የጎጃም ክልል ይመስረት – ከይገርማል

ይቅርታ ይደረግልኝና ከዚህ በፊት የሸዋ ክልላዊ መንግሥት ይመስረት የሚለው ሀሳብ አማራውን የሚያዳክም እየመሰለኝ ብዙም አልወደድሁትም ነበር። አሁን ግን የነበረኝን ቅሬታ አንስቼ የሸዋ ክልላዊ መንግሥት ይመስረት ከሚሉት ጎን መቆሜን እገልጻለሁ። ሸዋ ብቻ ሳይሆን ጎጃምም በክልል ደረጃ እንዲደራጅ እጠይቃለሁ። በታሪክ በራሳቸው ነገስታት ይተዳደሩ ከነበሩት ገናና መንግሥታት (Kingdoms) ውስጥ አንዱ ጎጃም ነበር። ይሁንና ከደረጃው ወርዶ እንደክፍለሀገር እንዲቆጠር የተሴረው፣ ግዛቶቹ ተሸንሽነው በተለያዩ ገዥወች ተረግጦ እንዲያዝ የተደረገው፣ በአጼ ሚኒሊክ ዘመነመንግሥት ጊዜ ሲሆን፣ በአጼ ኃይለስላሴ ዘመነመንግሥት ጊዜ ደግሞ ካለባህሉ የሸዋ ሰው የተሾመበት፣ ከስልጣን ተፎካካሪነት ወጥቶ ዝቅ ብሎ ተንበርክኮ እንዲገዛ ለማመቻቸት ነበር። በደርግ ወታደራዊ አገዛዝ ወቅት ምሥራቅ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎጃም፣ መተከል ልዩ ዞን በሚል ለሦስት እንዲከፈል የተደረገው ጎጃም በወያኔ ጊዜ ደግሞ መተከል ልዩ ዞን ከአሶሳ ጋር ተጣምሮ በክልል ደረጃ እንዲዋቀር ሲደረግ ቀሪው የጎጃም ክፍል አማራ ተብሎ በተፈጠረ አዲስ ክልል ውስጥ ተካቶ በወሎና በጎንደር ስር እንዲገዛ ተፈረደበት።

በብአዴን የድራማ መድረክ አቶ ደመቀ መኮንን ከኃላፊነት ቦታየ እለቃለሁ ብሎ እንደነበር ሰምተናል። ሌሎቹ “ተው፡ ተው አይሆንም! ካላንተ ድርጅቱስ ምን ድርጅት ትግሉስ ምኑን ትግል ይሆናል!” ብለው አገላግለው እሱም እግዜር ይስጠውና መንጋውን ካለጠባቂ ላለመተው በማሰብ፣ በተጨማሪም የብዙሀኑን ልመና ላለመግፋት በሚል ወደስልጣኑ ተመልሷል። ይኸው ዛሬ ደግሞ የሀገሪቱ ም/ጠ/ሚኒስትር ሆኖ ለሁለተኛ ጊዜ ተመርጦ በአማራነት ርካብ እንደገና ወደስልጣን መድረክ ወጥቷል። የእሱ በድጋሚ ም/ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን እንደድል በመቆጠሩ ድፍን አማራ በደስታ ሰክሯል ማለት ይቻላል። ከእንግዲህ በኋላ ችግሮች ሁሉ መልክ ይይዛሉ ማለት ይሆን! ባሳለፍናቸው የስቃይ ጊዚያት አቶ ደመቀ ምን አደረገልን? ገና ልጅ እያለ ቅል አንጠልጥለው፣ ውሻ አስከትለው ከመጡት ቤተሰቦቹ ጋር ተንከባክባ አሳድጋ ለቁምነገር ላበቃችው ጎጃም፣ በስልጣን ላይ በቆየባቸው አመታት እዚህ ግባ የሚባል የልማት ሥራ ሰርቷል? ታዲያ ምን አዲስ ነገር ተገኝቶ ነው ይኽ ሁሉ ዘፈን! ጉድ እኮ ነው!

