ውሉን የሳተ የትግል ጉዞ – ከእውነቱ ፈረደ   

የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚቋቋሙበት አንዱና ዋነኛው ዓላማ የመንግሥትን ሥልጣን ለመጨበጥ ነው።የመንግሥቱን ሥልጣን የሚጨብጡበት መንገድ እንደ አገሩ የፖለቲካ ሥርዓት የተለያዬ ቢሆንም ተልእኮአቸውን ግን አይቀይረውም።

አንድ የፖለቲካ ድርጅት የራሱ ህልውና መግለጫ የሚሆን ራዕይ ፣ርዕዩተዓለም(ፍልስፍና ወይም አይዶሎጂ)፣አማራጭ የፖሊሲ ሃሳብ መዋቅርና በመዋቅር የታቀፉ አባላት ፣አባላቱን ከሕዝቡ የሚያገናኝበት መረብና ለሕዝቡ የሚያቀርበው መርሃግብር(ፕሮግራም)አባላቱ የሚተዳደሩበት ደንብና መመሪያ ካለው ድርጅት ይባላል።ይኸው ድርጅት ለመንግሥት ሥልጣን የሚታገል በመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲ እንለዋለን።በዚህ መልክ የተገለጸ አካል ህልውና አለው ማለት ነው።

ሆኖም ግን ይህን መሰል ተቋም (ፓርቲ)ስለራሱ ወደ መንግሥትነት መምጣት ሳይሆን ስለሌላው ፓርቲ ማሸነፍ የሚያስተጋባና የሚታገል ከሆነ የዚህ ፓርቲ ህልውና በቅርጽ እንጂ በይዘት ባዶ ፣ንብ የሌለበት ቀፎ ነው።ዓላማውንና ተግባሩን የማያውቅ ባተሌ ድርጅት ነው።ባለቤት የሌለው መንደር በመሆኑ ከሌላ መንደር በመጡ ለመመራትና የነሱን ፍላጎት ለማራመድ ወዶ ገብ ደባል ይሆናል።

ኢሕአዴግን ከአራት ኪሎ ቤተመንግሥት በማስለቀቅ በሌላ የፖለቲካ ፓርቲ (ፓርቲዎች)በሚመራ መንግሥት ለመቀዬር የሚደረግ ትግል የቱን ያህል ሰላማዊ ቢሆንም የጨዋታውን ዓላማ ግን ሊገለብጥ አይችልም።ተፎካካሪ ወይም ተጋጣሚ ቡድኖች ቦታ ቦታቸውን ይዘው በጫወታው ሕግ መሰረት ሊፎካከሩ እንጂ አንዳቸው የራሳቸውን ማሊያ አውልቀው የሌላውን በማጥለቅ ከተቀላቀሉ ዳኛው ጨዋታውን ከማስቆም የተለዬ ምርጫ አይኖረውም፤ዳኝነት በተለያዩ አካላት መካከል የሚደረግን ውድድር ፍትሃዊነት የሚቆጣጠርና የሚያራምድ ነውና!ጨዋታው በመልኩ ባይጠናቀቅም የጨዋታው ውጤት ግን ማልያውን ባወለቀው ቡድን ተሸናፊነት ይመዘገባል።ምክንያቱም ትጥቃቸውን ፈትተው በገዛ ፈቃዳቸው ህልውናቸውን በትነው እጅ ሰጥተዋልና ነው።ከዚያ ሰዓት ጀምሮ ህብረተሰቡም ሆነ  ደጋፊው(ቲፎዞው) እንደ ጨዋታው አካልና ነጻ ቡድን አድርጎ አይቆጥራቸውም።እነሱም በአንድ ጨዋታ ላይ አሸናፊ ሆኖ ስለመውጣትና ፣ህብረተሰቡን ለዓላማው ስኬታማነት ማድረግ ስለሚገባው ጉዞ በተግባር ሆነ በቴዎሪ የማስተማር ፣አቅጣጫ የማመልከት ችሎታ አይኖራቸውም ማለት ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዲያስፖራ ሆይ! ዘራፊዎች እንደገና ሊያፈርሱት ተሚችሉት ጎጆ በፊት ፋኖን ገንባ!

