በየቡና ቤቱ በስብሰባው ሁሉ፣
ውጤት ያለው ስራ ተግባር የምትሉ፤
የሰራ ነውና የሚያምረው ሲጠይቅ፣
የናንተን አካፍሉኝ ገድላችሁን ልወቅ።
አልተሰራም ሳይሆን ይህን ሰራሁ በሉ፣
ጎድሏል አትበሉኝ እናንት ያንን ሙሉ።
ለማጣጣል ብቻ ከሚሆን ስራችሁ፣
ይህን ሰራሁ በሉኝ እንድኮራባችሁ።
ትንሳኤ ከተሰኘ ግጥም ተቀንጭቦ የተወሰደ- 2001
አጋጣሚው አስገራሚ ነው ፡፡ይህችን ሀሳቤን ወደ ጽሁፍ ለመቀየር እያወጣሁ እያወረድሁ ወደ መረጃ ቋት ስዘልቅ ከዘጠኝ አመት በፊት የተጻፈ ግን ልክ አሁን ላለው የሀገራችን ሁኔታ የተጻፈ የሚመስል ዘለግ ያለ ግጥም አገኘሁ፡፡ እናም ለመንደርደሪያ ትሆነኝ ዘንድ ከመካከል ይህችን ወሰድሁ፡፡መስራት እንደ ማውራት ቢቀል፤ማድረግ ይደረግልን እንደ ማለት የሚቻል ቢሆን በሁሉም ዘርፍ ከዓለም ቀዳሚውን ሥፍራ እኛ በያዝን ነበር፡፡ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነው እንደሚሉት ማለት ነው፡፡
ቅዱስ መጽሀፍም “ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ይጭናሉ እነርሱ ግን በጣታቸው ስንኳ ሊነኩት አይወዱም ፣ለሰውም እንዲታዩ ሥራቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፣ስለዚህ አሸንክታባቸውን ያሰፋሉ ዘርፉን ያስረዝማሉ ያላል፡፡”( ማቲዎስ 23፣ 4-7)
ሀገራችን የት ጋር እንዳለች ወደየትስ ልትሄድ እንደምትችል ግራ በገባበትና ተስፋው በጨለመበት፤ መድረክ ያገኘ ሁሉ በመስቀለኛ መንገድ ላይ ነች በሚልበት ወቅት ላይ ነበርን ፡፡ በዚህ ወሳኝም ፈታኝም በሆነ ወቅት አይደለንም እኛ ወያኔዎቹ ራሳቸው ባልጠበቁት ሁኔታና ባላሰቡት መንገድ ፈጽሞ ሊያቆሙት በማይችል ሁኔታ ከወደ ኦሮምያ የነፈሰው የለውጥ አየር ወያኔዎችን ቢያስደነግጥና ቢያበረግግም ብዙውን ሰው አረጋግቶት በሰማውና በሚያየው ተደስቶ እንደቃላችሁ ይደረግልን በምንችለው ከጎናችሁ ነን ብሎ ተስፋ ሰንቆ ነገሮችን በአንክሮ እየተከታተለ ነው፡፡
በነፈሰው የለወጥ ነፋስ ነገሮች አንድ ርምጃ ወደ ፊት የተጓዙ ቢሆኑም በአንጸሩ ጥቂት የማይባሉ በተለይ ከሀገር ርቀው የሚገኙ ግን እዛው የትናንት ቦታቸው ላይ ቆመው የሚነገረውንም ሆነ የሚተገበረውን በቀናነት ማየት አልቻሉም፡፡ ሌላው ቢቀር ትንሽ ርምጃ ታግሶ መመልከት ተስኖአቸው ነፋሱ መንፈስ ከጀመረበት እለትና ሰአት አንስቶ የሚነገረውን ማጥላላት የሚሰራውን ማናናቅ ከዚህ አልፈውም ህዝባዊ ተቃውሞው ይቀጥል ጥሪ ሲያስተላልፉ እየሰማን እያነበብን ነው፡፡
