ከመጥረቢያ ብረት የተሰራ ጦር ወደ አቡጀዲ ቢወረውሩት ወደ ጉቶ ይሄዳል – ይገረም አለሙ

በርዕስነት የተጠቀምኩበት አባባል በደቡብ ምዕራብ የሀገራችን ክፍል በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚነገር ነው፡፡ ከ አስራ አምስት አመት በፊት ነው ማሻ የሚኖር ወዳጄ የነገረኝ፡፡በአካባቢው ቋንቋ ሲነገር ለጆሮ ይጥማል፡፡ የጦር ጉዞ አንደወርዋሪው ፍላጎት በመሆኑ  ምሳሌው የሚመለከተው እኛን የሰው ልጆች ነው፡፡ ወረድ ብለን አንመለከተዋለን ፡፡

ሰሞነኛ አጀንዳ የሆኑት የለማ ቡድን የሚባሉት እዚህ ደረጃ ለመድረስ ብዙ ዳገት መውጣታቸውን ቁልቁለት መውረዳቸውን ከእኛ ግምት በላይ ንግግራቸው ይናገራል፡፡ በህውኃት አገዛዝ ውስጥ እየኖሩ በደደቢቶች ሳይበሉ ሥልጣን ወይንም ሞት የሚሉትን ደደቢቶች ከቤተ መንግሥት ማስወጣት መቻላቸው ከብዙ ትዕግስት እልህ አስጨራሽ ትግልና የውስጥ ለውስጥ ድርጅታዊ ስራ የተገኘእንጂ አንዳንዶች ሲሉ እንደሚሰማው የቄሮ ጎርፍ ያመጣቸው አይደሉም፡፡

ለነገ ራዕይ ያለው ዛሬን አያበላሽምና እነዚህ ሰዎች ሩቅ አልመው በአጭር እንዳይቀጩ ተጠንቅቀው የደደቢቶችን እብሪትና አንባገነናዊ አድራጎት ታግሰው፣ ስማቸው ሳይቀር በህውኃት የወጣላቸውንና በፓርቲም በኦሮምያ ክልል ባለሥልጣንነትም በወያኔ በጎ ፈቃድ የሚቀመጡትን  ሰዎች  በመሪነት ተቀብለው መስለው ተመሳስለው ኖረው የውስጥ ለውጥ ስራቸው  መሰረቱ መጥበቁን ወደ ላይም ልቆ ማደጉንና በደደቢቶች  ሊሰናከል አንደማይችል ባረጋገጡ ግዜ ብቅ አሉ፡፡ በኦሮምያ መስተዳድር ውስጥ ብቅ ካሉበት ለቤተ መንግስት እስከበቁበት ድረስ በነበረው  ግዜም ከወያኔ ጎራ የተቃጡ ብዙ አሰናካይ መሰናክሎችን በዘዴና በትእግስት አልፈው ስለመሆኑ ማየት ለሚችል ሁሉ የተሰወረ አይደለም፡፡ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ የሚለውን ብሂል በሚገባ የከወኑ ይመስላል፡፡

በአንጻሩ ሀያ ሰባት አመታትን ወያኔን ማንበርከክ አይደለም ፓርቲ በወጉ ማደራጀት ተስኖአቸው ይልቁንም የተቃዋሚ ፓርቲ ወንበር ሥልጣን ሆኖ  ለማስጠበቅ ሲለፉና ሲላፉ አባራሪና ተበራሪ ሆነው ሲሻኮቱ የተሳካላቸውም ይሀን ሁሉ አመት የፓርቲ መሪ እየተባሉ ሊቀመንበርነታውን ከማስጠበቅ የዘለለ ሀገራዊመ ሆነ ድርጅታዊ ተግባር ያልከወኑ  ሰዎች ራሳቸውን ማየት የሚችሉበትን መስተዋት ገደል ከተው አንደም የእነ አብይን ወደ ሥልጣን መምጣት ረብ የለሽ አድርገው ሲያናንቁና ሲቃወሙ፣ ሁለትም ራሳቸውን የፖለቲካው መሀንዲስ አድርገው ይህ ይደረግ እንደዛ ይሁን ሲሉ፣ አንዳንዶቹም ወያኔን የሚያውቁ እነርሱና እነርሱ ብቻ አንደሆኑ አድርገው ደርሰው መካሪ ለመሆን ሲናገሩና ሲጽፉ መስማትና ማየት ያሳዝናል፡፡

