ኢትዮጵያ ፣ በአስተማማኝ ሠላም ውሥጥ ሆና ዜጎቿ በአሻቸው የአገሪቱ ክልል እየተንቀሳቀሱ ሰርተው ብልፅግናንን እውን ለማድረግ የሚችሉት ፤ ያልወገነ ፣ ሁለንተናዊ ጥንካሬ ያለው እና በወታደራዊ ዝግጅቱ በዓለም ተወዳዳሪ የሆነ ፣ የአገር መከላከያ ኃይል ና ለህግ እና ለህሊናው ብቻ ተገዢ የሆነ ፣ ፍትህ ና ሠላም በመላው አገራችን እንዲነግስ የሚያደርግ ሙያውን አክባሪ ፣ ህግ አሥፈፃሚ ተቋም እና አንድ የጋራ መግባብያ ቋንቋ ሲኖር ምሑራን ያምናሉ ። ያለ እነዚህ በፍፁም ሰላም እንደማይመጣ የበለፀጉትን አገራት የትላንትና የዛሬን ታሪክ መለሥ ብሎ መመልከት አሥፈላጊ ነው ። ሲሉም ይመክራሉ ፡፡
ቻይና ፣ አሜሪካ ፣ ሩሲያ ፣ ጀርመን ፣ እንጊሊዝ ፣ ፈረንሣይ ፣ ጣሊያን ፣ ስፔን ፣ ፖርቹጋል ፣ ወዘተ ። በአገራቸው ሠላም ሰፍኖ ብልፅግና የመጣው ሁሉም ዜጋ የሚመካበት የህግ ሥርዓት ፣ መከላከያ ሠራዊት ና አንድ ገዝፎ የሚታይ ሁሉም የሚናገረው ብሔራዊ ቋንቋ ሥላለቸው ነው ።
ዛሬ አገራችን ተከታታይነት ያለው ወከባ ፣ ትርምስ ና ሰቆቃ ውሥጥ እንድትዳክር ያደረጋት ፣ የእነዚህ ሦሥቱ በወጉ ያለመኖር እንደሆነ እሙን ነው ።
በአገራችን 80% የሚነገረውን አማርኛን ፤ ብሔራዊ ቋንቋ ለማደረግ ባለመቻላችን እና የባቢሎንን ግንበኞች መንገድ በመከተላችን የተነሳ የአገራችን ህዝቦች ሠላም ክፉኛ እንደተናጋ ይታወቃል ። የህዝቡን ሰላም ያናጉትም የፖለቲካ ሊሂቃኑ ናቸው ። እነዚህ ሊሂቃኖች ፣ በምክር ቤት ና በክልል ምክር ቤት በአማርኛ ይናገራሉ :: ወደ ሚያስተዳድሩት ህዝብ ሲመለሱ ፣ “አማርኛ አናውቅም ፡፡ ” ይላሉ ። አማርኛ የአማራ ቋንቋ እንዲሆን ከፈጣሪ የተሰጠ እሥኪመሥለን ድረስ አማርኛን ይጠየፋሉ ። ጥላቻንም ይዘራሉ ፡፡
እነዚህ የፖለቲካ ነጋዴዎች ፣” ሁሉም ሰው የፈጣሪ ሸክላ ነው ብለው አያምኑም ።ፈጣሪም ለሰው ፊት አያደላም ፡፡ ሥለ ነገድ ፤ ጎሣና ቋንቋ ግድ አየሰጠውም ፡፡ የሱ አጀንዳ ፍቅር ነው ፡፡ የዘርና የቋንቋ ሹክቻ አይደለም ፡፡ ሁሉም ቋንቋ እኩል እና ሰውን ከሰው ጋር አቀራራቢ አግባቢ እና አፋቃሪ እንጂ አጣይ አይደለም ። ማንም ሰው ለማንም ሃሳቡን በአንደበቱ አልያም በምልክት ቋንቋ ሳይናገር ሊዋደድ ና ሊፋቀር አይችልም ። እንኳን ለፍቅር ለጥላቻም ቋንቋ ያሥፈልጋል ። ” በማለት ህሊናቸውን ለህብረት ኑሮ አያስገዙም ፡፤
ቋንቋ የመግባቢያ እንጂ የመጨቆኛ ና የፖለቲካ መሣሪያ አለመሆኑ ቢታወቅም ፣ በእኛ አገር ወደ ሥልጣን መወጣጫ እርካቡ ቋንቋ ከሆነ እንሆ 30 ዓመት ሞልቶታልና እነሱ ሁሌም በቋንቋ እያመካኙ ለመበዝበዝ ነው ፍላጎታቸው ። ከ 30 ዓመት በኋላ ፤ ግንቦት 28 / 2013 ዓ/ም አገራዊው ምርጫ ተካሂዶ ” የቋንቋ ንግሥ ና ያበቃል ። ” የሚል ተሥፋ ይህ ፀሐፊ አለው ። (…)
