የመላውን አገር ሕዝብ የሚመለከቱ ጉዳዮች መወሰን ያለባቸው በራሱ በባለቤቱ በመላው ሕዝብ ነው። ዲሞክራሲ ባለበት አገር ሕዝብ የሚመራበት ሕገመንግሥት በሕዝብ ፈቃድ ይወሰናል። የመሬት ይዞታ፤ መሪ ሥር ዓተ-ትምህርት፣ ብሔራዊ ቋንቋ፣ የአገር አከላለል፣… ወዘተ በቀጥታ በሕዝብ ፍላጎት መወሰን ያለባቸው ዋናዋና የአገር ጉዳዮች ናቸው።
ይህ ጽሑፍ የወቅቱና ምን ጊዜም መነጋገሪያ የሆኑትን የአሰብ የባህር በር፣ ተጨማሪ ብሔራዊ የኢትዮጵያ ቋንቋንና የአዲስ አበባ ክፍለሀገርን አከላለል ይመለከታል።
የአሰብ በር የአገራችን ጉዳይ ነው፤ ይህ ብሔራዊ በራችን ነው፤ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ክልል እውን ዲሞክራሲያዊ ሆኖ ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው ሲያስተዳድሩ ለአገር ውስጥ ምርትና ለውጭ ንግድ መውጫ በር ያስፈልጋቸዋል። “ድንቢጥ ብታልም ጥሬዋን” እንደተባለው አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የወያኔ አመራር አሰብን አሳልፎ መስጠቱ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ያልቆመ መሆኑን የሚያረጋግጥ ሲሆን፣ የሥልጣን ሕልም የሚያልሙ ፖሊቲከኞችም ነገ የአገር ሥልጣን ላይ ቢወጡ የሕዝባቸውን ፍላጎት ለማሟላት ማጣፊያው ጠፍቶባቸው ሕዝቡ የባሰ ችግር ውስጥ እንዳይገባ በመገንዘብ ይህን ጉዳይ አጀንዳቸው አድርገው መሥራት ኢትዮጵያዊ ያደርጋቸዋል። ራስን ስለመቻል አስቀድሞ አለማስተዋል እንደ ኤርትራውያን የባሰውን መናጢ ሆኖ የኃያላንን መንግሥታት እጅ በማየት የአገርን መሠረታዊ ጥቅሞች አሳልፎ እስከ መስጠት ይዳርጋል። የኢትዮጵያ በሮች የነበሩት ጅቡቲና ዘይላ ታሪክ ሆነው ቀርተዋል፤ አገር በመለገስ መቀጠል አያዋጣንም፤ መተማም ሆነ አልፋሸጋ የጎንደር ብቻ እንዳልሆኑ ሁሉ የአሰብ ጉዳይም የዚህ ወይም የዚያ ክልል ጉዳይ ሳይሆን የክልሎች ሁሉ ጉዳይ ስለሆነ ይዋል ይደር እንጂ እንደእሳተገሞራ ታምቆ ቢቆይም ወደፊት መፈንዳቱ አይቀርም።
አሰብ ለኤርትራ የተሰጠው ሕዝቡ በነፃ ባልመረጠው ሕገወጥ መንግሥትና በሕገወጥ መንገድ ነው፤ የኤርትራ ጉዳይ በፌዴሬሽን ከመወሰኑ በፊት የተበበሩት መንግሥታት ኢትዮጵያ ታሪካዊው የባህር በር የሚያስፈልጋት መሆኑን አውቋል። እ ኤ አ በ1950 ዓም በተደረግ 316ኛው የተባበሩት መንግሥታት ጉባኤ በውሳኔ ቁጥር 390 ገና ኤርትራ በፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቀላቀል ውሳኔ ሲሰጥ የባህር በሯን በተመለከተ እንደሚከተለው አስቀምጧል፦
The rights and claims of Ethiopia based on geographical, historical, ethnic or economic reasons, including in particular Ethiopia’s legitimate need for adequate access to the sea
