ማነው“እርስት(መሬት) አስመልሳለሁ”በሚል እየዶለተ ያለው? እነ ወልቃይትና አዲስ አበባ እንደ አስረጅ – ከፍትህ ይንገስ

ሁላችንም ልንረዳው እንደምንችለው ከአንድ ክፍለ ዘመን በፊት የነበሩ የኢትዮጵያ ንጉሰ-ነግስታት ላስተዳደራቸው ይመቻል ብለው ያሰቡትን ቦታ ዋና ከተማ አድርገው ይሰይሙ እንደነበር ግልፅ ነው። በዚህም መሰረት አፄ ሚኒልክና ወይዘሮ ጣይቱ አዲስ አበባን የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አድርገው መምረጣቸው ይታወቃል። አዲስ አበባ በዋና ከተማነት ለመመረጧ የተሰጠ ግልፅ የሆነ መነሻ ባይኖርም አንዳንዶቹ ግን ሁለት ምክንያቶችን ያስቀምጣሉ። አንደኛው የአዲስ አበባ የአየር ፀባይ ለመኖር የሚመች መሆኑ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የእንጦጦ ከፍተኛ ቦታ ፀጥታ ለማስከበር ጠቀሜታው የጎላ ሆኖ መገኘቱ ነው የሚል ነው። ከዚህ በተጨማሪም አዲስ አበባ አማካይ ቦታ ሆና መገኘቷ በዋና ከተማነት እንድትምረጥ አድርጓት ሊሆን ይችላል የሚል እሳቤ አለ።

አዲስ አበባ ዋና ከተማ ሆና የተመረጠችበት ምክንያት ምንም ይሁን ምን ግን ነገስታቱ   በጊዜው የነበራቸው የንቃተ-ህሊና ደረጃ “አንዲት ኢትዮጵያ” በሚል ጠንካራ አቋም ላይ የተመሰረተ ስለነበር ከአንዱ ወይም ከሌላው ተቃውሞ ሊመጣ ይችላል ብለው ሳይጨነቁ ለአስተዳደራቸው ይጠቅማል የሚሉትን የማዕከላዊ መንግስት መቀመጫ መርጠዋል። በዚህም መሰረት አዲስ አበባ ከአንድ ምእተ-አመት በላይ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆና አገልግላለች። ይህን ተከትሎም አዲስ አበባን ሁላችንም እንደምናውቃት ከአራቱም የኢትዮጵያ ማእዘናት የመጡ ህዝቦች የሚኖሩባት ከተማ ሆናለች። ስለሆነም አዲስ አበባ የተለያዩ ቋንቋዎች የሚነገሩባት፣ የተለያየ ማንነት ያላቸው ህዝቦች የሰፈሩባት፣ የተለያዩ ባህሎች የሚንፀባረቁባት፣ የተለያዩ ምግቦች የሚቀርቡባት ባጠቃላይም የኢትዮጵያዊያን ነዋሪዎቿ ትንሿ Melting Pot ለመሆን በቅታለች ቢባል ማጋነን አይሆንም።ያም ሆነ ይህ ግን አጼ ሚኒልክም ሆኑ ወ/ሮ ጣይቱና አማካሪዎቻቸው አዲስ አበባን የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አድርገው ሲሰይሙ ከአስተዳደራዊ ምቾት (Administrative Comfort) እና ጠቀሜታ ባለፈ ሆነ ብለው አንድን ብሄር ለመበደል ወይም ሌላውን ለመጥቀም ያደረጉት ነው ለማለት ማስረጃ ማቅረብ የሚቻል አይመስለኝም። በወቅቱ የተመረጠችው አዲስ አበባ ባትሆንም ሌላ ቦታ ዋና ከተማ መሆኑ አይቀርም ነበርና። በነገራችን ላይ በዚያ ወቅት የነበረው የህዝብ አሰፋፈር ቋሚ ባለመሆኑ ምክንያት አንድ ህዝብ ወይም የህዝብ ክፍል ምቾቱን እየተከተለ ቦታ የሚቀያይርበት ሁኔታ የተለመደ መሆኑ አጠራጣሪ አይደለም። በወቅቱ የነበሩት ነገስታትም አዲስ አበባን ዋና ከተማ አድርገው የመረጡበት ሁኔታ በዚሁ አግባብ የሚታይ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  "ህይወት አጭር ጣፋጪ ና በሥቃይ የተሞላች ናት።" መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ 

