June 19, 2011
28 mins read

"ይቅርታችን ሁልጊዜ ጅምር ነው" – ቃለ ምልልስ ከዘማሪ፣ ደራሲና ሰዓሊ ይልማ ኃይሉ ጋር

(ከሔኖክ ዓለማየሁ)
“እጅግ ደስ የሚያሰኝ ነገር ባየህ ጊዜ
ደስታን ትተህ ዙር ወደ ትካዜ
በዛ ደስታ ውስጥ እጅግ የመረረ፣ ውዴታው የጠና
አንድ ትልቅ ሐዘን አይታጣምና”
ይህ የከበደ ሚካኤል ግጥም የዛሬው እንግዳችን ዘማሪ፣ ደራሲና፣ ሰዓሊ ይልማ ኃይሉ ደስ ከሚሉት አባባሎች መካከል አንዱ ነው። “ነገሮችን ሁሉ በሰላም እና በመነጋገር መፍትሄ ያገኛሉ” የሚል የሕይወት ፍልስፍና ያለው ይልማ “በሕይወቴ ደስ የምትለኝ ቦታ ሃገሬ ኢትዮጵያ ናት” ይለናል።
የእግዚሪያ፣ ያዕቆብ እና ይኩኑአምላክ አባት የሆነው ባለትዳርና የመልካም ሚስት እድለኛ የሆነውና ነዋሪነቱን በርነዝቪል ሚኒሶታ ያደረገው ዘማሪ፣ ደራሲና ሰዓሊ ይልማ ኃይሉ የዛሬው የዘ-ሐበሻ ጋዜጣ እንግዳ ሆኗል። በሥራዎቹ ዙሪያ ያደረገውን ቃለ ምልልስ ከግል ሕይወቱ በመነሳት እንጀምራለን።
ይልማ፦ በቅድሚያ ስለሕይወቴ መናገር ካለብኝ የተወለድኩት አዲስ አበባ ነው። የተማርኩትም እዛው ሲሆን ለጥቂት ጊዜ አሪሲ ነገሌ ሄጄ ተምሬያለሁ። ከዛ በኋላ አዲስ አበባ ስነ-ጥበብ ኮሌጅ ተመርቄያለሁኝ። ኪራይ ቤቶች አስተዳደርም ሰርቻለሁ። ይህ አጠቃላይ ሁኔታዬ ሲሆን እዚህ አሜሪካ ደግሞ በ1998 ጀምሮ (እ.ኤ.አ) ሚኒያፖሊስ እየኖርኩኝ ነው። እኔ የተማረኩበት ሙያ ስዕል ነው። ከዛ በተጨማሪ ቤ/ክ ውስጥ መዝሙር እዘምራለሁ። እስካሁን ከ13 በላይ የመዝሙር ካሴቶች አሉኝ። አንድ በህብረት ሌላው በግል ማለት ነው። ከዛ ውጭ ስዕሎች ዕስላለሁ። በጣም በርካታስ ዕሎች አሉኝ። 2 ጊዜ በሚኒያፖሊስ በሕብረት እንዲሁም አንድ ጊዜ በአዲስ አበባ አንድ ጊዜ በሕብረት ኢግዚብሽኖችን አሳይቻለሁ። የመጨረሻ ኢግዚብሽኔ ከ2 ዓመት በፊት ሴንት ሜሪ ቸርች ውስጥ (ሚኒያፖሊስ) ያሳየሁት ነው። አሁን ደግሞ ለሌላ ኢግዚብሽን እየተዘጋጀሁኝ ነው። አጠቃላይ ሁኔታዬ ይህን ይመስላል። ካሁን ቀደም “ይቅርታ እና እርቅ” የተሰኘ መጽሐፍ አሳትሜያለሁ። በአሁኑ ወቅት ወደ 2 የሚጠጉ መጽሐፍቶቼ ተዘጋጅተው የተቀመጡ አሉ። ከነርሱ ውስጥ አንዱ በሚቀጥለው 2 ወራት ውስጥ ታትሞ ይወጣል የሚል ተስፋ አለኝ።
ዘ-ሐበሻ፦ ይልማ ካንተ ጋርማ ብዙ ነገር ማውራት እንችላለን ማለት ነው። ምክንያቱም ሙያህ ጥልቅ ነው። ደራሲ ነህ፤ ዘማሪ ነህ፤ ሰዓሊ ነህ። የነዚህን ሙያዎችህን አጀማመር አጫውተኝ።