ከ1966 ዓም አብዮታዊ የመንግሥት ለውጥ በፊት አሰብ ከኤርትራ ተለይቶ እንደአንድ ጠቅላይ ግዛት ልዩ አስተዳደር ነበር። ከዚህ በተጨማሪ አንድ አገር የወንዝ ተፋሰስን በመለወጥ የጎረቤት አገር ሕዝብ ሕልውና እንዳይጎዳ በማለት የቪየናም ሆነ የሄልሰንኪ ኮንቨንሽንሽኖች ኢትዮጵያ በወንዞቿ የመጠቀም መብቷን የማይገቱ ቢሆንም አባይን ለማልት በምታደርገው ጥረት ላይ በየጊዜው ተጽዕኖ እንደተደረገባት ይታወቃል። በአንፃሩ የገዛ ባህር በሯን ተቀምታ በችግር ላይ እንድትወድቅ የሚያደርግ ምንም ሕግ የለም፤ የዓለም ኅብረተሰብ አመለካከትም አይደለም። ኤርትራም ሌላ የባህር በር ያላት ከመሆኑም በላይ አሰብን ልትጠቀምበት ስለማትችል ለእጅ አዙር ቅኝ ገዥዎች አሳልፋ መስጠቷም ተቀባይነት የሌለው ጉዳይ ስለሆነ ኢጋድም ይህን ጉዳይ እንደችግር አለማየቱ ይገርማል፤ ለነገሩ ባለቤት ካልጮኸ ጎረቤት አይደርስም ይባላል። የክልሉ አካል በሆነው በር ዝንታለም የኖረው የአፋር ሕዝብ መብት ተረግጦና ያለፍላጎቱ እንደፍልስጥ ኤም አገር እንደሌለው ተቆጥሮ በኤርትራና በኢትዮጵያ ለሁለት ተከፋፍሎ ጥንታዊ ማንነቱን እንዲያጣ ተደርጓል። አንድ የኢጣሊያ የንግድ ድርጅት አሰብ ላይ መሬት መግዛቱን ሰበብ በማድረግ ቀጥሎ ኢጣልያ ባንዲራዋን እንዳውለበለች ሁሉ ትግራይን ነፃ ለመውጣት በሚንቀሳቀስ ድርጅት ትግርኛ ተናጋሪ ወገን ሥራ ፍለጋ ሄዶ በእንግድነት የኖረበትን መሬት ለትግራይ በማካለል በሌላ በኩል በራሱ ምድር ላይ የነበረውን አፋር ከፋፍሎ የሁለት አገር አናሳ ማድረግ ፍትሐዊ አይደለም። ለውጭ ጠላቶች የእግር እሳት ሆኖ ዳርድንበሯን በመጠበቅ ኢትዮጵያን ካቆዩት ወገኖቻችን መካከል የአፋር ሕዝብ ይገኝበታል። የስለሆነም በአሰብ ወደኤርትራ መካለል ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በሕዝበ-ውሳኔ የፈቀዱት ስላይደለ አያቶቻችን ደማቸውንና አጥንታቸውን ከስክሰው ያቆዩት ታሪካዊ የባህር በራችን ስለሆነ ለአገራችን ሊመለስ ይገባል።
ሁለተኛ ኦሮሞ ተጨማሪ ብሔራዊ የኢትዮጵያ ቋንቋ እንዲሆን የሚደረግ ጥረት አለ። ለዚህ ድጋፍ በመኖሩ አንፃር ተቃውሞም ሊኖር እንደሚችል ማወቅ የሕዝብን ፍላጎት ማክበር ነው። የኦሮሞ ቋንቋ ከሌሎች ማህበረሰቦች ጋር ሲታይ ቁጥሩ ከፍ ያለ ይሁን እንጂ የአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ መግባቢያ ቋንቋ አይደለም። አንድ ቋንቋም ባሔራዊ ሆኖ እንዲያገለግል መንግሥት በቀጥታ የሚወስን ቢሆን የሕዝብን ፍላጎትና ሥልጣን መጋፋት ነው የሚሆነው። በመሠረቱ ጉዳዩ ከ80 ያላነሰ ቋንቋ የሚናገሩ ማህበረሰቦችን ሁሉ ይመለከታል። ስለሆነም ይህ መታየት ያለበት በአገር ደረጃ ነው ማለት ነው። ስለቋንቋና ብሔራዊ መብት ሲነሣ አማርኛ ተናጋረውና ኦሮምኛ ተናጋሪው ብቻ ናቸው የአደባባይ መነጋገሪያ የሚሆኑት፤ ይህም ማለት ሌሎች ማህበረሰቦች መኖራቸውና ፍላጎታቸው ሁሉ እንዳልነበረ የሚታይ ያስመስላል። ስሙን ለ”አፍሪቃ” ሰጥቷል የሚባለው ከክርስቶስ ልደት በፊት በቀይ ባህር አካባቢ የሠለጠነና መርከቦችን በመሥራት በአካባቢው መንግሥታት የንግድ ግንኙነት ታዋቂ የነበረው የአፋር