በአንጻሩም ተፎካካሪ ነን ባይ ድርጅቶች ከፉክክሩ ጨዋታ ውስጥ ገብተው ሳለ፣ከጨዋታው በፊት ወይም በመሃሉ ለሕዝብ ዳኝነት ሳይደርሱ የሚፎካከሩትን አካል ከደገፉ ከጨዋታው በራሳቸው ፈቃድ ወጥተዋል ማለት ነው።ታዳሚው ወይም ደጋፊ ሕዝብም ማልያ በመልበስ እንዳጃጃሉት የእግር ኳስ ቡድኖች አውቆና ለቁም ነገር እንደማይበቁ አይቶ ይሸሻቸዋል እንጂ ለዳግመኛ ጊዜ አይታለልላቸውም፤ዓይናችሁ ላፈር ይላቸዋል።ይህ የፖለቲካ ጨዋታ የመግቢያ ዋጋ የሚከፈልበት እስታዲዮም ውስጥ የሚከናወን ቢሆን ኖሮ ታዳሚው ተሸውዶ፣ ገንዘቡንም ተቀምቶ እቤቱ ገባ ማለት ነው።ዱሮውንስ ቢሆን ከማያዛልቁ ጋር መጓዙ ውጤቱ ይህ አይደል?ደካሞችን አምኖ መሰለፍ  በነፋስ  የሚበታተንን ዳመናን ከለላ አድርጎ የመጓዝ ያህል ነው።አሁንም በአንዳንድ የስብሰባ አዳራሾችም የዚህ አይነት የፖለቲካ ድርጅቶች ሽወዳና ማጭበርበር በተደጋጋሚ ታይቷል፤የዋሁ ተስፈኛ ደጋፊ ነቄ ካላለ ወደፊትም ሲጭበረበርና ሲዘረፍ ይኖራል።

የጠ/ሚንስትር አብይ መምጣት የኢሕአዴግን መንግሥት አልቀየረውም።ማሻሻያ እንኳን አደረገ ቢባል ያው በኢሕአዴግ ፓርቲ የሚመራ መንግሥት ነው።በሌላ በኩል ተቃዋሚ/ተፎካካሪ/ድርጅቶች  በአገራችን ጉዳይ ያገባናልና የተሻለ ራዕይና መርሃግብር(ፕሮግራም)አንገበናል፣አማራጭ ይዘን ቀርበናልና ሕዝብ ይዳኘን ብለው የተሰለፉ ካሉና ነጻነታቸውንም ካረጋገጡ ምንም እንኳን ባለፈ ስህተታቸው ጥርጣሬ ቢኖረውም ሕዝብ እንደ አማራጭ ሊያያቸውና ሊቀበላቸው ይችል ይሆናል።ወሳኙ የነሱ ብቃትና ቁርጠኝነት ነው።

ስለሆነም የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች የራሳቸዉን ድርጅታዊ ብቃት አጎልብተዉ በመገኘት አማራጭ የፓለቲካ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ከመቼዉም ጊዜ በላይ ተጠናክረዉ  መገኘት አለባቸዉ።ለአሸጋጋሬ ስርአት(መንግስት) ሆነ ለምርጫ ዉድድር አማራጩ በህዝብ መተማመን እንጂ ኢህአዴግን(አብይን)መደገፍ አይደለም።

ጥያቄዉ–ኢህአዴግ ዉስጥ መሻሻል አለ? ከቀድሞዉ ጠቅላይ ሚኒስቴርና ከአሁኑ የቱ ይሻላል? ማንን እንምረጥ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ስልጣኑን ከኢህአደግ ቢቻል በሰላማዊ መንገድ በመዉሰድ ዲሞክራሲያዊ ስርአትን ይገነባ ዘንድ በታማኝነትና በቁርጠኝነት ከህዝብ ጋር በተግባር መቆም ነዉ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  (የሚኒሶታው መድሃኔዓለም ቤ/ክ ጉዳይ) ሁሉም ለበጎ ነው

“ጨዉ ለራስህ ስትል ጣፍጥ ፣ ያለበለዚያ………..” የተባለዉ ተረት እንዳይመሰክርብን እንጠንቀቅ።              ከእንግዲህ ማስተዋል ያለው ያስተውል!