ይልማ፦ እኔ ከሕጻንነቴ ጀምሮ ቤ/ክ ውስጥ ነው ያደግኩት ማለት ይቻላል። የሰንበት ት/ቤት ውስጥ ከህጻንነቴ ጀምሮ አገልግያለሁ። ከዛም በሃገር አገር አቀፍ ደረጃም መዝሙሮችን እስከማዘጋጀትና በአገልግሎትም ቁጥሩ በጣም ብዙ የሆነ ቦታ ሄጃለሁኝ። የኢትዮጵያን ክፍለ ሃገሮች ያልረገጥኩበት ቦታ የለም። አሁን እንደገና ደግሞ በመላው አውሮፓ፣ ካናዳ እና አሜሪካ ያሉት ስቴቶች በመዝሙር አዳርሻለሁኝ። እሁድና ቅዳሜ ብዙ ጊዜ በየስቴቱ እሄዳለሁ። ይሄ አጠቃላይ የቤተክርስቲያን ሕይወቴ ሲሆን ስነ-ጥበብም የተጀመረው ከቤ/ክ ይመስለኛል። ምክንያቱም ሁልጊዜ ሳስቀድስ ቀና ብዬ የማያቸው ዑራዔል ቤ/ክ ውስጥ ያሉትን እነ አለቃ ዘ-ዳዊት ሰዓሊዎቹ የሳሉት ስዕል፤ እንዲሁም የሌሎችም ነበሩ። እዛ ቤ/ክ ያሉት እና በጣም ቀለመ መልካም(colorfully) የሆኑ በጣም በጣም የሚገርሙ ስዕሎች ስለነበሩ እነዛን ስዕሎችን ሁልጊዜ በቅዳሴ ሰዓት ጀምሮ አይ ስለነበር ያ ሕሊናዬ ውስጥ ቀለሙ የተንቆረቆረ ይመስለኛል። በትምህርት ቤትም ሆነ ብዙ ቦታ ላይ ከድሮይንጉ ይልቅ [ድሮይንጉ መሠረቱ ቢሆንም] ግን ቀለም በጣም ወዳለሁኝ። እና ከዛ የተወሰደ ይመስለኛል እና የቤ/ክ አስተዋጾ ነው የምለው። ስዕሉ በአዛብዛኛው ኢትዮጵያ ቤ/ክ አስተሳሰብ የአሳሳል ዘይቤ፤ የግድገዳ ስዕሎች ዘይቤ ስለምከተል ማለት ነው;; በስዕሉ በኩል ያለኝ ፍላጎ የሚገርምህ በዚህ በሚኒያፖሊስ ሴንት ፖል ከ11 አሜሪካውያን ጋር በመሆን ባዘጋጀሁት ኢግዚቢሽን የተነሳ በጋዜጣና በመጽሄት ላይ ሥራዎቼ ወጥተዋል። በሴንት ሜሪ ቸርች ባዘጋጀሁት ኢግዚብሽን ላይም ከ300 በላይ ለሆኑ የአሜሪካ ዜጎች ስለ ስዕሉ ማብራሪያ ለመስጠት ሞክረናል። በዚህ ሁኔታ ላይ ሆኖ የኢትዮጵያን ባህል ለማስተዋወቅ የኢትዮጵያን የአዘማመር ስልት ወይም በዓለማዊ አጠራሩ የሙዚቃውን ነገር ለማስተዋወቅ በሴንት ሜሪ ቸርች ጋብዘውኝ ፕሮግራም አካሂጄ ነበር። እንደገና አማርድ ላይብረሪና በሚኒያፖሊስ ትልቁ ላይብረሪ ብዙ ዜጎች በሚገቡበት እንዲሁም መዝሙሮቼን በመሰንቆ. በበገና፣ በክራር አድርገን ፕሮግራም በማቅረብ ሀገራችንን ለማስተዋወቅ ጥሬያለሁ። በሚኒሶታ ያለኝ እንቅስቃሴ ይህን ሲመስል በዋሽንግተን ዲሲም በቅርቡ ትልቅ የስዕል ኢግዚብሽን በማዘጋጀት የኢትዮጵያን ስነጥበብ ዞር ዞር ብዬ ለማሳየት እንቅስቃሴ ላይ ነኝ።
ዘ-ሐበሻ፦ በዚህ በኩል የኮሚዩኒቲያችን አምባሳደር ነህ ለማለት እደፍራለሁ። ብዙ የውጭ ሃገር ዜጋ በተሰበሰበት መዝሙሩንም የ ስዕል ሥራውንም ስታቀርብ በዛውም የሃገራችን ስም ነው እየተጠራ ያለው። ለምሳሌ በሚኒያፖሊስ ባሳየኻቸው ኢግዚቢሽኖች ላይ የኛ ኮምዩኒቲ የነበረው ምላሽ ምንድን ነበር?
