ዶ/ር በቀለ ገሠሠ ([email protected])
1ኛ/ መግቢያ፤
በዉስጥ ወድቀናል። ህዝባችን በእልፍ አእላፍ ታድኖ እየተገደለና ተፈናቅሎ እጅግ በጣም ሲቃይና መከራ በማየት ላይ ይገኛል። በጎረቤቶቻችን ጭምር በዉጪ ተንቀናል። ሱዳን እንኳን ድንበራችንን ከደፈረች ቆየች። የግብፅ ማስፈራሪያ እንደቀጠለ ነዉ። ምዕራቦች አስከፊ ማዕቀብ ለመጣል እየተዘጋጁ ይገኛሉ።
ስለዚህ ከመንግሥትም ሆነ ከህዝባችን የሚጠበቁ እጅግ አስቸኳይ እርምጃዎች ይኖራሉ። እነዚህን በሚከተለዉ መልክ ባጭሩ አቀርባለሁ። ሁላችንም ኃላፊነታችንን ተወጥተን የዉድ ሀገራችንን ሉዓላዊነትና የህዝባችንን ደህንነት ማስጠበቅ ይኖርብናል። ቸሩ ፈጣሪያችንም ይጨመርበት።
2ኛ/ አንድነታችን ሲጠነክር እንከበራለን፤ ሲላላ ሰለባ እንሆናለን
እድሜ ለአባቶቻችንና አያቶቻችን ጀግንነት፤ አርበኝነትና መስዋዕትነት፤ ኢትዮጵያ ነፃነቷን አስጠብቃ ለዘመናት ኖራለች። ከራሷም አልፋ በቅኝ ግዛት እጅ የወደቁትን የአፍሪቃ ሀገሮች የተቻላትን ያህል ስትረዳና ስታሰለጥን ኖራለች። እንደነደቡብ አፍሪቃ ኒልሰን ማንዴላ፤ የኬኒያ ጆሞ ኬኒያታና የታንዛኒያዉ ጁሊዬስ ኔየረረ በግልፅ የሚጠቀሱ ምሣሌዎች ናቸዉ። በሰሜንና ደቡብ ሱዳን መካከል ለረጅም ዓመታት የዘለቀዉን የርስ በርስ ፍጅት በሽምግልና አስቀርተዉ ሰላም አዉርደዋል። በአድዋም ሆነ በማይጨዉ አስከፊ ጦርነቶች ላይ ያስገኘችዉ ድል ለዓለም ጭቁን ህዝቦች ተምሳሊት ሆኖ ነፃነታቸዉን እንዲጎናጸፉና ቀና ብለዉ እንዲሄዱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከፍለዋል። በዚህም ምክንያት ለዉጪ ጠላቶች ከባድ የጉሮሮ አጥንት ሆና እንደኖረች የታወቀ ሃቅ ነዉ። በመሆኑም፤ በኢትዮጵያ ጠንካራና ህዝባዊ የሆነ መንግሥት እንዲመሠረት አይፈልጉም። ጨፍጫፊዉ የደርግ አምባገነን መንግሥት በሶቪዬት ህብረት የተደገፈዉ ለኢትኦጵያ ህዝብ ጠቀሜታ ሳይሆን በኢትዮጵያ ምድር ዲሞክራሲ እንዳይመሰረት ነበር። ሀገር ወዳድ ወጣቶች፤ ምሁራንና መላዉ ተራማጅ ትዉልድ ክፉኛ ተጨፈጨፈ።
ደርጉ ደግሞ ለወያኔ፤ ለሸአቢያና ለኦነግ አስረክቦ እንዲፈረጥጥ የምዕራብ ኃይሎች ከፍተኛ ድጋፍ አደረጉ። የወያኔ/ኢህአዴግ መንግሥት ለኢትዮጵያ ስለሚጠቅም ሳይሆን ፍላጎታቸዉ ሀገሪቷን ከፋፍሎ እንዲያዳክም ነበር። ለዚህም ተረቅቆ እስካሁን በሥራ ላይ የሚገኘዉ ከፋፋይ ሕገ መንግሥት ተብዬዉ እንዲረቀቅና ህዝባችን በጎሣ ተከፋፍሉ እንዲጨራረስ የተደረገዉ። የተከፋፈለችና የተዳከመች ሀገር የሚፈልጉት ለማሽከርከር እንዲመቻቸዉና ከፍተኛ ጥቅማቸዉን ለማስጠበቅ ነዉ። በዚህም ላይ የተያዘብን የረጅም ጊዜ ቂም አለ። በቀድሞ ዘመናት ኢትዮጵያ የጠየቀቻቸዉ ቴክኖሎጂን እንጂ የምግብ ዕርዳታ አልነበረም። ለም መሬታችንን በማረስ ራሳቸዉን መመገብ ይችሉ ነበርና። በተለይ ባለፉት 50 ዓመታት ገደማ ግን ራሳችንን መመገብ አቅቶን በዉጪ እርዳታ ሥር ወደቅን። የወጣቶች ፍልሰትና ስደት እንደጉድ ነዉ። ዛሬ በአሜሪካ፤ በአዉሮፓ፤ በመካከለኛዉ ምሥራቅ፤ በአዉስትራሊያ፤ ወዘተ ተበትኖ የሚኖረዉን ወገን ቁጥርና ሁኔታ ማየት በቂ ነዉ፤ በየቀኑ መርዶ።
3ኛ/ ከመንግሥት የሚጠበቁ ኃላፊነቶች
ዛሬ እንደዚህ የተናቅነዉና የተዋረድነዉ እንድነታችን በመላላቱ፤ ጭቆና በመብዛቱና ህዝብን የሚታደግ ኃይል በመጥፋቱ ነዉ። ህዝብ እንዳይጨፈጨፍ የሚከላከል ኃይል የለም። መንግሥት በግልፅ ወጥቶ ይቅርታ ጠይቆ ዋስትና ሲሰጥ አይታይም። ግዲያና መፈናቀል እንደቀጠለ ነዉ። የተፈናቀሉት ወደየቀዬአቸዉ ሲመለሱ አይታዩም፤ በቂ ድጋፍም አያገኙም። የተላከልን የእርዳታ እህል ተሰረቀብን የሚሉም ብዙ ናቸዉ።
በዚህ እጅግ አስጨናቂ ወቅት ከመንግሥት የምንጠብቀዉ፤
- የህዝብ ግድያ ማስቆም፤
- ህዝባችን እንዳይፈናቀል መከላከል፤
- የተፈናቀሉትን ወደየሰፈራቸዉ መመለስ፤ በቂ ድጋፍ መስጠት፤
- ወንጀለኞችን ለፍርድ ማቅረብ፤
- ሰላም ያላት ኢትዮጵያ ለጎረቤትም ሆነ ለመላዉ ዓለም ሰላም እጅግ አስፈላጊ መሆኗን ለዓልም ህብረተሰብ ለመግለጽ መቻል፤
- እስካሁን ድረስ ራሷን ከመጠበቅና ከመከላከል በስተቀር የማንንም ሀገር ፍላጎት ነክታ እንደማታዉቅ ደጋግሞ ማስታወስና መግለፅ፤
- ህዝባችንን ለመከራና ሲቃይ የሚጋብዙ ሕገ መንግሥት የመሳሰሉ ጉዳዮች እንዲቀየሩ ማመቻቸት፤
- የሽግግር መንግሥት ማጠናከርና ወደዲሞክራሲ የሚያመሩ ተቋማትን መገንባት።
4ኛ/ ከሰፊዉ ህዝብ የሚጠበቁ ኃላፊነቶች
ከሀገር ወዳድ ህዝባችንም ብዙ ነገሮች ይጠበቃሉ። ከነዚህም ዉስጥ፤
- መንግሥት እላይ የተጠቀሱትን ኃላፊነቶች እንዲወጣ መቆስቆስና መጠየቅ፤
- ምንም ያላጠፋ ወጣትና መጪዉ ትዉልድ ሀገር አልባ ሆኖ እንዳይቀር የሀገርን ኅልዉና ማስጠበቅ፤
- የንፁህ ዜጋን ህይወት ማጥፋት ከባድ አረመኔነት መገንዘብ፤
- ራስን ከዉሸት ትርክቶች መጠበቅና ወገንን ማፍቀር፤ መንከባከብና መደጋገፍ፤
- ለተፈናቀሉት ወገኖቻችን የሚቻለዉን ድጋፍ ማድረግ፤
- በርካሽ ራስ ወዳድነት የተነሣ የዉጪና የዉስጥ ጠላቶች አገልጋዮች ከመሆን መቆጠብ፤
- ሰላም ያላት ኢትዮጵያ ለጎረቤትም ሆነ ለመላዉ ዓለም ሰላም እጅግ አስፈላጊ መሆኗን በተቻለ መንገድ ለዓልም ህብረተሰብ ለመግለጽ መሞከር፤
- ህብረታችን ሲጠነክር የዉጪ ኃይሎች ሊደፍሩን እንደማይችሉ መገንዘብ፤
- በዚህ ረገድ በተለይ የሺማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች ሚና ከፍተኛነት መገንዘብና መፈጸም፤