በመጀመሪያ ፈጣሪ አዳምን ፈጠረ ። ቀጠለና ሔዋንን ፈጠረ ። አዳምም ሔዋንን ሴት አላት ። ከእርሱ ቅንጣት አጥንት ተወስዳ ተፈጥራለችና !ሴት የቀጣዩ ትውልድ እናት መሆኗንን ልብ በል ። አዳም ግን ሌላ ሥም አልነበረውም ። ሌላ ቅፅል ሥም የለውም ።
አዳምና ሄዋን ከገነት በጥፋታቸው ምክንያት ፣ ተባረው በምድር ላይ ጥረውና ግረው እንዲኖሩ ፈጣሪ ብይን ሢሰጥ ፣ በሴት አማካኝነት ምድርን እንደሚሟሏት አሥቀድሞ ሥለሚያውቅ ነው ። ይኽ ማለትም ፈጣሪ ሰውን የሚፈጥርበትን ኢንዱስትሪ በሴት አካል ውሥጥ በመፍጠር አዳምና ሔዋን እንዲበዙ ጥርጊያ መንገዱን አመቻምቾ ነበር ማለት ነው ።
እናም በአዳምና ሄዋን ለመጀመሪያ ጊዜ ፣ አቤልና ቃዬን ተወለዱ ። ከአቤልና ቃዬን በኋላ የተፈጠሩ ብዙ ልጆች ናቸው ።ዛሬ እነሱ አድገው ነው ፣ እርስ በእርስ ተጋብተው ና ተዋልደው ምድርን የሞሏት ። ሴትና ወንድ የምትወልደው ሴት ናት ። …
ሴት የዚች ዓለም ሰው ሁሉ ፈጣሪ ናት ። ሴትን ፈጣሪያችን ባይፈጥር ኖሮ ፣ ማንኛችንም ወደዚች ምድር ለመምጣት አንችልም ነበር ።
ሴት ይኽንን ያህል ከፍታ ካላት ፣ በዓለም ላይ ለምን ተገቢውን ክብር አልተሰጣትም ። ለምን እሥከ 1977 ዓ/ም ድረስ የተባበሩት መንግሥታት የሴትን እኩልነት ና መብት ለማክበር ጊዜ ወሰደበት ? የማርች 8 የሴቶችን ትግል ማሰቢያ ቀን እንዲሆን የወሰነው በዚህ ዓመት ነው ።
ሴቶች እኮ በአሜሪካ በ1909 እኤአ ከፍተኛ የእኩልነት ትግል አድርገዋል ።ከአሜሪካ ሴቶች ተሞክሮ ተነስተው በጀርመን ሶሻሊሥት እንቅሥቃሴ ውሥጥም 1910 ዓ/ም እኤአ ሴቶች ጉልህ የትግል ተሳትፎ አድርገዋል ።
አብዛኛው የሴቶች ትግል ፣ እኩል የሥራና የትምህርት ምህዳሩ ለሴቶች የጠበበ መሆንን ና የጉልበት ሥራ በረከሰ ዋጋ መሥራታቸውን ፤ የቤት ውሥጥ ጭቆናን ፣ ባርነትን ፣ የፖለቲካ ተሳትፎ ውሥንነትን ፤ የመሪነት ተሳትፎ መጥበብን አሥመልክቶ የተደረገ ና ዛሬም እየተደረገ ያለ ነው ።
በሩሲያ በማርች 8 /2017 ዓ/ም በፔትሮግራድ ታላቅ ሠላማዊ ሰልፍ አድርገው ነበር ። ይኽ ሠላማዊ ሰልፍ የአንደኛው የዓለም ጦርነትን ተከትሎ በተከሰተው ርሃብ የተነሳ የተከናወነ ነው ። በሰልፉ ላይ የያዙት መፈክርም ” ሠላምና ዳቦ ! ” የሚል ነበር ።
”
ሴቶች በጦርነት ሰበብ በሚከሰተው ምሥቅልቅል ግንባር ቀደም ተጎጂ እንደሆኑ ይታወቃል ። ቤተሰቦቻቸውን ፣__ ልጆች ና አዛውንት አባትና እናቶቻቸውን ፤ ወዘተ ። ለመመገብ እንዴት እንደሚቸገሩ በሚገባ ያውቁታልና ሰላማዊ ሠልፍ መውጣታቸው አያሥገርምም ።
ተመልከቱ ፈጣሪ ያሳያችሁ ፣ የጦርነት ጥንቡሳስ ፣ ዛሬም ዓለምን እየለበለባት ነው ። በእኛ አገር ጦርነቱ ያሥከተለውን የሰው እልቂት ፣ በአማራና በአፋር ያፈናቀለውን እና ያወደመውን ሀብት ና ንብረት መለሥ ብሎ መቃኘትም ፣ ከቀጣይ የሞኝ ጦርነት ና ከእናት ጭንቀት እንደሚታደግ እወቁ ።…