ይልማ፦ አዎ ትንሽ የሚያስቀው እሱ ነው። እኛ ብዙ ሃብት አለን።የስነ ጥበብ ሃብት። ያንን ግን ለዓለም ለመግለጽ ያለን ፍላጎት በጣም ደካማ ነው። በሬድዮ ከ4 ሳምንታት በላይ ቀስቅሰን ነበር – መጥተው እንዲያዩልን። ቢያንስ ቢያንስ በዚህ በማንነት ቀውስ ውስጥ ያሉትን ሕጻናት ልጆቻቸውን መጥተው ኢትዮጵያዊ ሰዓሊ፤ ኢትዮጵያዊ ዘማሪ አለ እንዲህ እየተደረገ ነው፤ አሳዩ ብለን ነበር። ገር ግን ማንም ሰው ዝር አላለም። የተወሰነ የኔ ጓደኞችና በኢትዮጵያ ኦ/ተ/ቤ/ክ ውስጥ ያሉ ካህናት ብቻ ነው የተገኙት። ከነዚህ በቀር ሌላው የኛ ሕዝብ ጊዜ ከማጣትም ሊሆን ይችላል እንደዚህ ትንሽ ደከም ያለ ቅንስቃሴ ያደረገው። አሁን እየተማርን ስንሄድ ብዙ እንቅስቃሴውም ሰፋ እንደሚልና ለኢትዮጵያውያን ብቻ አንድ ፕሮግራም አዘጋጅተን በስነጥበቡ ዓለም ሃይለኛ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግ ተስፋ አለኝ።
ዘ-ሐበሻ፦ ዘፋኝ ወይም ፊልም መጣ ሲባል የኛ ሰው ይወጣል። ሆኖም ግን የስ ዕል ኢግዚብሽኖች ላይ ግን ሰው ብዙ የማይወጣበት ልምድ ከምን የመጣ ይመስልሃል?
ይልማ፦ አንድ አስተማሪ የነገረኝ ነገር አለ። ሙዚየሞች ብዙም አይዘወተሩም ለምንድን ነው ብለን ስንጠይቀው አንድ ዝምተኛን ሰው ጓደኛ ለማድረግና የሚናገርን ሰው ጓደኛ ለማድረግ የቱ ይቀላል ነው ያለን? ሁሉም ሰው የሚናገረውን ሰው ነው ቶሎ የሚወደው ሆኖም ፍቅሩ ከሚናገረው ሰው ጋር የተወሰነ ነው። ዝምተኛውን ለመቅረብ አስቸጋሪ ነው። ከዛ ከቀረቡትም በኋላ ለመለየት አስቸጋሪ ነው። ስዕልም እንደዛው ዝምተኛ ነው። ሄደው ሲያናግሩት፤ ሲኮረኩሩት መናገር ይጀምራል። መናገር ከጀመረ ደግሞ አያቆምም። የስ ዕል ሁኔታ ይህ ነው። 2ኛ ምሳሌ ልናስቀምጥ እንችላለን። አንድ ሰው ስታዲየም ውስጥ ሲገባ መጀመሪያ መግቢያ በሩ ራሱ ዝም ያለ ነው። ውስጥ ገብቶ ደግሞ እንቅስቃሴ የለም። አሁን ወደ ኳሱ ሲገባ ነው እንቅስቃሴ ያለው። ስዕል ያለው እንቅስቃሴ ረጋ ብሎ ነው የሚያስተምረው። እና በዚህ ምክንያት ይመስለኛል። ዝምተኛን ሰው እንደማናገር ነው ስነ-ጥበብ ማለት።
ዘ-ሐበሻ፦ ታዲያ እናንተ ሰዓሊዎች ሕዝቡን እንዴት አድርገን መሳብ እንችላለን ብላችሁ ታስባላችሁ ወደ ስነ-ጥበቡ።
