የአብዛኛዎቹ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ፍፁም ፀረ-ዴሞክራሲያዊ የሆነ ዝንባሌ… – መሰረት ተስፉ

መሰረት ተስፉ (Meserettesfu4@gmail.com)

በየትኛውም አገር ውስጥ  ካለው ስርዓት ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ግንኙነት ያላቸው ፖለቲከኞች አገር እየመራ ያለው እነሱ የወጡበት ብሄር፣ ብሄረሰብ፣ ነገድ ወይም ጎሳ ነው ሲሉ አይደመጡም። ለምሳሌ ባራክ ኦባማ “በዘሩ” ጥቁር አሜሪካዊ ቢሆንም እሱም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ አጋሮቹ አንድም ቀን አሜሪካን እየመሯት ያሉት ጥቁር አሜሪካውያን ናቸው ሲሉ ተሰምተው አያውቁም። ኦባማ በግሉም በፕሬዚደንትነት የተመረጥኩት የዴሞክራቲክ ፓርቲ ፖሊሲዎችን አስፈፅማለሁ ስላልኩ  እንጅ ጥቁር አሜሪካዊ  ስለሆንኩ ነው ብሎ የሚያስብ አይመስለኝም።

የብሪታኒያ መሪዎችም  ሃገር እየመራ ያለው  ህዝብ የመረጠው ፓርቲ እንጅ ስኮትላንድ፣ ዌልስ፣ ሰሜን አየርላንድ ወይም ኢንግላንድ  የሚባል ብሄር (አገር) ነው አይሉም።  በእርግጥ ጠቅላይ ሚ/ሩ ከአራቱ ውስጥ የአንደኛው ብሄር (አገር) አባል ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ጎርደን ብራውን እና ቶኒ ብሌየር ስኮታላንዳዊያን ናቸው። ነገር ግን እነሱ ጠቅላይ ሚ/ር በነበሩበት ጊዜ ብሪታኒያን እየመራ ያለው ስኮትላንድ የሚባል ብሄር (አገር) ነው ያሉበት ጊዜ አልነበረም። አሁን ደግሞ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚ/ር እንግሊዛዊ ነው። ይሁን እንጅ የእንግሊዝ ፖለቲከኞች ብሪታኒያን እየመራት ያለው ወግ አጥባቂው ፓርቲ እንጅ እኛ እንግሊዛውያን ነን ያሉበትን አጋጣሚ  አላስታውስም።

በሌሎች ሃገሮችም ቢሆን ሁኔታው ከዚህ የተለየ ነው ብየ አላምንም። ለምሳሌ ኬኒያን ብንወስድ አሁን ሃላፊነት ላይ ያለው ፕሬዚደንት ማንነቱ/ብሄሩ ኪኩዩ ቢሆንም ኬኒያን እየመራት ያለው ፓርቲው (The National Alliance Party) እንጅ የኪኩዩ ብሄር ነው ሲል የተሰማበት ጊዜ የለም። ሩዋንዳንም ብንመለከት ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ የቱትሲ ማንነት ቢኖረውም ሃገር እያስተዳደረ ያለው ግን እሱ በሊቀመንበርነት የሚመራው Rwandan Patriotic Front እንጅ የቱትሲ ብሄር ነው ብሎ አያውቅም።

ወደሃገራችን ተመልሰን ከጥንት ጀምሮ  በተለያዩ ጊዚያት ሃላፊነት ላይ የነበሩትን መንግስታት ስንመለከትም ከፍ ብለን ካየነው የአለም አቀፍ ልምድ የተለየ ነበር ማለት አይቻልም። ለምሳሌ ኢትዮጵያ በንጉሶች ስትመራ በነበረችበት ወቅት ንጉሶቹ “ስዩመ-እግዚያብሄር ነን” ይላሉ እንጅ የሃገሪቱ መሪ እነሱ የወጡበት ብሄር ወይም ብሄረሰብ ነው ይሉ ነበር የሚል ታሪክ አልተመዘገበም። ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የለውጡ ተግዳሮቶች በኔ ዕይታ - ይነጋል በላቸው (ከአዲስ አበባ)

በደርግ ጊዜ ሃገር ይመሩ የነበሩ ፖለቲከኞችም ቢሆኑ ኢትዮጵያን የሚያስተዳድረው ወታደራዊ ደርግ በኋላ ደግሞ  ኢሰፓ ነው ከማለት ውጭ ፕሬዚደንት መንግስቱ ወይም ጓደኞቹ የወጡበት ብሄር ነው ብለው የተናገሩበት አጋጣሚ አልነበረም።

