከማድረጉም በላይ በፈጣሪ ከተሰጠን የተፈጥሮ ፀጋ ጋራ ያለንን ቁርኝት መለሥ ብለን በመቃኘት ወደ ቀልባችን እንድንመለሥ መክሮናል ።

ሮፍ ናን ፣ በውብ ዜማው እያዋዛ ሥለ ኢትዮጵያዊነት ና ሥለ ሰውነት ፣ ሥለፍቅርና ሥለ ሰው አፈርነት ነግሮናል ። ትውልድ በቅብብሎሽ ሲጓዝ አኩሪ ታሪኩን እንዳይዘነጋ አሳስቧል ። ኢትዮጵያዊውው የዓለም አካል ነው ። ሰው የተባለ ፍጥረት ነው ። የሰውነት እና የኢትዮጵያዊነቱን ጉዞ የጀመረውም ከ3000 ዓመት በፊት ነው ።

ኢትዮጵያ የኃይማኖትም አገር ናት ። ኃይማኖት ሰው ሁሉ እኩል እና የአዳምና የሄዋን ዘር እንደሆነ የሚሰብክ ነው ። ኃይማኖት አባቶችም አለቃ ፈጣሪ መሆኑ ይታወቃል ። ( በእኛ አገር ግን አንዳንዶች ፣ አለቃቸው ገንዘብ እንደሆነ በድርጊታቸው እያረጋገጡልን ነው ። ፈጣሪ ይቅር ይበላቸው ። ) እንደምታውቁት በተረጋገጠ ታሪክ በ34 ኛው ዓ/ም ነው ኢትዮጵያ ፣ በኢትዮጵያዊው ጀንደረባ አማካኝነት ክርሥትናንን የተቀበለችው ። ( በ325 ዓ/ም ከኒቂያ ጉባኤ በኋላ ነው የሚሉ አሉ ። አሥገዳጁን የግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ተፅዕኖ እና እሥከ1955 ድረሥ ፓትርያርክ ሆነው የሚሾሙት ግብፆች እነደነበሩም አስታውሱ ። አትዘንጉ ። በአፄ ኀይለሥላሴ ዘመን ነው ። አቡነ ባሲለስ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ ሆነው በግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቴን በዓለ ሢመታቸው የተከናወነው፡፡ በወቅቱ ግርናዊነታቸው ታድመዋል ።

የእሥልምና ኃይማኖት ወደኢትዮጵያ የገባው በአረብ አገራት እሥልምና ሳይሥፋፋ በፊት ፣ እንደሆነም ይታወቃል ። ( በነገራችን ላይ ፣ በኃይማኖቱ ብቻ ሣይሆን የአሜሪካም ሆነ የአውሮፖ መንግሥታት ሳይፈጠሩ ኢትዮጵያ በለሰፊ ግዛት አገር ነበረች ። ቀይ ባህርም የኢትይጵያ ግዛት ነበር ። ኤርትራ የሚባል ስምም የ17 ኛውመ ክ/ዘ ታሪክ ነው ። እሥከ 19 ኛው ክ/ዘ ኤርትራ የሚባል ሥያሜ አልነበረም ። ቀይ ባህር በባህረ ነጋሾች የሚመራ የኢትዮጵያ ግዛት ነበር ። የባህር ንጉሶችን የሚሾሙትም የኢትዮጵያ ነገሥታት ነበሩ ። የመጨረሻው የባህረ ነጋሽ አሥተዳዳሪ ራሥ አሉላ አባነጋ ነበሩ ።

ዛሬ ወያኔ የዘራውን ሰውነትን የሚያሥረሳ የግብዝነት ፍሬ እየበሉ ያደጉ ሰው ጠል በመሆናቸው ፣ በቋንቋ እያመካኙ እጃቸውን ታጥበው መብላቱ እንዳይቀርባቸው የፖለቲካ ነጋዴዎቹ ፣ ዛሬም የኢትዮጵያ ብልፅግና እንቅፋቶች ሆነው ተገኝተዋል ።
በዚህ ወቅት ነው ሮፍ ናን የግብዞችን ናላ የሚያዞር ፣ ብዙሃኑንን ኢትዮጵያዊ ልቡን በሃሴት የሚሞላ ፣በደስታም የሚያፍነክንክ ፣” ሠከላ ” ብሎ ታላቅ መልዕክት እንሆ ኢትዮጵያዊያን ያለን ። ታላቅነታችንን አብሳሪ ፣ የአያቶቻችንን ና ቅድማያቶቻችንን ህብረት ና ፍቅር መሥካሪ የሆነውን የዘፈን ውብ ግጥሙን እንሆ !