ሕዝብ፣ እንዲሁም ዳሞት፤ ዛጉዌ፣ ሐዲያ፣ ከፋ፣ ሲዳማ፣ ወላይታ፣ … ወዘተ ግዙፍ ታሪክ ካላቸው ማህበረሰቦች መካከል ጥቂቶቹ ሲሆኑ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ክስተቶች በአስከተሏቸው ፍልሰቶች እንዲሁም በጋብቻና በሌሎች ማህበራዊ ትሥሥሮች ወይም ማኅበራዊ መስተጋብሮች ዝግመታዊ ለውጦች ኢትዮጵያውያንን አሁን ባሉበት ደረጃ እንዲገኙ አድርጓቸዋል። ሁሉም ወግ፣ ባህልና ከነዚህ ጋር የሚሄዱ እሴቶችና ጥቅሞቻቸው እንዲከበርላቸው መፈለጋቸው የማያጠያይቅ ሲሆን እንዲህ ያለ ለውጥ እነሱንም ይመለከታል። ማህበረሰቦቹ እያንዳንዳቸው የየራሳቸው ቋንቋ ቢያድግላቸው ወይም መግባቢያ ቢሆንላቸው አይፈልጉም ማለት አይደለም፤ ሆኖም መክረው፣ ዘክረው በሕዝበ-ውሳኔ የፈጸሙት ነገር ቢያንስ ሕጋዊ ነው። ነገር ግን ይህን ሕጋዊነት ባለመከተል የሚፈጸም ውሳኔ የማያባራ ንትርክና ውዝግብ በማስከተል አንድነታችንን የሚጎዳ ቀዳዳ ሊከፍት ይችላል።
አንድ ተጨማሪ ቋንቋ ብሔራዊ ሲሆን በሥር ዓተ-ትምህርት ላይ፣ በመንግሥት ሥራዎች ላይና በመንግሥት ይፋዊ ሥራ (official business) ላይ እንዲሁም ከዚህ ጋር በተያያዙ የምጣኔ ሀብት ላይ ጫናዎች በማስከተል የአገሪቱን አቅም የባሰ ሊያዳክም ይችላል፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚመጣን ዕዳ ከፋዩ ሕዝብ ሁሉ ውሳኔው ስለሚመለከተው የሚያስከትለውን ሁሉ በወቅቱ አውቆ ሲወስን ዕዳውን ለመክፈል ፈቃደኛነቱን በሕጋዊ መንገድ ስለሚያረጋግጥ የመንግሥት ባለሥልጣናት ምክርቤቱን ጨምሮ የሚያስከትልባቸው ተጠያቂነት ይቃለልላቸዋል ማለት ነው።
እንዲህ ያለ ለውጥ ከመደረጉ በፊት የኅብረተሰቡ አመለካከት ከፖሊቲካዊ አንፃር ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ፈርጆች በነፃ በታመነበትና ማኅበራዊ መግባባትን የተከተለ መሆን ይኖርበታል። እዚህ ላይ መጥቀስ የሚያስፈልግ ነገር አለ፤ ይኸውም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ አማርኛን ተጠቅመው ጉዳያቸውን መግለጽ የሚችሉ ዜጎች (አማሮች፣ ጉራጌዎች፣ ሐዲያዎች፣ ወላይታዎች… ወዘተ) አማርኛ የፌዴራል ቋንቋ መሆኑ እየታወቀ ጉዳያችሁን በኦሮምኛ (በቁቤ አጽፋችሁ) ካላቀረባችሁ አንቀበልም በማለት ብዙ ዜጎች ተጉላልተዋል፤ የገንዝብ ኪሣራም ደርሶባቸዋል፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ የኦሮሚያ ክልል አገራቸው እንዳልሆነ ተቆጥሮ በደረሰባቸው ተጽዕኖ የተነሣ ቤት ንብረታቸውን ያጡና የተፈናቀሉም እንዳሉ የአደባባይ ምሥጢር ነው። እንዲህ ያለ ተጽዕኖ የሚወገደው በአንድ አቅጣጫ ብቻ አጥብቦ በማየትና የተለያዩ ማህበረሰቦች መብት ባለመጠበቁ ስለሆነ በደፈናው ሕግ ሆኖ የሚወጣ ነገር ሁሉንም ነገሮች አይቶና እንዲህ ያሉ ቀዳዳዎችንም ደፍኖ ለመውጣት የሚችለው ተጠቃሚው ሕዝብ ሁሉ አስተያየቱን ሰጥቶ፣ ዳብሮና በሁለንተናዊ መልኩ በሕዝብ የታቀፈ ሲሆን ብቻ ነው።
