በቅድሚያ የበይነመረብ እና ማህበራዊ ትስስሮች ኮሚዩኒኬሽን ስነምግባር በተመለከተ አስተያየቴን እንድሰጥ በመጠየቁ አመሰግናለሁ። ርዕሰ ጉዳዩ ሰፊ ስለሆነ በአጭሩ ለመግለጽ ከባድ ቢሆንም እንደሚከተለው አስተያየቴን አቀርባለሁ። ይህ አስተያየት ከማንኛቸውም ፖለቲካዊ እና ሃይማኖታዊ አስተያየት ገለልተኛ የሆነ ሙያዊ መሆኑን እገልጻለሁ። በአጋጣሚ አብረን ትምህርት ከጀመርነው ከዶ/ር ሃምዛ መሃመድ ጋር በዚህ ጉዳይ በሰፊው ስንነጋግር ነበር። የሳይበር ቴክኖሎጂ ደህነንት ባለሙያ እና ብዙ ኩባንያዎችን የሚያማክር ነው። ጊዜ ኑሮት የእሱን ልምድ መካፈል ቢቻል ጥሩ ነው። በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ በምሰራበት መስሪያ ቤት በየአመቱ አንድ ጊዜ የሳይበር ደህንነት (Cybersecurity Training) ስልጠና መውሰድ እና ፈተናውን ማለፍ ግዴታ ነው።
- በዘመነ ዲጄታል ሰው ከማህበራዊ ኢንጅነሪንግ (social engineering) ተነስቶ ዛሬ ምሁራዊ የዲጅታል ሀብትን በመጠቀም የሰው ልጅ የተሸለ እንዲኖር ማህራዊ ተጽእኖ የሚፍጠር የማህበራዊ ቴክኖሎጂ (social technology) ላይ ደርሷል። ይህ ዲጄታላዊ የመቀየር ሥርዓት ጥሩ ነገርን እንዳመጣ ሁሉ ጎጂ ሁኔታም ተከስቷል። ለምሳሌ የማንነት ስርቆት፣ መረጃዎችን መጥለፍ፣ ማጭበርበር፣ ሞቢንግ፣ ማስፈራራት፣ የሀሰት ዜና፣ ስም ማጥፋት፣ ማጋጨት… ወዘተ. የመሳሰሉት በኋላ የተፈጠሩ ናቸው። “የአንድ ሰው መብት የሚቆመው የሌላኛው ሰው መብት ላይ ሲድርስ ነው” የሚባለው አዚህ ላይ አይሰራላቸውም። በዘመነ ዲጄታል በመጀመሪያ ደረጃ የሚሸጠው ስሜትን እንጂ ሸቀጥን አይደለም። አእምሮአችን በቀን ወደ 20ሺ ውሳኔዎችን ሲወስን አብዛኛው በደመ-ነፍስ የሚወሰን ነው። ከምንሰበሰባቸው መረጃዎች አብዛኛው በ15 ሰከንድ ተመልሶ የሚወጣ ሲሆን የተደጋገሙት ይቀራሉ። አንድ ሰው ሳያቋርጥ ቢስቅ ሌሎች መሳቅና ቢያንስ ፈገግ ማለት ይጀምራሉ። አንድ ሰው ሳያቋርጥ ምስጢር እያለ ቢያወራ ምስጢር ወይም ኢትዮጵያ እንደተለመደው “ሰበር” ነው ብለው ይቀበሉታል። ይህም በደመ-ነፍስ የሚከሰት አዕምሯዊ ኩረጃ ነው። ለመጥፎም ድርጊት እንደዚሁ። የመሸብለል ሳይኮሎጂ (manipulation psychology) እንደሚያሳየን ለምሳሌ በቀላሉ ፍራቻን በመፍጠር እና የወደፊት በሚከሰተው ላይ ጥርጣሬ እንዲፈጠር በማድረግም ሁለት ነገሮችን በማወዳደር ቁጭትን በመፍጠር ሰውን ማሸብለል እና ለጥሩም ሆነ ለመጥፎ ማነሳሳት ይቻላል። የሶሎሞን አሽ በ1951 በሰራው የተኳሀኝነት ምርመራ (conformity experiment) አንድ ቡድን የሚፈጥረውን ደመነፍሳዊ የማሰገድድ አንደምታን በተመለከተ ነው። አንድን ሐሰት አብዛኛው ሰው ስለተከተለው ብቻ እውነት ነው ብሎ መቀበልን ነው።