እነዚህ ነዋሪዎች አዲስ አበባ ላይ እትብቶቻቸው ተቀብረዋል፤ ጥረው ግረው ንብረት አፍርተዋል፤ ከተማዋንም  አሁን ላለችበት ደረጃ አብቅተዋታል። ስለዚህ የአዲስ አበባ ባለቤቶች እነዚህ ነዋሪዎች እንጅ ሌላ ማንም ሊሆን ከቶ አይችልም።  በሌላ አነጋገር የአዲስ አበባ ከተማን ባለቤትነት  ከነዋሪዎቿ ነጥቆ ለሌላ አካል ለመስጠት የሚያስችል ምንም አይነት ምድራዊ አመክንዮ ይኖራል ብየ አላስብም። ከዚህ አንፃር የአማራ ብልፅግናዎች የያዙትን አቋም በሚገባ አደንቃለሁ። ምክንያቱም በ’ነሱ እምነት አዲስ አበባ የተቆረቆረችበት ቦታ በታሪክ የአማራ ነው የሚል አቋም እንዳላቸው ብገምትም አሁን ላይ ግን የከተማዋ ባለቤቶች የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ናቸው የሚል ጠንካራ እይታ እንዳላቸው ተገንዝቢያለሁ። ኢዜማዎችም ቢሆኑ እንደ አማራ ብልፅግናዎች ሁሉ የአዲስ አበባ ባለቤቶች ነዋሪዎቿ እንጅ ሌላ ሊሆን አይችልም በሚል አበክረው ሲገልፁ አስተውያለሁ። ባልደራስ ከመጀመሪያውም የተመሰረተው የአዲስ አበባን ነዋሪዎች መብት አስከብራለሁ በሚል ስለሆነ አቋሙ ግልፅ እንደሆነ ይታወቃል።

ይህ ሆኖ እያለ ግን በአንድ በኩል አብንን የመሳሰሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አዲስ አበባ (በ’ነሱ አጠራር በረራ) የአማራ ናት የሚል አቋም ይዘው ታሪክ እያጣቀሱ ይከራከራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የኦሮሞ ብልፅግናዎችን ጨምሮ የኦሮሞ ፖለቲካኞች አዲስ አበባ (በ’ነሱ ስያሜ ፊንፊኔ) የኦሮሚያ ናት ከሚል ክርክር አልፈው ባገኟቸው አጋጣሚዎች ሁሉ የህዝቡን አሰፋፈር ለመቀየር የሚችሉትን ሁሉ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።  በርግጥ አብን ስልጣን ላይ ቢሆን ኖሮ በተግባር ምን ያደርግ ነበር የሚለውን መናገር ቢያስቸግርም ስልጣን ላይ ያሉት የኦሮሞ ብልፅግናዎች ግን የአዲስ አበባን ነዋሪዎች ከመጤፍ ሳይቆጥሩ መሬቱ የኛ ነው የሚል አቋም ከማንፀባረቅ አልፈው በተግባርም አዲስ አበባን የራሳቸው ለማድረግ የህዝብ አሰፋፈሯን ለመቀየር ከሚያደርጉት ጥረት በተጨማሪ ሌሎች ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ሲያደርጉ እየተመለከትን ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ምኒልክን ብትወቅሱ ማንነታችሁን ትረሱ (በኃይሌ ላሬቦ)