አይደለም የቤተ መንግሥት ዙፋን የፓርቲ ወንበር የሙጢኝ በሚባልበትና፣ የያዘው እድሜ ልኩን ለመዝለቅ፣ የሚከጅለው አውርዶ ራሱን ለማስቀመጥ ከፉከራ እስከ ሴራ፤ ከአሉባልታ እስከ ጥሎ ማለፍ ጨዋታ ወዘተ ስናይ በኖርንበት ሀገር ሥልጣን ከህዝብና ከሀገር በላይ ሊሆን አይችልም ያሉ፣ ብለውም ኢትዮጵያን ማዳን የምንችለው አንተ እዛ እኔ እዚህ ሆነነን ብንሰራ ነው ተባብለው በፍቅር ተነጋግረው፣ በመግባባት ሥልጣን ተደላድለው በዚሁ ጥንካሬአቸውም ወያኔዎቹን አሸንፈው ባቡሩን በለውጥ ሀዲድ ላይ መሾፈር የቻሉ ሰዎችን ተግባር በቁም ነገር አለማየት ይህም ቢቀር በሚችሉት ሁሉ ለማደናቀፍ ታጥቆ መዝመት ምን ሊባል እንደሚችል ይቸግራል፡፡
አንገታቸውን ደፍተው የልባቸውን ውስጥ ለውስጥ ሰርተው ድንገት የተከሰቱት ወገኖች የደደቢት ወያኔዎች በመቃብራችን ላይ ካልሆነ በስተቀር አታስቡት ሲሉን የነበረውን በአደባባይ በወያኔዎቹ ፊት ያውም የግል ንብረታችን አድርገነዋል ብለው ርግጠኛ በነበሩበት መድረክ ሲነገር ሰምቶ ከተቸከለበት በስንዝር እንኳን ነቅነቅ ማለት አለመቻልና ባሉበት ቆሞ የተለመደ ውግዘትና ጩኸት ማሰማት በርግጥ የጤነኛ አእምሮ ውጤት ነው ብሎ ለመናገር ይቸግራል፡፡
በተለይ ደግሞ በዚሁ የለውጥ ጅማሮ ከአመታት የእስር ቆይታ በኋላ ለመፈታት የበቁት ወንድም እህቶቻችን የለውጡን ጅማሮ አድንቀው ለለተነገረው አክብሮታቸውን ሰጥተው ተስፋ ማሳደራቸውን እየተናገሩ ሳለ ከበረሀ ታግለው የመጡ ሳይሆን ከመሀል ከተማ ተቀላቅለው ከደደቢቶቹ በላይ የደደቢት አላማን አስፈጻሚ ሆነው የኖሩና አልምች ብሎአቸው ወደ ተቃውው ጎራ የመጡ፣ ለአመጣጣቸው ምንነትን እንዴትነት ትኩረት ሳይሰጥ፣ ሰማኒያቸውን መቅደዳቸውም ኒካቸውን ማፍረሳቸው ከቁብ ነገር ሳይገባ አቀባበል ተደርጎላቸው በተቃውሞው ሰፈር አለኛ እስከማለት የደረሱ ወገኖች የለውጡን ነፋስ ሲቃወሙ፣ የሚነገረውን ሲያበሻቅጡ፣ የሚሰራውን ሲያናንቁ ወዘተ መስማት በእርግጥ ያማል፡፡ እንደ አያያዛቸውማ አቅሙ የላቸውም እንጂ የለውጡን ነፋስ በደቂቃ ውስጥ ቢያቆሙት ምንኛ በተደሰቱ ነበር፡፡ እባብ የልቡን አይቶ እግር ነሳው ነው የሚባለው፡፡
የጦቢያው ጸጋዬ ገብረመድህን አርአያ ሐምሌ 1989 ዓም ባስነበበን ጽሁፉ እንዲህ ብሎ ነበር፡፡“በአሥራ ስድስተኛው ዘመን ጭንቅላት የሃያ አንድኛውን ክፍለ ዘመን መግቢያ ችግሮቻንን ለመፍታት የምንደፋደፍበት ሁኔታ አለ ለማለት እደፍራለሁ፡፡በዚህ የተነሳም ነው ከዘመናችን የሀሳብ ትግልና የሰከነ ውይይት ብሔራዊ ራዕይ ሊሰርጽ ያልቻለው፡፡በ16ኛው ክፍለ ዘመን ጭንቅላት ማሰብ በዚህ የተነሳ በዚህ ሀገር በራሳችንም በመነግሥታችንም መተማመን እንደጠፋ እንኖራለን፡፡የምናምንበትን ህሊናችንን የሚኮረኩር አንዳች ኃይል በማጣትም የመንፈስ ሽባነት ያደረብን ይመስላል፡፡”