- ሰው በቀላሉ የሚሸበለለው ገንዘብ ሲሰጠው ወይም በነፃ ይገኛል ሲባል፣ ስልጣን ይሰጠሃል ሲባል፣ የተመኘውን መልካም ዜና አለ ሲባል ወይም በወሲብ ፍላጎቱ በማታለል ነው። ይህንን ማሸብለል በዴጄታል በብዙ መንገድ እና በስኬት ይጠቀሙበታል። በቅርቡ ጀርመን እያተደረገ ያለው ወንጀል ከህንድ ካለ የተደራጀ የሳይበር ማፍያ በየቤቱ በመደወል ከማይክሮሶፍት የተላኩ መሆኑን በመግለጽ ኮምፒውተሩ በቫይርስ ሊጠቃ እንደሚችል በመግለጽ ማዘመን (update) እንዳለበት በመናገርና በሪሞት እንዲሆን በመጠየቅ፣ ከዚያም ኮምፒውተሩ ውስጥ በመግባት የግል መረጃዎችን በመስረቅና ጠላፊ ሶፍትዌሮችን በመጫን ነው። በእንደዚህ አይነቱ በተለይም በእድሜ የገፉ ሰዎች ይታለላሉ።
- Online etiquette or “netiquette” የበይነመረብ ስነምግባር በመባል የሚታወቀው በአጠቃላይ የሚመክረን ሰው አክባሪ መሆንን፣ አስተያየቶቻችን እንዴት ሊነበቡ፣ ሊገነዘቡ ወይም ሊተረጎሙ እንድሚችሉ መረዳት (ለምሳሌ እኔ ስለኮሮና ልምድ ከጀርመን ስጽፍ ከመልቀቄ በፊት በሌላ ሰው አስነብቤ እና አስተያየት ጠይቄ ነው)፣ በቀልድ እና በስላቅ፣ ማሾፍም ካስፈለገ በጣም መጠንቀቅ፣ የሚጻፈውን የሚጋሩት ማን እንደሆኑ እና እነሱም መልሰው ለማን እንደሚያጋሩት መገመት፣ በአንድ ቡድን ውስጥ ወይም የማህበራዊ ትስስር የጓደኛ ጥያቄዎችን እና የቡድን ጥሪዎችን ከመቀበላቸው በፊት መፈተሽ፣ “ይህንን ለተወሰነ ቁጥር አስተላልፍ” የሚል Hoax መልእክቶችን አለማስተላለፍ፣ የስነምግባር ደንቦችን መጠየቅ፣ ስህተትን ማውቅ እና ከተደረገም ይቅርታ መጠየቅ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ።
- የኢንተርኔት ስነ- ምግባርን መጣስና ወደወንጀል ለመተላለፍ ቀዩ መስመር በጣም የሳሳ ነው። ይህንንም ብዙ ሰው በደመ-ነፍስ ሲፈጽመው ይታያል። ብዙ ሰዎች ያለፈቃድ አንድን ሙዚቃ በመገልበጥ፣ አንድን ሶፍትዌር፣ ሙዚቃ፣ ፊልምን ፍቃድ ከሌለው ሰው ገዝቶ በመጫንና የህሊና ንብረት ስርቆት በመፈፀም ከዚህ ይጀምራሉ። ስለሰዎች በመናገር፣ በስሜት አስተያየት በመስጠት ወይም ይህንን በመጋራት ወዘተ ሳይታወቅ ህግ እና ደንቦችን ይጣሳሉ። የጀርመን የኔትወርክ ኢንፎርሰመንት ህግ በዘለምዶ የፌስ ቡክ ህግ (NetzDG) የሚባለው በማህበራዊ ሜዲያ (ዩቲዩብ፣ ቲውተር፣ ፌስቡክ) ላይ የሚቀርቡትን የጥላቻ ንግግሮችን፣ የሀሰት ዜናዎችን እና የሳይበር ወንጀሎችን የሚቆጣጠር ሲሆን፣ ወንጀሉን ፈጻሚው ግለሰብ ወይም ቡድን ብቻ ሳይሆን አቅራቢውንም የሚጠይቅ ነው። በዚህም የሚዲያ ፕላት ፎርሞች በየሶስት ወሩ መረጃ እንዲያቀርቡ ይጠበቅባቸዋል።