ይልማ፦ በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው። እኔ አሁን በእኛ ሕዝብረተሰብ ውስጥ ስዕልን ብቻ ሳይሆን ጥበብ የሆኑ ነገሮችን እንዴት ለጥበብ ጊዜውን እና ሕሊናውን ይሰጣል የሚለው ሁኔታ በሰፊው እጨነቅበት የነበረ ነገር ነው። አንድ ቀን ግን አንድ መልስ አግኝቻለሁ። ያም መጀመሪያ ጊዜ ሕዝቡ ስዕልን ስላልቻለ ነው የስ ዕል አድናቂ ያልሆነው። ስዕልን ማንበብ ራሱን የቻለ መንገድ አለው። ለምሳሌ ስዕል ዘመን አለው። ደግሞ ምልክት(ሲንቦል) አለው። እነዚህ እነዚህን ነገሮች ማወቅ ከቻለ አንድ ሰው ስዕልን ማድነቅ ይችላል። ያለበለዚያ ግን ማድነቅ አይችልም። ለምሳሌ አንድ ሰዓሊ ሮማንቲክ የሆኑ ሥራዎችን ሲያቀርብ ምን ማለት ነው ሮማንቲክ? የሚለውን ነገር የሚያየውስ ሰው ካላወቀ በስተቀር ያ ስዕል ሊገባ አይችልም። ካልገባው ደገሞ ከዛ ስዕል ጋር አብሮ መቆየት አይችልም። ስዕልን ማንበብ ከቻልን እንደ አንድ ፊክሽን ወይም አንድ መጽሐፍ ጀምረን እስከምንጨርስ እንደማንለቀው ሁሉ ስዕልንም ብዙ ሰዓት የማየት ልምድ ይኑረን። ጊዜ ባይኖረን እንኳ ለስዕል ጊዜ መስጠት ይኖርብናል። ያለበለዚያ በ ኢንፎርሜሽን ከዓለም ጭራ ላይ ነው እየሆንን ያለነው። አባቶቻችን በየግድግዳው ስዕል ላይ፤ በየሕንጻው ላይ ያሳዩት መራቀቅ እኛ ጋር ሲደርስ እኛ ስዕልን መረዳት እንኳ የማንችል ሰዎች በመሆን ስዕልን መረዳት ከቻሉት ዓለማት ጋር ሲነጻጸር ጭራ መሆናችን ያሳዝናል። ከኛ ተርፎ ልጆቻችን ሙዚየም እንዳይሄዱ፤ ስነ ጽሁፍ እንዳያዩ ዓይናቸውን ሸብበነው የጥበብ ጠላት አድርገን ቤታቸው ውስጥ አፍነን ማስቀመጥ ይሄ ራሱ ራሱን የቻለ ወንጀል ነው። በኢትዮጵያ ኦ/ተ/ ቤ/ክ ውስጥ በየግድግዳው ላይ የተሳሉ ስዕሎች ምንድን ናቸው? አዳዲስ የኢትዮጵያ ሰዓሊዎች እነ አፈወርቅ ተክሌ፣ ገብረ ክርስቶስ ደስታ ምን እየሳሉ ነበር? በስነጥበብ ዓለም ውስጥ መጓዝ ካልቻልን ጭራ ነው የምንሆነውና ኢንፎርሜሽን ያስፈልጋል።
ዘ-ሐበሻ፦ ብዙ ጊዜ የኛ ሃገር ሰዓሊዎችን ስንመለከት ጸጉራቸውን ድሬድ አድርገው፤ አንዳንዶቹም በአደንዛዥ ዕፅ ተጠቅመው ነው ስዕልን የሚስሉት። አንተ ደግሞ በተቃራኒው መንፈሳዊ ሰው ነህ። ይህ የተደበላለቀ ስሜት ውስጥ ከተተኝ።
