“ዋለልኝ መኮንን” የሚለው ሥም በኢትዮጵያ (የቅርቡ) የሃምሳ ዐመት ፖለቲካዊ ትርክት ውስጥ ገዝፎም ሆነ አወዛግቦ መኖሩ አያከራክርም፡፡ ግርድፍና ስሁት ብያኔውንም የዓድዋ እና የወለጋ ልሂቅ እንደ “ዐሥርቱ ትዕዛዛት” ተቀብለው በሕዝብ መሃል ቁርሾ አንብረውበታል፤ ሰሜኑን ከደቡብ ነጣጥለውበታል፤ ሀገርን ወደ ፍርሰት ጠረዝ ገፍተውበታል፤ ሁለት ትውልድን በዘረኝነት ገርተውበታል…፡፡ የአማራ ሕዝብ የግማሽ ክፍለ ዘመን የጥቃት ተጋላጭነት ምንጩም ይሄው የሐሰት ትርክት ነው፡፡
ይህን ጉዳይ ከማብራራታችን በፊት ወደ ኋላ ተጉዘን የምንቃኘውን እናስቀድም…
የዘመናዊ ፖለቲካ ጅማሯችንን ስንመለከት የታሪክ ጎማ የ1960ዎቹ አብዮተኛ ተማሪዎች ጋር ያፋጥጠናል፡፡ ያ- ዘመን የራሳቸውን ሀገረ-መንግሥት ታሪክ በቅጡ ሳይረዱ፣ ስታሊን እና ማኦ ላይ የተንጠለጠሉት እኒያ ወጣቶች፣ በችኩል ግንፍልተኝነት ባህሪያቸው እየተነዱ ያነበነቧቸው የግራ ፖለቲካ ድርሳናት ‹ሳይፈላ ገንፍሎ የተቀሰቀሰውን የየካቲት አብዮት› የማዋለዱን እውነታም ያረዳናል፡፡
ከአውሮፓ እስከ ሰሜን አሜሪካ፣ ከአልጀሪያ እስከ ኢትዮጵያ… ቀሳውስትን ጭምር በግራ-ዘመም “ወንጌል” ለማጥመቅ ተዳፍረዋል፡፡ በጉያቸው የሸጎጡትን መጽሐፍትን አንብበው ከነባራዊ ሁናቴ ጋር አሰናስለው ከመራመድ ይልቅ፣ ሳያላምጡ መዋጡ ቀልሏቸዋል፡፡
ሥርየት-የለሽ ስህተታቸው ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ የተራመደበትን እግር፣ ለሶቭየት ህብረት የተሠራን ጫማ እስከማልበስ መዳፈራቸው ነው፡፡ በፍቅር በወደቁለት በዚህ ግርድፍ ኃልዮት ምሪትም ነባሩን ማኀበራዊ ስሪት ወደጎን ብለው፣ የፖለቲካ ዐውዱን የ‹‹ጨቋኝ›› – ‹‹ተጨቋኝ›› ትርክት አሸክመውታል፡፡ ይህም፣ በአብዮቱ ዋዜማ በነጻነት የተጓዙበት ጎዳና፣ በወራት ልዩነት በደም አበላ የሚታጠቡበት ይሆን ዘንድ አስገድዷቸዋል፡፡ በግልጽ አነጋገር መራራውን ጽዋ መጎንጨቱ ከእነሱ ከራሳቸው ጀምሯል፡፡
ዋለልኝ መኮንን፣ ለዚህ ሁሉ ምስቅልቅሎሽ መነሾ የሆነውን ‹‹On the Question of Nationalities in Ethiopia›› የተሰኘውን መርዛማ መጣጥፉን ሕዳር 1/1961 በቀ.ኃ.