እነ አብይ ወያኔን በሚገባ ስላወቁት ነው ያሸነፉት፡፡ ወያኔን በቅጡ ባለማወቅ ብዙዎች ተበልተዋል፡፡ ሳይታወቁ በውስጣቸው ያውም በቅርባቸው ኖረው ሊአስቆሙዋቸው በማይችል ሁኔታ አፈትልከው የወጡ ሰዎች ያደረሱባቸው ሽንፈት  ወያኔዎችን ምን ያህል ውስጥ እግራቸው ድረስ ጠልቆ እንደተሰማቸው የጠቅላይ ምኒስትሩን ሹመት ያጸደቀውን ፓርላማ ምስል ማየት ብቻ ይበቃል፡፡

ከሀገር ውጪ የምንኖር በኢትዮጵያ የሰፈነውን አገዘዛዝ የምንቃወም አወጣጣችን በባሌም ይሁን በቦሌ ወያኔ ጉያ የነበርንም እንሁን በተቃውሞው ሰፈር ከሀገር ስንወጣ ተሸንፈናል፡፡ ስለሆነም በርቀት ሆነን የምንሰጠው አስተያየት ስደተኛነታችንን ብቻ ሳይሆን ተሸናፊነታችንንም ያገናዘበ መሆን አለበት፡፡ ገር ግን በአንዳንዶች ዘንድ የሚታየው ከዚህ በተቃራኒ በትግሉ መስመር በፍሊሚያው አምባ ካለው በልጦ የመታየት አዝማሚያ የሚታይበት ነው፡፡ በህውኃት ውስጥ ኖረውስራቸውን ውስጥ ለውስጥ ሳይነቃባቸው ሰርተው አመች ግዜና ሁኔታ ጠብቀው ወያኔን ከቤተ መንግሥት ለማስወጣት ለበቁ ሰዎች ወያኔን ከእናንተ በላይ እኛ እናውቃለን አይነት ምክር ሲሰጡ ይሰማሉ፡፡ መሬት ላይ ያለወን ተጨባጭ ሁኔታ ፈጽሞ  ባላገናዘበ  የጠቅላይ ምኒስትሩ ሥራ ፍየል ከመድረሷ ቅጠል መበጠሷ ወይንም የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል ይሉ አይነት እንዲሆን ይገፋሉ ይገፋፋሉ፡፡ ሀያ ሰባት አመት ስር የሰደደውን ደደቢታዊ አደረጃጀትና  የሴራና የተንኮል አሰራር በአንድ ጀንበር እንዲለውጡ ይጠይቃሉ፡፡ የአንዳንዶቹ አድራጎት ከቅን ልቦና ለለውጥ ካላቸው ጉጉት ነው ሊባል ቢችልም የአንዳንዶች ግን በኢትዮጵያ ዴክራሲያዊ ሥርኣት ተመስርቶ ማደሪያ ተዳደሪያቸው የሆነውን ተቃዋሚነት አንዳያጡ በመስጋት ለለውጥ የተነሱትን ኃይሎች ለማደናቀፍ ከማለም የሚያደርጉት ስለመሆኑ አድራጎታቸው ይናገራል፡፡ ፡ምኞት ፍላጎታቸው ለውጡ በማን መጣ ሳይሆን ለውጥ ማየት የሆነማ ወገኖች የእነ ለማን አመጣጥ አድንቀው፤ ለትግላቸውና ለድላቸው አክብሮት ሰጥተው፤ ጠቅላይ ምኒስትሩ የተነገሩትን ተግባራዊ ማድረግ፣ የወጠኑትን ከግብ ለማድረስ ይቻላቸው ዘንድ በምንችለው ሁሉ እንተባበራለን ፈጣሪም ይርዳቸው ሲሉ ነው ያደመጥነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የዘረፋና ኢትዮጵያን ወደኦሮሞነት የመቀየር ዘመቻ - ስርፀ ደስታ