ከፖሊቲካ አመለካከት ተነሥተው አማርኛንስ ማን መረጠው ብለው የሚከራከሩ ሊኖሩ ይችላሉ። ለዚህ መልሱ በጣም አጭር ነው። አማርኛን የትኛውም መንግሥት አልመረጠውም፤ አማሮችም አልመረጡትም፤ እነሱ ራሳቸው የተፈጠሩት በአማርኛ ነውና። አማርኛ ቋንቋ የተናገረው ኢትዮጵያዊ አማራ ተባለ እንጂ አማራ የሚባል ነገድ አልነበረም፤ ቋንቋውን በመናገራቸው አማራ የሚባሉ ኢትዮጵያዊ ማህበረስቦች ጎንደሬ፣ መንዜ፣ ቡልጌ፣ ወሎየ፣ ጎጃሜ… ወዘተ ተብለው ይታወቃሉ እንጂ በአንድ ላይ ተጠቃልለው በብሔር-ብሔረሰብነት አይታወቁም ነበር፤ ይህ መለያ እየተቀረጸ የወጣው ከኢሐዴግ አመራር ወዲህ ነው። ለምሳሌ የዘመኑ ፖሊቲካ ከመከሰቱ በፊት በህትመት ሥራቸው የሚታወቁት ተስፋ ገብረሥላሴ ዘብሔረ-ቡልጋ እንጂ ዘብሔረ አማራ ብለው አያውቁም፤ ብሔረ-ዘጌ፣ ብሔረ-አገው የሚባሉም ታይተዋል። ኢሕአዴግ ካመጣው መለያ በፊት አማራ ከክርስትና ሃይማኖትና ከኢትዮጵይዊነት ጋር ራሱን አጣምሮ የሚያይ ሕዝብ እንደሆነ እንጂ እራሱን በብሔረሰብነት ለይቶ አያውቅም፤ እስከቅርብ ጊዜ ድረስም አማራን ከክርስትናና ከኢትዮጵያዊነት ጋር አጣምረው የሚያዩ ብዙ ማህበረሰቦች አሉ። በነበረው የድሮ ቋንቋ ለመግለጽ እንጂ ዛሬማ አማርኛ ተናጋሪው ሁሉንም ሃይማኖት ተላብሷል፤ ሁሉንም ሆኗል፤ አማራ የብዙ ኢትዮጵያውያን ደም ያለበት ኅብረተሰብ ስለሆነ ከምንም በላይ ኢትዮጵያዊ መለያውነቱ ይበልጥ እየተጠናከረ የመጣ ሕዝብ ነው። ከፊሉ አፍሪቃ ኢትዮጵያ ተብሎ በሚታወቅበት የዓለም ክፍል እስከሜሶፖታሚያ ድረስ መግባቢያ የነበረው ግዕዝ ተፈጥሯዊ በሆኑ ማህበራዊ ክስተቶች የተነሣ በዝግምታ ለውጥ ብሔራዊነቱ ሳስቶ በቤተክርስትያንና የቆዩ ሥነጽሑፎች መዘክር ውስጥ ተወስኗል። ሆኖም አማርኛ ከግዕዝ ተወለደ ሊባልም አይቻልም፤ አማርኛን በአማራነት የሚታወቁ ማህበረሰቦች እንዳልመረጡት ሁሉ በመንግሥት ውሳኔም ሳይሆን በተፈጥሮ እድገት ብሔራዊ የሆነ ቋንቋ ነው። በዝግመታዊ ለውጥ የዛሬዩቱ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ይዘት እየተቀረጸ ሲመጣ አማርኛንም ከብዙ ማህበረሰቦች አውጣጥታ አገራችን ኢትዮጵያ በብሔራዊነት የወለደችው ቋንቋ ነው። ከ500 ዓመታት ወዲህ አሜሪካንስ የተባሉት ሕዝቦች ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች በየጊዜው እየፈለሱ የመጡበትን ትተውና የእንግሊዘኛ ቋንቋን ቋንቋቸው አድርገው አሜሪካውያን ነን ሲሉ፣ ቢያንስ ከ1000 ዓመታት በፊት ጀምሮ ከየራሳቸው አውጣጥተው አማርኛን በመፍጠር ኢትዮጵያዊ የሆኑ ማህበረሰቦች አማራ መባል ተፈጥሯዊ የኅብረተሰብ እድገት ነው። በመሆኑም የዓለምን ታሪክ አካሄድ በመረዳት ይልቁንስ ወደፊት በጋራ የሚጠብቁንን ችግሮች በማስተዋል የጋራ ራዕይ ማየት ይገባል።