ጎጃም ከፖለቲካ ተፎካካሪነት ርቆ ሌሎች በሰፈሩለት ልክ መኖር የጀመረው በራሱ ሰዎች መተዳደር ካቆመ ከ1920ዎቹ ጀምሮ ነው። አጼ ኃይለሥላሴ ራስ ኃይሉ ተክለሀይማኖትን አዲስ አበባ ላይ በግዞት አስቀምጠው ራስ እምሩን ከሾሙበት ጊዜ ጀምሮ ጎጃም የስልጣን ተፎካካሪ ለመሆን ይቅርና ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር አልፈቀድለት ብሎ በገባርነት ተወስኗል። በ1950ወቹና በ1960ዎቹ ውስጥ የአባይ ማዶወቹ ደጃዝማች ፀሀዩ እንቁሥላሴና ደጃዝማች ደረጀ የጎጃም ገዥ ሆነው ገዝተዋል። በደርግ ጊዜም ቢሆን ብዙ የተለየ ነገር አልነበረም። አዎ! በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ጉልህ ድርሻ የነበረው ጎጃም በሸዋ ፖለቲከኞች ሴራ ከደረጃው ወርዶ ራሱን በራሱ እንዳያስተዳድር እንኳ ተከልክሎ ግብር ከፋይና ወታደር ሆኖ እንዲቀር ተደርጓል።

በደርግ የተበተነው የሸዋ ገዢ መደብ የበላይነቱን ለማስመለስ በወያኔ ጊዜ የአማራ ሕዝብ ተከራካሪ ነን በሚል በመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) ስም ተደራጅቶ ጠቅላላ አመራሩን በሸዋ ሰዎች ተቆጣጥሮ፣ ሌሎችን በጀሌነት አሰልፎ ሲንቅቀሳቀስ ቆይቷል። መአሕድ የትግል አድማሱን ለማስፋት በ1994 ዓ.ም ከብሔር ድርጅትነት ወጥቸ ሀገራዊ ድርጅት ሆኛለሁ ብሎ በመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ስም ቢደራጅም አመራሩ ግን ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ በሸዋ ሰዎች የተያዘ ነበር።

ጎንደር በበኩሉ የሀገሪቱን በትረ ስልጣን ለመረከብ ያልተቋረጠ ትግል እያደረገ ነው። በሀገር ውስጥ ከወሎ ጋር ግምባር ፈጥሮ ብሔረ አማራ ዴሞክራሲ ንቅናቄ (ብአዴን) የሚባል የአማራ ድርጅት መስርቶ ስልጣኑን ከወያኔ ለመቀማት ሲታገል ቆይቷል። ብአዴን ለአማራ ቆሚያለሁ የሚል ድርጅት ይሁን እንጅ ስለአማራ እያለቀሰ በአማራ ክልል ውስጥ የተካተተውን ሕዝብ አስተባብሮ የሀገሪቱን በትረ ስልጣን በመቀማት የጎንደርና የወሎን የበላይነት ለማስፈን የሚያደባ ድርጅት ነው። አብዛኛውን እና ቁልፍ የአመራር ቦታወችን በጎንደርና በወሎ ሰዎች አስይዞ የአማራ ዴሞክራሲ ፓርቲ (አዴፓ) በሚል አዲስ ስም የተደራጀው የሁለቱ ጥምረት በአማራ ላይ ፈላጭ ቆራጭነቱን ለማረጋገጥ ችሏል፤ የሚቀረው በሀገሪቱ ዙፋን ላይ መቀመጥ ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ አቡነ መርቆሪዮስ በስደት ላይ እያሉ በመላው አለም የሚኖረውን የዕምነቱ ተከታይ በሀይማኖት ስም ለመቆጣጠር ጎንደሬ ሊቃነጳጳሳትን መርጠው ሾመው ለጎንደር የበላይነት የድርሻቸውን አበርክተዋል። ወሎ በበኩሉ በአዴፓ ላይ ነግሦ ስልጣኑን ለማስጠበቅ እየታገለ ነው።

