ረቂቅ ነገሮችን በምሳሌ እያነሳሱ መወያየት እንዴት ጠቃሚ መሰላችሁ?። ምሳሌ (analogy) በሰዎች ህይወት ውስጥ ትምህርትን ለረጅም ጊዜ ጠብቆ የሚያቆይና ረቂቅ የሆነ ሃሳብን ግዘፍ ነስቶ በአእምሯችን በቀላሉ እንድናየው የማድረግ ልዩ ሃይል ያለው ነገር ነው። ታዲያ ዛሬ ከአንድ የጥንት ታሪክ በተለይ ስለ ተግባቦት ወይም ስለ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች የምንማረው ነገር ትውስ ባለኝ ጊዜ ከወገኖቼ ጋር ለመወያየት ተነሳሁ…………።
መቼስ በታሪክ ስለሚነሳው የባቢሎን ግንብ ጉዳይ ሁላችን ሰምተናል። በጥንት ጊዜ የሰው ልጆች ኮሙኒኬሽን ጠንካራ ነበር። ተግባቦታቸው ሃያል ነበር። ይሁን እንጂ ከእለታት እንድ ቀን እንድ ሰው ድንገት ተነሳና ኢንዲህ ሲል መከረ
ጎበዝ አንድ ነገር ታየኝ አለ ለማህበሩ አባላት ሁሉ
ወንድማችን ሆይ! ምን ታይቶህ ነው እስቲ እባክህ አካፍለን? አሉት የማህበሩ አባላት በጉጉት ……
የሸክላ ጡብ እንስራና አንድ አስከ ሰማይ የሚደርስ ግንብ እንገንባ፣ ከዚህ ከምናየው ደመና በላይ ከደረስን የመንግስተ ሰማያት በር ላይ ደረስን ማለት ነው። ይህ ስራችን ከኣምላክ ያጎራብተናል። ከዚህም በላይ ኣሻራችን ሁሉ ዘመን ተሻጋሪ ይሆንና ትውልድ ሁሉ ሲያደንቀን ይኖራል……………. አለ።
በዚህ ሃሳብ ብዙዎች ተገዙና ጭብጨባው ቀለጠ። ግጥም ተገጠመ፣ ዘፈን ተዘፈነ፣ ካርታ ተሰራ፣ ኣሰሪና ሰራተኛ ተለየ፣ የስራ ክፍፍል ተደረገ። ባቢሎን የድንጋይ እጥረት ስላለባት ጡብ ማምረት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነበርና በአንድ በኩል ጡብ የሚያመርት ሰራዊት በሌላ በኩል የተመረተውን ጡብ የሚገነባ ሰራዊት ተገነባና ይህ ሰራዊት ጎን ጎን ስራውን አጦፈ፣ ግንቡ ተጀመረ……..። በብዙ ድካም ግንቡ ከፍ እያለ መጣ…….። በዚህ ስራ ላይ የማይሳተፍ የለም ተባለ………። ህዝቡ በሚችለው ሁሉ ያለውን ይወረውራል…….። ግንበኞች ማታ ማታ አረፍ ሲሉ ፓርቲ እያደረጉ ይደንሳሉ…………። የባቢሎን ግንብ በእንዲህ ኣይነት ሁኔታ ትንሽ ከገፋ በኋላ የነዚህ ሰዎች ፍላጎት (motive) እግዚኣብሄርን ከሰማይ እጅግ አስከፋው። ታዲያ አምላክ ሲከፋው ጊዜ እርምጃ መውሰድ ፈለገ። ይህ ርምጃ የሰራተኛውን ኮሙኒኬሽን መምታት ነበር። ስለሆነም ግንበኞች በስራ ላይ እያሉ ድንገት ቋንቋቸው ሁሉ ተደበላለቀባቸው። ግንቡን የሚሰሩ እልፍ ሰዎች አዲስ በመጣው የኮሙኒኬሽንና ተግባቦት ችግር ትርምስ ውስጥ ገቡ። ከላይ ከግንቡ ጫፍ ላይ ያለው ዋና ግንበኛ ከታች ያለውን ሰው እስቲ እባክህ ጡብ አቀብለኝ ሲለው ይሄኛው ከታች ያለው ሰው ጭቃ ያቀብለው ጀመር። ኣንዱ ውሃ ሲጠይቅ ሌላው ጡብ ይወረውርለት ጀመር። አንዱ በዚህ በኩል ሳብ ሲል ሌላው በዚያ በኩል ይጎትታል። መደማመጥ፣ መግባባት የሚባል ነገር በድንገት ከባቢሎን መንደር ተነነ………….።