እንዲያውም አንዳንድ ጊዜስ በአዲስ አበባ ላይ አለን የሚሉት የባለቤትነት ጥያቄ ከወልቃይትና ከራያ አስበልጠው ለማሳየት  ሲፍጨረጨሩ ይታያሉ። ልብ በሉ እንግዲህ፡ የወልቃይትንና የራያን አከባቢዎች የእኛ ናቸው የሚሉት በዋነኛነት በውስጣቸው የሚኖሩ ህዝቦች ናቸው። የአማራ ብልፅግናም ሆነ ሌላው ኢትዮጵያዊ የወልቃይትናና የራያን ጉዳይ አጀንዳ ያደረገው ግን በዋነኛነት የየአከባቢዎቹ ነዋሪዎች ማንነት ይከበር ከሚል ሞራላዊ ግዴታ ተነስቶ ነው። በዚያ ላይ የወልቃይትና የራያ ነዋሪዎች ማንነታቸውና የሚኖሩበት መሬት የተዘረፈው በህወሓት ሲሆን ዝርፊያው የተፈፀመባቸውም በእኛ እድሜ ነው። ማንነታቸውንና የሚኖሩባቸውን አከባቢዎች መልሰው ያገኙትም ቢሆን ህወሃት እንደለመደው ሌላ የማንነትና የመሬት ዘረፋ ለመፈፀም በማሰብ ለማጥቃት ሲሞክር የተሰነዘረበትን የመልሶ ማጥቃት መቋቋም አቅቶት ሸሽቶ ሲሮጥ ጥሏቸው በመሄዱ ምክንያት ነው። በሌላ አነጋገር የወልቃይትና የራያ ነዋሪዎች በእንጥልጥል ላይ (Pending) የነበሩ ጥያቄዎች የተመለሱት በህወሃት በራሱ ጥፋት ነው ማለት ነው። ምክንያቱም ህወሓት አንድም ድሮ ቦታወቹንና ነዋሪዎቹን ወደ ትግራይ እንዲካለሉ ያደረገው በዘረፋ ሲሆን፤ ሁለትም ድሮም የማይመለከቱትን ነዋሪዎች እና የነዋሪዎቹን የባለቤትነት ይዞታዎች ጥሏቸው የሸሸው ራሱ በለኮሰው ጦርነት ምክንያት በመሆኑ ነው። መቸም ቢሆን ቀድሞ ንብረቱን የተዘረፈ አካል ዘራፊው ሃይል ጥሎት ቢያገኘው ማንሳትና የራሱ ማድረግ አልነበረበትም ተብሎ ሊወቀስ የሚችልበት ምክንያት ይኖራል ብየ አልገምትም። ከዚህ ባሻገር ህወሃት ቦታዎቹንና የሰዎቹን ማንነት የዘረፈው በእኛ እድሜ በመሆኑና አሁን ስልጣን ላይ ያሉት የኢህአዴግ ወራሾች ጭምር በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ለዝርፊያው አስተዋፅዖ ያደረጉ በመሆናቸው የህወሓትን ያልተገባ ዘረፋ በማስተካከል ህዝቡን ለመካስ  የሚቸግራቸው የማስረጃና የፍሬ ነገር ችግር ሊኖር እንደማይችል ግንዛቤ ውስጥ መግባት ይኖርበታል።

የኦሮሞ ብልፅግናዎች አዲስ አበባ የኦሮሞያ አካል ናት ሲሉ ግን ምን ለማለት ፈልገው እንደሆነ ግራ አጋቢ ነው። ምክንያቱም አዲስ አበባን በባለቤትነት የያዟት ነዋሪዎቿ ማንነታችን ኦሮሞ ነውና ወደ ኦሮሚያ  እንካለል የሚል ጥያቄ ሲያነሱ የተሰማበት ጊዜና ወቅት የለም። ከዚህ አለፍ ሲልም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች አዲስ አበባ የአዲስ አበቤዎች እንጅ የማንም አይደለችም እያሉ ሌት ተቀን ሃሳባቸውን ጮክ ብለው ሲገልፁ ነው የሚደመጡት። ለነገሩ የኦሮሞ ብልፅግናዎች አዲስ አበባን ብቻ ሳይሆን ራያ፣ ውረሂመኖ፣ ወረኢሉ፣ ወረባቦና የመሳሰሉ ቦታዎችም የእኛ “እርስቶች” ናቸው የሚል የጅል ሃሳብ ሲሰነዝሩም እየሰማናችው ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  “የሕዝብ ሰው/Public Figure” መሆን አንዳንዴ ሳያሰክር ይቀራል? - ብሥራት ደረሰ