አለማዊ ፖለቲካና (secular) የቤተክርስቲያን ፖለቲካ (chrch politics) እየተናበቡ ለአንድ አካባቢ የበላይነት የሚሰሩበት ሁኔታ ድሮም የነበረ ነው። የሰውን ልጅ ከተቻለ በጉልበት ካልሆነም በጥቅምና በዕምነት አነሁልሎ ተከታይ ማድረግ አዲስ ፈሊጥ አይደለም። የሀገሪቱን በትረ ስልጣን ከያዙት ከመጨረሻው የዛጉዌ ንጉሥ ናኩቶላብ በትረስልጣኑን በአቡነተክለሐይማኖት አደራዳሪነት ወደ አጼ ይኩኖ አምላክ እንዲመለስ ከተደረገበት ጊዜ በፊትም ቢሆን የዕምነት ተቋማት ፍትሀዊ ባልሆነ መንገድ ለአለማዊው አገዛዝ ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበረ ይታወቃል። ይህን የተረዳው ወያኔ አለማዊውን አስተዳደር ለማጽናት በእስልምናውም ሆነ በክርስትናው ሐይማኖት እጁን አስገብቶ የበላይነቱን ለመያዝ ደክሟል። በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ላይ ከሀይማኖቱ ዶክትሪን ውጪ በመጀመሪያ አባ ጳውሎስን ከእሳቸው ሞት በኋላ ደግሞ አባ ማትያስን ከትግራይ አምጥቶ ፓትርያርክ አድርጎ ሾሞ ቤተክርስቲያንን እስከታች ድረስ ለመቆጣጠር ታግሏል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሰው እና ጀምበር - መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

ወያኔ ከውጭም ከውስጥም ያጋጠመውን ውግዘት ለማለዘብ ተሸናፊ መስሎ አንዳንድ ነገሮችን የለቀቀ ቢመስልም በሀገሪቱ ላይ ያለውን ስልጣን ለማስጠበቅ የሚያስችለውን ኃይል እንደያዘ የሚያጠራጥር አይደለም። ኦሮሞ ኦነግን እንደማስፈራሪያ እየተጠቀመ አዴፓን ተመርኩዞ የበላይነቱን ለማረጋገጥ በስልት እየተንቀሳቀሰ ነው። ወሎና ጎንደር እየተጎሻሸሙም እየተደጋገፉም በአማራ ላይ ያላቸውን የበላይነት ለማረጋገጥና ከኦሕዴድ (ኦዴፓ) ጋር ተደጋግፈው በሀገሪቱ የፖለቲካና የዕምነት ስልጣን ላይ የማይናቅ ቦታ ለመቆጣጠር ችለዋል። የወሎ፣ የጎንደርና የኦሮሞ ትብብር ወያኔን ከጨዋታ ውጭ ማድረግ ቢችል ከዚያ በኋላ ስለሚሆነው ነገር ግምቱን ለእያንዳንዱ ሰው መተው ይሻላል።

በኢትዮጵያዉነት ስም ከየቦታው እየታደኑ የተገደሉና የተሳደዱ ወገኖቼ ሁልጊዜም እረፍት ይነሱኛል። ኃይሌ ገላዬ፣ የስጋት እብስቴ፣ ታደሰ ጌታሁን፣ አለምነህ እንዳሌ፣ ላቃቸው አባቴነህ – – – ስንቱን ልቁጠረው! ስለኢትዮጵያ ሲዘምሩ ሮጠው ሳይጠግቡ ገና በለጋ ዕድሜያቸው በደርግ ገዳዮች እስትንፋሳቸውን ተነጥቀዋል። ዴሞክራሲ ያለ መስሎት በስብሰባ ላይ ሀሳቡን በመግለጹ ብቻ ምላሱ ተጎልጉሎ የተቆረጠው መምህር፣ ተስፋሁን ወርቁ፣ ሳሙኤል አወቀ፣ – – – በወያኔና በአገልጋዩ በበፊቱ ብአዴን በአሁኑ አዴፓ በግፍ የተገደሉ ናቸው። አዎ ደርግ ጠፍቷል፤ ወያኔና ምስለኔወቹ ግን አሁንም አሉ። ከእንግዲህ በኋላ ጎጃሜ መሞት ካለበት ለኢትዮጵያዊነት ወይም ለአማራነት ሳይሆን ለጎጃምና ለጎጃሜነት ብቻ መሆን አለበት። ኢትዮጵያ እንደሀገር እንድትቀጥል ለማስቻል እንደማንኛውም ክልል የራሳችንን ድርሻ ማዋጣት ተገቢ ነው ተብሎ በሁሉም ዘንድ ከታመነ ያን ማድረግ ይቻላል። የጎሳወችን የነጻነት ጥያቄ ለማፈንም ሆነ በሌሎች ክልሎች ጉዳዮች ገብተን መስዋዕትነት ለመክፈል ግን መታሰብ የለበትም። ኢትዮጵያ ብትፈራርስ ከማንም በላይ ተጠቃሚወች እኛ ጎጃሜወች ነን ለማለት ባልደፍርም ተጎጅወች እንደማንሆን ግን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። የአመት ቀለቡን መሸፈን የማይችል አካባቢ እገነጠላለሁ ብሎ ደፍሮ መነሳት ከቻለ በተፈጥሮ ፀጋ የታደለው ትርፍ አምራቹ ጎጃም የሚፈራበት ምንም ምክንያት አይኖርም።

