ሕልውናው አደጋ ያንዣበበት ታሪካዊው የላሊበላ ቅርስ ደብር (ከ ሙሉጌታ ገዛኸኝ)

ኢትዮጵያ የሰው ልጅ ጥንተ ታሪክ መገኛ ሙዚዬም ናት፡፡ ጥንታውያን ነገሥታት በዘመናቸው ከሠሯቸው ታላላቅ የስልጣኔ ክዋኔዎች መካከል የዋሻና የድንጋይ ቅርፀ-ፍልፍል አብያተ መቅደሶች የላቀ ድርሻ እንደሚይዙ ላሊበላን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ የታሪክ ፈለግ በመከተል የአሁኑ ትውልድ በሚያካሂደው የመካነ

ጥናት ቁፋሮ (አርኪዮሎጂ) ምርምር መሰረት አገራችን በሳጥነቷ በአደራ የተቀበለቻቸውን የብዙ ሺህ ዘመናት ታሪክ ቅርስ ለዘመኑ ትውልድ እያስረከበች ትገኛለች፡፡ ለተመራማሪ ሊቃውንቶች የሥነ-አዕምሮ ሀሳብ ግኝት ማረፊያም ሆናለች፡፡ ይህም ለመላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ብሔራዊ ኩራትን አትርፏል፡፡ በታሪካዊ ቅርሶችና በጥንታዊ የዋሻ ቋጥኝ ወጥ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት በማሳነጽና ለዘመናት ተንከባክባ በማቆየት ለአሁኑ ትውልድ በማበርከት ረገድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ጉልህ ሚና እንዳላት የማይካድ ነው፡፡

ከቀደሙት አባቶች መንፈሳዊ ይዘትነት ያላቸውን ቅርሶች ለማቆየት እድል ካገኙት የኢትዮጵያ ነገሥታት መካከል ስመ መንግሥቱ ባዜን መናገሻ ከተማውን አክሱም አቅራቢያ በማድረግ አሻራውን አሳርፏል፡፡ እስከዛሬም ድረስ በድንጋይ ሰሌዳነት በመቃብሩ ላይ በግዕዝና በሳባውያን ቋንቋ ፊደሎች ተቀርጸው ይገኛሉ፡፡ ይህ ንጉሥ በነገሰ በስምንተኛው ዓመት ነበር ክርስቶስ በቤተልሔም የተወለደው፡፡ ከዚያም በኋላ ንጉሥ ኢዛና በአባ ፍሬሚናጦስ ከሳቴ ብርሃ ን ክርስትናን በኦፊሴል በመቀበል የመጀመሪያው ለመሆን የቻለና ወደተለያዩ የአገሪቱ ሥፍራዎች እንዲስፋፋ የበኩሉን መሰረት ጥሏል፡፡

ከአክሱማውያን ወደ ላስታዎቹ የዘአጌዌ ነገሥታት የሥልጣን ሽግግር ተደርጎ ከብዙ የዘመናት ውጣ ውረድ በኋላ በደብረ ሮሀ የከተመው አጼ ላሊበላ ከወጥ አለት ፍልፍል አስራ አንድ አብያተ ክርስቲያናትን አሳነፀ፡፡ ደብረ ሮሀም የንጉሡን ላሊበላን ስም ተረከበች፡፡ አድባራቱም በውስጣቸው የብራና መጻሕፍትንና ልዩ ልዩ መስቀሎችን አካተው ጠብቀው በማቆየት ባለውለታ ሆነው ይገኛሉ፡፡ በኪነ ሕንጻ ውበት ቅርፅ በዓለም እጅግ አስደናቂ ቅርስ ነው፡፡ አገራችን በመካከለኛው ክፍለ ዘመን ለኪነ ሕንጻ አሰራር እድገት የሰጠችውን ትኩረትና የደረሰችበትን ስልጣኔ አጉልቶ ያንፀባርቃል፡፡ እስከዛሬም ድረስ የብሔራዊ ስሜት ማስተሳሰሪያ ዓይነተኛ ሀብት ናቸው፡፡ ከዛግዌ ሥርወ -መንግሥት ነገሥታት መካከል የቅዱስ ላሊበላ መልካም ሥራ በልዩ ልዩ መዛግብት ተፅፎ ስሙ በሰፊው ይወሳል፡፡ የአብያተ መቅደስ ሕንጻዎቹ አሰራር ጥበብ በዓይነታቸው ለየት ያሉ በመሆናቸው ለመጎብኘትም ሆነ ለማጥናት በርካታ ተመራማሪዎች፣ አድናቂዎች ወደ አገራችን የሚጎርፉትን ያህል በአንጻሩ እንደነ በእውቀቱ ስዩም ያሉ ጎልዳፋ ፀሐፊዎች ያሳዝናል ታሪካችንን በማንኳሰስ “የላሊበላ አዳራሾች” በማለት ቢሳለቁም የቅርሶቹ ተቆርቋሪና ከጉዳት ለመታደግ ኢትዮጵያዊ የሆነ ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም ማኀበረሰብ ጭምር መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ይጋብዟል እንግዳ እንደ መልካም ሞላ!

ፖርቹጋላዊው ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ እና ሌሎችም አገር አሳሾች ላሊበላን ከጎበኙ በኋላ እማኝነታቸውን ግሩም አድርገው ፅፈዋል፡፡ አልቫሬዝ “ኢትዮጵያ በፖርቹጊዞች ዐይን” ተብሎ በተተረጎመው መጽሐፉ በእጅጉ የተገረመና የተደነቀበትን ከወጥ ቋጥኝ ተጠርበው የተገነቡትን የላሊበላ ፍልፍል አብያተ መቅደሶች ስሜቱን ኮርኩት ሲያትት ሌላ ሰው በቀላሉ ሊያምነው እንደማይችል እስኪመስለው ድረስ ገልጿል፡፡
እነዚህ መላው ዓለምን ያስደነቁ የላሊበላን ውቅር አብያተ መቅደሶች ተገቢው ጥበቃና እንክብካቤ ይደረግላቸው ዘንድ በዩኔስኮ መዝገብ የሰፈሩ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመሰንጠቅና መናጋት አደጋ እየተጋረጠባቸው መምጣቱ እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ የምንኮራባቸው የኪነ ሕንጻ ውጤት ትውፊቶች መጠነ ሰፊ ትኩረት ይሻሉ፡፡ መልሰን የማንገነባቸውና መቸውንም የማንተካቸው ስለሆኑ አገራዊ ዘመቻ ልክ ለቡናችን ብራንድ(መለያ) ታላቁን ጩኸት በዓለማቀፍ መድረክ በጋራ እንዳሰማነው ሁሉ ጥረት ማድረግ የግድ ይላል፡፡
የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የኢትዮጵያውያን ድንቅ የሥነ ሕንጻ ጠበብት ውጤት መሆናቸው የማያጠራጥር ሲሆን እደ-ጠበብቶቹ አክሱማውያንና አገዎች ያነፁት ቢሆንም ይኸንን ሀቅ ላለመቀበል ልዩ ልዩ አወዛጋቢ መላምቶች የሚያቀርቡ ተንታኞች አሉ፡፡ ዋና ማጠንጠኛቸው ደግሞ ግራም ሐንኮክ “ታቦተ ጽዮንን ፍለጋ” በተሰኘው መጽሐፍ መነሻነት ምናልባት የመስቀል ተዋጊዎች ወይም መቅደሳውያን እንዳነፁት ዘመኑም ቅድስት ከተማ ኢየሩሳሌም በኦቶማን ቱርኮች እጅ መውደቅ ያሳሰባቸው የዘመቻው ተሳታፊዎች አብዛኞቹ በሙያቸው ግንበኞች የነበሩ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ንጉሥ ላሊበላ ጥሪ እንዳደረገላቸው ያትታል፡፡