የኦሮሞ ብልፅግናዎች ከተጠናወታቸው ከዚህ “እርስት” እናስመልሳለን የሚል ቅዠት ተነስተው በተለይ አብንንና ባልደራስን አይናችሁን ላፈር እያሏቸው እንዳለ እየታዘብን ነው። ለዚህም ነው የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚ/ር ሳይቀሩ  በኣዲስ አበባ ጉዳይ ከባልደራስ ጋር ጦርነት እንከፍታለን ሲሉ የተደመጡት። በሌላ በኩል አቶ አዲሱ አረጋ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ሰብስበው አዲስ አበባ ላይ ብዙ ስራዎች እየሰራን ስለሆነ ዝርዝሩን  ባንገልፅላችሁም እመኑን እያሉ ሲናገሩ ንግግራቸው አፈትልኮ ወጥቶ ሰምተነዋል። እነአቶ ለማ ከነአቶ ታከለ ጋ በመቀናጀት የአዲስ አበባን የህዝብ አሰፋፈር ለመቀየር የሄዱባቸው ርቀቶች በተለያዩ መንገዶች ጆሯችን ላይ ደርሰዋል። አሁን በቅርቡ ደግሞ ጠቅላይ ሚ/ሩን ለመደገፍ በሚል ኦሮሚያ ላይ ተደርጎ በነበረው ሰልፍ አንዳንድ አጉራ ዘለል አባላቱ የሚያራምዷቸው ሃሳቦች የማይመቹ ቢሆኑም እንደ ፓርቲ ግን ሃላፊነት በተሞላበት መንገድ እየተንቀሳቀሰ ያለውን አብንን መሳሪያ አንስተው መንግስትን ከሚፋለሙት ኦነግ ሸኔና ህወሓት እኩል እንደጠላት ሲፈርጁት በአይናችን አይተናቸዋል።   ይባስ ብለው ደግሞ አዲስ አበባን ከጥቅም ውጭ ካደረግናት በኋላ ቀስ በቀስ ወደ ኦሮሚያ እንጠቀልላታለን የሚል እቅድ እንዳላቸው አሁንም የኦሮሚያ ብልፅግና ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በድብቅ ሲዘባርቁ አድምጠናቸዋል። ምናልባትም  ደግሞ አዲስ አበባን የተመለከቱ ያልሰማናቸው ብዙ የቁማርና የሴራ ሽረባዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል።

ከላይ የተገለፁትን ነጥቦች ጠቅለል አድርጎ በማየት “እርስት (መሬት) እናስመልሳለን” በሚል እላይ እታች እያሉ ያሉት የኦሮሞ ብልፅግናዎች ካልሆኑ ሌላ ማን ሊሆን ይችላል የሚል ጥያቄ ቢነሳ ስህተት አይሆንም።

 

 

 

 

 

 

2 Comments

  1. የኦሮሞ ብልፅግና (ኦዴፓ) ባለስልጣናት ባለፈው ሰላሳ አመታት ከማንኛውም የክልል መንግስት ባለስልጣናት በላይ የገዛ ክልላቸውን አክስረው እና በጉቦ ሀብት ኦሮሞን ጥቅም እንስጥ ሀብት አካብተዋል። ህወሀት ፌደራልን ዘረፈ እንጂ እንደ ኦዴፓ የእራሱን ክልልን ትግራይን አልዘረፈም። ትንሽ ኦዴፓዎችን አልዘርፍ ያለውን አለማየሁ እቶምሳንም ገደሉት። ከእዛም ኦሮሚያ ቄሮ ሲያምፅባቸው ወደ አዲስ አበባ ለዝርፍያ አመሩ፡ ፌደራልንም አላስተረፉትም። አባዱላ እና ቢጤዎቹ ፌደራል ገብተው ሐረርንም አላስተረፉትም ሁሉንም ሊውጡ አሰፍስፈዋል።

  2. Please re-read this quote taken from this piece. This is my invitation and it has been my idea too. This writer took it from the tip of my tongue!
    መቸም ቢሆን ቀድሞ ንብረቱን የተዘረፈ አካል ዘራፊው ሃይል ጥሎት ቢያገኘው ማንሳትና የራሱ ማድረግ አልነበረበትም ተብሎ ሊወቀስ የሚችልበት ምክንያት ይኖራል ብየ አልገምትም። ከዚህ ባሻገር ህወሃት ቦታዎቹንና የሰዎቹን ማንነት የዘረፈው በእኛ እድሜ በመሆኑና አሁን ስልጣን ላይ ያሉት የኢህአዴግ ወራሾች ጭምር በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ለዝርፊያው አስተዋፅዖ ያደረጉ በመሆናቸው የህወሓትን ያልተገባ ዘረፋ በማስተካከል ህዝቡን ለመካስ የሚቸግራቸው የማስረጃና የፍሬ ነገር ችግር ሊኖር እንደማይችል ግንዛቤ ውስጥ መግባት ይኖርበታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share