ከወሎና ከጎንደር የተሰባሰቡ የወያኔ አገልጋዮች እንኳን ጎጃምን ወሎና ጎንደርን እንደማይወክሉ ማንም ያውቃል። ወልቃይትና ራያ ፍዳ ሲቀበሉ እኒህ ሰዎች ያደረጉት አንድም ነገር የለም። አግድም አደጉ አለምነው መኮንን ለሀጫም እያለ አንቀጥቅጦ ሲገዛ የኖረው ሁሉንም የአማራ ክልል ሕዝብ ነው። ይህን ባለጌ ሰው በመቃወም “በሚያዋርደን ሰው አንገዛም!” ብሎ ሰላማዊ ሰልፍ ያደረገው የባህርዳር ሕዝብ በሀይል ተበትኖ አለምነው በስልጣን እንዲቀጥል የተደረገው ክልሉን በበላይነት ከተቆጣጠሩት ወገኖች ውስጥ ያለ በመሆኑ ነው። ይህን ያደረገው የጎጃም ወይም የሸዋ ሰው ቢሆን ኖሮ ሳይውል ሳያድር ከስልጣኑ ይባረር እንደነበር በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።

ግን አንድ ፍጥጥ ያለ ችግር አለ፣ ገዥወቻችን የተሰባሰቡት ከተወሰነ አካባቢ መሆኑ፤ በጎጃም ኮታ ሌሎች ተገልጋይ መሆናቸው! ከወሎና ከጎንደር ተጠራርተው የተሿሿሙብን ዱርየወች እንደፈለጋቸው እንዲያደርጉን ልንፈቅድላቸው አይገባም። በአማራነት መሰባሰብ ማለት በወሎና በጎንደር ሰው መተዳደር ማለት ከሆነ አማራነት ጥንቅር ይበል፤ አማራነት በአፍንጫችን ይውጣ! ተሾመ መንግሥቱ (ሀባር) ምሥራቅ ጎጃምን በአስተዳዳሪነት አስደግድጎ የገዛ፣ የጎዛምንን ወረዳ ሕዝብ ወክሎ ፓርላማ ገብቶ ሲያሾፍብን የኖረ፣ የጎንደር ሰው ነው። የቢውኝ ወረዳ አስተዳዳሪ ሆኖ ጠበንጃ ደብቃችኋል እያለ ሲገርፍ የነበረው በኋላም ቢቡኝ መርጦኛል ብሎ ፓርላማ የገባው አቶ አባቡ ከዚያው ከጎንደር የመጣ ሰው ነው። በሞጣ፣ በቢቸና፣ በዳሞት፣ በአገውምድር፣ በባህርዳርና በመተከል ውስጥ በሚገኙ ወረዳወች በአማራ ስም የተሾሙብን ጎንደሬና ወሎየወች ብዙ ናቸው። እነዚህ ተሿሚወች ሀገሬውን ከመጨቆን ወጥተው ለተሾሙበት አካባቢ የሰሩለት የልማት ስራ የለም። ባርነትን ተቀብለው እኛን የባሪያ ባሪያ አድርገው ሲመለከቱን የነበሩት ከሁለቱ አካባቢወች የመጡ የአማራ አድዋወች ዛሬ ደግሞ ይባስ ብለው የስራ አስፈጻሚውን ቦታ ካለሀፍረት ተቆጣጥረውታል። በራሱ ሰዎች ሊተዳደር የሚገባው የጎጃም ህዝብ በሌሎች ተገዥ ሆኖ ማየት ከምንም በላይ ያማል። “ከመናቅ በጨሬ መዛቅ!” ፣ አዎ እንደዚያ ይሻላል። ይህን በመቃወም በዌብሳይታቸው ገብቸ ለአማራ ብዙሀን መገናኛ ድርጅት ቅሬታየን አሰምቸ ነበር። እንዲህ ብየ፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  አንድነት፤ አንድነት ስንል አምሳ ዓመት ሊሆነን ነው- - አክሎግ ቢራራ (ዶር)