- ለምሳሌ በኢንተርኔት ላይ ወይም በማህበራዊ ትስስር መድረኮች የአንድ ሰው ስም ከተጠቀሰ ይህ የሰውን የስም መብት እና ክብርን መጎዳት ሊሆን ይችላል የተጠቀሰው ነገር እንኳን እውነት ቢሆን። በጀርመን ወንጀል ህግ እንደ ስድብ (§ 185 StGB)፣ ስም ማጥፋት (§ 186 StGB) ከሚታዩበት በተጨማሪም ግለሰባዊ መርጃን ያለግለሰቡ ፈቃድ መግለጽ የሳይበር ህግ እና የዳታ መከላከል ህግ (Datenschutz-Grundverordnung: DSGVO) ሊያስጠይቅም ይችላል። ሌላው ነገር ግን በበይነመረብ መድረኮች ወይም በሌሎች በኢንተርኔት መድረኮች ላይ የሰዎች ስም ሳይጠቀስም እንዲሁ የስም ወይም የግል መብትን በመጣስ ሊያስቀጣ ይችላል። ይህ ድብቅ ስም ማጥፋት የሚባለው ነው። ይህ የሚሆነው የሰው ክብርን የሚያወርድ ወይም የሰውየውን ጥፋተኛነትን በሚገልጹ መልኩ ሆኖ ግን አንባቢዎቹ ያለስም የተጠቀሰውን ሰው ማን እንደሆነ መመደብ የሚያስችሉ የተደበቁ መግለጫዎች ጋር ሲቀርብ ነው። ለምሳሌ የሚያገናኙ ቦታዎችን፣ ድርጊቶችን፣ ማንነቶችን፣ አመልካክቶችን ከዚህ በፊት ከተፍጠሩ ኩነቶች ጋር አንባቢ አገናዝቦ ስለማን እንደሆነ እንዲረዳ ሆኖ ሲቀርብ ነው።
- በሶሻል ሚዲያዎች ውስጥ ገብተን ስንወጣ ዱካችንን ጥለን ነው የምንወጣው። ለምሳሌ የጻፍነውን እንኳን ብንሰርዘው ይህ ከአቅራቢው ሰርቨር ላይ እንደተከማቸ ይቀራል። በዳታ ማይኒንግ እና ሌሎች የዲጂታል ዳሰሳ ቴክኖሎጂዎች እኛን በይበልጥ ለማውቅ ይረዳቸዋል። እንደነ ኢመዞን፣ ኢቤይ የመሳሰሉት ኩባንያዎች እንኳን አሁን ያዘዝነውን ቀርቶ ለወደፊቱም የምናዘውንም አስቀድሞ የማወቅ ብቃት ላይ እየደርሱ ማንነታችን ፕሮፋይል በማድረግ በአጠቃላይ እንቅስቃሴያችን በጥቂት ሰአታት ማስቀመጥ የሚችሉበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው።
- የፌስቡክ እና ትዊተር አካውንቶችን ለመክፈት መስፈርቱ እውነትኛ ስም/ እውነትኛ ማንነት/የትውልድ ቀን በመስጠት እና ውሎች እና ፖሊሲዎችን (termns and policies) በማረጋገጥ የሚከፈት ሲሆን ከዚህ የሚጻረር የተሳሳተ መርጃ መስጠት በእነዚህ ሶሻል ሚዲያዎች መጠቀምን ያሳግዳል። አብዛኛው የጥላቻ ንግግር እና የሃሰት ዜና የሚያስተላለፉት ሰዎች የቅጽል ስም ወይም የፈጠራ ስም በመጠቀም ነው። ይህም የፌስቡክ እና ትዊተርን የመጠቀም ደንብ የሚጻረር ሲሆን የሚያሳግድም ነው። ቢሆንም የIP አድራሻችውን፣ የኮምፒውተር ወይም የስማራትፎን መርጃቸውን ሳያውቁት አስመዝግበው ስለሚገቡ ለማግኝት ብዙም አያዳግትም።
- በአብዛኛው ለአገራችን በማሰብም ወይም በመቆጨትም ሊሆን ይችላል በስሜት የምንጽፋቸው ጽሁፎችን ከማጋራታችን በፊት ለቅርብ ገለልተኛ ጓደኛ ልኮ ማማከር፣ ወደ ቡድን የሚላክ የድምጽ መልእክት ካለም በተቻለ መጠን ማሳጠር፣ ነገሮችን እና ሰዎችን ነጣጥሎ ማየት፣ የተላለፉ መርጃዎችን “ነው” ከማለት ይልቅ “እንደደረሰኝ”፣ “እንደሚታየው“ ብሎ መግለጽ ይመረጣል።
መልካም ማሰብ እና ማበረታታት ወሳኝ ውጤት አለው።
በአጭሩ ለዛሬው ይህንን ይመስላል።
ከሰላምታ ጋር
ፀጋዬ ደግነህ ጉግሳ (ዶ/ር)