ይልማ፦ እንግዲህ ያልሆነውን መሆን ጥሩ አይደለም። ምንሆነውን ብቻ መሆን ያለብን። ለኔ የስነ-ጥበብ ሙያተኛ እንደማንኛውም ሙያተኛ ነው ብዬ ነው የማምነው። ከሌላው ሕዝብ ተለይቶ የተራቀቀ ወይም ደግሞ ሌላ ስታይል መፍጠር ያለበት ነው ብዬ አላምንም። እኔ ስነጥበብ ውስጥ በምኖርበት ሆነ ከሕዝቡም ጋር በምኖርበት ጊዜ እንደማንኛውም ሰው በሕብረተሰቡ ሕይወት ውስጥ መሳተፍ እፈልጋለሁኝ። ራሴን አግልዬ ከሕዝብ ላገኝ የምችለውን ነገር ማጣት አልፈልግም። ጸጉራቸውን ያንጨባረሩ ሰዓሊዎች አሉ። ለምሳሌ እነ ሊዎናርዶ ዳቪንቺንና የድሮዎቹን ሰዓሊዎች ብንወስድ ጸጉራቸውን ያንጨባረሩበት ምክንያትም አላቸው። ወደው ሳይሆን ጺማቸውንም ያሳደጉበት ምክንያት አላቸው። እነዚህ ሰዎች በዘመናቸው ሰው ሊሰራው የማይችል ነው የሰሩት። የሰሩት ሊዮናርዶ ራሱን እንደ 10 ሰው ሊሰራው የሚችለውን ነገር በመሥራት ያሳለፈው። 10 ሰው ሊሰራው የሚችለውን ሥራ ለብቻው ይሰራው ስለነበር ራሱን ጣለ። ጊዜው ቢኖረው ኖሮ ጸጉሩን ይሰራው ነበር። አሁን የኛ ሰዓሊዎች የሊዮናርዶን ያህል እየሰሩ ነው ወይ? የሚለውን መልስ ሰዓሊው ይመልሰው። እኔ ጸጉሬን ማበጠር እስከማልችልበት ድረስ ይህን ያህል ቢዚ አይደልሁም።እነ ሊዮናርዶ እነ ማይክል አንጀሎ የጣሊያንን የቤ/ክ ጣሪያዎች በስነጥበብ ሲከፍቱ፤ ሌላ ሕዋ ሲፈጥሩ ነው ጸጉራቸውን ያላበጠሩት። ያንን የሚያካክል የእምነበረድ ድንጋይ ወደ ሕይወት ሲለውጡት፤ ሕይወት ሲሰጡት ነው ጸጉራቸውን ማበጠር ያልቻሉት።
አንዳንድ የስነጥበብ ሰዎች የተለየ ባህሪይ አላቸው። ድራግ ምናምን ውስጥ የሚገቡ ሰዓሊዎች እንዳሉ የሚካድ አይደለም። የስነጥበብ ሰው ሆኖ ራስን ጠብቆ መኖር ይቻላል። በጠራ ሕሊና የስነ-ጥበብ ሰው መሆን ይቻላል። ለምንድን ነው ተደራቢ ነገር የምንጨምረው። እኔ አንዳንደ ጊዜ ቅዠት ይመስለኛል። ትክክለኛ ሰዓሊ ማለት የራሱ ስታይል ያለው ነው። የራሱ ማንነት አለው። ሰውነቱ ራሱ አቋም አለው። ያንን መፍጠር ይችላል። ያንን መፍጠር ይችላል። ያም ሰውን እንዳይረብሽ አድርጎ ከሰው ጋር ተግባብቶ ነው የሚኖረው እንጂ “ይህችም እውቀት ሆና ይመለኮስባት” ተብሎ ነው የሚያስተርተው። ብዙ አወቅን ብለን ልንራቀቅበት አይደለም። ራሳችንን ከሕዝብ ጋር አዋህደን መኖር ነው ያለብን። ይህ ይመስለኛል። የኔ አገላለጽ ይህ ነው: እዚህ ጸጉሬን እንደማንኛውም ሰው ተከርክሜ ነው የምሄደው። ጨዋታ ባለበት ቦታ እጫወታለሁ። ቤ/ክ ውስጥ ሃይማኖቴን በመዝሙር እሳተፋለሁ። ሕዝቤ ውስጥ ገብቼ ሕዝቤ የሚሆነውን እሆናለሁ እንጂ ራሴን አላገልም።

ዘ-ሐበሻ፦ በስነጥበብ ሙያ ላይ ሮል ሞዴልህ ማን ነው?