“ለአማራ ብዙሀን መገናኛ ድርጅት ባሕርዳር
እንደምን አላችሁ?
የሚጠዘጥዘኝን ቁስል የሚያሽር መድሀኒት ባገኝ ብየ ነው ወደ እናንተ መምጣቴ። የአዴፓ ስራ አስፈጻሚ ምርጫ በእጅጉ ስሜቴን ጎድቶታል። ባለኝ መረጃ መሰረት ወሎና ጎንደር ቁልፍና አብዛኛውን ስልጣን እንደተቆጣጠሩት ነው።

ኢሕዴን ሕወሀትን እየመራ ወደአማራው ክልል ሲዘልቅ ተዋጊና የድርጅቱ አመራር የነበሩት በአብዛኛው ከነዚህ አካባቢ የበቀሉ ሰዎች ናቸው። ወያኔ ደርግን ለመጣል ትልቁን ድርሻ የወሰድሁ በመሆኔ ከማንም የበለጠ ስልጣን ይገባኛል ብሎ ከሁሉም አፍ እየነጠቀ ሲዘርፍ ኖሯል። የአሁኑ አዴፓ አመራሮችም የወያኔን ፈለግ በመከተል በትግል ውስጥ ጉልህ ተሳትፎ ያደረግን እኛ ነን በሚል መንፈስ በብአዴንነታቸው ጊዜ ስልጣኑን ከጎሳቸው ውጭ መጥተው ከተጫኑብን ጋር ተካፍለው ጎጃምና ሸዋን የገፉበት ሁኔታ እንደነበረ የሚረሳ አይደለም።
በመላው ኢትዮጵያውያን ትግል፣ ለውጥ የሚመስል ነገር እየታየ ነው በሚባልበት በአሁኑ ወቅት የአዴፓ ሥራ አስፈጻሚ አባላት ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል መልኩ ወሎየወችና ጎንደሬወች እንደሆኑ እየተነገረ ነው። ደርግን ለመጣል በመታገላቸው ስልጣንን እንደካሳ ማየታቸው ከሆነ የሚጠቅም አይደለም።

ደርግ በመውደቁ የአማራ ሕዝብ ለከፋ ችግር ተጋለጠ እንጅ ያገኘው በጎ ነገር የለም። የደርግን መውደቅ ተከትሎ ለመከራ የተጋለጠው በዋናነት የአማራው ሕዝብ ነው። በዚህ ወቅት የአማራ ወኪል ነን ሲሉ የነበሩት የድርጅቱ ሰዎች የግፎችን ሁሉ ግፍ እንዲቀበል የአማራውን አንገት ሰብረው ይዘው እንዳስጨፈጨፉን መቸም ቢሆን የሚረሳ አይደለም። ይህን ወንጀላቸውን እንደጀብድ ወስደው አማራን መግዛት ያለብን እኛ ብቻ ነን ብለው መቧደን የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር የሚያስጠይቅ መሆኑ አይቀርም።

እኔ ጎጃሜ ነኝ። አማራው ተደራጅቶ ራሱን እንዲከላከል ለማስቻል አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ ከማድረግ አልቦዘንሁም። ለወገኔ የቻልሁትን ሁሉ ለማድረግ ስነሳ አማራው ሳይከፋፈል እጅ ለእጅ ተያይዞ መብቱን እንዲያስከብር በማሰብ እንጂ ወያኔን ጥሎ በአካባቢ ልጅነት በተሰባሰቡ ሰዎች እንዲገዛ በመፈለግ አይደለም።

