ምነው -ፕ/ር ጌታቸው በዚህ ሰዐት- ወደ ጎሰኝነት – ይገረም አለሙ

 

የአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው ክፍል ጋዜጠኛ አዲሱ አበበ አዲስ ተመሰረተ የተባለውን አንድ አማራ ድርጅት አስመልክቶ ከአራት ሰዎች ጋር ያደረገውን ውይይት የመጀመሪያ ክፍል አዳመጥኩት፡፡ ይሄ በአማራ ስም ድርጅት መሰረትን የሚል ነገር መች እንደሚያበቃ ከፈጣሪ በስተቀር የሚያውቅ የሚኖር አይመስለኝም፡፡ ምን አልባት የድርጅት መሪ መባል የሚፈልጉት “አማሮች” በሙሉ ሲዳረሳቸው ያቆም ይሆናል፡፡

ተደራጀን ብለው የውኃ ሽታ የሆኑትም ሆኑ ከማህበራዊ መገናኛ ባልዘለለ ሁኔታ አለን የሚሉት፤ ምን አልባት ነገ ከነገ ወዲያም ተደራጀን ሊሉን የሚችሉትም የሚያነሱት ሁለት ነገር ነው፡፡ አንድ አማራው በአማራነቱ ብቻ እየተጠቃ ስለሆነ፣ የሚልና የፕ/ር አሥራትን ስም፡፡ ለመደራጀት የመከጀላቸው መሰረታዊ ምክንያት ይህ የሚሉት ቢሆን ኖሮ ለቁጥር የሚያታክት ድርጅት መመስረት ያስፈልግ ነበርን?  ከቀደመው ትምህርትም ሆነ ተሞክሮ ሳይወሰድ ተደራጀን ማለት ብቻ እስከ ዛሬ መቀጠል ነበረበት ?ወዘተ ብሎ መጠየቅ ዋናው ዓላማ ከሚነገረው ጀርባ ነው ብሎ ለመጠርጠር ያበቃል፡፡

በዚህ ላይ ያለኝን ሀሳብ  ከሁለት አመት በፊት “በአማራነት መደራጀት ሌላው ኢትዮጵያዊነትን የማጥፋት ስልት” በሚልና “የጭቆናው ምክንያት አንባገነናዊ ሥርዓት ወይንስ የብሄር ማንነት” በሚሉ ሁለት ጽሁፎቼ በዋናነት  እንዲሁም በሌሎች ጽሁፎቼ በየጣልቃው  የገለጽኩና የዚህ ጽሁፍ አብይ ጉዳይም ባለመሆኑ አልሄድበትም፡፡ ግን ትንሽ ልበል፡፡

እኔ በወያኔ አገዛዝ ከአንድም ሶስቴ ታስሬአለሁ፤የመታሰሬ ምክንያት መታወቂያየ ላይ የሰፈረው የማላምንበት አማራነት አይደለም፡፡እንደውም የፖለቲካ አመለካከት ልዩነትም አይደለም፡፡በአባልነት የነበርኩበትን ፓርቲ ወያኔ ለወንበሩ የሚያሰጋው አድርጎ በማየቱ እንጂ፡፡ ከወያኔ ጋርየፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ያላቸው ግን የሚመሩት ፓርቲም ሆነ ግለሰቦቹ በግል ለወያኔ ወንበር አስጊ ሆነው ያልታዩ ሀያ ሰባት አመት ሙሉ አንድም ግዜ እስራት አይደለም ግልምጫ ሳያጋጥማቸው በፖለቲካው መድረክ ላይ አሉ ፡፡ አማራ መሆን ብቻም ለእስር እንግልት ካበቃ አማራ የተባለ ሁሉ እየታደነ መታሰር ነበረበት፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በኢትዮጵያ "ኢህአዴግ አስካለ " የመከራ ቀንበር ይኖራል !