ሥ ዩኒቨርሲቲ፣ ልደት አዳራሽ በተካሄደ ስብሰባ ላይ ካቀረበ ዘንድሮ ሃምሳ አምስተኛ ዓመቱ ተቆጥሯል፡፡ የዋለልኝን ጽሑፉ ከግልብነትና ጥራዝ-ነጠቅነትም ከፍ ያለ ምጸት የሚያደርገው ደግሞ ወረቀቱን በልደት አደራሽ ሲያቀርብ፣ ተወልዶ ያደገበት ቤተ-አማራ (ወሎ) በከፋ የተፈጥሮ ድርቅ መጠቃት ጀምሮ የነበረ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ግን ለእሱ ተራ ነገር ነውና፤ ያን ሕዝብ ‹‹ጨቋኝ›› የሚል ፍረጃ የሰጠበትን ጽሑፍ በስሙ ለማቅረብ አላፈረም፡፡ አልፎ-ተርፎም ባደገበት ቀየ ድርቅና ርዛት ያደከማቸው ገባር ዐርሶ ዐደሮች ህይወታቸውን የሚገፉበትን ሁኔታ እያወቀ “…to be an Ethiopian, You will have to wear an Amhara mask” (“…ኢትዮጵያዊ ለመሆን የአማራነት ጭምብል ማጥለቅ የግድ ይላል“) በማለት አላግጧል፡፡
ፕ/ር ተሻለ ጥበቡ፣ የዋለልኝ እና ጓደኞቹን ጥራዝ-ነጠቅነት እያሰበ ይመስለኛል፡- ‹‹The Making of Modern Ethiopia›› (1995) በሚለው የሦስተኛ ዲግሪ ማሟያ ጥናቱ ላይ የኢትዮጵያ ነገሥታት ለብሔር ማንነት ደንታ እንዳልነበራቸው አጽንኦት የሰጠው፡፡ ፕ/ሩ በጥናቱ አማራው፣ በነገሥታቱ ዘመን በተለየ ያገኘው ተዋረዳዊ የሥነ-ልቦናና የኢኮኖሚ ጥቅም አለመኖሩን በማሳያዎች ካመላከተ በኋላ፡- “በምኒልክ ዙፋን ላይ የተቀመጠው ሰው የብሔር ማንነት፣ ለአንድ የታረዘ የወሎ አርሶ አደር ምኑም አይደለም፤ (A starving peasant in wallo does not give a damn about the ethnic identity of the person sitting at the Menelik’s Throne.”) ሲል አስረግጧል፡፡
ለዋለልኝ እና ከጀርባ ለገፉት የኢትዮጵያ ጠላቶች ግን ይሄ እውነታ ሊታያቸው አልቻለም፡፡ ለዚህም ነው፣ ዋለልኝ ያነበነበው ወረቀት በዐውድ ደረጃ፡- ‹ያ-የታረዘ የቤተ-አማራ አርሶ አደር ከሌሎች (ብሔረሰቦች) የተሻለ ኢትዮጵያዊ ነው፤ ሌሎች ኢትዮጵያዊ ለመባል እንደርሱ መሆን አለባቸው› የሚል አንድምታ የያዘ ነበር፡፡
ያኔም ሆነ ዛሬ ብዙሃኑ አማራ (አርሶ አደር) ከተፈጥሮ ጋር የሚታገል አፈር-ገፊ ነው፡፡ በዚህ ዘመን የኦነግ-ኦሕዴድ ገዥዎች የአፈር ማዳበሪያ ተከልክሎ የእህል ዘሩን ከፀበል ጋር በፀሎት የሚዘራ፤ በዱዓ የሚያምን ነው፡፡ ከተሜውም ከዕለት ገቢው ያለፈ ሕይወት እንደሌለው ለሙግት አይቀርብም፡፡
ከዋለልኝ የሐሰት ትርክት ወዲህ አማራ፡- ሀብት ንብረት የማፍራት ዋስትና ከማጣቱም በላይ፣ ማንነቱ የጥቃት መነሻ ሆኖ፣ በብሔር ፖለቲካ አፉን ያሟሸ ሁሉ የሚዘምትበት ሆኗል፡፡ ዛሬ ደግሞ ይህ ስሁት ትርክት መሬት ረግጦ፣ የዘር ማጥፋት ዓላማ ያለው ጦርነት ታውጆበታል፡፡