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ስንክሳር “ገድለ ላሊበላ” እንደተጠቀሰው ንጉሥ ላሊበላ የቅድስና ማዕረግ ያገኘበት በፈጣሪ ተመጥቆ ሰማያዊት ኢየሩሳሌምን ከጎበኘ በኋላ ዳግማዊት ኢየሩሳሌምን በኢትዮጵያ እንዲያንፅ ልቡ ተነሳሳ፡፡ በመላዕክታን እየታገዘ በመንፈስ ቅዱስ እየተመራ ዋሻውን እየፈለፈለ እንደገነባቸው ገድሉ ይተርካል፡፡ በርካታ ምዕመናን እና ጎብኝዎች ከመላው ኣለም የሚጎርፉበት ቅዱስ ላሊበላ የተወለደበት ክብረ በዓል በታህሳስ 29 ቀን በመሆኑ የቤዛ ኩሉ ዓለም የኢየሱስ ክርስቶስ ገና ጋር በደማቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርኣት በደብረ ሮሀ-ላሊበላ በየዓመቱ ይከበራል፡፡
ንጉሥ ላሊበላ ከኣለማዊ ቤተመንግስት ሕንጻ አብልጦ እነዚህን ቅዱሳት አብያተክርስቲያናት በማነጽ ስያሜያቸውን ከቅድስቲቱ ኢየሩሳሌም ስሞች ጋር አዛምዶ ሰይሟቸዋል፡፡ በዘመኑ የምዕመናንን ወደ ቅድስት አገር ኢየሩሳሌም ፈታኝና የረጅም ጉዞ እንግልት ለማስቀረት እንደቻለም ይታወሳል፡፡
በተጨማሪም ልዩ ልዩ ሊቃውንት በማሰባሰብ ሥነ ጽሑፍ እንዲዳብ ጥንታዊ ሀይማኖታዊ እና የነገሥታት ታሪክ ገድልን ያካተቱ የብራና መጻሕፍት ከእብራይስጥና ከአረብኛ ወደ ግዕዝ በእጅ እየተጻፉ እንዲተረጎሙ ላሊበላ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክቷል፡፡ ዛሬም ድረስ በየገዳማቱና አድባራቱ ተጠብቀው የሚገኙ መሆናቸው የሚታወቅ ቢሆንም በየጊዜው ወደ አገራችን በሚመጡ ጎብኝዎች በብዛት የብራና መጻሕፍትን እያሳደዱ መዝረፋቸው አስደንጋጭ ሆኗል፡፡ ቱሪዝምን በማስፋፋት ሰበብ ከፍተኛ ድንግርግሮች እየተከሰቱ ያለ በመሆኑ እውነተኛውን ጎብኝና ሌላ ተልዕኮ ያለውን በቅጡ አጣርቶ በጥንቃቄ ለመለየት የሚደረገው አሁንም ጥረት እምብዛም ነው፡፡ ቅርሶቻችንም በቀላሉ ለአደጋ እየተጋለጡ መሆናቸው የዜና ዘገባዎች ያመላክታሉ፡፡ ሊታሰብበት እንደሚገባ ግልፅ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በአገር ውስጥ የሚገኙ የብራና መጻሕፍት ብዛት በአግባቡ ተመዝግቦ ጥበቃ እንዲደረግላቸውና እንዲጠኑ የሚመቻችበት ልምድ የበለጠ ማዳበር አስፈላጊ ነው፡፡ በልዩ ልዩ የታሪክ አጋጣሚዎች በውጭ አገራት የተመዘበሩ ቅርሶቻችን ለምሳሌ፡- በዘመነ መሳፍንት ወቅት በጎንደር ለረጅም ጊዜ የኖረውና የአባይን ምንጭ ፍለጋ መጣሁ የሚለው ነገር ግን ሌላ ተልዕኮ ተሸክሞ የመጣው