“መጠየቅ ማንን ይጎዳል? ማስተዋልስ ማንን ያሳፍራል?”

ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ
የኢኮኖሚክስ መምህርና ጸሓፊ
(ሸክም የበዛበት ትውልድ፡ 2009 እና  የምሥራቃዊት ኮከብ፡ 2010 መጻሕፍት አዘጋጅ)

በሀገራችን በየዕለቱ የምንሰማቸው ዜናዎች አስደሳችም – እጅግ አሳዛኝም ናቸው፡፡ በአንድ በኩል ተስፋ ሰጪ – ቀላል በማይባሉ ኹነቶች ደግሞ እጅግ ተስፋ አስቆራጭ ነው፡፡ በአንድ በኩል የሚያረጋጋና እረፍት የሚሰጥ ሲኾን በሌላ በኩል ደግሞ እንቅልፍ የሚነሣ ነው፡፡ አንዳንዱ ለሌሎች ሀገራትም ጭምር ተምሳሌት የሚኾን ሲኾን ሌላው ሰው መኾንን ጭምር እንድንጠየፍ የሚያደርግ ነው፡፡

ከነዚህ በሁለት ጽንፍ ካሉ ነገሮች አብነት እንኳ ብናነሣ ከመልካሙ ብንጀምር ለብዙ ዓመታት ከሀገራቸው ርቀው የነበሩ ግለሰቦች፣ ቡድኖችና ድርጅቶች ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውና በበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ የሚታዩ መነሣሣቶችና ተጨባጭ እንቅስቃሴዎች ተስፋ የሚሰጡና ሊበረታታ የሚገባው ተግባር ሲኾን በሌላ በኩል በሻሸመኔ ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት – በአደባባይ ሰው ቁልቁል ሲሰቀል በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ተመልከተናል፡፡ በቡሬ ዳሞት ከተማ በዋንገዳም ቀበሌ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰው ተገሏል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ተፈናቅለዋል፡፡

ድርጊቱን እጅግ የከፋና አሳሳቢ የሚያደርገው ሞታቸው ብቻ ሳይኾን አሟሟታቸውና ድርጊቱን ተከትለው የተከሰቱ ኹኔታዎች እጅግ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ ለምን?
1ኛ. ድርጊቱ ሲፈጸም ብዙ ሕዝብ በአደባባይ ነው፡፡ አንድስ እንኳ አስተዋይና ጠያቂ እንደምን ታጣ?
2ኛ. በየትኛውም ሰብዓዊ፣ ሞራላዊና ሕጋዊ መለኪያዎች ድርጊቱን የሚደግፍ አመክንዮ አለመኖሩ፤
3ኛ. የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዛኛው ሃይማኖተኛና አማኝ ነውና ይህ ድርጊት ከዚህ ማንነቱ ጋር ተስማምቶ የማይሄድ መኾኑ፤
– አማኝና ሃይማኖተኛ ራሱ ላይ እንዲደረግበት የማይሻውን ሌላው ላይ አለማድረግ የአስተምህሮቶቻቸው ትልቅ ዕሴት ነውና ይህ ፍጻሜ ይኾንበት ዘንድ የሚፈቅድ ማን ነው?
4ኛ. ድርጊቱ በጥቂቶች የተፈጸመ ቢኾንም አብዝሃ በመመልከትና በዝምታ ከመተባበራቸውም በላይ ድርጊቱ ያላስቆጣቸው መኾኑ እንደምን ከተጠያቂነት ነጻ ሊያደርጋቸው ይችላል?
– “ጠላትህን እንደራስህ ውደድ!!!” ብላ ቀን ከለሊት ለረዥም ምዕተ ዓመታት በምታስተምር ቤተ ክርስቲያን ከ2,000 ምዕመን፣ ካህናትና ሰባክያን ባሉበት ድርጊቱ ሲፈጸም ዕውን ዕምነት ከወዴት አለ? አስተምህሮቱስ ከወደምን ተሸሸገ? ዕውን ፈጣሪስ ይህን አይመለከትምን? የዚህን ሰው ዕንባና ስቃይ አይመለከትምን? ዕውን ከሞት በኃላ ፍርድ ሲሰጥ ይህ አይነሣምን?
– ክርስቶስን የሰቀሉት ጥቂቶች ናቸው – ብዙዎች ግን ተባብረዋል፡፡ በዝምታቸውና በመመልከታቸውም ውስጥ የትንቢት መፈጸሚያ ትውልድ ኾነዋል ብላ የምታስተምር ቤተክርስቲያን ጊቢ ውስጥ – ይህ ሲፈጸም ማን ከተጠያቂነት ይድናል?
5ኛ. ድርጊቱን የሰሙ ወገኖች እንደምን በቁጣ ወደ አደባባይ ወጥተው ቁጣቸውን መግለጽ አልቻሉም? እንደምን ብዙዎችን የሚያስነባና ቁጭት የሚፈጥር ሳይኾን ቀረ? ለምን? ምን አገታቸው? ድርጊቱስ ለምን ተድበስብሶ ቀረ?
– ይኸው ጉዳዩ የተወሰኑ ቀናት መነጋገሪያ ኾነ – ከዛ በቃ!!! ነገር ግን የሟች ቤተሰቦች ዕድሜ ልካቸውን ሲያስታውሱት የሚኖር ፍጻሜ ይኾናል፡፡
6ኛ. የሃይማኖት ተቋማት ድርጊቱን ያለ ልዩነት ትርጉም ባለውና ተጽዕኖን በሚፈጥር ኹለንተናዊ መንገድ አለማውገዝ – ስለምን ይኾን? ሚድያዎችስ ተገቢውን ሽፋን ሰጥተው ድርጊቱ ዳግም እንዳይከሰት ትርጉም ያለው ተግባራትን ማከናወን እንደምን ተሣናቸው?
7ኛ. ምሁራን በብዕራቸውና በአንደበታቸው ድርጊቱን ትርጉም ባለው መንገድ ሳይተነትኑት ለምን ቀሩ?
8ኛ. ከኹሉ በላይ ድርጊቱ ከተፈጸመ በኃላ ድርጊቱን የምናይበት ዕይታና ትንታኔ ስለምን ተለያየ? የአንድ ሀገር ዜጎች ኾነን – አንዳንዱ ድርጊቱን ሰምቶ እንዳልሰማ፣ አይቶ እንዳላየ ሌላው ደግሞ ይጮህና ደጋግሞ ይጽፍበት ዘንድ፤ አንዳንዱ የድርጊቱን ትክክለኛነት ለማስረዳት የሄደበት ርቀት ሌላው ደግሞ የድርጊቱን አስከፊነት ለመግለጽ የሄደበት ጫፍ – ዕውን በአንድ ሀገር ዜጎች መሐከል ይህን ያክል ልዩነት እንደምን ሊስተዋል ቻለ?

ተጨማሪ ያንብቡ:  ደቡብ ሱዳን-የሰላም ዉልና ጦርነት

እነዚህን ነጥቦች ሰፋ አድርጎ ከመመልከት ባሻገር ድንበር የሚሻገሩና ከማንም በላይ የሰው ልጆችን ኹሉ ያለ ልዩነት ከሚመለከቱ ነጻነት፣ ፍትህ፣ ነጻ ፍቃድና ተጠያቂነት ከሚሰኙ ዐበይት ማዕቀፎች አንጻር ተመልክተነው ይኾን? ለምን? በዚህ ግልጽ የማያሻማና የማያጠያይቅ ጉዳይ ላይ እንኳ ትርጉም ባለው መንገድ መግባባት ካልቻልን እንደምን እጅግ ሰፊ፣ ውስብስብና የተጠላለፉ ኹለንተናዊ ፍላጎቶችና ግንኙነቶች ባሉባቸው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ኹነቶች ላይ መግባባት ይቻላል?
ይህ በንዲህ እንዳለ የሥልጣን ፖለቲካችን ዛሬም እንደትላንቱ ከስሜት ወደ ሀሳብ፤ ከሀሳብ ወደ ዕሳቤ፤ ከዕሳቤ ወደ ርዕዮት ከፍ ብሎ ይኾን? በድርጊትና አሰራርስ ቢኾን ከጓዳዊነት ወደ አደባባይነት ተሻግሮ እንደኾን እንጂ በእምነት (በአስተሳሰብና አመለካከት)፣ በእውቀት (በስልትና ስትራቴጂ) እና በድርጊት (በተግባር) ደረጃ የተቋማዊነት ጉዳይ ገና አይደለምን? ከትኩረት አንጻርስ ቢኾን ከጥቃቅንና አነስተኛ ጉዳዪች ወደ ትርጉም ወዳላቸው ዐቢይ ጉዳዮች መቼ ተሻገርን? ከዕይታ አንጻርስ ቢኾን ከትላንት ትርክትና ንትርክ ወጥተን ዛሬና ነገ ማድረግ ስላሉብን ጉዳዮች መወያየት መቼ ጀመርን?