መቼም፣ አማራነትን የቡድን ስሜት አድርጎ መውሰድ ከተጀመረ (ያውም ገና ነው…) ከአንድ እጅ ጣት አይበልጥም፤ የእነ ዋለልኝ ፍረጃ ግን ከሃምሳ ዓመት ይቀድማል፡፡
እውነታው፣ ትላንትም ሆነ ዛሬ የአማራ ሃጢያቱ ራሱን ረስቶ ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነት የላቀ ዋጋ መክፈሉ ነው፡፡ አማራ የሀገር እንጂ የሥርዓት ዘብ አልነበረም፡፡ ይሄ በዘመናት መካከል የማይፋቅ ገድሉ በብዙዎቹ የውጭ ኃይሎች ዘንድ በጥላቻ እንዲታይ አድርጎታል፡፡ በዋለልኝ በኩል የቀረበው ወረቀትም፣ የጥላቻው ውጤት ነበር፡፡
በአስተዳደራዊና ተፈጥሯዊ ችግሮች በተጽዕኖ የሚኖረውን ሕዝብ ‹ጨቋኝ› የሚል ፍረጃ መስጠት ምንጩ ከፍ ሲል ጸረ-ኢትዮጵያ እና ጸረ-አማራ የሆነው የባሮን ፕሮችስካ አስተሳሰብ ተሸካሚ መሆን፤ ዝቅ ሲል ደግሞ አካባቢን በጥልቀት ካለመፈተሽና ጥራዝ ነጠቅነት ጋር ይያያዛል፡፡
ይህን ተከትሎም፣ ለዘመናት “አማራ እና የኦርቶዶክስ ክርስትና ጠላቴ ናቸው” በሚል ሲያሴር የነበረው የውጭ ኃይል ምቹ ዕድል አግኝቷል፡፡ ለእነዚህ ኢትዮጵያ-ጠል ኃይሎች ‘ትሮጃን ሆርስ’ ሆነው የተሰለፉት ደግሞ ግራ-ዘመሙን አስተምህሮ ዶግማ አድርገው ያከረሩት የያ-ትውልድ አባላት ናቸው፡፡ እዚህ ጋ ነው፣ ምዕራባውያን ታሪክ ጸሐፊዎች “ኢትዮጵያ ቅኝ-ገዢን በጦር ግንባር ብታሸንፍም፣ በትምህርት ቤት ክፍሎች ውስጥ ተሸነፈች” ሲሉ መሳለቃቸውን የምናነበው፡፡
በወቅቱ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ የተረዱ በኢትዮጵያ የነበረውን ችግር የአካባቢያዊነት ችግር (the problem of regionalism) ነው በማለት፣ አካባቢያዊነትንና የመገንጠል እንቅስቃሴዎችን በማውገዝ የተራማጆች ዋነኛው ትኩረት በመደብ ትግል ላይ መሆን እንዳለበት አጽንኦት በመስጠት መታገል እንደሚገባ ቢከራከሩም፣ የዋለልኝ ዘዋሪዎች የ‹ጨቋኝ-ተጨቋኝ› ትርክት በመሸከም የኢትዮጵያን ፖለቲካ አወሳሰቡት፡፡
ተማሪው ቆዳውን ዘልቆ ባልገባው ጥራዝ ነጠቅ ማርክሳዊ ርዕዮተ ዓለም እየተመራ፣ “የብሔረሰብ ጥያቄ”ን በተለመከተ ወደአደገኛ አቅጣጫ ገፋው፡፡ ቁንጽል በሆነ መረዳቱ በመዋቅራዊ መሻሻሎች መጠገን ይችል የነበረውን የአገሪቱን የተዋረሰ ማህበራዊ ህሊና አናግቶ፤ ቅጥ ያጣ ሥር-ነቀላዊነቱ የዛሬዋን ‹‹የኢትዮጵያ አዕምሮ›› ፈጥሯል፡፡