ፕ/ር አሥራትንም ብዙዎቹ ዛሬ በስማቸው መነገድ የሚከጅላቸው አይደለም ትግላቸውን ሞታቸውን እንኳን ብቅጡ አያውቁም፡፡ እኔ የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት አባል ነበርኩ፡፡ አባል የሆንኩት አማራ ነኝ ብየ ሳይሆን የወያኔን እኩይ ተግባር ከዳር ሆኖ መመልከት ህሊናየ ባለመቀበሉና በወቅቱ የተሻለ እንቅስቃሴ የነበረው ሀገራዊ ድርጅት ባለመኖሩ ከበጣም መጥፎ መጥፎን መምረጥ እንደሚባለው ሆኖ ነው፣፡ እንዲሁም የድርጅቱ መሪዎች ደጋግመው እኛ በአማራነት ስም የተደራጀነው ፈልገነው ሳይሆን የእሳት አደጋ ስራ ለመስራት ነው ያ ሲያበቃ ወደ ሀገራዊ ድርጅትነት እንለወጣልን ይሉ ስለነበረና ፕሮግራማቸውም ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሀገራዊነትን የሚያንጸባርቅ ስለነበረ ነው፡፡እናም ማቆሚያ የሌለው ለሚመስለው በአማራነት “መደራጀት ” የፕ/ር ዓሥራትን ስም እዛም እዚህም መጠቀም እኛም እንደ ወያኔ ነውር የሚባለውን ነገር አናውቅ ካልሆነ ነው እንጂ ነውር ነው፡፤

ኢትዮጵያዊ አጀንዳ በማራመድ ብቻ ሳይሆን በጎሳ መደራጀትን አጥብቀው በመቃወም ይታወቁ የነበሩት ፕ/ር ጌታቸው በጋሻው ዛሬ ያውም በዚህ ወቅት የእንቧይ ካብ የሆነውን በአማራነት መደራጀት ደግፈው ብቅ ማለታቸው ጋዜጠኛውንም ሳያስገርመው አልቀረምና በፖለቲካ እድሜዎን ያሳለፉ በጎሳ መደራጀትን ሲቃወሙ የኖሩ ይሄ ስህተት ነው ብለው አሁን በዘር መደራጀትን ሲደግፉ ስህተትን በስህተት ማረም አይሆንብዎትም ወይ በማለት ጠየቃቸው፡፡(ቃል በቃል አልጠቀስኩ ይሆናል)፡፡

የርሳቸው ምላሽ ሲቃወሙት የነበረውን በዘር መደራጀት ዛሬ ያውም በዚህ ወቅት ደጋፊ ሆነው ለመቅረብ የሚያበቃ በቂ ምክንያት ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ በየግዜው የማራ ድርጅት መሰረትን እያሉ ብቅ የሚሉት ወያኔን ዘረኛ እያላችሁ እንዴት ራሳችሁ በዘር ትደራጃላችሁ ተብለው ሲጠየቁ ሲሰጡት ከነበረውና አሁንም ከሚሰጡት ምላሽ ብዙም የተለየ አይደለም፡፡የተለየ ነገር ቢኖር እኔ ደገፍኩትም አልደገፍኩት የሚለው ነው፡፡

የፕ/ር ጌታቸው በጋሻውን የአቋም እንበለው የእምነት ለውጥ ቢያንስ ለእኔ እንቆቅልሽ ያደረገብኝ ኢትዮጵያዊነት ኮስሶ ጎሰኝነት በመድረኩ ነግሶ በነበረባቸው አመታት ሲቃወሙ የነበሩትን ጎሰኝነት፤በዘር መደራጀት  ዛሬ ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ትኖራለች፣ እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይጠብቅ፣ ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው፣ አድዋ የዘመትነው ቅጥረኛ ሆነን አይደለም፣ ወዘተ የሚሉ ለሀያ ሰባት አመታት ሰምተናቸው የማናውቃቸው ቃላቶች ከዛው ከወያኔ  ጉያ በወጡ ሰዎች ሲነገር በምንሰማበትና ኢትዮጵያዊነት ገዝፎ  አይንበርከኬነቱን በተግባር እያሳየ ባለበት ወቅት መሆኑ ነው፡፡ዘረኛ የተባለው ወደ ሀገራዊነት ሀገራዊ የነበረው ወደ ዘረኝነት እንቆቅልሽ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሁለት ፈረሶች ጥያቄ (ዳንኤል ክብረት)