ይልማ፦ ሁለት ናቸው። አንደኛው በአስተሳሰብ ገ/ክርስቶስ ደስታ። እሱ ስነጽሁፍም እንደሚጽፈው እኔም እጽፋለሁ። እሱ አንዳንድ አስተሳሰቡ ላይ የሚናገረውን ነገር እስማማበታለሁ። በሌላ በኩል የኢትዮጵያን የአሳሳል ዘይቤ እጅግ ያሳደገው ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ፤ እሱ ደግሞ ባህሉን በመጠበቁና በማጉላቱ የኔ ሞዴሌ ነው።
ዘ-ሐበሻ፦ በስነ-ጥበብ ምን ደረጃ ላይ ደርሻለሁ ብለህ ታስባለህ?
ይልማ፦ ምንም። ምንክያቱም ስነጥበብ ማለት ብዙ የምትሄድበት ነው። ድንገት ከሞትክ በኋላ ሌሎች ሰዎች ስለ አንተ ይናገራሉ። ግን ሰዓሊዎቹ በጣም እርካታ ሳይሰማቸው ጆሯቸውን ቆርጠው፤ እንደ ባንጎ ዓይነቱ የዳቦ አጥተው የሞቱ የስነ-ጥበብ ሰዎች ግን ሻማ ይሆናሉ። መጨረሻ ላይ ግን ይሄ ሰው እኮ እንደዚህ ነበር ይላሉ። እኔ እልፍ አህላፍ ሥራዎችን ገና አልሰራሁም። እንደ እነ ሊዮናርዶ በሚያስገርም የሆነ ዘመን አልፈጠርኩምና ማነኝ? ስታየኝ ምንም አይደለሁም፤ ገና ተማሪ ነኝ።
ዘ-ሐበሻ፦ ወደ ደራሲነትህ ብናልፍና ይልማ የጻፈው “ይቅርታና እርቅ” የሚለው መጽሐፍ ከአሁኑ የኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ጋር ተነሳስቶ ነው የጻፈው የሚሉ ሰዎች አሉ።
ይልማ፦ ትክክል ናቸው። ካለው የኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር ነው። የፖለቲካው ብቻ ሳይሆን መጀመሪያ ይቅርታ እርቅ የሚለው ቋንቋን በደንብ አድርጎ ለመግለጽ ነገሮችን አስታርቀን ነው ወደ ይቅርታ መምጣት ያለብን የሚል አስተሳሰብ ነው ያለኝ። ብዙ ነገሮች አልታረቁም። ያንን ስናስታርቅ ወደ እርቅ እንመጣለን። ወደ ይቅርታ እንመጣለን። ይቅርታችን ሁልጊዜ ጅምር ነው፤ አያልቅም። ለምን መጀመሪያ ስላልታረቅን ነው። ባንክ ውስጥ ሒሳቡን መጨረሻ ላይ ማታ ሰርተው የሚጨርሱት ጠዋት የመጀመሪያውን ካሽ (ቼክ) ሲቀበሉ እዛላይ የሰሩት ነው ማታ ላይ ታርቆላቸው ሁሉ ነገር አልቆላቸው በሰላም የሚተኙት። ብዙ ነገሮች አሉ። ከግል ሕይወት ጀምሮ ይቅርታ ከግል ነው መጀመር ያለብን። መጀመሪያ ራሳችንን ከራሳችን ጋር ነው ማስታረቅ ያለብን። ከዛ ከህጻናት ጋር መታረቅ አለብን። ከዛ ከሚስቶቻችን (ከሴቶች)፤ ከሁሉምጋር መታረቅ አለብን። ይሄ ነው የዚህ መጽሐፍ አስተሳሰብ። መጅመሪያው ምዕራፍ ላይ ይቅርታ ራሱ በ3 ይከፈላል። አንደኛው ነገሮችን መፍታት ይቻላል። ከቤተሰብም ከማህበረሰብም ጋር። ነገር ግን መታረቅ አይቻልም። ይቅርታ የለም የተሰራን ነገር በሙዚየም አስቀምጦ ነገር ግን ለጊዜያዊ ዲፕሎማሲ ጉዳይ ለመኖር ብቻ ለጊዜያዊ ነገር መስማማት፤ በዘመናችን የሚዘወተርው ይህ ነው። ሁለተኛ ይቅርታ ፈጽሞ አያስፈልግም የሚል ክፍል ደግሞ አለ። ጸብ ነው የሚያስፈልገው የሚል ሰው አለ። ማርክሲስቶች በግጭት ውስጥ ነው አንድ ነገር ሊገኝ የሚችለው ስለዚህ የአንድ ነገር ውጤት በግጭት ነው የሚነሳው ብለው ያምናሉ። በዚህ ዓይነት አስተሳሰብ የሚያምኑ አሉ። አንድን በደልና ጭቆናን ለማስወገድ ጸብ ብቻ ነው መፍትሄው፤ አይንህን ካወጣው አይኑን አውጣው; አፍንጫህን ሲልህ አፍንጫውን እየመታህ ብቻ ነው እንጂ ሌላ እርቅ እና ይቅርታ የሚባል ነገር አስፈላጊ አይደለም የሚሉ አሉ። ደግሞ እንደ ነ ማህተመ ጋንዲ ያሉ ደግሞ ምን ይላሉ? ዓይንህን ያወጣውን ዓይኑን የምታወጣ ከሆነ ዓለም በሙሉ ዓይነ ስውር ነው የምትሆነው ብለው የሚያስቡ አሉ። እኔ ለምሳሌ አሁን እምወዳቸው እነርሱን ነው። 3ኛው ግን ፈጽሞ ማህተመ ጋንዲን ወይም ሌሎችንም ፈጽሞ ይቅርታ ማድረግ ከልብም ያለማሰብ፤ በክርስትናው ዕይታ “የሚያደርጉትን፤ የሚሰሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” እስከማለት የደረሰውን አስተሳሰብ ነው በመጽሐፉ ውስጥ ያስቀመጥኩት።
ዘ-ሐበሻ፦ በዚህ ቃለ ምልልስ ውስጥ የቀረ የምትለው ነገር አለ?
ይልማ፦ እኔ አንድ ነገር ለሕዝቤ መናገር እፈልጋለሁ። ያለፈው ዘመን እነአፈወርቅ ተክሌን ሸልሞ፤ ሥራቸውን አድንቆ፤ እነ ሃዲስ ዓለማየሁን፣ እነ በዓሉ ግርማን፣ ብርሃኑ ዘርይሁንን ፈጥሮ ያለፈው ዘመን አሁን ከነ ብርሃኑ ዘርይሁንን የሚስተካክሉ ወጣቶች አሉ። እነዚህ ወጣቶች አዲሱ ትውልድ ውስጥ ሥራቸው አይታወቅምና ትውልዱ እንዳይቀብራቸው የሕብረተሰባችን ጌጦች፤ የስነ-ጥበብ ሰዎች የኛ ማንነት መግለጫ እንዳይቀበሩ እኛም መንፈሳችን ተቀብሮ እመንፈሳችን ተወሮ እንዳይቀር የስነ-ጥበብ ሰዎችን ከሕብረተሰቡ እንዲመለከት አዳዲስ ገ/ክርስቶስ ደስታን፤ አፈወርቅ ተክሌን እንድንፈጥር የኢትዮጵያን ሕዝብ እጠይቃለሁ። በድሮዎቹ ብቻ ሳይሆን አዳዲሶችንም መፍጠር አለብን። ስነ-ጥበብ መቋረጥ የለበትም። ማንነታችን መቋረጥ የለበትም። መንፈሳችን መመታት የለበትም።
ዘ-ሐበሻ፦ ይልማ በዘ-ሐበሻ ጋዜጣ አንባቢዎች ስም ስለሰጠኸን ቃለ ምልልስ በጣም እናመሰግናለን።µ

Latest from Blog

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

Go toTop