ፖለቲካው በሐሰት የታሪክ ትርክት ላይ ያረፈ በመሆኑ፣ በሕዝብ መስተጋብርና ሐገር-ምሥረታ ታሪክ ስር ቅራኔ ሲፈለፍልና እሱን ማታገያ ሲያደርግ ኑሯል፡፡ ዐማራውን ‹‹በዳይ›› ሌላውን ‹‹ተበዳይ›› አድርጎ የሚያቀርበው ይህ ሐሳዊ ትርክት፣ ‹ዳይኮቶሚውን› ለመፍጠር በሀገሪቱ የሚገኙትን ማኅበረሰቦች ማኅበራዊ ዕድገት በማጋነን፣ የስታሊንን “የብሔረሰቦች ንድፈ-ሐሳብ” በግድ እንዲሠራ ለማድረግ የፈጠራ ታሪኮች ተፈጥረዋል፡፡
ይህም የፖለቲካ ፍልስፍና ድህነት ተክሎ፡- በቁስ ሰቀቀን የታወረ፣ በማሰብ ብቃቱ የቀነጨረ የፖለቲካ ‹‹ልሂቅ›› ፈጠረ፡፡ አማራን እንደሕዝብ ማጥቃት ፖለቲካ ሆነ፡፡ ይህ የግማሽ ክፍለ ዘመኑ ‹‹የኢትዮጵያ አዕምሮ›› ሆኖ ታይቷል፡፡ በዚህ ሂደት የብሔረሰብ ጥያቄ ለጸረ-አማራ እና ጸረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች መጠቀሚያ እንዲሆን ቀዳዳ ተበጀለት፡፡
ሁለቱ ደቂቀ-ዋለልኝ…
በጽሑፌ ርዕስ ላይ “ዋለልኝ ዳግም ሞቷል!” ወደሚል መደምደሜያ የገፋኝ ሁለቱ የግማሽ ክፍለ ዘመን የብሔርተኝነት ግንባታ ልምድ ያላቸው ኃይሎች፣ አሁን ላይ የተከፋፈሉበት ደረጃ ነው፡፡ ለዚህም፣ ወያኔ እና ኦነግ-ኦሕዴድ ‘ከእኛ በላይ የሚወክለው ላሳር’ ሲሉት የነበረው የትግሬ እና የኦሮሞ ፖለቲካ ያለበትን ሁኔታ እንደማሳያ መጥቀሱ በቂ ነው፡፡
ሁለቱም በወጡበት ሕዝብ ፊት እንደ “ብሔር” መቆም ተስኗቸው፣ በውስጣቸው ተጠፋፊ ገዥ መደብነት ተፈጥሯል። ፍትጊያው በዚህ መሃል ነው።
ይህ ደረቅ ሀቅ ደግሞ፡- በኢትዮጵያ ዐውድ ገዥ መደብነትን የተንተራሰ ‹ነባር ኦሊጋኪ› እና ዐዳዲስ ‹ጥገኛ ኃይሎች› የሚያደርጉት ፉክክር እንጂ፣ ትርጉም የሚሰጥ የ”ብሔር ትግል፤ ሕይወት ያለው የብሔር እንቅስቃሴ” የለም ወደሚል መደምደሚያ ይገፋናል፡፡
(በነገራችን ላይ፣ የትግሬ አሁናዊ ሁኔታ የድኀረ-ግጭት ኹነት ያመጣው ሳይሆን፣ የዋለልኝ ዳግም ሞት ምልክቶች ናቸው፡፡)
ከስብሃት ነጋ እስከ ሌንጮ ለታ፣ ከመለስ ዜናዊ እስከ ዳውድ ኢብሳ፣ ከዳንኤል ብርሃኔ እስከ ጃዋር መሀመድ… የሚዘረዘሩ ሃሳዊ ነብያቶች (ደቂቀ-ዋለልኝ) የሰበኩት አስተምህሮ የወፈፌውን ዐቢይ አሕመድ ብልጽግናን (a.k.a. ዘመነ-ኦሮሙማን) አዋልዷል፡፡ (ልብ አድርጉልኝ! የአማራ ልሂቃንን የማልጠቅሰው ትግሉ ሀገረ-መንግሥቱን የመካድ ሳይሆን፤ ሕልውናን ማስከበር፤ለሀገረ-መንግሥቱ በጋራ የመቆም ትግል በመሆኑ ነው፡፡)