አስመሳዩ ሰላይ ጄምስ ብሩስ ከጎንደር ወደ አገሩ ስኮትላንድ(እንግሊዝ) ሲመለስ ይዟቸው የሄደው መጽሀፈ ሄኖክ፣ መጽሀፈ ፊሊፖስ እና ሌሎችም በርካታ የብራና ጽሑፎችን በግዥም ሆነ በስጦታ እንዲሰባሰቡ ብሎም ለብሔራዊ ቤተመጻሕፍት ወመዘክር ድጋፍ ማድረጉ ለእውቀት ማጎልመሻ ዘመቻው ብቻም ሳይሆን የማንነት ማንቂያ ደወል መሆናቸው ፈፅሞ አያጠራጥርም፡፡ ማስተዋል የአዋቂዎች ልጓም ናት ይባላልና ሥጋዊም ሆነ መንፈሳዊ ጥበብ የሚገለፀው መጻሕፍትን በመመርመር መሆኑን ለትውልዱ መልዕክት አዘል ነው፡፡ ታሪክ ደግሞ በአንድ ዘመን የተከናወነውን መስካሪ እንደመሆኑ መጠን አድራጎቱ በፅሑፍ ካልተቀመጠ በስተቀር ትውልዱ ተገንዝቦታል ለማለት አያስደፍርም፡፡ ሆኖም ታሪኩ በመነገሩ ብቻ ለሁሉም በአግባቡ ተላልፏል ሊባል የማይቻል ስለሆነ በራስ ተነሳሽነትና ጥረት ዕውቀት ማትረፍ የታሪክ ግንዛቤን ያጎለብታል፡፡
እንግዲህ ቅርሶቻችንን በተለይም ላለፉት ሰባት መቶ አምሳ ዓመት ፀንቶ የተላለፈው የላሊበላን ብርቅዩ የአለት ፍልፍል ቤተመቅደስ በዘላቂነት ለመታደግ ሁሉም ርብርብ ማድረጉ የዜግነት ግዴታን መወጣት ሲሆን በተለይም መንግስት ከታሪክ ተወቃሽነቱ ሊያመልጥ አይችልም፡፡ ላሊበላ ዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት መዝግብ ካሰፈረው በኋላ እስካሁን ድረስ ያደረገው ነገር ቢኖር በላዩ ላይ ከብረት ዳስ ከፀሐይ ሀሩርና ከቁርና ዝናብ እንዲያስጥል መታሰቡ ቅር ባያሰኝም አሁን ባለው ሁኔታ የበለጠ የቅርሱን መሰነጣጠቅ ሳያባብሰው አልቀረም፡፡ ምናልባትም ከመሬት ተለዋዋጭ ተያያዥ ባህሪያት ድንገት ብረቱ የመውደቅ ወይም ማዝመም አደጋ ቢያመጣ ቅርሶቹ በቀላሉ ሊናጉ ስለሚችሉ የከፋ የዘላለም ቁጭት ብቻ ይሆናል ትርፉ ፡፡ ከወዲሁ ትኩረት! ትኩረት! ትኩረት! አሁንም ትኩረት ያሻል፡፡ የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በጥር 2004 ዓ.ም ባወጣው የቱሪዝም ሥነ ምግባር መመሪያ አስፈላጊነት የሚከተለው ሀሳብ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ “ ቱሪዝም የሀገሪቱን ታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ሀብቶች በመጠቀም የሚንቀሳቀስ ክፍለ-ኢኮኖሚ እንደመሆኑ በሀብቶቹ አጠቃቀምና በአካባቢ ጥበቃ አንጻር ሀላፊነትና ዘላቂነት ያለው ቱሪዝም ማስፋፋት አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት…” ይላል፡፡ መልካም የገና በዓል፡፡
ቸር ይግጠመን!!!

ተጨማሪ ያንብቡ:  ቴዎድሮስ - ፋሲካ ገ/ጻዲቅ ወ/ሰንበት
Share