ሦስተኛውና ሌላው መታየት ያለበት የወቅቱ ጉዳይ የአዲስ አበባ ክልላዊ መንግሥት መብት ነው። አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ርዕሰ ከተማ ነው፤ በርዕሰ ከተማነቱ ደግሞ ከዳር እስከዳር ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ አዲስ አበባን የረገጠ ሠራተኛ ወይም ነጋዴ ሁሉ የተለያዩ ግብሮችን በመክፈልና ልማቱን በማሳደግ ከዳር እስከዳር ለብዙ ዘመናት ሀብቱን ያፈሰሰበት ከመሆኑም በላይ በመንግሥትም ሆነ በግል ሥራ ወይንም በንግድ የኖረበትና የሚኖርበት፣ ሌላውም ተወልዶ የኖረበት፣ ወልዶ ያሳደገበት አገሩ ስለሆነ የዚህ ወይም የዚያ ብሔረሰብ ንብረት ወይም እርስት አይደለም፤ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ክፍለሀገር እንደመሆኑ መጠን በአዲስ አበባ ላይ ውሳኔ መስጠት የሚችለው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ መንግሥትም ሆነ የመንግሥት ምክርቤት ሥልጣን ሊኖረው አይችልም።
Encyclopedia Britanica እንደ አዲአ አበባ ያለውን ክልላዊ መንግሥት ሲገልጽ፣ “City-state, a political system consisting of an independent city having sovereignty over contiguous territory and serving as a centre and leader of political, economic, and cultural life.” ይለዋል። ርዕሰ ከተማ የሁሉም ክፍለሀገሮች ማዕከል ነው። ርዕሰ ከተማ የሁሉም ክልሎች ተወካዮች ተሰብሰበው ውሳኔ የሚሰጡበት መቀመጫ ስለሆነ ሁሉም ወገኖች ባለቤት የሆኑበት ራሱን የቻለ ክልል ነው እንጂ አንዱ ወገን ለብቻው ባለቤት ሊባልበት አይችልም።
“Finance and Governance of Capital Cities in Federal Systems ” በሚል ኢትዮጵያም ያለችበት የከተሞችን ፋይናንሽያል አወቃቀር ዓለም-አቀፍ ጥናት ተከታታይ ጥናቶች አድርጎ አቡጃን፣ አዲስ አበባን፣ ካንቤራን፣ ዴልሂን፣ ሜክሲኮንና ዋሽንግተን ዲሲን በተመሣሣይነት ፌዴራል ዲስትሪክት ብሎ በመለየት ሚናቸውም እንደሚከተለው ተጠቅሷል፦
– National seat of government not under jurisdiction of any one state/province
– Extent of federal control ranges from Abuja (tightly controlled by federal government) to Canberra (largely an autonomous city-state)
– Issues of local democratic and accountability deficit
– Limited fiscal autonomy
– Direct access to federal funds
በበለፀጉ አገሮች ሕግ ሲወጣ የተለያዩ ሕዝቦች ፍላጎቶችንና ጥቅሞችን ለማካተት በአገር ላይ ያሉ የሕዝብ ክፍሎችን ሁሉ ከማዘሉም በላይ የሚያስከተለውን ማህበራዊ፤ ፖሊቲካዊና የምጣኔ ሀብት መዘዞች ሁሉ በርቀት እና በዝርዝር ታይቶ ሊያስከትሉ የሚችሉ ችግሮችን መፍትሔ በመስጠትና ሊነሱ የሚችሉ የመብት ጥያቄዎችን መፍትሔ ሰጥቶ ሊደነገግ ስለሚችል ሕዝብ ተቀብሎት በቀጣይነት ዳብሮ ያለማቋረጥ ያገለግላል። የሕዝብ ምክርቤቶችም የዚያን የሕዝብ ፍላጎት የሚያንፀባርቁ አካሎች ናቸው እንጂ በሕዝብ ተመርጠናል ብለው ሌሎች በጥቃቅን ጉዳዮች ላይ እንኳ ሕዝብን ሳያስመክሩ ሕግ አያወጡም።