ጥቂት የማይባሉ ምሁራን ግን ፣ ዛሬና አሁን ሥር ነቀል ለውጥ ይፈልጋሉ ፡፡ ለምን ተብለው ሲጠየቁ ፣ ” ከምርጫ በፊት ፣ ሌቦችንና የህዝብን ማጅረት የሚመቱ አስመሳይ ፖለቲከኞችን የለውጥ ኃይሉ አስቀድሞ ከጫወታ ውጪ ካላደረገ በስተቀር ፣ በምርጫ ወቅትና ከምርጫ በኋላ በሚደረጉ አሻጥሮች አገሪቱ ሰላሟን ታጣለች ብለን እንፈራለን ፡፡ ” ይላሉ ፡፡ ይህ እምነታቸው ባይናቅም ፤” የአገሪቱን የፀጥታ ኃይሎች በሙሉ በአንድ ዕዝ እንዲመሩ ማድረግ ፤ የአገሪቱን ና የህዝቧን ሰላም ለማስጠበቅ ዝግጁ በማድረግ፡ ይህንን ስጋታቸውን ማቃለል ይቻላል ፡፡” በማለት የመፍትሄ ሃሳብ የሚያዋጡ አሉ ፡፡ የእንባ ጠባቂ ተቋሙ ይህንን ሃሳብ ማዋጣቱን አትዘንጉ ፡፡ ሃሳቡን ሰምቶ እንዳልሰማ ማለፍ ፣ ዋጋ እንደሚያስከፍል ፣ መንግስት የሚገነዘብ ይመስለኛል ፡፡
ይህንን ሁሉ ሥጋት የደቀነብን ፤ ከ80 በላይ ቋንቋ ያላቸው ጎሣዎች ባሉባት አገር ፣ ሰው ያልፈጠረውን የአንድ ሉአላዊ መንግሥት ና ህዝብ መሬት በየክልሉ ሸንሽኖ ፤ ለአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ብቻ በመስጠት ፣ ዜጎች በዜግነታቸው ኮርተው ፣ በአገራቸው ምድር ፣ ሰርተው እንዳይበሉ የሚያደርግ የአንድ ጎሣ ቋንቋ ንግሥና ነው ፡፡ ይህ አይነቱ ርዕየት አብዮታዊ ዴሞክራሲም በለት መለሲዝም ፣ ዜጎችን የሚያናቁርና እሥከዘላለሙ የማያቀባብር የልዩነት ግንብ ነው ፡፡ ይህንን ሃቅ የለውጡ ወይም አሻጋሪው መንግስት የሚያጣው አይመስለኝም ። በአውሮፖ ና አሜሪካ ይቅር ና በጎረቤቶቻችን አገሮች የእኛን መሰል የማያቀባብር የቋንቋ አጥር በዜጎች መካከል እንዳልታጠረም የየክልሎቹ ፕሬዝዳንቶች የሚገነዘቡት ይመስለኛል ።
እርግጥ ነው የቋንቋ አጥሩ ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር” የመለስ ዜናዊ አዲስ ፍልሥፍና መሆኑ እና ለሙከራ ወደተግባር እንዳመጣው ለምራብውያኑ ግልጽ ነው ። “ይህ ሱሪ በአንገት የማውለቅ ያህል የተደናበረና የሚደናብር ፍልስፍና በዓለም አገራት የለም ። ህዝብ በየቋንቋው አጥር ውስጥ ሆኖ ( በዜናዊዝም ፍልስፍና እንዲተዳደር ) ለ 30 ዓመት ተደርጓል ፡፡ በየትም የሀገሪቱ ክፍል ፤ በቋንቋው እየተለየ ፣ የማይመለመል ወታደርና ፖሊሥ ይህቺ አገር ቢስፈልጋትም ይህ ለ30 ዓመታት አልነበረም ፡፡ በዚች አገር ውስጥ በቋንቋ ያቋቋምነውን የየክልሉን ኃይል ወደ ፌደራል በማምጣት ፣ ለሦሥት ወር በማሰልጠን እና በፊደራል ሥር በማድረግ ፣ ከሁሉም ብሔረሰቦች ጋር በመበወዝ ኢትይጵያዊ የሆነ ፣ ፖሊስና ወታደር መፍጠር ካልቻልን በስተቀር አበሳችን ይቀጥላል ።
ይህ መሆን የሚችለው ከምርጫው በኋላ ህገ መንግሥቱ ላይ ያሉ አሳሪ አንቀፆችን ፣ በተለይም ቋንቋን ፣ የክልል መንግሥታት ና የፊደራል መንግሥትን ሥልጣን በተመለከተ አዳዲስ ህጎችን በማውጣት ፤ የምርጫ ህጉን እና ለሥልጣን የመወዳደሪያ መንገዱ የሚቀየርበትን መንገድ በመቀየስ እንደሆነ ቢታመንም ጥቂት የማይባል ዜጋ ፣ የዛሬን እንዴት አድሬ እያለ ነው ።