ሠከላ
ሠከላ አባይን ወለደ
እናቴም እኔን !
ኢትዮጵያኖች እንደምንአላችሁ
የአንዲት እናት ልጆች በአድ የሌላችሁ
እሯ እላለሁ
እሯ በልዬ
የዛ ጀግና ልጅ
የዛ ሰውዬ ።
እሯ በል አንተ
እሯ በልዬ
የዛ ጀግና ልጅ
የዛ ሰውዬ
ግባልኝ !
ይህ ይድረሰው ለዛ ሰው
ወራሪውን ለመለሰው
የነፃነት ተምሳሌት አድርጎ
ሥሜን ክብር ላወረሰው
ያደረክልኝ ብዙ ነው ከፍዬም አልጨርሰው
ያረክልኝ ሁሌም አዲስ ነው
በሄድኩበት የምለብሰው ።
ብጠራው ሥምህን ዓመት መች ይበቃል
በዓለም ያለ ጥቁር ፣ ከትውልድ ትውልድ አንተን ያመሰግናል
እሯ በል አንተ
ምንም እንኳን ከአንተ ባያምርብኝ
ዛሬ ላይ የምፅፈው ፣ የእኔ የሚሆን ታሪክ ፣ ጭለማ ቢመሥልብኝም
ተሥፋ አለመቁረጥ ከአንተ ተምሬለሁ ፣ አደራህም አለብኝ !
እሯ ልበል እንደአንተ ምንም እንኳን ከአንተ ባያምርብኝ !
ሠከላ አባይን ወለደች
እናቴም እኔን ።
ቅድሚያ ሰው ! ደግመው ግን ማነህ ቢሉኝ ?
ኢትዮጵያ ነው ሥሜ ።
አልወድቅም ለመድረሥ ፣ እጄ ቢያጥርም
……..ከበላይ ባልዘልቅም ።
ባይመሥልም ፣ አንዴ አያቅተኝም
እንደ ቴዎድሮስ ባልደግምም ።
አዝማች ……..
እሯ በል !
እሯ በልልኝ !
የዚያ ጀግና ልጅ …
ግባልኝ !
አሀሀይ ጉማ !
ጦቢያው ለይቅርታ ቅደም
ቀድመህ እንድትተው ድገም ።
ድገም ቢያሥቀድምህ መልሥ
የአባትክን አደራ መልሥ
ያኔ በላይ ይዘልቃል
ያንጊዜም ቴዎድሮስ ይደገማል
ያንጊዜም አሉላ ራሥ ነው
ምኒልክ ዛሬም ንጉሥ ነው ።
በልልኝ አንተ ሰው
በልልኝ አንተው
ራሥህ ላይ
ይቀርባል አንተ ሰው ።
እሯ በልበት ጥላቻ ላይ
የአደዋ ዘማቹ የልጅ ልጅ ።
እኔ እና አንተ አይደለን
ሮፍ ናንን ዘእምነገደ ጦቢያው
የአንተም እንድያ አይደለም
ሠከላ አባይን ወለደች
አባቴም እኔን ።
ቅዲሚያ ሰው ደግመው ግን ማነህ ሲሉኝ
ኢትዮጵያ ነው ሥሜ !
ከቶ አልቀርም ለመድረሥ ፣ እግሬ ቢያጥርም
አብዲሳን ባልቀድምም ።
ሲይጨልም ሳይመሽ
ለይቅርታ ላዝግም ።
ጣይቱን አልሰጥም ።
እሯ እላለሁ
የልብ አድርሥ
የዛ ጀግና ልጅ
የዮሐንስ !
እሯ በል አንተ
እሯ በልልኝ
የጃጋማ ልጅ
ግባልኝ !
………አዝማች
ሁሉም ትውልድ አደዋ አለው
የእኔም አድዋ ልቤ ላይ ነው ።
ቢገኝ ፍቅር ማሳያ
በይቅር ልቆ መገኛ ።
ያንጊዜ አብዲሳ ይደርሳል
በልቤም ባልቻ ይነፍሳል
ዮሐንስ ደሙ ወርቅ ነው
ላልከዳው ጴጥሮሥ መልሥ ነው ።
ጠበቁኝ በደም እርሰው
የጥፋት ጉድጓድን ምሰው
በሰባራቸው አፍሰው ።
ሰባራ ሰንደቅን ይዘው ።
እንግዲህማ እኔ ልሻል
መርዙን በይቅርታ ልሻር ።
ከአባቶቼም በይሆንልኝ
ከአያቶቼ አንድነትን ልማር ።
እሯ ልበል የዛሬ ሰው
ፍቅር ፈሰሰብኝ ልፈሰው ።
ልንተባተብ ጀግንነቱን
ከልቤ ላግኝ ምህረቱን ።
አሹ !

 

2 Comments

  1. ዋው! ሰሚ ቢገኝ ጥሩ ምክር ነው። ዘመኑ በዳይ ተበዳይ ነኝ የሚልበት ጊዜ ሆነና ነው እንጂ ይቅር ማለት ተገቢ ነበር። ጠ/ሚ አቢይ ወያኔን ይቅር ቢላቸውም እነሱ ግን በእኛ ይባስ ብለው አሁን ያለንበት መቀመቅ ውስጥ ከተቱን። እንግዲህ የዚህ አይነቱን ጉዳይ በዚያው በተለመደው አረመኒያዊ ትንቅንቅ መፍታት ነው ሌላ ምን አማራጭ አለ?

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.