ከመጥረቢያ ብረት የተሰራ ጦር በቀላሉ በስቶት ሊያልፍ ወደሚችለው አቡጀዲ ቢወረወር አቅጣጫ ቀይሮ አጥፎ ሊያስቀረው አለያም ሰብሮ ሊመልሰው ወደሚችለው ጠንካራው ጉቶ መሄዱ ከስር መሰረቱ ከጉቶ ጋር የኖረ በመሆኑ ነው፡፡ እንደዚሁ በተቃውሞ ተወልደው ሲቃወሙ ያደጉ ምን አልባትም በዚሁ በተቃዋሚነት የከበሩ ያም ባይሆን ተቃውሞን የኑሮአቸው መሰረት ያደረጉ ሰዎች ከዚህም ሌላ ጎሰኝነትን ማቀንቀን ለእውቅናም ገንዘብ ለማካበትም ያበቃቸው ሰዎች የእነ ለማ አካሄድ፣ የዶር አብይ ብዙ ምሁራን ሰዋዊ ያሉት ከፖለቲከኞች የተለየ ንግግር ከደደቢቶቹ ባልተናነሰ ቢያስደነግጣቸው ከዚህም በመነሳት የእውር ድንብር ተግባር ቢፈጽሙ ብዙም ሊገርም አይችልም፡፡

ተቀዋሚነታቸው ለውጥ ከመሻት ሳይሆን ኑሮን ከማድርጀት አንጻር የሆነና የወያኔ ሥርዓት የተናጋ በመሰላቸው ግዜ ከወያኔዎቹ እኩል ስለሚበረግጉት ወገኖች ሳስብ ሁሌም የሚታወሰኝ የአቶ አሰፋ ጫቦ አባባል ነው፡፡ የአባባሉን እውነትነት ብቻ ሳይሆን የነኩትን ጉዳይ አደገኛነት የሚያሳየው ጉዳዩን በስፋት አንደአተቱበት የገለጹትንና በቅርብ ቀን አወጣዋለሁ ያሉትን ጽሁፍ ለንባባ ሳያበቁት መሞታቸው ነው፡፡ የሞታቸው ምሥጢር ሆድ ይፍጀው ሆኖ መቅረቱም ሌላው ጉዳይ ነው፡፡ ወደፊት ግዜ ይገልጠው ይሆናል፡፡ እንዲህ በማለት ነበር ለንባብ ሳይባቃ የቀደሙትን ጽሁፍ ያስተዋወቁን፡፡

“ “ያጋራ ቤታችንን”  ጨርሼ በ10 ቀን ውስጥ አደባባይ አዋጣለሁ። አማራና ኦሮሞ የሚመለከት ነው የሚል  Facebook  ላይና ሌላም ቦታ ጠቃቀስኩ። ይህ እርግማንና ዘለፋ የተጀመረው ገና ባልታየ፤ባልተነበበ ጹሁፍና አስተያየት ላይ ነበር። ያ ነው ይበልጥ የገረመኝ። ከማንውቀው ይሰውረን ማለት ይሆን ? ከምናውቀው ግን ከሸሸነው እውነት ሰውረን ነው? አውቀን የካንደነውን እውነት አታስታውሰን ማለት ይሆን?  ይህንን ደህና ያጧጧፍነውን ሥራና ገበያ ይሻማብናል ማለት ይሆን? ሥራ ያሰኘኝ በተለየ አንዳንድ ዲያስፖራው ኗዋሪዎች መተደዳደሪያም ወደመሆን የተቃረበ የሚያስመስል ፍንጭ ስለሚታይ ነው። በተፈጠረው የሕዝብ አመጽ ሳቢያ ታዋቂ  ሆነን፤አገር አውቆን ፣ፀሐይ ሞቆን፤ አንቱ የተባልንበትን  ልታፈርስብንም ነው  የሚል ስጋት ፈጥሮ ይሆን? የሚል መላ ምት ይፈጥራል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ማደናቆር ማሸጋገር ነዉን ?

በሀገር ቤትም በውጪም ጥቂቶች ከምር ለለውጥ፣ የህዝብን የሥልጣን ባለቤትነት ለሚያረጋግጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆን ቤት ንብረታቸውን ጥለው ጎጆአቸውን አፍርሰው ወይንም አዳክመው በጥቅሉ ራሳቸውን ለትግሉ ሰጥተው ከምር ይታገላሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ትግላቸው ለዴሞክራሰያዊ ሥርዓት እንጂራሳቸውን  ለምንይልክ ቤተ መንግሥት ለማብቃት ባለመሆኑ የሥልጣን ናፍቆት ከሚያመጣው የመጠላለፍ ጉዞም ሆነ የሴራ አካሄድ የጸዱ ናቸው፡፡ በትግሉ ወቅትም ሆነ በድሉ ማግስት የሚሹት ዝናም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የለምና ለውጡ ዴሞክራሲን ማዋለድ ስለመቻል አለመቻሉ እንጂ ቤተ መንግሥት ስለሚገባው ግለሰብም ሆነ ቡድን አይጨነቁም፡፡እኔ በምለው መንገድ ብቻ ነው ለውጥ ሊመጣ የሚችለው ብለው አካኪ ዘራፍ የሚሉ ሳይሆኑ በለውጥ መንገድ ላይ ነው ብለው ካሰቡት ወገን ጋር ሁሉ በመተባበር ይሰራሉ እነርሱ ያልተሳካላቸውን ሌላው ቢያሳካው ደስታቸው ወደር የለውም፡፡