ይህ እንደ ሥጋዊው ምሳሌ በቀላሉ ወደጎን የምንገፋው የሰው ሥጋት አይደለም ፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ከ80 በላይ ቋንቋዎች እየተነገሩ ፣ በ11 ክልላዊ መንግሥታትት ቋንቋዊ ሥልጣን ለጥቂቶች በመሥጠት አገርን መምራት ነገ ፣ እንደ ትግራይ ክልል ዓይነት አደጋ እንደሚያስከትል ከወዲሁ መገንዘብ የሥጋቱን እውነትነት ያረጋግጥልናል ፡፡ እናም ፣ በሁሉም ክልል ከ85 % በላይ ተናጋሪ ያለው የአማርኛ ቋንቋ ብሔራዊ ቋንቋ እንዲሆን ህገ መንግሥታዊ እውቅና እንዲሰጠው ማድረግ ፣ ከምርጫ በኋላ የመንግሥት ሥልጣን የሚይዘው መንግሥት ኃላፊነት መሆኑን ዛሬ ላይ ሆኜ ማሳሰብ እፈልጋለሁ ።
ይህን ሥል ለሱማሊኛ ተናጋሪው ሱማሊኛ የማይችል አሥተዳዳሪ ይሾምለት ማለቴ እንዳልሆነ ይታወቅለኝ ። በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሱማሊኛ ተናጋሪ ሰዎች በምሥራቁ የኢትዮጵያ ክፍለ አገር ይኖራሉ ። ( በአገሪቱ በሙሉ ይኖራሉ ፡፡ ) አብዛኛዎቹ በተለይም በከተማ የሚኖሩ አማርኛ ይነገራሉ ። አማርኛ ሁለተኛ የሥራ ቋንቋቸው ቢሆን ኢትዮጵያዊነትን ያጠናክራል ። ነው ፤ እያልኩ ያለሁት ።
በነገራችን ላይ ከጎረቤት ኬኒያ ጀምራችሁ ፣ የአብዛኞቹን የአፍሪካ መንግሥታትትን የሥራ ቋንቋ ና ብሔራዊ ቋንቋቸውን (official and national languages )የቅኝ ገዢዎቻቸው መሆኑንን መገንዘብ ጠቃሚ ነው ። የኢትዮጵያ መንግሥት የሥራ ቋንቋ ግን አማርኛ ነው ። ( official languages) ጥያቄዬ አማርኛ ቋንቋ ለምን ብሔራዊ ቋንቋ አይሆንም ነው ? ሁሉም የመንግስት ባለስልጣን በቋንቋው እየተራቀቀበት አይደለምን ? የትኛው የክልል ባለስልጣን ነው የአማርኛ ቋንቋ ሲደናገረው ያየነው ? በራሰችን ወርቅ ባንቀልድና እራሳችንን ባናኮስስ መልካም የመስለኛል ፡፡
የጥቂቶቹን የአፍሪካ አገራት ብሔራዊ ና የሥራ ቋንቋ በመጥቀስ የፅሑፊን ጭብጥ በማጠናከር ፅሑፊን እቋጫለሁ ፡፡ ።
አገር የሥራ ና ብሔራዊ ቋንቋ
አንጎላ ፖርቹጋልኛ
ቤኒን ፈረንሣይኛ
ቦትስዋና በከተማ እንጊሊዘኛ በገጠር ሳትስዋና
ቡርኪናፋሶ ፈረንሣይኛ
ብሩንዲ ፈረንሣይኛ ና ክሩንዲኛ
ካሜሮን እንግሊዘኛ ና ፈረንሣይኛ
ኬፕቨርዲ ፖርቹጋልኛ
ቻድ ፈረንሣይኛ ና አረብኛ
ኮሞሮስ አረብኛ ና ፈረንሣይኛ
ዴ/ሪ/ ኮንጎ ፈረንሣይኛ
ጂቡቲ ፈረንሣይኛ ና አረብኛ
ኢኮተሪያል ጊኒ ስፖንሽና ፈረንሣይ
ኤርትራ ትግሪኛ ፣ አረብኛ ፣ እንግሊዝኛ
ጋቦን ፈረንሣይኛ
ጋምቢያ እንጊሊዝኛ
ጋና እንጊሊዘኛ
ጊኒ ፈረንሣይኛ
ጊኒ ቢሳው ፖርቹጋል
ኬኒያ እንጊሊዘኛ ና ኪስኋሊ
ላይቤሪያ እንጊሊዝኛ ና 20 የጎሳ ቋንቋዎች
ማሊ ፈረንሳይ
ሞሪሸስ እንጊሊዘኛ ና ፈረንሣይኛ
ኒጀር ፈረንሣይኛ
ሩዋንዳ ፈረንሣይኛ ና እንጊሊዝኛ
ሴኔጋል ፈረንሣይኛ
ደቡብ አፍሪካ
ዛምቢያ እንጊሊዝኛ
ዚምባቡዌ እንጊሊዝኛእንጊሊዘኛ እና የራሷ 11 ቋንቋዎች የመንግሥቷ ና የአገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ ነው ።
ቶጎ ፈረንሣይኛ
ዩጋንዳ እንጊሊዝኛ
( ምንጪ Nation online project …one world )