ኢትዮጵያን ከዉድቀት ለማንሳት – ዶ/ር በቀለ ገሠሠ

ኢትዮጵያ ዛሬ አጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ የሚክድ ሰዉ ይኖራል ብዬ አልገምትም። እንደዚህ ወድቃ አታዉቅም። በፓሊቲካዉም፤ በኢኮኖሚዉም፤ በማህበረሰብዓዊዉም ሆነ በዲፕሎማሲዉ ዘርፎች በሙሉ በከባድ ኪሣራ ዉስጥ ትገኛለች። እኔ በጣም አሞኛል፤ እንቅልፍ አሳጥቶኛል። ያን ሁሉ ትምህርት የተማርነዉና የታገልነዉ እኮ ሰላምና ዕድገት ለማስፈን ነበር። በአንፃሩ ግን በተለይ ዛሬ በ21ኛዉ ክፍለ ዘመን ውስጥ እያለን ሁኔታዎቹ ወደ ድንጋይ ዳቦ ዘመን ሲመለሱ ሳይ እጅግ በጣም ይከፋኛል። ብሶቴንም የምትጋሩ ብዙ ወገኖች እንደምትኖሩ አልጠራጠርም። አሁንም ሁኔታዎቹ ከመባባሳቸዉ በፊት ምክንያቶቹን ማወቅ፤ ማመንና ቶሎ ማስተካከል የግድ ይላል። ጉዳዩ የሚመለከተዉ ወገን ሁሉ እንዲያስብበት አደራ እላለሁ።

1ኛ/        የዘር ማጥፋት አረመኔያዊ ድርጊቶች ቶሎ መቆም ይኖርባቸዋል

በፊተኛዉ ወታደራዊ አምባገነን ዘመናት ህዝቡ የቀይ ሽብር ሰለባ ሆነ፤ ዓለም ጉድ አለ። ከዚያ የባሰ አይመጣም የሚል ግምት ነበረ። ዳሩ ግን ባለፉት 30 ዓመታት በኢትዮጵያ ምድር ታይተዉ ተሰምተዉ የማይታወቁ የዘር ማጥፋት ድርጊቶችና ወንጀሎች ተፈጽመዋል። ዛሬም እየባሰበት ይገኛል። በዋናነት በአማራዉ ህዝብና በኦርቶዶክስ ኃይማኖት ተከታዮች ላይ ያነጣጠረ ነዉ። የቁጥር ጉዳይ ለመጥቀስ ያህል እንጂ በጋምቤላ፤ በወላይታ፤ በጉራጌ፤ ወዘተ ህዝብም ላይ አሰቃቂ ጉዳቶች ደርሰዋል። ለምን? የኢትዮጵያን ህዝብ ከፋፍለዉ ለመግዛት ያመቻቸዉ ዘንድ ሸአቢያና የትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ) የረጯቸዉ የትርክት መርዞች ዋናዉን ቦታ የያዙ ይመስላሉ። ምኒልክ፤ አማራ፤ ነፍጠኛ፤ ጡት ቆራጭ፤ ወዘተ፤ እያሉ እያስፃፉና እየሰበኩ በተለይ ወጣቶችን በዉሸት ይመርዛሉ። በጥቅማጥቅሞችና በመሳሰሉ መንገዶች ይመርዟቸዋል። ታሪኩ ዉሸት መሆኑን የሚያዉቁ የርካሽ ፖሊቲካ ጊዜያዊ አትራፊዎች ወጥተዉ ሃቁን አይመሰክሩም። ወንጀሎቹን በማስቆም ፈንታ ሁኔታዎቹን የሚያባብሱም አሉ። በዚህ ምክንያት በተለይ በዛሬዉ ኦሮሞና ቤኒሻንጉል አካባቢዎች የንፁሐን ዜጎች ደም በየቀኑ በግፍ እየፈሰሰ ይገኛል። ቤቶቻቸዉን እያቃጠሉ ከኖሩባቸዉ ቀዬዎቻቸዉ እያፈናቀሉ የርሃብና የእንግልት ሰለባዎች ያደርጓቸዋል። ንፁሕ ዜጋ በገዛ አገሩ የመኖር የተፈጥሮ መብቱን ይነጠቃል። ሰፊዋ የኢትዮጵያ ምድር የሁሉም ዜጋ መሆኗን ይረሳሉ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ታሪክ ይፋረደናል! - አንዱዓለም ተፈራ - የእስከመቼ አዘጋጅ