አንድ ነን እንላለን ነገር ግን አካሄዳችን የተለያየ ነው፡፡ ምላሳችን እንጂ ዕምነታችን፣ ዕውቀታችንና ድርጊታችን የመለያየት ነው፡፡ ብዙዎች ስለሀገራዊነት እናቀነቅናለን ይላሉ ነገር ግን በከባቢያዊነትና መንደርተኝነት እሰጣ ገባ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ሰፊ ነን ይላሉ ነገር ግን እጅጉን ጠበውና ወርደው ይገኛሉ፡፡ ምክንያታዊ ነን ይላሉ ነገር ግን ስሜታዊነትና ፍረጃን ገንዘባቸው ያደርጋሉ፡፡ ሌሎችን በሴረኛ፣ በድብቅና በፍረጃ ይከሳሉ – እነሱ ራሳቸው ግን ሴረኛነት፣ ድብቅነትና ፈራጅነት ዋነኛ መለያቸው ነው፡፡
ብዙዎች እጅጉን አብዝተው መኾን ስላለበት ነገር አብዝተው ይደሰኩራሉ፡፡ ነገር ግን እነሱ ራሳቸው መኾን ሚገባቸውን ያልኾኑና ማድረግ ሚገባቸውን ያላደረጉ ኾነው ይገኛሉ፡፡ ዘረኝነትን እናወግዛለን ይላሉ ነገር ግን እነሱ ራሳቸው በማውገዝ ውስጥ ዘረኝነትን ያስፋፋሉ፡፡ ቂመኝነትን እንጠላለን ብለው ቂመኝነትን ለማውረስ ቀን ከለሊት ይተጋሉ፡፡ ይህ አይጠቅምም ብለው ብዙ ነገር ያደርጉና አይጠቅምም ያሉትን ፈጻሚ ፊት አውራሪዎች ራሳቸው ኾነው ይገኛሉ:: ታድያ ትርጉም ያለው መፍትሔ እንደምን ከወዴት ይምጣ?

ተጨማሪ ያንብቡ:  አማራ የተሰጠውን ዕድል እንደማያበላሽ ተስፋ አደርጋለሁ!! - አምባቸው ዓለሙ (ከደሴ)

ዲዮጋን የተባለ ፈላስፋ በቀን በብርሃን ፋኖስ ይዞ ሲዞር “ምን ነው በቀን ብርሃን – ፋኖስ ይዘህ ትዞራለህ?” ቢሉት “እውነተኛ ሰው እየፈለኩ!!!” አለ የሚል ነገር ላለፉት በርካታ ዓመታት ሲነገር የነበረ ትልቅ ቁም ነገር ነው፡፡ ዕውን ኢትዮጵያዊ ዲዮጋን ማን ነው? ዕውነትን የሚፈልግ ማን አለ? በቀን ብርሃን በፋኖስ የሚፈለግ ኢትዮጵያዊስ ይኖር ይኾን?
በአንደበቱ በአደባባይ ሀገራዊነትን እያነሣ በሳሎንና በጓዳ – በመንደርተኝነትና ከባቢያዊነት ያልተጨማለቀ ማን ነው? “ሃይማኖተኛ ነኝ” እያለ በሴረኝነት፣ በአስመሳይነት፣ በሃሰተኛነትና በፍረጃ ድርጊት ያልተጥለቀለቀ ማን ይኾን? በእያንዳንዱ እንቅስቃሴው ውስጥ ኹሉ – ፈጣሪ ያየኛል – ይሰማኛል – ከሕይወት በኃላም ፍርድ ይሰጣል እያለ ኹለንተናዊ ተግባራቱን የሚያከናውን ከወዴት ይገኛል?

በጥቅሉ እንደሀገር እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ትርጉም ባለው መንገድ ለምን? ምን ለማግኘት? መቼ? የት? በማን? እንዴት? ፋይዳው ምንድነው? እያሉ መጠየቅ ማንን ይጎዳል? ይህንን ማስተዋልስ ማንን ያሳፍራል?” ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድን የኹሉ ነገር ማዕከል ወደ ሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!
ቸር እንሰንብት!

Previous Story

የጎጃም ክልል ይመስረት – ከይገርማል

Next Story

ኦነግ  (OLF) በአስቸኳይ ትጥቅ ይፍታ!! – ከሙሉቀን ገበየሁ

Latest from ነፃ አስተያየቶች

አትዮጵያ ያን ዕለት

ግም ሞት 20’ 1983 .ዓ.ም. ለህወሀት /ኢህአዴግ ልደት ለኢትዮጵያ እና ለብዙዉ ኢትዮጵያዉያን የዉድቀት ፣ጥልመት እና ሞት

የፋኖ አደረጃጀቶች አንጻራዊ ወሳኝነትና የእስክንድር ነጋ ወሳኝ ሚና

ጭራቅ አሕመድ ያማራን ሕዝብ ለመጨፍጨፍ የተነሳው  በእስክንድር ነጋ ላይ ግልጽ ጦርነት እከፍታለሁ ብሎ በመዛት ስለነበር፣ ያ ማራ ሕዝብ ደግሞ ጭራቅ አሕመድን  ጨርቅ በማድረግ ቅኔያዊ ፍትሕ  (poetic justice) ሊሰጠው የሚገባው  በእስክንድር ነጋ መሪነት ነው።    ________________________________________ ያማራ ፋኖ የጎንደር፣ የጎጃም፣ የቤታማራና የሸዋ

Share