የፖለቲካ ጥያቄ ከስልጣን እና ከውክልና ውጪ የሚታሰብ አይደለም። ከዚህ በፊት ብዙ የጎንደርና የወሎ ሰዎች በጎጃም ውስጥ በወረዳና በዞን ኃላፊነት ሲያገለግሉ፣ የተሾሙበትን ሕዝብ ወክለው ፓርላማ ሲገቡ አይተን እንዳላየን ሰምተን እንዳልሰማን ሆነን ሁሉንም በጸጋ ተቀብለን እዚህ ደርሰናል። አሁን ደግሞ ሁኔታወች ይሻሻላሉ ብለን ስንጠብቅ የቀጠለው ግን ያው የቀድሞው አሰራር ነው። አንድ አማራ እያልን የጮህነው ጎንደርና ወሎ እንዲገዙን ፈልገን መስሏቸው ከሆነ ትልቅ ስህተት ነው።

እንደሚመስለኝ እነዚህ ከሁለቱ አካባቢወች የወጡ ሰዎች የአማራውን አንድነት ለመበተን ቆርጠው የተነሱ ሳይሆኑ አይቀርም። ለማም ጠፋም ራስን በራስ ማስተዳደር ብቸኛ መፍትሄ እንደሆነ ተደርጎ በሚሰራበት በዚህ ዘመን በአማራ ስም ስልጣንን ጠቅልሎ መያዝ ተገቢ አይደለም ብቻ ሳይሆን ያስተሳሰረንን ገመድም የሚበጥስ ነው።

የአዴፓ ሥራ አስፈጻሚወች በክልሉ ም/ቤት አባላት አብላጫ ድምጽ የተመረጡ ናቸው ሊባል ይችል ይሆናል። እንዲያ ከሆነ ጎጃምን ወክለው የምክር ቤት አባል የሆኑት ሰዎች ስለፖለቲካ በቂ ግንዛቤ የሌላቸው የዋህ አማሮች ናቸው ማለት ነው። ድርጅቱም ቢሆን አቅም ያላቸውን ጎጃሜወች በማሸሽ ለስልጣን የማይገዳደሩትን ሲያሰባስብ ነበር ብሎ ማሰብ ስህተት አይሆንም።

አማሮች ያልተመለሱ ከፍተኛ ትግል የሚጠይቁ ብዙ ችግሮች አሉብን። በዚህ ወቅት ማንንም የሚያሳዝን አግላይና አስኮራፊ ሥራ መስራት ጎጅ እንጅ ጠቃሚ ተደርጎ መታሰብ አልነበረበትም። ይህን ያደረጉ ሰዎች አሁንም አማራውን በመከፋፈልና በማዳከም የወያኔን ተልዕኮ ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱ ናቸው፤ አሊያም ሞኛሞኝ ናቸው። ከእንግዲህ በኋላ ማንም በሞግዚት ሊተዳደር ፈቃደኝነቱ የለውም። በአማራነት ተሳስበን በዕኩልነት ተያይተን መቀጠል ካልቻልን ብቸኛው ምርጫችን የአማራነትን ጎጆ ታግሎ ማፍረስ ይሆናል። በአማራ ስም ማንም እንዲጨፍርብን አንፈቅድም። የአማራ አድዋወች አደብ ግዙ!”

ቆይቸ ሳየው ግን እንኳን መልዕክቱ የአስተያየት መስጫውም በቦታው የለም። አይገርምም! እዚያም ያሉት እነሱ ሊሆኑ ይችላሉ። ችግሮች መፍትሄ የሚያገኙት በአፈና መስሏቸው ከሆነ ትልቅ ስህተት ነው።

ወያኔ በህዝብ ላይ ግፍ ሲሰራ የትግራይ ህዝብ ዝም ብሎ ተመልክቷል ብለን ስንጮህ ኖረናል። በአማራ ስም የሚፈጸመውን ደባ ዝም ብሎ የሚመለከተው ወገንስ ምን ሊባል ይሆን? ጎንደርና ወሎ ሲሿሿሙ “ምን ነካችሁ! ድርጅቱን የአማራ አስመስሉት እንጂ! ሌሎች ወገኖቻችን የመገለል ስሜት እንዳይሰማቸው ማድረግ ይኖርብናል። በዚህ መልኩ ከቀጠልን ከወያኔ በምኑ ተለየን!” ብለው ቅሬታቸውን ያቀረቡ ጎንደሬወችና ወሎየወች ስለመኖራቸው አልሰማሁም። የአማራነት ከረጢት ቢቀደድና የታፈነው ነጻ ቢሆን ከመምረጥ ውጪ ሌላ አማራጭ ያለ አይመስለኝም።

