(በዘ-ሐበሻ ጋዜጣ ቁጥር 51 ላይ ታትሞ የወጣ)
ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ስሆን ከባለቤቴም ጋር በሰላም በፍቅር እንኖራለን፡፡ መቼም በሰው ላይ ብዙ ነገር ይመጣልና ባለቤቴም ጤነኛ አይደለችም፡፡ የሐኪም ክትትል ሳታቋርጥ በሽታዋን እየተንከባከበች ሲሆን ከዚህ በፊት ትወስደው የነበረውን የእርግዝና መከላከያ መድሃኒት እንዳትውጥ ሐኪም ከልክሏታል፡፡ አሁን ባለው ገቢያችን ከሶስት ልጆቻችን ተጨማሪ ልጅ ወልደን ማሳደግ አንችልምና ለጊዜው ኮንዶም መጠቀምን ነበር የመረጥነው፡፡ እኔ ግን ኮንዶሙ አልተስማማኝም፡፡ እንደ አለርጂክ ነገር አውጥቶብኛል፡፡ በዚህ የተነሳም ጥቂት ጊዜ ብቻ ነው የተጠቀምኩበት፡፡ አለፍ አለፍ እያልኩ ስጠቀምበት ደሞ ብልቴን በጣም ያቃጥለኛል፡፡ ከዚህ በተረፈ እኔና ባለቤቴ የኤች.አይ.ቪ ምርመራ ካደረግን በኋላ ነው የተጋባነውና በዚህ በኩል ጥርጣሬ የለብኝም፡፡ ጥያቄዬም ኮንዶም አለርጂክ ያመጣል የሚባለው ምን ያህል እውነት ነው? ኮንዶሙን ብተወው ሌላ ምን ማድረግ እችላለሁ? ችግሩ አለርጂ ከሆነ የሚታዘዝ መድሃኒት አለው? አለርጂክ ካልሆነ ምን ሊሆን ይችላል? አማራጭ ካጣሁ ግን ለማቆም እገደዳለሁ?
ቢኒያም ነኝ
ውድ ቢንያም፡- ጥያቄህን በጥሞና አንብበን ምላሹን ከአክብሮት ጋር እንደሚከተለው አስተናግደነዋል፡፡
በሰውነት ላይ የሚለበሱ ወይም የሚጠለቁ ነገሮች ከቆዳ ጋር ንክኪ ስለሚኖራቸው አለርጂ ሊያስከትሉ ይችላል፡፡ አለርጂ አዲስ ልብስ በመልበስ፣ በአንገት ሐብል፣ በጆሮ ጉትቻ፣ በጣት ቀለበት ወይም በእጅ አምባርና ሰዓት የተነሳ ሊፈጠር ይችላል ማለት ነው፡፡
ከሁሉም አስቀድሞ ግን ሁኔታው አለርጂ ለመሆኑ እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል፡፡ የቆዳ አለርጂ ምልክቶች ጥቃቅን ሽፍታዎች፣ ማሳከክ፣ መቅላት መጠነኛ የሆነ እብጠት ሲሆን መንስኤው በልብስ ወይም በሌላ ነገር ንክኪ ነው ለማለት የሚቻለው ህመሙ ከጀመረበት ጊዜ ጋር ተያያዥነት ካለው ነው፡፡ ማሳከኩ የመጣው ከአዲስ ልብሱ ጋር ከሆነ ልብሱን ደግሞ ባለመጠቀም ብቻ አለርጂውን መከላከል ይቻላል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን መንስኤው ሌላ ነገር ሊሆን ይችላል፡፡
አንዳንድ የቆዳ ህመሞች ከአለርጂ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ምልክት አላቸው፡፡ በፈንገስ ኢንፌክሽን የሚመጣውን ጭርት እንደ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል፡፡ እንግዲህ ያሉ የቆዳ ኢንፌክሽኖች ያለመድሃኒት የማይድኑና ‹‹አለርጂክ ፈጠረ›› የተባለውን ልብስ ወይም ሌላ ነገር በማስወገድ የሚጠፉ አይደሉም፡፡
የኤይድስ ስርጭትን በመከላከል ዘመቻ እንደ አንድ ወሳኝ አማራጭ ተደርጎ የሚታየው ኮንዶም በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም ላይ በስፋት ጠቀሜታ ላይ ውሏል፡፡ ይህም ሆኖ ግን አለርጂ ማለት በኮንዶም ዙሪያ ከሚነሱ ችግሮች ውስጥ እንደ አንኳር ጉዳይ ሊታይ የሚችል አይደለም፡፡ የብዙ ሰዎች ችግር አለመሆኑ እንደ አበይት ጉዳይ አይቆጠር እንጂ በአንዳንድ ሰዎች ላይ አለርጂ አይፈጥርም ማለት ግን አይደለም፡፡