አዎ! በዚህ ወቅት ምንም በጎ ነገር አልታይ ያላችሁ ወገኖች ዛሬን በትናንት መነጽር እያያችሁ ነውና ጊዜው ተለውጧል መነጽራችሁን ቀይሩ፡፡ ተቀዋሚ የለም ተፎካካሪ እንጂ እንመካከር ስትባሉ በመካከላችሁ ያለውን እንደ ራስ ዳሽን ተራራ የገዘፈ ጥላቻና እንደ ሊማሊሞ የተጠማዘዘ ልዩነት አቻችላችሁና አጥባችሁ አጀንዳ ቀርጻችሁ ለመነጋገር ዝግጁ ነን መድረኩ ይመቻችልን ከማለት ይልቅ ወሬ ሰልችቶናል እያሉ ማላዘን፣ በምርጫ ተወዳድረን ከተሸነፍን ሥልጣን እናስረክባለን ስትባሉ፤ ተገቢው ተግባር ነጻ የምርጫ ሜዳ ይመቻች ብሎ መጠየቅ የተጠየቀው እውን እንዲሆን ማገዝና ተወዳድሮ ለማሸነፍ መዘጋጀት ሆኖ ሳለ መሰረታዊ ለውጥ ነው የምንፈልገው ህዝባዊ አመጹ ይቀጥል ወዘተ እያሉ ከሺህ ኪሎሜትር ላይ ሆኖ ነጋሪት መጎሰም አይበጅም፡፡
ለመሆኑ ፍላጎታችሁ ምንድን ነው ? በዚህ መነሻነት ከታች የቀረቡ ጥያቄዎችን መመለስ እነዚህን ጉዮች እያስታወሱ ቢሆን ጥሩ ነው፡
1-ፖለቲከኞቻችን ሀያ ሰባት አመት ፓርቲ ይመሰርታሉ ህብረት፣ ቅንጅት፣ መድረክ ወዘተ ፈጠርን ሲሉ ብንሰማማ አንድም ጠንካራ የሚባል ቀርቶ ፓርቲ ሊሰኝ የሚበቃ ፓርቲም ህብረትም የለም፡፡ አለ የምትሉ ካላችሁ እገሌ በሉን፡፡
2-የፓርቲ ሥልጣን ቁም ነገር ሆኖ እየተቧደኑ ሲጣለዙ፤የቻለ ወንበሩን አስጠብቆ የእድሜ ልክ ሊቀመንበር ሲሆን፤ያልቻሉ እየተባረሩ ሌላ ፓርቲ እየመሰረቱ ብዙ ተባዙ የተባለውን ለፓርቲ ሲያውሉት ነው እስካሁንም የምናየው፡፡
3-ወያኔን በዘረኛነት እያወገዙ በዘር የተደራጁ እርስ በእርስም መስማማት ተስኖአቸው በአንድ ብሄር ስም እሰከ ሀያ የደረሱ ስመ ፓርቲዎችን እየሰማን ነው፡፡
4-ከወያኔ ጋር እርቅ፣ ምክክር ወዘተ የሚጠይቁት ፖለቲከኞቻችን እነርሱ ተቀዋሚ(ተፎካካሪ) በሚባለው በአንድ ጎራ የተሰለፉት እርስ በእርሳቸው መነጋገር ቀርቶ መከባበር የላቸውም፡፡ መተጋገዝ ቀርቶ አንዱ ለሌላኛው እንቅፋት ከመሆን አይታቀቡም፡፡