የግንበኞች ቁጣና ንዴት ተበራከተ። አንዳንዶች እርስ በርስ ተደባደቡ። ሌሎች ንግግር አቁመው ኩርፊያ ውስጥ ገቡ። ጭቃ አቀብለኝ ስልህ ጡብ እያቀበልክ ትቀልዳለህ ወይ? የምንሰራው ስራ የሁላችንም ኣይደለም ወይ? እያሉ ሁሉም ያጉረመርማሉ። ነገር ግን እንዱ ያንዱን ልሳን አልረዳው አለ። ግራ መጋባት በዚያ ግንብ ዙሪያ ሰፈረ። ይሄኛው ሰው የሚለውን ያኛው ኣይሰማም። ትርምስና ጥል ክርክር ሲበዛ ኣንዳንዶች የሰሩትን ጡብ እየፈነቃቀሉ ጨዋታ ፈረሰ ዳቦ ተቆረሰ ኣይነት ትርምስ ውስጥ ገቡ። የባቢሎን ግንብ በኮሙኒኬሽን ምክንያት ሳይሳካ ቀርቶ እነሆ የተረት የተረት ሆኖ ቀረ……….።
ከዚህ ምሳሌ የምንማረው ነገር ብዙ ነው። የሰው ልጅ በሚመሰርታቸው ትናንሽ ማህበሮች ብቻ ሳይሆን እስከ ትልቁ ማህበር ማለትም እስከ ሃገራዊ ማህበራችን ድረስ ኮሙኒኬሽን የኑሮዎቻችን ሁሉ የጀርባ አጥንት ነው። አንድ ማህበር የኮሙኒኬሽን ችግር ከገጠመውና ቋንቋው ከተደበላለቀ የሚሰራውን ስራ ሁሉ ከግብ ኣለማድረስ ብቻ ሳይሆን የሰራውን ሁሉ ሊያፈርሰው ይችላል።
እንደ ህዝብ ከእቁባዊ ማህበራችን ጀምሮ የግንኙነቶቻችን፣ የመረጃዎቻችን ጥራት የማህበራችንን ኣላማ ለመፈጸም የሚኖረንን የሃይል መጠን ይወስነዋል። በተለይ ደግም ትልቁና ወሳኙ ሃገራዊ ህብረታችን ከፍተኛ የኮሙኒኬሽን ጥራት ያስፈልገዋል። መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር የሚገናኝበት መስመር ላይ የቋንቋ መደበላለቅ ካለው፣ ኪሳራው ከባድ ነው። መሪዎች የቋንቋ መደበላለቅ ከገጠማቸው የሚገነቡት ነገር ኣይኖርም። መንግስት ለህዝቡ የሚሰጠው መረጃና በየጊዜው የሚተገብራቸው ተግባራት ተጠይቅን (logic) የማይጠብቅ ሲሆን ህዝቡ በሃይል ግራ ይጋባል። ከፍተኛ ግራ መጋባት ሲሰፍን ደግሞ ቁጣና እልህ ማህበራችንን ያምሳል። የባቢሎን ሰዎች ከፍ ካለው ጋር ስለተጋጩ ኮሙኒኬሽናቸው ተመታ።
ዜጎች ከፍተኛ የዴሞክራሲና የፍትህ መርሆዎችን ማመሳከሪያ እያደረግን የመንግስትን ተግባራትና መረጃዎች መተንተን የዜጎች መብትና የሚጠበቅ ነው፣ በዚህ ጊዜ የመንግስት የቀን ተቀን ተግባር ጥያቄ ለማኝ ሲሆን ኮሙኒኬሽን አደጋ ላይ ወደቀ ማለት ነው። ለዴሞክራሲያዊ መርሆዎች የማይገዙና የሚፋለሱ ድርጊቶችን ስናደርግ፣ ላጠፋነው ጥፋት የምንሰጣቸው ምላሾች ኣሳማኝ ያልሆኑ ምክንያቶችን ስናቀርብ፣ አንዱ መግለጫ ከሌላው ሲላተም ከህዝብ ጋር የሚኖረን ኮሙኒኬሽን ተበላሸ ቋንቋ ተደበላለቀ ማለት ነው። በመንግስትና በህዝ በመግስት ሰዎች መካከል ባቢሎን ፈጠርን ማለት ነው። መንግስት ተጠይቆችን የማይጠብቅ ነገር ሲያደርግ ህዝብ ሁል ጊዜም መንግስት ይህን ፈቶ ይህን ለምን አሰረ…..፣ ይህን አስሮ ይህን ለምን ፈታ…… ይህን አንስቶ ያንን ለምን ጣለ፣ ያንን ጥሎ ይህንን ስለምን አነሳ…… ። እያለ መላ ይመታል። የመንግስትን ስራዎች በሚዛኑ ይለካቸዋል። ወደድንም ጠላንም የሪፐብሊክ ዘመን እንደዚህ ነውና። ስለዚህ መንግስት የተግባር ቋንቋውም ሆነ መግለጫዎቹ የሚጣረሱና የሚፋለሱ ሲሆኑ በህዝብና በመንግስት መካከል የባቢሎን ነገር ተፈጠረ ማለት ነው። ከተለያዩ ባለስልጣናት በአንድ ጉዳይ ላይ ተለያየ መግለጫ ከወጣ በዚያ መንደር ባቢሎን ተፈጠረ ማለት ነው። ይህ ደግሞ ህዝብን ግራ ያጋባል። ማህበርን በመላምት ብዛት ያደናግራል። ለነገሩ መንግስት ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከህዝብ ጋር የሚኖራቸው የኮሚኒኬሽን ጥራት በህዝብ ዘንድ የሚኖራቸውን የቅቡልነት (legitimacy) መጠን ይወስነዋል። ከፍ ያለውን መርህ የጣሰና የተጣረሰ ስራ ስንሰራ ህዝቡ ከመርሆዎች ኣንጻር እያነጸረና ከተጠይቆች ኣንጻር አየመዘነ ያቀለናል። ኮሙኒኬሽን እጅግ በጣም ወሳኝ የሆነ መስመር ነውና ስለሃገር ሲባል ሁሉም ማህበራት መጠንቀቅ ኣለባቸው። ከፍ ሲል እንዳልኩት በተለይ መንግስት በየእለቱ በሚያደርጋቸው ነገሮች ህዝቡን ግራ ማጋባት የለበትም። በቅርቡ አንዱ ሰው ግራ መጋባቱን እንዲህ ሲል ገለጸ። ጀነራል ባጫ ከጥቂት ቀናት በፊት የሙሉ ጀነራልነት ማእረግ አገኙ የሚለውን ዜና አጣጥሜ ሳልጨርስ አሁን በሳምንቱ አምባሳደር ተባሉ የሚል ዜና እያየሁ ነው ግራ አጋቢ ነው በውነት ይላል። ሌላው ደግሞ የዛሬ ሳምንት እንዲህ ተብለን ነበር ዛሬ ደግሞ ይሄ ሆነ ምን እየሆነ ነው? አያለ ይደመማል ……..። የመንግስት ባለስልጣናት መግለጫዎች እርስ በርስ ይጋጫሉ፣ ምንድን ነው ነገሩ? የሚሉ ድምጾች ሲበዙ በጋራው ቤታችን ባቢሎናዊ ኮሙኒኬሽን እየተፈጠረ መሆኑን ያሳያል። በተለይ መንግስት ለህዝብ የሚቀርቡ ነገሮችን በጥራት ማቅረብ ካልቻለ፣ ለሚፈጽማቸው ነገሮች ሁሉ ተጠይቁን የጠበቀና ጥራት ያለው ምላሽ ካላቀረበ፣ ስራዎቹና መግለጫዎቹ ከመርህ ጋር የሚጋጩ ከሆነ፣ ኮሙኒኬሽን ፈረሰ ማለት ነው። ይህ ደግሞ ሃገርን ከምንም በላይ ይጎዳል። ስለዚህ ባቢሎናዊ ኮሚኒኬሽኖች መወገድ አለባቸው። ከባቢሎን ወንዞች ማዶ ያለውን በጎ የኮሙኒኬሽን መስመሮች መናፈቅ ለዚህም መስራት ያስፈልጋል።
እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