ብዙ ተባዙ የተባለው ለአማራ ፖለቲከኞች የሆነ ይመስል የአንዱ ተመሰረትኩ ዜና ከአየር ሳይወርድ ሌላው ተመሰረትኩ የማለቱ ነገር ፍች ያጣ እንቆቅልሽ በመሆኑ ጋዜጠኛው በቅርቡ 18 ድርጅቶች አንድ አማራ መሰረትን ብለው እኛም ዘግበን ነበር አሁን እናንተ ጋር ከእነዚህ ምን ያህሉ አሉ ሲል ጠየቀ፡፡ ፕ/ር በጋሻው ለዚህ የሰጡት ምላሽ “ 18 ድርጅቶች የሚባለው እንደው ቁጥሩን ብዙ ያስመስለዋል እንጂ መታየት ያለበት ነገር ምንድን ነው ሪሊ ያን ያህል አይደሉም፡፡ አሁን አቶ ተክሌን ብትወስዳቸው ( አንደኛው ተወያይ ናቸው) ከእርሳቸው ጋረ የተያያዘ አራት ግሩፕ ነው” በማለት በስም ከዘረዘሩ በኋላ ሲቀጥሉ “ አትላንታም ተብሎ ሁለት ሶስት ሰዎች ናቸው፤ቁጥር ለማብዛት የተደረገ እንጂ በተግባር ጥቂቶች ናቸው ” የሚል ነበር፡፡ ታዲያ በአማራነት መደራጀት እንዲህ የቁጥር ጨዋታ መሆን ደረጃ ከደረሰ ምን አይተው ምንስ ተስፋ ሰንቀው ነው ዘመናት አቋማቸውን ቀይረው የዛሬውን ወር ተረኛ የአማራ ድርጅ መደገፋቸው ?

በጎሳ መደራጀቱ በተለይ ዛሬ አላስፈላጊ ጉዳይ ሆኖ፣ በአንድ ሰው አራት አምስት ድርጅት መመስረቱ፣ ድርጅት መሰረትን ማለቱ መነሻ ዓላማም መድረሻ ግብም የሆነ ይመስል በየግዜው ድርጅት መሰረትን የሚሉ መሰማታቸው፣ እነዚህም በመካከላቸው መተባበሩ ቢቀር መከባበሩ ጠፍቶ ብቸኛው የአማራ ተወካይ አኔ ነኝ በሚል የጠመንጃውን ባይችሉም በቃላት የሚታኮሱ የመሆናቸው ነገር አማራ በአማራነቱ ብቻ  እየተጠቃ ነው በሚለውን ሽፋን የሚፈጸሙ ትምህርትም ሆነ እርማት ሊያገኙ ያልቻሉ ድርጊቶች ናቸው፡፡ መቸም ያለአንዳች ጥቅም ሰዎች በአካል ተገናኝተውም ይሆን በዘመኑ ቴክኖሎጂ አየር በአየር አውርተው ድርጅት አይመሰርቱም፡፡ ከአንድ አልፎ ፕ/ር ጌታቸው እንደነገሩን አንድ ሰው አራት አምስት ድርጅት መመስረቱ ያጣጣሙት ነገር ቢኖር ነው ሊባል ቢችልም የፕ/ር ጌታቸው በዋናነት በጎሳ መደራጀትን፣ ተያይዞም ውጥንቅጡ የጠፋውን አደረጃጀት ያውም በዚህ ጎሰኝነትን በኢትዮጵያ ታሪክ ለማድረግ ያበቃል ብለን ተስፋ የጣልንባት ኢትዮጵያዊነትን ያገነነ እንቅስቃሴ በተጀመረበት ወቅት ደጋፊ ሆነው ብቅ ማለታቸው ለዚህ የሰጡት ምክንያት ደግሞ አሳማኝ ሆኖ አለመገኘቱ ምነው ምን ነካቸው የሚያሰኝ ነው፡፡ ሲያልቅ አያምር ይሉት እንደማይሆን ተስፋ አለኝ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የመሠረታዊ ነፃነት ቀበኞች! (በሰሎሞን ተሰማ ጂ)