5-በጥቅሉ ወያኔ በህዝብ ሀይል ተገዶ ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ መስዋዕትነት ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር፣እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይጠብቅ እያለ በአደባባይ የሚናገር፤ የሆነው ሁሉ መሆን ያልነበረበት ነው ብሎ ይቅርታ የጠየቀ፣ ከእንግዲህ ለዴሞክራሲ ግንባታ አንድ ጥይት መጮህ የአንድ ሰው ህይወትም ማለፍ የለበትም ብሎ ተስፋ የፈነጠቀ ጠቅላይ ምኒስትር ሰጥቶናል፡፡ አብዛኛው ተቀዋሚ (ፖለቲከኛውም አክቲቪስቱም) ግን እዛው ትናንትና ከትናንት በስቲያ በቆመበት ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ፡… ጥያቄ…
አንድ ፣የምትመኙ የምትናገሩት አይሆንም እንጂ ቢሆን ብለን አስበን ህዝባዊ ማእበሉ ወያኔን ጠራርጎ ቢያስወግደው፤
ሁለት፣ ይህም አይሆንም እንጂ እንደው ቢሆን ዶ/ር አብይ ባህር ዳር ላይ በየሄድኩበት የምሰማው ችግር ሥልጣን ሳይሆን ሽሽት የሚያስመኝ ነው እንዳሉት ወያኔዎች መክረው ዘክረው ሀያ ሰባት አመት ይበጃል ባልነው መንገድ ሀገር መራን ህዝቡ ግን ሊቀበለን አልቻለም፣ በቃ ሥልጣኑ ያውላችሁ ቢሉ፣
ሶስት፤ የሽግግር መንግሥት የምትሉትን ጥያቄ ተቀብለናል በእኛ በኩል ዝግጁ ነን፤በእናንተ በኩል የሽግግሩ መንግስት በእነማን እንዴት ለምን ተግባር ለምን ያህል ግዜ? ወዘተ እንደሚቋቋም የመነሻ ሀሳብ በሰነድ አቅርቡልን ቢባል፤( ብዛታቸውና ልዩነታቸውን ያጤኗል)
አራት፣ ሁሉም ይቅርና ብሄራዊ እርቅ፣ ሀገራዊ መግባባት የውይይት መድረክ ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች ለአመታት ሲነሱ ቆይተዋል፡፡ በእኛ በኩል ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲ ሊያሸጋግር በሚችል በማናቸው ጉዳይ ከማናቸውም ወገን ጋር ለመነጋገር ዝግጁ ነን፡፡ ስለዚህ ለመድረኩ ውጤታማነት በሚበጅ መልኩ ተፎካካሪዎቸ የራሳችሁን ዝግጅት አድርጉና እንገናኝ፡፡ ከሀገር ውጪ ላሉትም ዋስትና እንሰጣለን ቢባል፡፡ ምን ሊሆን እንደሚችል ሀሳባችሁን፣ ከዚህ አለፍ ብሎ እቅድም ካላችሁ ግለጹልን፡፡
ገበያ ቢያመቻት እናቷን ሸጠቻት እንዲሉ አበው፣ የዘመኑ የመገናኛ ቴክኖሎጂ ተመቸን ብሎ ዝም ብሎ ውግዘት የተሰራን መናናቅ የተነገረን ማጥላላት የትም አያደርስም፡፡ ለነጭና ቀይ ሽብር መተላለቅ ያበቃን ይህን መሰሉ ነገር ነው፡፡ እየተስተዋለ ቢሆን መልካም ነው፡፡ እንዳገኙ መናገር እንደማይገባ ቅዱስ መጽኃፍም ያስተምራል፡፡
“ሳትመረምረው አትንቀፈው፣አስቀድመህ ነገሩን ጠይቀው፣ኋላ ትቆጣዋለህ፣ሳትሰማ አትመልስ፣በሰው ነገርም አትግባ፤ግዳጅህም ባልሆነ ነገር እልፍ እልፍ ብለህ አትናገር፤” መጽኃፈ ሲራክ Ú፣Ú፩ ከ፯-»