በኢህአዴግ አገዛዝ ዘመንም ምንም እንኳ ህወሃቶችና አጫፋሪዎቻቸው ሁሉም በእጃቸው ሁሉም በደጃቸው የነበረ ቢሆንም ሃገር እየተመራ ያለው በኢህአዴግ እንጅ  በትግራይ ብሄር ነው ሲሉ ተደምጠው አያውቁም። አቶ ሃይለማሪያም ጠቅላይ ሚ/ር ሆኖ ባገለገለበት ጊዜም የነበረው ሁኔታ ተመሳሳይ ነው።

አሁን ላይ ግን ምቾት የማይሰጡ ዝንባሌዎች መኖራቸውን እየታዘብን ነው። በአንድ በኩል  ሃገር እያስተዳደረ ያለው ዶ/ር አብይ በፕሬዚደንትነት የሚመራው ብልፅግና ፓርቲ ነው ሲባል እንሰማለን። ብልፅግና ደግሞ ፓርቲነቱ የአንድ ብሄር ሳይሆን የሁሉም ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንደሆነ ነው የሚገለፀው።

በሌላ በኩል ግን የኦሮሞ ፖለቲከኞች ኢትዮጵያን እየመራ ያለው የኦሮሞ ብሄር ተደርጎ እንዲቆጠር የመፈለግ ዝንባሌ  እንዳላቸው የሚያሳዩ ምልክቶች እዚህም እዚያም ይታያሉ። በዚህ ረገድ በምን ስሌት እንደሆነ ለመረዳት ቢያስቸግርም ጃዋር ቄሮን የኢትዮጵያ መንግስት አድርጎ የሰየመበትን ሁኔታ ሁላችንም አድምጠናል ብየ እገምታለሁ። አቶ ለማ መገርሳ በበኩሉ በተለያየ ጊዜ እየተነሳ (የኦሮሞ ብሄር አገር እየመራ ያለ ይመስል) “ኦሮሞ አገር መምራት አይችልም ተባልን” እያለ ሲናገር እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። ዶ/ር አብይም በተመሳሳይ መንገድ ሃገሪቱን ኦሮሞ እየመራ እንደሆነ ለማሳየት የሄደባቸው ተግባራዊና ፅንሰሃሳባዊ ርቀቶች እንዳሉ ታዝበናል። ይህን ለመረዳት ደግሞ በአንድ ወቅት “መንግስታችን ተነካ በሚል ስሜት የቡራዩና የሰበታ ህዝብ ግልብጥ ብሎ ሊመጣ ነበር” ያለውን ማገናዘብ ብቻ በቂ ነው ብየ አስባለሁ።

ሌላው ቀርቶ የፖለቲካ “ሀሁ”ን በተሻለ ሁኔታ ይገነዘባሉ የሚባሉት አቶ ሌንጮ ለታ እንኳ “ባሁኑ ወቅት ሃገር እየመራን ያለነው እኛ ኦሮሞዎች እንደሆንን “ባእዳን” እንኳ ተቀብለውታል…” ብለው የተናገሩት የዚሁ የኦሮሞ ፖለቲከኞች “ሀገር እየመራ ያለው ኦሮሞ ነው” እንዲባል የመፈለግ ዝንባሌ አንድ መገለጫ ተደርጎ ቢወሰድ ስህተት አይሆንም። አቶ ሽመልስን ጨምሮ ሌሎች የኦሮሞ ፖለቲከኞች በየፌዴራል መንግስቱ መድረኮች ሁሉ  እንታይ እንታይ የሚሉትም ቢሆን ከተመሳሳይ  ፍላጎት ተነስተው እንደሆነ ለመረዳት አይከብድም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የመሬት ወረራን በመቃወሜ የተፈፀመብኝ በደል - አበበ ሆንጃ (ከሰበታ)

የኦሮሞ ህዝብ  ይህን  ዝንባሌ የፈልገዋል ወይ?