በተቃራኒው ግን ተናግረው የሚደመጡት፣ ጽፈው ወይንም ራዲዮ ጣቢያ ከፍተው ገበያ የሚያገኙት፣ የተቀዋሚ ደርጅት መሪ ተብለው የሚኮፈሱት አክቲቪስት ተብለው እዚህም እዛም የሚታዩት ወዘተ የወያኔ ሥርዓት ከነደደቢት ህልሙ  ሲኖር በመሆኑ  የዚህ ሥርዓት መቆየት የእነርሱም ህልውና መቆየት ነውና በንግግራቸው በጽሁፋቸው ወዘተ ለውጥ ፈላጊ ለዴሞክራሲ ተዋጊ መስለው እየታዩ በሚችሉት ሁሉ የወያኔ እድሜ እንዲራዘም ይሰራሉ፡ባይችሉ ይጸልያሉ፡፡

ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ በ2001 ዓም አንድነት ፓርቲ እንደተመሰረተ የወቅቱ ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን እኛ የምንታገለው የህዝብን የሥልጣን ባለቤትነት የሚያረጋግጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን እንዲሆን እንጂ ለምንልክ ቤተ መንግሥት አይደለም( ቃል በቃል አልጠቀስኩ ይሆናል)  በማለቷ ጉድ ብሉ ለሥልጣን የማይታገል ፓርቲ ተፈጠረ ለሚል ተቃውሞና ስላቅ መዳረጓን አስታውሳለሁ፡፡ ለእኔ እንደሚገባኝ ራስን ለቤተ መንግሥት ለማብቃት መታገልና ህዝብን የሥልጣኑ ባለቤት ለማድረግ መታገል የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ የምርጫ ማጭበርበር፣ ኮሮጆ መገልበጥ፣ ሽንፈትን አሜን ብሎ አለመቀበል ወዘተ የሚመጡት ራስን ለማንገስ ከሚደረግ ትግል ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ወያኔ ጠላቴ ነዉ ያለዉ አማራን እንጅ ኢትዮጵያን አይደለም::አንተ ከዬት አምጥተህ ነዉ ወያኔ የኢትዮጵያም ጠላት ነዉ እያልክ የምትጽፈዉ?  - ሸንቁጥ አየለ

ዶ/ር አብይ ኢትዮጵያዊነትን አጉልተውም አክብረውም ተናገሩ፣ የሚበጀን መደመር መሆኑንም አጽኖኦት ሰጥተው ገለጹ፡፡ በዚህ ንግግር  ጎሰኝነት አራማጆች (ይቅርታ በጎሰኝነት ካርድ የሚነግዱ ማለቱ ይበልጥ የሚገልጻቸው ይመስለኛል) ቢደነግጡና ቢከፉ ባያስገርምም፡፡ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እያሉ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚሉ ሰንደቅ ዓላማ በመልበስ በየመድረኩ የሚታዩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የአብይ ተቀዋሚ ሆነው ብቅ ሲሉ ምስጢሩ ካልገባን ሊገርም ይችላል፡፡ የእነርሱ ስጋት ጭንቀት ኢትዮጵያዊነት በጠቅላይ ምኒስትሩ አንደበት አንዲህ ከተገለጸ እነርሱን ማንን ምንንስ እየተቃወሙ ይኖራሉ፡፡ ነገሩ ጩኸቴን ተቀማሁ የመጫወቻ ካርዴን ተነጠቅሁ ነው፡፡

ጠቅላይ ምኒስትሩ ፖለቲከኞችን ተቀዋሚዎች ሳትሆኑ አማራጭ ሀሳብ ያላችሁ ተፎካካሪዎች ናችሁ፣ ሀገራችን የሁላችንም ነች፣ ተነጋግረን እንስራ፣ የችግር መፍቻው አብዩ መንገድ መነጋገር እንጂ  ጉልበት መሆን የለበትም ሲሉ ከመነሻው  ለዴሞክራሲ  ሳይሆን በትግል ስም  ለሚገኝ ጥቅም ተቀዋሚ እየተባሉ ለኖሩት የመቃወሚያ ካርድ እያሳጡዋቸው ነውና ሰበብ እየፈጠሩ ቀዳዳ እየፈለጉ ቢቃወሙዋቸው  አይገርምም፡፡ሌላም ሌላም፡፡