እባክዎ ፕ/ር ሲናገሩትም ሆነ ሲሰሩት  የሚያምርብዎት እስከ ዛሬ ይዘውት የዘለቁት ኢትዮጵያዊነት ነውና እኔ ደገፍኩትም አልደገፍኩት በሚል ረብ የለሽ ምክንያት  ያለወርድዎና ቁመትዎ በኮት ላይ የደረቡትን ጃኬት ፈጥነው አውልቀው ይጣሉት፡፡ ጎሰኝነት/ዘረኝነት ባይወልደውም ካሳደገውና ካራባው ወያኔ ጋር ወደ ቅርስነት የሚቀየርበት ግዜ እየመጣ መሆኑ አይታይዎትም፡፡

የሀገራችን ህዝቦች እየተባለ ሲደሰኮርበት ከነበረው መድረክ “እኛ ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን” የሚል ቃል ሲሰማ በጎሰኝነት ባቡር የተሳፈሩ ሁሉ ይህን ያሰማኸኝ ፈጣሪ ተመስገን ብለው ወራጅ አለ ሊሉ ሲገባ ሙሉ እድሜአቸውን ኢትዮጵያ ከማለት አልፈው በጎሳ መደራጀትን በዘር ማሰብን ወዘተ ሲቃወሙ የኖሩት ሰው ወደ ባቡር ለመሳፈር መከጀላቸው የወዳጅ ዘመድ ያለህ የሚያሰኝ ነው፡፡ ፕ/ር እንዳመረብዎት በመጡበት መንገድ ይቀጥሉ፡፡

እግዚአብሄር አምላክ አብይና ጓደኞቻቸውን የዴሞክራሲ አዋላጅ ለማድረግ ያበቃቸው፡፤ አሜን

 

 

 

3 Comments

 1. እውነትም ይገረም ነህ። ጽፈህ ልብህ ውልቅ ብሏል። ይህንን ጮርቃ አስተሳሰብ ይዘህ ወደ አደባባይ ባትወጣ ይሻልህ ነበር። በአማራነትህ ባታምንበትም የመላው አማራ ድርጅት አባል እንደነበርክ ሳትሸማቀቅ ትጽፋለህ። መአህድ የተመሠረተበት አላማ እኮ ታላቁን ፕ/ር እሥራትን ጨምሮ አእላፍ የተሰዉለት ፣ የታስሩለትና የተንገላቱለት ዐላማ ነው። የድርጅት አባል መሆን ላንተ እድር ወይ ዕቁብ ማህበር ውስጥ ከመሳተፍ የተለየ አይመስልም። ቀድሞ ነገር ባላመንክበት ነገር እንዴት አባል ሆንክ? ያንተ ዓይነት ዐላማ ቢሶች በየድርጅቱ ስለሞሉ ነው የመከራ ዘመናችን የተራዘመው። ስለ አማራ መከራ ያለህ ግንዛቤም የአዕምሮህን ውስን እቅም ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ይህንን የምለው ግን አውቆ የተኛ መሠሪ ካልሆንክ ብዬ ነው። ለማንኛውም አማራ ካልሆንክ ወይም አይደለሁም ካልክ አሸር ባሸር ጽሁፎችህ በሌላ አማራን በማይመለከቱ ጉዳዮች ላይ ቢያተኩሩ ለራስህ ይበጅሀል።