በፍፁም አይፈልገውም ብሎ ደፍሮ መናገር ይቻላል። አንድ ህዝብ እንደህዝብ ፍላጎቱ ከሌሎች ወንድምና እህትቹ ጋር በጋራ ተሳስሮ አገር ማስቀጠል እንጅ በሌላው ላይ የበላይ ሆኖ ማስተዳደር የሚሆንበት አጋጣሚ እንደነበር የሚያሳይ ታሪክ አልተፃፈም። የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄም እንደሌሎቹ ብሄር ብሄረሰቦች የፍትህ፣ የመልካም አስተዳደር፣ የእኩልነት፣ የእኩል ተጠቃሚነት፣ የማደግ፣ የመበልፀግና ሃገር የመገንባት እንጅ በሌላው ላይ ፍላጎቱን የመጫን ይሆናል ብየ አላስብም። ስለዚህ “አገር እየመራ ያለው ኦሮሞ ነው” እንዲባል የመፈለግ ዝንባሌ ያላቸው ፖለቲከኞቹ እንጅ  ህዝቡ እንደማይሆን እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል።

ታዲያ የኦሮሞ ፖለቲከኞች አገር እየመራ ያለው ኦሮሞ ነው እንዲባል የመፈለግ ዝንባሌ ለምን ይታይባቸዋል?

የኦሮሞ ፖለቲከኞች ይህን ዝንባሌ የሚያሳዩት ከተለያዩ ምክንያቶች ተነስተው ሊሆን ይችላል የሚል እምነት አለኝ። አንደኛው በተሳሳተ ስሌት የኦሮሞን ህዝብ ድጋፍ ያስገኝልናል ብለው አስበው ሊሆን ይችላል። ከዚህ ጋር የተያያዘውና ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በኦሮሞ ህዝብ ስም በመነገድ  ድጋፍ እንዳላቸው ለሌሎች የማሳየት ፍላግት ገፍቷቸውም ይሆናል። በፈጠራ ትርክት ተነሳስተው አማራ እንደህዝብ ጨቁኖናል የሚል ቅሬታ ስላደረባቸው በዚህ ምክንያት የተፈጠረባቸውን የዝቅተኝነት ስሜት ለማካካስ ሲሉ የተረኝነት ስሜት አድሮባቸውም እንዳይሆንም ከፍተኛ ስጋት አለኝ።

ይህን አይነት ዝንባሌ ከነሱ አልፈው ሌላው ውስጥ በስፋት ማስረፅ ከቻሉ ደግሞ ልክ የትኛውም ገዥ ፓርቲ ሊያደርገው እንደሚችለው ሁሉ እነሱም በሁሉም ጉዳዮች ላይ አዛዥ ናዛዥ እንሆናለን፤ በተለይም ደግሞ፡

  1. ሁልጊዜም ጠቅላይ ሚ/ሩ ከነሱ ውስጥ አንዱ ወይም እነሱ የፈቀዱለት ብቻ እንዲሆን ለማድረግ፤
  2. የፈለጉትን ሰው በሚንስትርነት ለመሾም፣ ካቢኔውንም እንደፈለጉ ለመጠምዘዝ፤
  3. መከላከያና ፖሊስን ጨምሮ የሁሉንም ዋና ዋና ተቋማት ሃላፊዎች ሹመትና ምደባ በነሱ መልካም ፈቃድ ለማስኬድ፤
  4. ሃገር አቀፍ ፖሊሲዎችን፣ አዋጆችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን፣ እነሱ በፈለጉት መንገድ ለማርቀቅና ለመተግበር፤
  5. በጀት ድልድሎችና የመሳሰሉ መሰረታዊ ጉዳዮች ባሻቸው መንገድ ለማርቀቅና ለማስፀደቅ፤
  6. የተቋማት ሃላፊዎችን በፈለጉት ጊዜ ለማንሳት ወይም ለመተካት፤
  7. የአዲስ አበባንና ሌሎች መሰረታዊ ጉዳዮችን ህጋዊ መልክ በማስያዝ ለማስወሰን፤
  8. የሃገሪቱን አጠቃላይ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ለመቆጣጠር የሚያግደን አይኖርም የሚል እምነት ሳይድርባቸው አልቀረም ባይ ነኝ።
ተጨማሪ ያንብቡ:  "ማኅበረ ቅዱሳን አክራሪ ሆኖ የገደለው ሰው የለም' - ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ምላሽ ሰጠ

ፖለቲከኞቹ ይህን ዝንባሌ ማስፋፋትና ማስቀጠል ይችላሉ ወይ? ጥቅሙስ ምንድን ነው?

ዝንባሌውን ማስፋት ይቻል ይሆናል ቢባል እንኳ ለጊዜው ካልሆነ በስተቀር በቋሚነት ማስቀጠል ይቻላል ብየ አላምንም። ምክንያቱም ህወሓቶች እንደ ኦሮሞ ፖለቲከኞች ፍላጎታቸውን በአደባባይ ባይገልፁም እንኳ በተገባር ግን ሞክረውት እንዳልተሳካላቸውና የኋላ ኋላም የኢትዮጵያ ህዝብ ተንኮላቸውን በሚገባ በተረዳ ጊዜ አሽቀንጥሮ እንደጣላቸው ይታወቃል ። ከጥቅም አንፃር ከታየም የዚህ አይነት ዝንባሌ  አለመተማመንን እና መፈራቀቅን ማስፋት እንጅ ሌላ የሚፈይደው ነገር ይኖራል ብየ አላስብም።

ታዲያ መፍትሄው ምንድን ነው?