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!  እውነቱ ፈረደ

1 Comment

  1. እግር ኩዋስ ጫወታ ቡድን የመጫወቻ ህግ ሜዳ መለያ ወይም ማልያ ደጋፊ እና ተመልካች ይኖረዋል ተመልካቾች ጥሩ ለተጫወተ የማጨብጨብ ወይም ድጋፍ የማድረግ መብት አላቸው ደጋፊዎች ቡድኑ ተሸንፎም ቢሆን ይደግፋሉ ቡድኑን ከመውደዳቸው የተነሳ ሲሸነፍ ያለቅሳሉ ተቀባይነት ባይኖረውም ከፎቅ ራሳቸውን የወረወሩ ተቃራኒው ቡድን ላይ አደጋ ያደረሱ አሉ ድጋፋቸውን ለተቃራኒው ቡድን የሚያደረጉም ይኖራሉ ያለና የሚጠበቅ ነው::
    ሆኖም ተቃራኒ ቡድን ጥሩ ስለተጫወተ ብሎ በስህተት ካልሆነ ሆን ብሎ በራሱ ላይ ጎል የሚያስቆጥር አይኖርም ቢኖር እንኩዋን ጨዋታው ይቆማል ተጫዋቹም በቀይ ሊሰናበት ይችላል ::
    ለፖለቲካ ቡድኖችም ፀሃፊው እንዳስቀመጠው ከዚህ የተሻለ ምሳሌ አይኖርም አንዳንድ ፓርቲዎች ወያኔ ኢህአዴግ አይቀየርም ሲሉ የነበሩ ናቸው ደግሞም አልተቀየረም
    -ርዕዩቱ( አብዩታዊ ዲሞክራሲ)
    -ህገ መንግስት(በቁዋንቁዋ የተሸነሸነ ፌዴራሊዝም
    የመሬት ይዞታ)
    -የምርጫ ስርአት
    -የአንድ ፓርቲ የበላይነት
    -የአንድ ቡድን የበላይነት በኤኮኖሚው መስክ
    ስለዚህ ፓርቲዎች ለተሻለ አማራጭ ፖሊሲ የተመሰረቱ ናቸው እንጂ ያለው መንግስት ስለተሻሻለ የመሻሻል አዝማሚያ ስለአሳየ አይፈርሱም ወይም ትግል አያቆሙም የሚሰሩትም በተሻለ ፖሊሲ መንግስት ሆነው አገር ለመምራት ነው የራሳቸው መመሪያ ርዕዩተ አለም ደንብና መዋቅር ይዘው ምርጫ ካለ ደግሞ ለመወዳደር ነው::
    አዲሱ ጠ/ሚኒስቴር የሚናገረውም ሆነ የሚያደርገው የሚያስመሰግነው ቢሆንም ከላይ የተጠቀሱት ያልተለወጡ መሰረቶች እስካሉ ድረስ የሃይል ሚዛን ቢዛባ እንኩዋ የተፈቱትን ለቃቅመህ አስገባልኝ በሚል ቀጭን ትዛዝ ነገሮች ወደ ነበሩበት ሊመለሱ ይችላል በማያወላዳ ፖሊሲ ርእዩት እና የህግ ማእቀፍ እስካልተደገፈ ወይም እስካልተሸበበ ድረስ አስተማማኝ ነገር የለም::
    እርግጥ አንዳንድ ነገሮች ጊዜ ይፋልጋሉ ሌሎች ደግሞ ቁርጠኝነት ይጠይቃሉ እንደውም ፓርቲዎች ጠንካራ ርእዩትና ፖሊሲ በመቅረፅ ለወሳኙ ፍልሚያ የሚዘጋጁበት ጊዜ መሆን ይገባዋል እንጂ ተዘናግቶ ማዘናጋት አይገባቸውም ::

Comments are closed.

Share