ከ30 ዓመታት በፊት 14 ክፍለ ሀገራት ነበሯት። ከሺዎቹ ዓመታት ጀምሮ ህዝቡ በጎንደር፤ በጎጃም፤ በትግራይ፤ በወሎ፤ በሸዋ፤ በወለጋ፤ በኢሊባቦር፤ በከፋ፤ በአርሲ፤ በሲዳማ፤ በወላይታ፤ በሐረርጌ፤ ወዘተ ምድሮች በነፃ እየሰፈረ ኖሯል። ዘሩን ሆነ ይማኖቱን ሳይጠየቅ በነፃ እየተዘዋወረ ነግዷል። ወያኔ/ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ ጊዜ ጀምሮ ግን ሁኔታዎች እጅጉን ተለወጡ። ኦሮሚያ ብለዉ በከለሉት ምድር ላይ የሚኖሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሌሎች ዜጎች መብት ተገፈፈ። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሚኖሩ አማራዎች እያለቁ ናቸዉ፤ ያሉት ቁም ስቅል እያዩ ናቸዉ። ከደምቢዶሎ ዩኒቬርሲቲ የታገቱ ንፁሐን ሴት ተማሪዎችን ፈልጉ ነፃ ያወጣቸዉ አካል የለም። በነዚህ ጉዳዮች የሚከተሉት አካላት በታላቅ ኃላፊነት ሊጠየቁበት ይገባል።

 

2ኛ/        የማዕከላዊና የክልል  መንግሥታት ግዴታዎችና ኃላፊነቶች

የመንግሥት ዋናዉ ኃላፊነት የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ነዉ። እንደነዚህ ዓይነት ከባድ ወንጀሎች ሲፈጸሙ የፖሊስ ኃይል ሥራዉን መሥራት ነበረበት። ከፖሊስ ዐቅም በላይ ሆኖ ሲገኝ የመከላከያ ሠራዊት ጭምር መጠቀም ይጠይቃል። ይሄ ግን እስካሁን ድረስ አልታየም። እጅግ በጣም ግራ የሚያጋባዉ ነገር ቢኖር የዚህ ኃላፊነት ዉድቀት ነዉ። በገዛ ወንጀሎችዋ ምክንያት የወያኔ አስተዳደር ከሦስት ዓመት በፊት ሲያከትም የተጠበቀዉ ጠንካራ የሽግግር መንግሥት ማቋቋም ነበር። ይሄ ወርቃማ ጥያቄ ግን እንደተለመደዉ አልተፈቀደም። አሻግራችኋለሁ ያለዉ አካል ግን ብቻዉን ምንም ነገር መጨበጥ አቅቶት አገሪቷን በከባድ ጣጣ ዉስጥ ጥሏታል። በትግራይ የተወሰደዉ እርምጃ ከባድ ችግሮች አስከትሏል። እርምጃዎቹ በተሻለ መንገድ ቢወሰዱ ኖሮ በንፁሐን ዜጎች ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ጉዳቶች በከፍተኛዉ መጠን ሊቀነሱ በቻሉ ነበር። በዉስጥ ያለብንን ድክመት በመጠቀም ሱዳን እንኳን በድፍረት ገብታ ከባድ አደጋ ላይ ጥላናለች። ከግብፅ ጋር በማበር በግድባችን ግንባታ ላይ ሊሻጥሩ ይፈልጋሉ። ችግሮቻችንን በቅጡ ለዓለምአቀፍ ህብረተሰቦች መግለፅና ማሳመን አልተቻለም። ትናንት ተከብራ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅትና ለተለያዩ አለማቀፍ አካላት መቀመጫ የነበረችዉ አገራችን ዛሬ በዉስጥም ሆነ በዉጪ ተንቃለች። ሁኔታዎች ቶሎ ካልተሻሻሉ ችግሮቻችን እየተባባሱ መሄዳቸዉ የማይቀር ነዉ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አባ መላ ሳይበላ ተበላ! - ሆዳም! ስለሚበላው እንጂ ስለሚባለው አይጨነቅም!