እንዲህ ያሉት ውሳኔዎች በዲሞክራሲያዊ ሁኔታ ወይም በውሳኔ-ሕዝብ እንኳ ተወስነው ፍጹም ሊሆኑ አይችሉም፤ ቢያንስ ውሳኔው ዲሞክራሲያዊ ነው እንኳ ማለት አይቻልም። ዲሞክራሲያዊ አሠራር (1) የሕዝብ ውክልናን (representation) እና (2) የብዙሐን ድምፅን (majority) አሠራሮች ይመለከታል:: ለምሳሌ በአሜሪካ በተደረገው የፕሬዘደንት ምርጫ በብዙሐን ድምፅ ያሸነፉት ወይዘሮ ሔላሪ ክሊንተን ሲሆኑ ዶናልድ ጆ ትራምፕ የተመረጡት በውክልናው ዓይነት የምርጫ ክፍለሀገሮች ተቆጥረው ብልጫ ስላገኙ ነው። በመጀመሪያው ዓይነት ሲታይ የትኛውም ማህበረሰብ ከየትኛውም መኅበረሰብ አያንስም፣ አይበልጥም፤ ስለሆነም የሕዝብ ቁጥሩ ግምት ትልቅ ዋጋ ሳይሰጠው በክልልነቱ ከሌሎች ክልሎች ጋር እኩል ድምፅ ኖሮት አንድን ክልል በሚመለከት ውሳኔ ላይ ተሳታፊ ካልሆነና ሌላ መንግሥታዊ አካል የሜወስን ቢሆን ተጽዕኖ ተደረገበት ማለት ነው፤ ይህም ፀሪ-ዲሞክራሲያዊ ነው። በተለይም እንደኛ ባሉ በጠመንጃ አፈሙዝ ውሳኔን በሕዝብ ስም የመፈጸም ልምድ ባለበት አገር በፖሊቲከኞች ወይም የመንግሥት ሥልጣን ላይ ባሉ ሰዎች የሚወጡ ሕጎች በአንድ አቅጣጫ በሚተላለፍ የብዙሐን መገናኛ መግለጫዎች ሞገድ የግድ ለማሳመን ከሚደረግ ዘመቻ በስተቀር በሰከነ መልክ ሕዝብ እንዲመክርበት ስለማይደረግ በፖሊቲካ ጫና በሚደረግ ግርግር በግብታዊ መልክ እኛ ለሕዝቡ እናውቅለታለን በሚሉና በሥልጣን ላይ ባሉ ፖሊቲከኞች ውርጅብኝ ስለሚወሰኑ ሕጉም ዘርፈ-ብዙ ሆኖና በስሎ ስለማይወጣ ዝርዝር የሕዝብ ጉዳዮችንና ፈቃዳቸውን ካለማካተቱም በላይ አሠራሩም ሕዝባዊ ወይም ዲሞክራሲያዊ ስለማይሆን ማህበረሰቦችን የማያበራ ግጭት ውስጥ ሊጥል ይችላል። በአገር ደረጃ የሚወሰኑ ነገሮች ሁሉ በአገር ላይ ያሉ ብዙሐን ማህበረሰቦችን ሁሉ ይመለከታል፤ ስለሆነም ጉዳዩ ሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለሚመለከት መንግሥት ለሕዝብ ፍላጎቶች ተገዥ በመሆን ሕዝብን ያገለግላል እንጂ በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ወስኖ በአዋጅ ሕዝብ ላይ ጫና የማድረግ ሥልጣን ስለሌለው እንዲህ ያለው ጉዳይ የሚፈታው በውሳኔ-ሕዝብ ብቻ መሆኑ መታወቅ አለበት። “አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” እንደሚባለው የሕዝብን አንገብጋቢ ጉዳዮች በችልተኝነት እንደረመጥ አዳፍኖ ማቆየት ወይም ለጎታች የአገር ችግሮች እርሾ ማቆየት ስለሚሆን ወደፊት በእድገት ፋንታ ሌላ አዘቅት ውስጥ እንዳንገባ በወቅቱ ሊታሰብበት ይገባል። በቅድሚያ ያልተመከረበት ነገር የሚያስከትለው መዘዝ ብዙ ነውና። ስለዚህ ስለወደፊቷ ኢትዮጵያ ራዕይ አለን የሚሉ ሁሉ እነዚህን ጉዳዮች ዋና አጀንዳዎች ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ተፈራ ድንበሩ