 2. ዝም ብለህ አትዘባርቅ አማራው እንደበግ ሲታረድ አንተና ኢትዮጵያ ለአማራው ምን አደረጋችሁለት ??? የአማራ መደራጀት ለኢትዮጵያ አንድነት ጠንቅ ነው ብላችሁ ካሰባችሁ እናንተም ኢትዮጵያም ገደል ገቡ!!!!

 3. Yigerem Alemu, I have come across some of your articles. I read a few long time ago, and gave you my sincere advise that you should stop writing. You know what, your writings stink like animal skin soaked in water for some days. If one goes through your long sentences jammed with illogical and confused ideas, it is easy to see how much immature and childish you are. I have no problem that you stand against the cause of the Amharas. But the thing is that you are not doing any favour to those who promote Ethiopianism either.

  In the first place, why are you so bitter about the idea of organizing Amharas in order to defend themselves? Just keep on scribbling your crazy ideas about Ethiopiawinet. “…የመታሰሬ ምክንያት መታወቂያየ ላይ የሰፈረው የማላምንበት አማራነት አይደለም” If you hate to be identified as an Amhara, then stay away from Amhara issues. If you are addicted to say any nonsense that comes to your mind on paper, praise and fight for TPLF.

  “አማራ መሆን ብቻም ለእስር እንግልት ካበቃ አማራ የተባለ ሁሉ እየታደነ መታሰር ነበረበት”. See how much shallow and hotchpotch writer you are. The Woyanes would be more than happy to fulfill your ambition if they had the means and the capacity to wipe out the Amharas. The crimes committed so far against the Amharas has not yet satisfied and convinced you to give even a little humanitarian support to Amharas.

  Your article is not worth getting an intellectual attention, through logical analysis. But let me just say a few words about the Amhara cause versus Ethiopia. The name Ethiopia is not something supernatural or abstract that we worship. It was not dropped from the heavens as one whole and holy parcel of land. It is just a country with many ethnics ( call them gossa or bihereseb, I don’t care) living in it, shaped and transformed by a common economic, sociopolitical and historical phenomena. You and your likes should understand that each ethnic group is already an organized body of people with its own language, way of life, and a territory. These ethnics make up a country known as Ethiopia, with a political boundary, government and mode of administration.

  One of the components of the country called Ethiopia is the Amara; one out of about eighty of them. By the will of history, the language of the Amara ethnic group has been the language of government and thus a media of communication between the various ethnics. There have been many bad rulers through out
  the history of Ethiopia. But whatever suffering they brought, it was distributed for all. Their misrule emanated either from lack of knowledge or greed and power mongering. The current regime ruling Ethiopia is unique in its ability to create, spread, and implement sufferings. What makes it unique is that it has targeted the Amaras, and works diligently and systematically to eliminate one of the important building blocks of the country.

  When we talk about organization here, is to enable the Amaras to develop positive consciousness towards stopping the curse of TPLF, survive, and come out as one who can cooperate with other ethnics to coexist peacefully in democracy and mutual prosperity.

  Those who say Ethiopia first can go ahead and promote their ideology, as long as it helps creeple TPLF and lead the country to be a place of equality, freedom, legality and democracy. They don’t have to block the Amaras from self defense. the Amaras have never been, and would never be anti Ethiopia. Same is true to Oromos, and others. The fact that they organize for securing their rightful place in Ethiopian politics is an asset and not a threat.

  Only when a group or an ethnic is organized for the purpose of invading, looting, killing and torturing others becomes a danger to others and itself.

  Where are you from? I am an American; I am from Texas. I am an Ethiopian; I am from Amara or Oromo region. No harm to be this way. It is universal. It is human feeling.

Comments are closed.

Share