የሁለት ሀገረ-መንግሥት መንታ ልብ ይዘው የተነሱት ሁለቱም ኃይሎች፡- የሚራመዱበት መንገድ፣ በሀገረ-መንግሥቱ ኑፋቄ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ፣ ትላንት ትግራይን አግዝፎ ኢትዮጵያን አሳንሷል፤ ዛሬ ‹‹ኦሮሚያ››ን ከአናት፣ ኢትዮጵያን ደግሞ እንደ ቁማር ካርታ ጨዋታ ከስር (ከቂ*) አስገብቷል፡፡ “ታሪክ ገፍቶናል” ይሉበት የነበረው ጩኸት ቀጥታ ትርጓሜውም፣ ተረኝነት እንደሆነ ያለፉት ስድስት ዓመታት በግላጭ አሳይተውናል፡፡
የተከዜ-ማዶ ልሂቃን “ትግራይ ሲም ካርድ፤ ኢትዮጵያ ቀፎ” ነች እንዳሉት ሁሉ፤ የአባ-ገዳ ልጆችም “ኦሮሚያ ዲጂታል፤ ኢትዮጵያ አናሎግ” ለማለት ብዙ ጊዜ አልፈጁም፡፡ ይህ ከኑፋቄም በላይ ነው!
የአዲስ አበበ፣ ድሬደዋ እና ሐረር ዲሞግራፊ በብርሃን ፍጥነት የተቀየረው “መደመር”፣ (በ17ኛው ክፍለ-ዘመን አጠራር “ወረራ”) በሚሉት ስልት ነው፡፡ እኔን ከተጠራጠርክ፣ መለስ ብለህ የገዳ ሥርዓት ሃቲት በራሳቸው ልሂቃን ከተጻፉ ድርሳናት አንብብ፡፡
ዐቢይ አሕመድ፣ ሰሞኑን ስለ ዶሮ ወጥ ያወራውን እንደ አቩካዶውና እና ሙዝ-በዳቦው ጉዳይ አቅልለህ ካለፍከው ግን፣ ‘የብሔር ፖለቲካ አልገባህም’ ብዬ እዳፈርሃለሁ፡፡
ከላይ ከጠቀስኩት ከዋለልኝ ጽሑፍ አንዱ ጭብጥ፡- “ጥሩ ኢትዮጵያዊ ለመባል የእነሱን ዶሮ ወጥ መበላት አለብህ!” የሚል ነውና፡፡ ለአንድ ሀገርም ሆነ ብሔረሰብ አመጋግብ ዋንኛው የባህል መገለጫ ነው፡፡ እንጀራ በዶሮ ወጥ ደግሞ ከአማራ አልፎ፣ የኢትዮጵያ የባህል ምግብ ከሆነ ዘመናት መቆጠሩን ‹የበሻሻው ማንጁስ› Abiy Ahmed Ali
ጠንቅቆ ያውቀዋል፡፡
እናሳ፣ ዐቢይ ‘የአማራ የባህል ምግብ ነው’ ብሎ የፈረጀውን የዶሮ ወጥ አንኳስሶ፣ ‘በኬኒያ ጎዳናዎች ተጠብሶ እንደሚቸበቸበው አድርገህ በዳቦ ብላ’ ያለው ለምን እንደሆነ እየተገብባን ነውን…?!
እመነኝ፣ መቼም ቢሆን “ገንፎ”ን፣ አልያም “ጭኮ”ን እንዲህ ሲያጣጥል አታገኘውም፡፡ በጭራሽ!
ስለ-ባህል ከተነሳ አይቀር፣ ወያኔ አሸንዳን የፌደራል መንግሥቱ ክብረ-በዓል ልታደርገው ከጫፍ ደርሳ የነበረው፣ ‘ነባሩን (የብዙሃኑን) ነቅለህ፣ የራስህን ተካ’ በሚለው ዋለልኛዊ አስተምህሮ እንደሆነ ሳልጠቅስ ማለፍ አልችልም፡፡ (ዋለልኝ በወረቀቱ ‹የአማራ እና ትግሬ› እያለ የጠቀሰውን ፍቀው፣ በአማራ ላይ መከመራቸውን ያስታውሷል!)