መፍትሄውማ የአንዱ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ብሄሮችና ብሄረሰቦች የፖለቲካ ስልጣን ባለቤትነት የተከበረበት፣ ሁሉንም በእኩልነት የሚያይ፣ ማንኛውንም ዜጋ  ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ሊጠቅም የሚችል፣ የህግ የበላይነት የሰፈነበት፣ ቅንነትና ግልፅነት የተሞላበት፣ ተጠያቂነት ያለው በአጠቃላይም የሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች ነፀብራቅ የሆነ  ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ ያለው መንገድ ለጊዜው የሚሳካ መስሎ ቢታይም እንኳ ዞሮ ዞሮ ሃገር አፍራሽ እንደሆነ መረዳት እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው ብየ አምናለሁ።

ቸር እንሰንብት!!!

 

3 Comments

  1. የትግራይ ፖለቲከኞችን እየመለመለ ወያኔን አደራጅቶ እና አሰልጥኖ ኢትዮጵያውያንን ሊያስጠፋ የላከው ሻዕቢያ ፤ አሁን ደግሞ የኦሮሞ ፖለቲከኞችን ለተመሳሳይ አላማ እየላካቸው ይገኛል።

  2. አሁን ያሉት ልታይ ልታይ የሚሉ የኦሮመሞ ፓለቲከኞች ወያነ ጠፍጥፎ በእምሳሉ የፈጠራቸው፣ቀደም ያሉትም ዛሬ አምላክ ምስጋን ይግባውእና በኤጂፐት እና በኢትዬጵያ ጠላቶች አውቀውም ይሁን ሳያውቁት ለመፈጠራቸው ፤ስራቸውም ከጠላቶቻችን ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ ፀሀይ የሞውቀው ጉድ ከሆነ ሰነባበቶአል።
    ከነኝህ የበለፅገች፤ዲሞክራሲያዊ፣ እና ለሁሉም እኩል የሆነች ሀገርን ማሰብ ከእባብ እንቁላል እርግብ መጠበቅ ኘዉ።
    ኢተዮጵያን ያለ ሁሉ በነሱ በዘር የጨዋታ ህግ ሳይቡአደን አንድ ሆኖ በመነሳት በቁርጠኝነት ሊፋለማቸው ይገባል።ትናንት ባዩት የወያኔ ውድቀት እንኩዋን ሊማሩ ያልቻሉ ፈጡሮች ናቸው።
    የጥላቻ እና ዘር ፖለቲካቸዉ የእድገቱ መጨረሻ አብሮ አቸው የኖረውን ንፁሀን ተወዳዳራ በሌለው ጨካኔ፣ ፍፁም barbaric በሆነ መንገድ ህፃን አሮጊት ሳይለይ በገጀራ መተልትል ነው።
    ሰባት ትውልዳቸው በታሪኩ እንዲያፍር ፈርደውበታል።ለራሱ ክብርየሌለው ድሮስ ለሌላው ምን ያስባል ??

  3. በኢትዮጵያዊነት፤ በዲሞክራሲ፤ በሕግ የበላይነት፤ በእኩልነት፤ ወዘተ ጽንሰ ሀሳብ የትመሠረተ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ የሚደገፍ በመሆኑ ለጦማሩ ደራሲ ምሥጋናዬን በትሕትና አቀርባለሁ፡፡

    ነገር ግን፤ “ብሔሮች፤ ብሄረሰቦች” በተሰኙት ጽንፈኛና ዘረኛ በሆኑ ቃላት መጠቀም እጅግ በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አንድ ሐገር (ብሔር) ናት!

    ስለዚህ፤ መሠረታዊ የሆኑ ተግዳሮትን ለማስወገድ፤ ዘረኛነትንና ክልልን የሚያስወግድ ሕገ መንግሥት፤ ዲሞክራሲ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከድህነት አረንቋ የሚያላቅቅ ሥልታዊ የሆነ የተሟላ የልማት እቅድና መርሐ ግብር፤ የሕግ የበላይነት፤ ወዘተ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

    ቸሩ የኢትዮጵያ አምላክ ያበርታን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share