በበላይነህ አባተ [email protected]
ተሰው ልጅ የሥነ ልቦና ቀውሶች ሁሉ የዝቅተኝነት መንፈስን የሚያህል አደገኛና እርኩስ መንፈስ የለም፡፡ የመንፈስ መፍዘዝ (ዲፕሬሽን) ያለበት ሰው ራሱን ሊያጠፋ ይችላል፡፡ ነገር ግን ሕዝብን ወይም አገርን አያጠፋም፡፡ የመንፈስ ጭንቀት ያለበት ሰው ለራሱ ወይም ለቤተሰቡ ሳይጠቅም ሊቀር ይችላል፡፡ ነገር ግን እምብዛም ሕዝብን ወይም አገር አይጎዳም፡፡ የመንፈስ ዝቅተኝነት የተጠናወተው ሰው ግን ተአገር አልፎም አሀጉርንና ዓለምን ሊያናውጥ ይችላል፡፡
የመንፈስ ዝቅተኝነት የተጠናወታቸው ጉዶች ወጣንበት የሚሉትን ሕዝብ በተረት ተረት ወሬ እያወናበዱ በስንት ሰማእታት ደም ስትጠበቅና ስትገነባ የኖረቸዋን ጥንታዊት ኢትዮጵያን “እናፈርሳታለን” እያሉ በአደባባይ ሲዝቱ ይታያል፡፡ የዝቅተኝነት መንፈስ አንድ ቦታ ስለማያስቀምጥና በተናገሩት ስለማያቆይ በዘጠነኛው ምላሳቸው ደሞ “ኢትዮጵያን ስንጠብቃት የኖረነው እኛ ነን” ሲሉ ይደመጣል፡፡ ታዲያ እነሱ ሲጠብቋት የኖሯትን አገር ለማፍረስ ዲያብሎስ ለምን እንደ መስክ አለሌ ይጋልባቸዋል?
እነዚህ ዲያብሎስ በመንፈስ ዝቅተኝነትና በምቀኝነት የሚጋልባቸው እርኩሶች ጠቢቡ ሰለሞን የፈተናትን አንዲት ዓይና አውጣና ምቀኛ ሴት ያስታውሱናል፡፡
የብሉይ ኪዳኑ መጽሐፈ ነገስት ቀዳማዊ ምእራፍ ሶስት እነደሚያስተምረው በጠቢቡ ሰለሞን ዘመን በአንድ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ሁለት ሴቶች በሶስት ቀን ልዩነት ውስጥ ልጆች ወለዱ፡፡ በኋላ የወለደችው ሴት ሌሊት ልጇን ተጪና ገደለችው፡፡ ይህቺ ልጇን የገደለችው ሴት በእኩለ ሌሊት ተነስታ የገደለችውን ልጇን እንቅልፍ ተወሰዳት ሌላኛው ሴት ጎን አስተኛችና የእሩሷ ያልሆነውን ልጅ ወሰደች፡፡ እንቅልፍ የወሰዳት ሴት ተእንቅልፏ ስትነቃ የሞተ ልጅ ተብብቷ ሥር አገኘች፡፡ ነገር ግን በብርሃን ስትመለከተው የእርሷ ልጅ የሞተው ሳይሆን ሴትዮዋ በጨለማ የሞጨለፈችው መሆኑን ተገነዘበችና ጉዳዩን ተንጉስ ሰለሞን ፊት ለፍርድ አቀረበች፡፡
ንጉስ ሰለሞን የሁለቱንም ሴቶች የይገባኛል ክርክር ታዳመጠ በኋላ “ልጁን ለሁለት ሰንጥቄ እኩል አካፍላችኋለሁ!” የሚል ፈታኝ ሐሳብ አቀረበ፡፡ እውነተኛይቱ እናት “ጌታዬ ሆይ ለእርሷ ስጣት እንጅ አትገድል” ስትል ንጉስ ስለሞነን ተማጠነች፡፡ ልጇን ተጭና የገደለችው ምቀኛ ሴት ግን “ይገደል እንጅ ላንቺም ለኔም አይሆንም ስትል” ዛተች፡፡ ንጉስ ሰለሞንም እውነተኛዋ እናት የትኛዋ እንደሆነች በዚህ ጥበብ ተገነዘበ፡፡
ኢትዮጵያ ተመተራ ትሙት በሚሉ የትኛውንም ሕዝብ በማይወክሉ ነገር ግን መንጋን በሚያደናብሩ ጥቂት ጭራቆችና ኢትዮጵያ ተመትራ ተምትሞት እኛ እንሙት በሚሉ ብዙሐን ክርክር ውስጥ ትገኛለች፡፡ ይኸንን ተመልክቶ በመለኮታዊ ፍርድ ተጭራቆች የሚገላግላት ጠቢብ ወይም የጭራቆችን የሰይጣን ሰይፍ የሚቀለጥምላት ብርቱ ኃይል ቅዱሳን መጻሕፍት የሚያወሷት ኢትዮጵያ በመጠባብቅ ላይ ትገኛለች፡፡
ዛሬም እንደ ጥንቱ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ ሰማይ ዘርግታለች፡፡
ነሐሴ ሁለት ሺ አስራ ሶስት ዓ. ም.