ተጨማሪ ያንብቡ:   ከአድዋ ድል ብቻ ሳይሆን ከክፉ ቀን ድልም እንማር!!  - ከ ይሁኔ አየለ

ፍርሀት ተፈጥሯዊ ነው። የእኔ ፍርሀት ከሌሎች ይበልጥ እንደሆነ አላውቅም። ሆኖም ግን አንድ በእርግጠኛነት ልናገር የምችለው ነገር ቢኖር በፍርሀት የተነሳ የማላምንበትን ነገር አድርጌ የማላውቅ መሆኑን ነው። በጥቅም ወይም በኃይል ሊያስፈራሩኝ በሞከሩ ቁጥር የት እንደነበረ የማላውቀው ወኔና እልህ በመላ ሰውነቴ ይሰራጫል። ጥቃት እንደማልወድ ከዚህ በፊት በጻፍኋቸው ጽሁፎች ተናግሬአለሁ። የአዴፓን የሥራ አስፈጻሚ ምርጫ ካየሁ በኋላ ንዴቴን መቆጣጠር እስኪያቅተኝ ድረስ ነው የመጠቃት ስሜት የተሰማኝ።

ጎጃም ጦር ወርውሮ በሳተበት እጁ እንጀራ ቆርሶ ለመብላት የሚቀፈው እልኸኛ ሕዝብ እንደሆነ የሚያውቅ ያውቃል። እኔም የወጣሁት ከዚህ ሕዝብ አብራክ ነው። ጎጃም በሰላም ጊዜ ጎበዝ አምራች በክፉ ጊዜ ጀግና ተዋጊ ሕዝብ ነው። ጠላቶቹን ሲመክት የነበረው በልብ እንጅ በጦር መሣሪያ አልነበረም።

በተለያየ ጊዜ በጎጃሞች የተደረጉ የአመጽ እንቅስቃሴዎች የተዳፈኑት አንድም በስሜት የተነሳሱ ስለነበሩ ነው። ግብር በዛ ሲባል ተጠራርቶ ይወጣና ግብር ተሻሻለ ሲባል ተመልሶ ወደቤቱ የሚገባ፣ ከዚህ የዘለለ አላማ ያላነገበ፣ ያልተደራጀና ማዕከላዊ አመራር የሌለው በመሆኑ ነው። ሁለትም ሕዝቡ ሰላም ወዳድ በመሆኑ፣ ሲጨቆን ዘራፍ ብሎ የሚወጣ ቢሆንም፣ በሰላም ጊዜ ግን ተበድያለሁ ብሎ ነገር የማያላምጥ፣ ወይም ለመዝረፍና ስልጣን ለመቀማት የማያደባ በመሆኑ ነው። በዚህም ምክንያት በጥርሳቸው እየሳቁ ሲደራጁና ከጀርባ መሳሪያ ሲያከማቹ በኖሩ ኃይሎች ሲጠቃ ኖሯል፤ አሁንም ቢሆን መሣሪያ በታጠቁ የወያኔ አንጋቾች ተረግጦ እየተገዛ ነው። ሦስተኛው ምክንያት የመሬቱ አቀማመጥ ነው። ጎጃም ለእርሻ የተመቸ ሜዳማ በመሆኑ ለሽፍትነት ብዙም አመች አይደለም። ጎጃሞች ሲሸፍቱ ወደአባይ በርሀ ይወርዱና መሹለክለኪያ የሚያደርጉት የጎንደርን፣ የወሎን እና የሸዋን ወጣ ገባ መሬት ነው። በጎንደር የአርበኞች ግምባር እንቅስቃሴና የበላይ ዘለቀ የአርበኝነት ታሪክ ለዚህ ዋና አስረጅወች ናቸው። እኩል ሰልጥነን፣ አንድ አይነት የጦር መሳሪያ ታጥቀን፣ በወታደርነት በተሰለፍንባቸው ቦታወች ስለፈጸምናቸው የጀግንነት ተግባሮች ከጎናችን ተሰልፈው ይዋጉ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ በተቃራኒ ወገን ሆነው ሲዋጉን የነበሩት ሰወች ጭምር የምስክርነት ቃላቸውን ሊሰጡ እንደሚችሉ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።

