እንዲያውም ብዙም … ወደ የቅርብ ሩቅ የኋለ መለስ ብለን …፣ ልክ በ“ወንጀለኛው ዳኛ” መጽሐፍ በጉልህ እንደተመለከተው ሁሉ፣ምናልባትም ”ከወዳጅ ጠላት ያድን“፣ ”ልዩ ዋጋ ለማይከፍል ልዩ አስተያየት አያስፈልገውም“፣ “ከጠረጠሩት ክፉ ያልጠረጠሩትን መልካም መስማት ያስደነግጣል”፣ “የወደዱትን ሲያጡ የጠሉትን ይለማመጡ”፣ “ሞቴ ያሞማዋቴን ያህል አያሳዝነኝም”፣ “ድል ነስቶ መሸሽ”፣ “የህዝብ ድምጽ የግዜር ድምፅ …“ ዓይነት፣ በተለይም እንደ የተባበሩት አሜሪካ ስቴትስ አስተዳደርና ጋሻጃግሬዎቻቸው መልካም ነገር ያመጣሉ ብሎ ማሰብ … እጅግ በጣም አሳሳቢ እጅግ በጣም አስጊ እጅግ በጣም አደገኛ … የተሳሳተ የስሌት መላ ምት!!
እንደ አጠቃላይ፣ ብርቅ ዕፁብ ድንቅ ውድ ኢትዮጵያችን ዓውድ፣ በተለይም ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ጊዜ ያህል፣ ዓይነተኛ ሁነኛ የመፍትሔ መላ ባልተገኘለት፣ ከውስጥም ይሁን ከውጭ ኃይላት በሚወነጫጨፉብን፣ በፅንፍ ሰበዞች የተመረዘ፣ በተረኝነት አባዜ የተጠላላፈ እጅግ በጣም አደገኛ፣ የሴራ ፖለቲካ አዙሪት ማዕቀፍ ወስጥ ተተብትበን በመደነቃቀፍ ስንዳክር ስንደነጋገር ስንደፋደፍ ስንገፈታተር ስንታመስ ስንተረማመስ፣ ወዘተ፣ ይህ ነው ሊባል የሚችል ትርጉም ሠጪ የሆነ አዎንታዊ ለውጥ ማምጣት ያለመቻላችን ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ፣ ያፈጠጠ ያገጠጠ ጥሬ ሐቅ፤ እንዲያውም አያሌ መሥፈርቶች (በአስተዋይነት በትኩረት በጥንቃቄ በሉዓላዊነት በነፃነት ምድረ-ባህረ ነጋሽን (በአሁኑ የ“ኤርትራዊያን” ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን) ጨምሮ በአንድነት እና በመሣሠሉት ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን ለማስከበር በጥብቅ በቁርጠኝነት በጽናት በመከራከር በመሞገት) በኩል፣ ምናልባትም የኋልዮሽ ሊባል በሚችል ካልሆነ በስተቀር፣ …፤
በብዙሐኖቻችን ረገድ፣ በመሠረታዊ ማህበራዊ መሥተጋብሮቻችን (ግንኙነቶቻችን) በኩል፣ በሰላም በአስተዳደራዊ፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በውኃ፣ በመብራት፣ በፀጥታ በደህንነት፣ ወዘተ አገልግሎት ጥራት ረገድ፣ በተለይም ከህዝብ መጠን፣ ከዘመኑ የረቀቀ የሥልጣኔ (ዘመናዊ ዕውቀትና ተግባረዕደ) ደረጃ፣ ወዘተ ጋር በንጽጽር …፤ እጅግ በጣም ኋላ ቀር …፤ በአመዛኙ የካድሬዎች የጋሻጃግሬዎች የይስሙላ የድለላ የሽንገላ ትዕይንቶች መድረክ ካልሆነ በስተቀር፣ ትክክለኛ ነፃ ህዝባዊ ምክክሮችና ውሳኔዎችንም በተመለከተ፣ ገና በብርቅ በሩቅ … እንደተመኘናቸው ባጀን፤
እሺ እስኪ ሌላውን ሁሉ ትተን፣ ዓመታዊ የሰብል ግብርና ምርትን ብቻ፣ እንደ ዓይነተኛ ሁነኛ ማሣያ ብንወስድ እንኳን፣ ለአያሌ አሥርተ ዓመታት፣ ከዓመት ወደ ዓመት በነፍስ ወከፍ ተመን ከሁለትና ሦስት ኩንታል በላይ ዕመብዛም ያልተሻገረ … በነበረበት የመዳከር የዜሮ ድምር አዙሪት፤ የእንስሳትና የዓሣ ምርትም …፤ በየሣምነቱ በየቀኑ ማለት በሚቻል መልኩ፣ የዋጋ ንረት …፤
በውጭ ንግድ ረገድም እንዲሁ፣ ከዓመት ወደ ዓመት በዛ ቢባል ሦስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ብቻ የተወሰነ፤ ለንጽጽር ያህል፣ ብዙም ሩቅ መጓዝ ሳያስፈልገን፣ እንደ ታነዛኒያ፣ ኬንያና ዩጋንዳ የመሣሠሉት ሀገራት፣ በህዝብ ብዛት ወደ አንድ ሦስተኛ በዛ ቢባል ደግሞ አንድ ሁለተኛ ሲሆን፣ በገቢ ረገድ ግን፣ በየዓመቱ ከኢትዮጵያችን ከሦስት ዕጥፍ በላይ … ሩዋንዳም በአጭር ጊዜ …፤
የኢትዮጵያችንን ወቅታዊ የዲጂታል (በምጣኔ ሀብት ዙሪያ ልዩ ትኩረት) ስትራቴጂን በመቅረጽ ረገድ፣ ጉልህ የጥቅም ግጭት ያለባቸው እንደ እነ የቶኒ ብሌር ፈውንዴሽንና የመሣሠሉት ተቋማት በሁነኝነት በቅርብ ሩቅ ‘የሚቆጣጠሩት’ …፤
ብቻ ከወቅታዊ የተረኛ የአንዳፍታ መናኛ ቡድነኛ ወገንተኛ የታይታ የዝና ቱማታ ባለፈ፣ በመሠረታዊነት ይህ ነው የሚባል ዓይነተኛ ሁነኛ …፤
ከዚህ በላይ በተመላከቱት እጅግ በጣም ጥቂት ዋነኛ ጥቆማዎችን እና አያሌ ሌሎች ምክኒያቶችን ምርኩዝ በማድረግ፣ አጣዳፊዉንም የረዥም ጊዜዉንም በጣምራ፣ በሁሉም ግንባር ከመቼውም ጊዜ በላይ፣ እጅግ ልዩ በሆነ፣ በላቀ የአርበኝነት የቅንጅት ቁጭት ባለማሰለስ በብርቱ ለመረባረብ ‘የውዴታ ግዴታ’ አለብን ቢባል …!!
ሙሉጌታ በትረ ገብረማሪያም
ጥር ፬ ቀን ፪ ሺህ ፲፬ ዓ. ም.