ከመጥረቢያ ብረት የተሰራው ጦር ከአቡጀዲ ይልቅ ምርጫው የሚያውቀውና የለመደው ጉቶ እንደሆነ ሁሉ በተቃውሞ ተፈጥረው በተቀዋሚነት ኖረው በዚሁ ዝና አትርፈው ጥቅም ያካብቱ በየትኛውም ዘርፍ ያሉ  ወደ አቡጀዲ የሚጠራውን የዶ/ር አብይ ንግግር ገፍተው ወደ ለመዱት ወደ ጉቶ ( ተቃውሞ) መሄዳቸው የተፈጥሮአቸው ነውና ባያስገርምም ለለውጥ እንቅፋት መሆናቸው ስለማይቀር እረፉ ማለት በንቃትም መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡

በወያኔ ሥልጣን  ላይ ጀንበር ጨርሳ ከመጥለቋ በፊት የሚችሉትን የመጨረሻ የሞት ሽረት ትግል በማድረግ  የእነ ለማን ጉዞ ለማደናቀፍ ወያኔዎቸ የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደማይኖር ከወዲሁ በግልጽ እየታየ ነው፡፡ ሌሎች ግን የግል ጉዳያችንን ጥቅምም ሆነ የሥልጣን ፍላጎታችንን ገታ እናድርግና ወያኔ መልሶ እንዳያንሰራራ እንተባበር እነ ለማን አንደግፍ፡፡ቤተ መንግስቱም ሁሉንም አያስገባም፡፡ሀገራዊ ለውጥ ግን ሁሉንም ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ ስለሆነም ለማይገኝ በመሻኮት ያሳለፍነው ግዜ ይቆጨንና ለሁላችንም ይልቁንም ለልጆቻችን ለሚሆን ለውጥ በተባበርና በመከባበር እንታገል፡፡  ለአብይ ግዜ መስጠት ለወያኔ ግዜ መስጠት ነው የሚለውም ትክከልና ተገቢም አይመስለኝም ፡፡ እንደውም በተቃራኒው አብይን መርዳት ወያኔን ከነ ደደቢት አስተሳሰቡ ለመሸኘት የሚያስችል ነው፡፡

በመጨረሻም የተቀዋሚ መሪነት ሥልጣን ሆኖ ፖለቲከኞቻችን ሲሻኮቱ በምናይበት ሀገር የጠቅላይ ምኒስትርነት  ሥልጣን በእጃቸው ላይ የወደቀው አቶ ለማ ለሀገር ቅድሚያ በመስጠት ለጓዳቸው ማሳለፋቸው በእጅጉ የሚያስመሰግናቸውና በታሪክ ልዩ ስፍራ ሊያሰጣቸው የሚገባ ነው፡፡ ጥረታቸው ሰምሮ የተጀመረው ለውጥ ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲ ማድረስ ከቻለ የደግሞ የሚቆመው  ሀውልት የለማ መሆን ያለበት ይመስለኛል፡፡

ቸሩ ፈጣሪ አብይን የዘመናችን ሙሴ ያድርግልን

 

1 Comment

  1. BAD NEWS FOR SHABIAN PAYROLL MERCINARIES

    ትግራይ ለፍትህና ለእኩልነት ሞትን ተጋፍጠው ክቡር መስዋዕትነት የከፈሉ፤ ለኢትዮጲያን ግንባታ ቤዛ የሆኑ ጀግኖች፣ እንደነስሁል (ወደ ስሁል ፎቶ እየጠቆመ)፣ ሙሴ፣ ዋልታ፣ ሀፍቶም፣ ቀለበት፣ ሀየሎም፣ ብርሀነ መስቀል፣ ቀሽ ገብሩ፣ አሞራ፣ ጥላሁን ግዛው፣ በተለይ እንደጓድ መለስ ዜናዊ ያሉ (ጭብጨባ)፤ በአጠቃላይ ደግሞ ተቆጥረው የማያልቁ በሺዎች የሚቆጠሩ ጀግኖችና ታጋዮች ሀገር ናት። (ጭብጨባ) PM ABIY

Comments are closed.

Share