ነጋ ጠባ ሴራ በመጎንጎንና መሳሪያ በማከማቸት ልምድ ያላቸው አካባቢወች ተደራጅተው በየጉድባው ሰልጥነው እየተሹለከለኩ ሀገርና ሕዝብ ሰላም ሲነሱ እዚህ ደርሰዋል። ከእንግዲህ በኋላ እኛ ጎጃሞች በነዚህ ሰዎች እንድንገዛ አንፈቅድም። ወደነበርንበት የክብር ደረጃ ለመመለስ በጎጃሜነት ተደራጅተን ሞትን ንቀን ለትግል መነሳት ይኖርብናል። መብቱን ለማስከበር የማይቆርጥ ሕዝብ መብት ለመርገጥ በማይፈሩ ቡድኖች ተጥሎ በእግር መረገጡ ግድ ነው።

ጎጃም አማራ ሳይሆን የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የአገው፣ የሽናሻ፣ የወይጦ፣ የጉሙዝ ደም ያለበት ቅይጥ ሕዝብ ነው። የጎጃም ህዝብ ጎጃሜ ነው። ጎጃም ከአማራነት ሳጥን ወጥቶ ራሱን በራሱ ማስተዳደር እንዲችል የክልል ዕውቅና ሊሰጠው ይገባል። በአማራ ስም ታስሮ፣ በዞን ደረጃ ተከፋፍሎና አንሶ እንዲገኝ የተደረገው ለብዝበዛ እንዲመች ስለተፈለገ ብቻ ነው። ጎጃምን የማሳነስ ስራ መሰራት የተጀመረው በወያኔ ጊዜ እንዳልሆነ ከላይ ገልጫለሁ። ሆኖም ወያኔ የአንድ ወረዳ ሕዝብ ብዛት ያህል ቁጥር ለሌለው የሀደሬ ሕዝብ የሀረሪ ክልል እንዲመሰረት ሲፈቅድ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሰፊ ታሪክ ያለውን ጎጃምን ግን በአማራነት ስም ተገዥ ሆኖ በባርነት እንዲተዳደር ማድረግ አልነበረበትም።

እስካሁን ድረስ የአማራውን መደራጀት ስደግፍ ቆይቻለሁ። አሁን ግን የዕውነት አመመኝ። እንዲህ ያለ ተራ ነገር ሲሰራ የጎንደርና የወሎ ተወካዮች ከማጨብጨብ ወጥተው “የለም አይሆንም!” ብለው ለምን አልተከራከሩም? ብየ በግርምት ራሴን ጠይቄአለሁ።

ይህን ጽሁፍ በማውጣቴ ደስተኛ የማይሆኑ በዋናነት ሸፍጣቸው እንዳይገለጥባቸው የሚፈልጉ ወገኖች እንደሚሆኑ አልጠራጠርም። እኒህ ሰዎች የአማራውን ትግል ለመበተን የተነሳ የወያኔ ተላላኪ አድርገው ሊያሳድሙብኝ ይሞክሩ ይሆናል፤ ወደኃይል እርምጃ ለመሻገር ሊያስቡም ይችላሉ። መረዳት ያለባቸው ግን የተለኮሰን ትግል የበለጠ ያቀጣጥሉት እንደሆነ እንጂ በአፈና ሊገቱት እንደማይችሉ ነው። በራሳችን ሰዎች ተገዝተን ያገኘናቸው በጎ ነገሮች ባይኖሩም ራስን በራስ የማስተዳደር ክብርን መገፈፍ ከባርነት አይለይም። እግር ከወርች አስራችሁ፣ አንደበታችንን ሸብባችሁ፣ ፈጥጦ የሚታየውን ዕውነታ ለመደበቅም ሆነ ትግላችንን ለመግታት እንደማትችሉ አስረግጨ እነግራችኋለሁ።

የጎጃም ክልላዊ መንግሥት እንዲመሰረት እጠይቃለሁ።
ጎጃምን ከባርነት አገዛዝ ነጻ እናውጣ!
የጎጃም ክልል ይመስረት!

 

Share