መንግሥት የአዋቂዎችን ምክር መስማት አለበት። የአደጉት አገራት ሁሉ የሚያደርጉት ተግባር ነዉ። የህዝብን ልብ ትርታ ማዳመጥ አለበት። ካለዚያ በሥልጣን ላይ የመቀመጥ ጥቅሙ ምንድን ነዉ? መንግሥታት ጠንካራ የሚሆኑት የተማሩ ሰዎች በማሰማራትና ልምድ ካካበቱ ወገኖች ምክር በመሻት ነዉ። ነፃ ተቋማትን መበዘርጋት ነዉ። ተቀባይነት የሌለዉን ሕገ መንግሥት በተገቢዉ መንገድ እንዲሻሻሉ  በማመቻቸት ነዉ። ወንጀለኞችን ለፍርድ በማቅረብ ነዉ። ጥሩ ዲፕሎማሲ በመጠቀም በቢሊዮኖች ዶላር የሚገመተዉን የተዘረፈዉን የህዝብ ገንዘብ ሲያስመልስ ነዉ። ሰላም በማስፈን ነዉ። ዘለቄታ ያለዉ የኢኮኖሚ ግንባታ ሲዘረጋ ነዉ። ዜጎችን ከእልቂት፤ ከስደትና ከእንግልት ሲታደግ ነዉ። የአገርን ሙሉ ሉዓላዊነት ሲያስጠብቅ ነዉ። ያኔ ይከበራል፤ ይደመጣል። መንግሥት አለ ይባላል፤ ሰዉ ተስፋ ይኖረዋል።  ዛሬ ይሄ ሁሉ የለም። እጅግ በጣም ያሳዝነኛል።

 

 3ኛ/       የህብረተሰቡ ኃላፊነት

ህዝብ ጭፍን ደጋፊ ወይም ጭፍን ተቃዋሚ መሆን አይኖርበትም። መልካም ሥራዎች ሲሠሩ መደገፍ ጥሩ ነዉ። በህዝብ ላይ ከባድ ስህተቶችና ወንጀሎች ሲፈጸሙ ደግሞ ተቃዉሞ ማሳየት የግድ ነዉ። ያኔ ነዉ መንግሥት ጥሩ ጥንቃቄ ለመዉሰድ የሚገደደዉ።

የእያንዳንዱ ዜጋ ቅን አስተዋጽኦ ይጠበቃል። በሚከተሉት ነጥቦች ላይ ለመስማማት እንሞክር፤

ሀ)            የእያንዳንዱ ሰዉ ህይወት ቅዱስ መሆኑን መዘንጋት የለብንም።

ለ)            ማንም ግለሰብ የማንንም ህይወት ማጥፋት ከቶዉን አይችልም። የዘር ማጥፋት ድርጊት እጅግ በጣም ከፍተኛ ወንጀል ነዉ። ቢያድርም ቢቆይም በሕግ ማስጠየቁ አይቀርም።

ሐ)           የዉሸት ትርክቶች ሰለባዎች እንዳንሆን ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅብናል። ንፁሕ የአማራ ዜጋ የማንንም ጡት አልቆረጠም። ነፍጥ ማንገት ድንበርና ደህንነት ለመጠበቅ ነበር። የሄን ተግባር ደግሞ የፈጸሙት ከሁሉም ህብረተሰቦች የተዉጣጡ ዜጎች ነበሩ። የኢትዮጵያ ህዝብ ለሺዎች ዓመታት በመልካም መስተጋብርና ትብብር ነበር የኖረዉ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዛሬ በኢትዮጵያ ማን ተሹሞ ማን ተሻረ?