ኦሕዴድ-ኦነግም በአንድ በኩል፣ ‘መስቀል ዐደባባይ ላይ የዳመራን በዓል ስታከብር አለበበስህን እኔ ነኝ የምወስነው’ እያለ፤ በሌላ በኩል፣ ኢሬቻን ከደብረ ዘይት ወደ መስቀል ዐደባባይ (ከ‹‹ሆራ አርሰዲ›› ወደ ‹‹ሆራ ፊንፌኔ››) አዛዋውሮ ሲያበቃ፤ ከድፍን ኦሮሞ ‹‹ክልል›› የሰበሰባቸውን ሰዎች የጉዞ፣ ምግብ፣ ምኝታና አበል ወጪ ከአዲስ አበባ ግብር ከፋይ ሕዝብ ከሚገኘው ከክፍለ ከተማ እና ወረዳ በጀት ላይ ያደረገው ከዋለልኛዊው እሳቤ ቀድቶ ነው፡፡
አንባቢ ሆይ!
“ሕዳር 29 የብሔር ብሔረሰቦች ቀን” ተብሎ በሕገ-መንግሥት ጭምር የተደነገገው ለምን ይመስላችኋል?
ነገሩ እንዲህ ነው፣ …ከዕ’ለታት አንድ ቀን መለስ ዜናዊ እና ሌንጮ ለታ ከቀይ ባሕር ደሴቶች በአንዱ ዳርቻ ተቀምጠው ደርግን ከገረሰሱ በኋላ ስለሚያነብሩት ሥነ-መንግሥት ባህሪያት እየተወያዩ ነበር፡፡ ኢትዮጵያን በዘር መከፋፈል፣ አማራን ከሜንስትሪም ፖለቲካ ማፈናቀል፣ በመላ ሀገሪቱ እያሳደድን እረፍት መንሳት፣ የኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያንን፡- በብሔረሰብ ከፋፍሎ አያሌ ፓትሪያርክ ሾሞ-ማዳከም፣ የብሔረሰብ መብትን እስከ መገንጠል መለጠጥ… እያሉ እያወጉ ነው…
በዚህ መሃል ድንገት፣ አማራ ሆኖ ‹‹አማራ ጨቋኝ ነው›› የሚል የመምቻ መዶሻ ተቀብሎ-ያቀበላቸውን ልጅ አስታወሱ … “መታሰቢያ” ሊሰይሙለት ቃል ተገባቡ፡፡ አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ፣ ዋለልኝ መኮንን አውሮፕላን ሲጠልፍ ከእነ ጀሌዎቹ የተገደለበትን ህዳር 29ኝን (1964 ዓ.ም) ቀን ተጠብቆ የሞት መዝገብ የሆነው ‹‹ሕገ-መንግሥት›› እንዲፀድቅ ተደረገ፡፡
ከዐመታት በኋላ ደግሞ ይህ ቀን (ሕዳር 29ኝን) “የብሔር ብሔረሰብ ቀን”በሚል በዐል ሰየሙበት፡፡
ምንም እንኳን ሕዳር 29 ቀኑ፣ ትላንት ለትግሬ፣ ዛሬ ለኦሮሞ ልሂቃን ሆነ እንጂ፣ ለሌላው ከቡድን ጭፈራ የዘለለ ነገር ባይኖረውም ቅሉ፤ የወያኔ-ኦነግ ፖለቲካዊ ወልፈንዴነትን እና የሕገ-አራዊታቸው አንቀፆች እንዴት እንደተቀመሩ ይገልጥልናል፡፡
“ዋለልኝ መኮንን ዳግም ሞተ!” ያሉኩበትን ዐውድ በቀጣዩ ክፍል አመለስበታለሁ፡፡