ኮንዶም በሰውነት አካል ላይ የሚጠለቅ ፕላስቲክ ነውና ለአንዳንድ ሰዎች አለርጂክ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ፕላስቲኩ እንደ ልብስ ወይም ጌጣጌጦች በገላ ላይ ለብዙ ጊዜ የሚቆይ ባለመሆኑ ቆዳን የማስቆጣቱ ሁናቴ በጣም አነስተኛ ነው፡፡
ስለዚህም በግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅትና ከዚያም በኋላ የብልት ማሳከኩ ሁኔታ በፕላስቲኩ አለርጂክነት ምክንያት የመጣ መሆኑ ያጠራጥራል፡፡ በብልትህ ቆዳ ላይ ሌላ የቆዳ ህመም ላለመኖሩ መታወቅ አለበት፡፡ አንዳንድ የአባላዘር በሽታዎችም የብልት መቁሰልና ማቃጠል ያስከትላሉ፡፡
የብልት ማሳከኩ ሁኔታ በፕላስቲኩ ምክንያት የመጣ ለመሆኑ እርግጠኛ መሆን የምትችለው ኮንዶም መጠቀም ስታቆም ችግሩም አብሮ የሚጠፋ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ በዚህ መሰረትም ለተወሰኑ ቀናት ኮንዶም መጠቀም አይኖርብህም ማለት ነው፡፡ ያለመከላከያ ግንኙነት ማድረጉ የእርግዝና አደጋ ስለሚያስከትልም በነዚሁ ቀናት ወቅት ግንኙነት መፈፀም አይኖርብህም፡፡
ኮንዶም ባልተጠቀምክባቸው ቀናት ወቅት የማሳከኩ ህመም ከተወገደልህ ግን ምናልባት ፕላስቲኩ አለርጂ ፈጥሮብህ ስለሚሆን የኮንዶሙን ነገር እርግፍ
አድርገህ መተው ይኖርብሃል፡፡
ያም ሆኖ ግን ያለ እርግዝና መከላከያ ግንኙነት መፈፀም አይኖርብህም፡፡ ሌላ የመከላከያ ዘዴ ያስፈልጋል፡፡ ከኮንዶምና ከሚዋጠው ክኒን በተጨማሪ ሌሎችም የመከላከያ ዘዴዎች አሉ፡፡ አብዛኛዎቹ ሆርሞን ከሚባሉ ኬሚካሎች የሚቀመሙና ከሚዋጠው ክኒን ጋር ተመሳሳይ ባህሪ ስላላቸው ከባለቤትህ ህመም ጋር ላይስማሙ ይችላሉ፡፡ ባለቤትህ መከላከያውን እንድትጠቀም ያስከለከላትን ህመም ምንነትን ባለመጥቀሰህ ግን አማራጭ መድሃኒቶችን ለመጠቆም አላስቻለንም፡፡ ይሁን እንጂ ከሁሉም የሚሻለው ሌሎችንም ተመሳሳይ መድሃኒቶች (የሚዋጡ፣ የሚቀበሩ፣ የሚወጉ) ሁሉንም አለመጠቀም ነው፡፡
ወድ ቢኒያም፡- እስካሁን ድረስ ሶስት ልጆች ማፍራታችሁን ገልፀህልናል፡፡ ለመሆኑ ከአሁኑ በኋላ (እያራራቃችሁ) ተጨማሪ ልጅ የመውለድ ሀሳብ አላችሁ? በእኛ አስተያየት በመካከለኛ ወይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚኖሩ ሶስት ልጅ ለቤተሰቡ በቂ ነው፡፡ ይህ በእርግጥ አስተያየት ብቻ ሲሆን፤ የልጆቻችሁን ቁጥር የመወሰን መብቱም ኃላፊነቱም የእናንተ ብቻ ነው፡፡ እንጨምራለን የምትሉ ከሆነ ግን ኮንዶምም ሆነ የመከላከያ መድሃኒት ሳያስፈልጋችሁ እርግዝናን መከላከል የምትችሉባቸው ዘዴዎች አሉ፡፡
– ማህፀን ውስጥ የሚቀበር (IUD) የሚባል መሳሪያ
– በግንኙነት ወቅት በሴት ብልት ውስጥ የሚቀመጥ ‹‹ሉፕ›› የተባለ መሳሪያ
የልጆቻችን ቁጥር በቂ ነው በሚለው ውሳኔ ካመናችሁበት ግን ለዘለቄታው የሚያስተማምን የመከላከያ መንገዶች መጠቀም ትችላላችሁ፡፡ ይኸውም ‹‹Vasectomy›› የሚባለው ሲሆን የዘር ፍሬ ቱቦህን ማስቋጠር ህክምና ነው፡፡
ይህ ህክምና ከተደረገልህ በኋላ ዳግመኛ መውለድ አትችልም፡፡ ዘለቄታዊው ዘዴ ካስፈራህ እና ኮንዶሙን ልቀጥልበት ካልክ ግን እንደ ሲትሪዚንና ፌናርጋም የመሳሰሉ ፀረ አለርጂክ መድሃኒቶችን በማስታገሻነት መውሰድ ትችላለህ፡፡ አንባቢያችን ስለሆንክ እናመሰግናለን፡፡ መልካሙ ሁሉ ይገጠምህ!S