በአንክሮ ከመመልከት ተሻግራችሁም ፣ በዩክሬን ኮመዲያኑ ዘሌኒስኪ ያለአዋቂነቱ ያሥከተለውን ጥፋት ብተገነዘቡም መልካም ነው ። ዜሌኒሥኪ ሩሲያን ለማጥፋት ከአሜሪካ ጋር መሻረክ አልነበረበትም ። ሩሲያ ጎረቤቷ ከአሜሪካ ጋር ተሻርኮ ሊያጠፋት በማቀዱ የተነሳ ፣ ደጋግማ ይቅርብህ እረፍ ብላለች ። ኮመዲያኑ ና የፊልም አክተሩ ዜሌንስኪ ግን የገሃዱ ዓለም እውነት ፊልም መሥሎት ከኃያላኗ ሩሲያ ጋር ተጋጭቷል ። በዚህም ጥፋቱ ዩክሬንን አፈራርሷል ። ከ3 ሚ በላይ ዜጎችን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏል ። ሩሲያ ግን የዩክሬንን ከፍተኛ ኃይል ማመንጫ የኒኩለር ጣቢያዎችን በመያዝ ድሏን አረጋግጣለች ። እናም ” እረፉ ! ከእኔ ጋር መጋጨት ፣ በእሳት መጫወት ነው ። ” በማለት ደጋግማ እያሥጠነቀቀች ነው ። ይኽንን መሥጠንቀቂያዋንም ሲአይ ኤ በቅጡ በመገንዘብ ” በይደን ሆይ ይቅርብህ ! ” በማለት ምክሩን ለግሷል ። ማንም ኃያል መንግሥት ከዜሌንሥኪ ጋር እንደማይቆም ቀድሞም የታወቀ ነበር ። ምክንያቱም ባለፈው ፅሑፌ እንደጠቆምኩት ሦሥተኛ የዓለም ጦርነት ብሎ ነገር እንደማይኖር ኒኩለር የታጠቁ ሁሉ የተገነዘቡ ይመሥለኛል ። የፈረንሣይን ከሩሲያ ጋር መቆም ተመልከት ። በእሳት ላለመጫወት የሩሲያን የአደጋ ሥጋት ተገንዝበው ሌሎችም የእሷን ፈለግ ቢከተሉ መልካም ነው ። ደግሞም አሜሪካ ሥንትና ሥንት ኪሎሜትር አቋርጣ በየሰው አገር ጣልቃ የምትገባው ፣ ለዜጎቼ ህልውና ያሰጋኛል ። አሸባሪነትን ከጥንስሱ ቦታ ሄጄ በመዋጋት ማጥፋት አለብኝ በማለት እንደሆን አንዘንጋ ። የሩሲያ ሥጋትም ከአሜሪካ ያላነሰ እንደውም የላቀ መሆኑ መታወቅ አለበት ።
የእኛ አገር በሥጋ ና በውሥኪ የሚቃዡት 1% ፖለቲከኞቻችንም ከዚህ እውነት አንፃር ፣ ቅጥረኝነታቸውን ለማቆም የሚያሥችላቸውን እውነተኛ ልብ ቢገዙ መልካም ነው ። በፍቅር የተሞላ ልብ የኢትዮጵያ እናቶች ዘንድ አለ ። ከእነሱ ሃዘን እና ዋይታ በፀፀት የሚሸምቱትን ነፁህ ልብ ያገኛሉ ። ይኽንን ንፁህ ልብ አልሸምትም ካሉ ግን ” እነዚህ ለማይጠረቃ ሆዳቸው ብለው ጎሣን እና ቋንቋን የሙጥኝ ያሉ ፖለቲከኞች ሥለፖለቲካ ጥልቅ እውቀት የላቸውም ። ልክ እንደ ፊልም አክተሩ ዘለንስኪ የገሃዱ ዓለም የህዝብ ሰቆቃ ። የሴት አህቶቻችን ፣ ልጆቻችን እና እናቶቻችን ለቅሶ ተከታታይ ፊልም እንጂ እውነት አይመሥላቸውም ። ” ብለን ለመደምደም እንገደዳለን ። የሴቶችን ቀን ያከበሩትም ትርጉሙ ሳይገባቸው ፣ እልም ባለ ድንቁርና ነውና ሊያፍሩ ይገባቸዋል ።