መ)          እንደወትሮአችን የእያንዳንዱነ ዜጋ ኃይማኖትና እምነት ማክበር አለብን። የተፈጥሮ መብት ነዉና።

ሠ)           የተጠማነዉ ዲሞክራሲያዊ የሆነ መልካም አስተዳደር ነዉ። ባንድ ላይ ሆነን እንገንባ።

ረ)            ዋና ጠላቶቻችን ርሃብ፤ በሺታና ስደት ናቸዉ። በተጨማሪም የየራሳቸዉን ጥቅም የሚያሳድዱ የዉጪ ጠላቶች ይኖሩናል፤ ዕድል አንስጣቸዉ። የተበታተነች አገር ለነርሱ እንጂ ለኛ አትበጀንም። ሞኞች አንሁን፤ እንደሰዎች እናስብ፤ እናስተዉል።

ሰ)            በአቋራጭ ኃብታም ለመሆን ወይንም የኮንዶሚኒዬም ባለቤት ለመሆን የሚስገበገብ ካድሬ ካለ ክፉኛ ቢያስብበት ይሻላል፤ ዛሬ ወቅቱ አገር የማዳን ታላቅ ኃላፊነት ነዉ። ህዝብ እያለቀ፤ አገር እየፈረሰ ለግል ጥቅም መስገብገቡ ትልቅ የሞራል ዉድቀት ነዉ።

ረ)            ወንጀለኞችን ለፍርድ በማቅረብ ዘመቻ እንተባበር። በንፁሐን ዜጎች መካከል እርቀ ሰላም እናዉርድ። እጅ ለእጅ ተያይዘን የዉድ አገራችንን አንድነትና የህዝባችንን ደህንነት እናስጠብቅ።

 

ከመልካም ምኞት ጋር።

2 Comments

  1. የሰው ልጅን እና ከብትን መለየት አለብን። የሰው ልጅን ወልደን እንደ ከብት በመንጋ የሚነዳ ትውልድ መፍጠር የለብንም። እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ሰባ አምስት በመቶ ከሚሆነው ኢትዮጵያዊ ከሰማንያ ሚሊየን በላይ የሚሆነው ህዝብ በመንጋ እየተመራ ለመንጋጋት ተገድዶ በመንጋው መንገድ ያለፍላጎቱ የሚሄድ ነው። ከመንጋው ጋር እንደመንጋ አልራመድም ካለ በstampede ይደፈጣጣል በመንጋው። በመንጋው ተከብቦ መውጪያ አጥትዋል። እኛ ወላጆች መንጋ ውስጥ ወርውረን አሳልፈን እንደሰጠናቸው ከመንጋውም መንጥቀን ማውጣት ነው መፍትሄው።

  2. ኢትዮጵያ ተፈጥፍጣ ወድቃ አልተፈጠፈጠችም አልወደቀችም ብለው የሚያስቡ ሰዎች ኢትዮጵያ ሳትወድቅ ተንጋላለች ብለው እራሳቸውን ስላሳመኑ ከተንጋለልችበት እንስተው ለማቆም ሲጎትትዋት ተቀነጣጥሳ ሰቆቃዋን እያበዙባት ነው። የተፈጠፈጠችው ኢትዮጵያ እንኳንስ ጎትተዋት እንዲሁም ተሰባብራለች። በጥንቃቄ ማንሳት ነው እንጂ ምንጭቅ አድርገው ሲጎትትዋት መቀነጣጠስዋ ነው። በአዋቂ ወጌሻ በመታሽዋ ጊዜ እነርሱ ቁጭ ብድግ ሊያደርግዋት ያልማሉ። ፈታኝ ወቅት ፣ የደረሱ ችግሮች ብዛታቸው…..እያሉ እንደተንጋልላለች አስመስለው ቁስሎችዋን በድሪቶ ከመሸፈን እና ከማለባበስ መውደቅዋን በገሀድ መገንዘብ አነሳስዋን ለመዘየድ ይጠቅማል። የሀገር ሽማግሌዎች እና ኢህአዴጎች እባክችሁ መውደቅዋን ተገንዘቡ።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share